Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄ “የረዳት አብራሪው አኩሪ ገድል የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃ እስኪወጣ ይቀጥላል” አለ

 

“የወጣት ሃይለመድህን አበራ አኩሪ ገድል የኢትዮጵያ ህዝብ ነፃነትእውን እስኪሆን ድረስ ይቀጥላል” ሲል የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ። ንቅናቄው ለዘ-ሐበሻ በላከው መግለጫው ረዳት አብራሪ ሃይለመድህን አበራ ለአለም ህብረተሰብ ያስተጋባው መልዕክት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ድምፅን ነውና፤ አላማና ተግባሩም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ምኞትና ፍላጎት መሆኑን በፅኑ ያምናል” ብሏል። በተጫምሪም አኩሪ ተግባር ፈጽሟል ላለው ለረዳት አብራሪው የንቅናቄው የክብር አባል እንዲሆን የምስክር ወረቀት ሰጥቷል፡፡ ሙሉ መግለጫው ከምስክር ወረቀቱ በታች እንደወረደ እንደሚከተለው ተስተናግዷል።

 

“የወያኔ/ኢህአዴግ ጨቋኝ ሥርዓት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ቁጥር ስፍር የሌላቸው አፋኝ ህጎችን በመጫን፤ እንዳሻው ንጹሃን ዜጎችን መጥፎ ስም በመስጠት፤ ባልሰሩት ሃጥያትና በተፈበረከ የሃሰት ወያኔያዊ ውንጀላ በየእስር ቤቱ እንዲማቅቁ እያደረገ መሆኑ ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ ግልጽ ነው። ይህ አፋኝ ሥርዓት የምንወዳት ሃገራችን ኢትዮጵያንና ህዝቧን የማጥፋት እኩይ አላማ ሰንቆ፤ ምሁራን ዜጎች ለሚወዷት ሃገራቸውና ለሚሳሱለት ህዝባቸው የበኩላቸውን ማበርከት እንዳይችሉ፤ በተለይ ወጣት ምሁራን በሃገራቸው ጉዳይ ላይ ቀጥተኛ ተሳተፊ እንዳይሆኑ ከፍተኛ ግድያ፣ እንግልት፣ ጭቆና፣ በደልና፣ ወከባ እያደረገ ይገኛል።

ይህ ፋሽስት ሥርዓት በዘረጋው አፋኝ መዋቅር ህዝብ እርስ በርሱ በጥርጣሬ እንዲኖር፤ ቤተሰብ ከቤተሰብ እንዳይተማመን፤ አንዱ ብሄር በሌላው ብሄር ላይ ጥላቻ እንዲኖረውና፤ አንዱ ሃይማኖት ከሌላው ሃይማኖት ጋር በፍቅር፣ በመተሳሰብና፣ በመቻቻል እንዳይኖር፤ ባጠቃላይ በሃገሪቷ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር፤ ብሎም ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ከምድረገጽ ፈፅሞ ለማጥፋት፤ ያልፈነቀለው ድንጋይ ባይኖርም፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ያስተሳሰረው የፍቅርና አብሮ የመኖር አኩሪ ባህሉ ነውና፤ የወያኔ/ኢህአዴግ እልቆ መሳፍርት መሰሪ ተንኮልና ደባ ሳያንበረክከው፤ ሥርዓቱ በወጠነው መንገድ ሳይሆን በፍቅር፣ በመተሳሰብና፣ በመቻቻል አንድነቱን ጠብቆ አሁን ድረስ መዝለቅ ችሏል።

የታፈነ ጭስ መውጫ አያጣም ነውና፤ ታጋሽና ሰላም ወዳድ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ጭቆናውና በደሉ ከልክ በላይ ስለሆነበት፤ እየደረሰበት የሚገኘውን ቅጥ ያጣ ግፍ በተለያዩ አያሌ መንገዶች ሲገልጽ ቆይቷል። በየካቲት 10, 2006 የኢትዮጵያ አየር መንገድ አብራሪ በሆነው ወጣት ሃይለመድህን አበራ የተፈጸመው አኩሪ ተግባር ይህንኑ የስርዓቱን አስከፊ ገጽታና በህዝብ ላይ የሚደርሰዉን ግፍ፣ ወከባ፣ እንግልት፣ እስራት፣ ግድያና፣ ሰቆቃ የሚያረጋግጥ አይነተኛ ክስተት ነው። ወጣት ሃይለመድህን አበራ በሥርዓቱ እየደረሰበት የነበረዉን አስከፊ በደል ለማምለጥ በግሉ በርካታ መንገዶች ነበሩት። የአውሮፕላን አብራሪ በመሆኑ አለም ላይ ካሉ ሃገራት ሁሉ በሚፈልግበት የመሄድና የመኖር እድሉ በእጁ ነበር። በኢኮኖሚም ቢሆን በሃገሪቱ ከፍተኛ ክፍያ ከሚያገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች አንዱ በመሆኑ በግል ኑሮው ተንደላቆ የመኖር ችሎታው እንደነበረው ለማንም አጠራጣሪ አይሆንም።

ነገር ግን ወጣት ሃይለመድህን አበራ የኢትዮጵያ ህዝብ ቁስል ስላመመው፤ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የሚደርሰው ግፍና በደል የሱም እንደሆነ ቀድሞ ስለተረዳ፤ ህልሙ የኢትዮጵያ ህዝብ ነፃነት እውን ሆኖ፤ መብቱ ተከብሮለት፤ በሃገሩ የመኖር ተስፋን አንግቦ፤ በፍቅር፣ በሰላምና፣ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ሲኖር ማየት በመሆኑ፤ በዙሪያው የጨበጠው እድል ሳያጓጓውና ወጣትነት ሳያታልለው፤ በማስተዋል ለኢትዮጵያ ህዝብ ነፃነት እጅግ ከፍተኛ መሥዕዋትነትንና ጀግንነትን በተግባር ፈጽሟል።

የወጣት ሃይለመድህን አበራ ታላቅ ተግባር የወያኔ/ኢህአዴግ ከልክ ያለፈ ግፍንና የኢትዮጵያ ህዝብን የታፈነ ሰቆቃ ለአለም ህዝብ በይፋ ከማጋለጡም ባለፈ፤ በኢትዮጲያችን እጅግ ብዙ እሱን መሰል ጀግና ወጣቶች ያለጥርጥር እንደሚገኙና፤ በኢትዮጵያ ነፃነት፣ ፍትህና፣ እኩልነት በአስተማማኝ ሁኔታ እውን እስኪሆን ድረስ፤ ህዝብ ለነፃነቱ ምንግዜም እንደማይተኛ ያረጋገጠ ብሄራዊ የጀግንነት ተግባር ነው። በመሆኑም ወጣት ሃይለመድህን አበራ ለኢትዮጵያ ህዝብ ነፃነት የፈፀመው አኩሪ ተግባርና የከፈለው ታላቅ መሥዕዋትነት በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ለዘላለም ሲታወስ እንደሚኖር ጥርጥር የለንም። ነገር ግን በዚህ ውድ ኢትዮጵያዊ ጀግና የተከፈለው ታላቅ መሥዕዋትነት በኢትዮጵያ ሰላም፣ ፍትህ፣ እኩልነትና፣ ተስፋ እንዲመጣ በቁርጠኝነት የታቀደ በመሆኑ፤ ውጥኑ ለታለመለት አላማ ግቡን እንዲመታ፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ እድሜ፣ ሃይማኖት፣ ብሄር፣ ወይንም ሌላ ማንኛውም ልዩነቱ ሳይገድበው፤ ለጋራ ነፃነቱ በጋራ በመነሳት አንድነቱን ለአለም ማሳየትና የዚህን ቆራጥ ኢትዮጵያዊ ጀግንነት ማስተጋባት ይኖርበታል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሄራዊ ንቅናቄ ወጣት ሃይለመድህን አበራ ለአለም ህብረተሰብ ያስተጋባው መልዕክት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ድምፅን ነውና፤ አላማና ተግባሩም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ምኞትና ፍላጎት መሆኑን በፅኑ ያምናል። ስለሆነም ንቅናቄያችን በአለም ዙሪያ የሚገኙ አባላቶቹን ሙሉ በሙሉ በማስተባበር፤ የወጣት ሃይለመድህን አበራን ድምፅ መልሶ በማስተጋባት፤ አንድነቱን ለአለማቀፉ ህብረተሰብና ለአለም መንግስታት፣ እንዲሁም ለሚመለከታቸው አለማቀፋዊ ተቋማት በሙሉ በማስመስከር፤ እውነታዉን ለማሳወቅ የተለያዩ ሰላማዊ ሰልፎችን፣ ዲፕሎማሲያዊ ሂደቶችንና፣ ሌሎች ተዛማጅ ተግባራትን በማከናወን፤ ግንባር ቀደም ሚና እንደሚጫወት ከወዲሁ እያስታወቀ፤ ወጣት ሃይለመድህን አበራ ለኢትዮጵያውያን የነፃነት ትግል ላበረከተው ታላቅ አስተዋዕፅዎ ብሄራዊ ጀግና ሲል መሰየሙን ለኢትዮጵያ ህዝብ በታላቅ ኩራት እያበሰረ፤ የብሄራዊ ጀግና የክብር የምስክር ወረቀት በአድናቆት ያበረክታል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄ በዚህ ዘረኛ የወያኔ/ኢህአዴግ መንግስት ከልክ ያለፈ ጭቆና፣ ረገጣና፣ እንግልት ሠለባ ሆኖ በመሰቃየት ላይ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ህዝብ ተቆርቋሪ ለሆናችሁና በምንወዳት ሃገራችን ሰላም፣ ነፃነት፣ ፍትህ፣ ተስፋ እንዲሰፍንና ለህዝብ የሚበጅ ቀና ለውጥ ለዘለቄታው ይሰፍን ዘንድ ለምትመኙ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ፤ እንዲሁም ለተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ለሃይማኖት ተቋማትና፣ ለሲቪክ ማህበራት ታላቅ ሃገራዊ ሃላፊነትና የህዝብ አደራ በጫንቃችሁ እንደተሸከማችሁ በመገንዘብ፤ ልዩነታችሁን ወደ ጎን በመተው ለዚህ ወሳኝ ህዝባዊ ጥሪ በአንድነት ምላሽ በመስጠት የሚጠበቅባችሁን ህዝባዊ አደራ እንድትወጡ ዘንድ በጥብቅ እያሳሰበ፤ ሃገራዊ የመተባበር ጥሪውን በአክብሮት ያቀርባል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ንቅናቄ

Ze-Habesha 

 
posted by Tseday Getachew
Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: