Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

ተስፋዬ ገብረአብ እና የመከነ ብእሩ፡ ከቡርቃ ዝምታ እስከ የስደተኛው ማስታወሻ – መስፍን አማን (ከሃርለም፣ኔዘርላንድ)

Tesfaye Gebreab Ethiopian author and writer

ተስፋዬ ገብረአብ

ከጥቂት ሳምንታት በፊት አንድ ቅዳሜ ሻይ ቡና ለማለት አምስተርዳም ከወዳጆቼ ጋር በነበረኘ ቀጠሮ ላይ እንደአጋጣሚ ተስፋየም በመሃላችን ተገኝቶ ነበር።የባጥ የቆጡን ስናወራ፣ስለአዲሱ የተፋየ መጽሃፍ አንስቶ የውይይታችንን አቅጣጫ ቀየረው።በመሃሉ ተስፋየ፣ከመጽሃፉ ውስጥ አንዳንድ የማልወዳቸው ምእራፎች ቢኖሩ ትችቶቹን የምቀበል ስለመሆኔ አስረግጦ ጠየቀኝ?።እኔም መጽሃፋን ካነበብኩት በሁዋላ ለጥያቄው መልስ ብሰጥ እንደሚሻል ገልጨለት በዛው ተለያየን። አይደርስ የለም መጽሃፉን ለህዝብ ከመበተኑ በፊት ረቂቁን አነበብኩት። ረቂቁን አንብቤ እንደጨረስኩ ለተስፋየ ጥያቄ መልስ መመለስ እንዳለብ ወሰንኩኝ። ይሁንና በቀድሞው ዳኛ ወልደሚካኤል መሸሻ ተጽፎ የተሰራጨውን ጽሁፍ መውጣት ተከትሎ በዳያስፖራው አካባቢ አዋራው በመጨሱ ያዘጋጀሁትን ትችት በይደር ለማቆየት ወሰንኩ። በዚህ መሃል ተስፋየ ገብረአብ “የስደተኛው ማሰታወሻ” በማለት ያዘጋጀውን መጽሐፍ ባለፈው ሰሞን በነጻ አሰራጭቶልናል።

ወደ መጽሃፉ ትችት ስመለስ “በደራሲው ማስታወሻ” ውስጥ ያገኘሁት ደራሲ ኢህአዴግን ያገለግል ከነበረው ከቀድሞው ማንነቱ ያልተፋታውን ተስፋየ ገብረአብን ነበር። የእፎይታ መጽሄት ዋና አዘጋጅ እና የቡርቃ ዝምታ ደራሲን የድሮው ተስፋየን በዚህኛው የስነ-ጽሁፍ ስራ ውስጥም ዳግም አገኘሁት።የድሮው ተስፋየ ስል ታዲያ ስነጽሁፍን ለፍቅር፣ለመቻቻል፣እና ለእውቀት ሳይሆን የቆዩና የሻሩ ቁስሎችን መቆስቆሻ፣ያልነበሩትንም በመፍብረክ የእልቂት ነጋሪት መምቻ መሳሪያ አድርጎ የሚጠቀመውን ማለቴ እንደሆነ አንባቢ እንዲያስተውልእፈልጋለሁ።”የስደተኛው ማስታወሻ” የነዛ ስራዎች ቀጣይ እንጂ በይዘቱም ሆነ በመልእክቱ ጭብጥ አዲስ የስነ- ጽሁፍ ስራ ነው ለማለት የማያስደፍሩ የብዙ ምእራፎችን አካቶአል። ለዚህ የማቀርበው ምክንያት ሃያስያኑ እንደሚሉት የገጸ-ባህሪ አሳሳሉና የመልእክቱ ጭብጥ አመራረጥ እንዲሁም እንደ ደራሲ በዋነኝነት ማስተላለፍ በፈለገው መልእክት ላይ ነው።

በእርግጥም አንድ ፀሃፊ መፅሃፍ ሲፅፍ ብዙ አይነት አላማዎችን ይዞ ሊነሳ ይችላል፡፡የሚፈልገውን ሀሳብን እና ዓላማ በስነ-ጽሁፍ መልክ አንባቢውን በማስደመም የእኔ የሚለውን መልእክት ማስተላለፍ ዋነኛ አላማው ሊሆን ይችላል፡፡ሆኖም ከዓላማ ሁሉ ገዝፎ የሚታየውና የመፅሃፉን ዋጋ ከፍ የሚያደርገው ደግሞ መፅሃፉ በህብረተሰቡ ውስጥ ያሳደረው ወይንም ሊያሳድር የሚችለው ዘላቂ የሆነ በጎ ተፅዕኖ እና አዲስ ሃሳብ የማፍለቅ ችሎታው ነው፡፡ አንባቢውም መፅሃፉን ገዝቶ ሲያነብ ከደራሲው አንድ ቁም ነገር መጠበቁ አይቀርም፡፡ እናም የደራሲው ዋና ሚና የሚጠበቀውን አዎንታዊ ተፅእኖ ባማረና በተከሸነ ስነ-ጽሁፍ ለተደራሲው ማድረስ ነው፡፡የተስፋየ ገብረአብ የአሁኑን ስራ ከዚህ አንፃር ስንገመገም የምናገኘው መልእክት ሃሳዊነት እና ትንኮሳ አዘል ስነ-ጽሁፍ መሆኑን ብቻ ነው። በዚህ ፅሁፍ ለማየት የሞከርኩት በሁሉም አይነት መፅሃፍት ውስጥ ለኔ ገዝፈው የሚታዩኝን አውራ ጉዳዮችን
ነው፡፡ከዚህ አንፃር ተስፋየ ርእስ እየቀያየረ አዲስ መጽሃፍ ነው ይበለን እንጂ፣እንደ ደራሲ የሚያስተላልፍልን መልእክት ትላንትም ሆነ ዛሬ አንድና አንድብቻ ነው፣ጥላቻ እና መቃቃር። ተስፋየ ስነ-ጽሁፍን የሚጠቀመው በፍራቻ እና ጥላቻ የሚመለከተውን ማህብረተሰብ ማጥቂያ መሳሪያ በማድረግ ነው። ምናልባትም በዓለማችን የኖቤል ተቃራኒ የሆነ ሽልማት የሚሰጥ ድርጅት ቢኖር አጓዋጉል ነገሮችን በመጻፍ በሰውልጆች መሃከል ጥላቻን በማስፋፋም ተሰፋየን አለምንም ጥርጥር የዓመቱ ተሸላሚ ያደርገው ነበር።

ተስፋያዊ የገጸ-ባህያርት አሳሳል፤

በስነ-ጽሁፍ ስራዎቹ ወደሳላቸው ገጸ-ባህሪያት ስንመጣ ተስፋየ እነዚህን ልቦለዳዊ ባህሪያት ከአንዱ ወይንም ሌላው የሃገራችን ብሄርሰቦች ጋር በማዛመድ የሚፈልገውን ፖለቲካዊ መልእክት ለማስተላለፍ ሲጠቀምባቸው እናያለን። ካለትፉና ከአሁን ስራዎቹ አንድ ሁለት ብለን የተወሰኑ ምሳሌዎችን እያየን ብንመርምር የቡርቃ ዝምታው አኖሌ፣እና የስደተኛው ማስታወሻ ጫልቱ ለዚህ ተጠቃሽ ምሳሌዎች ይሆናሉ። ሁለቱንም የብሶት፣የጭቆና ሰለባዎች ያደርጋቸዋል። እንዳውም በቡርቃ ዝምታ ከሰዉ አልፎ ግኡዙን ወራጅ ውሃ (የቡርቃ ወንዝ) ቂመኛ በማድረግ የቁጭት ስሜት ለመቀስቀስ ተጠቅሞበታል።ተስፋዬ በሌላ አንጻር ከነአኖሌና ጫልቱ በተቃራኒ የሳላቸው ገጸ-ባህሪያት በቡርቃ ዝምታ ነፍጠኛው አስናቀ፣ በስደተኛው ማስታወሻ ሳምሶን ዘለቀን አንድ ማህበረሰብን ወክለው ግፍ ፈጻሚ እና የአጥቂነት ገጸ-ባህሪ ሚና እንዲጫወቱ አድርኋቸዋል።ይባሱኑ በደሎቹ በድንገት ወይንም በአጋጣሚ የተፈጠሩ ሳይሆኑ ሆነ ተብለው ታስቦባቸው መደረጋቸውን ከታሪኩ ጋር እያንደረደረ ወስዶ መደምደሚያው ላይ ይነግረናል። በዚህ “የስደተኛው ማስታወሻ” ላይ የተጠቀሰውን ብንመለከት ተስፋዮ የጫልቱን በደል አክርሮ በሚከተለውን መልኩ ይደመድመዋል፡

“እኔን የጨቆኑኝ እነማን ናቸው?” ብላ አጥብቃ ራሷን ጠይቃ ነበር። ሳምሶን ዘለቀ፣ ሽንኩርት ነጋዴው ወይስ አክስቷ? መልስ አልነበራትም። …………………….. የሆነችውን አፍርሶ፣ ያልሆነችውን እንድትሆን ያደረጋት ማነው? ይህ ስርአታዊ ሽብር (systemic Violence) ስለመሆኑ ጫልቱ ግንዛቤው አልነበራትም። የተቸገረችበት ሌላ አቢይ ጥያቄ ከፊቷ ተደቅኖባት ነበር። ሄለንነቷ እንዲህ በንኖ ከጠፋ፤ ወደ ጫልቱነትም መመለስ ካልቻለች ማንን ነው የምትሆነው? ወይም ምንድነው የምትሆነው?” ገጽ 99

ታዲያ የመጽሃፉ አንባቢ ተስፋየ እንዲህ አይነት ትረካዎች ላይ ለምን አጽንኦት ይሰጣል በማለት ጥያቄ ቢያነሳ መልሱ አንድና አንድ ነው።በብሔረሰቦች መካከል ፍርሃት እና ጥርጣሬን መፍጠር የሚለው አንደኛውና ዋንኛው መልስ ነው። ተስፋየ የሚተረካቸው ትረካዎች ችግሩን ሌላ መልክ በመስጠት ውጥንቅጡ የወጣ ማህበረሰብን የመፍጠር አላማ አድርገው የተነሱ መሆናቸውን የበዙ ምክንያቶችን በመደርደር ማሳየት ከባድ አይደለም። እንዳውም በደምሳሳው ስነ-ጽሁፎቹ ፈጽሞ መፍትሄ አማጪነት ባህሪ አይታይባቸውም። እናም እንዲህ አይነት
ሃላፊነት የጎደላቸው የፍብረካ ትረካዎች በአንዳንድ አንባቢያን ላይ የሚፈጥሩትን ስሜት ለመገመት ተመራማሪ መሆን አያሻም። የሚፈጥረው ስሜት በድርጊት ሲታገዝ ምን እንደሚከሰት መገመቱ ቀላል ነው። እዚህ ጋር መነሳት ያለበት ሌላው ጥያቄ ተስፋየ ይህን በብዙ ህዝብ ሊነበብ የሚችል ትረካ ፣ ጥሬ-ታሪክ ከየት አገኝ የሚል መሆን አለበት።በትረካው መጨረሻ ላይ እንደገለጸው የታሪኩ ምንጭ የእኔና የተስፋየ ወዳጅ ከሆነ የኦነግ አክቲቪስት ነው። ይሄ በራሱ የተስፋዬ ድርሰቶች ዓላማ ላይ ያለንን ጥርጣሬውን ውሃ እንዲያነሳ ያደርጉታል።የድርጅት
አክቲቪስት በነገረው ላይ የተስፋየ ስነ-ጽሁፍ ታክሎበት የሚቀርብ ታሪክ በአንባቢ ዘንድ፤ በተለይም ራሳቸውን እንደተጠቂ በሚቆጥሩ አንባቢዎች ዘንድ፤ ምን ስሜት እንደሚፈጥር ሁላችሁም መገመት ትችላላችሁ። በእሳት ላይ ቤንዚን እንደማርከፍከፍ ነው፡፡

ተስፋየን በሁሉም መጽሃፎቹ ውስጥ የቀረጻቸውን ገጸ-ባህሪያት ልብ ብሎ ለተከታተለ የሚያገኘው አንድ የጋራ ባህሪ አለ።እውናዊም ሆነ የፈጠራ በሆኑት እነዚህ የተስፋየ ገጸ-ባህሪያት በጨቁዋኝነት፣እና በግፈኛነት የሚሳል አንድ ማህበረሰብ አለ።በአንጻሩ ሁልግዜ ተበዳይ እና፣ብሶተኛ ገጸ-ባህሪን የሚወከል ማህበረሰብ፣ቁርሾውን እና ቂሙን እንዲወጣ በገደምዳሜ ምክር ብጤ ይሰጠዋል።ስለ ገጸ-ባህሪያቱ ካነሳን በሁሉም የተስፋየ ስራዎች ላይ የሚቀርቡ የኤርትራ (እርሱ እንደሚጠራቸው የአባት ሃገር) ሰዎች፣ ጀግንነትን እና ደፋርነትን የመሰሉ ባህሪያት አይነተኛ መለያቸው እንዲሆን ተደርገው ተስለዋልን። በተራራውን ያንቀጠቀጠው ትውልድ የአስመራ ልጆች በማለት የሚጠራቸው፣በየስደተኛው ማስታወሻ እንደ ኮለኔል እዮብ ያሉ መኮንኖችን የጀግንነት ወሰን ጥግ ላይ አድርሶ ለተደራሲው አቅርቧቸዋል። በገጽ 214-14 ላይ ሰለኮለኔሉ እንዲህ ብሎን ያልፋል፡-

“በርግጥ በቀጣዩ ቅዳሜ ከኮሎኔል እዮብ ጋር በሰፊው ተገናኘን። ለረጅም ጊዜ በተደጋጋሚ እየተገናኘን ታሪኩን አጫወተኝ።እዮብ ያወጋኝ ታሪክ በርግጥም አስደናቂ ሊባል የሚችል የኢንተሊጀንስ ታሪክ ሆኖ አገኘሁት። በቀይ ኮከብ ዘመቻ ወቅት መረጃዎች ወደ ሻእቢያ እንዴት ይተላለፉ እንደነበር በዝርዝር ሲተርክልኝ በመደነቅ ነበር ያዳመጥኩት። በዚህ ቅፅ ዝርዝር ታሪኩን ልፅፈው ግን አልቻልኩም። በሰማሁት ታሪክ ውስጥ ከደርግና ከሻእቢያ ባለስልጣናት በህይወት ያሉ በርካታ ሰዎች ስማቸው ይነሳል። ስማቸው የሚነሳ ሰዎችን በማነጋገር መረጃዎችን ማዳበር እና ማረጋገጥ እንዳለብኝ ስላወቅሁ፣ ዝርዝሩን ለማዘግየት ተገደድኩ። ወደፊት “የስለላ ስራ” በሚል ርእስ እተርከው ይሆናል…”

ገጽ214-15.

ከዚህ በመነሳት የሚቀጥለው የተስፋየ መጽሀፍ በሻእቢያ የስለላ ታሪክ ላይ ሊያተኩር እንደሚችል መገመት እንችላለን።ይህ የሚሆን ከሆነ አለምዓየሁ መሰለ በራሱ ተስፋዮ ገብርአብ ላይ የሰራውን አስደናቂ የስለላ ስራ የመጽሃፉ አካል ቢያደርገው የመጽሃፉን ውበት እና ሚዛናዊ ጸሃፊነቱን ያሳየናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ይህንን ካልሆነ ደግሞ ያው ተስፋየ ነው
ብለን እናልፈዋልን።

የስነ ስሁፍ ምሁራን እንደሚሉት፤ ገጸ-ባህሪያት አብዛኛውን ግዜ የደራሲው ፍላጎት እና ምኞት ነጸብራቆች ናቸው። ባህርያቸውን የሚወስዱት ከደራሲው ፈጣሪያቸው ነው።ደራሲው ገጸ-ባህሪያቱን የሚፈልገውን መልእክት ለመናገር ይጠቀምባቸዋልና።”የስደተኛው ማስታወሻ” ደራሲ ተስፋየም ያደረገው ይህንኑ ነው፡፡ የጫልቱን ታሪክ ያነበበ ማንም በቁጭት ስሜት እንዲነሳ መገፋፋቱ አይቀርም።ስነ-ጽሁፍ ከባድ የሆነ ሃይል አለውና።ምናልባትም ለዚያ ይሆናል ከታሪክ ነጋሪው የበለጠ አጡዞ በጫልቱ ውስጥ ብቅ እያለ የሚያስደምመን፡፡ ይህም በገጸ-ባህርያቱ በኩል የራሱን የደራሲውን ፖለቲካዊ መልእክት እንድናይ ያደርገናል።

በ“የስደተኛው ማስታወሻ”መጽሐፍ የተስፋየ ስደት ግለታሪክ፣ ሌሎች አጋጣሚዎች እና የአንዳንድ ሰዎች ትረካ ጭምር ተዳሷል። የስደት ተሞክሮዎችና ከስደት ህይወት ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ታሪኮች፣ በመጽሐፉ ተሸፍነዋል። እነዚህም ተስፋየ በተግባር የተሳተፈባቸው ድርጊቶች ብቻ ሳይሆኑ በሰሚ ሰሚ ያገኛቸውን መረጃዎችን ይጨምራል።ከዚያም ባሻገር በሰበብ አስባቡ ምክንያት እየፈለገ በመኮርኮም ታሪካቸውን በማኮስመን ስነ-ጽሁፍን ታሪክን የማዛባት ወይም የመደለዝ ተልእኮው መሳሪያ ሲያደርግ ይስተዋላል፡፡

የፍስሃጽዮን ፖለቲካ ወይስ የተስፋየ ገብረአብ ፖለቲካ፣

ተስፋዬ በመጽሐፉ ውስጥ “የፍስሃፅዮን ፖለቲካ”በተሰኘ ርእስ ስር የማይገናኙ ታሪኮችን በመጠቃቀስ ታሪክን የማጠልሸት ሙከራ ሲያደርግ ይታያል። ተስፋዬ በ”የስደተኛው ማስታወሻ” ውስጥ አለምንም አመክንዮ የፍስሃጽዮንን ገድል በዚህ አይነት ሁኔታ ልናምነው እንችላለን ወይ? እያለ ሲጠይቅ ይስተዋላል። አንባቢ የእርሱንም ሃሳዊ የሆኑ ታሪኮች እንዲህ ቢጠይቅ ተገቢ ሊሆንም ይችላል። ይህን የምልበት ምክንያት የፍስሃጽዮን (የአቡነ ተክለሃይማኖት) ታሪክ ከስደት ማስታወሻ ጋር ሊያናኘው የሚችል አንድም ምክንያት አልታይህ ስላለኘ
ነው።ያም ቢሆን ነገሩ ከታሪክ ግምገማነት አይን ይታይ ቢባል እንኳ፣ ተስፋየን በቅርብ የምናውቅ ሰዎች የታሪክ አጠናን ዘዴ ብቃቱ እንዲህ ላለ ስራ እንደማያበቃው አፍ ሞልቶ መናገር ይቻላል።ለዚህም በርካታ ምክንያቶች አሉን።አንደኛ ተስፋየ ሃሳዊ የፕሮፓጋንዳ ሰራተኛ እንጂ የታሪክ ተመራማሪ አይደለም ።ሁለተኛው በከዚህ ቀደሞቹ ስራዎቹ ሲገመገም ተስፋየ እንደ አጥኚ ሚዛናዊ በሆነ አይን ታሪክን ይመለከታል የሚለውን መከራከሪያ የሚያስተውን የበዙ ምክንያቶች አሉ። ሶስተኛው አንዳንድ ትረካዎቹ ላይ እንዳየነው የምንጭ አጠቃቀም ዘዴው መደዴ የሚባል አይነት ነው። ከነዚህ ምክንያቶች በመነሳት ተስፋየ ታሪክን የፈልገው ለመደለዝ ወይንም ማደፍረስ እንደሆነ እንረዳለን።

ከዛ ይልቅ ተሰፋየ ያተኮረው በታሪኩ ሂደት ላይ ሳይሆን አቡነ ተክለሃይማኖትን ጨምሮ አብዛኞቹ ሃገር በቀል ጻድቃን ለምን የአንድ አካባቢ ሰወች ሆኑ የሚለው ጉዳይ ነው ከመልእክቱ ጎልቶ የወጣው ክፍል። ለዚህ ደግሞ የዳኛቸው ወርቁ አደፍርስን በማናገር ምክንያቱን ለማጠናከር ሞክሮአል።ይቀጥልናም እራሱን ለመከላከል የሃገራችንን ደፋር ጸሃፍያንን ስም በማንሳት እነሱ የዛ አካባቢ ሰዎች ሰለሆኑ ዝም ተባሉ፣ሌላ ሰው ቢጽፈው ግን ሌላ ይባላል ለማለት ላይ ታቸ እያለ ምክንያት ፍለጋ ሲንከራተት ይታያል፡-

“ከዳኛቸው ወርቁ በመቀጠል አቡነ ተክለሃይማኖትን የተቹ ሁለት ብእረኞች ብቅ ብለው ነበር። ፅጌ ስጦታው እና በእውቀቱ ስዩም። በአጋጣሚ አሁንም ሁለቱም ብእረኞች አማራና ኦርቶዶክስ በመሆናቸው አጃንዳው እንዳይጋነን አድርጎታል።” ገጽ317

እርግጥ ነው፣ ተስፋየ እዚህ ጋር የሳተው ቁም ነገር በደፋር ጸሃፊና በሃሳዊ ጸሃፊ መሃከል ያለው ልዮነት የሰማይና
የምድር ያህል መሆኑን ነው።ደፋር ጸሃፈያን የሚጽፉት እውነትን ለመፈለግ፣ከተቻለም የተዛባውን ለማረም ነው። ሃሳዊ ወይንም ተንኳሽ ጸሃፍያን ግን ቁርሾን ለማስፋትና ታሪክ ላይ ውንብድና ለመፈጸም እስከሆነ ድረስ የመልእክታቸው ተቀባይነት ምን ግዜም በጥርጣሬ መተጽር ውስጥ መውደቁ አይቀርም።በኛ ሃገርም ታሪካዊና ታሪክ ቀመስ ልቦለዶችን ያስነበቡን ደራሲያን ጥቂት አይደሉም፡፡ በተለይ ደራሲ ብርሃኑ ዘርይሁን እና፣ ሃዲስ ዓለምአየሁ የስርአት ችግርን ነቅሰው በማውጣት ህብረተሰብ ወደፊት እንዲራመድ በስነ-ጽሁፋቸው ደፍረው አስተምረዋል።

ህብረተሰቡን አቅጣጫ በማሳየታቸው፣ስነ-ጽሁፋቸው የሃገራችን ዘመን አይሽሬ ስራ ለመባል በቅቷል። ሌላው ለአቡነ ተክለሃይማኖት የቅድስና ክብር የሰጠችው የግብጽ ቆፕት ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ እንጂ ሌላ አይደለም።እንዲህ ለማድረግ ደግሞ ቆብጦቹ ረጅም የሆነ የማጣራት ስነ-ስርአት አላቸው።ወደ አሌክሳንድርያ ብቅ ካልክ በስማቸው የተሰየመ ትልቅ ቤተክርስትያን ስላለ ኤዛ ቋሚ ምስክር ታገኛለህ።በኋላም አምስቱ የኦርየንታል (ምስራቃውያን) አብያተ ክርስቲያናት የቆፕጥ ቤተክርስቲያንን ውሳኔ ተቀብለው በክብረ በዐላቶቻቸው መዝገብ ውስጥ አሰገብተዋቸዋል።

ባለበት የእውቀት እጥረት ምክንያት ተስፋየ አላነበበ ይሆናል እንጂ ከደርዘን በላይ እውቅ አለማቀፍ የጥናት ስራዎች እና የዱክትርና መሟያ ምርምሮች በጠቀስከው የፍስሃጽዮን ታሪክ ላይ ተሰርተዋል።ሁሉም ባይሆኑ አንዳንዶቹ ምክንያታዊ የሆነ ሂሳዊ ግምማቸውን ከአሳማኝ መላምት ጋር አቅርበዋል።እንደነዚህ ያሉ ጥናቶችን ለምን በፈረንጅ፣ በተለይም ጣልያናዊ በሆኑ የካቶሊክ እምነት ተከታይ ተጻፈ የሚል ትችት እስካሁን አልገጠመኝም።ልክ እንደ ፍስሃጽዮን ሁሉ አባት ሃገር ከምትለው ሰራዬ አካባቢ በወጡት አባ አውስጣቴዎስ (ቤተ- አውስጣቴዎስ) ላይም ብዙ ተጽፎአል። ታሪክ በባለሙያውና በትክክለኛው መንገድ ከተጠና ሁላችንም ያለፈ ጉዞአችንን እንድናይበት በር ይክፍታል እንጂ ጉዳት የለውም። በተስፋየ መጽሃፍ ውስጥ የሚገኙ ትረካዎች ግን አስፈላጊነታቸው እና ያላቸው የብቃት ደረጃ ጥያቄ ውስጥ የሚወድቁ ብቻ ሳይሆኑ የሃሳዊነት እና የትንኮሳ ባህሪ ስላላቸው ነው ከደፋር ጸሃፍያን ወይንም ከታሪክ ተመራማሪወች የሚለዩት።

ታሪክን በማዛባት ረገድ ተአማኒነት ይጎድላቸዋል ከምላቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ተስፋየ ስለ አጼ ቴወድሮስ አሟሟት እስካሁን ካነበብነውና ከሰማነው የተለየ አዲስ ታሪክ ይዞ ብቅ ማለቱ ነው፡፡ወርቂቱ የተባለች የወሎ ሴት ባላባት ገደለችው ከሚለው የታሪክ ውሽት በተለየ መልኩ፣ አሟሟታችው ላይ አዲስ ነገር ጭምሮ ብቅ ብሎአል። በይፋዊው ታሪክ ላይ የተዘገበው በገዛ እጃቸው ህይወታቸው ማጥፋታቸውን ሲሆን፣ይህንን በቦታው የነበሩ የናፔር ዘመቻ ተሳታፊ ወታደሮች ሳይቀሩ አረጋግጠዋል።እንዳውም አንዱ ወታደር በጻፈው ግለ-ታሪክ አስከሬናቸው በወራሪው የእንግሊዝ ጦር የክብር አቀባበር ተደርጎለት እንደነበረ የአይን ምስክርነቱን ሰጥቶአል። ይሁንና ተስፋየ የንጉሱን አሟሟት እንዲህ በማለት ጽፎታል፡-

“አጤ ቴዎድሮስ ራሱን ሲገድል አስተካክሎ ባለመተኮሱ ነፍሱ ሳትወጣ ጥቂት ተሰቃይቶአል። እንግሊዞች ደርሰው፣ መሬት ለመሬት እየጎተቱ ሲያንገላቱት ጭምር ቴዎድሮስ ህይወቱ ነበረች። ልብሱን አውልቀው ራቁቱን አድርገው በሚጠሉት ወገኖች ሲያስደበድቡት ግን የቋረኛው ንጉስ ህይወት አለፈች።”ገጽ390

ይህ ምን እንደሚባል አንባቢ የራሱን ፍርድ ቢሰጥ የሚሻል ይመስለኛል። ” የስደተኛው ማስታወሻ” እኩይ ለሆነ አላማ ታሪክን የማንጋደድ ስራ ጥሩ ማሳያ ነው የምለውም ከዚህ የተነሳ ነው።በእርግጥም ደራሲው በተራ ቋንቋ ሃሳቡን በቀላሉ በመግለጽ የታሪክ መሰረት የሌላቸውን ክስተቶች እዚህም እዛም በማስገባት ትውልድን የማሳሳት ሃሳዊ ስራውን ተወጥቶበታል ማለት ይቻላል፡፡

የተስፋየ ሃሳዊ ብዕር በአንድ በኩል የሃገራችንን ታሪክ ማደብዘዝ መደለዙን ስራየ ብሎ መያዙን እንዳየነው ሁሉ በሌላ በኩል አባት ሃገር ብሎ የሚጠራትን ኤርትራ፣ በአሁኑ ወቅት ያለው እውነታ እየታወቀ አንድም ነገር ለማለት አለመድፈሩ ሚዛናዊ ሃቀኛ የሰ-ነጽሁፍ ሰውነት ጥያቄ እንዲነሳበት በር ይከፍታል።ተስፋየ በሆላንድ የመኖሪያ ፈቃድ ካገኘ በሁዋላ ለበርካታ ግዜያት ወደ አባት ሃገር ኤርትራ ቢመላለስም የነገረን ከተገመተው በታች ነው። አስታውሳለሁ፣ በቀደምት ስራዎቹ ስለኤርትራ ለምን አንዳልጻፈ? ስጠይቀው፣የሰጠኝ ምክንያት ‘ስለኤርትራ ምንም የሚያውቀው ነገር ስለሌለ ነው’ የሚል የነበረ።ሆኖም ተስፋየ በዚህኛው “የስደተኛው ማስታወሻ” ጥቂት ምዕራፍ ሰጥቶ ስለ አባት ሃገር ኤርትራ አንዳንድ ነገሮችን ለማንሳት ሞክሯል።ይሁንና ስለኤርትራ ትንሽም ቢሆን በጻፈባቸው ምዕራፎች የተገለጸው፣ በዐለም መናኛ ብዙሃን ከምናውቃት ኤርትራ ጋር የማይመሳሰል ነው።ይህ ብቻ
ሳይሆን “የስደተኛው ማስታወሻን” በሻእቢያ የጦርነት ጅብዱዎች ገድል ዙሪያ እንዲያጠነጥን አድርጎታል። ይህ የኢትዮጵያን ፖለቲካ፣ ታሪክ እንዲሁም የህዝቦች ግንኙነት አሉታዎ ገጽታውን የማናር ትረካው፣ አባት ሃገር ኤርትራን ለመግለጽ ከተጠቀመበት ስልት ጋር ሲነጻጸር ጉልህ የሚዛናዊነት ችግር እንዳለበት ያሳያል።

ሲጠቃለል፣

“የስደተኛውን ማስታወሻ”ስራ ጥሩ መጽሃፍ እንዳይሆን ካደረጉ በርካታ ምክንያቶች አንዱና ዋነኛው የመልእክቱ ጭብጥ ሃሳዊነት እና ተንኩዋሸ ባህሪ ስነ-ጽሁፋዊ ፋይዳውን አሳጥቶታል።ይህ ብቻ ሳይሆን ጸሃፊው ባሳየው ሚዛኑን የሳተ የአጻጻፍ ስልት ስነ-ጽሁፉን አጠወልጎታል፡፡ በ”የስደተኛው ማስታወሻ” ላይ የተወሰነ ስነ-ጽሁፋዊ ውበት ብናይም ፣ጸሃፊው ለማስተላለፍ የሚፈልገው የፖለቲካ መልእክት፣ እንዲሁም ህዝብና ህዝብን አናካሽ በሆነው የአጻጻፍ ስልቱ ምክንያት የስደተኛው ማስታወሻ ከመከኑ የስነ-ጽሁፍ ስራዎች ተርታ እንዲመደብ አድርጎታል።

http://ecadforum.com

posted by Tseday Getachew

 

Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: