Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

በአዲስ አበባ በርካታ ቤቶች ሊፈርሱ ነው

 ኢሳት ዜና :-በከንቲባ ድሪባ ኩማ የሚመራው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የያዘውን የአምስት ዓመት ዕቅድ ሰሞኑን ባካሄደው ስብሰባ ወደሁለት ዓመት ካጠፈ በኋላ በሚቀጥሉት ሁለት አመታት የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ያረጋግጣል ያለውን መልሶ ማልማት ሥራ በሰፊው እንደሚያከናውን አስታውቆአል፡፡

በዚህ የመልሶ ማልማት ሥራ በመሃል ከተማ የሚገኙ በርካታ ቁልፍ ቦታዎች የሚፈርሱ ሲሆን ነዋሪዎችም የመፈናቀል አደጋ ተደቅኖባቸዋል፡፡

በ2006 እና  በ2007 በጀት ዓመትም የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር  በጥቅሉ 2 ሺህ 140 ሄክታር ቦታ ለመልሶ ማልማትና ለማስፋፊያ ስራዎች ለማዋል አቅዷል። ቦታዎቹ ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ ለንግድ ቦታዎች፣ ለኢንዱስትሪና ለመሳሰሉት በጨረታና በምደባ ስራ ላይ የሚውሉ ናቸው፡፡

የመልሶ ማልማት ከሚከናወንባቸው አካባቢዎች መካከል ፥ አራዳ ክፍለ ከተማ ደጃች ውቤ ሰፈር 11 ነጥብ 6 ሄክታር ፣ አራዳ ክፍለ ከተማ  የሚገኘው  የአሜሪካ ጊቢ   6 ሄክታር መሬት ያህል  የሚለማ ይሆናል፡፡ አፍሪካ ህብረት ቁጥር 2 ፣ ቡልጋሪያ ኤምባሲ አካባቢ 12 ሄክታር እና ለገሃር ዙሪያም 40 ሄክታር እንዲሁ የሚዘጋጅ  ይሆናል፡፡

በተመሳሳይ በልደታ ክፍለ ከተማ ዲአፍሪክ አካባቢ ለመልሶ ማልማት 10 ነጥብ 43
ሄክታር ተዘጋጅቷል ፤ ቀደም በመልሶ ማልማት የኮንደሚኒየም ቤቶች ግንባታ ከተከናወነበት አጠገብ የሚገኘው የጌጃ ሰፈርም  16 ነጥብ 7 ሄክታር መሬት በመልሶ ማልማት ስራው ተካቶአል።

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማም የአሜሪካ ጊቢ ጨምሮ 36 ሄክታር ቦታም ይለማል ተብሎ ይጠበቃል።

የቀበሌ ቤቶችን ተከራይተው የሚኖሩ የአ/አ ነዋሪዎች በመልሶ ማልማት ምትክ የኮንዶሚኒየም ቤቶች የተሰጣቸው ሲሆን በደባልነትና በአነስተኛ ክፍያ ተከራይተው የሚኖሩ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ምትክ ቤት ባለመሰጠቱ እንደ አራት ኪሎ ባሉ አምና የተነሱ አካባቢዎች ዜጎች ለጎዳና ኑሮ ተዳርገው መታየታቸው የሚታወቅ ነው፡፡

ከመንግስት የእድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጋር እንዲጣጣም በማሰብ የአምስት ዓመቱ ዕቅድ ወደሁለት ዓመት የታጠፈ ሲሆን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ 70ሺ የጋራ የመኖሪያ ቤቶች ለመገንባት ተይዞ የነበረው ዕቅድ ከወዲሁ ከፍተኛ ትችት ስለገጠመው ወደ130ሺ እንዲያድግ ተደርጎአል፡፡

ይህም ሆኖ በተለይ የጋራ መኖሪያ ቤት ልማት፣  ቤት ለማግኘት ከተመዘገበው ጋር ሲነጻጸር እንዲሁም አስተዳደሩ ካለው አቅምና የአፈጻጸም ታሪክ ጋር ሲነጻጸር የዕቅዱን ስኬት ጥያቄ ላይ ጥሎታል።

ለኮንዶምኒየም ቤት ብቻ ከ800 ሺ በላይ ነባርና አዲስ ቤት ፈላጊዎች መመዝገባቸው የሚታወቅ ሲሆን በየዓመቱ 65 ሺ ቤቶችን እየገነቡ ይሳካል ቢባል እንኩዋን ተመዝጋቢውን ለማዳረስ በትንሹ ከ12 ዓመታት በላይ እንደሚፈልግ ታውቆአል፡፡

ይህ አፈጻጸም ደግሞ የቤት እጥረት በፍጥነት ለመፍታት ቃል ለገባው አስተዳደር ራሰምታት ነው ተብሎአል፡፡

ESAT

posted by Tseday Getachew

Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: