Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

“በወያኔ ምክንያት በወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ ይቁም” – አርበኞች ግንባር

“በወያኔ ምክንያት በወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ ይቁም!!!”
ከኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር/ኢሕአግ/ የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ህዝብ አገር ውስጥ በሚደርስበት ሰቆቃና ጫና ሳቢያ ለስደት እየተዳራገ ይገኛል። ህዝቡ በአገሩ ሰርቶ ለመኖርም ሆነ ዴሞክራሲያዊ መብቱን ለማስከበር አልቻለም። ኢትዮጵያ በታሪኳ ገጥሟት በማያውቅ መልኩ በኢኮኖሚውም ሆነ በሌሎችም ዘርፍ ውድቀት ውስጥ ገብታለች። ለዚህ ውድቀትና ድቀት ብዙ ምክንያቶችን መጠቃቀስ ይቻላል መሰረታዊው ምክንያት ግን ወያኔና ወያኔ ብቻ ነው። ከቀን ወደ ቀን ወደ ከፋ ደረጃ የሚገኘው የኑሮ ውድነት ዜጎች የእለት ጉርሳቸውን እንኳን ለመሸፈን አዳጋች ሆኖባቸዋል። የኑሮ ውድነቱ እንደ እግር እሳት እያንገበገበው የሚገኘው ወገናችን ከዚሁ በተጓዳኝ በፖለቲካው በኩል ሃሳብን በነጻነት የማንሸራሸር፣የመደራጀት፣ የመብት ጥያቄዎችን የማቅረብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፣የፈለገውን የመቃወምና የመደገፍ መብት፣ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት፣ የሰብዓዊ መብት መከበር … የመሳሰሉትን መሰረታዊ ጥያቄዎችን ህዝቡ በሚያቀርብበት ወቅትና ለመብቱ ፣ ለነጻነቱ፣ ለአንድነትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ በሚንቀሳቀስበት ወቅት በአምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ ዘንድ እየተወሰደ የሚገኘው ኢ-ዴሞክራሲያዊና ኢ-ሞራላዊ የሆኑ ጭፍን እርምጃዎች ምክንያት ህዝቡ ባገኘው አጋጣሚና ባመቸው መንገድ ሁሉ በየአቅጣጫው እንዲሰደድ አድርጎታል።

ወያኔ ሰራሽ በሆኑ ችግሮች ተገዶ ስደት እንደ አማራጭ ወስዶ በሰው አገር እየተንከራተተ የሚገኘው ወገናችን ህመም እጅግ ያመናል ለመፍትሄውም በአገር ቤትና በስደት ከሚገኘው ወገናችን ጋር አብረን እንቆማለን። በአረብ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን የማንገላታ፣ የማሰር፣ የመደብደብና ለአካል ጉዳት የመዳረግ ብሎም በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደል በየጎዳናው ዜጎቻችን እንደ አልባሌ እቃ ተጥለው ስንመለከት በቃላት ሊገለጽ የማይችል ልዩ ስሜት አእምሮአችን ላይ ፈጥሯል ። ጉዳዩ በግራም ተኬደ በቀኝ ከወያኔው ቡድን አለቆች ተጠያቂነት ጋር የተያያዘ ነው።

ለአባይ ግድብ ግንባታ ቦንድ ግዥ ድንፋታ ወቅት ዲያስፖራው ገንዘብ እንዲያዋጣ በዓለም አገራት የሚገኘውን ኢትዮጵያዊ ኪስ ለመበርበር ቁጥር ስፍር የሌለው ስብሰባ በማካሄድና ባዶ ፕሮፖጋንዳ በመንዛት ውጭ የሚኖረውን ወገናችንን ጥሪት ለማግበስበስ ሲሯሯጥ የነበረው የወንበዴ ቡድን ዛሬ ወገኖቻችን በአረብ አገራት ቅጥ የለሽ በደል ሲፈጸምባቸው የኢትዮጵያ መንግስት ተብዬውና በአረብ አገራት የሚገኙ ኤምባሲዎች ምነው ዝምታውን መረጡ? እየፈሰሰ ያለው የንጹሃን ደምና ያለ አግባብ እየሞተ የሚገኘው ዜጎቻችን ጉዳይ አይቶ እንዳላየ ማለፉ ህዝባዊ ፍቅር ወገንተኝነትና ተቆርቋሪነት መንፈስ ጭራሽ ያልፈጠረባቸው መሆኑ ማረጋገጫ ነው። የሚገርመው ነገር የሚጠሉትን የኢትዮጵያ ህዝብ በግድ ካልመራንህ እያሉ ፍዳውን ማሳየታቸው ሲሆን ህዝብን በመናቅና በግብዝ አመለካከት አገርን እናስተዳድራለን ማለቱ ከንቱ አባዜ ነው ስለሆነም ድርጅታችን የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር በአረብ አገር ኑሮአቸውን ባደርጉ ወገኖቻችን ላይ የሚደርሰው ግፍ የወያኔው ቡድን መልካም አስተዳደር ባለመስፈኑ ምክንያት መሆኑን በጽኑ ያምናል። ኢሕአግ ዜጎቻችን ከተዘፈቁበት አደጋ እንዲወጡ የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል ድርጅታችን ለተነሳለት ቅዱስ አላማ መሳካት በአገር ውስጥና በውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያዊያን በጋራ እንድትነሱ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
አንድነት ሃይል ነው!
የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር/ኢሕአግ/
ህዳር 6/2006 ዓ/ም

http://www.zehabesha.com/

posted by Tseday Getachew

Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: