Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

ተማጽኖ ለጠ/ሚ ኃይለማሪያም: ሳዉዲን በተመለከተ (ግርማ ጌታቸዉ ካሳ)

ግርማ ጌታቸዉ ካሳ
(muziky68@yahoo.com)

ኖቬምበር 16 2013 ዓ.ም
አይኖቼ በደም ቀሉ። ልቤ ተሰበረ። ከሳዉዲ አረቢያ፣ ከባህር ማዶ፣ የወገኖቼ  ጩኸትና ሮሮ፣  ከጣራዬ በታች የመነጨ ይመስል፣ በጆሮዬ በቅርበት ያቃጭላል። በርግጥ እንደ አገር፣ እንደ ሕዝብ ፣ እንደ ኢትዮጵያዊ መዋረዳችንን አየሁ። በተለይም ደግሞ በአሁኗ ሰዓት፣ እንደ ወገን ምንም ማድረግ ባለመቻሌ ዉስጤ ደበነ። የማድርገዉን ሳጣ መሬት ተንበረከኩ። አይኖቼን ወደ ላይ አንስቼ፣ እጆቼን ዘረጋሁ። «ሄሮድስ ሊገድልህ ፈልጎ በነበረ ጊዜ፣  በልጅነትህ ከእናትህና እናታችን ቅድስት ማሪያም እንዲሁም ቅዱስ ዮሴፍ ጋር ተሰደሃል። የስደትን ኑሮና መከራ ምን ማለት እንደሆነ ታውቃለህ። አንተ መድሃኔአለም ኢየሱስ ክርስቶስ፣  እባክህ እነዚህ ስደተኞች ወገኖቼን አስባቸው። አንተ ድረስላቸው» እያሉ ጮኽኩኝ።

ትላንትና በአገራቸው መከራ ሲያጋጥማቸው፣  የኢትዮጵያ ንጉስ ነበር  በክብርና  በሰላም፣ ኢትዮጵያ መጠለያ እንድትሆናቸው ያደረገዉ። ዛሬ ፣ እነርሱ በእዉቀታቸዉና ጭንቅላታቸው  ሳይሆን ፣ ከመሬት በታቸ ፈረንጆች ባገኙላቸው፣ ዘይት «ሃብታም» ሆኑና፣ አሸዋ ላይ ከመተኛት ዳኑና፣  ይኸዉ ኢትዮጵያዉያንን  እንደ እንስሳ እያሰሩ ሲገርፉ እያየናቸው ነዉ። በርግጥ ይህ እንደ ኢትዮጵያዊ አንገት የሚያስደፋ ነዉ። የኢሕአዴግ ደጋፊ እንሁን፣ የኢሕአዴግ ተቃዋሚ፣ እንደ ኢትዮጵያዊ ሁላችንም ተዋርደናል።

ይህ በኢትዮጵያዉያን ወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት፣ በርግጥ፣ ያለ ምንም ማጋነን፣ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ከማወጅ ያነሰ ተደርጎ ሊቆጠር አይገባም።

በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት ሳዉዲ አረቢያ ለፈጸመችው ግፍ፣  ኦፌሴላዊ ይቅርታ እስክትጠይቅና ግፍ ለፈጸመችባቸው ወገኖች ሙሉ ካሳ እስክትከፍል ድረስ፣ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ማቋረጥ ይኖርበታል። የሳዉዲ አምባሳደር፣ ዲፕሎማቶች በአስቸኳይ ከአዲስ አበባ መባረር ይኖርባቸዋል።

ያ ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያዉያን ብቻ ሳይሆኑ በርካታ ቀለማቸው ጠቆር ያሉ አፍሪካዉያን ተመሳሳይ  እድል ገጥሟቸዋል። ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ለጥቁር ሕዝብ በሙሉ፣  ያላትን ንቀት ነዉ ሳዉዲ አረቢያ ያሳየችው። ሌሎች የአፍሪካ አገራትን በማስተባበር፣ በአፍሪካ ሕብረት ዘንድም፣ ጠንካራ አቋም እንዲወሰድ ማድረግ ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ፣ መንግስት የራሱ በሆኑ ምክንያቶች ማቅማማት ካሳየ፣  ከሁሉም ማእዘናት ኢትዮጵያዉያን በመንግስት ላይ ግፊትና ጫና እንዲያደርጉ እጠይቃለሁ።

ወደ ሁለተኛዉ ነጥቤ ልመለስ። ሳዉዲ አረቢያን ማዉገዝ በራሱ በቂ አይደለም። ከማዘን፣ ከመናደድ፣ ከማዉገዘና ሰልፍ ከመዉጣት ያለፉ እርምጃዎችን ፣ እንደ ሕዝብ መዉሰድ ያለብን ይመስለኛል።

በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ወደ አገር ቤት ሊመለሱ ነዉ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎናቸው ሊሰለፍ ይገባል። አረቦቹ እንደዚያ ቢያዋርዷቸውም ፣ ወገንና ሕዝብ ያላቸው መሆናቸውን ማሳየት ይኖርብናል። አገራቸው መመለሳቸው የተሻለ ነእንጂ የባሰ እንደማይሆን የሚያመላክት ተስፋ፣ በትንሹም ቢሆን ጭል ጭል ማለት ይኖርበታል።

በዚህ አጋጣሚ ለተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሃይለማሪያም  ደሳለኝና ጓዶቻቸው፣  ኢትዮጵያዊ፣ ወንድማዊና አክብሮት የተሞላበት ተማጽኖ ማቅረብ እፈልጋለሁ። ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው። በአገራዊ ጉዳይ ላይ ህዝብን ማሰባሰብ ያስፈልጋል። ለአባይ ትኩረት እንደተሰጠዉ፣ በሳዉዲ የተጎሳቆሉ ወገኖቻችንን ለማቋቋም ከፍተኛ ገንዘብና ርብርብ ይጠይቃል። በዉጭ አገር የሚገኘው፣ የገንዘብ አቅም ያለዉ ኢትዮጵያዊ፣ አገር ቤት ያሉ ባለሃብቶች፣  ሁሉም የድርሻዉን መወጣት ይኖርበታል። አገር ቤት ካሉ ተቃዋሚዎች ጋር በጋራ በመነጋገር አንድ ጠንካራ፣ ገለልተኛ፣  የሳዉዲ ስደተኞች ኮሚሽን እንዲቋቋም እመክራለሁ። ይህ ኮሚሽን ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለበት መልኩ፣ በሕግ፣ በኢኮኖሚክስ፣ በሲሻል ዎርክ ባለሞያዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች በተወከሉ ኢትዮጵያዉያን  በመሳሰሉት ተዋቅሮ፣ በቅርበት ከመንግስት ጋር እየሰራ፣ በስፋት የገንዘብ ማሰባሰብ እንቅስቃሴዎች በማድረግ፣  ስደተኞችንም የማቋቋም የሚሰራ ይሆናል። በአለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች ስደተኞችን ወክሎ በሳዉዲ አረቢያ ላይ ክስ የሚመሰረትበትንም ሁኔታ ሊያመቻችም ይችላል።

ኢትዮጵያዉያን መጀመሪያውኑ ከአገር ለመሰደድ የሚሞክሩት እንዲሁ በባዶ አይደለም። የኑሮ ዉድነት፣ የኢኮኖሚ ችግር፣ የሰብአዊ መብት ረገጣ፣ የመልካም አስተዳደር እጦት የመሳሰሉ ናቸው ለስደት ሰዉን የዳረጉት።  መንግስት በዚህ ረገድ አዎንታዊና ስር ነቀል ለዉጦች ቢያደርግ፣  የታሰሩ የሕሊና እስረኞች ቢፈታ፣ ብሄራዊ እርቅ እንዲኖር፣ ቅንነት ያለበት ዉይይት፣ ቢያንስ ቢያንስ፣ አገር ቤት ካሉ ተቃዋሚዎች ጋር ቢያደርግ፣ የሕግ ስርዓቱ የመጨቆኛ ዱላ ሳይሆን ፍትህ የሚገኝበት ስርዓት ቢሆን፣ የአገራችን አየር የራቁትን የሚስብ እንጂ በቅርብ ያሉትን የሚያርቅ አይሆንም ነበር።

በዚህ አጋጣሚ፣  አገር ቤት ላሉ ተቃዋሚዎች ፣ የሳዉዲን ኢሰብዓዊ እርምጃዎች በማዉገዝ፣ ለጠሩት ሰላማዊ  ሰልፎች ያለኝን ታላቅ ድጋፍ እየገለጽኩ፣ አብሮ መስራት በሚቻልባቸዉ ጉዳዮዎች ዙሪያ፣ ከኢሕአዴግ ጋር ለመነጋገር ፍቃደኝነቱን እንዲያሳዩም እጠይቃለሁ። መቃወም መልካም ነዉ። ግን ከመቃወም አልፍዉ በአገር ጉዳይ ከገዢዉ ፓርቲ ጋር አብሮ መስራት ያስፈልጋል።

እሰከምቼ ነዉ አገር እያለን የምንሰደደው ? እስከመቼ ነዉ ምግብ እያለን የምንራበዉ ?  እስከመቼ ነዉ ክብር እያለን የምንዋረደው ? እስከመቼ ነዉ ወገን እያለን ብቸኞች የምንሆነዉ ? ሳዉዲዎች ዘይት አላቸው። እኛም እኮ ፍቅር አጥተን ነዉ እንጂ፣ ማንም የሚመኘው የተፈጥሮ ሃብት አለን። እንደ ምሳሌ ያሉንን በርካታ ወንዞች መጥቀስ ይበቃል። ደግሞም ማን ያወቃል ?  ዛሬ ሳዉዲዎች የተመጻደቁበት ዘይትም እኮ አገራችን ሊገኝ ይችላል። መቼ በስፋት ተፈልጎ ?

በሕዝብ ብዛት ከሳዉዲዎች ሶስት አራት እጥፍ ነን።  እጅግ በጣም በርካታ ምሁራን፣ ጠበብት፣ ሳይንቲስቶች አሉን። ሳዉዲዎቹ ሁሉንም ነገር የሚያሰሩት በነጮች ነዉ። እኛ ግን ለእኛዉ እንበቃለን። የጎደልን ፍቅር ብቻ ነዉ !!!!!

በነገራችን ላይ ፍቅር ሲኖረን፣ ይቅር ስንባባል፣ ፊታችንን ወደ ኢግዚአብሄር ስናዞር፣ ምድራችንንም አምላክ ይባርካታል። እንኳን ለኛ ለሌሎችም የምንተርፍ እንሆናለን።  እንግዲህ እግዚአብሄር  ፍቅሩን ይስጠን ! ጮሮ ያለው ይሰማ ፤ ልብ ያለው ያስተዉል።

(ይሄን ጽሁፍ ለአንባቢያ ከመበተኔ በፊት፣  የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እግር ኳስ ጨዋታን ተመለከትኩ። እርግጥ ነው ለአለም ዋንጫ አልበቃንም። ነገር ግን  ለተጨዋቾቻችን፣ ለአስለጣኙ ያለኝን ትልቅ አክብሮትና አድናቆት መግለጽ እፈልጋለሁ። እዚህ መድረሳቸው በራሱ ትልቅ ዉጤት ነዉ። ኮርቼባቸዋለሁ። በዚህ ጉዳይ ላይ ወደፊት በስፋት እመለስበታለሁ)

http://www.zehabesha.com/

posted by Tseday Getachew

Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: