Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

በደም በተበከሉ እጆችና በወንጀለኞች የምትመራ አገር- አበራ ሽፈራው /ከጀርመን/

 

 

ዛሬ ይኸንን ፅሑፍ እንድጽፍ ያነሳሳኝ ጉዳይ አንድ ነገር ነው። ይኸውም አቶ ገብረምድህን አርዓያ ከአውስትራሊያ በኢትዮጵያ አቆጣጠር መስከረም 6 ቀን 2006 በተጻፈውና “የህወሓት ፀረ ኢትዮጵያ አካሄድና ዓላማ በመቃወም የሕይወት መሰዋዕትነት የከፈሉ አመራር ነበሩ ወይ? ከነበሩስ እነማን ናቸው?“ የሚለውንና በኢንተርኔት የተለቀቀውን ጽሁፍ ካነበብኩኝ በኃላ በርግጥም የህወሓት መሪዎች ምን ያህል የክፉ መንፈስ ፈረሶች መሆናቸውን ከጽሁፉ ከተረዳሁ በኃላ  ይህንን መጻፍ ግድ አለኝ።

የጽሁፉ ቁም ነገር በተለይም በኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት፣ የአማራው ህዝብ የትግራይ ህዝብ ጠላት አይደለም ይህ በውሸት አማራን ለማጥቃት የተፈበረከ ታሪክ ነው፣ ኤርትራ የአማራው /ኢትዮጵያ/ ቅን ግዛት ናት የሚለው ቅንጣት ታህል ሃቅነት የሌለው እናንት አመራር የፈጣችሁት የተገንጣይ ዓላማ ነው፣ ትግራይ የአማራ ቅኝ ግዛት ናት ማለት የአዕምሮ ድህነት ጠባብ ዘረኝነት ነው፤ ስለዚህም መወገዝ አለበት፣ ተሓህት የኢትዮጵያን ጥንታዊና ታሪካዊ ግዛትዋን እና ባህር በሯን የሚያስነጥቅ ፕሮግራም ነው፣ እና ሌሎች ሃሳቦችን ባነሱ ታጋዮችና በዛሬዎቹ መሪዎች መሃል የነበረን ሁኔታንና ፤ብዙዎች በዚህ የተነሳ ለሞት የተዳረጉ መሆኑንና፤ ዛሬ የአገራችን መሪዎች ሆነው የሚመሩን ምን ያህል ዘግናኝ ግድያዎችን አብረዋቸው በታገሉ ላይ የወሰዱትን አረሜናዊ ጭፍጨፋንም ያትታል። ከዚህም ጋር ተያይዞ እነዚህ ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት፣ ለህዝቦች እኩልነት የታገሉት ሃይሎች የከፈሉትንም መሰዋዕትነት ያትታል።  ሃገሬ የሞተልሽ ሳይሆን የገደለሽ በላ” ።

አስቀድሞም ቢሆን ኢትዮጵያዊነት ስነምግባርና አስተዳደግም የጐደላቸው ፤የስነልቦናና የበታችነት ሥሜት ሁሌ የሚፈታተናቸው ፤ለዓመታትም በፍርሓት ከመዋጣቸው የተነሳ ያገኙትን ሁሉ አብሮአቸውም የበላውንም ፣አብሮ አደጐቻቸውንም በየምክንያቱ የገደሉ መሆናቸውን ከጽሁፉ ተረድቻለሁ ።

ፈሪ በጩኸት ብቻ በርግጐ የመቃብሩን ግዜ ያፋጥናል ይኽንንም ከጨካኙ መሪያቸው ሞት በቀላሉ ለመረዳት ችያለሁ። አሁንም የሚታየው እውነት እንደሚያሳየው አዲስ አበባ ወጥተው የሚጮሁትን ፈርተው እየደጋገሙ የፍርሓት ዛቻ ሲያዘንቡባቸው ይሰማሉ፤ አንዳንዶችንም ይመታሉ ፣ያስራሉ፣ የሚፈልጉትን ሁሉ ያደርጉባቸዋል። ከዚህ ድርጊታቸው ስንነሳ አሁን እየፈጸሙ ያሉት ድርጊት ቀድሞውንም ሲፈጽሙት የነበረና አሁንም ያለቀቃቸው መሆኑን ስመለከት ህወሓቶች ኢትዮጵያዊ ስነምግባርና አስተዳደግ የጐደላቸው ፣ በክፋታዊ አስተሳሰባቸው የተበረዙ፤ የሌሎች ጭቁን ህዝቦችን ህልውና እየተዳፈሩ እነሱ ብቻ ነፃ አውጭ እነሱ ብሎ ነፃ አውጭ፤ ሌላው ለራሱ ነፃ መውጣት የማይታገልና እነሱ ባዘጋጁት የክፋት መዋቅር ውስጥ ለሁሌም እየገዙት የሚኖሩ የሚመስላቸው፤ እነሱ ለዚህ ክፋታዊ ግባቸው እንደታገሉ ሁሉ ለእውነተኛው ነጻነትማ ህዝቡ ለምን አይታገላቸው?

ህወሓቶች እጅግ በታሪክም፣ በሰውምና በአምላክም ፊት የ39 አመታት የወጀለኝነት ዶሴዎች ጥርቅም በፊታቸው ያለ መሆናቸውን የተረዳሁበት እጅግ መራራ ጽሁፍ ነበር ያነበብኩት ።

ብዙዎቹ አሁን አገሪቷን የሚመሩት የህወሓት አመርሮችና የተወሰኑት አባላት በሙሉ አብረዋቸው ለትግል የውጡትን ሰዎች እየጨረሱ ለዛሬ የደረሱ መሆኑንና እንቅልፍ የሌላቸው መሆኑን በቀላሉ ተረድቻለሁ። ከዚህ ጽሁፍ ተነስቼና ላለፉትም 22 አመታት በአጠቃላይ በኢትዮጵያና በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ከህወሓቶች አሸባሪነትጋር ተያይዞ ህወሓቶች በግለሰቦች ፣በቡድኖች፣ በአገርና በአለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች እንዲሁም ፍጹም ቅን ፈራጅ በሆነው በአምላክ ፊት ብዙ የወንጀለኝነት የወንጀሉም ክብደት ደግሞ በሰው ልጅ ግድያና በዘር ማጥፋት ወንጀሎች የሚጠየቁበት ሰፊ ምስረጃዎች በአገር ቤት በግለሰቦች፣በቡድኖች፣በጓደኞቻቸው በአብሮ አደጐቻቸው፣በአካባቢያቸው ሰዎች ሳይቀር የሚፈለጉ መሆናቸውን ይበልጥ እንድረዳ ጽሁፋ አድርጐኛል።

በነገራችን ላይ “እግዚአብሔር የለም” ከሚሉ የፖለቲካ ፈላስፎች የተማሩትን ለመተግበር በሚጥሩ ህወሓቶች በሰው ልጅ ላይ ከዚህ በላይ ወንጀሎችን ቢፈጽሙ ምንም የተለየ ነገር አይጠበቅባቸውም፤እግዚአብሔር የለም ለሚሉ ሠይጣን ግን በእነሱ ውስጥ እንዲኖር ይገደዳሉ። ሰይጣን የመጀመሪያው ተግባሩ በአምላክ አምሳል የተፈጠረውን የሰው ልጅ ከአምላክ ያገኘውን ክብር  ማሳነስና ክብሩን መንካት ዋናው ተግባሩ ነው። ለዚህም ነው ይህንን የሰውን ክብር ለመመለስና የዲያብሎስን ሥራ ሊያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ የተገለጠው።የሰውም ልጅ በአምላክ ፊት ትልቅ ክብር ያለው ከመሆኑም በላይ የክብሩ ማለትም የመንፈሱም ማደሪያም አድርጐታል። ይህ ከቡር ፍጡር ነው እንግዲህ ሁሌ በህወሓቶች ፊት እየቀለለ የሚገኘው።

ህወሓቶች ግን አምላክ የፈጠረውን ሰው እንደፈለጋቸው በማሰር፣ በመግረፍ፣ በመግደልና በማሳደድ ሰፋፊ ሰይጣናዊ ተግባራቸውን ይፈጽሙበታል። የሰው ልጅ በህወሓቶች ፊት እንደተዋረደ በማንም ፊት በአሁኑ ሰአት ሲዋረድ አናይም። ጊዜና ዘመን ቆጥሮ አምላክ ይመጣል ለሁሉም በጊዜው እንደዋጋቸው ይከፍላቸዋል። በእርግጥም የአምባገነኑ መሪያቸው ሞት ለዚህ ትልቅ ደውል ነበረ፤ መማር ለሚፈልጉና ወደአይምሮአቸው ለመመለስ ለሚፈልጉ ሁሉ፤ ካልሆነ ግን በነዚህ ዘመናት ላፈሰሱት የንጹሓንን ደም ከሰማይ ዋጋ አለውና ሁሌም ይህ ደም ይጮሃልና የነዚህ ጨካኞች ፍርድ በሰማይ ብቻ ሳይሆን በምድርም ማየትን እንድንጀምር በጨካኙ መሪያቸው ላይ አምላክ ሥራውን ጀምሯል፤ ይቀጥላል።

ወደ ዋናው ሃሳቤ ስመለስ በተለይም ሲፈልጉ አንጋፋ ሲፈልጉ ደግሞ አቦይ እያሉ የሚያመጻድቁት ትልቁ የክፋት ፈረስ ሥብሃት ነጋ፣ መለስ ዜናዊ፣ ስዩም መስፍን፣ አባይ ፀሃዮ የፈጸሟቸውን አረመናዊ ድርጊቶች በጣም በሚገርም መልኩ ተመልክቻቸዋለሁ። በእርግጥ ከነዚህ ውስጥ በቅርብ ከሆነውና እራሳችን ከሰማነው የአንዳቸውን የክፋት ማስረጃም እንደምሳሌ እንወሰድ። አቶ መለስ በሞቱ አካባቢና የኢሳት ረዲዮና ቴሌቪዥን ፕሮግራም ሁኔታውን ቀድሞ ባሳወቀ ሰሞን ይህ አብሮት የበላውና የጠጣው ስብሃት ነጋ ለኝህ መሪ የነበረው ንቀትና ግዴለሽነት ምን ያህል ሰውየው ለሰው ልጅ ምንም ክብር የማይሰጥና በምንም መለኪያ የወረደ ለመሆኑ ትልቅ ማስረጃ ነበር። ሰውየው አምላክ ቀደመው እንጂ ስብሓት ለመሪያቸው ሊተኛለት እንደማይፈልግ በትክክል ንግግሩ ሁሉ ያሳያል።

ካነበብኩት ጽሁፍ ላይ እንደ አቶ ገብረመድህን ምስክርነት ከሆነ እነዚህ እና ሌሎች በሽብር ተግባራቸው የሚታወቁት የህወሃት አመራሮችና  የተወሰኑ አባላቶቻቸው አብረዋቸው በትግል ወቅት የነበሩትንና የተማሩ የነበሩትን፣እውነተኛ አገር ወዳዶችን፣የፍትህና የነጻነት ጉዳይ ያሳስባቸው የነበሩትን፣ስውር አላማ የሌላቸውንና እውነተኛ ታጋዮች በእነዚህ ክፉዎች እየተገደሉ እንዳለቁ ማንበብና መስማት እጅግ ይከብዳል።

እነዚህ በደም የተበከሉ እጆች ያላቸው ሰዎች ለዓመታት በትግራይ ክልል ፣ በአማራና በሌሎች ክልሎች የገደሉአቸውና ያስገደሉአቸው የሰዎች ብዛት ቀላል ባይባልም ምን ያህል በሰው ልጅ የመኖር ተፈጥሮአዊና ህገመንግሥታዊ መብቶች ላይ ክፉኛ ጠላት እንደሆኑና በእነዚህ ሰዎች ውስጥ በነበረው የሰይጣን ተልዕኮ ብዙዎችን ወደመቃብር እንዲወርዱ አድርገዋል።

እነዚህ ሰዎች የሰው ልጅ ሆነው ተፈጥረው እንደነሱ እኩል የተፈጠረውን ሰው ሲገድሉ፣ ሲያሰቃዩና ሲያሳድዱ ቅንጣት ያህል የማይሰማቸው ከመሆኑምበላይ ብዙ አረመኔያዊ  ድርጊታቸውን ሊፈጽሙ የሚችሉ ብዙዎችንም ከዙሪያቸው ማሳደጋቸውና መፍጠራቸውን ሳስብ ህዝቡ ለመከላከል ካልቆረጠ ከባድ ፈተና ከፊትም እንዳለ በግልጽ ያሳያል።

እነዚህ ነፍሰ ገዳዮች ዛሬም የሚጠማቸው ሰው የመግደል አባዜ አለቅ ብሎአቸው ንጹሃንን መግደልና ማስገደል ተያይዝውታል። ገዳዮች ህወሃቶች በግድና በቅስቅሳበወጣው ህዝብና ወታደሮች እየታጀቡ ይቀበራሉ፤ ከንቱ ድካም የምድር ሥርዓት ይኸም ከንቱ ነው እንዳለው ጠቢቡ ሰለሞን። በህወሓቶች ወይም በአጋዚዎችና በሌሎች የህወሓት ወታደሮች የተገደሉት ንጹሃን ግን ሲፈለግ  ሬሳውን ገንዘብ ከፍላችሁ ውሰዱና ቅበሩ የተባሉ በኢትዮጵያ ምድር ስንቶች አሉ ዋ ኢትዮጵያ ታዲያ በደም የተጨማለቁ እየመሩሽ እንዴት መፍትሔ ታገኝ? እንዴትስ ትፈወሺ?

እንደ አቶ ገብረመድህን አርዓያ ምስክርነት ከሆነ ገሠሠው አየለ፣አጋዚ ገሰሰ፣ ሙሴ መሃሪ ተክሌ፣ አጽበሃ ዳኘው፣ ዶ/ር አታክልት ቀጸላ እና ሌሎች አመራር የነበሩ ሰዎችና አባላቶቻቸው ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ለህዝቦች እኩልነት ያደረጉት ተጋድሎ ቀላል እንዳልነበረ ይገልጻሉ።

አንድ ነገር ያሳዝነኛል አገራችን በደም በተለወሱ እጆችና በወንጀለኞች የምትመራ አገር መሆኗንና የአገራችንም መከራ የእነዚህ ሰዎች የደም ጩኸት ውጤት ነው ብዮም እገምታለሁ። እነዚህ ሰዎች የገደሏቸው ሰዎች ደም ይጮሃል መልስንም ከአምላክ ይፈልጋል። ወደድንም ጠላንም በደም የተነከረ እጅ ባላቸው ሰዎች ፣ ለሰው ልጅ ምንም ክብር በሌላቸው ግለሰቦች፣እግዚአብሔር አለ ብለው በማያምኑና እምነት በሌላቸው ሰዎች ስብስብና ለ39 ዓመታት መጠነ ሰፊ ወንጀልን በፈጸሙ እየተመራን መሆናችን በአገሪቷ ላይ ትልቅ ፈተና ነው ብዮ አስባለሁ።

እንዚህ ቡድኖች ለኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለሚመሩት የህወሓት/ኢህአዲግ ፓርቲና በተለይም ለትግራይም ህዝብ ሳይቀር ትልቅ ፈተና ሆነው ያሉ ፓርቲውንም ወደቤተሰባዊ ትሥሥር የቀየሩና የብዝበዛ መዋቅራቸው እጅግ የተጠናከረ በመሆኑ ለአገሪቷና ለህዝቧ ትልቅ ሸክም ሆነው ያሉ መሆናቸውን ሁሉም ሊረዳው ይገባል።

ለዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እውን አለመሆን ሚስጥሩ እነዚህ ሰዎች አሁን ካለቡት ትልቅ ፈተና የተንሳና ሊገጥማቸው የሚችለው የተጠያቂነት ሁኔታ በፍጹም ሥልጣናቸውን በሃይል እስካልተቀሙ ድረስና ወይም ለፈጸሙት ወንጀል ከለላ እስካላገኙ ድረስ በአገራችን ውስጥ መፍትሔ ይመጣል ብሎ ለሚያስብ ሁሉ ዛሬ መርዶ ልነግር እፈልጋለሁ። እነዚህ ገዳዮች በትግራይ ጨምሮ በሁሉም የአገራችን ህዝቦች የሚፈለጉ መሆናቸውና ወንጀለኞች በመሆናቸው ከስልጣናቸውለመልቀቅ በፍጹም እንዳማይፈልጉ ሊታወቅ ይገባል። ለዚህ ሁኔታ መፍትሄ ለማስቀመጥ ሶስት ብቻ አማራጮች እንዳሉ ይታዩኛል።

  1. ወንጀለኝነታቸውን የሚያጠናክሩ መረጃዎችን ለማሰባሰብ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ማዘጋጀትና በአለም አቀፍ ደረጃ ተከሰው ወደፍርድ እንዲቀርቡ የሚሆኑበትን ሁኔታ መፍጥርና ተገቢውን ፍርድ እንዲያገኙ ማድረግ።
  2. ተገቢውን ሃይል አደራጅቶ ለእነሱ የሚመጥን ትግልና መሰዋዕትነትን ከፍሎ ከአገሪቷ ላይና ከህዝቡ ላይ ለሁሌም ማንሳት።
  3.  ይቅር ሊባሉ የሚችሉበትን ዋስትና መስጠትና አገሪቷ ከዚህ በኃላ በሰላምና በፍቅር በጋራ የምንኖርበትን ሁኔታ መፍጠር እንዳለብን ይታየኛል። ይህ ካልሆነ አይምሮአቸው ቆሽሿልና ሊፈወስ አይችልም ምን አልባት አንዳንዶቹን አምላክ በምህረቱ ካልተገኛናቸው በስተቀር፤  እንዚህ ሁኔታዎች በሌሉበት ሁኔታ መግደላቸውንም ብዝበዛቸውንም አያቆሙም።

በቅርብ ደግሞ በአክራሪነት ሰበብ ቀደም ሲል ሲያጠቁት የነበረውን የማንኛውንም ሃይማኖት እንቅስቃሴ ለመገደብ ትልቅ ሥራ ጀምረዋል። የሥራ መለኪያቸውም የኃይማኖት አክራሪነት እንዳይፈጠር የሚያስችል ሁኔታ እንደሆነ አስመስለው መነፈሳዊውን እንቅስቃሴ ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ሰፊ እቅዳቸውን መተግበር ጀምረዋል። ይህንንም ለመተግበር በስልኮች የሚደረግን ጥሪ ምንም ኃይማኖታዊ ይዘት እንዳይኖረው፣የሃይማኖት ሁኔታ አንዱ የሥራ መገምገሚያ ሊሆን እንደሆነና ሊተገበርም እንደሆነ ይሰማል እነዚህንና እና መሰል ነገሮችን በማድረግ በሃይማኖት ላይ የተቃጣም ሥራ ጀምረዋል። በነገራችን ላይ አክራሪነት ከአስተምሮቱ የሚነሳና ወደ ጽንፈኝነት የሚያዘነብል እንቅስቃሴ እንጅ ሁሉንም በዚህ መልኩ ፈርጆ በኢትዮጵያ ሃይማኖትን ለማዳከም የሚደረግ እንቅስቃሴ ሁሉ ይልቁንም ነገ የሚጐዳው እራሱን ህወሃትን እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ።

ቀደም ሲል በእግዚአብሔር ላይ ትልቁን ዘመቻ በአገራችን የተደረገ እንቅስቃሴ ነበረ ደርግም በዚህ አባዜ ተለክፎ እንደነበር ይታወሳል። በወቅቱ በተነሱ የሶሻሊስቶች አስተሳሰብ በ60 ዎቹ መጨረሻ ባሉ ፓርቲዎች አካባቢ አምላክ የለም በሚሉ ሃይሎች መካከል የተደረገው የደም መፋሰስ ይኸው አስተሳሰባቸው ባመጣባቸው መዘዝ የዲያብሎስ መፈንጫ በመሆን የመጣባቸው መዘዝና የአስተሳሰባቸው ውጤት እንጂ የፖለቲካ አስተሳሰብ ተደርጎ መወሰዱ አይዋጥልኝም። ምክንያቱም የሰላማዊ  ፖለቲካና እምነት መገለጫዎች አንዱ ለሰው  ልጅ ባለን ክብርና ፍቅር መጠን የሚገለጽ እንጂ በአስተሳሰብ ልዩነት ላይ ተነስቶ ሰውን መግደል እንዳልሆነ ሁሉም ያውቃል። ሰውን መግደል የክፉ ሃይማኖቶች አስተምሮቶች ውጤትና የክፉ ፖለቲካ አስተሳሰቦችና አስተምርኦቶች ውጤት እንጂ ሌላ ጉዳይ ነው ብዮ አላስብም።

እንደኔ አስተሳሰብ የሰው ልጅ ትልቅ ሥፍራ ሊሰጠው የሚገባውና በአምላክ መልክ የተፈጠረ ፍጡር መሆኑን አምናለሁ። ይህንን ሰውና እምነቱን ሊጐዳ የሚመጣ ኃይል ሁሉ መነሻው ፖለቲካ ሳይሆን ከፖለቲካው ጀርባ ያሉ የሠይጣን ተልዕኮ ውጤቶች ናቸው።

እንግዲህ እነዚህን ወንጀለኞች ማወቅ፣ መለየት፣ ማስረጃን ማሰባሰብ፣ ለዚህም የሚረዳ ድርጅት ማቋቋምና ወደ ሥራ መግባትና በፍርድ ፊት ማቅረብ ያለብን ጊዜ አሁን እንደሆነ አስባለሁ። ወገኖች እንዚህን ወንጀለኞች በሁሉም አቅጣጫ ታግሎ ማሸነፍና ለህግ ማቅረብ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለምና ዛሬ እንነሳ።

ከአቶ ገብረምድህን አርአያ ብዙ ተምሬአለሁ፡፤ አገራችን አሁን የምትመራው በደም በተበከሉ እጆች ባላቸው ቡድኖች እጅ ነው። እነዚህ ሓይሎችን በትክክል መቃወም፣ ለፍርድ ለማቅረብ አስፈላጊውን ርብርቦሽ ማድረግና ከአገሪቷ ጫንቃ ላይ ማንሳት ለአገሪቷ ሰላም፣ ብልጽግናና የሰዎችንም እኩልነትና ሰላም ስለሚያረጋግጥ ልንነሳ ይገባል እላለሁ። በዚሁ አጋጣሚ ለአቶ ገድረመድህን አርዓያ ያለኝን ትልቅ አክብሮት ለመግለጽ እፈልጋለሁ። አሁንም ሌሎች መረጃዎችን ለህዝቡ በማቅረብ ማወቅ የሚገባው ህዝብ ሉለ እንዲያውቅ እንደሚያደርጉ ተስፋዮ ትልቅ ነው፤ በተለይም ጽሁፎችዎን በመጽሃፍ መልክ ለማውጣት ቢጥሩ ሰፊ አንባቢ ለማግኘት ይችላሉና እባክዎ ይበርቱ እላለሁ ። ቸር ይግጠመን።

 እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ !

posted by Tseday Getachew

 

 

Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: