Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

Archive for the month “April, 2014”

ሚሊዮኖች ድምጽ – የእሪታ ቀን ሰልፍ በሚያዚያ 26 ቀን እንደሚደረግ የአዲስ አበባ አስተዳደሩ እውቅና ሰጠ !

«ህግንአክብረንለድርድርየማናቀርበውንህገመንግስታዊመብታችንንአሳልፈንአንሰጥም።ታላቁህዝባዊሰላማዊሰልፍ ‹‹የእሪታቀን ›› በሚልመሪቃልሚያዚያ 26፣2006 ዓ.ምበአዲስአበባከተማይደረጋል፡፡» ሲሉ የአንድነት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ አቶ ሃብታሙ አያሌው ገለጹ።

ፓርቲዉ ከአዲስ አበባ አስተዳደር አስፈላጊዉን እውቅና ያገኘ ሲሆን ፣ ከትንሳኤ በዓል በኋላ በሃያ ሶስቱም የአዲስ አበባ ወረዳዎችና በአዲስ አበባ አካባቢ ባሉ ቦታዎች ቅስቀሳ እንደሚያደርግ ለማወቅ ተችሏል። የአዲስ አበባ ሕዝብ በዚህ ቀን፣ በነቂስ ወጥቶ ድምጹን ያሰማል ተብሎ ይጠበቃል።

ሰልፉ ሊደረግ የታሰበው መጋቢት 28 የነበረ ሲሆን፣ በወቅቱ አስተዳደሩ ሕግን ባልጠበቀ መልኩ፣ አማራጭ ቀን ወይም ቦታ እንዲቀርብ ሳይጠይቅ በደፈናዉ እውቅና አልሰጠም የሚል ደብዳቤ መላኩ ይታወቃል። ለሕገ ወጥ እርምጃ እውቅና አንሰጥም በሚል፣ አንድነት የአስተዳደሩን ደብዳቤ እንደማይቀበል በማሳወቅ፣ የቅስቀሳ ዘመቻ ማድረጉን ፣ ከዚያም ጋር በተገናኘ 4 አባላት በፖሊስ መደብደባቸውን ፣ አምስት ደግሞ ለሳምንት መታሰራቸው ይታወቃል።

አስተዳደሩ የላከዉን ሕገ ወጥ ደብዳቤ በመቀልበስ፣ ለሚያዚያ 26 ቀን 2006 ዓ.ም  በአዲስ አበባ ከተማ ሰልፍ እንዲደረግ እውቅና  እንዲሰጥ መደረጉ ፣ የአንድነት አባላትና ደጋፊዎች ያደረጉት ትግል ዉጤት እንደሆነም የሚያመላክት ነው።

Ze-Habesha

posted by Tseday Getachew

Advertisements

ይድረስ ለብዙሃኑ የሠራዊቱ አባል ወገናችን!! የግንቦት7 መልእክት

 

የመከላከያ ሚኒስትር በተሰኘው የውሸት ሥልጣን ላይ የተቀመጠው አድርባይ ሲራጅ ፈርጌሳ ለይስሙላው ምክር ቤት ባቀረበው ሪፓርት፣ “የመከላከያ ሚኒስትር የብሔር ተዋጽዖ የተመጣጠነ” እንደሆነ ገለፀ። እንደ ሰውየው ሪፓርት ከሆነ የመከላከያ ሠራዊቱ 29.46 በመቶ አማራ፣ 25.05 በመቶው ከደቡብ ብሔሮች የተውጣጣ፣ 24.45 በመቶ ኦሮሞ፣ 17.47 በመቶው ትግራይ እና የተቀሩት ክልሎች ድርሻ 4.17 በመቶ ነው። መረጃው የተቀናበረው በክልል ቢሆንም የቀረበው ግን በዘር ነው። “ተመጣጠነ” የተባለውም የክልሎች ተዋጽዖ ሳይሆን የዘር ተዋጽዖ ነው። ሠራዊቱን እንዲህ በዘር ሸንሽንኖ የስታትስቲክስ ጨዋታ መጫወት አሳዛኝም አሳሳቢም ነገር ነው። የሆነ ሆኖ ይህ መረጃ፣ መረጃ ነው ተብሎ ለሕዝብ ቀርቧል።
ይህንን መረጃ የሰማ ማሰብ የሚችል አዕምሮ ያለው ሰው የሚጠይቀው የመጀመሪያ ጥያቄ “የሠራዊቱ ስብጥር በተገለፀበት ዓይነት የመኮንኖቹም ስብጥር ለምን አልተገለፀም?” የሚል ነው። ይህ ጥያቄ በአስተዋይ ሰው አዕምሮ ውስጥ በተነሳነበት ፍጥነት ምላሽ ያገኛል፤ ምክንያቱም ምላሹ እዚያው እቁጥሮቹ ውስጥ አለ። የመኮንኖቹ ስብጥር ያልተነገረበት ምክንያት አብዛኞቹ መኮንኖች በ17.47 በመቶው በመሆናቸው ነው። ወደዚህ መምደሚያ የሚደርሰው አሳቢው ስለፈለገው ሳይሆን የመረጃው አቀራረብ አመክኖ (ሎጂክ) ወደዚያ ስለሚገፋ ነው። በዚህም ምክንያት በሲራጅ ፈርጌሳ አንባቢነት የቀረበው የህወሓት ሪፓርት በገዛ ራሱ ላይ ነው የተኮሰውም።
እኛ እንደ ሲራጅ ፈርጌሳ የዘር ስታትስቲክስ ውስጥ አንገባም፤ መልዕክታችን ለተገፋውና እየተበደለ ላለው ለመላው የሠራዊቱ አባል ነው።
ይድረስ ሹመትና ኃላፊነት ተነፈገህ፤ የጥቂቶቹን ሀብትና ዝና ጠባቂ እንድትሆን ለተፈረደብህ ወገናችን!!! እስከመቼ ለህወሓትና ጥቂት አጎብዳጅ መኮንኖች ባርነት ትገዛለህ? ይህ ውርደትህ የሚያበቃው መቼ ነው? የታጠቀው መሣሪያ የአገርህና የራስህ ክብር ማስጠበቂያ፤ ነፃነትህን መጎናፀፊያ የምታደርገው መቼ ነው? ለመሆኑ ለመኮንንነት የሚያበቃ ጭንቅላት፣ ልምድ ወይም እውቀት ከፓርቲ አባልነት ነው የሚገኘው? ህወሓቶችና አጋሮቻቸው በሠራዊቱ ያሉትን ቁልፍ ኃላፊነቶችን ሁሉ ጠቅልለው ይዘው “ጀሌዎቻችን እንዲሆኑ ፈቅደንላቸዋል” የሚል ሪፓርት የሚያቀርቡት ምንኛ ቢንቁን ነው? ይህንን ውርደት ኢትዮጵያዊው ወኔህ እንዴት ይቀበለዋል?
ኢትዮጵያዊው ወታደር ከሌላው ኢትዮጵያዊ በባሰ በአምባገነንና ዘረኛ አለቆቹ እየተዋረደ እንደሆነ በገሃድ የሚታይ ጉዳይ ነው። የህወሓት አባላት ቁልፍ የስልጣን ቦታዎችን ይዘው ጦር ሠራዊቱን እንደ ፓርቲ መዋቅር ሲመሩት ማየት የሠራዊቱን አባላት ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚያንገበግብ ጉዳይ ነው። ሠራዊቱ አገርና ሕዝብን ሊጠብቅበት ይገባ የነገረው መሣሪያ በንጹሃን ዜጎች ላይ እንዲያነሳ፤ ሰላማዊ ሰዎችን እንዲደበድብ፣ እንዲረግጥና እንዲገድል የሚያዙት እነዚህ የህወሓትና ጥቂት አጎብዳጅ አለቆቹ እንደሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቃል። ሆኖም የኢትዮጵያ ወታደር የታዘዘው ሁሉ የሚፈጽም ባርያ አይደለምና በእነዚህ ጥቂት ዘረኛ አለቆችህ ላይ እንዲነሳ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይጠይቃል።
ውድ የኢትዮጵያ ወታደር ሆይ!!! “ዘረኛነት በቃኝ” በል። ለነፃነት፤ ለእኩልነት፤ ለአገር ክብር በሚታገሉ ወገኖችህ ላይ ክንድህን አታንሳ። የጥቂት ዘረኞችን ሥልጣን በማራዘም ከሚመካብክ የኢትዮጵያ ድሃ ሕዝብ ጋር ዘላቂ ቂም ውስጥ አትግባ። በትእቢት “ሁልሽንም ረግጠን እንገዛለን” ብለው የሚፎክሩት አንተን ከወገንህ ጋር ደም በማቃባት ነውና “እምቢ!” በላቸው። ለዘረኞች ስልጣን ብለህ አትሙት! እንዲያውም ለገዛ ራስህ ክብር፣ ለቤተሰቦችህና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነት ግንባር ቀደም አርበኛ ሁን።
ከላይ የተባለው ለፓሊስ አባላትም ይሠራል። በህወሓትና ህወሓት በየቦታው በፈጠራቸው ጀሌዎች የሚመራ በመሆኑ ከሕዝብ ፍላጎት በተፃፃሪ የቆመ ይምሰል እንጂ የኢትዮጵያ ፓሊስ የሕዝብ ወገን እንደሆነ በተለያዩ አጋጣሚዎች የታየ ጉዳይ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ በፍትህ እጦት የሚሰቃየውን ያህል ብዙሃኑ ፓሊስ በፍትህ እጦት እየተሰቃየ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ የኑሮ ጫና እንዳዳከመው ሁሉ የኢትዮጵያ ፓሊስም ኑሮ ከብዶታል። እንደሌላው ሰው ሁሉ ፓሊስንም ዘረኝነት አስመርሮታል። ብዙሃኑ ፓሊስ አቅሙን በጥቂት አምባገነን አለቆቹ ላይ የሚፈትሽበት ጊዜ ደርሷል።
የስለላ ተቋማቱ ጉዳይ ለየት ይላል። “ደህንነት” ተብሎ በሚሞካሸው የጆሮጠቢዎች ስብስብ በሆነው መሥሪያቤት እና በኤክትሮኒክስ ብርበራ የተሠማሩ “ባለሙያ ጆሮ ጠቢዎች” ውስጥ ህወሓት በአለቃነትም በምንዝርነትም አብዛኛውን ቦታ ይዟል። ሆኖም እዚህም የሕዝብ ወገኖች እንዳሉ ይታወቃሉ። በእነዚህ ቦታዎች ያላችሁ የሕዝብ ወገኖች ሲቻል በገሃድ ሳይቻል በሚስጥር ተቋማቱን የማዳከም ሥራችዎችን መሥራት የህሊናና የዜግነት ግዴታችሁ ነው። ከእናንተ ብዙ፤ እጅግ ብዙ ይጠበቃል። የምታሾልኳት ትንሿ መረጃ የብዙዎችን ሕይወት ልትታደግ ትችላለች፡
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በህወሓት የጦር፣ የፓሊስና የስለላ መዋቅሮች ውስጥ የሕዝብ ወገኖች እንዳሉ ያውቃል። እነዚህ ወገኖቻችን እንደሌላው ሕዝብ ሁሉ – አንዳንዴም ከሌላው በባሰ ሁኔታ – በፍትህ እጦት፣ በኑሮ መክበድና በዘረኝነት እየተሰቃዩ መሆናቸው ያውቃል። እነዚህ ወገኖቻችን ጥለው እንዲወጡ፤ ይህ ካልተቻለም ከውስጥ ሆነው የወያኔን የጦር፣ የፓሊስና የስለላ መዋቅሮች እንዲያፈራርሱ ጥሪ ያደርጋል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
posted by Tseday Getachew

ስለፍትህ ሲባል ስርዓቱ ይፍረስ! ፪ (ተመስገን ደሳለኝ )

በዚህ ርዕስ ሥር ባለፈው ሳምንት በይደር ካቆየሁት ተከታይ ጽሑፍ በፊት አንድ እርምት የሚያሻው ጉዳይን በአዲስ መስመር ላስቀድም፡፡

ሬዲዮ ፋና እና “አምደኞቹ”

ተመስገን ደሳለኝ

በ1988 ዓ.ም በኤፈርት ባለቤትነት ስርጭቱን አሀዱ ያለው “ሬዲዮ ፋና”፣ ከምስረታው አንስቶ ዛሬም ድረስ ልክ እንደ በረሃው ዘመን ሁሉ የሥርዓቱ ቀኝ እጅና የርካሽ ፕሮፓጋንዳው ማስተላለፊያ ቱቦ ሆኖ መዝለቁ ለወዳጅም ለጠላትም የማያከራክር ገሀድ የወጣ ሐቅ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተወሰኑ የግል ሚዲያዎች ላይ የርግማን ዘመቻ የታወጀ ይመስል ለተከታታይ ሳምንታት “ስመ-ጥር” ረጋሚዎችን ጣቢያው ድረስ ጋብዞ ማብጠልጠልና ማውገዙን ቀንደኛ ሥራው አድርጎ ይዞታል፡፡ በርግጥ ይህ ዘመቻ ከወራት በፊት በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የፕሬስ ድርጅት በኩል በ“ጥናት” ስም የወጣው ውንጀላ ቅጥያ ሲሆን፣ በቅርቡ ኢቲቪ ሰርቶ እንዳጠናቀቀው የሚነገርለት ዶክመንተሪ ፊልም ደግሞ “ሳልሳዊ” ዘመቻ ሆኖ ለጥቆ የሚቀርብ መሆኑን የመረጃ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

ሰሞነኛውን የፋና ዘመቻ ከተለመደው አቀራረብ የተለየ የሚያደርገው ከህወሓት ከበሮ መቺነት መሻገር የተሳነው ዛሚ ሬዲዮ ጣቢያን ከወከለው አቶ ዘሪሁን ተሾመ በተጨማሪ፣ የኢዴፓው አቶ ሞሼ ሰሙ እና የ‹‹ፎርቹ››ኑ ጋዜጠኛ ታምራት ወልደጊዮርጊስ በውጋ-ንቀል ስልት የርግማኑ ቡራኬ ሰጪ ሆነው መቅረባቸው ነው፡፡ ‹‹አዲስ አማኝ ከጳጳስ በላይ ልሁን ይላል›› እንዲሉ ሩቅ አላሚው የሕዳሴው ግድብ የሕዝብ ተሳትፎ አስተባባሪ ም/ቤት ምክትል ዳይሬክተር የሆነው ዛዲግ አብረሃም ሆነ ሚኒስትር ዴኤታው ሽመልስ ከማል የረከሰውን የአፈና መንፈስ ‹‹ለማቀደስ›› በቁርጠኝነት መሰለፋቸውን ሳንዘነጋ ማለት ነው፡፡ በርግጥ እነዚህ ሰዎች በቀጥታ ከስርዓቱ ህብስት ተቋዳሽ በመሆናቸው በዚህ ደረጃ ‹‹ማሸብሸባቸው›› ብዙም አያስገርምም፤ አስገራሚው ነገር ታምራት ወልደጊዮርጊስ ‹‹እንቁ›› እና ‹‹ፋክት›› መጽሔቶችን በአንድ ሰው የሚዘጋጁ አስመስሎ ከማቅረብም አልፎ፣ ማሕበረ ቅዱሳን የገጠመውን የመበተን አደጋን በተመለከተ የወጣውን ዘገባ እስከማውገዝ የደረሰበት ጽንፍ ነው፡፡

በወቅቱ ዛዲግ አብረሃ ሚዲያዎቹ እንዲደመሰሱ ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ፣ ታምራትም የማሕበረ ቅዱሳን አባላት ተቋማቸውን ከመንግስታዊ አፈና መከላከል እንዳለባቸው የምትመክረውን የ‹‹ፋክት›› ዘገባ ቃል በቃል ጠቅሶ ሲያበቃ ‹‹ቋቅ እያለኝም ቢሆን ከዛዲግ አብረሃ ጋር የምስማማበት ጉዳይ ይህ ነው›› በማለት ከፕሬስ አፈናው ጎን መቆሙን አስረግጦ ተናግሯል፡፡ በአናቱም መጽሔቶቹ ‹‹አብዛኛው ህዝብ የሚፈልገውን መርጠው የሚዘግቡ ናቸው›› ያለበት አውድ ነቀፋ ይሁን ምስጋና ግልፅ ባይሆንም፣ ቢያንስ አምባገነኑን በረከት ስምኦን እና ጋሻ-ጃግሬዎቹን ከማስደሰት፤ ብዙሃኑን ግፉአን ማገልገል የተሻለ ብቻ ሳይሆን የተቀደሰ ተግባር ስለመሆኑ በረከትም በልበ-ሙሉነት እሰጥ-እገባ ሙግት የማይሞክርበት ነጭ እውነት እንደሆነ ታምራት ቢያስተውለው የተሻለ ይመስለኛል፡፡ ግና፣ ሐቁ ይህ ቢሆንም ወንድም ታምራት ራሱ ብቻ ሙያውን አክብሮ የሚሰራ ጋዜጠኛ፤ ሌላውን ደግሞ ኃላፊነት የማይሰማው ከማድረጉም በዘለለ፣ እነዚህን ሚዲያዎች ከአርበኝነት ጋር አዳብሎ ለማውገዝ መሞከሩ የተኮረኮርኩ ያህል ሳልወድ በግድ ያሳቀኝ ጉዳይ ሆኖብኛል፡፡ ምክንያቱም በእኔ እምነት በኢትዮጵያችን ላለፉት ሁለት ዓስርታት ሥልጣኑን የተቆጣጠረው ለሕግ የማይገዛ እና በሙስና የተጨማለቀ ሥርዓት ከመሆኑ አኳያ በጋዜጠኝነትም ሆነ በየትኛውም ሙያ ለሚንፀባረቅ አርበኝነት የተሻለው ብያኔ፣ ሀገርን ከፍርሰት መታደግ ማለት ነውና፡፡

ደግሞም በዚህች ሀገር ዝግመታዊ-ሞት ፊት ላይ ቆሞ የኮሪደር ሐሜቶችን ከመዘገብ በእጅጉ ለቆና ረቆ በመሻገር የውደቀታችን ምክንያት የሆነውን አገዛዝ በሕዝባዊ እምቢተኝነት ማስወገድ ቅድሚያ የሚሰጠው ነው፡፡ የሆነው ሆኖ ብዙ ጊዜ በእንዲህ አይነት ውይይቶች ላይ ሚዛናዊ ለመሆን ይሞክር የነበረው ታምራት (ለዚያኛውም አቋሙ በግሌ አመስግኘው አውቃለሁ)፣ ማሕበረ ቅዱሳንን በተመለከተ የወጡ ዘገባዎችን ባወገዘበት አዛው ሬዲዮ ጣቢያ ስቱዲዮ ውስጥ ተቀምጦ፣ ሽመልስ ከማል አንድ እንኳ የታሰረም የተሰደደም ጋዜጠኛ እንደሌለ ጠቅሶ አይኑን በጨው አጥቦ ሲከራከር ትንፍሽ አለማለቱ የቀራኒዮ መንገድ እና የንግድ ስራ ፍፁም የማይተዋወቁ ሆድና ጀርባ መሆናቸውን የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡

በነገራችን ላይ በዚህ ውይይት የአደባባይ ምሁሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ እና የኢትዮ-ምህዳሩ ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ መሳተፋቸው ከሞላ ጎደል ከዘመቻው ጀርባ ያለውን ኢህአዴጋዊ ሴራ አጋልጦታል ብዬ አስባለሁና ባርኔጣዬን ከፍ አድርጌ አክብሮቴን ልገልፅላቸው እወዳለሁ፡፡ በተለይ ጉምቱ የፍልስፍና መምህር ዶ/ር ዳኛቸው፣ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብቶችን ብቻ ሳይሆን የሥርዓቱን ሃሳብ አልባነት ለመሞገት ለሚያደርገው አበርክቶ በድጋሚ አመሰግነዋለሁ፡፡…ከዚህ ሁሉ ሰበር ሐተታ በኋላ ወደ ክፍል ሁለቱ ዋናው አጀንዳችን ዘልቀን፣ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ለፍትሕ መበላሸት የዳኝነት ሥርዓቱ ብቻ ሳይሆን ፖሊስ እና ዐቃቤ ሕግም የአንበሳውን ድርሻ ስለመውሰዳቸው ለማመልከት እሞክራለሁ፡፡
ፖሊስ ሲባል…

…የተወሰኑ የፌደራል ፖሊስ አባላት ዝሆን አድነው እንዲያመጡ በአለቃቸው ይታዘዛሉ፡፡ ከሰዓታት በኋላም ፖሊሶቹ ግዳያቸውን አምጥተው ለአለቃቸው ያስረክባሉ፡፡ ይሁንና አለቅየው ግዳያቸውን ባየ ጊዜ ባለማመን ዓይኖቹ ፈጥጠው ሊወድቁ ደረሱ፤ ለምን ቢሉ፣እሱ ያዘዛቸው ዝሆን፣ እነርሱ ያመጡት ግን ሁለት ጥርሱ የወለቀ፣ አንድ ቀንዱ የተሰበረ፣ አንድ አይኑ የጠፋ፣ ምላሱ የተቆረጠ… ብቻ ምን አለፋችሁ በድብደባ ብዛት ሊሞት የተቃረበ ፍየል ነበርና፡፡ እናም በቁጣ፡-
‹‹ዝሆን አይደል ወይ አምጡ ያልኳችሁ?›› ሲል ያፈጥባቸዋል፤
‹‹ጌታዬ፣ ዝሆን ነኝ ብሎ እኮ አምኗል!›› በማለት ቆፍጣና ፖሊሶቹም በሕብረት መለሱለት፡፡

…ይህችን ቀልድ ለዚህ ንዑስ-ርዕስ መግቢያ ያደረኩት፣ በነባሩ ባሕል እንዲህ ያሉ ጉዳዮች በቀልድ፣ በግጥም፣ በምሳሌዊ አባባል… መገለፃቸው የተለመደ ከመሆኑ አኳያ ስለሀገራችን የፖሊስ አባላት ስንነጋገር ከቀልዷ ጀርባ መራራ እውነት ማድፈጡን አምነን እንድንቀበል ገፊ-ምክንያቶች በመኖራቸው ነው፡፡

እንደሚታወሰው በየትም ሀገር የተፈፀመ ወንጀል ከዐቃቤ ሕግም ሆነ ከፍርድ ቤት በፊት በፖሊስ የምርመራ ሂደት ውስጥ ማለፉ የግድ ነው፡፡ የዘርፉ ምሁራን ‹‹የፖሊስ ምርመራ ሳይንስ ነው›› እንዲሉ ሙያው ክህሎት የሚጠይቅ መሆኑ አይካድም፡፡ ይሁንና ተጨባጩ እውነታ የሚነግረን የ83ቱን የመንግስት ለውጥ ተከትሎ በዘርፉ እንዲሰማሩ የተደረጉት አብዛኞቹ መርማሪዎች ድርጅቱን ለቡሕተ-ሥልጣን ያበቁ ታጋዮች መሆናቸውን ነው፡፡ በርግጥም በረባውም ባልረባውም ወንጀል ተጠርጥሮ እጃቸው የገባውን ሁሉ አፈር-ድሜ በማስጋጥ የ‹‹ሚመረምሩበት›› መንገድ ኩነቱን ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ ይህ ሁናቴም ይመስለኛል የፖሊስን ሙያ ከሳይንሳዊ ጥበብ ወደ አሳረ-ፍዳ ማሳያ አውርዶ የተጠላ ያደረገው፡፡ ለዚህም ኩነና በርካታ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ የሩቁን ትተን የቅርቡን እንኳ ብንመለከት የህዝበ-ሙስሊሙ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ችሎት ላይ ቀርበው በማዕከላዊ ምርመራ እስር ቤት መርማሪ ፖሊሶቹ ሰብዓዊ መብቶቻቸው ተገርስሶ ሲያበቃ ምን ያህል አካላዊና መንፈሳዊ ስቅየት እንደደረሰባቸው ከተናገሩት መሀል የሚከተሉትን በዋናነት እናገኛለን፡-

‹መርማሪ ፖሊሶቹ እንቅልፍ ከልክለው የተዳከመ አካልን ልብስ አስወልቆ እርቃን በማስቀረት መግረፍ፣ የዘር ፍሬ ብልት ላይ በውሃ የተሞላ ጠርሙስ ማንጠልጠል፣ በኤሌክትሪክ ገመድ የውስጥ እግርን መግረፍ፣ ጢምን በአሰቃቂ ሁኔታ መንጨት፣ እጅና እግርን ሰብዓዊነት በጎደለው መልኩ ለረጅም ሰዓታት ማሰር፣ ጭንቅላትን በቆሸሸ ውሃ ውስጥ መንከር፣ ከ24 ሰዓታት በላይ ቀጥ ብሎ እንዲቆሙ ማስገደድ፣ በኤሌክትሪክ ኃይል ሾክ ማደረግ እና የመሳሰሉት፡፡› በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማትም በተደጋጋሚ ጊዜ በተለይም ከደርግ ስርዓት ጀምሮ ዋነኛ ማሰቃያ በሆነው ማዕከላዊ የምርመራ ጣቢያ የሚፈፀመውን ተግባር በሪፖርት መልክ ማውጣታቸው ይታወሳል፡፡ ከወራት በፊት ሂዩማን ራይትስ ዎች ይህንን የስቃይ ጣቢያ አስመልክቶ ‹‹They want a confession: Torture and Ill-treatment in Ethiopia’s Makelawi Police Station›› በሚል ርዕስ ባሰራጨው ሪፖርት በጣቢያው የሚፈፀመውን ግፍ ከመግለፁም በተጨማሪ፣ ታሳሪዎች እንዴት ባለ ሁኔታ ‹‹የእምነት ቃል››እንደሚሰጡ አመላክቷል፡፡ ለማሳሌም አንድ ስሙ ያልተጠቀሰ፤ ነገር ግን በጣቢያው ታስሮ የነበረ ሰው ገጠመኝን ከሪፖርቱ እንደሚከተለው ልጥቀሰው፡-

‹‹ወደ ጣቢያው የገባሁ ቀን ኢ-ሜይል አድራሻዬን ከነምስጢር ቁልፉ እንድሰጣቸው ጠየቁኝ፤ ሰጠኋቸው፡፡ በውስጡም ምንም አይነት የፖለቲካ አንድምታ ያለው መልዕክት አልነበረም፡፡ ይሁንና ከሶስት ቀን በኋላ በዛው አድራሻዬ ‹ከኦነግ የተላከ መልዕክት ተግኝቷል› ብለው ጠየቁኝ፡፡ ሆኖም ነገሩን እንደማላውቅ እያወቁ ‹ለእኔ የተላከ መልዕክት ነው› ብለህ ፈርም ሲሉ አዘዙኝ፡፡ እኔም ከታሰርኩ በኋላ የተገኘ በመሆኑ አልፈርምም አልኩ፡፡ በዚህም የተነሳ ከፍተኛ ድብደባ ፈጽመውብኛል፡፡››

በርግጥም የሀገሪቱን የወንጀል ምርመራ ስራን ተነቃፊና ተወጋዥ ያደረገው በእውቀት ማነስ፣ በስቅየት (በቶርቸር) እና በሙስና የተተበተበ መሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ በአደረጃጀቱም ነው፤ ለምሳሌ ከፌዴራልና ክልል ፖሊስ በተጨማሪ ግምሩክ የራሱ እስር ቤት፣ የራሱ መርማሪና ዐቃቢ-ሕግያን አሉት፡፡ ፀረ-ሙስናም እንዲሁ የጠረጠረውን ሁሉ አስሮ ይመረምራል፤ ይከስሳልም፡፡ አንዳንድ ምንጮቼ እንዳቀበሉኝ መረጃ ከሆነ ደግሞ በሽብር ጉዳይ የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን (ቡድኖችን) ራሱን ችሎ አስሮ የሚመረምር እና የሚከስ ተቋም በቅርቡ በአዋጅ ሊቋቋም ዝግጅቱ ተጠናቅቋል፡፡ እንግዲህ እነዚህ ሁሉ መዋቅራዊ ትስስር በሌለው ሁኔታ በፖሊስ ስራ የመሰማራታቸው ምስጢር፣ አንድም ሳይንስ እንጂ አሳር ዕውቀት ባለመጠየቁ፣ ሁለትም ንፁሀንን ከወንጀለኛ ጋር ደባልቆ ለመውቀጥ ስለሚመች፣ ሶስትም ስርዓቱ ተቀናቃኞቹን ለመደፍጠጥ በ‹‹ሕጋዊ አሠራር›› ሽፋን ተጨማሪ ጡንቻ እንዲኖረው ማስቻሉን በማስላት ይመስለኛል፡፡ በዚህ አይነት ምርመራ የተገኙ መረጃዎችም ፍርድ ቤት ቀርበው እንደሕጋዊ ማስረጃ እየተቆጠሩ እስከ ዕድሜ ልክ የእስር ቅጣት ሲያስበይኑ ደጋግመን ተመልክተናል፡፡

ይህም ሰፊው ሕዝብ በፍርሃት እየተርበደበደ ሰጥ-ለጥ ብሎ እንዲገዛ፤ አሊያም እንደ ጥንቸሊቷ አገር ጥሎ እንዲጠፋ ለማድረግ ያለው ጉልበት በግልፅ ተተግብሮ የታየ የሥርዓቱ የዕለት ተዕለት ምግባር ነውና ከዚህ በላይ ትንታኔ አያሻውም፡፡ ከዚህ ይልቅ የጥንቸሏ አፈ-ታሪክ ተብሎ የሚነገረው ነባራዊ እውነታውን በሚገባ ያንፀባርቃልና እንደወረደ ልጥቀሰው፡-…ከለታት አንድ ቀን አንዲት ጥንቸል ከመጣባት የመዓት ናዳ ማምለጥ የምትችለው ቀዬዋን ጥላ ስትሰደድ እንደሆነ ብቻ በማመኗ ልቧ እስኪፈነዳ ድረስ ጋራ-ሸንተረሩን እያቆራረጠች ስትሮጥ ድንገት ከሀገሪቱ ድንበር አጠገብ ከሚኖር አንድ ግድንግድ ጦጣ ጋር ፊት-ለፊት ተፋጠጠች፣ በድካም ዝላም ቁና ቁና እየተነፈሰች ‹‹ይህ ጦጣ ፖሊስ ይሆን እንዴ?›› ብላ እየተጠራጠረች ማምለጫ ዘዴ ስታውጠነጥን፣አያ ጦጣ፡- ‹‹ወይዘሪት ጥንቸል፣ ለመሆኑ ምን የከበደ ጉዳይ ቢገጥምሽ ነው እንዲህ ልብሽ እስኪፈርስ ድረስ የምትሮጪው?›› ሲል ይጠይቃታል፤‹‹የዝሆን ዘር በሙሉ ከያለበት ተለቅሞ በቁጥጥር ስር እንዲውል አስቸኳይ ትዕዛዝ መውጣቱን እስካሁን አልሰሙም እንዴ?›› ብላ በጥርጣሬ ትክ ብላ እያስተዋለችው ጥያቄውን በጥያቄ ስትመልስለት፣

አያ ጦጣ፣ እጅግ በጣም ከመደነቁም በላይ ግራ ግብት እያለው ‹‹ታዲያ አንቺ ምን አገባሽ፤ ዝሆን አይደለሽ?›› ሲል መልሶ ይጠይቃታል፤ ‹‹ወይ አያ ጦጣ! ዝሆን ባልሆንስ?! አለመሆኔ ተጣርቶ እስክለቀቅ ድረስ ለምን ብዬ ታስሬ ልገረፍ? ደግሞስ በዱላ ብዛት ዝሆን ነኝ ብዬ ያመንኩ እንደሆነ መጨረሻዬ ምን ሊሆን እንደሚችል አስበውታል? ይልቅ እርስዎም አይሞኙ! በጊዜ አብረውኝ ከመዓቱ ዘወር ብለው ቢቆዩ ይሻሎታል፤ ኑ እንሂድ›› ብላ በፍርሃት የተዋጠችው ምስኪኗ ጥንቸል ሩጫዋን ቀጠለች፡፡ …በእኛይቱ የመከራ ምድርም፣ እኛና ኢህአዴግ በዚህ ደረጃ ፍፁም የማንተማመን፣ በጎሪጥ የምንተያይ ሆነን ከቀረን እንደ ዘበት ሃያ ምናምን አመታት ተቆጥረዋል፡፡

ዐቃቢ ሕግ ሲባል….

በዚህ አውድ ሌላው ተጠቃሽ ተቋም፣ ፖሊስ በ‹‹የትም ፍጪው…›› መንገድ ያመጣለትን ‹‹መረጃ›› ሳያላምጥ በመዋጥ ለክስ የሚያበቃው ዐቃቤ ሕግ ሲሆን፣ ለአጠቃላዩ የፍትሕ መዛባትና መጨማለቅም በዕኩል ደረጃ ተጠያቂ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

ለአደባባይ ያልበቁ አያሌ የዐቃቢ-ሕግያን ሸፍጦችን ትተን በድህረ ምርጫ 97 የተከሰተውን አለመግባባት ተከትሎ ለእስር ከተዳረጉት የቅንጅት ለአንድነትና ለፍትህ ፓርቲ አመራሮች ጋር የተያያዘውን እንመልከት፡፡ እንደሚታወሰው መጀመሪያ የቀረበባቸው ክስ ‹‹የዘር ማጥፋት›› የሚል የነበረ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያን በተመለከተ ለረዥም ዓመታት ጥናት ያደረገው አሜሪካዊ ፕ/ር ዶናልድ ሌቨን፣ አቶ መለስን ‹‹ዘር ማጥፋት እኮ ቀልድ አይደለም›› በማለት አጥብቆ ከወቀሰው በኋላ ክሱ ‹‹ሕገ-መንግስቱን በኃይል የመናድ እና ዘር የማጥፋት ሙከራ›› ወደሚል መቀየሩን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ይናገራሉ፡፡

የሆነው ሆኖ ጉዳዩ ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት ዐቃቢ-ሕግያኑ በተከሳሾቹ ላይ በ‹‹ማስረጃ››ነት ካቀረቡት ሰነዶች መካከል የአባላዘር በሽታ የህክምና ምርመራ ወረቀትን ጨምሮ፣ ሀሰተኛ (ፎርጅድ) ደብዳቤዎች እና ከክሱ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌላቸው የቪዲዮ ፊልሞች እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ‹‹የቃሊቲው መንግስት›› በሚለው መጽሐፉ፣ በጥቅምት 25/1998 ከ‹‹አዲስ አበባ ፖሊ ከፍተኛ ክሊኒክ›› ቢኒያም (የአባቱም ስም ተጠቅሷል) ለተባለ ሰው የአባላዘር ምርመራ አድርጎ የተሰጠው የሕክምና ምስክር ወረቀት ‹‹ሕገ-መንግስቱን በኃይል ለመናድ ሞክረዋል›› በተባሉት የቅንጅት መሪዎች ላይ በ‹‹ማስረጃ››ነት መቅረቡን ከመጥቀሱም በላይ ሰነዱን በገጽ 444 ላይ እንዳለ በማተም ለታሪክ ምስክርነት አብቅቶታል፡፡ መቼም ይህ ሁናቴ አቶ መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያ ጦር ሶማሊያን የወረረው የአሜሪካንን ተልዕኮ ለማስፈፀም ነው? ተብሎ ለቀረበበት ወቀሳ አከል ጥያቄ፣ አሜሪካ የምትሰጠው ዕርዳታ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን መከላከል ላይ ያተኮረ እንደሆነ ከገለፀ በኋላ ‹‹ሶማሊያ ውስጥ ደግሞ በኮንዶም አንዋጋም!›› ብሎ እንደመለሰው አይነት ቧልት አቅልለን እንዳናልፈው የሚያግደን ጉዳዩ ‹‹አንድ ንፁህ በሀሰት ከሚፈረድበት፣ ሺ ወንጀለኞች በነፃ ቢለቀቁ ይመረጣል›› ከሚባልለት ፍትሕ ጋር የሚያያዝ በመሆኑ ነው፡፡

በጥቅሉ ላለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ ለእስር የተዳረጉ ንፁሀንም ሆነ በሙስና የተወነጀሉት ላይ እየቀረበ ያለው ክስና ማስረጃዎችን ሥራዬ ብሎ ለመረመረ ሰው፣ የፍትሕ መዛባቱን ደረጃ ፍንትው አድርገው ያሳዩታል ብዬ አስባለሁ፡፡ ለምሳሌም ከወራት በፊት ‹‹በገቢዎችና ግምሩክ ባለሥልጣን የአ/አ ኤርፖርት ቅ/ጽ/ቤት የመንገደኞች ጓዝ የሥራ ሂደት መሪ›› ባለሥልጣን ላይ የተመሰረተውን ክስ ብናየው እንዲህ የሚል ሆኖ እናገኘዋለን፡-

‹‹ከአሜሪካና ከአውሮፓ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ መንገደኞች ዕቃዎቻቸውን አስፈትሸው ቀረጥና ታክስ ሊከፈልባቸው የሚገቡት ላይ መክፈል እንዳለባቸው ኮንትሮባንድም ከሆነ እንደሚወረሱ እያወቀ ማንነታቸውና ብዛታቸው ያልተለዩ መንገደኞች ዕቃቸው እንዳይፈተሽ ማድረግ፡፡››

መቼም ይህ አይነቱ ክስ በምድራችን የመጀመሪያው ሳይሆን አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ማንነታቸውና ብዛታቸው፣ ቀኑና ወሩ ተለይቶ ባልታወቀበት ጊዜ ከመንገደኞች ጋር በመመሳጠር የተሰራ ወንጀል አለ ብሎ ክስ መመስረት ከጥንቆላ በምንም ሊለይ አይችልምና ነው፡፡ ኧረ ለመሆኑስ! የሰዎቹ ቁጥርና ያስገቡት የዕቃ ዓይነት ካልታወቀ ባለሥልጣኑ ‹‹ፈፀመ›› በተባለው ሙስና ሀገሪቱ ከቀረጥ ማግኘት የነበረባትና ያሳጣት ገቢ ምን ያህል ነው? አንድ ብር? አንድ ሺህ? አንድ ሚሊዮን ወይስ አንድ ቢሊዮን? ይሁንና የተከሳሽ ጠበቆች ክሱ በዚህ መልኩ መቅረቡን በፍርድ ቤት በመቃወማቸው ዐቃቢ ህግ አሻሽሎ እንዲያቀርብ ይታዘዛል፡፡ ተሻሽሎ የቀረበው ደግሞ ባጭሩ እንዲህ ይጠቀሳል፡-

‹‹ቀኑና ወሩ ተለይቶ ባልታወቀበት በ2002 ዓ.ም ዜግነታቸው አሜሪካዊ የሆነ ሁለት ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ሁለት ሻንጣ የመኪና መለዋወጫ ከተያዘባቸው በኋላ አስለቅቋል፡፡ ግንቦት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የሰንሻይን ኮንስትራክሽን ባለቤት አቶ ሳሙኤል ታፈሰ ከዱባይ ሀገር ያስገቡት የመኪና መለዋወጫ ዕቃ እንዲያልፍ ሲያስደርግ በሌላ ባልደረባው ተይዟል፤ ከሐምሌ ወር 2002 ዓ.ም እስከ ነሐሴ ወር 2003 ዓ.ም ከጠዋቱ አንድ ሰዓት እስከ አራት ሰዓት ባለው ጊዜ ከተለያዩ ሀገራት ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ መንገደኞች ሠልፍ ይዘው እያለ ከዚህ መለስ ያሉት መንገደኞች ሻንጣቸውን ሳያስፈትሹ፣ ቀረጥና ታክስ ሳይከፍሉ እንዲያልፉ ማድረግ፡፡››

እነሆም እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ሀገሪቱ እንዲህ ባሉ የሕግ ባለሙያዎች ስር ወድቃለችና ‹እግዚኦ በሉ›፡፡ እግዚኦታው ግን የሁለቱ እንስቶች ስም እና ያሳለፉት ዕቃ ተመን ባለመታወቁ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም በጽሁፍ በቀረበ ክስ ላይ ከሠልፈኞቹ መካከል ‹‹ከዚህ መለስ ያሉት መንገደኞች…›› ተብሎ ድፍን ያለ ነገር ‹‹መረጃ›› ሆኖ መቅረቡ ነው፡፡ ግና፣ ይህ ምን የሚሉት መረጃ ነው? ያውም ለፍርድ ቤት! እናም ጥያቄያችን እንዲህ እያለ ይቀጥላል፡- የትኛው ሠልፍ ጋ ያሉ መንገደኞች ናቸው በሕገ-ወጥ መንገድ ያለፉት? የቀኙ? የመሀለኛው? የግራው? የሠልፉስ ርዝመት ምን ያህል ነው? የሠልፈኞቹስ ብዛት? አምስት? ሀምሳ ወይስ አምስት መቶ? በርግጥ ክሱ ለአንዱም ጥያቄያችን ምንም አይነት ምላሽ አይሰጥም፡፡ ጉዳዩን ይበልጥ የሚያወሳስበው ደግሞ ይህ ‹ሾላ በድፍን› የሆነ ወንጀል የተፈፀመው ከሐምሌ ወር 2002 ዓ.ም እስከ ነሐሴ ወር 2003 ዓ.ም ድረስ በየቀኑ መሆኑ ነው፡፡ መቼም እነዚህ ሁሉ ጉዶች እውነት ከሆኑ በዚህች ሀገር፣ ማፍያ እንጂ መንግስት አለ ብሎ የሚመሰክር ደፋር ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡

በጥቅሉ የፖሊስም ሆነ የዐቃቢ-ሕግያኑና የዳኞቹ እንዲህ ሙያውን እና ተቋሙን የማራከስ አካሄድ ከአንድ ገፊ-ምክንያት የዘለለ ሌላ መነሾ የምናገኝለት አይመስለኝም፡፡ ይኸውም ሥልጣኑን ለማራዘም ምንም ነገር ከማድረግ የማይመለሰው ኢህአዴግ፣ በዋናነት ዋስትና የሚሆኑትን ፖሊስ፣ ዐቃቢ-ሕግ እና ፍርድ ቤቶችን በታጋዮች እና በካድሬዎች በመሙላት፣ በተለየ የፖለቲካ አቋም ከፊቱ የሚቆሙትን እየጨፈለቀ ለማለፍ አስልቶ የቀመረው በመሆኑ ነው፡፡

ኦርዌላዊ ስርዓት

የዚህን ስርዓት ቅጥ ያጣ አምባገነንነት ማብራራት አድካሚ እየሆነ ነው፡፡ የሚፈርሰው ማህበራዊ ዕሴት፣ የሚናደው ሀገራዊ ማንነት፣ እንደ አምባሻ የሚቆራረሰው መሬት፣ አልፎ ተርፎም እየጠፋ ያለው ትውልድ እና መሰል ጉዳዮችን ጠቃቅሶ፣ የነገይቷ ድህረ-ኢህአዴግ ኢትዮጵያ በገዢው ስብስብ ክፉ መዳፍ ሳቢያ ህልውናዋ ከገደሉ ጠርዝ ላይ ስለመቆሙ ማተት መደጋገም ነውና እንለፈው፡፡ ይህም ሆኖ ግን አገዛዙ በፍትሕ ስርዓቱ በኩል የሚያካሂዳቸው ዘግናኝ ድርጊቶች የመዓቱን ጊዜ ቅርብ የሚያደርጉ መሆናቸውን ማስታወስ (የሚሰማ ባይኖርም) የዜግነት ግዴታ ይመስለኛል፡፡ የአሜሪካ መንግስት ስቴት ዲፓርትመንትን ጨምሮ፣ ቁጥራቸው የበዛ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ተቋማት በተደጋጋሚ እንደዘገቡት፣ የዚህች አገር ምስኪን ልጆች በማይታወቁ ድብቅ እስር ቤቶች ጭምር መከራ እየወረደባቸው ነው (እኔ ይህንን ጽሑፍ በማዘጋጅበት፣ እናንተም አሁን በምታነቡበት ሰዓትም ቢሆን ለይተን በማናውቃቸው በርካታ የስቃይ እስር ቤቶች፣ በእልፍ አእላፍ ወገኖቻችን ላይ ግፍ እየተፈፀመ መሆኑን መካድ አይቻልም)፡፡

እነዚህ ማሰቃያ ቦታዎች ከምስራቅ እስከ ምዕራብ፣ ከደቡብ እስከ ሰሜን ባሉት የሀገሪቱ አካባቢዎች ተሰበጣጥረው የተዘጋጁ ናቸው፡፡ በነዚህ ካምፖችም የሚታጎሩት ዜጐች በዋነኝነት ከገዢው ግንባር የተለየ (የሚቃረን) ፖለቲካዊ አመለካከት ያላቸው ስለመሆኑ የተቋማቱ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡ በተለይም ብረት አንስተው የሚታገሉ ኃይሎች የተነሱባቸው ክልል ተወላጆችን ማሰቃያ ካምፖቹን የሚያደልቡ ‹የተመረጡ› መከረኞች ሆነዋል፡፡ ኢህአዴግ እንጥፍጣፊ ለሕገ-መንግስቱ አክብሮት ቢኖረው፣ የዜጎቹ ወንጀሎች የቱንም ያህል ቢከፉም እንኳ፣ በግልጽ የፍርድ ሂደት ተገቢ የሆነ ተመጣጣኝ ቅጣት ማግኘት በተገባቸው ነበር፡፡

የዚህ አይነቱን የፍትህ ምኩራቡ አስፀያፊ እርክስናን፣ በግላጭ የሚያሳየን ሌላኛው ጭብጥ በኦጋዴናውያኑ ላይ እየወረደ ላለው ግፍ ተጠያቂ ተቋምም ሆነ ባለሥልጣን እስካሁን ድረስ አለመኖሩ ነው፡፡ የስዊድናውያኑን ሁለት ጋዜጠኞች መታሰርና በይቅርታ መፈታት ተከትሎ፤ በክልሉ ያለው ፍርድ ቤት ስለማያውቀው ዝርፊያ፣ እስርና ግድያ በምስልና በድምፅ የተደገፉ ማስረጃዎች ከጥቂት ወራት ወዲህ ተሰምተዋል፡፡ የአካባቢው የቀድሞ ባለስልጣን ወደስዊድን በተሰደደ ማግስት ያቀረባቸውን እነዚህን ማስረጃዎች ኢህአዴግ እንደለመደው የኦብነግ ከንቱ ውግዘት አድርጎ ማለፍ አይቻለውም፡፡ በዚህ ሰው ማስረጃም ሆነ ክልሉን ባጠኑ ምሁራንና ተቋማት ዘገባዎች መሰረት የጠቀስኳቸው ዘግናኝ ክስተቶች ማህበረሰቡን እየናጡት ነው፡፡

በተለይ ልዩ ሚሊሺያ የሚባለው ሕገ-ወጥ ሀይል፣ በሱማሌ ክልል ጎዳና ላይ ያሻውን እያነቀ እንዲያስር፣ ልጃገረዶችን እንዲደፍር፤ ገፋ ካለም በጥይት አረር እንዲረሽን የተተወበት አግባብ የሚመሰክርልን የፍትሕ ስርዓቱ ድምጥማጡ ስለመጥፋቱ ብቻ ነው፡፡ በዚህ መልኩ በሌሎቹም የሀገራችን ክፍሎች ካለዘውግ፣ ሐይማኖት እና ዕድሜ ልዩነት፤ ካለፍርድ ቤት እውቅና እየተፈፀመ ያለው ግፍ፣ የፍትህ ተቋሙ የዜጎችን ህልውና ለመጨፍለቅ ከገዢዎች ጋር በጥብቅ የተጋመደ ስለመሆኑ ያስረግጡልናል፡፡ እንግዲህ ፍትሕና ርትዕ የሰማይ ላይ ሩቅ ተስፋዎች እንዲሆኑብን የፈቀደውን ስርዓት እስከ መቼ መታገስ ይቻለናል? ስለርትዕ በኢትዮጵያ ምድር ላይ መስፈን ሲባልስ፤ የኢህአዴግን ቅፅር በህዝባዊ ሰላማዊ አብዮት ብንንደው፣ መስዋዕትነታችን ሀገርን ከመዓት ለማዳን ሲባል በፈቃደኝነት የሚከፈል ትውልዳዊ ግዴታ አይደለምን?! (በቀጣዩ ከአራጣ ማበደር ወንጀል እስከ መንግስታዊ ሙስና ላሉ ጉዳዮች እና ለፍትሕ ሥርዓቱ ሞቶ መቀበር ማሰሪያ አበጅቼ አጀንዳውን ለጊዜው እደመድመዋለሁ)

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ

አዲስ አበባ

 

Ze-Habesha 

posted by Tseday Getachew

የኢህአዴግ “አሸባሪነት”በ2007 ምርጫ ማንን ያስር ይሆን?

ሳሙኤል ተወልደ በርሔ/ሃርስታድ ኖርዌይ/

ሰው በላው የኢህአዴግ “አሸባሪነት” ለ2007 ምርጫ ምን እየቆመረ ይሆን?…ኢህአዴግ  ስልጣኑን ከተቃውሞም ሆነ ከነፃው ፕሬስ ወቀሳ የሚያረጋጋበት በርካታ ኢ-ፖለቲካዊ (ኢ-ዴሞክራሲያዊ) አካሔዶች አሉት፡፡ ኢህአዴግ እንደቀደምቶቹ የኢትዮጵያ መንግስታት ሁሉ የተቃውሙትን ፖለቲከኞች አስሯል፤ በዩኒቨርስቲ ውስጥ የአካዳሚ ነፃነታቸውን የጠየቁ ተማሪዎችን በፖሊስ አስደብድቧል፤ ከፍ ሲልም በእስር አሰቃይቷል፡፡ ብዙዎችንም በፖለቲካ አመለካከታቸው (በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ) ከገዛ ሀገራቸው እንዲሰደዱ አድርጓል፡፡ ንቁ  የፖለቲካ ተሳትፎ በሚያደርግ አባወራ ምክንያት የቤተሰቡ አባላት ከፍተኛ ወከባ እና እንግልት እንዲደርስባቸው አስደርጓል፡፡

የ1997 ዓ.ም ምርጫ ውጤት ፍፁም ወደተቃዋሚዎች ማጋደሉን የተመለከተው እና ስልጣኑ አደጋ ላይ መውደቁን የተገነዘበው ኢህአዴግ ከ97 ዓ.ም በኋላ እስከአሁን ድረስ ያለውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ እጅግ አስጨናቂ ማድረጉ የአደባባይ ሐቅ ነው፡፡ ከአስጨናቂ እና ከኢ-ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ርምጃው መካከል በዋነኝነት ሊጠቀስ የሚችለው ደግሞ “አሸባሪነት” የሚለው ታፔላው ነው፡፡

በዚህ ሰው በላ ሐሳዊ ፍረጃውም ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ ተቃዋሚዎችን፣ ሞጋች የነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞችን፣ የሰብዓዊ መብት አቀንቃኞችን…ባጠቃላይ ስልጣኔን በዓይነ ቁራኛ ይመለከቱብኛል ብሎ ቀይ መስመር ያሰመረባቸውን ሰዎች አስሮ አስቀምጧቸዋል፡፡

በዚህ ስጋቱ የሚቀጥል ከሆነ ደግሞ በ2007 ዓ.ም በሚካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ ንቁ ተሳታፊ ይሆናሉ ብሎ የሚገምታቸውን የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች እንዲሁም የነፃው ፕሬስ  ሞጋች ጋዜጠኞችን በ“አሸባሪነት” ሰበብ እየቀፈደደ ወህኒ ሊያወርዳቸው እንደሚችል የማይጠረጥር የኢህአዴግን አስከፊ የፖለቲካ ስነ-ባህሪ የማያውቅ ብቻ ነው፡፡

ይህን ያልኩት ያለ በቂ ምክንያት አይደለም፡፡ በ1997 ዓ.ም የምሁራን ስብስብ በነበረው ቅንጅት የደረሰበት ወደር አልባ ሽንፈት ዳግም እንዲደገምበት ስለማይፈልግ ለስልጣኑ የሚያሰጉ ፓርቲዎችን (አመራሮቻቸውን) አነፍንፎ ከመያዝ ወደ ኋላ አይልም፡፡

በዚህም የተነሳ የ2007ቱን ብሔራዊ ምርጫ ተቃዋሚዎች እንደፈለጉ እንዲሆኑበት እና የነፃው  ፕሬስ አባላት በነፃነት እንዲዘግቡት ሁኔታዎችን ያመቻቻል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ እናም በ97  ዓ.ም ምርጫ ለወህኒ ቤት እንደተገበሩት ተቃዋሚዎች እና ጋዜጠኞች ለ2007ቱም ምርጫ እንደ አድባር የሚገበሩ ተቃዋሚዎች እና ጋዜጠኞች አይጠፉም፡፡ ጥያቄው ይገበራሉ ወይስ አይገበሩም? የሚለው ሳይሆን፤ እነማን ይገበራሉ? የሚለው ነው፡፡

ደርግ በዘመነ ስልጣኑ የተቃውሞ ድምፅ ሲያሰሙት የነበሩ ሰዎችን “አድኃሪ፣ አወናባጅ…” ወዘተ እያለ ይፈርጅ ነበር፡፡ ፈርጆ ሲያበቃም “አድኃሪዎች” ምኖች፣ ምናምኖች ያላቸውን ሰዎች  ከማሰርና ከመደብደብ አልፎ እስከ መግደል የደረሰ እርምጃ ይወስድባቸው ነበር፡፡ ደርግ እንዲያ ሲፈርጅ፣ ሲገድል፣ ሲያስር፣ ሲደበድብ የነበረው ለህልውናው ስለሚሰጋ ነበር፡፡

እየፈረጀ ባያስር፣ እያሰረ ባይገድል…የተቃውሞ ድምፅ የሚያሰሙ ወገኖች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ ስልጣኑ (ህልውናው) አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ስለሚያምን የስልጣን ትንኮሳ ለሚያደርጉበት ሰዎች እንቅልፍ የለውም ነበር፡፡ ጃንሆይም ተቃውሞ ያሰሙባቸው የነበሩ  የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን “ፀረ ዘውድ፣ ፀረ ንጉስ…” እያሉ በመፈረጅ ለህልውናቸው ማቆያ  ወይም ለስልጣን ማረጋጊያ የሚያግዙ ርምጃዎችን ይተገብሩባቸው ነበር፡፡

እነሆ ኢህአዴግም “ከማን አንሼ” በሚል ስሜት የሰላ ሂስ የሚያቀርቡ ጋዜጠኞችን፣ ለስልጣኔ  (ለወንበሬ) ያሰጉኛል የሚላቸውን ጠንካራ ተቃዋሚዎችን እያደነ በ“አሸባሪነት” ስም ወህኒ ያወርዳቸው  ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል፡፡ በጋዜጠኞቹ በእነ እስክንድር ነጋ እስር (“የአሸባሪነት ታፔላ”)  ነፃውን ፕሬስ ለማስበርገግ፣ በፖለቲከኞቹ በእነ አንዷለም አራጌ ተመሳሳይ ታፔላ የተቃውሞውን መንደር ለማስደንበር መላ ዘይዶ የተነሳው ገዢው ፓርቲ “አሸባሪ” የሚለውን ሰበብ የህልውናው ማስጠበቂያ “ዘበኛ” ሳያደርገው የቀረ አይመስለኝም፡፡

ጋዜጠኞች በ“አሸባሪነት” ስም ወህኒ በወረዱ ቁጥር መንግስት የሰላ ሂስ ከሚሰነዝሩ የነፃው  ፕሬስ አባላት ሂስ “ነፃ” እየወጣ ይሄዳል፡፡ እንዲሁ ከፍተኛ የህዝብ ቅቡልነት የተቀዳጁ  የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች “አሸባሪ” በሚል ሰረገላ ወህኒ ሲወርዱ ገዥው ፓርቲ የስልጣን ማገሩን ይበልጥ እየተከለው እና እያጠበቀው ይመጣል፡፡ ታዲያ ከ”አሸባሪነት” በላይ  የመንግስትን ህልውና (ስልጣን) እያስጠበቀ ያለ ዘብ ይኖር ይሆን?

ኢህአዴግ “አሸባሪነት”ን ለብቻው የሚረዳበት (የሚተረጉምበት) የተለየ መዝገበ ቃላት እንዳለው የምናውቀው የነ አሜሪካን አቋም በአንክሮ የገመገምን ዕለት ነው፡፡ እንደሚታወቀው አሜሪካና  ኢትዮጵያ “የጸረ ሽብር” አጋር ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግስት “አሸባሪ” እያለ የሚያስራቸውን ጋዜጠኞች እና ተቃዋሚ ፖለቲከኞች አሜሪካ “አዎ! አሸባሪ ናቸው” ብላ አታምንም፡፡

ይባስ ብላ “በሽብርተኝነት” ስም የታሰሩ ጋዜጠኞችን እና ፖለቲከኞችን በአስቸኳይ ይፈታ ዘንድ የኢትዮጵያን መንግስት ያሳሰበችበት ጊዜ በርካታ ነው፡፡ የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማትም የኢትዮጵያ መንግስት “ሽብርተኛ” እያለ ወህኒ የወረወራቸውን ጋዜጠኞች እና ፖለቲከኞች  “ጀግና” እያሉ ሲሸልሟቸው ነው የምናስተውለው፡፡

ከዚህ እውነታ የምንገነዘበው ኢህአዴግ ራሱ በፈለሰፈው እና የተቀረው አለም በማይስማማበት “ሽብርተኝነት” ስም እየነገደ መሆኑን ነው፡፡ አዎ! ሽብርን እና አሸባሪዎችን የማይጠየፍ ጤነኛ  ሰው የለም፡፡ ነገር ግን ኢህአዴግ “አሸባሪ” የሚለውን ቃል የሚተረጉምበት መዝገበ ቃላቱ  ከሌላው አለም የተለየ በመሆኑ ሰርክ እንደተወገዘበት ነው የሚገኘው፡፡

አንድ የማውቃቸው ባለትዳሮች ነበሩ። ምንም እንኳን ዛሬ ተነጣጥለው ለየብቻ መኖር ቢጀምሩም፤ ሚስትየው ባሏ መጠጥ እንዲያቆም ያልተሳለችው ስለት እና ያላንኳኳችው የቤተክርስቲያን በር የለም። ከዚህም ሌላ ጠዋት ከቤት ሊወጣ (ወደ ስራ ሊሄድ ሲል) እግሩን ከመላስ በማይተናነስ መልኩ ማታ ጠጥቶና ሰክሮ እንዳይመጣ ትወተውተዋለች፣ ትለምነዋለች፣ ታስጠነቅቀዋለች።

ውትወታዋም ሆነ ልመናዋ እንዳልሰመረ የምትረዳው ማታ ወደ ቤት ሲመጣ ሰክሮ እየተንገዳገደ  መሆኑን ስትመለከት ነው። ጠዋት ሲወጣ አስጠንቅቃው ማታ ሲገባ የሚሰክረው ለምንና ምን በድላው እንደሆነ ስትጠይቀው `ሰይጣን አሳስቶኝ ነው` ይላታል በመጠጥ የተላወሰው ምላሱ  እየተደናቀፈበት። እሱ እየሰከረ እሷ እየመከረችና እየለመነች ለአንድ አመት ያህል አብረው ቢኖሩም, መፋታታቸው ግን አልቀረም ነበር። አብረው በኖሩባቸው ወቅቶች ጠጥቶ ሲመጣ `ለምን?` ማለቷን አትተውም ነበር። `ሰይጣን አሳስቶኝ ነው` የሚለው ቃል የዘወትር መልሱና ሰበቡ መሆኑን የተገነዘበችው ሚስት `ምን አለበት ለአንድ ቀን እንኳን ሰበብህን ለወጥ ብታደርገው? ሁልጊዜ ሰይጣን አሳስቶኝ ነው እያልክስ ለምን ታሞኘኛለህ?` ብላ በተናገረች ማግስት እቃዋን ይዛ ላትመለስ ተለየችው።

እውነት ነው! አመቱን ሙሉ ወይም ለአመታት በአንድ በማይለወጥና በማይሻር ሰበብ  አድራጎታችንን (ስህተታችንን) እየሸፋፈንን ለመቀጠል የምናደርገው ሙከራ ሰበባችንን  በሚያደምጠው ሰው ላይ የማይሰረይ መሰላቸት ይፈጥራል። ሁልጊዜ በአንድ ሰበብ ለመጓዝ መሞከር ፋራነታችንን እና አራዳ አለመሆናችንን ያሳብቅብናል።

በማይለወጥ ሰበባቸው (ምክንያታቸው) ልንጠቅሳቸው ከምችላቸው አካላት ደግሞ ገዥያችን ኢህአዴግ አንዱ ነው። ኢህአዴግ መንግስት እንደመሆኑ የአገሪቱን ፀጥታና ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት አለበት። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ (አንዳንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በርከት ለሚሉ አንዳንድ ጊዜዎች) ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን፣ ጋዜጠኞችን፣ ሙስሊሙን ወክለው የሚንቀሳቀሱ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን ሲከስስ ወይም ሲያስር እንደ ምክንያት (ሰበብ) የሚያስቀምጣቸው መልሶች  እጅግ ተመሳሳይ እና ማሻሻያ የማይደረግባቸው ናቸው። ጋዜጠኛን ሲያስር ‹‹ህገ-መንስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርአቱን በሀይል (በሽብር) ለመናድ ሲቀሳቀስ…›› የምትል የተለመደችውን ምክንያት ያስቀምጣል። ይህ ምክንያት ጋዜጠኛውን ለመክሰሻ አገልግሎት ብቻ የሚውል አይደለም። ተቃዋሚዎችን ሲያስርም ‹‹ሽብርተኛ›› የምትለውን ቃል ለመክሰሻ ፍጆታው ያውላታል። በአሁን ሰአት በእስር ላይ የሚገኙ የሙስሊሙን ተወካዮች ሲያስር እንደ ምክንያት የተጠቀመው ጋዜጠኞችንና ተቃዋሚዎችን ለመክሰስ የደረደራቸውን ሰበቦቹን ነው።

ከላይ የባለትዳሮቹን የህይወት ተሞክሮ ያነሳሁት ያለ ምክንያት አይደለም። ከኢህአዴግ ምክንያት ድርደራ ጋር ተቀራራቢ (ተመሳሳይ) ባህሪ ስላለው ነው እንጂ። ሚስት ‹‹ሰይጣን አሳስቶኝ ነው›› በሚለው የባሏ ቋሚ ተሰላፊ ሰበብ ትዳሯን እስከመናድ ያደረሰ መሰላቸት  አሳድሮባታል።

የ1997 ዓ.ም የምርጫ ውጤቱ ወደ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ካጋደለና ሁኔታዎች ወደአላስፈላጊ አቅጣጫ ከዞሩ በኋላ በርካታ ተቃወሚዎች እንዲሁም ጋዜጠኞች ወህኒ ወርደዋል። የዛን ጊዜ የታሰሩበት ምክንያት ‹‹ህገ-መንግስቱን እንደ ሾላ በድንጋይ ለማውረድ…›› የሚል ነበር። 1997 ዓ.ም ጥሎን ከነጎደ ዛሬ ወደ ስምንት አመት ሆኖታል። በነዚህ ስምንት አመታቶች ውስጥ ፖለቲካው፣ ኢኮኖሚው፣ ኑሮው፣ የሰው አስተሳሰብ… በውድቀትና በእድገት ምህዋር ውስጥ ወይ ወደ ላይ ወጥቷል፤ አሊያም ወደታች ወርዷል። በአጠቃላይ ሁኔታው ተለውጧል፤ ተለዋውጧል። “ህገ-መንግስቱንና ህገ-መግስታዊ ስርዓቱን በሀይል (በሽብር) ለመናድ ሲንቀሳቀሱ…›› በመንግስታችን ቋንቋ፤ የቁመት፣ የወርድ፣ የመጠን ለውጥ ሳይደረግባት ይኸው እስከዛሬ እንዳለች አለች። ኢህአዴግ ወደፊት እስከሚኖርበት ጊዜ ድረስም አብራው ትኖራለች፤ ሰንደቁና አርማው ናትና አትጠፋም። ጋዜጠኞች፣ ተቃዋሚዎች፣ ‹‹እምቢየው›› መብቴን የሚሉ ዜጎች ከኢትዮጵያ ምድር  ሲጠፉ ብቻ ነው ያቺ የኢህአዴግ ምክንያት ‹‹በክብር›› ወደ ማህደሯ የምትመለሰው። እስከዚያው ድረስ ግን፤ እንደ ርዕዮተ አለም የተያዘችው ምክንያት ሳትከለስ፣ ሳትበረዝም ሆነ ተሐድሶ ሳይደረግባት በዶግማ (Doctrine) መልክ ትቀጥላለች።

የአዲስ ነገር ጋዜጣ አዘጋጆች ‹‹መንግስት በሽብርተኝነት ሊያስረን እንደሆነ ከታማኝ ምንጮቻችን ሰማን›› ብለው አገር ጥለው ከተሰደዱ በኋላ፤ እንዳሉትም በሌሉበት በሽብርተኝነት ተከስሰውና ‹‹ሽብርተኛ›› ተብለው ተፈርዶባቸዋል። ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ፣ ርእዮት አለሙ ተከስሰው የተፈረደባቸው ‹‹ሽብርተኛ›› በምትለዋና ለአዲስ ነገር ጋዜጣ ባልደረቦች በተለጠፈችው ቦሎ ነው። አንድ ጋዜጠኛ ሲታሰር የክሱ ምክንያት ምን እንደሆነ ለማወቅ የግድ የሚመለከተው አካል መግለጫ እስኪሰጥ መጠበቅ አስፈላጊ ላይሆን ይችላል። አሁን አሁን እከሌ የሚባል ጋዜጠኛ ታሰረ የሚል ወሬ ሲሰማ፤ ያው ‹‹በሽብርተኝነት›› እንደሚከሰስ አስቀድሞ ማረጋገጥ እየተለመደ መጥቷል። ይህ እንዲሆን በር የከፈተው መንግስታችን በተለይም ከ1997 ምርጫ በኋላ እየተከተለው የመጣው ተሐድሶ አልባ ምክንያቱ (ሰበቡ) ነው።

ለአዲስ ነገር ጋዜጠኞች ክስ የተጠቀመውን ምክንያት ለእስክንድር ነጋ፣ ለእስክንድር ነጋ  የተጠቀመውን ለርዕዮት አለሙ… ለውብሸት ታዬ… ነገ  ደግሞ አንድ ጋዜጠኛ ሲታሰር፤ ለእሱም ፍጆታ ያውለዋል።

በአንድ ተመሳሳይ ምክንያት የተለያዩ ጋዜጠኞችን ማሰር አይሰለችም? የሰው ልጅ አንዴ፣ ሁለቴና ሶስቴ በሰይጣን “ሊሳሳት” ይችል ይሆናል። ግን እንዴት ዘለአለአም በሰይጣን እየተሳሳተ ይኖራል?  እያንዳንዱ ጋዜጠኛስ እንዴት ‹‹ሽብርተኛ›› ሊሆን ይችላል?

በደርግ ጊዜ ነው አሉ፤ ‹‹አንድ ሰው አይደለም በጤናው ሰክሮ እንኳን የመንግስቱ ኃይለማርያምን አስተዳደር መውቀስም ሆነ መተቸት አይችልም ነበር ይባላል። “ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል” የሚለው አባባል በደርግ ጊዜ አይሰራም ነበር።” ሲሉ አንድ አባት አጫውተውኛል። ደርግ ከተገረሰሰ ከሃያ ሁለት አመታት በኋላ ማለትም ዛሬ፤ ያውም “ዴሞክራሲና ነፃነት ያለገደብ መስፈኑ” በሚነገርበት በዚህ ጊዜ ሳይሰክሩ መንግስትን መተቸት ከባድ እየሆነ መጥቷል። ከባዱን መከራ እጋፈጠዋለሁ ያለ ጋዜጠኛም ‹‹ያቺ ነገር›› ትመዘዝለታለች።

እንግዲህ በደርግና በኢህአዴግ መካከል ያለውን ልዩነት እንመርምር። በደርግ ጊዜ ተሰክሮም ሆነ ሳይሰከር ትችት እሰነዝራለሁ ማለት ከባድ ነበር። በኢህአዴግ ጊዜ ዲሞክራሲው “ያለ ገደብ”  በመንሰራፋቱ፣ በገደብ ሰክረው ያለገደብ የመንግስትን ስህተት መተቸት ይቻላል። ታዲያ  በመጠጥ ስካር እንጂ በኑሮው ንረት፣ በመልካም አስተዳደር ችግር፣ በመኖሪያ ቤት እጥረት ስካር መንግስትን ማማረር፣ ከማማረርም አልፎ ለተቃውሞ መውጣት “ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርአቱን በኃይል ለመናድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ግለሰቦች…” ለሚል የክስ ፋይል አሳልፎ ይሰጣል። መቼም አሜሪካና አውሮፓ የሽብርተኞች ደጋፊና አፍቃሪ ስለሆኑ አይደለም-የኢትዮጵያ መንግስት “አሸባሪ” ያላቸውን እነ እስክንድርን እየሸለሙ ያሉት፡፡ እናም ኢህአዴግ ሆይ! የተበላች ዕቁብ የመሰለችውን ምክንያትህን (አሸባሪነትን) ቀየር ብታደርጋትስ?!…

Ze-Habesha

posted by Tseday Getachew

ኢህአዴግ፣ ምርጫ እና አማራጭ ፓርቲዎች ግርማ ሠይፉ ማሩ

173girmasaifu

ባለፈው ፅሁፌ በሀገራችን ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአንድ እጅ ጣት ቁጥር ከማይሞሉት ውጭ ያሉት እንዲሁም ምርጫ ቦርድ ተገፍተው እንኳን ለመነሳት ባትሪያቸውን የጨረሱ እንደሆነ ለማሳየት ሞክሬ ነበር፡፡ ይህን ሀሳብ የሚያጠናክር ዜና በጋዜጣ ላይ አነበብኩኝ እና ድጋሚ ስለ ኢህአዴግ፣ ምርጫ እና አማራጭ ፓርቲዎች ግንኙነት ለመፃፍ ወሰንኩ፡፡ ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነው የምርጫ ስነ ምግባር ደንብ የፈረሙ አና በፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል የሆኑ ፓርቲዎች ኢህአዴግ (ልብ በሉ መንግሰት አላሉም) ከዚህ በፊት ሲሰጣቸው የነበረውን ብር አንድ ሚሊዮን ድጋፍ ወደ ብር ሁለት ሚሊዮን ሊያሳድገው እንደሆነ ነገር ግን እነርሱ ምርጫ ለመሳተፍ ዝግጅት እንዲረዳቸው ወደ ብር አራት ሚሊዮን እንዲያሳድግላቸው ፍላጎታቸው መሆኑን፤ ይህን ጥያቄም በቀጣይ የጋራ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ እንደሚያነሱት ገለፁ የሚል ዘገባ ማንበቤ ነው፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲች ገዢውን ፓርቲ ገንዘብ ጠየቁ የሚለው ፌዝ መሳይ እውነት ለብዙ ሰው እንዲገባ በእግር ኳስ ምሳሌ ማስረዳት ጥሩ ነው፡፡ አቶ ሀይማሪያም ደሳለኝ የክልል ርዕስ መስተዳደር በነበሩ ጊዜ ለክልል ምክር ቤት አባላት ምርጫን በእግር ኳስ ምሳሌ ሲያስረዱ፤ ከከንባታ ዞን፣ ከአንጋጫ ወረዳ የተወከለ ተቃዋሚ አይደለም በሩጫ ይሁን ብሎ ተሰብሳቢውን አሰቆ እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ እኔ በእግር ኳስ ላስረዳ የእንግሊዝ ጫወታ ለሚወድ ማንችስተር ሲቲ ወይም ማንችስተር ዩናይትድ ተቀናቃኛቸው አርሴናል ዋናጫ መብላት ስለተቸገረ ቡድኑን ለማጠናከርና ለዋንጫ እንዲበቃ ማሊያ እና ጠንከር ያሉ አዳዲስ ተጫዋቾች መግዣ ብለው ገንዘብ እንደመስጠት የሚቆጠር ነው፡፡ ወይም በሀገራችን ጊዮርጊስ ቡናን ለማጠናከር የገንዘብ ድጋፍ እንደማድረግ ነው፡፡ የልምድ ልውውጥ እንዳይመስላችሁ ጊዮርጊስ ብዙ ዋንጫ ስለበላ በአዘኔታ ቡና ዋንጫ እንዲያገኝ ለማገዝ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ስላቅ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ነብስ ዘርቶ ነው ያለው፡፡

ለነገሩ እነዚህ ፓርቲዎች በኢህአዴግ ተቆራጭ እየተደረገላቸው የሚቆሙ በመሆናቸው ለወጉ ነው እንጂ አማራጭ ናቸው ብለን የምናስባቸው አይደሉም፡፡ እነዚህ ፓርቲዎቸ ከኢህደዴግ ሀጋር ድርጅቶች የሚለያቸው የአብዮታዊና ልማታዊ መንግሰት ፍልስፍና ተቀብለናል ብለው በኢህአዴግ ፕሮግራም ነው የምንመራው ያለማለታቸው ነው፡፡ ከዚህ በሰተቀር በሚባል ደረጃ የፓርቲያቸው ፕሮግራም ስለመኖሩ አይታወቅም እና አማራጭ አላቸው ብለን እኛም አናምንም ህዝቡም በዚህ ጉዳይ አይጠረጥራቸውም፡፡ ሁሌም
እንደምለው የእነዚህ ፓርቲዎች መኖር በኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ ለማገዝ ሳይሆን ምዕራባዊያን በኢትዮጵያ ብዙ ፓርቲዎች አሉ ለማስባል ነው፡፡ ይህ ደግሞ ገዢው ፓርቲ ለረዥም ጊዜ ያለተቀናቃኝ በስልጣን ለመቆየት ያስቀመጠውን ዕቅድ ለማሳካት ጭምር የሚጠቀምበት ነው፡፡ አማራጭ እንዲሆኑ የሚጠበቅባቸው ፓርቲዎች በተቃራኒው ቆመው ሀገር አማራጭ ያሳጣሉ፡፡

ይህ ተግባር የሞራልና የመርዕ ጥሰት ብቻ ሳይሆን ህገወጥ ድርጊት ነው፡፡ ኢህአዴግ ለእነዚህ ፓርቲዎች የሚያድለውን ገንዘብ የሚያገኘው ከመንግሰት ካዝና ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ ባለፈው ዓመት ለምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት መሰረት ለፓርቲዎች የሚሰጠው ድጋፍ በክልልና በፌዴራል ምክር ቤቶች ባገኙት መቀመጫ መሰረት በመሆኑ እነዚህ በፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል የሆኑ ፓርቲዎች ደግሞ መቀመጫ ስለሌላቸው ገንዘቡን በሙሉ ጠቅልለው የወሰዱት ኢህአዴግና አጋሮቹ መሆናቸው አስታውቆዋል፡፡ ኢህአዴግ ግን በዚህ መሰረት ያገኘውን ገንዘብ በቸርነቱ ለነዚህ ፓርቲዎች እንዲታደል አድርጎዋል፡፡ ለዚህም ምርጫ ቦርድ ትብብር ማድረጉን በአደባባይ አምኖዋል፡፡

የመጀመሪያው ህገወጥ ተግባር ኢህአዴግ እንዲጠቀምበተ ከመንግሰት ካዝና በምርጫ ቦርድ በኩል የተሰጠውን ገንዘብ ለሌሎች ፓርቲዎች አሳልፉ የሚስጥበት አንድም የህግ አግባብ የለም፡፡ ለምሳሌ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ከመንግሰት የተመደበለትን በጀት ለክልል ጤና ቢሮ ወይም ለትምህርት ሚኒስትር አሳልፎ መስጠት አይችልም፡፡ ካልተጠቀመበት ወደ መንግሰት ካዝና መመለስ ብቻ ነው ያለው አማራጭ፡፡ ይህን ድርጊት ለምርጫ ቦርድ ሃላፊው ፕሮፌሰር መርጊያ በቃና የተነገራቸው ቢሆንም አሁንም ለማረም ዝግጁ የሆኑ አይመስልም፡፡

በሹመት ላይ ሆኖ ህግ የሚተላለፍ ባለስልጣን የሚቀጣበት ሀገር ስለአልሆነ በማንአለብኝነት በህገወጥ ድርጊቱ ቀጥለዋል፡፡ ቀን የጨለመ ዕለት ግን ማጣፊያው እንደሚያጥር ጥርጥር የለኝም፡፡ ይህን ፅሁፍ እያዘጋጀው እያለ ፕሮፌሰር መርጊያ መግለጫ ሲሰጡ ሰማው እንዲህ ብለው “ገለልተኛ አይደላችሁም ይሉናል፤ ለገዢው ፓርቲ ያደላሉ ይሉናል፤ በእውነት ገዢው ፓርቲ የእኛ ድጋፍ ያስፈልገዋል?” እስኪ አንድ ዳኛ ጫወታ ከመጀመሩ በፊት እንዲ ማለት ምን ማለት ነው? ገዢው ፓርቲ ተቃዋሚዎችን እንደሚበልጥ እርግጠኛ ቢሆኑ እንኳን እንዲህ ዓይነት አስተያየት አይሰጥም፡፡ ቢያንስ በአደባባይ፡፡ ለነገሩ ከኢህአዴግ ጋር ተባብሮ የመንግስት ገንዘብ በማከፋፈል ተግባር መሰማራት ድጋፍ ካልሆነ ምን ይሆናል?

ስለዚህ ሌላኛው ህገወጥ ተግባር ምርጫ ቦርድ ከመንግሰት ካዝና ወስዶ ለኢህአዴግ የሰጠውን ገንዘብ በህጉ መሰረት ለታለመለት ዓላማ ብቻ ማዋሉን ማረጋገጥ ሲገባው ይልቁንም በዚህ ጉዳይ ኢህአዴግ ለሚፈልጋቸው ፓርቲዎች የማሰራጨት ተግባርን መስራቱ ቦርዱ ከተሰጠው ኃላፊነት እና ተግባር ውጭ ህገወጥ ድርጊት መፈፀሙን የሚያሳይ ነው፡፡ ኢህአዴግ ለፈፀመው ህገወጥ ተግባራም ቦርዱ ተባባሪ ነው፡፡ ይህ ቦርዱ አድሎዋዊ መሆኑን ያሳያል፡፡ ቦርዱ በግፊም አይነሳም ወይም በግፊ የሚነሳው ኢህአዴግ ሲገፋው ነው ያልኩት ለዚህ ነው፡፡

ሌላ አስቂኙ ነገር ደግሞ ኢህአዴግ ለሰጣቸው ገንዘብ የኦዲት ሪፖርት እንዲያቀርቡ ከተጠየቁት ውስጥ የኦዲት ሪፖርት ማቅረብ የቻሉትሶሰቱ ብቻ ናቸው የሚለው መረጃ ነው፡፡ የሚያስቀው የኦዲት ሪፖርት ያለማቅረባቸው ወይም የኦዲት ሪፖርት ያቀረቡት ትንሽ መሆናቸውአይደለም፡፡ የኢህአዴግ ሪፖርት ጠያቂነት እና እነርሱም ሪፖርት ለማድረግ ፈቃደኛ መሆናቸው ነው፡፡ ለነገሩ እነዚህ ፓርቲዎች መሞታቸው የተረጋገጠው ገንዘብ ከኢህአዴግ ለመቀበል የወሰኑ ዕለት ነው፡፡ የዛን ዕለት አለቃቸው ማን እንደሆነ ተጠሪነታቸውም ለማን እንደሆነ ተረጋግጧል፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች እንዴት ብለው አማራጭ ያቀርባሉ? ሌላው አስገራሚ ነገር የተጠበቀባቸውን አማራጭ ያለማቅረባቸው ብቻ ሳይሆን የኢህአዴግንም ፖሊሲ በቅጡ ሊደግፉ የሚችሉ ያለመሆናቸው ነው፡፡ ከሁለቱም የሌሉ ጉዶች ናቸው፡፡ የእነዚህ ፓርቲዎች ስብስብ አባል ነው እንግዲህ ሰሜን አጣፋችሁ እያለ ክስ መስርቶ ዜጎችን በየጣቢያው እያስጠራ የሚያንገላታው፡፡ ሰም ሲኖር መስሎኝ የሚጠፋው!!

ፓርቲዎች በዋነኝነት የገቢ ምንጫቸው መሆን ያለበት ከአባላት የሚያገኙት መዋጮ ነው፡፡ አባላት ከሌሏቸው ደግሞ ፓርቲ ናቸው ብሎ ከምር መውሰድ አይቻልም፡፡ በዚህ ፅሁፍ ያነሳሁትን ሃሳብ የሰጠሁት ኢህአዴግ ለነዚህ ፓርቲዎች የሚያድለው ገንዘብ ከምርጫ ቦርድ የወሰደውን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን የኢህአዴግ የገንዘብ ምንጭ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በህገወጥ መንገድ ከያዛቸው የንግድ ድርጅቶች በሚስጥር ከሚያገኘው በተጨማሪ የፓርቲውን አቅም ለማሳደግ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የመንግሰትን ሀብትና ንብረት ያለአግባብ ይጠቀማል፡፡ የተወሰኑ ማሳያዎችን ለመግለፅ፤

በቅርቡ ኢህአዴግ ያሰለጠናቸውን ካድሬዎች ለምሳሌ የመንግሰት ተቋም በሆነው የሲቪል ሰርቪስ ዮኒቨርሲቲ ሲያስመርቅ፣ በተከታታይ በዩኒቨርሲቲው ጊቢ ውስጥ ውለው አድርው አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሲሰለጥኑ ማየትና መስማት የተለመደ ነው፡፡ ይህ ገንዘብ ፓርቲው በተዘዋዋሪ ከመንግሰት የሚወስደው መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ኢህአዴግ ከመንግሰት በተዘዋዋሪ የሚወስዳቸው እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡ የፓርቲ አባላት በተደራጁበት መዋቅር አይደለም ወርሃዊ መወጮ የሚከፍሉት፤ በመንግሰት መዋቅር በኩል ነው መዋጮ የሚሰበሰበው፡፡ በቅርብ በማውቀው የተወካዮች ምክር ቤት ከላይ እስከ እታች ያለው መዋቅር በመንግሰት የስራ ሰዓት ሁሉ የፓርቲ ስብሰባ ይደረጋል
እንዲሁም ሌሎች ልዩ ልዩ ተግባራትንም ያከናውናሉ ለነዚህ ተግራራት ሁሉንም አስተዳደራዊ መዋቅር ይጠቀማል፡፡

የኢህአዴግ ቢሮዎች በሙሉ የመንግሰት ናቸው፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ ከመንግሰት ቢሮዎች ጋር ብዙ ሀብት በሚጋሩበት ሁኔታ ነው ቢሮዎቹን የሚከፈቱት፡፡

በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ፅ/ቤቶች በዋና ዋናዎቹ የክልል ፖሊሶች ጥበቃ ሲያደርጉ ብታዩ በፍፁም መገረም አይኖርባችሁም፤ አሁን እርግጠኛ አይደለሁም እንጂ ሬዲዮ ፋና በፌዴራል ፖሊስ ነበር የሚጠበቀው፡፡ ሸገር ኤፍ ኤምን ፌዴራል ፖሊስ የሚጠብቀው አይመስለኝም፡፡

የመንግሰት መኪና ያለምንም እፍረት ለፓርቲ ስራ ሲያውሉ ማየት በፍፁም የሚያሸማቅቅ ሳይሆን፣ በኩራት ልብ የሚያስነፋ ነው፡፡ ለፓርቲ ስብሰባ ከመንግሰት ነዳጅ ሞልተው ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡

ይህን ሁሉ ስታሰቡት ኢህአዴግ ለአነዚህ ፓርቲዎች ያሰበውን ብር ሁለት ሚሊዮን ወይም እነርሱ የፈለጉትን ብር አራት ሚሊዮን ቢሰጣቸው በእጅ አዙር ከመንግሰት የሚቀበለው ነው፡፡ አሉኝ ከሚላቸው ስባት ሚሊዮን አባሎችም ሃምሳ ሳንቲም ቢሰበስብ ሊሰጣቸው ይችላል፡፡ የገንዘቡ ምንጭ ሳይሆን መርዕ ያለመከበሩን ስናስብ ነው ጉዳዮን ጉዳይ ብለን እንድናነሳው የሚያስገድደን፡፡

በነገራችን ላይ እነዚህ ከኢህአዴግ ድርጎ/ደሞዝ የሚቆረጥላቸው ድርጅቶች ከመንግሰት ለፅ/ቤት የሚሆን ቢሮ አላቸው፡፡ አንዳንዶቹ አከራይተው እንደሚጠቀሙበት እና ለግል ጥቅም እንደሚያውሉት እርስ በራስ ሲካሰሱም ሰምተናል፡፡ ለማነኛውም ገንዘብ ሰጪው ኢህአዴግ፣ ገንዘብ ተቀባይ ፓርቲ ተብዬዎችም ሆኑ ምርጫ ቦርድ ይህን በማድረጋቸው ምንም ቅር የሚላቸው አይመስልም፤ ዶክትር በድሉ ዋቅጅራ ባለፈው ሳምንት ባቀረበው መጣጥፍ ላይ በተጠቀመው አባበል ብዘጋው ወደድኩ፡፡ እነዚህ ተዋንያን ተግባራቸው

ለአስደሳች ህልም ካልሆነ በቀር ለአሰፈሪ ቅዠት አይዳርጋቸውም፡፡ ይህ ሲሆን ስታዩ አንድ የጎደላቸው ነገር ያለ አይመስላችሁም፡፡

ቸር ይግጠመን!!!

ኢትዮሚድያ – Ethiomedia.com

April 5, 2014

posted by Tseday Getachew

 

 

ስለፍትሕ ሲባል፤ ሥርዓቱ ይፍረስ! (ተመስገን ደሳለኝ)

teme

 

ባለፉት አራት አስርታት ሀገሪቱ አያሌ ተግዳሮቶችን መጋፈጧ ባይዘነጋም፤ በተለያየ ጊዜ ሚሊዮኖችን ካረገፈው አሰቃቂው ረሃብ በማይተናነስ መልኩ ሕዝቦቿን ዋጋ ያስከፈለ ጉዳይ ቢኖር የፍትሕ አለመከበር ያስከተለው ሁለንተናዊ ምስቅልቅሎሽ ነው ብሎ ለመናገር የሚያስደፍሩ በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡ የየካቲቱን አብዮት ጠልፎ ሥልጣኑን የተቆጣጠረው ወታደራዊው ደርግ፣ የፍርድ ቤት ደጆችን በጓጉንቸር ቆልፎ ሲያበቃ፣ የራሱ አባላት እጃቸውን እያወጡ ድምፅ በመስጠት በአፄው ባለስልጣናትንም ሆነ ግብረ-አበሮቹ በነበሩ መኮንኖች ላይ የሞት ቅጣትን ያህል የመጨረሻ ከባድ ውሳኔ የማሳለፍን አስደንጋጭ ክስተት ጨምሮ፤ ከከተማ እስከ ገጠር ያደራጃቸው የአብዮት ጠባቂዎችና የገበሬ ማሕበራትከየቤቱ አንቀው እያወጡ “ነፃ እርምጃ” እንዲወስዱ፣ ከየእስር ቤቱ እየለቃቀሙ በጅምላ እንዲረሽኑ በአዋጅ የፈቀደበት ጊዜ የፍትሕ ምኩራቡ ፈርሶ በግላጭ የተቀበረበት ዕለት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በርግጥ ይህ የማን-አለብኝነት አረመኔያዊ አገዛዝ የታቃውሞውን ጎራ በማጠናከር ታሪካዊ ውድቀቱ እንዲፋጠን ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ እንደነበር ለመረዳት 17 ዓመታትን መውሰዱ አይዘነጋም፡፡

“ፍትሕ አልባው አምባ-ገነናዊ የደርግ ስርዓት አማርሮ በርሃ ያስወጣንና ብሶት የወለደን የለውጥ ሃዋርያት ነን፤ በመቃብሩም ላይ ፍትሕ-ርትዕ የሰፈነባት ዲሞክራሲያዊት አገር እንመሰርታለ” በማለት ከበሮ ይደስቁ የነበሩት የያኔው “ነፃ አውጪዎች”ም፣ ደርግ አፍርሶ የቀበረውን የፍትሕ ምኩራብ አመዱን አራግፈው ቢያነሱትም፤ ባነበሩት አስመሳይ ሥርዓት በኩል በዘውግ ማንነት፣ በሙስናና በሙያ አልባ ዜጎች በክለው ክብር የለሽ ሲያደርጉት በጣት የሚቆጠሩ ወራት እንኳ አልፈጀባቸውም፡፡ ‹‹አዲስ ንጉስ አንጂ ለውጥ መቼ መጣ!›› እንዲል ከያኒው፤ ካስወገዱት የደርግ መንግስት ጋር ልዩነታቸው-ደርጉ ያልቻለበትን የተቃውሞ ድምፆች በአዋጅ እንዲንቀሳቀሱ በአንድ በኩል ፈቅደው፣ በሌላ በኩል መልሶ ለመጨፍለቅ የፍርድ ቤቶችን ባረኮት የመጠቀም ባለ ሁለት ገፅ ብልጠታቸው ብቻ ነው፡፡

ይህ አይነቱ አገዛዝም ሥልጣን በያዘ ማግስት ሀገሪቱን እንዳሻው ለመርገጥ ሲቪል ቢሮክራሲውን ብቻ ሳይሆን የፍትሕ ስርዓቱንም በአምሳሉ አፍርሶ መስራት ነበረበት፡፡ ይሁንና ተቋሙን በዚህ መልኩ ለማዋቀር ጊዜ እንደሚያስፈልግ በመረዳቱ አሁን ድረስ በቂ መከራከሪያ ሊቀርብላቸው የማይችሉ ጉዳዮችን ከፍትሕ ሥርዓቱ ነጥቆ ሕገ-መንግስቱ ውስጥ በመዶል ለሌሎች ሰጥቷል፡፡ ለዚህ ደግሞ በቂ ማሳያ የሚሆነው፤ ሕገ-መንግስታዊነትን አስመልክቶ የሚነሱ የማጣራት ኃላፊነቶችን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መስጠቱ ነው፡፡
በርግጥ አንዳንድ የወቅቱ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ሕገ-መንግስቱ በተረቀቀበት ሰሞን፣ ከሕገ-መንግስቱ የሚጣረሱ አዋጆች፣ ክሶች አሊያም ኩነቶች ሲፈጠሩ፣ የማጣራቱ ኃላፊነት የፍርድ ቤት መሆን አለበት ሲሉ የተከራከሩ ድምፆች ነበሩ፡፡ ዳሩ ውሎ-አድሮ ምን እንደሚሰሩ አስቀደመው የሚያውቁት ታጋዮች፣ በዛ ካድሬ-ዳኞች ባላፈሩበት ወቅት እንዳሻቸው ሕገ-መንግስቱን እየናዱ ቢያስሩ፣ አዋጅ ቢያወጡና ቢያስፈርዱ ድጋፉን የሚሰጣቸው ተቋም፣ በኢሠፓውያን እንደተሞላ የሚጠረጥሩት ፍርድ ቤት ሳይሆን፣ እንደ ልብ ሊቆጣጠሩት የሚችሉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት መሆኑን በመረዳታቸው፣ በፓርላሜንታዊ ሥርዓት ትመራለች በተባለች ሀገር ብዙም ባልተለመደ አኳኋን ሕገ-መንግስታዊ ትርጉም የሚሻቸውን ጉዳዮች የማጣራት ስራን ለዚሁ ምክር ቤት ሰጡት፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም በጥቂት ዓመታት ውስጥ የፍትሕ ተቋሙን በፓርቲ ፖለቲካ የተተበተበ፣ ለጉልበተኛ የሚገብር፣ ገንዘብ ሊገዛው የሚችል፣ ተቀናቃኝ ድምፆችን የማፈኛ መሳሪያ… አድርጎ የመቅረፅ ዓላማቸውን ማሳካት ችለዋል፡፡ በውጤቱም ተቋሙ የህግ የበላይነት የተደፈጠጠበት አድሎአዊና በየጊዜው ደካሞችን የሚያጠቃ ከሆነ እነሆ ከሁለት አስርት በላይ አስቆጥሯል፡፡

የሆነው ሆኖ የሥርዓቱን ፍትሕ ረጋጭነት በተጨባጭ ፍፃሜዎች አስደግፎ ለማቅረብ ሁለት አብነቶችን እጠቅሳለሁ፡፡ ቀዳሚው የበርካታ ግፉአንን እሪታ ሲወክል፤ ተከታዩ ደግሞ የገዥዎቹን የሙስና እና የጓዳ ፖለቲካ ትስስሮች ይጠቁመናል ብዬ አምናለሁ፡፡

የሞገስ ወልዱ-ጩኸት

ሰማይ ከመፍገጓ በፊት፣ ሁሌ ንጋት ላይ ኮተቤ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ተነስቶ፣ በእግሩ ሰከም ሰከም እያለ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ግድም ልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይደርስና ዋናው በር ፊት ለፊት ቆሞ ከአንድ ሰዓት ላላነሰ ጊዜ ‹‹ሌባ ዳኛ!›› እያለ ይጮኻል፡፡ ያፏጫል፡፡ ‹‹እናንተ ገላችሁኛል፤ ቀብራችሁኛል፤ አምላክ ፍርዱን ይሰጣል!›› በማለትም ተስፋው በሰማያዊው መንግስት ላይ ብቻ እንደሆነ ያውጃል፡፡ …ይህ ሰው እንደምን ያለ ከባድ በደል ቢደርስበት ይሆን ምሬቱ እንዲህ ጣራ የነካው?

አሳዛኙ የሞገስ ታሪክ እንዲህ ይጀምራል፡- በ1997 ዓ.ም የወላጅ እናቱን ወ/ሮ አስካለ ቢፋ ህልፈት ተከትሎ፣ ወንድሙ ኃይሉ ወልደአማኑኤል የወራሽነት ድርሻውን እንዲያካፍለው ክስ መስርቶ ሲያበቃ፤ ሶስት ጥያቄዎችን ለፍርድ ቤቱ ያቀርባል፡- ‹‹ንብረትነቱ የእናታችን የሆነ ቀበሌ 14/15 ውስጥ የሚገኝ 250 ካሬ ሜ. ላይ ያረፈ መኖሪያ ቤት፣ ሁለት ማሳ የእርሻ መሬት እና በንግድ ባንክ አራት ኪሎ ስላሴና መገናኛ ቅርንጫፍ የተቀመጠ መጠኑ ያልታወቀ ገንዘብን ያካፍለኝ፡፡››

የከሳሽ ወንድም የሆነው ኃይሉም ፍርድ ቤት ቀርቦ ‹‹ቤትም ሆነ የእርሻ መሬት የሚባል ነገር የለም፤ በባንክ አለ ስለሚባለው ገንዘብም አላውቅም፤ እናታችን በሞተችበት ወቅት ስሟን ለማስጠራት ስል የእርሷ የነበረውን መሬት በ30 ሺህ ብር ሸጬ፤ ለአርባ፣ ለመንፈቅ፣ ለተስካር 10 ሺህ ብር ያወጣሁ ሲሆን፤ ቀሪውን 20 ሺህ ደግሞ ለወንድሜ ማረፊያ የሚሆን ቤት ሰርቼበታለሁ›› ሲል ምላሽ ይሰጣል፡፡ ችሎቱም ‹ቤቱንና የእርሻ መሬቱን በተመለከተ የቀረበ ማስረጃ አለመኖሩን› ገልፆ ‹የ30 ሺህው ጉዳይ ግን ያለይግባኝ ባይ
ፍቃድ ወጪ የተደረገ ስለሆነ፤ የገንዘቡ ግማሽ 15 ሺህ ብር ድርሻው ስለሆነ እንዲሰጠው› በማለት ወስኖ መዝገቡን ይዘጋል፡፡ በውሳኔው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ

እጅግ በጣም የተበሳጨው ሞገስ፣ ጉዳዩን በይግባኝ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ይወስደዋል፤ ይግባኝ ሰሚውም ‹‹ቤቱ ይገኝበታል›› የተባለው ቀበሌ የእናታቸውን ማህደር እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡ ግና፣ ሀገሪቷ ኢትዮጵያ ናትና፤ ቀበሌው ማህደሩ መጥፋቱን፣ ሟችም በተከሳሽ ቤት ይኖሩ እንደነበረ በደብዳቤ ያሳውቃል፡፡ ሆኖም ቀበሌው ይህንን ምላሽ ከሰጠ ከ14 ቀን በኋላ ‹የቀድሞውን አስተዳደር ጠይቄ ያገኘሁት መረጃ ነው› በማለት ለፍርድ ቤቱ እንዲህ የሚል ሌላ ደብዳቤ ይልካል፡- ‹ወ/ሮ አስካለ የግል መኖሪያ ቤት የነበራቸው ሲሆን፣ ቤቱ ያረፈበት መሬት ለ‹‹ሪል እስቴት›› በመሰጠቱ፤ ምትክ ቦታና ስድስት ሺህ ብር ወስደዋል›፡፡ የሰው ምስክሮችም ቀርበው ሟች እናት ቤት ሰርተው እንደነበረ ያረጋግጣሉ፡፡ ይህም ሆኖ የወ/ሮ አስካለ ማህደር ከቀበሌው ‹‹ጠፍቷል›› በመባሉ ምንም አይነት ማስረጃ ስላልቀረበ የቀድሞው ውሳኔ በይግባኝ ሰሚው ችሎትም ሊለወጥ አልቻለም፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ላለፉት ሁለት ዓመታት ከፍተኛው ፍርድ ቤት በር ላይ ቆሞ መጮኽን ስራዬ ብሎ ይዞታል፡፡ በርግጥ ከቀን ቀን አካላዊ መዳከም እየበረታበት መሄዱ በግልፅ ቢታይም የ40 ዓመቱ ጎልማሳ ሞገስ ወልዱ ዛሬም ከፍርድ ቤት ደጅ ቆሞ መጮኹና ማፏጨቱ የበርካታ ግፉአንን ድምፅ የሚወክል
ይመስለኛል፡፡

ይህ ጉዳይ የሚያሳየው፣ የመንግስት ደመወዝ እየተከፈላቸው በዜጎች ሕይወት ላይ ሊወስን የሚችል እንዲህ አይነቱን ማስረጃ ያለአንዳች ጭንቀት ‹‹ጠፋ›› ብሎ ለመናገር የሚደፍሩ፣ ስለሕዝብ ብሶትና ችግር ምንም ግድ የሌላቸው ካድሬዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውን ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም እንደ ሞገስ ያሉ የፍትሕ እጦት ረመጥ ሆኖ ያንገበገባቸው ምስኪኖች በአደባባይ ሲጮኹ ውለው፤ ሲጮኹ ቢያድሩ ‹‹ምን ይሆን ችግራቸው?›› ብሎ ለማድመጥ የሚሞክር አንድ እንኳን ባለሥልጣን መታጣቱንም ጭምር ነው፡፡ ‹‹ሳይሰሙ ቀርተው ይሆናል!›› ማለቱን ከባድ የሚያደርገው ደግሞ፣ በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አካባቢ የሚተላለፉ መንገደኞችም ሆኑ ወደ ተቋሙ የሚመጡ ባለጉዳዮች ክስተቱን የማወቃቸው እውነታ ነው፡፡ ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ሰዎችን የችሎት ውሎ ለመሰለል ከተከሳሾች ቀድመው የሚደርሱ የደህንነት ሰራተኞችም ሞገስን ለማወቃቸው እኔው ራሴ ምስክር ነኝ፡፡ በአናቱም ከዚህ ቀደም በሸገር ራዲዮ ‹‹ኧረ በሕግ›› የሚል ፕሮግራም ያዘጋጅ የነበረውና በአሁኑ ወቅት በ97.1 ኤፍ.ኤም ‹‹የእኔ መንገድ›› የተሰኘ በተመሳሳይ ጭብጥ ዙሪያ የሚያተኩር ፕሮግራም የሚያዘጋጀው በሳሉ የሕግ ባለሙያ ሰለሞን ጓንጉል፣ ይህንን ታሪክ ከአንዴም ሁለቴ ለአድማጭ አድርሶታል፡፡ እንግዲህ እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ነው ከቀበሌ አንስቶ ላይ ድረስ ያሉ መንግስታዊ መዋቅሮችን የዘረጋውና የሚቆጣጠረው የኢህአዴግ አመራር አባላት፣ የሞገስን ጩኸት ‹‹አልሰሙም›› ማለቱን ከባድ ያደረገው (በነገራችን ላይ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ግቢ ለአስር አመት ያህል በየቀኑ እየተመላለሱ የሚቆሙ አንዲት አዛውንት እና በፍትሕ ሚኒስቴር በር ላይ ቆማ መዋል ከጀመረች ስድስት ዓመት ያለፋት ራሄል የተባለች አቤት ባይ እንስት… መኖራቸውን አልዘነጋሁም)

ሙስና እና የጓዳ ፖለቲካ ትስስሮሽ

አገሪቷ በዚህ ሁሉ መፍትሔ እጦትና በፍትሕ መዛባት እየተመሰቃቀለችና በሕዝቦቿም ዋይታ እየተናወፀች ቢሆንም፤ መጽሐፉ ‹‹ዓይን አላቸው አያዩም፤ ጆሮ አላቸው አይሰሙም›› እንዲል፤ ገዥዎቻችን ይህን መሰሉን የድሆችና የአቅመ ደካሞች ብሶት መስማትን ፍፁም አይሹም፡፡ እነርሱ የታጋሉትም ሆነ የሚሰሙት አለቆቻቸውንና ባለፀጋዎችን ብቻ እንደሆነ ከሚያሳዩን በርካታ ማስረጃዎች መሃል ለአብነት አንድ ምሳሌ ላቅርብ፡-

ጉዳዩ በሙስና ተጠርጥሮ በእስር ላይ ከሚገኘው የቀድሞ ገቢዎችና ጉምሩክ ዳይሬክተር መላኩ ፈንቴ ጋር ይያያዛል፡፡ ከዚህ ሰው ሃያ አንድ ገፅ ከፈጀ የእምነት ክህደት ቃል ውስጥ ኮነ ምህረቱ የተባለ ግለሰብ በአራጣ ማበደር ተጠርጥሮ ከተያዘ በኋላ ‹‹እነአየለ ደበላ ለዳኛ ጉቦ ሰጥተው በዋስ ከእስር ተፈትተው፣ ከሀገር ለመውጣት ያስባሉ›› የሚል ‹‹መረጃ›› በመስጠት መተባበሩን ገብረዋህድ ወ/ጊዮርጊስ እንደነገረው ገልፆ፣ ከእስር እንዲለቀቅ መደረጉን እናገኛለን፡፡ መቼም በሙስና ወንጀል ከተጠያቂነት የሚድን ተከሳሽ
የሚሰጠው መረጃ ተጠርጣሪዎችን በሕግ ለመጠየቅ የሚጠቅም ሲሆን እንጂ፤ እንዲህ ባለ ከዋናው ክስ ጋር በማይዛመድ ተራና የአሉ-ባልታ ወሬ አለመሆኑን እነገብረዋህድና እነመላኩ ቀርቶ ማንኛውም መንገደኛ እንኳ ሊጠፋው አይችልም፡፡ አውቆ የተኛ… እንደሚባለው ካልሆነ በቀር፡፡

የሆነው ሆኖ ከመላኩ ፈንቴ የእምነት-ክህደት ቃል ትኩረት የሚስበው፣ ግለሰቡ በዚህ መልኩ ከሱ ተነስቶለት ከእስር ከተፈታ በኋላ ንብረቱና የባንክ ሒሳቡ መታገዱን አስመልክቶ የተፈጠረው ኩነት ነው፡፡ አቶ መላኩ ጉዳዩን ለመርማሪዎቹ ሲያብራራ ቃል-በቃል እንዲህ ነበር ያለው፡-

‹‹አቶ አባይ ፀሀዬ እና አቶ ደመቀ መኮንን ደውለው ‹ግለሰቡ አቤቱታ እያቀረበ ነው፡፡ ለምን አታዳምጡትም? ሲሉኝ፤ እኔም ከዚህ በኋላ
ነው ግለሰቡን እቢሮዬ አግኝቼ ከላይ በገለፅኩት ሁኔታ እንዲስተናገድ ያደረኩት፡፡››

እነዚህ ሰዎች ‹‹ነፃ አወጣነው›› የሚሉትን ሕዝብ ለስቃይ ዳርገው፣ ጥቂት ባለፀጎችን ብቻ ለማገልገል የቆሙ መሆናቸውን ለማስረገጥ ከዚሁ የእምነት-ክህደት ቃል አንድ ማሳያ ልጨምር፡- ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ የተባለ የአዲስ ልብ ህክምና ክሊኒክ ባለቤት ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው የሕክምና መሳሪያዎች (የልብ ፒስ ሜከር ተብሎ ተጠቅሷል) በሕገ-ወጥ መንገድ ሲያስገባ በቦሌ ኤርፖርት ጉምሩክ ሠራተኞች እጅ ከፍንጅ ከተያዘ በኋላ መለቀቁን በተመለከተ የህወሓት ከፍተኛ አመራር አባል የሆነው ዶ/ር ቴዎድሮስ አድህኖም ስልክ ደውሎ ‹‹ክሱን ብታነሱላቸውና በአስተዳደራዊ መፍትሔ ብትሰጧቸው›› ብሎ ከመንገሩም በላይ የግለሰቡ ክስ እንዲቋረጥ የሚጠይቅ ደብዳቤ እንደፃፈላቸው መላኩ ፈንቴ ለመርማሪዎቹ መናገሩ በመዝገቡ ላይ ተጽፎ ይገኛል፡፡ ይህንን ሁናቴም ከወቅቱ የፖለቲካ አሰላለፍ አኳያ ስንተነትነው አቶ መላኩ ‹ዶ/ር ቴዎድሮስን መስማት፤ ህወሓትን እንደመታዘዝ ነው› የሚል እምነት አድሮበት የተባለውን ፈፀመ ብለን ብንደመድም ተምኔታውያን አያሰኘንም፡፡


እነዚህ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ያውም ሀገር በሚጎዳ ወንጀል የተከሰሰ ተጠርጣሪን በተመለከተ ከሥልጣን ገደባቸው አልፈው ‹‹አድምጥ!›› እያሉ የማዘዛቸው ምስጢር ሥርዓቱ ለፍትሕ ያለውን ግድየለሽነት እና በዚህ ሥርዓት የሕግ የበላይነት ብሎ ነገር እንጦሮጦስ መውረዱን ፍንትው አድርጎ ያሳያል ብዬ አምናለሁ፡፡ በርግጥ ይህንን ጉዳይ ለጥጠን ከተመለከትነው ‹‹…ለምን አታዳምጡትም?›› የምትለዋን ቃል ሰምና ወርቅ የለበሰች ቅኔ አድርገንበመውሰድ ልንፈታት እንችላለን፤ በተለይም መላኩ ፈንቴ ከዚህች ጥያቄ መሰል ትዕዛዝ በኋላ ግለሰቡን ቢሮ ጠርቶ ማስተናገዱን ስናስተውል፡፡ ምንም እንኳን አባይ ፀሀዬ በጊዜው በጉዳዩ ላይ መላኩን ሊያዝበት የሚያስችል መንግስታዊ ሥልጣን /የዕዝ ተዋረድ/ ባይኖረውም፤ አንጋፋ የህወሓት አመራር አባልና የበለጠ የፖለቲካ ጉልበት ያለው መሆኑ፤ ደመቀ መኮንን ደግሞ በብአዴን በኩል የአለቃነቱ ነገር ሲታሰብ፣ አሁንም መላኩ ፈንቴ የተጠየቀውን ‹‹ጥያቄ›› ከማስተናገድ ውጪ ሌላ አማራጭ አይኖረውም ወደሚል ጠርዝ ይገፋናል፡፡ በርግጥ እውነታው ይህ ቢሆንም፣ መላኩ ዛሬም እስር ቤት ውስጥ ሆኖ የቀድሞ አለቆቹንም ሆነ ራሱን ተጠያቂ ለማድረግ አልደፈረም፡፡ በግልባጩ ለቀረቡበት ክሶች በሙሉ ተጠያቂው ገብረዋህድ እንደሆነ ከመናገሩም በላይ እንዲህ በማለት ወንጅሎታል፡-

‹‹የአያት ባለቤት በግብር ማጭበርበር ተከሶ በነበረበት ወቅት የተከሳሹ ቤተሰብ የሆነ ሰው እቢሮዬ መጥቶ ‹ገብረዋህድ ምንም ጥፋት ሳያጠፋ ነው የአያት አክሲዮን ማሕበር ባለቤትን ያሳሰረው፤ አሁንም አንድ ሚሊዮን ብር ካመጣችሁ ከእስር ይፈታል ብሎናል› የሚል ጥቆማ አመጣልኝ፡፡ …ገብረዋህድ እና ነጋ ገ/እግዚአብሔር (የነፃ ትሬዲንግ ባለቤት ነው) ጓደኛሞች ናቸው፡፡ ነጋ ዕቃ ሲያስመጣ አያስፈትሽም፤ የነጋም ጓደኞች እነ አልሳም፣ ጌት አስ የመሳሰሉት ድርጅቶች ዕቃ በቀላል ቀረጥና ታክስ እንዲሁም አልፎ አልፎ ሳይፈተሹ ያልፋሉ፤ …ባለቤቱ ሃይማኖትም፣ በነጋ ድርጅት ውስጥ ትሰራለች…››

መላኩ ፈንቴ ይህንን ጉዳይ ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ መናገሩንና ጠቅላይ ሚኒስትሩም፣ ፀጋዬ በርሄን ‹‹ተከታተል›› ብሎት እንደነበረ ከአስረዳ በኋላ እንደሚከተለው ይቀጥላል፡-

‹‹ገብረዋህድ በኋላ እንደነገረኝ ባለቤቱን ከነጋ ድርጅት አስወጥቶ በአዜብ ትዕዛዝ መሰረት ኤፈርት ውስጥ ያስቀጠራት መሆኑን ገልፆልኝ ‹አንተም ላይ የሚወራው ስለምትታገል ነው ብላኛለች አዜብ› ሲለኝ እኔም ተከታትዬ ፀጋዬ በርሄ ከምን እንዳደረሱት አልጠየኩም፡፡ መጠየቅ ነበረብኝ፤ ጥፋት ነው፡፡ በአጠቃላይ ገብረዋህድ ላይ ብዙ ነገር ይባል ነበር፡፡››

መቼም ይህ ምላሽ በ1981 ዓ.ም ከአስመራ ዩንቨርስቲ በኢኮኖሚክስ ዲግሪውን፣ ከአውስትራሊያ በገቢ አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪውን፤ ከለንደንም በቢዝነስ አስተዳደር በተመሳሳይ መልኩ ትምህርቱን ካጠናቀቀና የረዥም ዓመታት የስራና የፖለቲካ ተሞክሮ ካለው ሰው የተሰጠ መሆኑን ስናስተውል፤ ሀገሪቱ የአምባገነን ባለሥልጣናት መቀለጃ ብቻ ሳትሆን፤ የሰዎቹንም የአቅም ማነስ ያመላክታል፡፡ እንዲሁም እነሞገስ ሰሚ ያላገኙበትን ምክንያትም ሆነ በዚህች ሀገር ገንዘብ ያለው የፈቀደውን መፈፀም የመቻሉን ምስጢር ይገለፅልናል፡፡

ኢህአዴጋዊ ዕድሜ ማራዘሚያ…

ገዥው ስብስብ የፍትሕ ስርዓቱን ተቋማዊነት ሳይነካ፣ ለጨቋኝነቱ መጠቀሚያ የሚያደርግበት አንዱ መንገድ ከጠቅላይ እስከ ታች በተዋረድ የሚገኙ ፍርድ ቤቶች ድረስ ያሉ ዳኞችን የሚመድብበት አካሄድ ነው፡፡ በርግጥ እንዲህ አይነቱ ሀገርና ሕዝብ አልያም ሞራላዊ ልዕልና እና የሕግ-የበላይነት የማያስጨንቀው አገዛዝ፣ የፍትሕ ስርዓቱ ቅጥ የለሽ ተባባሪነት ሳይታከልበት የሥልጣን ዕድሜውን ማራዘም እንደማይችል መረዳት አይሳነውም፡፡ ይህን ለማድረግም ያለው ብቸኛ ምርጫ ዳኞቹን ከስሩ መሰብሰብ ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢህአዴግ መሩ-መንግስት ሁለት አካሄዶችን ለመተግበሩ ያሳለፋቸው ሁለት አስርታት በሚገባ ያሳያሉ፡፡

የመጀመሪያው የሚሾሙት ዳኞች፣ የግንባሩ ከፍተኛ የካድሬ ማሰልጠኛ እንደሆነ ከሚነገርለት ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ተማሪዎች መካከል ማድረጉ ነው፡፡ ከዚህ ‹‹የትምህርት›› ተቋም ውስጥ የሚወጡ የሕግ ምሩቃን ደግሞ ስለጥልቅ ዘመናዊ የሕግ ፅንሰ-ሃሳብ ለማወቅ ከመትጋት ይልቅ፤ የኢህአዴግ ፖሊሲዎች እና አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሕግን እንዴት ‹‹ለመደብ ጠላት›› መጠቀም እንደሚያስችሉ በሚሰብኩ መምህራን ስር እንዲያልፉ ይገደዳሉ (ስለመምህሮቹ ምሁራዊ ልሽቀት ለመረዳት የሕዝብ ሙስሊሙን ጥያቄ በሽብር ተግባር ለመፈረጅ እና ማሕበረ ቅዱሳንን በአክራሪነት ለመወንጀል በ‹‹ጥናታዊ ጽሑፍ›› ስም የተጓዙበትን ርቀት ማየቱ ብቻ በቂ ይመስለኛል)፡፡ ተማሪዎቹም በዚህን መሰሉ የካድሬ ተቋም ስልጠና ስር ሰንብተው ሲወጡ፤ በፍፅምና ሊታመኑላቸው ይገቡ የነበሩትን ፍትሓዊ ዳኝነትና ህሊና የሚባሉ ጉዳዮችን ጨፍልቀው፣ በተለይም ፖለቲካዊ ነክ በሆኑ አይረቤ ክሶች ፊታቸው በሚቆሙ ንፁሀን ዜጎች ላይ መከራን የሚያዘንቡ አሽከሮች ይሆናሉ፡፡ ይህንን አስነዋሪነት ካለመታከት የሚፈፅሙትም፣ ሥልጣንን እና ተያያዥ ጥቅማ-
ጥቅሞችን እያጋበሱ ወደ ከፍታ ሲወጡ ተመልክተናል፡፡

ሁለተኛው የግንባሩ አካሄድ ከካድሬ ማሰልጠኛውም ሆነ የተሻለ ነው ከሚባለው የአ.አ.ዩ. የሕግ ፋካሊቲ የሚመረቁትን፣ በተከታታይ ርዕዮተ-ዓለማዊ ጠመቃ የሥርዓቱ ጋሻ-ጃግሬ ማድረግ ላይ ያተኮረው ነው፡፡ በሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ሲያገለግሉ ቆይተው ስደትን የመረጡ ዳኞችና ዐቃቢ-ህግያት በተለያየ ጊዜ እንደ መሰከሩትም አሰልቺ የርዕዮተ-ዓለም ጠመቃ የፍትሕ ሥርዓቱን ነፃነት ጽልመት ካላበሱት ሂደቶች በዋነኛነት ተጠቃሽ ነው፡፡ በአንድ ወቅትም ሟቹ አቶ መለስ ዜናዊ የሀገሪቱን ዳኞች ሰብስቦ ስለሕገ-መንግስት እና ሕገ አተረጓጎም መርህ ሲያስተምር ለማየት የተገደድነው የዚሁ የጠመቃው አንድ አካል በመሆኑ ይመስለኛል፡፡ ዳሩስ፣ ይህማ ባይሆን ኖሮ እስክንድር ነጋ ላይ 18 ዓመት መፍረድ ሕሊና እንዴት ይፈቅድ ነበር? ኦልባና ሌሊሳንስ ለ11 ዓመታት ወህኒ ያስወረወረው ጥፋት ምን ተብሎ በአሳማኝ መልኩ ሊጠቀስ ይችል ይሆን?

… ቀሪው ለሳምንት ይቆየን!

 

 

posted by Tseday Getachew

 

Post Navigation

%d bloggers like this: