Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

“ተገዥነታችን ለሕዝብና ለሕግ እንጅ ለአምባገነኖች ማስፈራሪያ አይደለም” – አንድነት

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ(አንድነት) የተሰጠ መግለጫ

ፓርቲያችን አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ተመዝግቦ በሀገራችን ላይ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲሰፍንና ፍትሃዊነት እንዲኖር በቁርጠኝነት እየታገለ ይገኛል፡፡ በትግሉ ውስጥም ፓርቲያችን የተጋረጡበትን ፈተናዎች እየተወጣና የሚከፈለውን ዋጋ እየከፈለ ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ በመቀጠል ለህዝቡ ያለውን ታማኝነት እያረጋገጠም ነው፡፡

ፓርቲያችን በመላ ኢትዮጵያ ያለውን አደረጃጀት በመጠቀምና ሕዝቡን በማሳተፍ ለሶስት ወራት የሚቆይ ህዝባዊ ንቅናቄ በማካሄድ የመጀመሪያ ዙር የሆነውን ሰላማዊ ትግል ለማጠናቀቅ ችሏል፡፡ የሚልዮኖች ድምጽ ለነፃነት በሚል መሪ ቃል የተጀመረው ይህ ህዝባዊ ንቅናቄ አራት መሰረታዊ ጥያቄዎችንና ወቅታዊ ጉዳዮችን ያነገበ ሲሆን እንደ ሁልጊዜውም ፓርቲው ሰላማዊነቱን በጠበቀ መልኩ በቁርጠኝነት ንቅናቄውን በታቀደለት መሰረት አካሂዷል፡፡ ወደፊትም ይህንን አጠናክረን የምንቀጥል መሆኑን ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡

ኢህአዴግና መሪዎቹ መንግስት እንደመሆናቸው መጠን በሰላማዊ መንገድ ለምንንቀሳቀስ ፓርቲዎች ድጋፍና ትብብር ማድረግ ሃላፊነታቸው ቢሆንም ከዚህ በተቃራኒ በሰላማዊ መንገድ እየተንቀሳቀስን ያለን ፓርቲዎችን ለማጥፋት ቀን ከሌሊት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ልክ ከዚህ በፊት ሲያደርጉት እንደነበረው ባልዋልንበት ዋሉ፣ ባልተገኘንበት ተገኙ… በማለት ህዝባዊ መሰረታችን ጥርጣሬ ላይ እንዲወድቅ ለማድረግ ያገኙትን አጋጣሚ ሁሉ ይጠቀማሉ፡፡ ለዚህ አባባላችን ጥሩ ማስረጃ የሚሆነን ባለፈው ሳምንት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በመሪ ደረጃ በማይጠበቅ መልኩ ህጋዊና ሰላማዊ እንቅስቃሴችንን እሳቸው ከፈለጉት አካል ጋር በማገናኘት ስም ለማጥፋት መሞከራቸው ነው፡፡

አቶ ኃይለማርያምም ሆኑ መንግስት የሆነው ፓርቲያቸው ለሚነሱ ሀገራዊ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ከመስጠትና በተነሱ ጉዳዮች ዙሪያ ለመነጋገር በርን ከመክፈት ይልቅ ዙሪያ ጥምጥም በመሄድ ለጥያቄ አቅራቢዎች የተለየ መልክ ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት የምናውቀውና የነበረ አሮጌ መንገድ ነው፡፡

ፓርቲያችን ህዝባዊ ንቅናቄ ያደረገው ህጋዊ አግባቡን ጠብቆና የራሱን አጀንዳ ቀርፆ ነው፡፡ ጠ/ሚንስትሩ የራሳቸው አጀንዳ የላቸውም፤ የሻዕቢያ መልክት አድራሾች ናቸው ወዘተ ያሉበት ድፍረት የራሳችን አጀንዳ እንዳለን ጠፍቷቸው ሳይሆን ሆን ብለውና አቅደው ስም ለማጥፋት፣ ህዝቡ ውስጥ ጥርጣሬ ለመጫር በመፈለጋቸው ብቻ ነው፡፡ እኛ ተላላኪነታችን ለኢትዮጵያ ህዝብና ይጠቅማል ብለን ለቀረፅነው የፖለቲካ ፕሮግራም ብቻ ነው፡፡ እንደዚህ አይነቱን ስም ማጉደፍም ፓርቲያችን በቸልታ አይመለከተውም፡፡ ስለዚህ አቶ ኃይለማርያም ከባለፈው ስህተታቸው በመማር ከአጉልና ማስረጃ አልባ ፍረጃ እንዲላቀቁ አጥብቀን እንመክራለን፡፡

የሙስሊም ወገኖችን ጥያቄ በተመለከተ ፓርቲችን ያለው አቋም ግልፅ ሲሆን አሁንም ጥያቄያችው በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ መመለስ፤ ዜጎች የመብት ጥያቄ ሲያነሱ መፈረጁ ይቁም፤ ካላግባብ የሃማኖት ነፃነት ጥያቄ ስላነሱ ወደ እስር ቤት የተወረወሩ ዜጎች ባስቸኳይ ይፈቱ የሚል ነው፡፡ በተጨማሪም ስርዓቱ ካላግባብ ያሰራቸው ጋዜጠኞችና የፖለቲካ እስረኞች ባስቸኳይ ይፈቱ ብለን እንጠይቃለን፡፡ ወደፊትም ይህንን ጥቄያችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ እኛ እያልን ያለነው ከኢ-ፍትሃዊነት ጋር አንደራደርም፤ አንቀበለውም ነው፡፡ ስለዚህ ፓቲያችንን ከሙስሊም ወገኖች ጥያቄ ጋር በማያያዝ ትርፍ ፍለጋ መሯሯጥ ስህተት ብቻ ሳይሆን ወንጀልም ነው፡፡

አቶ ኃይለማርያም በህገ መንግስቱ በግልጽ የተቀመጡ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፣ የመሰብሰብና አቤቱታ የማቅረብ መብትን በአደባባይ የጨፈለቀው ንግግራቸው ሰላማዊ ሰልፍን በተመለከተ ነው፡፡ በቂ ጥበቃ የለንም በሚል ተልካሻ ሰበብ የዜጎችን መብት መንጠቅ አይቻልም፡፡ በቂ ጥበቃ ማድረግ ያልቻለ መንግስት ስልጣኑን ለህዝብ በማስረከብ ይቅርታ ጠይቆ መሄድ እንጅ ከአሁን በኋላ መብታችሁን አታገኟትም በማለት መዛት ትዝብት ውስጥ የሚጥል ድርጊት ነው፡፡

ስለዚህ ፓርቲያችን አንድነት አሁንም ተገዥነቱን ለህዝቡና ለህግ አድርጎ በአምባገነኖች ዛቻ ሳይበረግግ፤ ዘር፣ ፆታ፣ ሀይማኖት፣ ቀለም ሳይለይ ዜጎች የሚያነሱት ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች እንዲመለሱ፤ የመንግስት በሐይማኖት ጣልቃ ገብነትም እንዲቆም ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ያረጋግጣል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ፓርቲያችን የአፍሪካ መሪዎች ብዙ መፍትሄ ፈላጊ ችግሮች ባሉባት አፍሪካ ተሰብስበው እንግደል፣ እንሰር፣ እንጨፍጭፍ፣ ዘር እናጥፋ፣ ዜጎቻችንን እናሰቃይ ግን መታሰርም መከሰስም የለብንም በሚል የያዙት አቋም አሳፋሪና ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡ ሕግ እየጣሱ በህግ አለመጠየቅ አይቻልም፡፡ ዘር እያጠፉ ያለመታሰር መብት አይኖርም፡፡ ማንም ሰው ከህግ በላይ የመሆን መብት የለውም፡፡

የአፍሪካ መሪዎች ተሰብስበው ማለት ያለባቸው አይሲሲ ሊከስሰን አይገባም ሳይሆን የዜጎቻቸውን እንባ ማበስ ነው፡፡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲረጋገጡ መጣር ነው፡፡ መሳሪያና ጉልበት የችግሮች መፍቻ መሆናቸው እንዲያበቃ የሰለጠነ መንገድ መከተል ነው፡፡ የሚያስከስሳቸውና የሚያሳስራቸው ስራቸው እንጅ ሌላ አይደለም፡፡ ስለዚህ ፓርቲያችን አሁንም ሆነ ወደፊት በዜጎቻቸው ላይ ግፍና ሰቆቃ የሚፈፅሙ ሁሉ ሳይውል ሳያድር ወደ ፍርድ መቅረብ አለባቸው ብሎ ያምናል፡፡ አንዳንድ የአፍሪካ መሪዎች አይሲሲን በተመለከተ የሚያራምዱት የአትክሰሱን አቋም ፓርቲያችን አይቀበለውም፡፡

ዘላለማዊ ክብር ለኢትዮጵያ!!!

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)

ጥቅምት 11 ቀን 2006 ዓ.ም

አዲስ አበባ      

 

Download (PDF, 75KB)

posted by Tseday Getachew

 

 

 

Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: