Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

የኢትዮሚዲያ ወቅታዊ መፈክር (ክፍሉ ሁሴን)

ethiowaga.gif

ክፍሉ ሁሴን

“ከ40 ግድብ አንድ የቀይ ባሕር ወደብ!”የኢትዮሚዲያ ድረገጽ የወቅቱ መፈክር ነው።ከመፈክሩ ጋር ወይም በመፈክሩ ላይ ምንም ችግር የለብኝም።ይልቁንም ወያኔ ከሌሎች ክፉ ነገሮች በተጨማሪ ወደባችንን አስበልቶ በምድር ብቻ ተቀርቅበን የቀረን አገር ስላደረገን እስከ ዛሬ ድረስ ከሚንገበገቡት ኢትዮጲያውያኖች አንዱ ነኝ።የባሕር በር ባለቤትነታችን በእኔ እድሜ እንኳ ባይመለስ ቢያንስ የባሕር በር እንድናጣ ባደረጉን ዋና ዋና ከሃዲዎች ላይ በአገር ክህደት ወንጀል ክስ ሲመሰረት በሕይወት ዘመኔ ለማየት ከፍተኛ ጉጉት አለኝ።በነገራችን ላይ በዚህ ክስ በቀንደኛነት እንዲካተቱ ከምፈልጋቸው ሰዎች ውስጥ አንዱ መንግስቱ ኃይለማሪያም ወልዴ ነው።ስለምን?በዋናነት የተበላነው እሱ የ”አብዮታዊ ጦር ጠቅላይ አዛዥ”በነበረ ጊዜ ነውና።

ከላይ የጠቀስኩትን የኢትዮሚዲያን ወቅታዊ መፈክር ተንትርሶ አንድ ራሱን ጋሻው አባተ ብሎ የሚጠራ አንባቢ ከፕሪቶሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ በጻፈው ደብዳቤ ኢትዮሚዲያን አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ ብሎ ካሞካሸና እነተስፋዬ ገብረአብን (ገብረ እባብ–ጋሻው እንዳሰቀመጠው) ጭምብላቸውን ገሽልጠሕ ስላጋለጥክልን እናመሰግናሃለን ገለመሌ ካለ በኋላ፤ ግን “ወደባችንንም አጥተን ግድብ አይኑራችሁ ነው ወይ የምትለው?” ብሎ መፈክሩ ችግር እንዳለበት በሻዕቢያዊ መሰሪነት ይሁን ወይም ስለ”ልማት” በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፕሮፓጋንዳ ሆዱ እንደተነፋ “ልማታዊ”ደንቆሮ ይሁን የመሰለውን ብሏል።

“Remove Assab! What? Reader vs Ethiomedia”በሚል ርዕስ ድረገጹ የለበደውን ፅሁፍ ይመልከቱ።

የኢትዮሚዲያ ዋና አዘጋጅ ለአስተያዬት ሰጪው “ጋሻው” ከሰጠው ምላሽ ውስጥ አንዳንዶቹ ነጥቦች ትኩረቴን በመሳብ ሌላ ቦታ ያነበብኩትን እንዲሁም በሕይወት ዘመኔ ያስተዋልኩትን እንዳስታውስ ስላደረጉኝ ይህን ለመጫር ተነሳሁ።ኢትዮሚዲያ በመፈክሩ ላይ የጸና አቋም እንዳለውና መፈክሩም በድረገጹ አናት ላይ ጎልቶ መታየቱን እንደሚቀጥል ካተተ በኋላ “በህዋሃት ውስጥ እውነተኛ ስልጣን በትግራይ ልጆች ሳይሆን እንደ መለስ ዜናዊ፣ስብሃት ነጋ ወዘተ በመሳሰሉ የለየላቸው ኤርትራውያን ቅጥረኞች እጅ”እንደነበረና ከሻዕቢያ ጋር የነበረውን መሞዳሞድ የተቃወሙ አንዳንድ የህዋሃት አባላት ምናልባትም እንደዋና አዘጋጁ አገላለጽ አንድምታ “ንጹህ የትግራይ ልጆች”በ”ለየላቸው ኤርትራዊያኖች”እጅ ተገድለዋል፤ወይም ተገልለዋል።

ትልቁ ችግሬ እዚህ ጋር ነው።ማነው ንጹሕ የትግራይ ልጅ? ማነው ንጹሕ የኤርትራ ልጅ?ሁለቱም ቡድኖች ወይም ከሁለቱም ክፍለሃገሮች ተወላጅ ነን የሚሉ የዚያን ጊዜ ልሂቃን በጎሳ ወይም በክፍለሃገር ጠባብ ስሜት ተከታትለው በመነሳትና በመደጋገፍ ጎሳን ወይም ክፍለሃገርን ብቻ “ነፃ” ሊያወጡ ነው የተነሱት እንጂ የኢትዮጲያን ሕዝብ በማስተባበር በኢትዮጲያ የግፍ ስርዓት እንዲቀር አልታገሉም።እነሱ የጀመሩትና የሰበኩት የክህደትና የጎሳ በሽታ ዛሬ ስር ሰዶ ከዘር ወይም መንደር ነፃ አውጪነት በላይ ማሰብ በኢትዮጲያ “ፖለቲካ” እጅግ አዳጋች ሆኗል።በበኩሌ ለኢትዮጲያ ባህር በር ማጣት ከሻዕቢያ እኩል ወያኔን እንዲሁም ላይ እንደጠቀስኩት የደርጉን ቁንጮ መንግስቱን ኃ/ማሪያምንም ጭምር በኃላፊነት እይዛለሁ።በእኔ መጽሃፍ በተለይ በዚያን ጊዜ በጎሳ “ነፃ አውጪነት”የተሰባሰቡት ሁሉ በአገር ክህደት የሚፈረጁ ናቸው።በተቀር ትግሪኛ ተናጋሪ ወገኖቻችንን በተመለከተ አንዱ የአገራችን ክፍል በፋሺስት ጥልያን ተቆርሶ ስለተወሰደብን ግማሾቹ ከኛ ጋር ሲቀሩ ሌሎቹ ከመረብ ወንዝ ወዲያ ማዶ በፈረንጅ ባላንጣ እጅ በመክረማቸውና በዚህና በሌላ ውሉ በደንብ ባልለየ ምክንያት እርስ በርስ ከሚናናቁ በቀር በመካከላቸው በደግም ሆነ በክፉ ብዙ ልዩነት በበኩሌ አይታየኝም።

በትግራይና በኤርትራ የሚገኙ ትግሪኛ ተናጋሪዎችን አንድ መሆንና ግራ የሚያጋባ ስር የሰደደ መናናቅ እና መጠላላት በአምባሳደር ዘውዴ ረታ ‘በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የኤርትራ ጉዳይ ‘መፅሃፍ ላይ በገጽ 376-377 ላይ የሰፈረው የተድላ ባይሩና የወልደአብ ወልደማሪያም የከረረ ንግግር አመላካች ነው።ከብዙ በጥቂቱ ልጥቀሰው።

“አንድ ጊዜ በአስመራና በምፅዋ መካከል በሚገኘው “ቤተ ጊዮርጊስ”በተባለ ሥፍራ፤ጥቂቶች ያገር ፍቅር ማህበር መሪዎችና አባሎች ተሰብሰበው ሲወያዩ፣ተድላና ወልደአብ የተለዋወጧቸው ቃላቶች የሁለቱን ሰዎች በሀሳብ መራራቅ ብቻ ሳይሆን፣መጠላላታችውንም በትክክል ያሳያል።እንደተለመደው ወልደአብ ወልደማሪያም፣ኤርትራ ከኢትዮጲያ ጋር የምትቀላቀለው በሕግ በተደነገገ ውል መሆን አለበት፣የሚሉትን ሀሳብ እየደጋገሙ ይናገራሉ።የአንድነት ማህበር ዋና ጸሐፊ ደግሞ፣ተለያየተው የኖሩ እናትና ልጆች ብዙ እፍዳ ደርሶባቸው፣ከብዙ ዓመታት በኋላ ሲገናኙ ምን ውል ያስፈልጋቸዋል?በማለት ለማስረዳት ሲሞክሩ፣ወልደአብ ፊታቸውን አጥቁረው ለማዳመጥ የማይጥማቸው መሆኑን ያሳያሉ።በዚህ ጊዜ ተድላ ግልፍ ይላቸውና፣ኧረ ለመሆኑ መሠረተ ትውልድዎየት ነው?ብለው ይጠይቋቸዋል።ትውልዴ አክሱም አጠገብ ከምትገኝ “ዓዲ ክልተ”ከምትባል ቀበሌ ነው ብለው፣ወልደአብ ይመልሳሉ።አቶ ተድላ ቀጠል ያደርጉና፤ትውልድዎ አክሱም ከሆነ፣ታዲያ የኤርትራ ጉዳይ ምን ይመለከትዎታል?ይሏቸዋል።ወልደአብ በገነፈለ ስሜት “—–እንኳንእኔአክሱምአገሬ፤በኩረሎሚየሚሸተውትውልዴቀርቶ፤ከናይጄሪያየመጣጀዓሊ፣ከየመንየመጣጀቦሊ፣በኤርትራኖሬአለሁብሎ፣ስለኤርትራእድልለመናገርችሎየለምወይ?—ብለው መለሱላቸው።”

ወልደአብ ወልደማሪያም የመጀመሪያውና አንጋፋው የኤርትራ ግንጠላ አራማጅ እንደሚሉት “ንጹሕ”የአክሱም ተወላጅ ከሆኑ ኢትዮጲያን ያለ ባህር በር ባስቀረው የአገር ክህደት ወንጀል ላይ ከመረብ ወዲያ ማዶ ብቻ ተወለዱ የምንላቸውን “የለየላቸውን”የኤርትራ ልጆች ብቻ ለመወንጀል አይመችም።የጉዳዩ ውስብስብነት ሰለሞን ዴሬሳ እንዳለው የጦርነትና የፍልሰት ታሪክ ባጥለቀለቃት ኢትዮጲያ ውስጥ “የጠራሁ አማራ፤የጠራሁ ኦሮሞ፤የጠራሁ ትግሬ ማለት ጥጋብ ነው”ሲል የተናገረውንም ያስታውሰናል።ያውም ሰማይን በማሽቀንጠር እግዜሩን ካራቀብን የበቅሎ እርግጫ የባሰና አሁን በቀድሞ ኢትዮጲያውኖች ወይም በኤርትራውያኖች ላይ መዓት እንዳመጣው አይነት ሌላ መዓት የሚያስከትል ጥጋብ።

የመዋዠቅ መብት

የኢትዮሚዲያን የወቅቱን መፈክር ሳነሳ እስከ ቅርብ ጊዜ የነበረው የቀድሞ መፈክሩ ትክዝ አለኝ።ህዋሃት ሊታደስ አይችልም።ልክ እንደ አፓርታይድመፍረስ ነው ያለበት።የሚል ነበር።ታዲያ በቅርቡ ኢትዮሚዲያ ከዚህ መፈክሩ በተጻራሪ ሁኔታ ከመለስ ዜናዊ ሞት በኋላ ደብረፅዮን የመሳሰሉትን አይነት ሰዎች የህዋሃት አዳሽ አድርጎ በማቅረብ ወያኔዊው አገዛዝ የመታደስ ተስፋ እንዳለው በርዕሰ አንቀፅ መልክ በማስቀመጥ ያሳየው የአቋም መዋዠቅ አግራሞትን ፈጥሮም እንደነበር ትዝ ይለኛል።

ዛሬ ላይ ሆኜ ሳስበው እጅግ አድርጎ መርገምት የተጠናወተው የኢትዮጲያ “ፖለቲካ” እንዲህ ያለ መዋዠቅ ቢያስከትል ሊያስገርመንም ሊያናድደንም እንደማይገባ፤ይልቁንም ኢትዮጲያ የተባለችውን መሰረታችንን እስካለቀቅን ድረስ በዚያው መሰረት ላይ ሆነን በተስፋ እና በተስፋ መቁረጥ መካከል ብንዋዥቅ ሊበረታታ እንደሚገባ፤መዋዠቃችንም ተስፋ ባደረግን ጊዜ እንደ ስዬ፣ብርሃኑ፤ነጋሶ፤ልደቱ፤እስክንድር፤ዳዊት ወዘተ የመሳሰሉ ግለሰቦችንም ጭምር እስከማምለክ ወይም ሰማይ ድረስ እስከ መቆለል ሊወስድን እንደሚችል፤ ተስፋ ስናጣ ደግሞ እርስ በርስም ሊያዘረጣጥንም እንደሚችልና ይህም በኛ ብቻ የሚታይ ሳይሆን በሌሎችም አገር ሕዝቦች ላይ የሚታይ መሆኑን በማወቅ የ”መዋዠቅ መብታችንን”ተጥቅመን ከስህተታችን ትምህርት እየወሰድን መቀጠል እንችላለን።ዋናው ቁም ነገር ግን መረጃ በመስጠት ተግባር ላይ ተሰማርተናል የምንል ሰዎች ከመዋዠቃችን በፊት–ምንም እንኳ ሰዎች እንደመሆናችን ባንዳንድ ጉዳይ እኛም ከመዋዠቅ ባናመልጥም—በጥንቃቄ ማሰብና መመርመር ይጠበቅብናል።ከዚህ አንጻር ኢትዮሚዲያ ልክ ህዋሃት ሊታደስ አይችልም ባለበት አንደበቱ በህዋሃቱ ውስጥ ጥርሳቸውን የነቀሉና ሌላ ሕይወት የማያውቁ ሰዎችን ከመለስ ሞት በኋላ ሊያድሱን ይችላሉ እንዳለው አይነት መዋዠቅ ነገ ተነስቶ ወደብ ባይኖረንም ግድብ ይበቃናል እንደማይል ተስፋ አለኝ።

እኔም ዋዠቁ መሰለኝ። መሰረታችን ኢትዮጲያ እስከሆነች ድረስ በኢትዮጲያ ጉዳይ  የመዋዠቅ መብት የማይጠበቅበት ምን ምክንያት አለ?ቅንነቱ እስካለ ድረስ ዋዥቀን ዋዥቀን ረግተን መቆማችን አይቀር።

Email;kiflukam@yahoo.com

Twitter;@Hussainkiflu

http://ecadforum.com/

posted by Tseday Getachew

Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: