Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

ማለዳ ወግ .. ለሰብዕና መደፈር እኩል መጮህ ባንችል እኩል ከንፈር መምጠጥ እንዴት ያቅተን ?

 

ጫወታውን ከአሃገር አቀፍ ወደ ቀጠና ሳወርደው ደስ ባይለኝም ለማለዳ ወግ የመረጥኩት ርዕስ ያን ሰሞን ሃገር ቤት በሚታተመው እንቁ መጽሔት የጻፍኩበት መሆኑን ያስታወስኩት ብዙ ከተብተከተኩና ከሞነጫጨርኩ በኋላ ነበር … ይህን የማደርገው ከአልጋየ ተጋድሜ በታጠፉት እግሮቸ ላይ የአርባ ቀን ሴት ልጀን አስተኝቸ እያባበልኩ ነው …በሌላ ጎን አብራኝ በብርታት አመት ልትዘልቅ በምትንደፋደፈው “ሳምሰንግ ታብሌት 10.1″ ሚጢጢ ኮምፒውተር ከወደ ቀኝ ጎኔ በኩል አድርጌ በፊስ ቡክ ገጼ ከመሰንበቻው የሆነውን የተሰጡ አስተ…ያየቶችን እየገማገምኩ ነው …

አንድ ወዳጀ “የሳውዲው ሲናሚ” ብሎ ከከባዱ ማዕበል ያመሳሰለው ሰሞነኛውን የአለምን ትኩረት የሳበው የሳውዲ ህገ ወጥን የማጥራት ዘመቻ አፈሳና የሪያድ ቤት ሰበራም በርካታ ተሳታፊዎች ተመለከትኩ… በወገን ስቅየትና ግፍ ያዘኑ የተበሳጩና የአረብ ሃገር ኑሮ ተየሰንበለጥ ቤት መሆኑን የተረዱ አውሮፖና አሜሪካ የሚኖሩ ወዳጆቸ እየሆንን ባለው አዝነው በየሃገራቸው ባሉ ሃገራት የሳውዲ ኢንባሲዎች ሰላማዊ ሰልፍ ሊወጡ እንደሚታሰብ ፣ በተለይም በቀጣይ ቀናት ልሰደድበት ጓጉቸ ሳይሰምርልኝ የቀረው ሃገር በአሜሪካ ዋሸረንግተን ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚደረግ መስማቴ አስደስተኝ! አዎ ከንፈር ከመምጠጥ ባለፈ ለተጎዳ ወገን እንዲህ አለኝታ መሆን መታደል ነው ! በሳውዲው ሱናሜ ዙሪያ በአደባባይ ከሚሰጡ አስተያየቶች በተጓዳኝ በወስጥ በር ያስተናገድኳቸውን ውረፋና ዘለፋዎች አይጠቅሙምና አላነሳቸውም። አንዳንዶች የአረቦችን ስም ልታከፋ ነው ሲሉኝ የቀሩት የመንግስትን እና የሃገርን ገጽታ ልታቆሽሽ ነው ብለውኛል ! ከጀርባ የተሳጠውን አስተያየት ባይመሳሰልም በፊት ለፊት የፊስ ቡክ ገጼ የተሰጡኝ ሁለት ቀልብ አስተያየቶች ደርሰውኛል!

Ramatohara Dertogada ራማቶሃራ ዴርቶ ጋዳ ጽንፈኛ የምለው የመንግስት ደጋፊ ወዳጀ ነው ። ራህማቶ ወዳጀ ያን ሰሞን የአደባባይ ምሁር በሚል የማከብራቸውን ፕሮፊሰር መስፍንን ወልደ ማርያምን ፎቶ ነውረኛ አስተያየት ለጥፎ ሳየው አስቆጥቶ በስጨት ብየ ወርፎዋለሁ። እሱ ግን በምላሹ የጨዋ ምለስ ሰጥቶ አሳፈረኝ! እናም መረጃው ብዙም ባይገባኝ ስነ ምግባሩ ስቦኝ በጓኝነት አብሮኝ የዘለቀ ወዳጀ ነው ። እናም የሳውዲውን ሰሞናኛ ፍተሻና በዜጎች የደረሰውን በደል ባብራራሁበት መረጃ ቅበላየ የጻፈው አስተያየት ሳውዲ ያሉት ዲፕሎማቶች የት አሉ? በሚል በመብት ጥበቃው ዳተኛ የሆኑትን በሳውዲ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ሸነቋቁጦልኛል። ይህን መሰል ያልጠበቅኩት ኢትዮጵያዊ ወገናዊነት ጎልቶ የሚታይበት አስተያየቱ እንዳስደሰተኝ ከማስደሰት አልፎ ልዩንትን አቻችሎ በሰብዕና አንድ ለመሆን እንደማይገደን መልዕክቱ በውስጤ ተሰራጨ …

ሌላው ተጠቃሽ አስተያየት ሰጭ ወዳጀ Tsadik Desta ጻድቅ ደስታ ይባላል ። ጻድቅን አሳምሬ አውቀዋለሁ። እኔ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅተ ተላላኪ አድርጎ ከሸከሸኝ ። ጻድቅና ጓዶቹ ላለፉት አስር አመታ ሳውቃቸው የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት የፖለቲካ ድርጅትን የበረታ ጉልበት በጅዳ ቆንስል ላይ በማሳረፍ “ሰብዕናና ኢትዮጵያዊነት ይቅደም !” የምንለውን ወገኖች በማስፈራራት ፣ በማሳደድና እንደ ዜጋ ኮርተን የኢንባሲና ቆንስል ግልጋሎት እንዳናገኝ ፣ በህዝባዊ ስብሰባዎች እንዳንሳተፍ ተጽእኖ ፈጣሪ ወንድም ነው ። እናም ጻድቅ የእኔን እንቅስቃሴ ለመግታትና ለማጥለፍ አቅሙም ፈጣሪም አልፈቀደም …በዲፕሎማሲው እና በመብት ጥበቃው ረገድ ጎድሎብን የከፈልነው ሰቆቃ ያለፈው ይቅር ቢባል በሳውዲ ዋና ከተማ በሪያድ እየሆነ ያለውን የመብት ገፈፋና የሃላፊወቻችን ዳተኝነት በምንም መንገድ መሸፋፈን ይከብዳል! ጻድቅ ወዳጀ ዛሬም ባረጀ ባፈጀ መላ ምት መረጃየን “የተቃዋሚዎች እና ተላላኪዎች ነው !” ማለቱ የአቅሙን ያህል ነው ቢባልም ሰብዕናውን ሊፈትሽ ይገባል ከማለት አልፊ አንድ የምንሆንበትን ቀን ከመመኘት አልፊ እሰጣ ገባ ወደሚያገባን ምላሽ አልሔድም!

ሌላው በዋናነት ለነፍሴን በአግርሞት እና ትዝብት ወጥሮ ወደዛረጰው የማለዳ ወግ እንድሻገር ያደረገኝ በዚህችው ኮምፒውተሬ ከለጣጠፍኳቸው መረጃዎች መካከል “በሳውዲው ሱናሜ” የተመታው የጅዳ ትምህርት ቤት ጉዳይ ነው ። በትምህርት ቤቱ 3000 ሶስት ሸህ ታዳጊዎች ይማራሉ ። ዛሬ ትምህርት ቤታቸው ለጊዜውም ቢሆን ተዘግቷልና ትምህርትን መቅሰም አቁመዋል። የእኛ ልጆች እንደ ቀረው አለም እንደፈለጉ ክእናት ፣እህት እና ቀሪ ቤተሰቦች ጋር ወጣ ብለው መዝናናት አይችሉም ። የእኛ ልጆች ሌላው ይቅር ቢባል ጸሃይ ብርሃንን የሚያገኙበት ፣ ከጓደኞቻቸው ጋር የሚገናኙበት የትምህርት ማዕከል በመንግስትና ህዝብ ተወካዮች እንዝህላልነት ተዘግቶባቸዋል። ለተራ ጥቅማ ጥቅም እንበለው ያለ እውቀት በተሰራ ሃጢያት ሰባት ወራት የፈጀውን የመምህራን ዝውውር የውስጥ ለውስጥ ሽኩቻና የተበላሸ አካሄድ ያማልና አልነግራችሁም … ይህም አይጠቅምምና ብዙ አልሄድም …

ወደ ተሰማኝ ስሜትና ትዝብት የእኔው ቅኝት እንመለስ ፣ በትምህርት ቤቱ ዙሪያ ከወራት ጀምሮ በርካታ መረጃዎችን አቅርቤያለሁ ። በቅርቡመ ስለመዘጋቱ እና በዙሪያው ስላለሀ መረጃዎች ጀርመን ራዲዮ ምስጋና ይድረሰው የተቻለውን ሁሉ መረጃ ቀርቧል ። በፊስ ቡክ ገጼ መረጃዎች ከተለያዩ ወዳጆቸረ ሳይቀር ቀርበው ለማወያየት ተሞክሯል ! ብዙ የተሳካ ነው ለማለት ግን አይቸሰልም ። ከሁሉም የሚገርመው ብዙ አስተያየቶች የሚስተዋሉት ስለ ትምህርት ቤቱ ከሚቀርቡ መረጃዎች ላይ ሳይሆን በግል በምለጥፈው ፎቶ ላይ የሚሰጡት አስተያየቶች ላየረ መሆኑ ነው ። ሶስት ሽህ ተማሪዎችን በምናስተምርበት በትምህርት ቤቱ ዙሪያ ለምን ብዙ አስተያየት የለም ? እጠይቃለሁ ፣ እመለሳለሁ …

ወደ መልሱ ለመድረስ ብዙ በማይገባኝ ሂሳብ የቃላት ስሌት ላምራ … በጅዳ እና አካባቢው በአሁኑ ጊዜ ከመቶ ሽህ ያላነሰ ኢትዮጵያዊ እንደሚኖር ይገመታል ። የሶስት ሽህ ተማሪ ወላጅ አንድ ሽህ ይደርሳል ብለን እንገምት። ከአንድ ሽህ አባወራ ቤተሰቦች ውስጥ አንድ ሁለት መቶ ማህበራዊ ድህረ ገጾችን ተጠቃሚ እንደሚኖር የራሴን ግምት ላስቀምጥ ። በከባቢያችን ካለው ከሁለት መቶው ተጠቃሚ መቶም ይቅር ሃምሳው ስለ ትምህርት ቤቱ ሲነሳ ” የልጆቸ ጉዳይ ነው ፣ ያገባኛል !” ብሎ አንድም ጣቱን ፊን አለያም ዘርዘር ያለ የተቃውሞ ሆነ የድጋፍ አስተያየት የማይሰጥበት አባዜ ፍርሃት ብቻ እንጅ ሌላ አይመስለኝም! የልጆች ትምህርት ቤት ጉዳይ አንድ ተረት አስታወሰኝ ፣ ሁለት ጓደኛሞች ባንድ ተኝተው አባ ጅቤ ጅቤ በደረቁ ሌሊት የአንዱን እግር ሲቆረጣጥመው የተመለከተ ሌላኛ ጓደኛው ” ጅቡ እግርህን ያዘው!” ቢለው ” ተወው እግሬን ነው !” አለው አሉ … የልጆቻችን ጉዳይ ሲነሳ ከፍቅራቸው የተነሳ ስሜታች ህይዎታችን እስከ መስጠት የሚያደርስ መስዋዕትነት እንደምንከፍል በልበ ሙሉነት የምንናገረው ወላጆች በትምህርት ቅበላው መሰናከል አብሮ ሊያመን ሲገባ እንደ ተረቱ ” ተወው እግሬን ነው !” ተብለን እንተወው ዘንድ በአሳፋሪ ፍርሃት ሽሽት ከዛሬው አሳፋሪ ቀን ደርሰናል ….

በአጠቃላይ ይህንና ሌላውን ሳየው እኔኑ ጨምሮ ፍርሃትን ፈርተን ስንኖር ከላይ ፈጣሪ ማየቱን ለአፍታ የረሳነው ይመስላል። በቅርብ የሆነውን እና እየሆነ ያለውን እስኪ ዘወር ብለን እንመልከተው?
– አንድ ሳምንት ሊደፈር እንድ ቀን በቀረው የአፈሳ ማዕበል በሪያድ መንፉሃ እየደረሰ ስላለው ወከባ ከሁሉም ዜጎች ኢትዮጵያዊ ተለይቶ ተጎዳ ፣
– በጅዳ የ3000 ታዳጊ ተማሪዎች የትምህርት ማዕከል ተዘጋ ፣
– በሪያድ ኢንባሲና በጅዳ ቆንስል በመቶዎች የሚቆጠሩ በህጋዊ መንገድ ለስራ መጥተው እና ተፈናቅለው በመጠለያ የተጠጉ ልጅ እግር ጉብል እህቶቻችን ውሎ አዳር ከቀን ቀን የከፋ ሆነ ፣ ያበዱትና አልፎ አልፎ ታመው በየታዛው ወድቀው ፣ በየአውራ ጎዳናው ነሁልለው የምናያቸው እህቶች ዘልቆ ልባችን በሃዘን ሰበረው ፣
– በተለያዩ ሆስፒታሎች ማንነታቸው ሳይታወቅ በሬሳ ቤቶች የሚገኙትን ሬሳዎችን ጉዳይ ሰማን ፣
– መከረኞቹ መብታቸው የተገፉ የጠመመባቸውን ለስራ ያለደረሱ እህቶች እተደፈሩ በውርደት ከስራ የሚበረሩበትን ፣ ደሞዝ የሚቀሙ ፣በሽተኛ የሚሆኑ ፣ ታንቀው የሚሞቱ ፣ በአዕምሮ መታወክ አንቀው የሚገሉ ዜጎች ማፍራታችን መለስ ብለን እንመልከተው! በገሃዱ አለም ከአፍንጫችን ስር በአይነ ህሊናችን እንቃኝና ከቶ ይህ ሁሉ ሰቆቃ በተቃዋሚዎች እና በአጫፋሪዎቻችው የሚሰራ ስራ ነው ወይስ በመብት ማስከበሩ በማይተጉ የመንግስት ሃላፊዎቻች የተፈጠረ ችግር ነው? ብለን ራሳችን እና ዙሪያችን እንጠይቅ! ከዚያም ህሊና የሚፈቅደውን የራስን ፍርድ እንስጥ !

እኔ ዛሬ የምለው አንድ ነገር በቻ ነው …አዕምሯችን ሰብሰብ አድርገን ከሚያናቁረን ቡቱቶ ፖለቲካ ፣ ከሐይማኖትና ከዘር ልዩነት ወጥተን እየሆንን ፣ እየሆነ ያለው በፍጹም ሰብዕና መንፈስ ብናየው ይበጀናል! ይህ ከሆነ ፈጣሪ ከታረቀን በፍርሃት የጨከነ ልባችን በሃዘን ተሰብሮ ባንድ ልናብር አንድ ሊያደርገን ይችል ይሆናል ! … ከሆነ በጀ ! ካልሆነ ለእኔ አማራጩ አንድ ብቻ ነው! በልዩነት መስማማቱ ሰብዕናቸው ለሚገፈፉ ዜጎች መብት መከበር እኩል መጮህ ባንችል እኩል ከንፈር መምጠጥ ያስችለን ይሆናል … !
በማለዳው በአልጋየ ላይ ተጋድሜ ከጉልበቴ ላይ ያለችው ማህሌት ከእንቅልፏ ነቅታለች … ባለቤቴ የኒም እንደ ለመንቃት ትገላበጣች… ከነቃች እና መሞነጫጨሬን ካየች ደግሞ ዋ …! ትናንት ምሽት የሪያድን ግፉአን ጩኸት የቀዳሁትን ድምጽ ሰምታ ሰላም አጥታለች! ይህና ያ ተጨማምሮ እርሷም ያለወትሮየ ” ቀን ስራ ትውላለህ ፣ እቤት ስትገባ ትጽፋለህ፣ ለእኛም ጊዜ ስጠን እንጅ ! ?” ማለት ማጉረምረም ጀምራለች ! እውነት አላት! የማለዳ ወግ መልዕክቴንም አንድ እንሁን ስል ይህው ጨረስኩ … ! ልብ ያለው ልብ ይበል !

ቸር ያሰማን !

ነቢዩ ሲራክ

posted by Tseday Getachew
Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: