Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

“በስልጣን ምክንያት ህወሓት ለሁለት የተከፈለ ይመስለኛል” – አቶ ገብሩ አስራት (ቃለ ምልልስ)

ሐገር ቤት የሚታተመው ሎሚ መጽሔት አቶ ገብሩ አስራትን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ አነጋግሯቸዋል። ዘ-ሐበሻ ለአንባቢዎቿ ይጠቅማል በሚል እንደወረደ አቅርባዋለች።

ሎሚ፡- ባለፈው መቀሌ ላይ “አረና” ሕዝባዊ ስብሰባ አከናውኖ ነበር፡፡ የነበረው ሁኔታ በአጠቃላይ ምን ይመስል ነበር;

አቶ ገብሩ፡- እንግዲህ የመቀሌውን ስብሰባ ከሁለት ጉዳዮች አንፃር ልንመለከተው እንችላለን፡፡ አንዱ ሕዝቡ እንዴት እንደተቀበለው ስብሰባውን … ሁለተኛው መንግስት ወይም በክልሉ ያለው ፓርቲ ስብሰባው እንዳይካሄድ ያደረጉትን ጫና በተመለከተ መመልከት ይቻላል፡፡ እንግዲህ አስቀድሜም መንግስት ስብሰባው እንዳይካሄድ የፈጠረውን ጫና ነው የማየው፡፡ እንግዲህ ትግራይ ውስጥ ገዢው ፓርቲ ህወሓት ነው፡፡ ህወሓት ከእሱ ውጭ ሌላ ፓርቲ እዛ ቦታ ላይ እንዲንቀሳቀስ ፍላጐት የለውም፡፡ ይህም ባፈለው 2002 ዓ.ም. በተካሄው ምርጫ ጠ/ሚ መለስ ትግራይ ውስጥ ምንም አይነት ክፍተት መኖር የለበትም፣ ምንም አይነት የሀሣብ ልዩነት መኖር የለበትም ብለው የተናገሩበትና በርካታ ስድቦች የተሰነዘረበት በተለይም በ”አረና” ላይ በርካታ ስድቦችን ያወረዱበት ጊዜ ነበር፡፡ እንግዲህ አሁን ያለው አመራርም የእሣቸውን “ሌጋሲ” ፈለግ እከተላለሁ የሚል ስለሆነ አካሄዱ ተመሳሳይ ነው፡፡ በትግራይ ውስጥ ምንም አይነት የፖለቲካ አስተሳሰብ እንዲኖር አይፈልግም፡፡ በህገ መንግስትም ፣ በቃልም ተቃዋሚ ቢኖር አንጠላም ሊሉ ይችላሉ፡፡ ዋናው ስጋታቸው በአካባቢው የተለየ ሀሣብ ፣የተለየ አመለካከት ፣ የተለየ አደረጃጀት እንዳይኖር ስጋትና ጭንቀት ያለባቸው ስለሆነ አጠቃላይ ድርጅቱን በእነሱ ስር የተደራጀ ሲቪክ ማህበረሰብ፣ የመንግስት ድርጅቶችን አደራጅተው ነው አንድ ፓርቲ በዛ አካባቢ ስብሰባ እንዳያካሂድ የሚያደርጉት፡፡ ባለፈው ጊዜም ስብሰባ ስናካሂድ እንደውም እነሱ በሚመሯቸው ድርጅቶች ፣ ኩባንያዎች /ኢፈርት/ ሠራተኞችን ሰብስበው በዚህ ስብሰባ ላይ መገኘት ከጠላት ጋር እንደማበር ይታሰባል ብለዋቸዋል፡፡ እና ስለዚህ ስራ ለማግኘት አትችሉም፣ ስጋት ላይ ትወድቃላችሁ ፣ ከጠላት ጋር የመተባበር ያህል አድርገን ነው የምናየው ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡

ይህንን ካሉ በኋላም በዚህም አላበቃም በኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ መሠረት እንደተፈቀደው ማንም ፓርቲ ሊቀሰቅስ ይችላል፡፡ መቀስቀስ የማይችለው በትምህርት ቤትና በቤተ እምነት ቦታ ውስጥ እንጂ በሌላ ቦታ ድምፅ ማጉያ ተጠቅሞ መቀስቀስ ይችላል የሚል ነገር አለ፡፡ መቀሌ ላይ ግን ሌላ ህግ አውጥተዋል ወይም አውጥተናል ነው የሚሉት፡፡ እኛ ግን አላየነውም፣ ህጉ ምንድነው የሚለው ማንኛውም እንቅስቃሴን ማጉያ ተጠቅሞ መቀስቀስ አይቻልም ነው የሚሉት፡፡ ይሄ እንግዲህ ከሀገሪቱ ህግ ፣ ከፌዴራል ህግ ጋር የሚጣረዝ ህግ ነው፡፡ ህግም ቢሆን ማለቴ ነው፡፡ ማውጣትም አይችሉም፡፡ እንደዚህ ያለ የምርጫ ቦርድ ሕግ እያለ መንግስት ወይም አስተዳደር ይሄንን ህግ ሊያወጣ አይችል፡፡ እኛ ህግ አውጥተናልና መንቀሣቀስ አትችሉም እያሉ ነው የሚናገሩት፡፡ ለምን ስንላቸው ደግሞ ድምፅ ማጉያው ማለት ነፍሰ ጡሮችንና በሽተኞችን ሊያውክ ስለሚችል መናገር አይቻልም ፡፡ በዛ ምክንያት ነው የከለከል ነው ይላሉ፡፡ ያም ሆኖ ግን መስኪዶች፣ ቤተክርስቲያኖች በድምፅ ማጉያ መልእክት ያስተላልፋሉ፡፡ ራሣቸው ህውሓቶችም በድምፅ ማጉያ ዳንኪራ እየመቱ የሚያጥለቀልቁበት ሁኔታ አለ፡፡ ለተቃዋሚዎች ነው ያልተፈቀደው እንጂ ራሣቸው በማይክራፎን ከተማውን የሚያውክ ነገር ይጠቀማሉ፡፡ ስለዚህ በዚህ ምክንያት ያንን ከለከሉን፡፡ እና ይሄ ህግ ይፈቅድልናል ብለው የኛ አባላትም ተንቀሣቀሱ፡፡ ግን አሰሯቸው፡፡ ሁለት ሦስት ጊዜም ነው ይህንን ያደረጉት፡፡ ሹፌሮችንና የተከራየነውንም መኪና አገቱ፡፡ ስለዚህ በዚህ መልኩ ስብሰባ እንዳይካሄድ አግተዋል፡፡ በንጋታው ደግሞ ስብሰባ ስናካሂድ እያንዳንዱ የቀበሌ አስተዳደር ማን እንደሚገባ እንዲመለከት እዛ አሰልፈዋቸው ነበር፡፡ አብዛኞቹም ሴቶች ናቸው፡፡ /የቀበሌ ሴቶች/ እነዚህን አሠልፈው ማነው ወደዚህ ስብሰባ የሚገባው የሚል ሊስት ይዘው አስቀመጡ፡፡

ጭራሽ ስብሰባ እንዳይካሄድ ነው የሞከሩት፡፡ በሌላም እያንደንዱ ቀበሌ ለሕዝቡ ስብስባ እንዲመጣ በፅሁፍ ጭምር ደርሰው እንድትገኙ የሚል አስተላለፉ ….የምንናገረው ስለመልካም አስተዳደር ፣ ስለ ንግድ ምናምን ነው ብለው መቅረታ የለባችሁም ወሣኝ ስብሰባ ነው ብለው ፣ እኛ ስብሰባ በምናደርግበት ቀን እነሱም ስብሰባ ጠሩ፡፡ ይሄ አካሄድ ደግሞ ምንም አይነት ሰው ወደኛ እንዳይመጣ የማድረግ አላማ ያለው ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን ሕዝቡ ፍላጐት ነበረው እንዲያውም ስብሰባውን እንድናካሂድ ግፊቱ የመጣው ከሕዝቡ ነበር፡፡ ያም ሆኖ እነሱ ባይከለክሉት ኖሮ አዳራሹም አይችልም ቦታም አይበቃም ነበር፡፡ ይሄም ሆኖ ወጣቱ ይሄን ሰብሮና ጥሶ አድራሹን ሞልቶታል፡፡ እና እዚህ ላይ ለማለት የምፈልገው በተለይ በሁለት ጉዳዮች ላይ እኛ ያቀረብነው በከተማ የሊዝ አዋጆች ላይ ፣ በነጋዴዎች የግብር ጫና፣ በዜጐች ሰብአዊ መብት እጦት እንደዚህ እንደዚህ ያሉ በርካታ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ ሕዝቡ ግን ትኩረት አድርጐ ያቀረበው ነፃነቱን እንደተነፈገ ነው፡፡ ትግራይም ውስጥ እንደተነፈጉ ተናጋሪዎች ናቸው፡፡ እኛ ንግግሩን ጀመርነው እንጂ የጨረሰው እዛ የተሰበሰበው ሕዝብ ነው፡፡
ሌላው ደግሞ ይሄ የሊዝ መሬት ዜጐችን ጭሰኛ ለማድረግ እየሞከረ እንዳለ በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡ መሬታችንን ቀሙን፣ በወላጆቻቸው /ውርስ/ ያገኙት መሬት ላይ ዋስትና እንዳጡ ፣ ይህንንም ተናገሩ፡፡ እንግዲህ የሚገርመው ስብሰባውን በፀሎት ለመጀመር ነው ፕሮግራም የያዝነው፡፡ ሁሉም የስብሰባው ታዳሚ ተነስቶ ለሰማእታት ፀሎት ሲያደርግ አንድ ወጣት ግን ከመቀመጫው ሣይነሳ ቁጭ ብሏል፡፡ ኋላ ላይ ግን ለምን በፀሎቱ ወቅት እንደተቀመጠ ምክንያቱን ተናገረ፡፡ ይሄ ወጣት ሲናገር “እኔ እናንተ ለምን ተነስታችሁ እንደምትፀልዩ አልገባኝም፡፡ ምክንያቱም እኔ አባቴ በትግሉ ተሰውቷል፣ ወንድሜና እህቴ ተሰውተዋል፡፡ ግን ያመጡልን ምንም ነገር የለም፡፡ ለምንድነው የምፀልየው; እኔ የምፀልየው ኢትዮጵያው ውስጥ ነፃነት ሲረጋገጥ፣ መብት ሲረጋገጥ ነው እንጂ አሁን ቆሜ አልፀልይም፡፡ ቤተሰቦቼ የተሰዉበት ሁሉ ተግባራዊ እየሆነ አይደለም፡፡ አፈና ፣ ሙስና ይህንን ለማምጣት ከሆነ የተሰዉት አልፀልይም፡፡ የምፀልየው ኢትዮጵያ ውስጥ ነፃነት ሲረጋገጥ ብቻ ነው” ብሏል፡፡ ይህ ንግግር ተሰብሳቢውን በጣም ያስገረመ ንግግር ነው የነበረው፡፡በአጠቃላይ መንግስትና የክልል ፓርቲ ስብሰባ እንዳይካሄድ ሕዝቡ ሌላ አማራጭ እንዳይሰማ ቢያደርጉም ሕዝቡ ግን ከፍተኛ ፍላጐት ነበረው፡፡ እንዲያውም እኛ ካሰብነው ጊዜ በላይ ተወያይቶ በጥሩ ሁኔታ ስብሰባውን አጠናቀናል፡፡

ሎሚ፡- አንዳንድን ዘገባዎች አሉ ይህ በሕዝብ ውስጥ የሚባለው ነው መረጃውን በእርስዎ አንደበት የማስተላለፉ መልእክት ደግሞ የእርስዎ ይሆናል፡፡ አረና ጥሩ እየተንቀሣቀሰ ቢሆንም የአባላቶቹ ወደ አሜሪካ መጓዝ በፓርቲው ላይ ችግር አይኖረውም ወይ የአቶ ስዬ እና የአቶ አሰግድን የሚያነሱ ሰዎች አሉ;

አቶ ገብሩ፡- ይሄ ምናልባትም የመረጃ ጉዳይ እንዳይሆን ለመናገር እሞክራለሁ፡፡ አቶ ስዬ የአረና አባል አይደሉም፡፡ የአንድነት አባል ናቸው፡፡ አቶ አስግድም ተመልሰዋል፡፡ አሁን ትግራይ ውስጥ ነው ያሉት፡፡ ስለዚህ የእኛ አባል ሆኖ ከሀገር ውጭ የሚገኝ የለም፡፡ ስለዚህ ይህን መረጃ ሕዝብ እንዲያውቀው ይገባል፡፡

ሎሚ፡- በህወሓት ውስጥ እውነት ልዩነት አለ; ህወሓት ለሁት ተከፍሏል የሚባል ነገር አለ ይሄን እንዴት ይገልፁታል;

አቶ ገብሩ፡- እኔ እንግዲህ በፖለቲካ ምክንያት ፣ በፖለቲካ ልዩነት ምክንያት ህወሓት ውስጥ መከፋፈል አልተመለከትኩም፡፡ ያም ሆኖ በስልጣን ምክንያት ህወሓት የተከፈለ ይመስላል፡፡ ይህም የታየው መቼ ነው ባለፈው የፓርቲው ጉባኤ በተካሄደበት ጊዜ ነባሮቹን ሙሉበሙሉ ጠራርጐ አስወጥቷል፡፡ ካድሬዎቹ ይሄ የሆነው ምንድነው ህወሓት ውስጥ የተጠናከረው በካድሬ ደረጃ አባል ነው ስልጣኑን የተቆጣጠረው እንጂ ራሱ ሀሣብ ሊያመነጭ የሚችል ፣ ሀሣብን ሊቀምር የሚችል፣ ንድፈ ሀሣብን በደንብ ተገንዝቦ ሊያስረዳ የሚችል ኃይል ህወሓት ውስጥ አሁን የለም፡፡ ከፋም በጀም የተሻለ አቅም ያላቸው ሰዎች ከዚህ ተገለዋል ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ስለዚህ የስልጣን ሽግሽግ ነው ለዚህ ያነሱት፡፡ ይህንን መሠረት አድርገው ነባር የተባሉትን ጠራርገው አስወጡ፡፡ እዚህ ላይ ግን ነባር የተባሉትንና ተጠርገው ከወጡት እኩል በፓርቲው ረጅም እድሜ ያላቸው ደግሞ እዛው ቀርተዋል፡፡ ስለዚህ ነገሩ የስልጣን ሽኩቻ ይመስላል ብሎ መናገር ይቻላል፡፡

ሎሚ፡- አሁን የኃይል ሚዛኑ የትኛው ክፍል ጋር ነው;
አቶ ገብሩ፡- ይሄ ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡ እንግዲህ የኢትዮጵያ ፖለቲካና ስልጣን የተመሠረተው በማን ላይ ነው የሚለውን መመልከቱ ጥሩ ነው፡፡ ሦስት አካሎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አንዱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማየት ይቻላል፡፡ ሁለት የመንግስት አካላት፣ ሦስተኛው መከላከያና የደህንነት አካላትን ነው ማየት የሚቻለው፡፡ አቶ መለስ በነበሩበት ጊዜ እነዚህ ሦስት አካላትን ተቆጣጥረው የሄዱበት ጊዜ ነበር፡፡ እንግዲህ የአቶ መለስ መንግስት አምባገነን መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ እንደ አምባገነንነቱም ሁሉንም የስልጣን አካላት ተቆጣጥረው በእጃቸው ውስጥ አስገብተው ቆይተዋል፡፡ እንደውም አሁን ኢህአዴግ ተዳክሟል የሚያሰኘው ምንድን ነው በአንድ ሰው ተሰባስቦ ፣ የአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭ፣ ስልጣን የነበረው አሁን ተበታትኗል፡፡ ከስልት አንፃር ይሄ መዳከምን ያሣያል፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ ስልጣኑ የት ላይ ነው የሚለው ነገር በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ እንደ አቶ መለስ ተጠናክሮ የወጣ ሰው የለም፡፡ የአቶ መለስ ፍላጐት ቀድሞም ምንድነው የፑቲን አይነት አስተዳደር ነው በዚህች ሀገር ላይ ፍላጐታቸው የነበረው፡፡ ደካማውን ፊት ላይ አስቀምጠው እሣቸው ከኋላ ሊነዱት ነበር አቶ ኃ/ማርያምንና ሌሎችንም ወደ ስልጣን ያመጡት፡፡

ያም ሆኖ ግን እሣቸው አልቆዩም፡፡ አቶ ኃ/ማርያም በዚህ አጋጣሚ ስልጣን ያዙ፡፡ አሁን አቶ ኃ/ማርያም መከላከያውንና ደህንነቱን በእጃቸው ለመቆጣጠር ይችላሉ 1111 የሞራል ብቃትስ አላቸወይ; የፖለቲካው ብቃትስ አላቸወይ; የሚለው ጥያቄ የሚያስነሳ ነገር ነው፡፡ ፓርቲውንስ ቢሆን እንግዲህ ነባሮች ዳግም ተመልሰዋል ብአዴን ውስጥ አቶ መለስ እያሉ ውጡ ተብለው ታዘው ወጥተው የነበሩትም እንደገና ተመልሰው መጥተዋል፡፡ እነዚህንስ ለማዘዝ ይችላሉ ወይ;ከፍተኛ ውሣኔዎች ላይ የማዘዝ አቅም ይኖራቸዋል ወይ; የሚለው አንድ ጥያቄ ነው፡፡ እንግዲህ በመንግስት የሚባሉት ፣ በፓርላማ፣ በካቤኔ ውስጥ የዚህ ነፀብራቅ ነው፡፡በደህንነቱ፣ በመከላከያው የማዘዝ ስልጣን ከሌለህ በመንግስት ውስጥም የማዘዝ ችሎታህ አነስተኛ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ችግሩ የስልጣን ክምችት በአንድ አካል ላይ አለ፡፡ ይሄ ነው የሚወሰነው፡፡ ደህንነቱም ሆነ መከላከያው ትልቅ ተፅእኖ አለው በኢትዮጵያ፡፡ እንደውም ወሳኙ እሱ ነው፡፡ እሱን ማዘዝ፣ ማሰማራት ፣ እሱን መቆጣጠር የማይችል ኃይል በኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይል ይዣለሁ ማለት አይችልም፡፡ ይህንንስ ማድረግ ይችላል ወይ; አሁን ያለው አመራር ለሚለው ነገር ጥያቄ ውስጥ ያስገባል፡፡ ፓርቲዎችም ቢሆን ከአቶ መለስ ሞት በኋላ የየራሣቸው ነፃነትና መብት ለማስከበር አዝማሚያም እየታየባቸው ነው፡፡ የብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ህወሓት በአጠቃላይ የፖለቲካ ሂደት ላይ ተፅእኖ ለማሣደር እየሞከሩ ነው ያሉት፡፡ በይፋ ያልወጣ ሽኩቻ እየታየ ነው፡፡ ውስጥ ለውስጥ፡፡ ድሮ የነበረው የአንድ ግለሰብ ተፅእኖ አሁን የመሰበር ሁኔታዎች ነው ያሉት፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉንም ለመወሰን ኃይሉም አቅሙም ያለው የለም፡፡ የሚፈለገው እሱ ነው ወይ ሌላ ጥያቄ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሄ የአቶ መለስ ሌጋሲ የሚባለው ግን እንደዛ ያለ ሰው ካልፈጠረ በስተቀር ጥንካሬ አለው ብሎ ለማለት አይቻልም፡፡

ሎሚ፡- አሁን እንግዲህ በስርአቱ ውስጥ ሙስና በከፍተኛ ሁኔታ መንሰራፋቱ ይነገራል፣ የሚታይም ነገር ነው፡፡ከሀገር ውጭም ገንዘብ የማሸሽ ሁኔታ አለ ይሄን እንዴት ይመለከቱታል;

አቶ ገብሩ፡- እንግዲህ ሁልጊዜም እንደምለው ራሱ የሙስና ምንጭ በኢትዮጵያ ያለው የሙስና ምንጭ የለሚው ነገር ካልታወቀ መፍትሄም አይገኝለትም፡፡ ኢህአዴግ ሙስናን እየታገልኩ ብሎ ለማስመሰል የተወሰኑ ባለስልጣኖችንና ነጋዴዎችን ያስራል፡፡ ይፈታል፡፡ ግን ይሄ መፍትሄ ነው ወይ; በኢትዮጵያ የሙስና ምንጭ መሠረት የሆነው እነዚህ ነጋዴዎች ናቸው ወይ; የተወሰኑ ባለስልጣናት ናቸው ወይ; የሚለውን ነገር ማንሣቱ የሚጠቅም ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሙስና ሊቀንስ፣ ሊቃለል የሚችለው ከስርአቱ ጋር በቀጥታ ተያያዥነት አለው፡፡ የአንድ ስርአት ፓርቲ አገዛዝ ከሆነ ዞሮ ዞሮ ሙስናን ነው የሚያነግሰው፡፡ደጋፊዎቹን ያጠናክራል፣ በሀብት ያጠናክራል፣ በገንዘብ ያጠናክራል፣ ፖሊሲው ነው፡፡ አባሎቼ የሚላቸውን ቢሰርቅ ፣ ቢዘርፍ ምንም ሊላቸው አይችልም፡፡ ፖለቲካውን የሚቃወሙ ሊነካኩ የሚችሉ ሰዎች አንዳንድ ጊዜም በሰውም ምንም ለውጥ አያመጣም ብሎ የሚያስባቸውን ሰዎች በሙስና ይቀጣል እንጂ ከመሠረቱ ስርአቱ ነው፡፡

እንደሚታወቀው ይሄ በውጭ ሀገር ገንዘብ አላቸው ወይ; አስቀምጠዋል ወይ; የሚለው ነገር በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን የአለም ተቋማት እንደሚነገረው የሸሸው ገንዘብ በርካታ ነው፡፡ ይሄ ገንዘብ የማነው የኔ ነው የሚል ባይታወቅም በኢትዮጵያ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እየሸሸ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ግን ወደዛ መሄድ አያስፈልግም፡፡ እዚህ ሀገር ያለው ሀብት ከየት መጣ የሚለው ነገር ቢጠየቅ እኮ መልስ የለም፡፡ሰርቶ ነው ወይ; ከደሞዙ ነው; በተለይ አንድ የመንግስት ባለስልጣን ትላልቅ ቤቶችን የሚያሰራ ደሞዝ አለው ወይ; ህንፃዎችን የሚያሰራ ደሞዝ አለው ወይ; ብዙ ሀብት ቤተሰቦቹን በከፍተኛ ደረጃ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውጭ ድረስ ልኮ የሚያስተምር ደሞዝ አለው ወይ ተብለው ቢጠየቁ የኢህአዴግ አመራሮች መልስ የላቸውም፡፡ ስለዚህ ሙስናው የራሱ የስርአቱ ባህሪ ነው፡፡ ምክንያቱም ሙስናን እንታገል ቢባል፣ ኢህአዴግ በሚከተለው አግባብ እንዴት ሙስናን መታገል ይቻላል; ነፃ ማህበረሰብ ፣ ሲቪል ማህበረሰብ በሌለበት እኮ ይሄ ሙሳኝ አለ ብሎ መቃወም አይቻልም፡፡ ጠንካራ ነፃ ጋዜጦች “Invest get journalism”መስራት በማይቻልበት ሁኔታ እንዴት ነው ሙስናን መዋጋት የሚቻለው; የመንግስት ተጠያቂነት ግልፅነት በሌለበት እንዴትነው ሙስናን መታገል የሚቻለው; ሕዝብ ሰልፍ ወጥቶ መቃወም በማይችልበት፣ ተሰብስቦ መነጋገር በማይችልበት እንዴት ነው ሙስናን መታገል የሚቻለው; ስርአቱ በባህሪው አምባገነናዊ ስርአት ነው፡፡ “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” ብሎ የአንድ ፓርቲ ፈላጭ ቆራጭነት አረጋግጣለሁ የሚል መንግስት ከሙስና አይነፃም፡፡ ነፃ ሊሆን አይችልም፡፡ በአለምም ያየነው፣ በአፍሪካም የሚታየው ፓርቲዎች የህብረተሰቡን እንቅስቃስቃሴ በሙሉ “ገዢ ፓርቲዎች” ሕዝቡ ትንፍሽ እንዳይል ፣ እንዳያጋልጥ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ኢህአዴግም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ መታየት ያለበት የአንድና ሁለት ባለስልጣን የማሰርና የማጋለጥ ጉዳይ አይደለም፡፡ ዋናው ነገር ስርአቱ በቁርጠኝነት መታገል የሚችል እስከሆነ ብቻ ነው፡፡ ይሄንን ደግሞ ኢህአዴግ አይችልም ያውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ መሬት እንደተዘረፈ ያውቃል፡፡ እሱ ነው የሚያዘርፈው፡፡ የመንግስት በጀት እንደተዘረፍ ያወቃል ግን እራሱ ነው የሚያዘርፈው፣ የመንግስት ልማት ተቋማት በሚሊዮኖች ይዘረፋሉ ያውቃል መንግስት ግን መፍትሄ የለውም፡፡ መፍትሄም ከኢህአዴግ ይመጣል ብሎ ማሰብ የዋህነት ይሆናል፡፡ ምንም ሊመጣ አይችልም፡፡

ለዚህም ነው ከአመት አመት እየተባባሰ እንደውም አሁን የስርአቱ ዋና መገለጫ እየሆነ ያለው ከዚህ በመነሣት ነውና፡፡ አንድ እንደ አቅጣጫ መታየት ያለበት፣ መረሳት የሌለበት ሙስና ከስርአቱ የሚመነጭ ስለሆነ ፣ በፀረ ሙስና በኩል የተወሰኑትን በማሰር የሚቋጭ አይደለም፡፡ሰፊ ነፃነት፣ሰፊ መብት፣ ጠንካራ የህግ የበላይነት፣ ነፃ ባለስልጣኖችን ሊጠይቅ ሊያስር የሚችል አቃቢ ህግ “ነፃነት ያለው” ፍርድ ቤት ሊወስንባቸው የሚችል ያለምንም ተፅእኖ ከሌለ ሙስናን መታገል እንዴት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ታዩታላችሁ ሙስና ኢህአዴግ እስካለ ድረስ እየባሰበት የሚሄድ ይሆናል፡፡ አሁን ተራ ሙስና አይደለም የማፍያ አይነት የተደራጀ ሙስና ነው እየተካሄድ ያለው፡፡
ሎሚ፡- እንደታዘቡት ከሆነ ፣የሙስሊሙ ጥያቄ አለ ይሄን እንዴት ይመለከቱታል; ሌላው ከቅርብ ቀናት ወዲህ በመንግስት በኩል አክራሪነት ፣ ሽብርተኝነት፣ አሸባሪነት የሚሉ ቃላት ይሰማል ይሄስ በእርስዎ እይታ እንዴት ታዘቡት;

አቶ ገብሩ፡- እንግዲህ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ጊዜ ተናግረናል፡፡ እኔ እንግዲህ ኢህአዴግ አንዳንድ ችግሮች ሲነሱ የሚሄድበት አግባብ ችግሮች አሉበት፡፡ የሙስሊሙ ጥያቄ ፣ የአባይ ጥያቄ፣ የብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ እነዚህ በዚህ አገር ከባድ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ በተለይ በሙስሊሞች ጉዳይ መታየት ያለበት ካለው ማህበረሰባዊ እድገት፣ አለም አቀፋዊ ሁኔታ መንገድ ነው መታየት ያለበት፡፡እንግዲህ የሙስሊሞች ጥያቄ መታየት የጀመረው እኮ መለስ በነበረበት ጊዜ ነው፡፡ እንደማስታውሰው እኔ ከተለያዩ የአለም ክፍሎች የተውጣጡ ፣ የሙስሊም አባላት መጥተው ከአቶ መለስ ጋር ተገናኝተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሙስሊሞች አያያዝ የሚያሳስባቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ጥያቄዎችም ያኔ አንስተዋል፡፡ ካነሷቸው ጥያቄዎች መሀል፣ የበአላት ማክበር፣ ወለድ የሌለው ባንክ የመክፈት ጉዳይ እንዲህ እንዲህ ያሉ ወደ አስር የሚጠጉ ጥያቄዎች አንስተው ነበር፡፡ በወቅቱ እናየዋለን የሚል መልስ ነው የተሰጣቸው፡፡ ከዛ በኋላ የታየም ነገር የለም፡፡ ውስጥ ለውስጥ የሚነሱ ጉዳዮች አሉ፡፡ ብዙ የመብት ጥያቄዎች፡፡ ይሄ እያለ ግን ኢህአዴግ ይሄን የሚያባብስ እርምጃ ወስዷል፡፡ ምንድነው እንደምታስታውሰው በተለይ “ፌድራል ጉዳዮች” የሚባል የመንግስት አካል የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን በሌላ ሙስሊም ለማስጠመቅ ሙከራ አደረገ፡፡ “አልሀበሽ” የሚባል ገንዘብ አውጥቶ ይሄን ተማሩት አለ፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሙስሊም በዚህ ውስጥ እንዲጠመቅ ሙከራ አደረገ፡፡ ሙስሊሞች ተቃወሙት ፣ ሃረር ላይ ….. ሚኒስትሩ ሣይቀር ስብሰባ አደረገ፡፡ ይሄ ጣልቃ ገብነት ነው፡፡ …. አንድን ኃይማኖት በሌላ ኃይማኖት በዚህ እመን ማለት ጣልቃ ገብነት ነው፡፡ ያለጥርጥር ነገሩ ከዚህ ተነሣ ከዛ የአወሊያ ትምህርት ቤትም ተነሣ ይሄ የቆየ ነው፡፡ ድሮ የነበረ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ያንን ለመቆጣጠር ሞከረ፣ ያም አይሆንም የሚል ምላሽ ቀረበ፡፡

እንደገና የምርጫ ጉዳይ ተነሣ፡፡ ቀላል ጥያቄ በጣም ቀላል …. ምርጫው በመስኪዶች ይሁን የሚል፡፡ ይሄ ሁሉ ኢህአዴግ የማያዝበት መንገድ ግን ሽንፈት ነው የሚመስለው፡፡ አንዳንዶቹን ጥያቄዎች መመለስ ሽንፈት ስለሚመስለው ነገሩን ያጦዘዋል፡፡ ወደ አስቸጋሪ ሁኔታ ይገፋዋል፡፡ የኢትዮጵያን ሙስሊሞች እንደማውቃቸው በመሠረቱ በጣም ተቻችለው በመኖር ተግባብተው በመኖር የሚታወቁ ሙስሊሞች ናቸው፡፡ የሱፊ እምነት ፣ ካተሚያ እምነት በኢትዮጵያ ያለው ተቻችሎ የኖረና የሚኖር ሙስሊም ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን ልክ በክርስቲያኑ ውስጥ እንደሚታየው ድሮ የሚታወቁት ኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክ አልፎ አልፎ የድሮ ፕሮቴስታንቶች ይታወቁ ነበር፡፡ በኋላ ላይ ግን ጴንጤዎች መጡ፣ ሌሎችም መጡ፣ ጆባ መጣ ይሄ በነበረው አይን ሲታይ ፅንፈኛ ነው እና ክርስቲያኑ ሁሉ ያኔ ተደናገጠ ግን ሊያቆመው አይችልም፡፡ ከአለም ጋር ይገናኛል፡፡ ሕዝቡ ብዙ ብዙ እምነቶች አሉ ተቀብሎ ያምናል፡፡ በሙስሊምም የሚሆነው ይሄ ነው፡፡ ዋህቢያ መጣ፣ ሳላፊ መጣ ሌሎችም ሌሎችም ሺሀ ሊነሳ ይችላል፡፡ ይሄ እንግዲህ መንግስትም ይሁን ማንም ሊያቆመው አይችልም ይሄንን ዝንባሌ፡፡ መንግስት ማድረግ ያለበት እነዚህ አስተያየቶች፣ እነዚህ መስመሮች፣ ከህገ መንግስቱ ወጥተው፣ ሰላም እንዲኖር፣ መረጋጋት እንዳይጠፋ መቆጣጠር እንጂ ከዛ ባለፈ ይሄ እምነት ነው ትክክለኛ ይሄ ደግሞ ትክክለኛ አይደለም ብሎ መናገር መብቱ አይደለም፡፡ ማስተማርም የለበትም፡፡ ግን ኢህአዴግ ትንሹን ነገር አግዝፎ ስለሚያየው ነው፡፡ ኢህአዴግ መንግስት ሆኖ ከግለሰብ ጋር እየተጣላ የሚውል መንግስት ነው፡፡ በጣም ነው የሚያሣዝነው፡፡ አይንቀውም ትንሽ ነገር ነው እቆጣጠረዋለሁ ብሎ አያምንም፡፡ ሰራዊትይዞ ፣ ስፍር ቁጥር የሌለው ፌድራል ፖሊስ ፣ የክልል ፖሊስ፣ የፀጥታ ኃይሎች ይዞ እያለ በሁለት ሦስት ሰዎች እየተሸበረ ነው ያለው፡፡ ኢህአዴግ ሽብር ነው ውስጡ ያለው፡፡ ስለዚህ በሙስሊሙ ይሄ ነገር ሲነሳ ይሸበራል፡፡ ሲሸበር ደግሞ ለዚህ ምላሽ የሚሰጠው በማተራመስ ነው እንጂ ነገሮችን ከስትራጄክ አንፃር አያያቸውም፡፡ ሰልፍ ያስወጣል፣ አገሪቱን በሙሉ በስብሰባ ያስወግዛል፣ በየቀበሌው ፣በየከተማው …. አውግዙ ይሄ መፍትሄ አይሆንም ፣ ሰልፍ ውጡ ይሄ ፕሮፖጋንዳ ነው፡፡ከፕሮፖጋንዳ በዘለለ ነው መታየት ያለበት፡፡ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ሲነሱ በስትራ

ቴጂክ እንጂ በፕሮፖጋንዳ ሊፈቱ አይችሉም፡፡ ምን ማለቴ ነው የአባይ ጉዳይ ሲነሳ ያነሣነው ነገር ነበር፡፡ አባይን ስንነካ አንድ ስትራቴጂክ ጉዳይ ነው ለኛ …. ስትራቴጂክ ጉዳይ ስለሆነ በአንድ ፓርቲ ፣ በአንድ ክፍል ብቻ መፍትሄ የሚያመጣ አይደለም፡፡ መግባባት ያስፈልጋል፡፡ ተቃዋሚዎች ሁሉ ለዚህች ሀገር ኃላፊነት አለብን የሚሉ ተግባብተው መሄድ አለባቸው፡፡ ምክንያቱም ይሄንን ትልቅ ነገር ከነኩ በኋላ ተባብረው መስራት እንጂ የሚያስፈልገው እንዲሁ “አካኪ ዘራፍ” ብሎ ማሰናበት አይቻልም፡፡ የሙስሊም ጥያቄ ሲነሳ እኔ ኢህአዴግ እንደሚያየው አያስደነግጠኝም፡፡ ያን ያህል የሚያስደነግጥ ፣ የሚያስፈራ፣ የሚያሸብር ነገር የለም፡፡ መቆጣጠር የሚቻል ነው፡፡ ያም እሱ በሚያስበው ችግር ቢኖራም፣ እሱ ባወጣው የፕሮፖጋንዳ አቅጣጫ መመራት ሣይሆን ፣ እስቲ እንነጋገርበት ሙስሊሞችን ሲያነጋገር አንዱን ክፍል ብቻ ማነጋገር የለበትም፣ ሁሉንም አነጋግሮ መፍታት ይችላል፡፡ ከተቃዋሚዎችም ጋር ቢሆን መቶ በመቶ የሚቃወሙትንም ማነጋገር እንጂ የራሱን ደጋፊዎች ብቻ አንድ የዩንቨርስቲ ምሁር ማናገር ተገቢ አይደለም፡፡ ስለኔ ምን ይላል ብሎ የተለየ ሀሣብ ሊያገኝ ይችላል፡፡ ስለዚህ የሙስሊሙም ጥያቄ ከአጠቃላይ የዴሞክራሲና የሰብአዊ መብት ጋር ተያይዞ መታየት ያለበት ነው የሚመስለኝ፡፡

Short URL: http://www.zehabesha.com/amharic/?p=7183

posted by Tseday Getachew

 

Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: