Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

ኢትዮጵያዊነት የታላቁን የሰላም አባት የኔልሰን ማንዴላ ህይወት የታደገ ታላቅ ሚስጢር …. አነጠረ

ኢትዮጵያዊነት የታላቁን የሰላም አባት የኔልሰን ማንዴላ ህይወት የታደገ ታላቅ ሚስጢር …. አነጠረ።

ወርቁ ፈለቀ፤ ገድሉ – ተገለጠ፤ እውነት -ሳቀ፤ የሙያ ሥነ – ምግባር
ከበረ፤ በዘውዳችን በሻንበል ጉታ ዲንቃ ….
„የተከበሩ ረቂቅ ሰው ናቸው“ ይሏቸዋልም።

ታሪክ ይዋባል። ኢትዮጵያ የኔልሰን፤ ኔልሰንም የኢትዮጵያ … ፍቅር – ድህነት።

ከሥርጉተ ሥላሴ

 

 

ወደ አራት ወራት ሆነኝ የሲቢሊቲ ሩም ታዳሚ ከሆንኩኝ። ወረፋው አይጣል ነው። ሌሊት ላይ ተነስቼ ድንጋይ አስቀምጥና ድምጹን ቀንሼ እተኛለሁ። አሁን አሁን ሰንበት ይናፍቀኛ ጀምሯል። ያው እዬተዝናኑ ቁምነገር መልቀም መልካም ነውና ተመቸኝ። የአባ መላን ሞደሬተርነትም እወደዋለሁ። ይስቃል … ቀልድ ጣል … ጣል ያደርጋል …. ይችላልም። እርግጥ ስጀምረው ትንሽ የሚታመሱ የመንደር ጉዳዮች በተለይም እስከ አባ መላ የመጀመሪያ ቡና ድረስ ነበሩ። ከዛ በኋላ ሁሉም ነገር መልክ ይይዝና መኮምኮም ነው። … የዛሬው ሰንበት ግን ወርቅን ያነጠረ ዕንቁ ነበር …. ዋው! እግዚአብሄር የኢትዮጵያዊነትን ሚስጢር ከኔልሰን ማንዴላ የህይወት ዘመን ጋር እርስ በእርሳቸው እንደ ሊማሊሞ መንገድ አያይዞ ፍትኃት የሰጠበት ታላቅ ቀን ነበር። ሳንተኛ ተግተን ከሰራንበት ኢትዮጵያዊነትን የክብር ካባ በ21ኛው ምዕተ ዓመት የሚያጎናጽፍ ፍጹም አዲስ የወርቅ እንክብል በእጃችን ሰተት ብሎ እንሆ ገባ። ተመስገን አልኩ ማለት ነበረብኝና። እኔ እንደማስበው የኢትዮጵያዊነት ሚስጢር ገና የሚፈልቅ ልዩ የሰማይ ሥነ – ጥብብ ብዬ ነበር። ዛሬም እላሁ – በድፍረትና በእርግጠኝነት።

 

እንደሰማን …. በተደሞና በግራሞት ሁላችንም ተደመምን … አባ መላ / አቶ ብርኃኑ ዳምጤ/ የሩሙ ባለቤት ዛሬውኑ አድራሻውን ፈልጌ ቃለ ምልልስ አድርጋለሁ በማለት በጸጸት ቃል ገባ … እየተቁነጠነጥን ሰዓቱን ጠበቀን። ሰዓቱ በጣም ራቀ … አይደረስ የለም ደረሰ …. በቀጥታ ከጀግናው ጋር ቃለ ምልልሱ ተጀመረ … በባተሌው ጠቅለል ሲል … እንዲህ ነው ….

የ78 ዓመት አዛውንት ናቸው። ምዕራብ ሽዋ አንቦ አካባቢ ነው የተወለዱት። የቄስ ትምርት ቤት ትምህርታቸውን እዛው አካባቢ አጠናቀው የአንደኛ ደራጃ ትምህርታቸውን እስከ 6ኛ ክፍል ተምረው፤ ከዚህ በኋላ ወደ ተመረጡበት ወደ ውትድርና ሙያ ተሰማሩ – በኮልፌ ፈጥኖ ደራሽ። ከህግ ባለቤታቸው ከወ/ሮ አስቴር ፈንታ ጋር በሥርዓተ ጋብቻ የሁለት ሴት ልጆችና የስድስት ወንድ ልጆች እንዲሁም የአራት የልጅ ልጆች አባት ባለ ጸጋ ናቸው። በአዲስ አበባ ከተማ ላፎቴ ካልተሳሳትኩ በ450.00 የኢትዮጵያ ብር በጡረታ ይኖራሉ። የታሪካችን አንብርት የተከበሩ ሻንበል ጉታ ልጆቻቸው የተሟላ ድጋፍና እንክብካቤ እንደሚያድረጉላቸው አባ መላ ካደረገላቸው ቃለ ምልለስ ለማወቅ ችያለሁ።

የኢትዮጵያዊነታችን ሚስጢር የሆኑት እኒህ ታላቅ ሰው እንደ ቀደምቶች ወርቆቻችን እንደ አብዲሳ አጋ፤ እንደ አብርኃም ደቦጭ፤ አንድ ሞገስ አስገዶም እንደ ዘርዓይ ደረስ ታሪክን የፈጠሩ የነፃነታችን ቀንድ ናቸው። ለእኛ ብቻ አይደለም የዓለም የነፃነት ትግል ጠባቂና አዲስ ፊኖሚና እንዲሁም አምክንዮም ናቸው ብል ማገነን ተብዬ እንደማልከሰስ ነው። ዘውዳችን የሆኑት እኒህ እንቁ የተከበሩ ኔልሰን ማንዴላ ለተለዬ ተልዕኮ ለሥልጠና ወደ ኢትዮጵያ በመጡ ጊዜ በስውር፤ በረቂቅና በርቀት እንዲጠብቋቸው ከተመደቡት ወገኖቻችን አንዱ ነበሩ። የሰላም ሐዋርያውን ኔልሰን ማንዴላ እንዲህ ይገልፆቸዋል“ ስልጡን ….የተከበሩ ረቂቅ ሰው ናቸው። ቀልጣፋና አንባቢ፤ ሰውነታቸውን በማፍታት በተለይም በቦክስ ስፖርት ላይ የሚተኩሩና መዝናናትም የሚወዱ ነበሩ“

ብሄራዊ ኃላፊነታቸውን በጀግንነት የተወጡት እኒህ ታላቅ ሰው ሳንበል ጉታ፤ ኔልሰን ማንዴላ ለስልጠና በመጡ በወራቸው በአንድ የስልጠና ጓደኛቸው ኔልሰን ማንዴላ ህይወት በአጭሩ ለመቅጨት ከአሴረው ድርጅት ጋር አብረው እንዲሰሩ ተጠዬቁ። እዬፈሩ ፈቃዱን ተቀበሉ። ምሳ እቴጌ ሆቴል ተጋባዙ፤ ተልዕኮው ተነገራቸው፤ የ2000.00 ፓውንድ ብርና ካሜራም ተሰጣቸው። ሂደቱን በፎቶ እንዲያነሱ ተገለጸላቸው። የግድያው እቅድ መራራ ነበር። በገመድ አንቀው እንዲገድሉ ነበር የተነገራቸው። ከግድያው በኋላ ከኮልፌ የፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ማሰልጠኛ ጣቢያ 500 ሜትር ላይ በርቀት በመኪና እንደሚጠብቃቸውና ከዚህ በኋላ ውጭ ሀገር እንደሚኖሩ፤ ከድህነት ጋርም ለአንዴና መጨረሻ ጊዜ እንደሚፈቱ ተነገራቸው። ውሉ በጳውሎስ ቤተክርስትያን ቃል እንዲታሰርም ተሰማሙ። ሁሉን ከከወኑ በኋላ ታማኙ ወታደር በቀጥታ ወደ አዛዣቸው በመሄድ ዝርዝር ሪፖርቱን ገለጹ ለጄ/ ታደሰ ብሩ። ዕለተ ሰንበት ልክ ከምሽቱ ሶስት ሰዓት የነፃነትን ነፍስ የታደገ ሕይወት፤ የዘርኝነትን ቅስም የሰበረ፤ የአፍሪካ መብራታ እንዲጠፋ ነበር ብይኑተ። ለዛውም በፍጹም ሁኔታ ታምና አፍሪካ ልጇን ለላካችባት የነፃነት ዓርማ ሀገር ኢትዮጵያ መሬት ላይ። ለተልእኮው አንድ ነጭና ሌላ ጥቁር ሰው እንደነበረ ባለ ታሪኩ ይናገራሉ …. ድርድሩ ቅዳሜ ነበር።

ክቡር ሻንበል ጉታ በበነገታው ሰንበት ተራኛ ነበሩ። ቅደመ መሰናዶውን ያሟለው ወታደራዊ የደህንት ክፍል ወንጀሉን ቀድሞ ስለደረሰበት አከሸፈው። … ቅጣቱም ለስም የለሽ ተሰጠ። …. እሩቅ ቦታ ተመደበ …. ሁለቱ የውጭ ሀገር የሴራው መሪዎች በ24 ሰዓት ኢትዮጵያን እንዲለቁ ተደረገ። የኛው ክብር፤ ተክሊላችን ሻንበል ጉታም ዲንቃም ኃላፊነታቸውን በድልና በብቃት አጠናቀቁ። ታማኝታቸው ለኢትዮጵአዊነት ክብር ሸለሙ። የተሰጣቸውን የ2000.00 ፓውንድና ካሜራም አስረከቡ ለክፍሉ። ሚስጢሩ በሚስጢርነት ቀጥሎ ለሌሎች የሙያው ባልደረቦች ሹመት ሲሰጥ በሚስጢር የዛሬው ሻንበል ጉታ የ10 አለቃነት ለደበበ የ50 አለቃነት ማዕረግ ተሰጠ ይላሉ። ድንቁ …. ይህም ሚስጢር ነበር። የሚገርመው ሂደቱም ድርጊቱም ሚስጢርነቱ እጅግ ጥብቅ መሆኑ ነው።

የታወቁት የተከበሩት ኔልሰን ማንዴላ በስውርና በርቀት ጥበቃ እንደሚደረግላቸው ሆነ የግድያ ሙከራው ታስቦ እንደከሸፈ ሳያውቁ ነበር ያለፉት። ዛሬ …. ለነገም ሌላ ከመቃብር በላይ ሌላ አዲስ ትዕይታዊ የታሪክ ምዕራፍ ኪኖ ልበለው ገድል …. የመረጣችሁትን ብያለሁ። ያን ጊዜ በሴራው ውስጥ ስለነበረው ዛሬ 08.12.2013 አባ መላ ሲጠይቃቸውም ስሙን ለመስጠትና በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ለመግለጽ ፈቃደኛ አልሆኑም። ይህ በራሱ ከወርቅ የነጠረ ወታደራዊ ሥርዓት …. ያኮራል። ግን ዛሬ …. ቅንቅን የበላው ይመስለኛል በወያኔ …

ህልም ነባራቸው የሀገራቸውን ባህላዊ ልብስና ጃኖ የተግባር አዛውንቱን፤ የጽናት አብነቱን፤ የምህረት ድርጊተኛውን አጎናጽፈው ከኔልሰን ጋር ፎቶ ለመነሳት …. ለ2 ዓመታት ቢጥሩም አልተሳካላቸውም። የመንፈስ ሚስጢራቸውን እንደ ቋጠሩ ዛሬ ሀዘናቸው መራር ቢሆንም በቀብሩ ላይ ለመገኘት ፈልገዋል። እንኒህ ታላቅ ሰው የዓለምን ተስፋ የታደጉ በመሆናቸው በርካታ ዓለም ዓቀፍ ሽልማት ማግኘት አለባቸው እላለሁ። ቢያንስ ዛሬ ለቀበር ሥርዓቱ በክበር እንዲገኙ በደስታ ምኞታቸውን ለማሳካት ደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ወገኖቻችን ሥጦታቸውን በደስታ አክበረው በማሰተናገድ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ በወገኖቼ እዬተማመንኩ ቢዛ ካገኙም መሄድ በቀብር ሥርዓቱ ላይ መገኘት ስለ አለባቸው የሎቢ ተግባራትን ከመከወን በተጨማሪ ጠቅላላ ወጪያቸውን እንሸፍን ዘንድ ቆሜ እለምናችኋለሁ።

አዎን …. የመጨረሻው የተከበሩ የኔልሰን ማንዴላ ጉዞ ድንገተኛ ነበር። የምሽት እራት ግብዣ ነበር። ዝግጅቱም በክበቡ ነበር። ከሌሎች አርቲስቶች ጋር ቀደምቷ አርቲስ ሂሩት በቀለ ተገኝታለች። በመጨረሻዋ ሰዓት የፈጥኖ ደራሽ የማዕከሉ አዛዥ ጄ / ታደሰ ብሩና የሰላሙ አባት ኒልሰን ማንዴላ አብረው አሳለፉ። የነበራቸውን ልዩ አድናቆት፤ ክብርና ፍቅራቸውንም የተከበሩ ጄ/ ታደሰ ብሩ የወገባቸውን ኮልት 38 ሽጉጥ ፈተው ለኔልሰን ሸለሙ። ልጅን፤ ክብርን የመስጠት ያህል ነበር። ጌታችን መዳህኒታችን እዬሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ለወዳጁ ለቅዱስ ዮኋንስ ቀበቶውን እንደ ሰጠው ሁሉ። ዕንቁው አባታችን ከ ኢትዮጵያ እንደተመለሱም ነበር የካቴና ስንቅ የሆኑት።

የላቀ ሜዳሊይ፤ ዓለም አቀፍ ሽልማትና ተደማጭነትን ሊአተርፍ የሚችለው ይህን ታላቅ ተልዕኮ የእፍሪካ እናት ምድር፤ የዓለም እናት እምዬ ኢትዮጵያ ስታስተናግድ በዛን ወቅት በአጠቃላይ በካንፑ ውስጥ የተከበሩ ኔልሰን ማንዴላ ስልጠና የሚያውቁ 5 ሰዎች ብቻ ነበሩ። ጠባቂዎቹ ከጄኒራላቸው ጋር በቀጥታ የመገናኘት መብት ነበራቸው። ተፈልፍሎ … ተዝቆ የማያልቅ ብቃትና መክሊት …. ከድንቅነሽ አንባ ….

ኮንታክት ኢሜል ለእርዳታ bdamte56@gmail.com

ኢትዮጵያዊነት የነጠረ ወርቅነት!

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

posted by Tseday Getachew

Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: