Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

ሀገርን ቆርሶ በመስጥት በስልጣን መቆየት አይቻልም

ብሌን ንጉሴ (ከጀርመን)

አንባገነኑ የኢትዮጵያ  መንግስት የሀገሪቱ እና የህዝቦችን ጥቅም ያላአንዳች ይሉኝታ ለባእዳን አሳልፎ ሲሰጥ እነሆ 22 አመታት ተቆጥረዋል፡፡ መቼም እያንዳንዱን የወያኔ ጉድ መዘርዘር አንባቢን ማሰልቸት ቢሆንም ከሰሞኑ ደግሞ የአቶ መለስን ራዕይ ከማስፈጸም ውጭ የራሱ የሆነ አመክንዮ የሌለው ጠ/ር ሀይለማሪያም ደሳለኝ በአያት ቅድመ አያቶቻችን አጥንት ተከብሮ የቆየውን የሀገራችን ለም መሬት ለሱዳን አሳልፎ ለመስጠት ሙሉ ፈቃደኝነቱን አሳይቶ ተፈራርሞ ተመልሷል፡፡ወያኔ የኢትዮጵያን ህዝብ በምንም ጉዳይ ላይ አማክሮት አያውቅም፡፡ሀገሪቱን ለማስተዳደር መጀመሪያም ውክልና ስላልተሰጣቸው ምንም ጎጅ ውሳኔ በሀገር ላይ ሲያስተላልፉ ህዝቡ ምን ይለናል ብሎ የሚያስብ ህሌና የላቸውም፡፡ባለፉት 2 ወራት በመቶ ሺ በላይ ኢትዮጵያውን በአሰቃቂ ሁኔታ ከሳውዲ አረቢያ ሲባረሩ በቦታው በመገኘት ወገናቸውን ለመርዳት ያልሞከሩ ባናዳዎች ዛሬ ሱዳን ድረስ በመሄድ ዳር ድንበራችን ለሱዳን ለመስጠት ሽር  ጉዱን ተያይዘውታል፡፡ወያኔ ተደብቆ የሚቀር እየመሰለው ሀገራዊ ክህደት ሲፈጽም  ከህዝቡ የሚመጣውን ተቃውሞ ለማርገብ ምንም የማይቆፍረው ድንጋይ የለውም፡፡Ethiopian government to hand over land to Sudan

የአሰብን ወደብ ለኤርትራ አሳልፎ በሰጠበት ወቅት የክህደት አባት የሆነው ሟቹ አቶ መለስ ዜናዊ ለአንድ ሀገር እድገት ወደብ ምንም ሚና አይጫወትም ፡፡በገንዘባችን አማርጠን  ወደብ መከራየት እንችላለን በማለት አያናችሁን ጨፍኑ ላሞኛችሁ አይነቱን የደንቆሮ ፕሮፖጋንዳ እንዳላዘኑ ህይወታቸው ቢያልፍም ዛሬም ድረስ አሰብ ከኢትዮጵያውያን ህሌና ሳይፋቅ አብሮን ተቀምጡዋል፡፡  ጦርነት ላለመግባት አሰብን አሳልፎ የሰጠው ወያኔ ውሎ አድሮ ሸአቢያ  ባድመ ላይ ወረራ ሲፈጽም የማይቀረውን ጦርነት ተገባ፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ከአራቱም ማዕዘን ትንቀሳቅሰው መተኪያ  የሌለው ህይወታቸውን ከፍለው ባድሜን በቁጥጥር ስል ቢያውሉም የህዝቡን ይሁንታ ሳያገኝ በደም የተገዛውን መሬት በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለው በሄግ  አለም ፍርድ ቤት ለትግል አጋራቸው  አስረክበው ተመለሱ፡፡ ድንበሩን ማስረከባቸው ሳያንስ ደሙን አፍሶ አጥንቱን ከስክሶ  ድል የተቀዳጀውን ወታደር ፤ ጡዋሪ ቀባሪ ልጆቻቸውን በሞት የተነጠቁ ወላጆችን እና ባሉዋን በሞት ተነጥቃ በሀዘን የተጎሳቆለች የሙዋች ወታደር ባለቤትን ሰብስቦ ባድሜ ለኢትዮጵያ ተፈረደልን ወጥታችሁ በሰላማዊ ሰልፍ  ደስታችሁን ግለጹ በማለት የሀሰት ከበሮ እያስደለቀ ህዝቡን አታለዋል፡፡ዛሬም በሱዳን ድንበር ዙሪያ እውነታውን በመደበቅ  እያታለሉት ይገኛሉ፡፡

ወያኔ መድሀኒታችን እየሱስ ክርስቶስን በ30 ብር አሳልፎ የሸጠውን ይሁዳን እና ለምስር ንፍሮ ብሎ ብኩርናውን የሸጠውን ኢሳውን ይመስል፡፡ ይሁዳ ፈጣሪውን ለገንዘብ አሳልፎ ቢሰጥም በገንዘቡ እንኩዋን ሳይጠቀምበት ህይወቱ እንዳለፈው ሁሉ ወያኔም ምንም ያክል በስልጣን ለመቆየት ሀገርን እየቆረጠ ቢሰጥም በክህደት የሚገኝ ስልጣን እንደይሁዳ ሞትን ይዞላቸው እየመጣ ነው፡፡ ይሁዳ በደም የገዛውን መሬት አኪልዳማ ብሎ እንደሰየመው ወያኔም በስልጣን የሚቆይበትን ጊዜ አኪልዳማ ነው፡፡

ለሱዳን መሬትን ቆርሶ በመስጠት በስልጣን ለመቆየት የሚደረግ የቀቢጸ-ተስፋ ተግባራት በምንም መልኩ ህዝባዊ ጥያቄን አዳፍኖ ማስቀረት አይችልም፡፡ወያኔ ህዝቡን ሳያውቀው አንድ ቀን እንኩዋን በድፍረት ክህዝብ ሳይወያይ ሌባ እና ፖሊስ ድብብቆሽ በመጫወት ወደ ግብአተመሬቱ እየተቃረበ ይገኛል፡፡ሁሉንም የመጫወቻ ካርዶች ወደመሬት ጥሎ ፋርዳ የወጣው አንባገነን የዘር ጥላቻውንም፤የእምነት ጥላቻ ዘመቻውን በግልጽ እና በስውር ቢያካሂድም ከልዩነት ይልቅ  አንድነቱ እና ወገናዊነቱ እያመዘነ የመጣውን የህዝቦችን ህብረት መቋቋም ተስኖታል፡፡ለዚህም እንዳበደ ውሻ ያገኘውን ሁሉ እየነከሰ ይገኛል፡፡መጻፍ ፤መደራጀት ሽብርተኛ እያሉ  ዜጎችን በጅምላ በማሰር በመግደል የህዝብን አመጽ ማስቆም አይቻልም፡፡ሀገርን እየቆረሱ ለባእዳን በመስጠት በስልጣን መቆየት አይቻል፡፡በስልጣን ለመቆየት የሚያስችለው የማሸነፊያ ካርድ በሱዳን እጅ ሳይሆን በተባበሩት የኢትዮጵያ ህዝቡች እጅ ነው ሚገኘው፡፡

እግዚያብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!

posted by Tseday Getachew

Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: