Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

በዛሬው ሰልፍ ላይ ከወጡት መካከል ከ200 በላይ ሙስሊሞች ታሰሩ

 

 

(ዘ-ሐበሻ) ኢሕአዴግ በሃይማኖቶች ጉባኤ ስም ሽብርተኝነትንና አክራሪነትን ለመቃወም የጠራው ሰልፍ ላይ ፖሊስ ሙስሊሙን ብቻ እየመረጠ ማሰሩን ድምፃችን ይሰማ በፎቶ ግራፍ ጭምር ባወጣው መረጃ አስታወቀ። “ኢሕአዴግ በጠራው ሰልፍ ላይ እንዲገኝ በየወረዳው አውቶቡስ የተዘጋጁ መሆኑ ሲታወቅ አውቶብሶችን ደልድለው ሰውን ያስገቡት የወረዳ ሀላፊዎች ናቸው፡፡ የአውቶብሶቹ ወጪዎች የተሸፈነውና ስምሪት የተደረገው በመንግስት ሲሆን የሰልፉ አዘጋጅ የተባለው የአዲስ አበባ የሃይማኖቶች ጉባኤ የሚባል “አሻንጉሊት” እንዳልታየ ድምጻችን ይሰማ ገልጿል። ኢሕአዴግ በዛሬው ሰልፍ 1 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ወጣልኝ ቢልም አብዛኛው ሰልፈኛ ከድምጻችን ይሰማ የመጡ ናቸው።

በተለይ በመጨረሻው ሰዓት ላይ ድምጻችን ይሰማ ኢሕአዴግ በጠራው ሰልፍ ላይ ተገኝቼ “እኔም አክራሪነትን እንደምቃወም እገልጻለሁ” ባለው መሠረት በርከት ያሉ ሙስሊሞች ወደ መስቀል አደባባይ የተመሙ ቢሆንም ከመንገድ ላይ ፌደራል ፖሊሶች በመቆም ሙስሊሞቹን እየመረጡ ወደ ሰልፍ እንዳይሄዱ ሲያደርጉ እንደእዋሉ የአይን እማኞች ገልጸዋል። ከፖሊስ ተርፈው በመስቀል አደባባይ የተገኙት ሙስሞች ደግሞ ተቃውሟቸውን ለመግለጽ እጃቸውን ወደ ጆሯቸው ባስጠጉ ቁጥር የደህንነትና የፖሊስ አካላት ለምን እጃችሁን አስጠጋችሁ እያሉ ውክቢያ ሲፈጽሙ ነበርና “ለምን ወደዚህ ሰልፍ መጣችሁ?፡ በሚል ሲያዋክቧቸው እንደዋሉ ተዘግቧል። ፖሊሶቹ ስም እየጠየቁ የሙስሊም ስም ያለውን ይመልሱ እንደነበርም ከተገኙት መረጃዎች ለማቀቅ ተችሏል።

በመስቀል አደባባይ ከተገኙት ሙስሊሞች ውስጥ ቁጥራቸው ወደ ከ200 ባልይ የሚሆኑትን ፖሊስ ይዞ ያሰረ ሲሆን ሰልፉ እስኪጠናቀቅ ድረስ በኢግዚብሽን ማዕክል አስሯቸው ከቆየ በኋላ በአውቶቡስ ወዳልታወቅ ሥፍራ እንደወሰዳቸው የደረሰን መረጃ ያመለክታል። ዘ-ሐበሻ ጉዳዩን ለማጣራት ባደረገችው ሙከራ እስካሁን እነዚህ ሙስሊሞች ያሉበት ያልታወቀ ሲሆን ምናልባትም “ሽብር እና ሁከት ለመፍጠር” በሚል መንግስት አንድ ድራማ በመሥራት ክስ ሊመሰርትባቸው እንደሚችል ታዛቢዎች ይናገራሉ።

ዛሬ ኢሕአዴግ በጠራው ሰልፍ ላይ በመገኘት “የትኛውንም አይነት አክራሪነት እንደማንቀበልና እንደምናወግዝ ዛሬ በድጋሚ በተግባር አሳይተናል” ብሏል ድምጻችን ይሰማ ከሰልፉ መጠናቀቅ በኋላ።

በሌላ በኩል ከሕወሓት የንግድ ድርጅቶች ውስጥ አንዱ የሆነው ራድዮ ፋና የዛሬውን ሰልፍ በማስመልከት ያቀረበው ዘገባን ለግንዛቤ እንዲረዳችሁ በሚል እዚህ አምጥተነዋል።

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች አክራሪነትንና ሽብርተኝነትን በመቃወም አደባባይ ወጡ

አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 26 ፣ 2005 (ኤፍ. ቢ. ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር በአስሩም ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎች አክራሪነትና አሸባሪነትን በመቃወም ዛሬ በመስቀል አደባባይ ሰለማዊ ሰልፍ አካሄዱ።

ሰለማዊ ሰልፉን የጠራው የአዲስ አበባ ከተማ የሃይማኖትች ጉባኤ ጽህፈት ቤት ሲሆን ፥ ለዛሬ ማለዳ በተጠራው ሰለፍ ላይ ቁጥሩ ከአንድ ሚለየን የሚልቅ ሕዝብ በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ተሳተፏል።

የማለዳው ዝናብና ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ ሳይበግረው ከአዲስ አበባ ከተማ ሁሉም አቅጣጫዎች በመትመም መስቀል አደባባይ የተገኙ ነዋሪዎች “ ሕገ መንግስታችን በአክራሪዎችና ደጋፊዎቻቸው አይናድም ” ፣ “ አክራሪነት ቻው ቻው ” ፣ “በኪራይ ሰብሳቢዎች ስር የተጠለሉ አክራሪዎችን አንሻም” ፣ “የምንፈልገው ሰላምና ሰለም ብቻ ነው ” ፣ “ መንግስት በአክራሪዎችና አሸባሪዎች ላይ አስፈላጊውን እርርምጃ ይውሰድልን ” ፣ ” የፀረ ሽብርተኝነት ህጉን እንደግፋለን ” የሚሉና ሌሎች በርከት ያሉ መፈክሮችን አሰምተዋል።

ከአዲስ አበባ ከተማ የሃይማኖትች ጉባኤ ጽህፈት ቤት የተወከሉ የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖቶች አመራሮች ለሰልፈኞቹ ባሰሙት ንግግር ነዋሪዎቹ የጽህፈት ቤቱን ጥሪ አክብረው በመገኘታቸው አመስግነው ሰልፉ ኢትዮጵያ የምትታወቅበት መቻቻል አንድናትና እኩልነት በድጋሚ የተረጋገጠበት መሆኑን አመልክተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ዲሪባ ኩማም ባሰሙት ንግግር መንግስት የነዋሪዎችን ጥያቄ በማክበር በአሸባሪዎችና አክራሪዎች ላይ ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሰላማዊ ሰልፉ ተሳፊዎች በሰልፉ ጠሪዎችና በክብር እንግዶች የተላለፉ መልዕክቶች ከሰሙ በኋላ የኢትዮጵያን ህዝብ መዝሙር በመዘመር ወደየመጡበት ተመልሰዋል።

Short URL: http://www.zehabesha.com/amharic/?p=6933

 posted by Tseday Getachew

Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: