Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

ማስተር ፕላኑ ይቁም ከተባለ፤ የታሰሩት ይፈቱ፣ገዳዮችም ለፍርድ ይቅረቡ!

 

በይድነቃቸው ከበደ
ምንጭ- ‎በኢትዮ ምኅዳር‬ ጋዜጣ

“….የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ንጹሃና ዜጎች በመንግሥት ታጣቂ ኃይሎች መገደላቸውን አስመልክቶ፣ መጽናናትን ለቤተሰቦቻቸው ከመመኘት ባለፈ ምንም አይነት ውሳኔ አለማሳለፉ ፣በእርግጥም ውሳኔው የኦህዴድ እንዳልነበረ የሚያሳብቅ ነው፡፡”

“የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላን” የሚል ስያሜ የተሰጠው መንግሥታዊ ውንብድና ፣በአገራችን አለመረጋጋትን ፈጥሯል፤መተኪያ የሌለው የሰው ልጅ ሕይወት እንዲጠፋ፣ የንብረት ውድመትና ኪሳራ እንዲደርስ ምክንያት ሆኗል፡፡ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ማስተር ፕላኑን እንዲቆም እና ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ያላትን ጥቅሞች ተግባራዊ ለማድረግ ወስኛለው ማለቱ እየተሰማ ነው፡፡Yidnekachew Kebede of the Blue Party

የሕዝብ ጥቅም እና ፍላጎትን ያልጠበቀ ውሳኔ ማሳለፍ ከአንባገነን መንግሥት ሁሌም የሚጠበቅ ድርጊት ነው፡፡የፌደራል መንግሥትም ሆነ የኦሮሚያ ክልል አስተዳዳር “የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላን”ን አስመልክቶ፤ የጉዳዮ ቀጥተኛ ባለቤት የሆነው የአካባቢ አርሶ አደሮች፣ የክልሉ ነዋሪዎችና የሚመለከታቸው ሁሉ በጋር በግልፅ ድርጊቱን ሲቃወሙ ነበር፡፡

ለሕዝብ አቤቱታና ተቋውሞ፣ ተገቢውን ክብርና ምላሽ የማይሰጠው የህውሓት/የኢህአዴግ አንባገነን መንግሥት፣ ይህ ነገር ለእኛ አይጠቅምም ያሉ፣ቅሬታቸውን በሠላማዊ መንግድ የገለጹ ፣በታጣቂ አይሎች በአደባባይ እንዲገደሉ ተደርጓል፣የአካል ጉዳትም የደረሰባቸው አሉ፣በመንግሥት የማሰቃያ እስር ቤቶች እየተሰቃዩ የሚገኙ ሰላማዊ ዜጎች እና የፖለቲካ አመራሮች እንዲሁም አባላት ይገኛሉ፡፡

ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ፣በህውሓት የሞግዚት አስተዳደር የሚመራው ፣የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ እንደ-ቀልድ ማስተር ፕላኑ ይቁም ማላቱ ፣ከውሳኔው ጆርባ ያለው ፓለቲካዊ አንድምታ ብዙ ርቀት ሄዶ ምርምርን የሚጠይቅ አይደለም፡፡የአፍንጫ ሥር ፖለቲካ ቁማር ነው ! ኦህዴድ ቀድሞ ነገር “የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላን”ን አስመልክቶ የእቅዱ ባለቤት አልነበረም ፣ልሁንም ቢል የማይቻለው ነገር ነው፡፡ለዚህ እንደ-ማሳያ ብዙ ነገሮችን ማንሳት የሚቻል ቢሆንም ፣ከማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ ፣ለሁለት ዓመት ያኸል ሕዝብ በይፋ ማስተር ፕላኑን ሲቃወም ነበር፤ኦህዴድ በሕዝብ የሚመራ ከሕዝብ የተመረጠ፣በራሱ ድርጅታዊ አቋም የሚጸና ቢሆን ኖሮ፣አሁን ላይ ሳይሆን ከሁለት ዓመት በፊት፣ የመሬት ወረራና ንጥቂያ በቆመ ነበር፡፡ግን አልሆነም፣መሆን ስለማይቻል!

በኢህአዴግ ውስጥ ያለው የሥልጣን ተዋረድ እንዲሁም የኃይል አሰላለፍ፣ በቁጠር ብዛት እንጂ በውሳኔ ሰጪነት ቦታ የማይኖራቸው እህት ድርጅቶች ፣ሁሌም ቢሆን ከሚወክሉት ሕዝብና አካባቢ ይልቅ፣ለበላይ ተጠሪያቸው ለህውሓት ማገልገል እና ታማኝ መሆን መገለጫ ባህሪያቸው ነው፡፡የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን በተመለከተ የቀረበውን መሪ እቅድ በዋነኝነት ይደግፉ የነበሩት እንዲሁም ለተግባራዊነቱ ዘብ የቆሙት፣አቶ ሙክታር ከድርና አስቴር ማሞ በግንባር ቀደመ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

እነዚህ ሁለት የኦህዴድ ባለስልጣናት በመከተል ቁጥራቸው የበዛ የኦዴድ ካድሬዎች ፣ የወከላቸውን የኦሮም ሕዝብ ከማገልገል ይልቅ ፣የግል ጥቅማቸውን በማሰብ ለአሳድሪያቸው ገብረዋል፣አሁንም እየገበሩ ይገኛሉ!ጫና የበዛበት ፣የአስተዳደር በደል መሸከም ያቃተው የኦሮሞ ሕዝብ ፣ዓይን ባወጣ መልኩ ከቦታው በሃይል እንዲፈናቀል መደረጉን አምርሮ በመቃወሙ፣ይህም ተቃውሞ ዓይነቱና መጠኑ እየበዛ መምጣቱን ተከትሎ ፣ለአገዛዙ ሥርዓት አስጊ መሆኑን የተረዳው የህውሓት/ኢህአዴግ ገዢ መንግሥት “የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላን”ን እቅድ እንዲቆም ወስኗአል፡፡

እቅዱ እንዲቆም መወሰንና እቅዱን መሠረዝ፣ የየራሳቸው ትርጉም እና እሱን ተከትሎ የሚመጣ ፖለቲካዊ መዘዙ ብዙ ነው፡፡የታሰበው የማስተር ፕላን እቅድ እንዲቆም መደረጉ ሳይሆን፣ መሠረዝ ወይም ማስቀረት ብቻ ነው፣ ለኦሮሞ ሕዝብ ለጥያቄው ትክክለኛ ምላሽ የሚያስገኝለት!!! ይህን በቅጡ ያልተረዱ ወይም ለመረዳት ያልፈለጉ የኦህዴድ ባለሥልጣናት “ሾላ በድፍኑ” አይነት ውሳኔ እንዲያሳልፉ በተሰጣቸው ትዝዛዝ መሠረት ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡

የተወሰነ ውሳኔ እንደሚያመለክተው “የውዝግቡ መንስኤ ሆኖ የቆየው የአዲስ አበባና በፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ሙሉ በሙሉ እንዲቆም” በማለት ወስኗል፡፡ውሳኔው የመሬት ነጠቃና ወረራ ላወገዙ፣ተቃውማቸውን በአደባባይ ለገለጹ ኢትዮጵያዊን ሁሉ ትልቅ ድል ነው፡፡ ትንንሽ ድሎችን በመሰብሰብ ለተሻለ ደል መብቃት በእርግጥም ተጨማሪ ሥራ ይጠይቃል፡፡ነገር ግን የኢህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ንጹህና ዜጎች በመንግሥት ታጣቂ ሐይሎች መገደላቸውን አስመልክቶ፣ መጽናናትን ለቤተሰቦቻቸው ከመመኘት ባለፈ ምንም አይነት ውሳኔ አለማሳለፉ ፣በእርግጥም ውሳኔው የኦህዴድ እንዳልነበረ የሚያሳብቅ ነው፡፡

“በየትኛውም የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ ሕዝብ የልማትና የግልፅነት ጥያቄዎችን ማቅረቡ ድርጅቱ ከሌሎች ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ጋር በመሆን እየገነበ የሚገኘው ስርዓት ውጤት በመሆኑ በአድናቆት እንደሚመለከተውና ከፍተኛ ክብር እንዳለው” የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ በሰጠው መግለጫ ውስጥ ተካቶ ይገኛል ፡፡በሕዝብ ላይ ከዚህ በላይ መቀለድ ምን አለ ?! እነሱ እንደሚሉት ሕዝብ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄውን በማቅረቡ እና በመቃወሙ ብቻ ሕይወቱን እንዲያጣ ተደርጓል፡፡ኦህዴድ እወክለዋለው የሚለው ሕዝብ በጠራራ ፀሐይ ሙሉ ትጥቅ በታጠቁ ወታደሮች ሲገደል፣ይህን ድርጊት የፈጸሙ ግዳጁን እንደጣለ ጀግና በአደባባይ ሲዘባበቱ፤የሟች እና የገደይ ድርጊት ኦህዴድ “…..ከሌሎች ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ጋር በመሆን እየገነበ የሚገኘው ስርዓት ውጤት በመሆኑ በአድናቆት እንደሚመለከተውና ከፍተኛ ክብር እንዳለው” ብቻ አይቶ ማለፉ፣ ድርጅቱ እውነትም የሕዝብ ውክልና አለው ወይ ብሎ የሚያስጠይቅ ነው፡፡
የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላን በመቃወማቸው ብቻ፣የተገደሉ ዜጎቻችችን ደም ደመከልብ ሆኖ መቅረት የለበትም! የመግደል ትእዛዝ የሰጡ ፣ግድያውንም የፈጸሙ እና ያስተባበሩ ፣በእውነተኛ ፍርድ ቀርበው መዳኘት አለባቸው፡፡ይህ ሲሆን ብቻ ነው የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ትክክለኛ ምላሽ የሚያገኘው፡፡ከዚህ ባነሰ “ሕይወታቸውን ላጡ እናዝናልን” ማለት ብቻ በቂ አይደለም፣ንጹሃንን የገደሉ እና ያስገደሉ ለፍርድ ይቅረቡ !!!

ይህም ብቻ አይደለም፣አሁን ላይ የፌደራል መንግሥትም እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል አስተዳዳር የሚመራው የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ ስሕተት መሆኑ አውቆ ይቁም ስላለው ማስተር ፕላን ፤አስቀድመው ማስተረት ፕላኑን እንደማይጠቅም የተረዱ፣ መረዳታቸውንም በአደባባይ በመግለፃቸው ብቻ፣በተለያየ የአገዛዙ ሥርዓት የማሰቃያ እስር ቤቶች የሚገኙ፤ የኦሮሞ ተወላጆች፣ የፓለቲካ መሪዎችና አባላቶች እንዲሁም ማንኛውም ዜጋ ፣ከማጎሪያ እስር ቤት ሊፈቱ ይገባል፡፡እናም ማስተር ፕላኑ ይቁም ከተባለ፤ የታሰሩት ይፈቱ፣ ገዳዮችም ለፍርድ ይቅረቡ

ecadaf

posted by tseday getachew

Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: