Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

ኢትዮጵያዊቷን የማደጎ ልጅ በርሀብ የገደለችው አሜሪካዊት በ37 አመታት እስራት ተቀጣች

Hana’s parents broke down in tears as they get maximum sentences (+video)

 የ42 አመቷ ካሪ ዊሊያምስ የ13 አመቷን ታዳጊ ሐና ዊሊያምስን በረሀብና በብርድ በመቅጣት ህይወቷ እንዲያልፍ ማድረጓን ፍርድ ቤቱ አረጋግጧል።

የገዳዩዋ ባለቤት በ28 አመታት እንዲታሰር ተፈርዶበታል። ሌላው የ10 አመቱ የማደጎ ታዳጊ ኢትዮጵያዊም ለሌሎች አሳዳጊዎች እንዲሰጥ ተደርጓል። ፍርዱን የሰጡት ዳኛ ከፍተኛ የሚባለው ቅጣት ማስተላላፋቸውን ተናግረዋል። ሁለቱም ሰዎች ከሁለት አመታት በፊት መታሰራቸው ይታወሳል።

የስሚንቶ ፋብሪካዎች የገበያ ችግር እንዳጋጠማቸው ተዘገበ

ጥቅምት (ሃያ)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :- ሪፖርተር ዛሬ ባወጣው ዘገባ በአገሪቱ የሚገኙ ሶስቱ ታላላቅ ስሚንቶ ፋብሪካዎች በአመት 12 ሜትሪክ ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም ቢኖራቸውም በገበያ ውስጥ የሚገኘው ስሚንቶ ድምር ከ5 ሚሊዮን አይበልጥም።

አብዛኛውን ስሚንቶ የሚገዛው መንግስት ሲሆን፣ የግሉ ዘርፍ ድርሻ ቀዝቃዛ መሆኑ ተዘግቧል።

የሼክ ሙሀመድ አላሙዲን ንብረት የሆነው ደርባን ኩባንያ የዋጋ ቅናሽ በማድረግ በኩንታል 209 ብር እየሸጠ፣ ለደንበኞቹ ቤታቸው ድረስ እያደረሰ ነው። ሙገር ስሚንቶም በተመሳሳይ ለልዩ ደንበኞቹ ምርቶቹን ቤታቸው ድረስ እያደረሰ ነው።

ለሪፖርተር አስተያየታቸውን የገለጹ ባለሙያዎች ” ብዙም ግልጽ ባልሆነ ምክንያት የሲሚንቶ ገበያ እየተቀዛቀዘ መጥቷል፡፡ በዚህም ምክንያት በ2006 ዓ.ም 21 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን፣ በ2007 ዓ.ም. 27 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ሲሚንቶ አገሪቱ እንደምትፈልግ ከአራት ዓመት በፊት የወጣው ጥናት ጥያቄ ተነስቶበታል፡፡

‹‹ለሲሚንቶ ፋብሪካ ግንባታ ከፍተኛ የካፒታል ኢንቨስትመንት ፈሷል፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን የሚሰጡት ባለሙያዎች፣ ጉዳዩን መንግሥት ከሥሩ ሊያጤነው እንደሚገባ አሳስበዋል።

በዚህ ሁሉ መሀል መሰቦ ስሚንቶ ፋብሪካ 70 በመቶ የሚሆነውን ምርቱን ለአባይ ግድብ እና ለግልገል ጊቤ 3 የሀይል ማመንጫ ግድቦች በማቅረብ ላይ ነው። መሰቦ ሲሚንቶ በምን መስፈረት ለአባይ ግድብ ግንባታ አቅራቢ ሆኖ እንደተመረጠ አልታወቀም። ሙገር ስሚንቶ የመንግስት  ወይም የመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ንብረት ሆኖ ሳለ፣ እንዲሁም ለአባይ ግድብ ማሰሪያ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ  በውድም በግድም ገንዘብ እንዲያዋጣ እየተደረገ ፣ ለድርጅቱ ስሚንቶ የሚያቀርበው ሙገር መሆን ሲገባው የህዝባዊ ወያን ሀርነት ትግራይ ኩባንያ የሆነው መሰቦ ስሚንቶ ፋብሪካ እንዲሆን መደረጉ ” የኢትዮጵያ ህዝብ ያዋጣል፣ ገቢው ወደ ህወሀት ኪስ ይገባል” ሲል አስተያየቱን የተጠየቀው የኢሳት የአዲስ አበባ ዘጋቢ ገልጿል።

ህዝቡ ለአባይ ግድብ ማሰሪያ ገንዘብ እንዲያዋጣ ቢገደድም፣ ገንዘቡ በተዘዋዋሪ መንገድ ወደ ህወሀት ካዝና ነው የሚገባው የሚለው ዘጋቢያችን፣ መስፍን ኢንጂነሪንግና የወ/ሮ አዜብ መስፍን የእህት ልጅ ንብረት የሆነው ወርኪድ የተለያዩ የግንባታ እቃዎችንና የብረታ ብረት ውጤቶችን በማቅረብ ከግድቡ ከፍተኛ ገቢ እያገኙ ነው ብሎአል።

ሼክ ሙሀመድ አላሙዲን ለአባይ ግድብ ለማዋጣት 500 ሚሊዮን ብር  ቃል ቢገቡም በተለያዩ ሰበቦች እስካሁን አጠናቀው አልከፈሉም።  ዘጋቢያችን  ምናልባትም ኩባንያቸው ደርባን ለግድቡ ስሚንቶ እንዳያቀርብ በመከልከሉ ተበሳጭተው ሊሆን ይችላል ብሎአል።

የቆዳና ሌጦ አክስፖርት በችግር ላይ ነው

ጥቅምት (ሃያ)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :- የጥሬ ቆዳና ሌጦ ኤክስፖርት ባለፉት አምስት ዓመታት የተሻለ ገቢ ያስገኘ ቢሆንም ግብይቱ ኃላቀር፣ሰንሰለቱ የተንዛዛና ከፍተኛ የግብይት ወጪዎች የሚታዩበት እንዲሁም በምርት ጥራት በኣለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነቱ እጅግ አነስተኛ መሆኑን ከንግድ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ አመለከተ፡፡

የጥሬ ቆዳና ሌጦ ኤክስፖርትን በማቆም እሴት የተጨመረባቸውን የተለያዩ የቆዳ ውጤቶች ለውጪ ገበያ በመላክ የተሻለ የውጪ ምንዛሪ ለማስገኘት ጥረት እየተደረገ መሆኑን መረጃው ጠቁሞ ዘርፉን ከብክነትና ከጥራት ጉድለት ግን መታደግ ባለመቻሉ አሁንም በብዙ ችግሮች ውስጥ የሚውተረተር ሆናል ይላል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት ከዘርፉ 430 ሚሊየን ዶላር መገኘቱን ጠቁሞ ይህ ግን ዘርፉ ማመንጨት ካለበት ገቢ ጋር ሲነጻጸር እጅግ አነስተኛ ገቢ ነው፡፡

የእንስሳት እርባታው ከውልደት ጀምሮ ኃላቀርና በባህላዊ ዘዴ በመከተል የሚከናወን በመሆኑ የቆዳና ሌጦ ጥራቱ ላይ ከፍተኛ ችግር መፍጠሩን፣በእርድ ወቅትና ከእርድ በኃላ የሚከሰቱ የተለያዩ የጥራት ጉድለቶች መኖራቸው ፣የግብይት
ሒደቱ ኃላቀር ፣የተንዛዛ፣ ቅብብሎሽ የበዛበትና እሴት የማይጨምሩ ግን ዋጋ የሚያንሩ ተዋንያን የበዙበት መሆኑ እንዲሁም ለንዑስ ዘርፉ ልማት እና ግብይት ጠንካራ አደረጃጀት አለመፈጠሩ እንደችግር ተጠቅሰዋል፡፡

በሌላ በኩል የጥራት ችግር እያመጣ ባለው የውጪ ጥገኛ በሽታ አምጪ ህዋሳት ላይ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት በሽታዎቹ በሚያይሉባቸው በሰሜኑ የኢትዮጽያ ክፍል ማለትም በአማራ፣በትግራይና በአፋር ክልሎች የኬሚካል ርጭት ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ በመካሄድ ላይ መሆኑን መረጃው ይጠቁማል፡፡ ይህም ሆኖ የኬሚካል ርጭቱ በአማራ ክልል መጠነኛ ለውጥ ያሳየ ቢሆንም በሌሎቹ ክልሎች ውጤቱ እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን ያስረዳል፡፡ በዚህ ምክንያት በአሁኑ ጊዜ ተጨማሪ 25 ሚሊየን ብር በጀት ተይዞ በመላ አገሪቱ የኬሚካል ርጭቱ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሷል፡፡

ወደ አዲስ አበባ የሚጎርፉ አረጋውያን ለማኞች ቁጥር ጨምሯል

ጥቅምት (ሃያ)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :- የከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚሉት በልመና የሚተዳደሩ አረጋውያን ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በላይ ጨምሯል። አረጋውያኑም ከክልል ከተሞች ወደ አዲስ አበባ እንደሚጎርፉ ነዋሪዎች ይናገራሉ። መንግስት የገጽታ ግንባታ በሚል አረጋውያንን ሰብስቦ ወደ ክልል ቢበትናቸውም፣ አረጋውያኑ ተመልሰው በምጣት በልመናው ቀጥለዋል።

አንድ ነዋሪ እንዳሉት ቀድሞ ” አብያተ ክርስቲያናት ቅጥር ግቢ ውስጥ አይለመንም ነበር፣ አሁን ግን ልመናው ቤተክርስቲያን ውስጥ ሁሉ ሆኗል፣ ህዝቡ ጸሎት ማድረስ በማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል ” ብለዋል፡፡ በአገሪቱ የሚታየው የኑሮ ውድነት መባባስ እንዲሁም አረጋውያኑን የሚንከባከብ ድርጅት መጥፋት ለአረጋውያኑ ስደት በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።

በችግሩ ዙሪያ የአዲስ አበባን መስተዳድር ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።

የስኳር ህመምተኞች መድሀኒት የለም ተባሉ

ጥቅምት (ሃያ)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :- በዘውዲቱ ሆስቲታል መድሀኒቱን ለመቀበል ከሳምንታት በላይ ሲጠባበቁ የነበሩ የስኳር ህመምተኞች በመጨረሻ መድሀኒት የለም መባላቸውን ለኢሳት ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚሰጠው እርዳታ መቋረጥ ለችግሩ መፈጠር ምክንያት ነው ቢባልም፣ አንዳንድ ወገኖች ደግሞ የችግሩ ምንጭ መድሀኒቱ አየር ባየር ስለሚሸጥ ነው ብለዋል።

ህመምተኞች እንደሚሉት መድሀኒቱን በግላቸው ገዝተው ለመጠቀም ዋጋው የሚቀመስ አይደለም። ብዙዎቹ መድሀኒቱን ለማግኘት ባለመቻላቸው ህይወታቸው አደጋ ላይ መውደቁን ገልጸዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርን ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።

የቦሌ ሩፋኤል ቤተክርስቲያን የድረሱልኝ ጥሪ አሰማች

 

ጥቅምት ፲፱(አስራ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :- የቦሌ ለሚ ቅ/ሩፋኤል የጻዲቁ አቡነ ኤዎስጣቲዎስ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ የሆኑት መልአከ ብርሀን ተከስተ ካሳሁን “የድረሱልን ጥሪን ይመለከታል” በሚል ርእስ ለለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ረዳትና የጅማ ሀገረ ሰብከት ሊቀ ጳጳስ ለሆኑት ለ ብጹዕ አቡነ እስጢፋኖስ በጻፉት ደብዳቤ ላይ፣ የመንግስት ባለስልጣናት ቤተክርስቲያኑዋን በ7 ቀናት እንዲያፈርሱ እንዳዘዙዋቸው ተናግረዋል።

ደብዳቤው ” ቤተከርስቲያኑ ከተመሰረተ 4 አመታትን አስቆጠረ ቢሆንም በ2001 ዓም እንደማንኛውም አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተነስቶ ካርታውን በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን። በተለይም የመንግስት አካላት በተለያየ ወቅት  ቦታው ድረስ እየመጡ፣ ቦታው የኢንዱስትሪ ቦታ ስለሆነ አፍርሱ የሚል ትእዛዝ በተደጋጋሚ ደርሶናል። አሁንም በቀን 12/02/2006 ኣም በመ/ቁጥር ቦ/ክ/ከ/መዝ/9539/06 በተጻፈልን ደብዳቤ ቦታው ለልማት ስለሚፈለግ ቤተ ክርስቲያኑን በ7 ቀን እንድታፈርሱ ሲል በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 አስተዳዳር የደምብ ማስከበር አገልግሎት ጽ/ቤት አሳውቆናል።” ይላል።

ደብዳቤው በማያያዝም “  የአካባቢው ህብረተሰብ አሁን በተረጋጋ መንፈስ የጸሎት ስነስርአትና አምልኮ ስነስርአት በሚፈጽምበት ወቅት በድጋሜ መጥተው በአስቸኳይ ቤተከርስቲያኑን እንድታነሱ የሚል ትእዛዝ ማስተላለፋቸው ምእመኑን እጅግ አሳዝናል ( አስቆጥቷል)። ስለሆነም ጉዳዩ ጊዜ የማይሰጥ ስለሆነ ለብጹእ ወቅዱስነታቸው ደብደቤ እንዲጻፍልንና ቅዱስነታቸውም ለክቡር አቶ ድሪባ ኩማ የአዲስ አበባ ከተማ አስተደዳደር ከንቲባ አስቸኳይ ደብዳቤ እንዲጽፉልን ስንል በቅድስት ቤተክርስያን  ስም እንጠይቃለን ብሎአል። ከደብዳቤው ጋርም የህዝቡን አቤቱታ የያዘ 10 ገጽ ወረቀት ተያይዞ ቀርቧል።

የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ደንብ ማስከበር አገልግሎት ጽ/ቤት በ12/02/06 ለሩፋኤል ቤተከርስቲያን በጻፈው ደብዳቤ ፣ ትእዛዙን የሰጠው የቦሌ ክ/ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽ/ቤት መሆኑን ጠቅሷል። በአቶ ጌታቸው አዲስ ፈለቀ የተጻፈው ደብዳቤ ቤተክርስቲያኑ በ7 ቀናት ውስጥ ካልተነሳ አስተዳደሩ ለሚወስደው እርምጃ ጽ/ቤቱ ሀላፊነቱን ይወስዷል ብሎአል።

የአዲስ አበባ ሀገረስብከትም ሆነ የፓትሪያርኩ ጽህፈት ቤት በጉዳዩ ላይ የሰጡት ምላሽ አልታወቀም።

የኦርቶዶክስ ሀይማኖት አንዳንድ አባቶች በቅርቡ መንግስት በቤተከርስቲያኑዋ ላይ እያደረሰ ያለውን ተጽእኖ መንቀፋቸው ይታወሳል።

 

በሁለት አመታት ብቻ ከ400 ሺ በላይ ዜጎች በህገ ወጥ መንገድ ተሰደዋል

ጥቅምት ፲፱(አስራ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :- ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ባለፉት 2 ዓመታት ብቻ ከ400 ሺ በላይ ዜጎች   ሲሆን፣ በህጋዊ መንገድ የተጓዙትን ሲጨምር አሀዙ በእጥፍ ሊጨምር ይችላል።

መንግስት በቅርቡ ለስራ በሚል ወደ ውጪ በሚጓዙት ላይ እገዳ መጣሉ ይታወቃል።  የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ስምሪት ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ አበበ ሀይሌ እንዳሉት ፥ እገዳው ከተጣለባቸው ሀገራት መካከል ሊባኖስ ፣ ኳታር ፣ ሳውዲ አረብያ ፣ ኩየት ፣ የመን ፣ ሱዳንና ደቡብ አፍሪካ ይገኙበታል።

በእገዳው መሰረት ካሁን ቀደም ቪዛ ያገኙትን ጨምሮ ቪዛ ለማግኘት እየተጣጣሩ ያሉትም ቢሆን ወደ ሀገራቱ መጓዝ አይችሉም።፤ እገዳው በቤት ሰራተኝነት ተቀጥሮ ለመስራት ከሚደረጉት ጉዞዎች ባሻገር አለም አቀፋዊ ተቀባይነት ባላቸው ሙያዎች ላይ የሚደረጉ ጉዞዎችን እንደማይመለክትም  ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በመንገድ የቀረው ቀርቶ ወደ መጨረሻ መዳረሻ ሀገር የገቡት ዜጎች እጣ ፈንታ አብዛኛውን ጊዜ ስቃይና እንግልት ቢሆንም ፥ ዛሬም በዚያ የሞት ጎዳና ላይ የሚተሙ ዜጎች ቁጥር ሊቀንስ አልቻለም።

ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር  በሰጠው መግለጫ  እገዳው ከስድስት እስከ ሰባት ወራት ይቆያል።

በአገሪቱ ውስጥ እየተስፋፋ የመጣው ድህነትና ስራ አጥነት ለስደቱ ዋና ምክንያቶች ናቸው። ከፖለቲካ ጋር በተያያዘም የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር በእየጊዜው እየጨመረ መሄዱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃዎች ያመለክታሉ።

 

መምህራንን ለመቆጣጠር መንግስት አዲስ አደረጃጀት ተግባራዊ አደረገ

ጥቅምት ፲፱(አስራ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :- መምህራን ለኢሳት እንደገለጹት አደረጃጀቱ ተግባራዊ በሆነባቸው በጎንደር በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የኢህአዴግ አባላት ከሆኑ ከመምህራን አንድ፣ ከተማሪዎች አንድ ከፖሊስ አንድ እንዲሁም ከወላጆች አንድ በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚገኙ መምህራንን የቀን ተቀን እንቅስቃሴ፣ ፖለቲካ አመለካከት እና ሌሎችንም ተያያዥ ጉዳዮች ይከታተላሉ።

መመሪያው በሁሉም ትምህርት ቤቶች የወረደ ሲሆን፣ በአብዛኛው ትምህርት ቤቶች የአንድ ለአምስት አደረጃጀቱ ተግባራዊ ሆኗል።

በዚህ ድርጅት ውስጥ የሚመደቡት የኢህአዴግ አባላት ከተራው መምህር በላይ ስልጣን ያላቸው ሲሆን፣ መምህራንም እነሱን በመፍራት ሀሳባቸውን በግልጽ ለመናገር እየተቸገሩ ነው።

ኢህአዴግ በመላው አገሪቱ እየገነባ ባለው የአንድ ለአምስት  አደረጃጀት ህዝቡን ለመቆጣጠር ሙከራ ቢያደርግም እስካሁን ውጤታማ አለመሆኑን ገንባሩ ከወራት በፊት ባደረገው ጉባኤ መግለጹ ይታወቃል።

 

በታች አርማጭ በደዊ ቀበሌ አንድ የጸጥታ ባለሙያ አንዱን ግለሰብ ከእስር ቤት በማውጣት መግደሉ ተሰማ

ጥቅምት ፲፱(አስራ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :- ለኢሳት ከስፍራው የደረሰው ዘገባ እንዳመለከተው ጋሻው የቆየ የተባለው የጸጥታ አስከባሪ የ28 አመቱን  ጎሹ እያዩ የተባለውን አርሶ አደር  ከመጠጥ ቤት ውስጥ እንዲወጣ ካደረገ በሁዋላ፣ ወደ እስር ቤት ወስዶታል።

በመንግስት የተሾመው ታጣቂ ወጣት የጸጥታ ማስጠበቅ ስራ ለመስራት በሚል ለመስክ ስራ ተልኮ በነበረበት ወቅት ነው ወጣቱን ያለምክንያት ወደ እስር ቤት ካስገባው በሁዋላ፣ ከእስር ቤት አስወጥቶ የገደለው።

ገዳዩ በቁጥጥር ስር ውሎ እንደተመሰከረበት የአካባቢው ሰዎች ገለጸዋል።

 

 

የቀድሞው የፌዴራል ቤቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በሙስና ተጠርጥረው ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ።

ጥቅምት ፲፱(አስራ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :- አቶ ተፈሪ ፍቅሬ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የፌዴራል ቤቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በመሆን ከ2002 እስከ 2005 ዓመተ ምህረት ያገለገሉት አቶ ተፈሪ ፍቅሬ የፌደራል የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና አቃቢ ህግ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ክስ እንደመሰረተባቸው የዘገበው ፋና ነው።

የስነ ምግባርና ፀረሙስና ኮሚሽን አቃቤ ህግ በክሱ ፣ ተከሳሹ ህግ እና አሰራርን በመጣስና በዜጎች መካከል ልዩነት በመፍጠርና የመንግስትን መብትና ጥቅም በሚጎዳ መንገድ በመስራት፤ በጥቅሉ ከ33 ቤቶች መንግስት ማግኘት የነበረበትን 370 ሺህ 446 ብር ተቀንሶ እንዲከራይ የማድረግ ስልጣን ሳይኖራቸው ከአሰራር ውጪ እየወሰኑ በመንግስት ላይ ጉዳይ ያደረሱና ግለሰቦችን ያለአግባብ ተጠቃሚ አድርገዋል ብሎአል።

ፍርድ ቤት የግለሰቡን የዋስትና መብት ማንሳቱም ተዘግባል።

ESAT

posted by Tseday Getachew

 

 

 

 

 

Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: