Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

በአዲስአበባ ከተማ የማጅራት ገትር ወረርሽኝ በአዲስ መልክ ተቀሰቀሰ

ESAT

 ኢሳት ዜና :- በአዲስ አበባ ከተማ ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር 2005 አካባቢ ተከስቶ የነበረው ማጅራት ገትር ወረርሽኝ እንደገና በአዲስ መልክ በመቀስቀሱ የክልሉ ጤና ቢሮ ሕዝቡን የመከተብ ስራ ላይ መጠመዱ ተሰማ፡፡

ክትባቱ በሁሉም ጤና ጣቢያዎች በመሰጠት ላይ ሲሆን ክትባቱን መውሰድ ያለባቸው ደግሞ ዕድሜያቸው ከ30 በታች የሆኑ ነዋሪዎች ብቻ መሆናቸው ለምን የሚል ጥያቄ አስነስቶአል፡፡ ምንጮቻችን እንደሚሉት መንግስት የገጠመውን የመድሃኒት ዕጥረት ለመቅረፍ የወሰደው ዘዴ በዕድሜ ገደብ ክትባቱን መስጠት እንዳስገደደው ጠቁመዋል፡፡

ከአዲስአበባ ጤና ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው ግን የማጅራት ገትር በሽታ ሁሉንም ሰው የሚያጠቃ ቢሆንም ዘጠና በመቶ የሚታየው
ዕድሜያቸው ከ2 አስከ 30 ዓመት ባሉት ላይ ብቻ መሆኑን በመጥቀስ እድሜያቸው ከ30 በላይ የሆኑት ያልተካተቱት ተጋላጭ ባለመሆናቸው እንጂ መድሃኒት ባለመኖሩ አይደለም ይላል፡፡

የማጅራት ገትር ሕመም በተዋህሲን አማካይነት ተከስቶ የአንጎልን ህብለሰረሰር በተለይ ከራስ ቅል በታች ያለውን የሰውነት ክፍል የሚያጠቃ ሕመም ነው፡፡

በባክቴሪያ አማካይነት የሚከሰተው ማጅራት ገትር በሽታ በወረርሽኝ መልክ
የሚተላለፍ ፣ በምድር ወገብ አካባቢ በሚገኙ አገራት በ10 ዓመት አንድ ግዜ የሚከሰት ሲሆን በኢትዮጽያ በ8 ኣመት አንድ ጊዜ እንደሚከሰት ከአ/አ ጤና ቢሮ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

በሽታው በባክቴሪያ ወይም በቫይረስ አማካነት የሚመጣ ሲሆን ዋናው የበሽታ ምልክት የአንገት መቆልመም፣ ትኩሳት፣ብርሃንን ለማየት መቸገር በዋንናነት ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይ በሕጻናት ላይ አናታቸው አካባቢ የማበጥ፣የማቅለሽለሽ ፣ትኩሳት ፣አእምሮ መሳት፣የቅዥትና የመሳሰሉ ምልክቶችን ያሳያሉ፡፡

የአማራ ወጣቶች የጋራ ንቅናቄ ሶስት የአማራ ክልል አመራሮችን ማገቱን አስታወቀ

ጥቅምት ፲፭ (አስራ አምስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም

ኢሳት ዜና :-

የአማራ ወጣቶች የጋራ ንቅናቄ በአማራ ክልል ላኩማ ወረዳ ሁለት የሚሊሽያ ሀላፊዎችንና አንድ የወረዳ አስተዳዳሪን በቁጥጥር ስራ ማድረጉን ገለፀ፡፡

ንቅናቄው ሰሞኑን 22 የፖለቲካ አመራሮች በላኩማ ወረዳ በሚገኘው በሰላ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ በስብሰባ ላይ እንዳሉ በቁጥጥር ስር ካዋለ በኋላ መልቀቁን ገልጾ ሶስቱን አመራሮች ግን አሁንም ድረስ በቁጥጥር ስር አድርጎ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

የተያዙት አመራሮች በቁጥጥር ስር ውለው ከነበሩት ፓለቲከኞች ዋነኛ እና የአካባቢውን ህብረተሰብ በመበደል የሚታወቁ እንደሆነ ንቅናቄው አመልክቷል፡፡

አቶ አልዩ ጋሹ የላኩማ ወረዳ አስተዳደር ስብሳቢ፣ አቶ አንበሱ በዙ የሰገላ ወረዳ ሚሊሺያ ዘርፍ ሀላፊ፣ እንዲሁም አቶ ኢያና ካሳ የባምበል ወረዳ ሚሊሽያ ዘርፍ ሀላፊ ሶስቱም በቁጥጥር ስር የሚገኙ ሀላፊዎች እንደሆኑ ንቅናቄው ገልጿል፡፡

ይሁንና ኢሳት በቁጥጥር ስር ስለዋሉት ሀላፊዎች ከገለልተኛ ወገን ያገኘው ማረጋገጫ የለም፡፡

ላኩማ ወረዳ ብዙ የሙስናና የመልካም አስተዳደር እጦት ያለባት ስፍራ እንደሆነች የገለጸው ንቅናቄው ከዚህ በፊት የአካባቢውን ሰዎች ሲያጉላላ የነበረ ሀላፊ እርምጃ ተወስዶበት እንደነበር አስታውሷል፡፡

ንቅናቄው በክልሉ ባሉ ህዝቦች ላይ የሚፈፀመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሰቃይ እንዲቆም ጠይቋል፡፡

የጎጃም ዞን ዋና የህወሀት ባለስልጣን በነበሩት አቶ ዳኘ ገብረማርያም ላይ በቅርቡ እርምጃ መወሰዱን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡

በደቡብ ክልል የመምህራን ተቃውሞ እየተስፋፋ ነው

ጥቅምት ፲፭(አስራ አምስት)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :- መምህራን ለአባይ ግድብ ማሰሪያ በሚል  የመስከረም ወር ደሞዛቸው ያለፈቃዳቸው ተቀንሶ ከተሰጣቸው በሁዋላ የጀመሩት ተቃውሞ እየተስፋፋ መሆኑን ለኢሳት የሚደርሱት መረጃዎች ያመለክታሉ።

የጨንጫ ወረዳ 7 ትምህርት ቤቶች መምህራን የተቆረጠው ደሞዛችን ካልተመለሰ ስራ አንሰራም በሚል አድማ ከመቱ በሁዋላ፣ በዛሬው እለት ደግሞ በጋሞጎፋ ዞን በምእራብ አባያ ወረዳ የሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራን ” የተቆረጠብን ደመወዝ የማይመለስ ከሆነ ስራ አንሰራም በሚል ” በስፍራው ለተገኙት ባለስልጣናት ተናግረዋል።

የወረዳው አስተዳዳሪ፣ የወረዳው የድርጅት ጉዳይ ሃላፊና የወረዳው የመምህራን ማህበር ተወካይ በስፍራው ተገኝተው መምህሩን ለማወያየት የሞከሩ ሲሆን፣ መምህራኑ ግን ደሞዛችን ተመልሶ እስካልተሰጠን ድረስ ከእናንተ ጋር ለመወያየት ፈቃደኛ አይደለንም የሚል መልስ ሰጥተዋል።

ባለስልጣናትም መምህራኑ ” አመጹን እንዲያቆሙ፣ የተቆረጠባቸው የመስከረም ወር ደሞዝ እንደሚመለስና በጥቅምት ወርም ያለ ፈቃዳችሁ እንደማይቆረጥባቸው”  ቃል ገብተው ለማረጋጋት ሞክረዋል።

ባለስልጣናቱ መምህራኑን ይቅርታ በመጠየቅ ለማረጋጋት ቢሞክሩም፣ መምህራኑ ይቅርታውንም ለመቀበል ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀርተዋል ። ስለአባይ ግድብ ከእናንተ የተሻለ  በቂ መረጃ አለን በማለትም መምህራኑ በባለስልጣናቱ የቀረበውን ልመና ውድቅ አድርገዋል።

በዚሁ ወረዳ የአይዶ አንደኛ ደረጃ፣ ወሌ አንደኛ ደረጃ፣ ምእራብ አንደኛ ደረጃ፣ ገልዶ አንደኛ ደረጃ እና የሌሎችም ትምህርት ቤቶች መምህራን የተቃውሞ ፊርማ አሰባስበው ለወረዳው ትምህርት ቤት ጽህፈት ቤት አቅርበዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ከምእራብ አባያ መሰናዶና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 15 የኢህአዴግ አባላት የሆኑ መምህራን ከድርጅት አባልነት ለመሰናበት የመልቀቂያ  ደብዳቤ አስገብተዋል። መምህራኑ ድርጅቱን ለመልቀቅ  ካቀረቡዋቸው መክንያቶች መካከል፣ “የኢኮኖሚ ችግር፣ የድርጅቱ ኢ- ዲሞክራሲያዊ ባህሪና በየጊዜው የሚፈጠርውን ጫና  ለመቋቋም አለመቻል” የሚሉ ይገኙበታል።

ቀድም ብሎ በመሰናዶ ትምህርት ቤቱ ውስጥ 75 የኢህአዴግ አባላት መምህራን የነበሩ ሲሆን፣ 47 መምህራን ድርጅቱን በመልቀቃቸው 28 አባላት ብቻ ቀርተው ነበር። ከ28ቱ መምህራን መካከል ደግሞ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ 15ቱ መምህራን የመልቀቂያ ደብዳቤ አስገብተዋል።

 

በጋምቤላ ለሞቱ የሰራዊቱ አባላት ካሳ ተከፈለ – ለሞቱ ነዋሪዎች ግን ካሳ አለመከፈሉ ታወቀ

ጥቅምት ፲፭ (አስራ አምስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም

ኢሳት ዜና :-በቅርቡ በጋምቤላ ክልል ንዌር ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ሚኒኛንግ ከተማ ተካሂዶ በነበረ ግጭት ለሞቱ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በነብስ ወከፍ 90 ሺህ ብር እንዲከፈል ተወሰነ፡፡ ለሞቱ ሲቪል ሰዎች የካሳ ክፍያ ሳይፈጸም መቅረቱን ግን ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል፡፡

የዞኑ ሚሊሺያዎች እና ነዋሪዎች ከመከላከያ አባላት ጋር ባደረጉት ግጭት ስምንት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ሞተው ሰባት መቁሰላቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡

ከሞቱ እና ከቆሰሉት የመከላከያ አባላት በተጨማሪ ስድስት ነዋሪዎች ለቀናት በዘለቀው ግጭት ተገድለዋል፡፡

የጋምቤላ መስተዳደር ለክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ለሞቱ ስምንት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ለእያንዳንዳቸው 90 ሺህ ብር እንዲከፈል ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ለቆሰሉ ሰባት አባላትም ለእያንዳንዳቸው 30 ሺህ ካሳ እንዲከፈል የተወሰነ ሲሆን ለሞቱ የአካባቢው ነዋሪዎች ግን ምንም የካሳ ክፍያ ሳይፈጸም መቅረቱን የኢሳት ምንጮች አስታውቀዋል፡፡

ለተገደሉት ነዋሪዎች ክፍያ አለመፈጸሙ የሟች ቤተሰቦችን እንዳሳዘነ የገለጹት እማኞች ጉዳዩ በበርካታ ነዋሪዎች ዘንድ ጥያቄ አስነስቷል፡፡

ለመከላከያ አባላት የተመደበው ገንዘብ ለቤተሰቦቻቸው እንደማይደርስ የጠቆሙት እማኞች ትዕዛዙ የክልሉን ገንዘብ ከመበዝበር ያለፈ እንደማይሆን ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡

ከሳምንት በፊት በንዌር ዞን በተቀሰቀሰ ግጭት የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና አፈ-ጉባኤ መገደላቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ግጭቱ የተቀሰቀሰው እግር ኳስ ሲመለከቱ በነበሩ ሰዎች መካከል ቢሆንም ነዋሪዎች የፖለቲካ አጀንዳ ሊኖረው እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡

 

በአዲስአበባ የውሃ ችግርን ተባብሶ ቀጥሎአል

ጥቅምት ፲፭(አስራ አምስት)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :- በአዲስአበባ ከተማ የውሃ ሽፋን 94 በመቶ ደርሶአል ቢባልም በአሁኑ ወቅት መሃል አዲስአበባን ጨምሮ አብዛኛው አዳዲስ የማስፋፊያ አካባቢዎች በቂ የውሃ ሽፋን የማያገኙት ከ40 በመቶ አይበልጡም።

የአዲስአበባ ከተማ ውሃና ፍሳሽ ባለሰልጣን እንደሚናገረው የከተማዋ የውሃ ሽፋን እያደገ ቢመጣም ውሃን በቁጠባ የመጠቀም ልምድ ባለመዳበሩ እስከ40 በመቶ የሚደርስ ከፍተኛ ብክነት በከተማዋ ውስጥ አለ ብሎአል፡፡ ይህ ሁኔታም
ያለውን ውሃ በቁጠባ ለማዳረስ የሚደረገውን ጥረት ማስተጓጎሉን ጠቁሟል፡፡

የከተማዋን የውሃ እጥረት ለመቅረፍ በተያዘው 2006 በጀት ዓመት 6 ቢሊየን ብር ገንዘብ መመደቡን የአስተዳደሩ ምንጮች ጠቅሰው በዚህም ሥራ በቀን 110 ሺ ሜትር ኪዩብ የነበረውን ስርጭት ወደ210 ሺህ በማሳደግ ችግሩን
ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ ተወስቶአል፡፡

በተለያዩ የአዲስአበባ አካባቢዎች በየዕለቱ የመጠጥ ውሃ በአግባቡ የሚሰራጭ ባለመሆኑ ሰዎች ስራቸውን በመተው ጭምር ውሃ ፍለጋ ከቦታ ቦታ ሲንከራተቱና ለውሃ ማጓጓዣ ከፍተኛ ወጪ ሲያወጡ ማየት የተለመደ ሆኖአል፡፡ በአንዳንድ
አካባቢዎችም ውሃ በለሊት ይመጣል በሚል በርካታ ቤተሰቦች ውሃ በመጠባበቅ እንቅልፍ ሳይተኙ የሚያድሩበት ሁኔታ መኖሩ ይታወቃል፡፡

 

በኢትዮጵያ የሰሜን ኮርያ ዲፕሎማት በደቡብ ኮርያ ኢምባሲ ጥገኝነት ጠየቁ

ጥቅምት ፲፭ (አስራ አምስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም

ኢሳት ዜና :-በኢትዮጵያ የሰሜን ኮርያ ዲፕሎማት ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩ ኮርያዊ በደቡብ ኮርያ ኢምባሲ ጥገኝነት መጠየቃቸው ተገለጸ፡፡

ስማቸው ይፋ ያልሆነው ዲፕሎማት የሚወክሉትን ሀገር ትተው ከአንድ ወር በፊት የደቡብ ኮርያን መንግስት አዲስ አበባ በሚገኘው ኢምባሲ በኩል ጥገኝነት መጠየቃቸውን የተለያዩ የሁለቱ ኮርያዎች መገናኛ ብዙሀን በመዘገብ ላይ ናቸው፡፡

ዲፕሎማቱ ወደ ደቡብ ኮርያ ኢምባሲ በመግባት ጉዞአቸውን እንዲያመቻችላቸው ጠይቀው ከአዲስ አበባ ወደ ደቡብ ኮርያ ማቅናታቸው ታውቋል፡፡

ዲፕሎማቱ የሰሜን ኮርያ ኤምባሲ ውስጥ የንግድ ተወካይ ሆነው ሲያገልግሉ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

የሰሜን ኮርያ መንግስት በእርምጃው መበሳጨቱ የተገለጸ ሲሆን ደቡብ ኮርያ ግን ማረጋገጫን ከመስጠት ተቆጥባለች፡፡

በየዓመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሰሜን ኮርያ ዜጎች ወደ ደቡብ ኮርያ ይኮበልላሉ፡፡

ከ25 ሺህ በላይ ሰሜን ኮርያውያን በደቡብ ኮርያ የሚገኙ ሲሆን ቻይናን እና ሌሎች ሀገራትን እንደ መሸጋገሪያ ይጠቀሙበታል፡፡

ይሁንና የሰሜን ኮርያ ዲፕሎማት ወደ ደቡብ ሲኮበልሉ የተለመደ እንዳልሆነ ተነግሯል፡፡

 

በእርዳታ ስም በርካታ ዜጎች ስቃይ እየደረሰባቸው ነው

ጥቅምት ፲፭(አስራ አምስት)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :- በባሌ ዞን በጎባ ከተማ ቀበሌ 03 ልዩ ስሙ አዲስ ከተማ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው ኤም ኦ ሲ ሚሺኒሪ ኦፍ ቻርቲ የተባለው ድርጅት በ1984 ሲቋቋም ዋና አላማው በዞኑ እና በአካባቢው የሚኖሩ እና እንዲሁም ከመላው ኢትዮጵያ የሚመጡ የአካል ጉዳት ያለባቸው ማለትም፤ መስማት እና ማየት የማይቸሉ፤ መራመድ የማይችሉ፤የአዕምሮ ዘገምተኞች፤እንዲሁም በዕድሜ የገፉ እና ጧሪ አልባ አዛውንቶችን ተቀብሎ ሲያስተናግድ እና ሲንከባከብ እንዲሁም ወላጅ አልባ ህፃናትን ተቀብሎ ማሳደግ መሆኑን ሲገልጽ ቆይቷል።

ይህ መንስታዊ ያልሆነ ድርጅት እነዚህን አገልግሎቶች ለመስጠት ዋና ገቢው ከውጭ በሚያገኘው ድጋፍ መሆኑን የውስጥ ሠራተኛ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ይጠቁማሉ፡፡

ድርጅቱ በቅርቡ ምክንያቱ ባልተገለጸ ሁኔታ በስሩ ታቅፈው የነበሩ አካል ጉዳተኞች፣ ማለትም የአዕምሮ ዘገምተኞች እና ታማሚዎች፣  ማየት  እና መስማት የተሳናቸውን ታዳጊዎች እና አረጋውያንን  ከመጠለያ ስፍራው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በማባረሩ ፣ ጎስቋሎቹ፣ በከተማው ውስጥ እየተንከራተቱ እንደሚውሉና ለጎዳና ተዳዳሪነት እንደተዳረጉ ዘጋቢያችን ገልጿል። ከተባረሩት ዜጎች መካከል ቁጥራቸው በውል ያልተዋቀ ሰዎች ሞተዋል፡፡ እራሳቸውን ያጠፉ አዛውንት መኖራቸውም ይነገራል ፡፡

በብዛት ከአማራ ክልል እና አካባቢው የመጡት እነዚህ ዜጎች በአሁን ሠዓት ወዴት መሄድ እንዳለባቸው ባለማወቅ የጎባ ከተማ ጎዳና መኖርያቸው አድርገው ይኖራሉ፡፡

ይህ ድርጅት በአሁን ወቅትም ያልተዘጋ እና በሀገሩቱ ውስጥ ተመዝግቦ ያለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሲሆን ፣እኒህ ተጎጂዎች እስከ ፌደራል መስርያ ቤት ቢያመለክቱም ሰሚ በማጣት የሚመለከተው አካልም የጥቅም ትስስር እንዳለው በሚያሳይ መልኩ ተጎጂ እና ቅሬታ አቅራቢዎችን እስከ ማሰር እንደደረሰ ለማወቅ መቻሉን ዘጋቢያችን ገልጿል።

በድርጅቱ ውስጥ የሚሰሩ ኢትዮጵያን እንደሚናገሩት እስካሁን በተወገዱት ተጎጂዎች ስም የሚመጣው እርዳታ እንዳልቆመ እና ይኸው እርዳታም ወዴት እንደሚገባ እንደማታወቅ ቁጥጥርም እንደማይደረግበት ድርጅቱም በማናለብኝነት እንዳሻው በወገኖች ላይ ግፉን እየቀጠለበ እንዳለ ታውቋል። እነዚህ የውጭ ሃገር ሰዎች ያሻውን የማሰሰር፣ የማባር እና አካል ጉዳተኞችን እስከ መብደብ የሚደርስ ግፍ እንደሚሰሩ እና የአካባቢው የመንግስት ባለስልጣናትም ሽፋን እንደሚሰጧቸው ዘጋቢያችን ያነጋጋራቸው ሰዎች ገልጸዋል። በጉዳዩ ዙሪያ የድርጅቱን ሃላፊዎች እና መንግስት ባለስልጣናትን ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።

ESAT

posted by Tseday Getachew

 

 

Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: