Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

ከአቶ ኃይለማሪያም መጠበቃችን ስህተት ነበር – ግርማ ካሳ

Hailemariam-PM1-300x282

በሕገ መንግስቱ መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣  የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥና የሚኒስቴሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ናቸዉ። የጦር ኃይሎች ኤታ ማጆር ሹምን፣ ተቀዳሚ ጠቅላይ ሚኒስትርን፣ የሚኒስቴር ካቢኔዎችን፣ የፌደራል ፖሊስ አዛዦችን … የመሾምና የመሻር ሙሉ ስልጣን አላቸው። ፓርላማዉን በትነው አዲስ ምርጫ መጥራትም ይችላሉ። ፓርላማው በፈለገ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስቴሩን አዉርዶ፣  ሌላ መሾም ይችላል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ተጠሪነታቸው ለፓርላማዉ ብቻ ነዉ።

የፓርላማ አባላት፣ በፓርቲያቸው ለእጩነት ቢቀርቡም፣ በሕዝብ የተመረጡ፣ ተጠሪነታቸው ለፓርቲዉ አመራር አባላት ሳይሆን፣ ለመረጣቸው ሕዝብ ብቻ ነዉ። በፓርላማዉ ካሉ 547 መቀመጫዎች ደግሞ፣ የሕውሃት አባል የሆኑት 38ቱ ብቻ ናቸው (6.9 በመቶ ብቻ)።

የአቶ መለስን ሕልፈት ተከትሎ፣ በሕጉ መሰረት፣ ፓርላማዉ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስቴር እስኪመርጥ፣ በወቅቱ ምክትል ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ደሳለኝ፣ አክቲንግ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆነው ወዲያዉኑ መቀጠል ነበረባቸው። ነገር ግን የሕውሃት ሰዎች (አንዳንዶቹ የፓርላማ አባል እንኳን ያልሆኑ) «ኢሕአዴግ እንደ ፓርቲ ሳይወስን፣ አቶ ኃይለማሪያምን አክቲንግ ጠ/ሚ ማድረግ አይችልም» ብለው አቶ ኃይለማሪያም በምክትል ጠ/ሚኒስትርነት እንዲቀጥሉ አደረጉ። በሕገ መንግስቱ፣ ጠቅላይ ሚኒስቴርን የሚሾሙት፣ የፓርላማ አባላት እንጂ፣ የፓርቲዎች ፖሊት ቢሮ አለመሆኑ እየታወቀ፣ ሕውሃቶች በዚህ ሁኔታ፣ ለስድስት ወራት አቶ ኃይለማሪያም ጠ/ሚ እንዳይሆኑ፣  ማከላከላቸው የሚያሳየዉ፣  ሕገ መንግስቱን በአፍጢሙ እንደገለበጡት ነዉ።

ከስድስት ወራት በኋላ፣ ሕወሃት፣ አቶ ኃይለማሪያም ጠ/ሚ እንዲሆኑ እያቅማማ ለጊዜዉ ተስማማ። ነገር ግን በአቶ ኃይለማሪያም አንገት ላይ ማነቆ ታሰረላቸው። ሶስት ምክትል ጠ/ሚ እንዲሾሙ ተደረገ። አቶ ደመቀ መኮንን፣ አቶ ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል እና አቶ ሙክታር ከድር።

አቶ ደብረጺዮን እንደ ቴሌ ያሉትን መስሪያ ቤቶች ከመቆጣጠራቸዉ በተጨማሪ፣ የኢኮኖሚክና የፋይናንስ ዘርፉም በርሳቸው ስር እንዲሆን ተደረገ። በስልክ ፣ በኢንተርኔት የምንነጋገረዉን ሁሉ አቶ ደብረጽዮን ያዳምጣሉ፡፡ ባንኮችን፣ ቀረጥን የአገር ዉስጥና የዉጭ ንግድን የመዓድን እና የመብራት አገልግሎትን በሙሉ የሚቆጣጠሩትና የሚመሩት እኝሁ ሕወሃቱ አቶ ደብረ ጽዮን ናቸዉ።

ከትምህርት፣ ከጤና ፣ ከቱሪዝም ከመሳሰሉ ጋር የሚገናኙ  መስሪያ ቤቶች ብቻ፣  ለአቶ ሙክታርና ለአቶ ደመቀ ተሰጡ።  መከላከያ፣  ዉጭ ጉዳይና ደህንነት መስሪያ ቤቶች በአቶ ኃይለማሪያም ስር እንዲቆዩ ቢደረግም፣ ከታች ይቆጣጠሯቸው ዘንድ፣ አቶ ቴዎድሮስ አዳኖም የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሆነው ተሾሙ። ጀነራል ሳሞራ የነሱ የጦር ኃይሎች የኢታ ማጆር ሹም ፣ አቶ ጌታቸው ደግሞ የደህንነት ቢሮ ሃላፊ ሆነው እንዲቀጥሉ ተደረገ። ሁሉም ሕውሃቶች !!!!

«ዝም ብላችሁ ነዉ የምትደክሙት» ተብለን ነበር። እኛ ግን  « አይ ፣ አቶ ኃይለማሪያም  በሂደት ነገሮችን ያስተካክላሉ። ጊዜ ይሰጣቸው። ኢሕአዴግ ዉስጥ ጥሩ ልብ ያላቸው ብዙ አሉ»  እያልን ተከራከርን። በዚህ አቋማችንም በተቃዋሚ ወግን ባሉት ተተቸን። «ወያኔ ናቸው» እስከመባልም ደረስን። 94% በመቶ የሚሆኑት ሕውሃት ያልሆኑ የፓርላማ አባላትም፣ ሕገ መንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው፣ ጡንቻቸውን በማሳየት በሕውሃቶች፣ ዉስጥ ዉስጡን የሚሰራዉን ጸረ-ዴሞክራሲያዊ፣ ጸረ-እኩልነትና ጸረ-ሕዝብ ተግባራትን ሊያስቆሙ የሚችሉበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችልም አሰብን።

ነገር ግን እንዳሰብነዉና እንደገመትነው አልሆነም። ኦሕድድ፣ የደቡብ ህዝቦች ፣ የነአዲሱ ለገሰ የአማራዉ ድርጅት አባላትና መሪዎች፣  በሚያስገርምና በሚያሳፍር ሁኔታ ለሕዝብ ጥቅም ከመቆም፣  ዉሻ ለባላቤቱን እንደሚታዘዘው፣ የጥቂት ሕወሃት ባለስልጣናት ታዛዦችና ባርያዎች መሆናቸውን ቀጠሉ።

በሳዉዲ ወገኖቻችን ላይ በተከሰተዉ ግፍ ዙሪያ «ተማጽኖ ለጠ/ሚ ኃይለማሪያም» በሚል ርእስ፣ ጠ/ሚኒስትሩ፣ ሕዝቡን እንደ አንድ ሕዝብ እንዲያስተባብሩና ከተቃዋሚዎች ጋር በመሆን፣ ገለልተኛ የስደተኞች ኮሚሽን እንዲያቋቅሙ ጠይቀን ነበር። ነገር ግን ፣ ዶር ቴዎድሮስ አዳኖምን፣ ቁልፍ ሚና ሲጫወቱ  በየሜዲያዉ ስንመለከት፣ አቶ ኃይለማሪያም ድራሻቸዉን አጠፉ። (በነገራችን ላይ ዶር ቴዎድሮስ የሕውሃት አመራር ሆነው በሕውሃት ድርጅታቸው የሚደረገዉን ግፍ እያዩ ዝም ማለታቸው፣ ወይንም የግፉ አካል መሆናቸው እንደተጠበቀና ወደፊት በስፋት የምንነጋገርበት ሆኖ፣ በስደተኖች ዙሪያ እየሰሩ ያሉት ግን ማለፊያ ነው)

«በዚህ ብሄራዊ ዉርደትና ቁስል ወቅት፣ ሕዝብ ከርሳቸው መስማት ሲፈልግ፣ አቶ ኃይለማሪያም መሰወራቸው ተገቢ አይደለም። ዛሬ ብቅ ብለው ይሆን?» ብዬ በስማቸው ጉግል ሳደርግና ድህረ ገጾችን ሳካልል ፣  ያላዳመጥኩት፣ ከአንድ ወር በፊት ገደማ፣ በጸረ-ሽብርተኝነት ሕግ ዙሪያ፣  በእንግሊዘኛ የሰጡትን ቃለ ምልልስ አገኘሁ። ሊንኩን ነካ አድርጌ ቪዴዎዉን ማየትና ማዳመጥ ጀመርኩ። ዘገነነኝ። ሰዉዬዉ «የአገር መሪ ነኝ ፤ መጽሃፍ ቅዱስ አነባለሁ፤ እጸልያለሁ ..» ይላሉ። ግን በዚህ ቃለ ምልልስ የሰማሁት የአንድ ዱርዬና ጀብደኛ ቃለ መልስን ነዉ። አዘንኩ። አፈርኩ። አቶ ኃይለማርያም ሕሊናቸውን፣ ወይንም «አነባለሁ» የሚሉትን መጽሃፍ ቅዱስ የሚያዳምጡ ሳይሆን፣ ሙሉ ለሙሉ የሕውሃትን ጥቅም የሚያስጠብቁ፣ ትግሪኛ የማይናገሩ «ሕውሃት» መሆናቸው ገባኝ።

«አንዳንዶች ሕውሃቶች አጥረዋቸው እያስገደዷቸው ነዉ» ሊሉ ይችላሉ። እኔ ግን አልስማም። የሚናገሩትን ተገደው ሳይሆን፣  የሚናገሩት፣ በስሜት፣  ጠረቤዛ እየደበደቡና አምነዉበት ሲናገሩ ነው የምንሰማቸው። ይቅርታ ይደረግለኝና፤  ለእኝህ ሰው የነበረኝ ከበሬታ ፍጹም ተሟጣል። እኝህ ሰው የመጡበትን ብሄረሰብ ያሰደቡ፣ የእግዚብሄርን ስም ያሰደቡ፣ ስለርሳቸው ጥሩ ሲናገሩና ሲጽፉ የነበሩትን  «ደጋፊዎቻቸውን» ያሳፋሩ የማይረቡ ሰው ናቸው። [1]

በቃለ ምልልሱ ፣ አቶ ኃይለማሪያም ስለ ቦምብ ያወራሉ። እስክንድር ነጋ፣ አንዱዋለም አራጌ፣ ርዮት አለሙ፣ በቀለ ገርባ እንዲሁም በፖለቲካ አቋማቸው ምክንያት ሽብርተኞች ተብለው የሚማቅቁ ወገኖቻችን፣ ጀግኖቻችን እንጂ ሽብርተኞች አይደሉም። በአንድ ሰዉ ላይ አንዲት ጠጠር አልወረወሩም። በቤታቸው የተገኘ ፈንጂ፣ የተገኘ የራዲዮ ኮሚኒኬሽን መሳሪያዎችና ሚስጥራዊ ሰነዶች የሉም። የቀረበባቸው የተጨበጠ ማስረጃ የለም። በዚህም ምክንያት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ፣ አቶ አማረ አሞኜም «ሽብርተኞች አይደሉም» ብለው ሊፈቷቸውም ነበር። ሕውሃቶች «መለስ አደገኛ ያላቸውን መፍታት የለብንም። እዚያዉ ቃሊቲ ይበስብሱ» በማለት አቶ አማረን፣ በሌላ ዳኛ ለዉጠው፣  ፍርደ ገምድል ዉሳኔ አስወሰኑ እንጂ። የእነ እስክንድር ወንጀል፣ ሕዝብና አገርን መዉደዳቸው፣ እዉነት፣ ፍትህና  እኩልነትን መስበካቸው ነዉ።

አቶ ኃይለማሪያም፣ የ«ሕወሃት» መሪ ሆነው እቅጩኝ ነግረዉናል። ደንፍተዉብናል። «የሕሊና እስረኞች አይፈቱም። የሕግ ስርዓት፣ መልካም አስተዳደር አይኖርም። የትግራይ ሕዝብን ሳይቀር እያሰቃዩ ካሉ፣ ከጥቂት የሕውሃት አመራሮች ፣ ከነስብሀት ነጋ ፍቃድ  ዉጭ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍቃድ የለዉም። እነርሱ የሚሉትን ተቀብሎ፣ ተሰለፍ ሲሉት በነቂስ እየተሰለፈ፣ ከቤትህ እንዳትወጣ ሲሉት ቤቱ እየተቀመጠ፣ ከወጣም ደግሞ እየተደበደበ፣ ተናገር የሚሉትን እየተናገረ ፣ ተናገር ያልተባለዉን ከተናገረ እየታሰረ፤ ምረጥ የተባለዉን እየመረጠ፣ ምረጥ ከተባለው ዉጭ ከመረጠ ደግሞ፣ ድምጹ እየተሻረ፣  የባርነት ኑሮ ይቀጥላል» ነዉ እያሉን ያሉት።

እንግዲህ አብዛኞቻችን በእርቅ በሰላም በንግግር እናምናለን። በገዢ ፓርቲ ዘንድ በማንኛዉም ጊዜ ለእርቅና ለሰላም ዝግጁነት ከታየ እሰየው ነዉ የምንለው። ነገር ግን ከአቶ ኃይለማያም ጸያፍ ንግግር እንደሰማነዉ፣ ሕወሃት ከሕዝብ ፍላጎት ተቃራኒ የሆነ መንገድ የመረጠ ይመስላል። በመሆኑም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የራሱን እድል በራሱ ለመወሰን መዘጋጀት ይጠበቅበታል። 90 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ፣ እፍኝ በሚያህሉ ጥቂቶች፣  ታስሮና መብቱ ተረግጦ መቀጠል የለበትም። የአለም አቀፍ ሕግ በሚፈቅደዉ መሰረት፣ ሰላማዊ የእምቢተኝነት ዘመቻ በተቀናበረ መንገድ መደረግ አለበት።በዉጭ፣ በአገር የምንኖር ኢትዮጵያዊያን ሁሉ፣ በቤታችን ጸሎት ከማድረግ ጀምሮ፣  የድርሻችንን ለመወጣት መነሳት አለብን። ነጻነታችችን፣ መብታችንን፣ ክብራችንና ማስመለስ ይኖርብናል።

ስለሰላም፣ ስለእርቅ፣ ስለፍቅርና ስለ ብሄራዊ መግባባት ስናወራ፣ በዚያኛዉ ወገን እርቅን የሚፈልግ የሰለጠነ ቡድን አለ ብለን እንጂ፣ ፈርተን፣ ባርነትንና ዘረኝነት አሜን ብለን ተቀብለን አይደለም። የሰው ልጅ እግዚአብሄር ሲፈጥረው በነጻነት ነዉ። የሰው ልጅ ያለ ነጻነቱ ሰው አይደለም

http://www.zehabesha.com/

posted by Tseday Getachew

 

Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: