Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

የፊታችን ሰኞ የኢሕአዴግ ፓርላማ “አበባ ቆራጭ” ይሾማል

ከኢሳያስ ከበደ

ላለፉት 12 ዓመታት የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት በመሆን ከአበባ መቁረጥና መትከል፣ ከእንግዳ መቀበልና መሸኘት፣ በስተቀር አንዳችም ስልጣን ያልነበራቸውን ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስን በመሸኘት አዲስ “አበባ ቆራጭ” ፕሬዚዳንት እንደሚመረጥ የኢሕአዴግ ፓርላማ አፈጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ አስታውቀዋል።
እንደ አስተያየት ሰጪዎች ገለጻ ለፕሬዚዳንትነት የሚመረጠው ሰው ከፓርላማው ውጭ ያለም ሰው ሊሆን እንደሚችል የተገለጸ ሲሆን ፕሬዚዳንት የሚለው ስያሜ ከአበባ መቁረጥ ያለፈ ስልጣን ስለሌለው በርከት ያሉ ኢትዮጵያውያን ጉዳይም አይሰጣቸውም። ፕሬዚዳንቱ ተጽዕኖ ፈጣሪ ቢሆንና ከአበባ መቁረጥ ያለፈ ስልጣን ቢኖረው የሰዎች መነጋገሪያ ሊሆን የሚችል ቢሆንም ሟቹ አቶ መለስ ዜናዊን የስልጣን ዘመን ለማራዘም ተብሎ የተቀረጸ ሕገመንግስት ነው ሃገሪቱ ያላት።

የአበባ ቆራጭነቱን ስልጣን እንደተቆናጠጡ መቶ አለቃ የሚለውን ስም አትጠቀሙ “ፕሬዚዳንት ግርማ በሉኝ” ያሉት መቶ አለቃ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ በመንግስታዊው ሚዲያዎች ለቀጣዩ አበባ ቆራጭ ስልጣናቸውን ሲያስረክቡ “ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ተደረገ ተብሎ” ሊዘግብላቸው 72 ሰዓታት የቀሯቸው ሲሆን በዚህ ዋዜማ ከመንግስታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ ብዙዎችን በሹፈት እንዲመለከቱት እያደረገ ነው። የአዲስ ዘመኑ ጋዜጠኛ ዳንኤል ንጉሴ መቶ አለቃ ግርማን “በሕይወቴ ያዘንኩባት ቀን አቶ መለስ ዜናዊ የሞቱበት ቀን፤ የተደሰትኩበት ቀን ደግሞ ግንቦት 20 ነው” እንዲሉት ፈልጎ “በሕይወትዎ ያዘኑበትና የተደሰቱበት ቀን የቱ ነው?” በሚል ላቀረበላቸው ጥያቄ መቶ አለቃ ግርማ የሰጡት መልስ የሚከተለው ነው፡-
“አዲስ ዘመን፦ በጣም ያዘኑበትና የተደሰቱበት ቀን?
ፕሬዚዳንት ግርማ፦ በራሴ ጉዳይ ያዘንኩበት ቀን የለም፡፡ አድርጌው ቢሳካልኝ ለአገር ይጠቅም ነበር ብዬ የተበላሸብኝ ጉዳይ ግን አለ፡፡ ይኸውም የሲቪል አቪዬሽን ዋና ዳይሬክተር በነበርኩበት ጊዜ ሞንቲሪያ (ካናዳ) እመላለስ ነበር፡፡ ያኔ የአዲሱ ቦሌ አየር ማረፊያ ግንባታ ተጠናቆ ነበር፡፡ በዚህም አሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ ባዶ ይሆን ነበር፡፡ ዓለም አቀፍ አቪዬሽን ድርጅት አፍሪካኖችን ለማሰልጠን አንድ የማሰልጠኛ ቦታ በኮትዲቯር፤ በምስራቅ አፍሪካ አሩሻ ላይ ነበራቸው፡፡ ለኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽንም አንድ አስተማሪ ልከውልን ያሰለጥኑ ነበር፡፡
እኔ አዲስ አበባ የበረራ ኮሌጅ እንዲኖራት ፍላጎት ነበረኝ፡፡ የቋንቋ ችግር አለመኖሩንም አስረዳኋቸው፡፡ አሮጌ አውሮፕላን ማረፊያውን በሙሉ በነፃ ለመስጠትም ተስማማን፡፡ ግብዣውንም ተቀበሉ፡፡ ሁኔታውን ለመንግሥት ካስረዳሁና መንግሥት ካፀደቀው በኋላ ነው እንግዲህ ግብዣው ሥራ ላይ የሚውለው፡፡ አዲስ አበባ ስመጣ ግን ወንበሬ ተሰብሮ ነው የጠበቀኝ፡፡ ከሲቪል አቪዬሽንም እንድወጣ ተደረግሁ፡፡
አዲስ ዘመን፦ ለምን?
ፕሬዚዳንት ግርማ፦ ከአሜሪካኖች ጋርም እጣላ ነበር፡፡ በመሆኑም ከሙያው ውጪ አደረጉኝ፡፡ በዚህም አልተናደድኩም፡፡ አልተቃጠልኩም፤ አልታመምኩም፡፡ ያቀድኩት ነገር ተግባራዊ ባለመሆኑ ግን አዝኛለሁ፡፡ በእኔ ቦታ ሰው ለመተካት ስድስት ወር ፈጅቶባቸዋል፡፡ እኔን ለመተካት ግን ቀላል ነበር (እነ አላምረው ወልደማርያም፤ ዋጋዬ ሐጎስ… የመሳሰሉ የአቪዬሽን ሰዎች ነበሩ) ግን የተፈለገው አሜሪካንን የሚወድ ሰው ነው፡፡
ከስድስት ወር በኋላ በእኔ ቦታ የተተካው ሰው እኔ የጀመርኩትን እንቅስቃሴ ጥቅሙንና ዓላማውን በደንብ አልተገነዘበውም፤አልተረዳውም፡፡ የእኔን ግብዣ«አንድ እብድ መቶ አለቃ ያመጣብን ጣጣ ነውና ይሻሩልን» ብሎ ለንጉሡ አቅርቦ አሻረው። ይሄ በጣም ያሳዝነኛል፡፡ ከእዚያ ውጪ ሁልጊዜ ደስተኛ ነኝ፡፡ ሲያወጡኝም ሲያወርዱኝም ደስ ብሎኝ እቀበላለሁ፡፡”

የፊታችን ሰኞ የሚሾመውና ለሚቀጥሉት 12 ዓመታት አበባ ሲቆርጥ የሚከርመው ሰው ማን ይሆን?

http://www.zehabesha.com/

posted by Tseday Getachew

Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: