Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

መፍትሔው (አበራ ሽፈራው ከጀርመን)

አበራ ሽፈራው ከጀርመን

በተለይም ባለፉት 22 ዓመታት በሀገራችን ለተከናውኑት አበይት ችግሮች ሁላችንም እጆቻችንን ወደ ህወሓት እየቀሰርን ለችግሮቻችን መፍትሔ መስጠት አቅቶን ይባሱኑ ለከፍተኛ ስቃይና መከራ መዳረጋችንና፤ መፍትሔውን ከህወሓት እየጠበቅን ለችግራችን መባባስ አስተዋጽኦ በማድረጋችን ችግራችን እየተባባሰ ቀጥሏል። በምን መልኩ ነው አስተዋጽኦ አደረግነው?

በምን መልኩ አስተዋጽኦ አደረግን? ለምንል ደግሞ በተደጋጋሚ የህወሓትን ማንነት አይናችን እያየና እየተመለከት መስዋዕትነት ለመክፈል መወሰን ባለመቻላችንና የሀገራችንን እጣፋንታና የወደፊት እድላችንንም ጭምር በህወሓት እጅ አስቀምጠን አሁንም ለህወሓት ባርነት እራሳችንንና ሀገራችንን አሳልፈን መስጠታችን መቀጠሉ አስገራሚ ጉዳይ መሆኑና እኛም ለዚህ ውርደታችን መባባስ ለህወሓት ከፍተኛ እድል በመስጠታችንም ጭምር ነው።

ለችግራችን መፍትሔ ፈጣሪ ለመሆን እስካልቻልንና መፍትሔ የመፈለጉ ጉዳይ በራሱ በኢትዮጵያ ህዝብ እጅ እስካልገባ ድረስ አሁንም የህወሓት ጥቂት ጨቋኝ ቡድን የባርነት ቀንበር ተጭኖብን ለመኖር በመፍቀዳችን መፍትሔ አልባ ህዝቦች ሆነን ለመኖር መፍቀዳችንን ልንገነዘብ ይገባናል።

ባለፉት ዓመታት ህወሓት በሀገርቷና በህዝቧ ላይ መጠነ ሰፊ ግፍን ሲፈጽም ዝም ተብሎ ዛሬ እዚህ ደርሰናል። ሀገር እየተቆረሰ ለሌላ ሀገር ሲሰጥ፣ ህዝብ በጅምላ ሲገደል፣ ህዝብ እያፈናቀሉ ወደመጣህበት ዘር ሂድ ሲሉና የሰውን ልጅ ከደን ውድመት ጋር እያዛመዱ ሲሳለቁብን፣ በታጋይነት ሰበብ የአገሪቷን ጠቅላላ ወታደራዊ ሥልጣንን በቁጥጥር ውስጥ አስገብተው ጥቂቶች በህዝብ ሃብትና ንብረት ሲሳለቁ ፣ ጠቅላላውን የአገሪቷን የንግድ እንቅስቃሴ በመቆጣጠር የራሳቸውን የፓርቲ ንግድ ሲያስፋፉና ሌላውን የንግድ እንቅስቃሴ ሲያቀጭጩ እየተመለከትን፣ የአገሪቷ ህዝቦች በስደትና በመከራ ላይ ሆነው እነሱ የአገሪቷን መሬትች በመኖሪያ ቤት፣ በንግድ ቦታና በእርሻ ቦታነት እየተከፋፈሉ የራሳቸውን መስፋፋት ሲያጠናክሩ እየተመለከትን፣ በተለይም ላለፉት 22 ዓመታት የአገሪቷን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትን በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ያሉትን ጠቅልለው ይዘው የንግድና የራሳቸው የኑሮና የመስፋፋት ዓላማን ለማስፈጸም ከፍተኛ እድልን ፈጠረው ሲቀልዱብን አይናችን እያየ እየተመለከትን ለመሆኑ እኛ ማን ነን? ምንስ እንጠብቃለን?

ስለሆነም ህወሓት አሁን ካለበት ሁኔታ አንጻር በምን አይነት ሁኔታ እንዳለና ምን መፍትሔ መፍጠር እንደሚቻል ትንሽ ነገር ልበል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት ህወሓት/ ኢህአዴግ አሁን ያለበት ሁኔታ በእኔ እይታ

ህወሓት ለአለፉት 22 ዓመታት ህዝቡን ሲረግጥ፣ ሲጨቁንና ሲከፋፍል የኖረ ከመሆኑ አንጻርና በህዝቡ ላይ ከመቼውም ጊዜያት ባልታየ ሁኔታ የኢትዮጵያ ህዝብን ለመከራ፣ለረሃብ፣ ለስደትና ለብዝበዛ ከበዳረጉም በላይ ጥቂቶች ባልተጠበቀ ሁኔታ በሃብት ጣራ የነኩበት ሀገር ከመሆኗ አንጻርና ከሌሎችም ተያያዝ ጉዳዮች ጋር ሲታይ ህወሓት ኢትዮጵያን ለመምራት ሃላፊነት በህዝቡ ሊሰጠው የማይችል መሆኑን ህዝቡና እራሱ ህወሓትና ባለሟሎቹ ጠንቅቀው ያውቃሉ፤ ይሁንና በጉልበትና በአንባገነነነት፣ እንዲሁም ህዝብን በማሸበር የመንግስትን ስልጣን ተቆጣጥረው ለመቀጠል ቆርጠዋል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን እየደረሰበት ካለበት መከራ አኳያ ሲታይ ህወሓት ሁኔታዎች እንደከዚህ በፊቱ ሁሉም አልጋ ባልጋ ይሆኑለታል ማለት ግን አይደለም። ምክንያቱም ህወሓት እኩይ የሆነው ተግባሩ ሰፊ ጠላትን አፍርቶለታልና ነው። ስለሆነም ህወሓትን ከዚህ አንጻር ልንገመግመው እንችላለን።

1. ህወሓት በራሱ በህወሓት ውስጥ ሲታይ

በነገራችን ላይ ህወሓት ህዝባዊ መሰረት እንዳለው የሚነገረው ትክክለኛ አለመሆኑን የተለያዩ ማስረጃዎች ማሳየት ይቻላል። ህወሓት በመሰሪነትና በገዳይነት የሚታውቅ ድርጅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በትግራይ ውስጥም ሆነ በራሱ በታጋዮች መካከልም ለዓመታት ታጋዮችን ጭምር በመግደል፣ በማሰቃየት፣ በማሰር፣ በማጥፋት እና መሰል የሽብር ተግባርን በመፍጠር ፍርሃትን በማንገሱ ፣እንዲፈራ በማድረግ በፍርሃት የተፈጠረ ድጋፍ እንጅ ሰው አምኖበት የደገፈው ድርጅት አልነበረም አሁንም አይደለምም። ህወሓት አሁንም በትግራይ ህዝብም ሆነ በሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ እየፈጠረ ያለው አንባገነናዊ ሥርዓት በህዝቡ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን ህዝብን በመንግስታዊ ሽብርተነት በማስገደድ እንዲሰገድለት ማድረግ ትልቁ አላማ አድርጎ ያለ ድርጅት እንጂ በፍጹም በዲሞክራሲያዊ ግባቶች እንደማያምን የራሱ የፓርቲው አፈጣጠርና አመጣጥ በግልጽ ያሳየናል።

እነዚህ ሁኔታዎች ህወሓት በራሱ ፓርቲ ውስጥ ሰፊ የሆነን ጥላቻን ይዞና፤ ቂም በቀልን የያዞ መሆኑና ብዙዎቹ ሁኔታዎችንና ጊዜዎች እየተጠባበቁ ያሉ መሆናቸውንም ጭምር ሊገባን ይገባል። በተወሰነ አጋጣሚ ሁኔታዎች ቢለወጡ ብዙዎቹ ለመበቃቀል የሚፈላለጉ መሆናቸውን በግልጽ እናያለን፤ ከዚህም በላይ አሁንም ቢሆን በመሃከላቸው ትልልቅ ልዩነቶች ያሉባቸው ከመሆናቸው አንጻር ለአደጋ የተጋለጡም መሆናቸውንም በቀላሉ መረዳት እንችላለን።

2. ህወሓት በኢህአዴግ ውስጥ ካለው ቦታ አንጻር ሲታይ

 • ህወሓት ሌሎችን የኢህአዴግን ፓርቲዎች በማስፈራራትና የሚፈልገውን እየሾመባቸው ለመኖር የሚሻ መሆኑ
 • ሁሌም የበላይነትን ይዞ ለመቆየት ሲል ሌሎችን በማሰር፣ በመግደል፣ በማስፈራራትና የመብትና የዲሞክራሲያዊ መብት ጥያቄዎችን እንዳያነሱ በማድረግ ጥቂቶች በበላይነት እንዲቀጥሉ በማድረግ
 • ዋና ዋና የአገሪቷን ሥልጣኖች በሙሉ በራሱ ቁጥጥር ውስጥ ከማስገባቱ ጋር ተያይዞ በሌሎች ፓርቲዎች ውስጥ ተቀባይነቱ እየተሸረሸረ መሆኑና፤ በተለይም ከ1997 ምርጫ በኋላ አይን ያወጣ አንባገነንነቱን ይዞ መቀጠሉ ችግሩን በይበልጥ እየጎላ መምጣቱና በፓርቲዎቹ መካከል አለመተማመን እየተፈጠረ መምጣቱ
 • ጥቂቶች በመቀያየር እየተሽከረከሩ የሚያስተዳድሩት መሆኑና ለዘለቄታ የሚሆን መሰረት የሌለው መሆኑ
 • በራሱ አባላት ጭምር የተጠላ አንባገነን ፓርቲ መሆኑ

3. ህወሓት በኢትዮጵያ ህዝብ አንጻር

 • ጥቂቶች ይባስም ብለው በቤተሰብ ደረጃ የተሰባሰቡበት ቡድን መሆኑ መታወቁ
 • ኢትዮጵያን የማይወክል ቡድን መሆኑ መታወቁ
 • ጥቂቶች እስከ እድሜ ልካቸው ድረስ በዚህ ቡድን ውስጥ ተሸሽገው የኢትዮጵያ ህዝብ ደም እስከ ጡረታቸው ድረስ የሚፈልጉትን ለማደረግ እንዲችሉ የተዋቀረ የማፍያ ቡድን መሆኑ መታወቁ
 • ወታደራዊ ሃይሉን የሚያስተዳድሩ ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ ሳይሆኑ ጥቂቶች አንድን አካባቢ ብቻ የሚወክሉ ተሰባስበው አገሪቷንና ህዝቧን እያስፈራሩ ለመኖር የተዋቀሩ የማፍያ ቡድን አባላት መሆናቸው መታወቁ
 • በሙስና የተጨማለቁ መሆናቸው ህዝቡ ጠንቅቆ የሚያውቅ መሆኑ
 • ለህይማኖት ነጻነት ክብር የማይሰጥ መሆኑና የነጻነት አምልኮ መገደቡ መታወቁ
 • በአጠቃላይ በየትኛውም መለኪያ በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ የተጠላ ቡድን መሆኑ

4. ህወሓት በመከላከያ፣ በፖሊስና በልዩ ልዩ ወታደራዊና የደህንነት መስሪያ ቤት ሲታይ

 • ኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊቷና ሌሎች ወታደራዊ አደረጃጀቶቿ እጅግ በሚገርም መልኩ የአገሪቷ ሳይሆኑ የጥቂት ይልቁንም የአንድ አካባቢ ሰዎች ተሰባስበው የሚያስተዳድሩት መስሪያ ቤት ከመሆኑም በላይ በየትኛውም የአገሪቷ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ አገሪቷ ለትልቅ የብዝበዛ መዋቅርነት እንዲያገለግል ተደርጎ የተደራጀ መሆኑ፤ ይህ ተቋም የአገሪቷ ተቋም ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ ለወደፊቱም ቢሆን ለአገሪቷም ሆነ ለህዝቦቿ ነጻነት ትልቅ አደጋ መሆኑ
 • ብዙዎች የመከላከያ ሰራዊት አባላትም የአገሪቷ የመከላከያ አወቃቀር መስተካከል እንዳለበት በመጠየቅ ላይ መሆናቸው
 • ወታደሩ ለኢትዮጵያ ከማገልገል ይልቅ የእነዚህን ጥቂት ዘረኞች የብዝበዛ መዋቅር እያስጠበቁ መሆናቸውን እያወቁ መምጣታቸው።
 • በአጠቃላይ ወታደሩ በልዩ ልዩ ጭቆና ውስጥ ያለ መሆኑና ጥቂት ነገር የሚፈልግ መሆኑ

ከላይ እንደተመለከትነው ህወሓት በአጠቃላይ ባለፉት ዓመታት ህዝቡን ባስመረረ መልኩ መጠነ ሰፊ ግፍን በህዝቡ ላይ ፈጽሟል ከዚህ በላይ ምን እስከምንሆን እንደምንጠብቅ አላውቅምም ወይም አልገባኝም። አንድ ነገር ግን ይገባኛል፤ እሱም እያንዳንዳችን ለራሳችን፣ ለህዝባችንና፤ ለሀገራችን የሚጠቅመውን ባለማድረግ፣ በመፍራት፣ እራስን በመውደድ፣ ለግል ጥቅም በመራራጥ፣ በግድየለሽነት፣ ነግበዕኔ ባለማለት፣ ህወሓት ለአቀረበልን ልዩ ልዩ ጥቅማ ጥቅሞች እየተገዛን በመንበርከካችንና በጋራ ባለመታገላችን፣ ከጋራ ጠላታችን ከህወሓት ይልቅ ሌሎች ተቃዋሚዎችን ለመተቸት በመሽቀዳደማችንና በሌሎችም ምክንያቶች አሁን እየደረሰብን ላሉ ሀገራዊ ውርደቶች እንድንዳረግ ሆነናል። እነዚህን ነገሮች ለመቀየር እንችል ዘንድ ቆም ብለን ማሰብ መቻል ያለብን ጊዜ ግን አሁን መሆኑ ግልጽ እየሆነ መጥቶልናልና እስኪ እናስብ።

ህወሓት አሁን ለምናየው እኩይ ተግባሩ ታግሎ መጥቶ በምስጊን ህዝብ ደም በነጻነትና በእኩልነት ሰበብ ይህንን ተግባሩን ሲፈጽም እንዴት እኛ ለእውነተኛው እኩልነት መነሳትና የራሳችንን መብት ለማስጠበቅ እንዴት ያቅተናል? ለዚህስ መስዋዕት ለመሆን ለምን ተቸገርን? ማን መስዋዕት እንዲሆን እንጠብቃለን? ግንቦት ሰባት ታግሎ ነጻ እዲያወጣን፣ አርበኞች ነጻ እንዲያወጣን፣ ኦነግ ነጻ እንዲያወጣን ወይስ ሌሎች ነጻ እንዲያወጡን እንደኔ ድርጅት ነጻ አያወጣንም። መጀመሪያ እራሳችን በግል እራስን ነጻ ለማውጣት መቁረጣችንን ማረጋገጥ አለብን። ከዚያ በኋላ ነው ድርጅቶችን መፈለግ ያለብን፣ከዚያ በኋላ ነው በመረጥነው የትግል መንገድ ከጠላታችን ጋር መፋለም የምንችለው፣ በመጀመሪያ ነጻነት ያስፈልገናል ወይስ አያስፈልገንም የሚለው ጉዳይ ሊያግባባን ይገባል፤ ከዚያም ነጻነትን እንዴት እናገኛለን ካልን የመጀመርያው መልስ ድርጅትን መምረጥ ሳይሆን ለመታገልና መስዋዕትነት ለመክፈል መነሳትና መቁረጥ ያስፈልጋል፤ ከዚያም ከቆረጡ ታጋዮች ጋር መደራጀት ይጠብቅብናል። መስዋዕትነት ለመክፈል መቁረጥ ይኖርብናል ሲባል ግን መስዋዕትነት የህይወት መሰዋዕትነት ብቻ አይደለም የጊዜ፣ የገንዘብ፣የእውቀት ማካፈል፣ የመረጃ መስጠት፣ ሌሎችም እንዳሉ ማመንና በአንደኛው ወይም በሌላኛው የትግል መስክ ተሰማርቶና የትግሉ አካል በመሆን ወደትግሉ በመቀላቀል የጋራ ጠላታችንን ዓላማ መቀልበስ ጊዜ የሚሰጠው አይደለምና እሁን እናስብበት! ግዜው አሁን ነው! ያለንም መፍትሔም ይኸው ብቻ ነው።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

ሀገራዊ ውርደት ይብቃን!

አበራ ሽፈራው ከጀርመን
aberay12@googlemail.com  

 posted by Tseday Getachew

Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: