Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

ኑሮ በካንጋሮ ምድር (ክፍል ፫)

እዚያው ፉትስክሬይ ቁጭ ብለን ወግ በመሰለቅ ላይ ነን፡፡ ባለፈው ወዳጄ ስለ ‹‹ኢምፖርት›› አንሥቶ ነበር ያቆመው፡፡ እስኪ ይቀጥል፡፡
‹‹ምንድን ነው ኢምፖርት የሚያደርጉት ኢትዮጵያ ሄደው››
‹‹ሚስት ነዋ››
‹‹እንዴት ነው ደግሞ ሚስት ኢምፖርት ማድረግ ማለት››
‹‹እዚህ ሀገር ያለ ሐበሻ በሦስት መንገድ ነው ሚስት የሚያገኘው››
‹‹በምን በምን››
‹‹በኢምፖርት፣ በኤክስፖርትና በባላንስ››
‹‹ይሄ ትርጓሜ ያስፈልገዋል››
‹‹ኦኬ፤ ኢምፖርት የሚባለው ሀገር ቤት ትሄድና ሚስት ወይም ባል ይዘህ ስትመጣ ነው፡፡ ኤክስፖርት የሚባለው ደግሞ የውጭ ሀገር ሰው በተለይም የዚህን ሀገር ሰዎች ስታገባ ነው፡፤ ባላንስ ሠራህ የሚባለው ደግሞ ሁለት አበሾች እዚሁ ተገናኝተው ሲጋቡ ነው፡፡››
‹‹ታድያ የትኛው ነው የሚሻለው››
‹‹ሁሉም የራሱ ጣጣ አለው፡፡ ኢምፖርት ስታደርግ ከታደልክ ትዳር የጠማትን ወይም የጠማውን ታገኘዋለህ ወይም ታገኛታለህ፡፡ ካልታደልክ ደግሞ እዚህ ከመጣች በኋላ አቢዩዝ አደረገኝ ብላ ልትፈነግልህ ትችላለች፡፡ ወንዱም ትቷት ሊሄድ ይችላል፡፡ ወይም ይፋታሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እዚህ ኢምፖርት ተደርገው ከመጡ በኋላ ስቃያቸውን ያዩም አሉ፡፡ ውጭ እንሄዳለን፣ ባል እናገኛለን፣ አለፈልን ብለው ሳያመዛዝኑ ውጭ ሀገር ስለተባለ ብቻ ይመጡና አበሳቸውን ያያሉ፡፡ በተለይ ስደት ላይ ብዙ ዘመን ኖረው፣ እድሜያቸውን ጨርሰው፣ ራሳቸውን መልጠው፣ ሁለት ጠጉር አውጥተው ከሀገር ቤት ዘልላ ያልጨረሰች ሚስት የሚያመጡ ፌንት ይገጫሉ፡፡››
እንዴት ነው የሚገጩት››
‹‹አየህ አንተ ሃያ ዓመቷን ሱዳንና ኬንያ ከጫርካት በኋላ አባባ የምትልህን ቆንጆ ልጅ ስታመጣ፤ እርሷ እያማረባት ሲሄድ አንተ ግን እድሜ ሲያናጭርብህ ቅናቱን አትችለውም፡፡ የነገር አባቷ እንጂ ባሏ ስለማትመስል ሥጋት እየገባህ ይሄዳል፡፡  ያም ያም አንተን ረስቶ የሚስትህን ቁንጅና ሲያወራ እርሷ ተጨዋች አንተ ተመልካች የሆንክ ይመስልሃል፡፡ ያን ጊዜ አበሻነትህ ይነሣብሃል፡፡ አውስትራልያ መሆንክን ትጠላውና መንዝና ሞላሌ፣ ወልቃይት ጠገዴ፣ ሽሬ እንዳ ሥላሴ መሆን ያምርሃል፡፡ መሳደብ፣ መጨቃጨቅ፣ ሲብስም መማታት፣ ሲያልፍም አካል መጉዳት፣ በመጨረሻም ሕይወት እስከ ማጥፋት ትሄዳለህ፡፡
እዚህ ሜልበርንኮ አንዱ እልኩና ቅናቱ አልወጣለት ሲል ከሕንድ ቤት ቀይ ቃርያ ገዝቶ ሚስቱን በበርበሬ አጥኗታል፡፡ ስንቱ ሚስቱን ገድሏል፤ ስንቶቹስ ተደብድበውና ተፈንክተው በሐኪም ጥረት ከሞት ተርፈዋል፡፡ ኢምፖርት ዕዳው ብዙ ነው፡፡
የዚህን ሀገር ሰዎች አግብተው የሚኖሩ ብዙ አበሾች አሉ፡፡ በተለይ ሴቶቹ በዚህ ጎበዞች ናቸው፡፡ እነርሱ ጋር እስካሁን የሰማሁት የከፋ ችግር የለም፡፡ ባይሆን ወንዶቹ ፈተና ይገጥማቸዋል፡፡ ፈረንጅ ወዳጄ ፍቅራዊ (ሮማንቲክ) ነገር ይወዳል፡፡ እኛ ደግሞ ሃኒ፣ ስዊት፣ ዳርሊንግ የሚል ነገር አልለመድነው፡፡ እኔ ሐኒ የማውቀው ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ ማር በእንግሊዝኛ ሐኒ መሆኑን ነው፡፡ ስዊት – ጣፋጭ ነው፤ በቃ፡፡ ዳርሊንግ እዚህ ነው የሰማሁት፡፡ እኛ ደግሞ ቆፍጠን ያልን ነን፡፡ ‹ሌቱን ለአራዊት ቀኑን ለሠራዊት› ነው ወዳጄ፡፡ የኛ አኗኗር ለእነርሱ መሥሪያ ቤት ይሆንባቸዋል፡፡ እንኳን እነርሱ እዚህ ሀገር ቆየት ያሉት ሴቶች እንኳን ‹‹የኛ ወንዶች አባወራነት እንጂ ፍቅረኛነት አይችሉም›› ይሉናል፡፡
ከቻልክ እዚህ ሀገር ባላንስ መሥራት ነው፡፡ ተዋውቀህ፣ ሀገሩንም ዐውቀህ መጋባት፡፡ ችግሩ እዚህ እንደ አሜሪካ ዲቪ የለ፣ እንደ አውሮፓ በመርከብ የሚገባ የለ፣ ከየት ታመጣለህ፡፡ ወይ እዚያው ስደት ላይ ተጋብተህ ካልመጣህ በቀር፡፡ ››
‹‹ይህን ችግርኮ ተባብራችሁ መፍታት ትችሉ ነበር››
‹‹አንዳንዱን አበሻ ተባበር ከምትለው ተሰባበር ብትለው ይሻለዋል፡፡ ሁሉም በየጎጡና በየሠፈሩ ነው፡፡ አብዛኞቹ ቤተ ክርስቲያኖች እንኳን ዘርን መሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡ የአማራውን፣ የትግሬውን፣ የኦሮሞውን ቤተ ክርስቲያን ትለየዋለህ፡፡ ትግሬውም አንድ መሆን እያቃተው አድዋ፣ ሽሬ ሲል ታገኘዋለህ፡፡ አማራውም ወልቃይት፣ ጎንደር እየተባባለ ለብቻው ቸርች ይከፍትልሃል፡፡ ኮሙኒቲውም ለየብቻ ነው፡፡ እዚህ ሀገር የኦሮሞ፣ የሶማሌ፣ የሐረሪ፣ የትግራይ ኮሙኒቲዎች አሉ፡፡ አንደኛው ከአንደኛው ጋር የሚጠራጠሩ፣ የማይተባበሩ፡፡ ከትብብር ርቀው ንጽሕ ጠብቀው የሚኖሩ፡፡ በፍቅር የተጎዱ፣ ከኅብረት የጸዱ፡፡ አንዳንዶቹ ኢትዮጵያውያን ነን ይላሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ‹‹ምሥራቅ አፍሪካ›› የሚባል ሀገር ፈጥረውልሃል፡፡ …››
‹‹ኧረ እንዲያውም አዳሙ ተፈራ በጻፈው ‹‹ገመናችን በሰው ሀገር› የሚለው መጽሐፍ ላይ ሜልበርን የሚገኘው የኦሮሞ ኮሙኒቲ በ2010 እኤአ 25ኛ ዓመቱን ሲያከብር የጻፈውን አይቼ ገርሞኝ ነበር፡፡
‹‹The Oromo are indigenous African people from the north eastern ofAfrica.›› ይላል፡፤ ኢትዮጵያ ላለማለት አዲስ ሀገር ፈጥረዋል፡፡ ››
‹‹እይውልህ እንደዚያ ነው እንግዲህ፡፡ የሚገርምህኮ እዚህ ያለ ሰው መገንጠልን የሚጠላ ተገንጣይ መሆኑ ነው››
‹‹በዚህ ብቻ አይበቃም ትርጓሜ ያሻዋል – ብሏል ኪነ ጥበብ›› አልኩት፡፡
‹‹በውጭ ያለ ዳያስጶራ ስለ ኤርትራ መገንጠል ሁል ጊዜ እየተንገበገበ ያወራል፡፡ እርሱ ግን ራሱ በፈቃዱ ያለ ሪፈረንደም ተገነጣጥሏል፡፡ በምትቃወመው ነገር ውስጥ ራስህን እንደማግኘት ያለ አስነዋሪ አካሄድ የለም፡፡ በየስብሰባው ‹ዐንቀጽ 39› የምትባል ነገር ትነሣለች፡፡ ‹‹የብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠል›› የምትባለው፡፤ ይህች ዐንቀጽ እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ አልተደረገችም፡፡ እዚህ ግን ተግባራዊ ተደርጋለች፡፡ የተገበሯት ደግሞ የሚቃወሟት ሰዎች ናቸው፡፡ ለዚህ ነው ‹‹መገንጠልን የማይደግፍ ተገንጣይ›› ያልኩህ፡፡ አሁን ዘመን መለወጫ እየመጣ አይደለ? ሦስት ቦታ ነው ፕሮግራም የተዘጋጀው፡፡ ከዚያ መርጠህ እንደየብሔረሰብህ መሄድ ነው፡፡ ወዳጄ እዚህ ሀገር ጩኒ ይምጣብኝ››
‹‹ማነው ጩኒ ደግሞ››
‹‹ጩኒ ሰው አይደለም፤ ሕዝብ ነው››
‹‹ጩኒ የሚባል ሕዝብ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ መስማቴ ነው፡፡››
‹‹ጩኒ ማለት ቻይና ነው፡፡ እዚህ ሀገር ጩኒ ነው የምንላቸው፡፡ ጩኒ እርስ በርስ በመደጋገፍ ማንም አይችላቸውም፡፡ ብድር ይሰጡሃል፤ መረጃ ይሰጡሃል፡፡ ያቋቁሙሃል፡፡ ከዚያ ምርጥ ኢንቨስተር ትሆናለህ፡፡ ያለበለዚያ ደግሞ ወጥሬ እሠራለሁ ካልክ በቀላሉ የምትከራየው ቤት ይሰጡሃል፡፡ እንዲት ክፍል ተከራይተህ ኑሮ ሳይከብድህ ወጥረህ ትሠራና በዓመትህ ቀና ትላለህ፡፡ ወዳጄ ጩኒ አንገቱን ደፍቶ እየሠራ ልጁን ምርጥ ትምህርት ቤት ነው የሚልከው፡፡ ኮሙኒቲያቸው ልጆቹን በሚገባ ነው የሚረዳቸው፡፡ ስለዚህ ልጆቹ ውጤታማ ናቸው፡፡ እኛጋኮ ወላጆችና ልጆች አልጣጣም ብለዋል፡፡ ልጆቹን የቤት ሥራ ማን ያሳያቸው፡፡ ማን በትምህርት ያግዛቸው፡፡
አገርሽ ምንኛ መንደርሽ ምንኛ
አላውቅበት አልኩኝ ያንችን አማርኛ
ሲባል አልሰማህም፡፡ በምን ቋንቋ በምን ዕውቀት ከልጆቻችን ጋር እንግባባ፡፡ ልጆቻችን አያውቁም ብለው ንቀውናል፡፡ በዚህ የተነሣ ከትምህርት የሚያቋርጡት ብዙ ናቸው፡፡››
‹‹ቆይ ግን እዚህ መጥተው የተሳካላቸው የሉም››
‹‹ለዓይነት ያህልማ አሉ፡፡ መቼም ለስማችን መጠሪያ ቁና ሰፍተናል፡፡ ለአካባቢ ምርጫ እስከመወዳደር የደረሱ አሉ፡፡ ያው ከሆቴልና እንጀራ ቤት ባናልፍም ቢዝነስ ያላቸውም አሉ፡፡ በተማሩት ሞያ የሚሠሩም በመጠኑ አሉ፡፡ እኔ የሚገርመኝ ግን በኢሕአፓ፣ በኢሕአዴግ፣ በግንቦት ሰባት፣ በኢዲዩ፣ በቅንጅት ውስጥ ለመግባት እንጂ በምንኖርበት ሀገር በሚገኙ ፓርቲዎች ውስጥ ገብቶ፣ አባል ሆኖ፣ ተወዳድሮ ፓርላማ ለመግባት፣ የአካባቢ ተመራጭ ለመሆን የሚተጋ አበሻ ብዙ አናይም፡፡ አሜሪካ እንኳን ሚሊዮን የሚሞላ ኢትዮጵያዊ ተከማችቶ እስካሁን አንድ የአካባቢ ተወካይ እንኳን አለማግኘታቸው ይገርመኛል፡፡ እኛ በሀገራችን አምባሻ ነው የምንራኮተው፡፡ ለምሳሌ እዚህ አውስትራልያዊ ዜግነት ካለህ መምረጥ ግዴታህ ነው፡፡ እንደ አሜሪካ አይደለም፡፡ የመምረጥ ግዴታ አለብህ፡፡ ያለበለዚያ ቅጣት አለው፡፡ የፓርቲዎቹ አባል ስትሆንና ሳትሆን ዕድልህ ይለያያል፡፡ if you are not a member, you are a numberይሉሃል፡፡ ችግሩ ግን እዚህ ሀገር ተመልካች እንጂ ተጨዋች የለም፡››
‹‹ማለት››
‹‹ኳሱ ጉዳያችን ነው፡፡ ሜዳው አውስትራልያ ይባላል፡፡ ሕጉ የሀገሪቱ ሕግ ነው፡፡ ዳኛው ሲስተሙ ነው፡፡ ዋንጫው ውጤትህ ነው፡፡ እዚህ በሚገባ ተጫውተህ የስኬትን ዋንጫ መሳም ትችላለህ፡፡ ምን ያደርጋል ታድያ፡፡ በዙሪያህ ቆሞ ለምን ይህ አይሆንም? ለምን ይሄ አይደረግም? እገሌ ለምን እንዲህ ያደርጋል? እንዲህ በመሆኑ አኩርፌ ቀርቻለሁ፣ የሚል የዳር ተመልካች እንጂ ሜዳው ውስጥ ገብቶ ለመጫወት የሚፈልግ የለም፡፡ እዚህ ያለውን ሰው ‹‹ሰይጣን›› ከምትለው ‹ኮሙኒቲ› ብትለው ደንግጦ ያማትብብሃል፡፡ ተበላ፣ ተጠጣ፣ ተጣሉ፣ ተከፋፈሉ ብቻ ነው የምትሰማው፡፡ አንድ ወዳጄ ምን ይላል መሰለህ
የትልቅ ሰው ልጅ ቀረ በከንቱ
ሀገር ሳይገዛ ሳይባል አንቱ – እንዲህ ነው እንግዲህ፡፡
ካሮላይን ስፕሪንግስ፣ አውስትራልያ
posted by Tseday Getachew
Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: