Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

ተከብሮ ያላስከበረ ሕገ-መንግስት…… ከይድነቃቸው ከበደ (የሰማያዊ ፓርቲ የሕግ ጉዳይ ሃላፊ)

ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም ሕገ-መንግስቱ የፀደቀበት ቀን ነው፡፡ይህንንም ተከትሎ በመንግስት አሳሳቢነት እልፍ ሲልም አስገዳጅነት ህዳር 29 በየዓመቱ ከተለያዩ ጎሳ የተወጣጡ ሰዎች ተሰባስበው በመንግሰት ሹማምንቶች ፊት በአደባባይ ከበሮ የሚደለቅበት ቀን ነው፡፡ይሁን እንጂ የአብዛኛው ኢትዮጵያዊያን መልካም ፍቃድና ተሳትፎ ባልታየበት የፀደቀው ህገ መንግስት በብዙሃን ዘንድ ተቀባይነቱ ጥያቄ ውስጥ የገባ ነው፡፡በዚህም መሠረት ከቃሉ አጠቃቀም ጀምሮ እስከ አከባበሩ ክብረ በዓል አብዛኛዉ ሰው እኔንም ጨምሮ ግድ አይሰጠንም፡፡
‹‹ይህ ህገ-መንግስቱን የመነዳ ተግባር ነው!!!›› ከገዢው መንግስት ተደጋግሞ የሚሰማ ለመፈረጅ ወይም ለመከሰስ የሚጠቀሙበት ቃል ነው፡፡ አንድ ወዳጄ እንዲህ አለኝ ‹‹ ይህ ህገ መንግሰት ዝም ብሎ የተደረደረ ብሎኬት ነው እንዴ የሚናደው ?›› በማለት ሲተች ሰምቸዋለው፡፡በመናድ እና ደግፎ በማቆየት ላይ የተመሠረተሁን ህገ መንግስት እጅግ በጣም ብዙ ነገር ተብሎለታል፡፡

(ይድነቃቸው)
እየተንገዳገደ ያለው ህገ መንግስት ከአፀዳደቁ ጀምሮ የሚቀሩት ድንጋጌዎች መኖራቸው ለማንም ግልፅነው፡፡ ቢሆንም ፀድቆ በተግባር ላይ የሚገኘው ህገ መንግስት ዋጋ እንዳይኖረው እያደረገ ያለው የገዢው መንግስት አካሄድና ተግባር መሆኑ በአጭሩ ለማሳየት እሞክራለው፡፡
1ኛ. መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፤ሃይማኖትም በመንግስት ጣልቃ አይገባም የሚለው በሕገ መንግስት አንቀጽ 11 ንዕሱ አንቀፅ 3 ተደንግጎ የሚገኝ ነው፡፡ይሁን እንጂ ገዢው መንግስት በሃይማኖት ላይ ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት እየፈፀመ ይገኛል፤ለዚህም ጥሩ ማሳያ የሚሆነው በእስልምና አይማኖታ እየተፈፀመ ያለው በደል ነው፡፡በደሉ በይፋ የወጣ ሲሆን በተለይ ለእምነታችን እንቢኝ ያሉ ለሞት፣ለእስርና ለእንግልት ተዳርገው ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪ በኦርቶዶክስ እምነት ውስጥም ጣልቃ ገብነቱ እንደተጠበቀ ነው፡፡ገዳማትና አድባራት በልማት ስም ፈርሰዋል የተቀሩት ቦታቸው ተጎምዶ ተወስዶል በዚህም ምክንያት የሀይማኖት አባቶችና ጥቂት የማይባሉ የእምነቱ ተከታዮች ለእስርና ለእንግልት ተዳርገዋል፡፡
ከምንም በላይ ደግሞ በሁሉም በተለይ በኦርቶዶክስና በእስልምና የሀይማኖቱ መሪዎች (አባቶች) ሹመታቸው ከሚያመልኩት አምላክ እና ከምዕመናኖ የመነጨ ሳይሆን በመንግስት ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት የተፈፀመ ነው፡፡
2ኛ. የመንግስት አሠራር ለሕዝብ ግልፅ በሆነ መንገድ መከናወን አለበት፡፤ በሕገ መንግስት አንቀጽ 12 ንዕሱ አንቀፅ 1 ተደንግጎ የሚገኝ ነው፡፡ቢሆንም ከታችኛው የስልጣን እርከን ከሆነው ከቀበሌ ጀምሮ እስከላይኛው የመንግስት ባለስልጣናት አማከኝነት የሚከናወኑ የመንግስት አሰራሮች ግልፅነት እጅግ በጣም ጠባብ ነው፡፡በመሆኑም ህብረተሰብ በአገሩ ጉዳይ ቀጥተኛ ተሳታፊ በመሆን በመንገስት አሠራር ላይ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አልተደረገም፡፡
በዚህም ምክንያት የመንግስት አሠራር ለሙሱና የተጋለጠ ነው፤ሙሱና በአሁን ወቅት በአገራችን ህጋዊ እስከመሆን ደርሷል፡፡በመሆኑም ማናኛውም የመንግስት ኃላፊ ኃላፊነቱን ወይም ስልጣኑን መሠረት አድርጎ ሲበድል እንጂ ለበደሉ ተጠያቂ ሲሆን አልታየም፡፡ስለዚህም የመንግስት አሠራር በየትኛውም ደረጃ ለህዝብ ግልፅ አይደለም ይህ ደግሞ የህገመንግስቱ ድንጋጌ ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡

3ኛ. ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር፣የአካል ደህንነትና የነፃነት መብት አለው፡፡ተብሎ በህገመንግስቱ አንቀፅ 14 ተፅፎ ይገኛል፡፡ነገር ግን የሰው ደህንነትን ለመጠበቅ የተቋቋመው የደህንነት መስሪያ ቤት በየደኑና በየጫካው የስንቱን ሰው ህይወት እንዳጠፋና የአካል ጉዳት እንዳደረስ የሚያውቀው ያውቀዋል፡፡ በተጨማሪ ይህ የነፃነት መብት ገዢው መንግስት በችሮታ ወይም በፍቃዱ የሰጠን እንጂ ሰው በመሆናችን ያገኘነው መብት እንዳልሆነ በሚያሳብቅ መልኩ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነትና የነፃነት መብት በገዢው መንግስት መልካም ፍቃድ ላይ የተመሠረተ እስከሚመስል ደረስ ተደርሷል፡፡
4ኛ. ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት ፣ኢሰብዓዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት አለው፡፡የሚለው በህገመንግስቱ አንቀፅ 18 ላይ ይገኛል፤ ይህ የህገመንግስት ድንጋጌ መሸራረፍ ሳይሆን መገርሰስ የሚጀምረው በህገመንግስቱ በተቋቋመው በህግ አስፈጻሚው አካል ነው፡፡
በመሆኑም ክብርን ለማወረድና ጭካኔን ለማሳየት የሰለጠኑ አሰቃዮችና ማሰቃያ ቦታዎች መኖራቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ነገሩን ለማነፃፀር እንዲረዳ ፖለቲከኛ ወይም በህግ ጥላ ስር ያለ ሰውን ይቅርና ስታዲዮም እግር ኳስ ለመመልከት ወራፋ የሚጠብቅ በወረፋ ምክንያት ለተነሳ አለመግባባት ፖሊስ እንዴት አድርጎ እንደሚቀጠቅጥ ዱላውን የቀመሰ ያውቃል፡፡
5ኛ. በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች ሰብዓዊ ክብራቸውን በሚጠብቅ መልኩ የመያዝ እና ከሰዎች ወይም ከጠያቂዎቻቸው የመገናኘት መብት አላቸው፡፡ በማለት በህገመንግስቱ አንቀፅ 21/1እና2 ተፅፎ ይገኛል፡፡ይሁን እንጂ ነፃ ጋዜጠኞች እና የፖለቲካ እስረኞች አያያዛቸው ክብርን ከመንካት አልፎ በህይወታቸው ላይ አደጋ የሚያስከትል ነው፡፡በተጨማሪ ከቤተሰብ፣ከወዳጅ መጠየቅ የማይሞከር ነገር ነው፤ የመጠየቅ እድል ያላቸው እስረኞች እድላቸው በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡
6ኛ. ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የአመለካከት እና ሐሳብን በነፃ የመያዝና በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ የመግለፅ ነፃነት አለው፡፡የሚለው በህገመንግስቱ አንቀፅ 29 ተፅፎ ይገኛል፡፡ በእርግጥ ይህ መብት ገደብ ሊጣልበት እንደሚችል በህገ መንግስቱ ላይ ተገልፆ የተቀመጠ ሲሆን ገደብ ግን መሠረታዊ የሆነውን መረጃን የመስጠት እና የማግኘት እንዲሁም አስተሳሰብ ላይ ወይም አመለካከት ላይ ውጤት እንደማይኖረው በህገመንግስቱ ተገልፆ ይገኛል፡፡
ይሁን እንጂ አሳብን በነፃ ማሰብና ማንሸራሸር በአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ እጅግ አዳጋች ነው፡፡ነፃ አሳብ የሚንሸራሸርባቸው ነፃ ጋዜጦችና መፅሔቶች ምን ያህል አሉ ? እርግጥ ነው ገብያውኑ መሰረት ያደረጉ መዝናኛ ላይ ያተኮሩ መፅሔትና ጋዜጣ ለቁጥር በዝተው ይሆናል፡፡ ግን ሁሉ ነገር በአገር ነው የሚያምረው! ታዲያ ስለ አገር በነፃ አሳብ የሚንሸራሸርበት መፅሔትና ጋዜጣ ምን ያኸል ነው ? ጋዜጠኞችን በማሰቃየት፣በማሰር እና እንዲሰደዱ በማደረግ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ መጥፎ ሪከረድ አስመዝግባለች፡፡መንግስትን ተችቶ የፃፈና ፁሁፉ የወጣበት ጋዜጣ ወይም መፅሔት ጨምሮ ሁሉም ተጠራርጎ ቃሊቲ የሚገባበት ወይም አደገኛ ዛቻና መስጠንቀቂያ የሚሰጥበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡
7ኛ. ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሣሪያ ሳይዝ ሠላማዊ ሠልፍ እና ስብሰባ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት አለው፡፡ ተብሎ በህገመንግስቱ አንቀፅ 30/1 ላይ ይገኛል፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆን የቅርብ ጊዜ አይን ያወጣ የህገመንግስት ጥሰት ማቀረብ ይቻላል፡፡በሳውዑዲ በሚገኙ ወገኖቻችን ላይ እየተፈፀመ ያለው ግፍና በደል ይቁም፣ይህንንም የፈፀሙ ለፍርድ ይቅረብ በማለት አቤቱታ ለማቅረብ የተጀመረው ሠላማዊ ሠልፍ በፖሊስ ዱላ እና እስራት ነው የተጠናቀቀው፡፡ በተጨማሪ በመንግስት እየታየ ያለው የአስተዳደር ብሉሹነት ለማመልከት እና ምላሽ ለማገኘት የተጠሩ የተለያዩ የተቃውሞ ሰልፎች እና ስብሰባዎች በመንግስት ቀጥተኛ ትእዛዝ ተከልክሏአል፡፡ሠላማዊ ሰልፍ ማድረግ እና አቤቱታ ማቅረብ መብት ነው! በማለት ክልከላውን ወደ ጎን በመተው አደባባይ ለመውጣት የሞከሩ ለእስርና ለድብደባ ተዳርገዋል፡፡በመሆኑም የተቃውሞ ሠልፍና ስብሰባ በማድረግ አቤቱታ በኢትዮጵያ ማድረግ የሞት ሽረት ትግልና ጥያቄ ከሆነ ሰንብቷል፡፡
8ኛ. የዳኝነት አካል ከማንኛውም የመንግስት ባለስልጣን ሆነ አካል ተፅዕኖ ነጻ በመሆን በሙሉ ነፃነት ከህግ በስተቀር በሌላ ሁኔታ አይመሩም፡፡በማለት በህገመንግስቱ አንቀፅ 79 እና በተከታዮቹ ንዑስ አንቀፅ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ በየትኛውም ደረጃ የሚገኙ ዳኞች የመንግስት አስፈፃሚ አካል ከሆነው ነው ሹመታቸውን የሚያገኙት፡፡በመሆኑም ከመንግስት ጋር ቀጥተኛ ግኝኙነት ያላቸው የፍርድ ውሳኔዎች ምንያኽሉ በህግ እና በህሊና ላይ የተመሠረቱ ናቸው ? በተለይ የህሊናና የፖለቲካ እስረኞች የፍርድ ሂደታቸው ምን ይመስል ነበር ? እነዚህን እና መሰል ዳኝነቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት በህገመንግስቱ የሰፈረው ነጻ ዳኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡
9ኛ. የሀገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት የጎሳዎች ሚዛናዊ ተዋጽኦ ያካተተ ይሆናል፡፡ ተብሎ በህገመንግስቱ አንቀፅ 87/1 ተደንግጎ ይታያል፡፡ነገር ግን በየድንበር እና በተልኮ ጭዳ ከሚሆነው ውጪ አብዛኛው የሠራዊቴ አባል እና አዛዥ የአንድ ጎሳ ስብስብ ነው፡፡ ስለዚህም ሠራዊቱ የማነው የኢትዮጵያ ወይስ ወደሚል ጥያቄ እያመራ ይገኛል፡፡
10ኛ. በየደረጃው ትክክለኛ ምርጫ እንዲካሄድ ከማንኛውም ተጽእኖ ነፃ የሆነ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ይቋቋማል፡፡የሚለው በህገመንግስቱ አንቀፅ 102 ላይ ይገኛል፡፡ይሁን እንጂ የምርጫ ቦርድ ሃላፊዎች ሹመታቸው ከመንግስት መልካም ፍቃድ የመነጨ ሲሆን አሰራራቸውም ለገዥው መንግስ በእጅጉ በጣም ያደላ ነው፡፡ስለዚህም ምርጫ ቦርድ ህገመንግስቱን መሠረት አድርጎ ነጻ እና ገለልተኛ ነው ለማለት ከበድ ድፍረትን የሚጠይቅ ነው፡፡

 

በመሆኑም እነዚህ እና መሰል የህገመንግስቱ ድንጋጌዎች ጥሰት ወይም በእነሱ ቋንቋ የመንድ ተግባር እየተፈፀመ ያለው በህገመንግስቱ በየወንዙ ዳር የሚማማለው ገዥው መንገስት ነው፡፡ ህገመንግስት የበላይ ህግ ነው፡፡ማንኛውም ህግ፣ልማዳዊ አሰራር እንዲሁም የመንግስት ባለስልጣን አሰራር ከህገመንግስቱ የሚቃረነረ ከሆነ ተፈፃሚነት አይኖረውም ፡፡ የሚለው አንቀፅ 9 ንዑስ አንቀፅ 1 የገዥው መንግስት ደራሽ ዉሃ ጠራርጎ ወስዶታል፡፡ ስለዚህም የብሔሮ፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የሚለውን መጠሪያ ስም በመስጠት ከበሮ ተይዞ የሚደለቅለት እና የሚከበረው ህገመንገስት መልሶ ካላስከበረ ፌሽታው እና ቀረርቶው ከምን የመነጨ ነው ?

posted by Tseday Getachew

Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: