Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

Archive for the month “September, 2013”

Hiber Radio: “ኢትዮጵያ የሽማግሌ ያለህ እያለች ነው” – ዶ/ር አክሎግ ቢራራ

 

የህብር ሬዲዮ ዕሁድ መስከረም 19 ቀን 2006 ፕሮግራም

 

<<…ሰልፍ ፈቅደናል ብለው የሰሩት ማደናቀፍ ለኢህአዴግ እጅግ አሳፋሪ ተግባሩ ነው ። ..በዚህ ተስፋ ሳንቆርጥ የአዲሱን ዓመት ዕቅድ በማውጣት በሁሉም ቦታዎች መስቀል አደባባይን ጨምሮ ኢህአዴግ ተገዶ ሰልፍ እናደርጋለን….>> ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ለህብር ከሰጡት ቃለ ምልልስ የተወሰደ

 

<<…ኦባማ ኬር አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ይጠቅማል…>>

 

አቶ ተካ ከለለ በአትላንታ የቲኬ ሾው አዘጋጅ

 

https://i1.wp.com/www.zehabesha.com/amharic/wp-content/uploads/2013/02/habtamu-150x150.jpg

                                                            ጋዜጠኛ ሃብታሙ አሰፋ

<<…በኢትዮጵያ የኑሮ ውድነቱ ዜጎች ባህላዊ እሴቶቻቸውን ጭምር እንዲተው ህጻናት በበዓል የሚያደርጓቸውን ጨዋታዎች እንዲተው ጭምር አድርጓል። ብዙዎቹ የጉራጌ ልጆች ለመስቀል አገር ቤት ለመሄድ አቅም አጥሯቸዋል። በአዲስ አበባ ለዕንቁላል እንኳ ሌሊት ወጥተው ሰልፍ የሚወጡ በጥበቃ የሚንቃቁ አሉ…>> ስለ መስቀል በዓል ከተጠናቀረው ዘገባ

አልሸባብ እውን ለኢትዮጵያ ስጋት አይደለም(ልዩ ዘገባ)

 

<<…ኢትዮጵያ የሽማግሌ ያለህ እያለች ነው…የተቃዋሚ መሪዎች አብረው በውህደት ተብሎ ተብሎ ባይሳካም ቢያንስ አብረው ተባብረው መስራት አለባቸው። በውጭ ያለነውም ግፊት በማድረግ…>> ዶ/ር አክሎግ ቢራራ

 

(ሌሎችም ቃለ መጠይቆች አሉን)

 

ዜናዎቻችን

 

ግብጻውያን በኢትዮጵያ ላይ ዛሬም ማጉረምረም ቀጥለዋል

 

ስዊድናዊ ዜግነት ያላት ኢትዮጵያዊቷ አትሌት አበባ የዘረኝነት ሰለባ መሆኑዋን ገለጸች

 

የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት ሰልፍ በፖሊስ ታግቶም ከ80 ሺህ ሰው በላይ ወጥቶ ተቃውሞውን አሰማ

 

ዶ/ር ነጋሶ ኢህአዴግ ተገዶ መስቀል አደባባይን ጨምሮ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ እንቅስቃሴው ይቀጥላል አሉ

 

የመን በኤርትራ ተያዙ ያለቻቸውን ዜጎቿን ለማስለቀቅ መዘጋጀቷን ገለጸች

 

የግንቦት ሰባት ሕዝባዊ ሐይል በኖርዌይ የተሳካ የገቢ ማሰባሰብ አካሄደ

 

የአገዛዙ ደጋፊዎች ስብሰባውን በአሸባሪነት ከሰው ለማደናቀፍ ያልተሳካ ሙከራ አደረጉ

ሌሎችም ዜናዎች አሉን

http://www.zehabesha.com/

posted by Tseday Getachew

Advertisements

አዲሱ የኢህአዴግ አሰላለፍ – ከተመስገን ደሳለኝ (ጋዜጠኛ)

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የዘንድሮው የዘ-ሐበሻ አንባቢዎች ምርጥ ጋዜጠኛ አሸናፊ ነው።

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ
የዘንድሮው የዘ-ሐበሻ አንባቢዎች ምርጥ ጋዜጠኛ አሸናፊ ነው።

ኢህአዴግ ከቀድሞ ሊቀ-መንበሩ አቶ መለስ ዜናዊ ህልፈት በኋላ በተከሰተበት ውስጣዊ ልዩነት በተለዋዋጭ የኃይል ሚዛን ሥር ለማደር በመገደዱ የስልጣኑን መዘውር የሚያሽከረክረውን አካል ለመለየት አዳጋች ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህ ሽኩቻ መፍትሄ ማግኘቱን የሚያመላክቱ ሁናቴዎች መፈጠራቸውን የውስጥ አወቅ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡

እንደ መግቢያ
ድንገቴው የመለስ ህልፈት ህወሓትን ቢከፍለውም፣ ብአዴን ራሱን እንዲያጠናክር መደላድል ፈጥሮለታል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት መለስ ዘመኑን ሙሉ በብአዴን ታማኝነት ላይ ጥርጣሬ ስላልነበረው ቀድሞውንም እንዲዳከም ባለማድረጉ ይመስለኛል፡፡ እርሱ በአይነ ቁራኛ ይጠብቀው የነበረው ህወሓትን ነበር፤ በተለይም በሠራዊቱ እና በደህንነቱ ውስጥ ‹‹ተፅእኖ መፍጠር ይችላሉ›› የሚባሉት አቦይ ስብሃት ነጋ እና የትግራይን መዋቅር በእጁ ያደረገው የቀድሞ የክልሉ አስተዳዳሪ ፀጋዬ በርሄ በጥርጣሬ ዓይን የሚታዩ ሆነው ቆይተዋል፡፡ በምርጫ 2002ቱ ማግስትም ድርጅቱ አቦይን ‹‹በክብር›› እንዲሸኝ ሲደረግ፣ ፀጋዬ በርሄን ደግሞ ‹‹አማካሪ›› በሚል ሽፋን ከመቀሌ ወደ ቤተ-መንግስት (ጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ) አዛውሮ በቅርብ እይታ ስር በማዋሉ ሁለቱንም ከጨዋታ ውጪ አድርጓቸዋል፡፡ በግልባጩ አዜብ መስፍንና ‹የመለስ ታማኞች› የሚባሉት እነአባይ ወልዱና ቴዎድሮስ ሀጎስ የፖሊት ቢሮውን ተቀላቅለዋል፡፡ ሁነቱም ከእነአቦይ ጋር በስጋ ዝምድናና በጋብቻ የተሳሰሩ ባለስልጣናትን በማስከፋቱ በድርጅቱ ውስጥ ብቻ የሚታወቅ (አደባባይ ያልወጣ) ልዩነት ፈጥሮ እንደነበረ ይታወሳል (በነገራችን ላይ ኦህዴድ የማዳከሙ ሴራ ሰለባ ነው፡፡ ይህ ሁናቴ ከመለስ ህልፈትም በኋላ ቀጥሏል፤ ለምሳሌ ባለፈው ዓመት የግንባሩ አባል ድርጅቶች፣ የየራሳቸውን ጠቅላላ ጉባኤ ባካሄዱበት ወቅት ብአዴን በ‹ክብር› ካሰናበተው ሁለት ዓመት ያለፈውን መሪውን አዲሱ ለገሰን ወደ ቦታው መልሶ ራሱን ሲያጠናክር፣ በተቃራኒው ኦህዴድ አንጋፋ አመራሮቹን፡- አባዱላ ገመዳ፣ ኩማ ደመቅሳና ግርማ ብሩን ከስራ አስፈፃሚነታቸው እንዲያነሳ ተገድዷል፡፡ ይህንን ነው መተካካት የሚሉትም፡፡

ህወሓት

የመለስን ህልፈት ተከትሎ በውስጡ ያደፈጠው ቅራኔ ፈንቅሎ በመውጣቱ ህወሓትን የ‹መቀሌው› እና የ‹አዲስ አበባው› በሚል ለሁለት ከፍሎት ነበር፤ ይህ ግን የመቀሌው-በአዲስ አበባ፤ የአዲስ አበባው-በመቀሌ ደጋፊ አልነበረውም እንደማለት አይደለም (የመቀሌውን አዜብ መስፍን፣ አባይ ወልዱ፣ ቴዎድሮስ ሀጎስ… መርተውታል፤ የአዲስ አበባውን ደግሞ አቦይ ስብሃት ነጋ፣ አባይ ፀሃዬ፣ ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል እና ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ በርካታ አንጋፋ ታጋዮች ዘውረውታል)፡፡ ይህ አጋጣሚም ከእነ አዜብ ቡድን ጋር ትብብር የፈጠረውን ብአዴንን ለጊዜያዊ ድል አብቅቶት ነበር (በ93ቱ ክፍፍልም የብአዴን ድጋፍ መለስ በአሸናፊነት እንዲወጣ ጉልህ ድርሻ ማበርከቱ ይታወሳል)፡፡ አቦይ ስብሃት ነጋ በትግርኛ ቋንቋ በሚታተመው ‹‹ውራይና›› መፅሄት ላይ ‹‹ህዝቢ ትግራይ ዘቃልሶ ኣቃሊሱ ዝጠቕሞ ወያናይ ውድብ ይግብኦ›› (የትግራይ ህዝብ የሚያታግለው፣ ታግሎም የሚጠቅመው ወያኔያዊ ድርጅት ይገባዋል) በሚል ርዕስ በፃፉት ፅሁፍ ችግሩን እንዲህ ሲሉ ገልፀውታል፡-

‹‹አባይ ወልዱም ባለፈው የህወሓት ጉባኤ ላይ በተደጋጋሚ ‹ህወሓት ውስጥ ማጠለሻሸትና (የሥልጣን) ሽኩቻ በስፋት እየተስተዋለ ነው› በማለት ሁኔታውን ገልፆታል፡፡ ከዚህ በላይ ማረጋገጫ ደግሞ የለም፡፡ እንዲህ ያለ በኃይል አሰላለፍ ደረጃ ሊታይ የሚችል የአንድን የፖለቲካ ድርጅት አቅም ከማዳከምና መርሀ-ግብሩን ከማሰናከል አልፎ ተርፎም ድርጅቱን ለአስከፊ ውድቀት ሊጥል ከሚችል አደገኛ ሁኔታ የበለጠ አደጋ ያለ አይመስለኝም፡፡›› (‹ውራይና› ቁጥር 4 ነሐሴ 2005 ዓ.ም)

ከኃይለማርያም ጀርባ

ኃይለማርያም ደሳለኝ የግንባሩ ሊቀ-መንበር በመሆኑ ጉዳይ ላይ ብአዴንም ሆነ ሁለቱ የህወሓት ቡድኖች ቅሬታ አልነበራቸውም፤ ምክንያቱም እርሱም ሆነ ‹ደቡብን እወክላለሁ› የሚለው ድርጅቱ ለአሸናፊ ኃይል ከማገልገል አልፈው የፖለቲካ አመፅ ሊያስነሱ እንደማይችሉ ይታወቃልና፡፡ ይሁንና በወቅቱ ኃይለማርያም ሰልፉን በ‹መለስ ባርኔጣ› ከሚንቀሳቀሰው ከመቀሌው ህወሓትና ብአዴን ጋር ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝበማስተካከሉ የኃይል ሚዛኑ በአንፃራዊነት ወደእነርሱ እንዲያጋድል አድርጓል፡፡ በግልባጩ ለእነ አቦይ እና ደጋፊዎቻቸው የመሸነፍ መገለጫ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ እንግዲህ እስከ ዘጠነኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ድረስ ‹መልከ-ኢህአዴግ› በዚህ መልኩ ነበር የቀጠለው፡፡

‹መፈንቅለ-ህወሓት›
ብአዴኖች፣ ከመቀሌው ህወሓት ጋር የፈጠሩትን ግንባር፣ ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር መንበር ካገኙት ድጋፍ ጋር በማዋሀድ፡- የአዲስ አበባውን ህወሓት የአመራር አባላት ሙሉ በሙሉ፣ የደህንነት ሀላፊው ጌታቸው አሰፋን እና አንጋፋ የህወሓት ታማኝ ጄነራሎችን ከመንግስታዊውም ሆነ ከፓርቲው ኃላፊነታቸው በማንሳት በአሸናፊነት ለመወጣት ስልታዊ እንቅስቃሴ አድርገው እንደነበር ለድርጅቱ ቅርብ ከሆነ ሰው አረጋግጫለሁ፡፡ በባህርዳሩ ጉባኤ ላይም መላኩ ፈንቴ ‹አላሰራ አሉኝ› ብሎ በአደባባይ እንዲያጋልጣቸው ከተደረጉት የንግድ ደርጅቶችና ሀብታም ነጋዴዎች አብዛኞቹ ከአዲስ አበባው ህወሓት ጋር የተሳሰሩ እንደነበረ ይታወቃል፡፡ እነዚህን ኩነቶችም ነው ‹መፈንቅለ-ህወሓት› ለማለት የተገደድኩት፡፡ ሴራው የከሸፈው በሁለት ምክንያቶች ይመስለኛል፤ የመጀመሪያው በሰውየው ህልፈት ማግስት (ተተኪው ጠቅላይ ሚንስትር ገና ባልተመረጠበት) እነአባይ ፀሀዬ ሶስት ሜጀር ጄነራል እና ሰላሳ አራት ብርጋዴር ጄነራሎች (አብዛኞቹ የህወሓት ሰዎች ናቸው) መሾማቸው ኃይላቸውን ሲያጠናክርላቸው፣ በአንፃሩ የመቀሌውን ህወሓትና ብአዴንን በሠራዊቱ ውስጥ የነበራቸውን ተፅእኖ ከማዳከሙም በላይ ኃይል የማሰባሰብ ሩጫቸውንም ገትቶታል፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በደህንነት
መስሪያ ቤቱ አቀናባሪነት በ‹ፀረ ሙስና› ሽፋን የተከፈተው ዘመቻ ነው፤ እነበረከትንም ስልታቸውን መልሰው እንዲያጤኑ ያስገደዳቸው ይህ አይነቱ አስደንጋጭ እርምጃ ይመስለኛል፡፡

መላኩ ፈንታ።

የህወሓት ‹ቆሌ›
የኢትዮጵያን ልማዳዊ ፖለቲካ ከነሴራው ጠንቅቀው ከተረዱት ጥቂት ሰዎች መሀል አቦይ ስብሃት ነጋ አንዱ መሆናቸው ተደጋግሞ ተነግሯል፡፡ አቦይ ህወሓትን ጠፍጥፎ በመስራቱም ሆነ በስልጣን ለማቆየት የመለስን ያህል (ሊበልጥም ይችላል) ለፍተዋል፡፡ ዛሬም ተፈጥሮ ላመጣባቸው እርጅና እጅ ሳይሰጡ በህወሓት ላይ የሚሴረውን-ለመበጣጠስና ለተቀናቃኞቻቸው-ጉድጓድ ለመቆፈር እንደማይሳናቸው አሳይተዋል፡፡ ይህ ሁኔታም ነው ‹የህወሓት ቆሌ› የሚል ቅጥያ ያሰጣቸው፡፡

ከመለስ ዜናዊ ጋር የነበራቸው ጥብቅ የመተባበር መንፈስም ከጓዳዊነትም በላይ እንደነበር የቅርብ ሰዎቻቸው ይመሰክራሉ፡፡ ግና ይህ የጦፈ ፍቅራቸው ከ2000 ዓ.ም ወዲህ መደብዘዝ ጀምሮ ነበር፤ ልዩነታቸውም ቅስ በቀስ እየሰፋ ለመምጣቱ ብዙ ማሳያዎች አሉ፡፡ አንዱ መለስ፣ ለአዜብ መስፍን እየሰጠ የነበረውን የፖለቲካ ጉልበት፣ አቦይ ‹ህወሓትን በሴት ቀሚስ እንደማሳደር› አድርገው መውሰዳቸው ነበር፡፡ ሌላው የሴቲቱ ኃይለኝነት የአቦይን የተሰሚነት ክልል ከመፈታተን አልፎ በአደባባይ ክብራቸውን እስከ መዳፈር መድረሱ ይመስለኛል፡፡ ችግሩን ለመፍታትም ከመለስ ጋር ተገናኝተው መነጋገር አልቻሉም፤ ለህወሓት ቅርብ የሆኑ ወዳጄ እንደነገሩኝ መለስ ህይወቱ ሲያልፍ አቦይን ካገኛቸው ከሁለት ዓመት በላይ ሆኖታል፤ ምክንያቱ ደግሞ እርሱ ማግኘት ባለመፈለጉ ነበር፤ ይህም ሆኖ አቦይ ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርጉም በልዩ ረዳቱ አማካኝነት ‹አስቸኳይ ጉዳይ ላይ ነው› እያስባለ መልሷቸዋል፤ በስራ አጋጣሚ ከቢሮ ውጪ ሲገናኙም ‹አጣዳፊ ስራ ስለተደራረበብኝ ነው፤ እኔ ራሴ አስጠራሀለሁ› እያለ ለሁለት ዓመት ያህል ሲርቃቸው ከቆየ በኋላ ነበር ድንገት ህይወቱ ያለፈው፡፡

አቦይ ወደ ህወሓት ተመልሰው በንቃት መሳተፍ የጀመሩት የመለስን ጤንነት ሲከታተሉ የነበሩ ሐኪሞች ‹ተስፋ የለውም› ባሉበት ማግስት ነበር፤ እንደምክንያት ያስቀመጡት ህወሓት ከድህረ-መለስ በኋላ፣ የብአዴንን የትከሻ ግፊያ መቋቋም አይችልም የሚል ስጋትን ነው፡፡ የሰውየው መጨረሻ ከታወቀ በኋላም የተፈጠረውን ክፍፍል ተከትሎ የታየው የኃይል ሚዛን ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነበር፡፡ በወቅቱም አቦይ ‹መፍትሄ› ብለው ያቀረቡት ‹ብአዴንና ከጎኑ የተሰለፉትን የህወሓት የአመራር አባላትን ማሸነፍ ስለማንችል፣ አንጃው (የእነ ስዬ ተወልደ ቡድን) ተመልሶ ያጠናክረን› የሚል ነበር፤ በስማቸውም ‹‹ውራይና›› መፅሄት ላይ በፃፉት (ርዕሱ ከላይ በተጠቀሰው) ፅሁፍ ጉዳዩን እንዲህ በማለት ገልፀውት ነበር፡-

‹‹…ሁላችንም ህወሓት ውስጥ እያለን እኮ አንጃው ድርጅቱን ተቆጣጥሮት በትረ-መንግስቱንም ሊጨብጥ ተቃርቦ ነበር፡፡ በአንጃው የመዋጥ አደጋ ጊዜ ሁላችንም ተኝተን ነበር፡፡ እነዚያ የተሰናበቱት ሰዎች በማዕከላዊ ኮሚቴው ውስጥ ቢቆዩ ኖሮ ይተኙ ነበር ማለት ግን አይደለም፡፡ አሁን ላለው አመራር ይደግፉት ነበር ይሆን ማለቴ ነው እንጂ፡፡ …ከዚህ ቀደምም ሆነ አሁን ከህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የወጣ ሁሉ እንደአዲስ ተደራጅቶ አሁን ላለው ማ/ኮሚቴ እገዛ የሚያደርግበትን መንገድ ማፈላለግ አለበት፡፡…›› (‹ውራይና› ቁጥር 4 ነሀሴ 2005 ዓ.ም)

አቶ አባይ ጸሐዬ

ሆኖም አባይ ፀሀዬ፣ አርከበ እቁባይ፣ ፀጋዬ በርሄ፣ ጌታቸው አሰፋን የመሳሰሉት ‹በጭራሽ አይሆንም! የእነርሱ መመለስ ያውከናል› የሚል አቋም በመያዛቸው ሃሳቡ ተፈፃሚ ሳይሆን ቀርቷል፡፡

ከዚህ በኋላ የእነ አቦይና አባይ ቡድን ‹ህወሓትን ማዳኛ› ያለውን ሁለት ወሳኝ እርምጃ ወስዷል፤ ከህግ ውጪ ሶስት ሜጀር እና ሰላሳ አራት ብርጋዴር ጄነራሎችን ሲሾም፣ በደህንነት መስሪያ ቤት ውስጥ ቁልፍ ሰው የነበረውን ወ/ስላሴ ወ/ሚካኤልን ከየትኛውም አይነት ‹ኦፕሬሽን› እንዲገለል አደረገው፤ ቀጥሎ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ከሀላፊነቱ አነስቶታል፡፡ በዚህ በኩል ያገኙትን የፖለቲካ ጉልበት በመመንዘር ከህገ-መንግስቱም ሆነ ከተለምዶአዊው አሰራር በማፈንገጥ ተጨማሪ ሁለት ም/ጠቅላይ ሚንስትሮች እንዲሾሙ ጫና ፈጥረው ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል፣ ኃ/ማርያም ደሳለኝን በቅርብ ርቀት እንዲከተል አድርገዋል (በነገራችን ላይ ባለፈው ዓመት አጋማሽ ህወሓት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን በመረጠበት ወቅት ወልደስላሴ ሲጠቆም፣ ጠንካራ ተቃውሞ አቅርቦ እንዳይመርጡት ያነሳሳበት የደህንነቱ ሀላፊ ጌታቸው አሰፋ ሲሆን፣ በአንፃሩ ጌታቸው የተጠቆመ ጊዜ ወልደስላሴ እና ገብረሃዋድ ተቃውሞውን ቢያስተባብሩም ታናሽ ወንድሙ በላይ አሰፋን ጨምሮ ከመመረጥ ማደናቀፍ አልቻሉም፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ወልደስለሴና ገብረሃውድ በሙስና ተጠርጥረው በእስር ላይ ይገኛሉ)፡፡

ሌላኛው የህወሓት ‹ጠባቂ መልአክ› አባይ ፀሀዬ ነው (በ2005 ዓ.ም ወርሃ ጥቅምት በታተመችው ‹አዲስ ታይምስ› መፅሄት ላይ አባይ፣ መለስ ያደረገውን ማድረግ የሚችል /ከንግግር ችሎታ በቀር/ አደገኛ ሰው መሆኑን መግለፄ ይታወሳል) ዘግይቶም ቢሆን ቡድኑን የበላይ ባደረገው የ‹ፖለቲካ ጨዋታ› እርሱም የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስድ ታይቷል፡፡ ደብረፅዮንም ቢሆን ከህወሓት ጋር ባሳለፈው ዘመን ‹ትጉህ ደቀ-መዝሙር› ስለነበር ያካበተው ልምድ ህወሓትን በታደገው ንቅናቄ ላይ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የሆነው ሆኖ እነ አባይ ከባህርዳሩ ጉባኤ በኋላ ነው ‹ከመከላከል ወደ ማጥቃት› ተሸጋግረው ብአዴንንና የመቀሌውን ህወሓት በ‹ሙስና› ስም ሰለባ ያደረጉት፡፡ ይህንን እውነታም የሚያጠናክርልን አቦይ ስብሃት ‹‹ውራይና›› መፅሄት ስለ ጉዳዩ ጠይቋቸው የሰጡት ምላሽ ነው፡-

‹‹አሁን በእስር የሚገኙት [እነመላኩ ፈንቴን ማለታቸው ነው] ሙሰኞች ብቻ አልነበሩም፡፡ የፖለቲካዊ ኃይል አሰላለፍንም ሲለውጡ የነበሩ ናቸው፤ ያስፈራሩም ነበር፤ ‹የስልጣን ሹዋሚም ሻሪም እኛ ነን› አስከማለትም ደርሰው ነበር፡፡›› (‹ውራይና› ቁጥር 2 ሠኔ 2005 ዓ.ም)

የብአዴን የአመራር አባል የሆነ አንድ ሚንስትር ለእስር ሲዳረግ፣ ሌላ ሚንስትር ደግሞ ከኃላፊነቱ መነሳቱ ይታወቃል፡፡

አዲሱ ግንባር
ብአዴን የአዲስ አበባው ህወሓት ክንደ-ብርቱ እየሆነ በመምጣቱ፣ የእነ አዜብን ቡድን አውላላ ሜዳ ላይ ትቶ አብሮ ለመስራት ተደራድሯል፡፡ እነ አባይም ‹ከብአዴን ተሻርኮ ሊያስበላን ነበር› ያሉትን የመቀሌውን የህወሓት ኃይል ከሞላ ጎደል ሲያስገብሩት፣ የቡድኑ መሪን አዜብ መስፍንን ደግሞ ከኤፈርት ከማሰናበታቸውም በላይ የፓርላማ ወንበሯን የሰዋችለትን የአዲስ አበባ የከንቲባነት ምኞቷን አጨልመው፣ በመለስ ፋውንዴሽን ገድበዋታል (የመለስ ሙት ዓመት በተከበረበት ወቅት የትግሉን ዘመንና የመለስን ገድል በኢቲቪ ሲተርኩልን የነበሩት የታሪኩ ዋና ተዋንያን አቦይ ስብሃት ነጋ፣ አባይ ፀሀዬ፣ ሳሞራ የኑስ…ሲሆኑ፣ በህልፈቱ ሰሞን ግን መድረኩን ተቆጣጥረውት የነበሩት ብአዴኖች፣ እነኩማ ደመቅሳ እና ትግሉን በመፅሀፍትና በቴሌቪዥን የሚያውቁት እነ ሬድዋን ሁሴን መሆናቸውን ስናስታውስ የእነ አባይ ፀሀዬ ህወሓት ምን ያህል ተገፍቶ እንደነበረ እንረዳለን፡፡)

በአናቱም ብአዴን የበላይነቱን በጨበጠበት ወቅት እንደ ስጋት ቆጥሮት ‹ሊፐውዘው› አስቦ የነበረውን መከላከያም፣ ከድርድሩ በኋላ በሁለቱ ኃይሎች ስምምነት ለአምስት ቀናት ኪራይ ሰብሳቢነትን እና ሙሰናን በተመለከተ ብቻ ተገማግሞ እንዲታለፍ ተደርጓል፡፡ ከኃላፊነታቸው ለማንሳት የታሰቡት ጄነራሎች ጉዳይም ‹ያልታሰበ አደጋ ሊያመጣ ይችላል› በሚል ለጊዜው ተዘሏል፡፡ ይሁንና ኤታማዦር ሹሙን ጄነራል ሳሞራ የኑስን በዚሁ ዓመት መጨረሻ በ‹ክብር› ሸኝቶ፣ ጄነራል አበባው ታደሰን የመተካት ዕቅድ መኖሩን ምንጮች ጠቁመዋል (ከዚህ በኋላ በጡረታ የሚሰናበቱ ጄነራሎች ‹መከላከያ ቴክኖሎጂ› /መቴክ/ በሚመራውና ወደፊት በሚያቋቁማቸው ኢንዱስትሪዎች ውስጥ በስራ-አስኪያጅነት ወይም በቦርድ አባልነት እንደሚመደቡ ቃል ተገብቶላቸዋል)

ከኃ/ማርያም ጀርባ ያደፈጠ-ስውር እጅ
በሁለቱም ቡድን ካሉ ምንጮቼ ‹‹ኃ/ማርያም ስራው ከብዶታል›› የሚል ቅሬታ እንደነበራቸው ሰምቻለሁ፤ ይሁንና መፍትሄ ተደርጎ የተወሰደው በረከት ስምዖንን የጠቅላይ ሚንስትሩ ‹የፖሊሲና ጥናት ምርምር› አማካሪ በሚል ሹመት በጽ/ቤቱ ማስቀመጥን ነው፤ እርሱሁሉንም ነገር ከጀርባ ሆኖ እንዲያከናውን ወስነዋል፡፡ በረከት የተመረጠው ‹ከመለስ ጋር በቅርብ ስርቷል፣ መለስ ያነበበውን አንባቧል፣ የመለስን የዕለት ተዕለት ሥራ በቅርብ ተከታትሏልና መንገድ ይመራል› በሚል እንደሆነ ምንጮቼ ነግረውኛል (በነገራችን ላይ መለስ ሞት ባይቀድመው ኖሮ የወደፊት ዕቅዱ ቤተ-መንግስቱ ውስጥ ጀምሮት የነበረውን ግንባታ አጠናቅቆ፣ ከ2007ቱ ምርጫ በኋላ ስልጣኑን፣ ከአሻንጉሊቶቹ ለአንዱ አስረክቦ፣ መኖሪያውንም ወደ አዲሱ ህንፃ አዛውሮ፣ በለቀቀው ቤት ውስጥ የሚያስገባውን ጠቅላይ ሚንስትር ከጀርባ ሆኖ መዘወር ነበር፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ህልፈቱን ተከትሎ ግንባታውም የተቋረጠው፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ግንባታው ሊቀጥል እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡ በረከት ስምዖን እንዲገባበት ታስቦ ይሆን? …አባይ ፀሀዬም ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ የጠቅላይ ሚንስትሩ ‹አማክሪ› ሆኖ እንደሚሾም ‹ፎርቹን› ጋዜጣ በ‹ጎሲፕ› አምዱ አትቷል፡፡ መቼም ኃ/ማርያም ‹‹ሰርክ ‹እኔም አንደ ዳዊት ጨርቄን ልጣልለት› እያልኩ እዘምርለታለሁ›› ያለን አምላኩ ካልታደገው በቀር፣ ከእነዚህ ጉልበታም ሰዎች በጤና መውጣቱን እንጃ!)

ህወሓትና ብአዴን ልዩነታቸው መፈታቱን ለማሳየት፣ በረከት ስምዖን ከአዲሱ ሹመት በኋላ በሃያ ሁለት ዓመታት የስልጣን ዘመኑ አድርጎት የማያውቀውን መንግስትን ወክሎ (በግሉ ሄዶ ሊሆን ይችላል) በትግራይ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች የስራ ጉብኝት አካሄዷል፡፡ ‹ድምፀ ወያኔ› የተባለው የክልሉ ሬዲዮ ጣቢያም ጉብኝቱን ሳምንት ሙሉ ሳይታክት ደጋግሞ አስተላልፎታል፡፡

ስብሃት ነጋ

ሽራፊ-መረጃ
የአቦይ ስብሃት ነጋ ቡድን በኢህአዴግ ውስጥ ተከስቶ ከነበረው ክፍፍል በአሸናፊነት መውጣቱ ከተረጋገጠ በኋላ አዲስ ወሬ እየተሰማ ነው፡፡ ይኸውም ‹ህወሓት የጠቅላይ ሚንስትርነት ቦታውን በመልቀቁ፣ ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የሚያስረክቡትን ወንበር አቦይ ስብሃት መያዝ አለባቸው› የሚል ነው፤ ምንም እንኳ ሃሳቡ ተፈፃሚነት ባይኖረውም፣ ምንጮቼ አቦይ ራሳቸው በዘወርዋራ መንገድ ያሰራጩት ወሬ ሊሆን ይችላል ብለው ያምናሉ፡፡ አዜብ መስፍንም ቦታውን የመያዝ ፍላጎት ያላት ይመስለኛል፡፡

ብዙ ሲባልለት የቆየው የድህረ-መለስ ኢህአዴግ ከላይ ለማቅረብ በሞከርኩት መንገድ ግራና ቀኝ ሲዋልል፣ የመከፋፈል ተግዳሮትን ሲሻገርና እንደገና እየተመለሰ ሲሰባሰብ እዚህ ደርሷል፡፡ በዚህ ኮሮንኮቻማ ሂደት ውስጥ የጠቅላይ ሚንስትሩ ሚና ‹እዚህ ግባ› የምንለው እንዳይመስለን ሆኗል፡፡ ኃይለማርያም መንግስታዊ ብቻ ሳይሆን የፓርቲው ሊቀ-መንበርነትን የመሰለ ጠንካራ ፖለቲካዊ ስልጣን መያዙ ይህ ሰው የሚባለውን ያህል የዳር ተመልካች ሆኖስ ይቆያልን? ለሚለው ጥያቄ ቀጣይ ጊዜያቶች ብቻ መልስ ይኖራቸዋል፡፡ የጠቀስኳቸው የስርዓቱ ጉምቱ ሰዎች በዚህ መልኩ እየተንቀሳቀሱም ቢሆን፣ ይህን የኃይል መገዳደር እያደረጉ ያሉት በስልጣን ሞኖፖሊ ላይ ተቀምጠው
መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ እናም ባቀረብኳቸው ሂደቶች እያለፉም ይሁን አይሁን ለስልጣናቸው የሚያሰጋ ጠንካራ የታቃውሞ ስብስብ አለመኖሩን ማመናቸው ይመስለኛል፣ የኃይል ትንቅንቁን ‹ግዜው አይደለም› ብለው ለማራዘም ሳይጠነቀቁ በግላጭ እርስ በእርስ የተፋለሙት፡፡

የሆነው ሆኖ የፓርቲው የታሪክ ድርሳን እንደሚነግረን ‹ይሆናሉ› የተባሉት ተቀልብሰው፣ ባልተጠበቁ ሁነቶች (የኃይል መገለባበጥ ተከስቶ) ፖለቲካው የሚመራበት አጋጣሚ ሊፈጠር የሚችልበት ዕድል ሊኖር እንደሚችልም መዘንጋት አያስፈለግም፡፡

http://www.zehabesha.com/

posted by Tseday Getachew

ከአንድነቶች ሶስት ወር ዘመቻዎች የተማርናቸው! ግርማ ሞገስ

ግርማ ሞገስ (girmamoges1@gmail.com)
ቅዳሜ መስከረም 18 ቀን 2006 ዓ.ም. (September 28, 2013)

ቀጣዩን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

http://www.zehabesha.com/

posted by Tseday Getachew

 

“አንድ ሄክታር መሬት በ1 ፓኮ ሲጋራ ዋጋ መቸብቸብ ራዕይ ነው?” – የተስፋዬ ገ/አብ ቃለ ምልልስ

life

(ይህ ቃለመጠይቅ አዲስአበባ ላይ በየ15 ቀኑ ከሚታተመው “ላይፍ” መፅሄት ጋር የተደረገ ሲሆን፤ ቃለመጠይቁ የተካሄደው ከመፅሄቱ ጋዜጠኛ ጋር በፌስቡክ በኩል በተደረገ ግንኙነት በፅሁፍ ነው። መፅሄቱ ለአገር ውስጥ አንባብያን ቅዳሜ መስከረም 28 ገበያ ላይ የሚውል በመሆኑ ግልባጩ በዚህ መልኩ ቀርቦአል።)

• አዲሱ “የስደተኛው ማስታወሻ” መጽሐፍህ ከ“የደራሲው ማስታወሻ” እና ከ“የጋዜጠኛው ማስታወሻ” በምን ይለያል?

 “የስደተኛው ማስታወሻ” ከቀዳሚዎቹ ማስታወሻዎች የቀጠለ ነው። በዚህ ቅፅ በተመሳሳይ ገጠመኞቼን ነው ያሰፈርኩት። በርግጥ እንደ ሰንሰለት የተያያዙ የአውሮፓ የስደት ገጠመኞቼ ተተርከውበታል። ይህ ቅፅ የማስታወሻዎቼ መደምደሚያ ሲሆን፣ ከዚህ በሁዋላ ወደ ስነፅሁፍ ስራዎች ነው የምገባው።

• “የስደተኛው ማስታወሻ” አሳታሚ ማነው? መቼ ለገበያ ይቀርባል?

 “ነፃነት አሳታሚ” ይባላል። ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኝ የኢትዮጵያውያን ንብረት የሆነ አሳታሚ ድርጅት ነው። ውል አድርገን መፅሃፉን አስረክቤያለሁ። የጀርባና የፊት ሽፋኑን ዲዛይን ሰርተው ልከውልኝ አፅድቄያለሁ። መፅሃፉ በህትመት ፕሮሰስ ላይ እንደሆነ መስከረም ወር መጀመሪያ ላይ ነግረውኛል። ጥቅምት ገበያ ላይ ይውል ይሆናል። በትክክል ቀኑን አላውቅም። መረጃዎቹን በድረገፃቸው በኩል ይፋ ያደርጉታል።

• አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች ስራዎችህ የሁለት የተለያዩ ሰዎች ተጽዕኖ ውጤት ነው ይላሉ፡፡ ከአሰፋ ጫቦ ሽሙጥን፣ ከበዓሉ ግርማ ጀብደኝነትን። ምን ትላለህ?

 አሰፋ ጫቦ አሽሟጣጭ ነው ብዬ አላስብም። በአሉ ግርማም ጀብደኛ አይመስለኝም። ስለሁለቱ ብእረኞች በዚህ መንገድ ማሰብ ስህተት ነው። የአሰፋ ጫቦን ብዕር አደንቃለሁ። አሽሟጣጭ ሳይሆን እውነታዎችን በቀጥታና በግልፅ የሚናገር ደፋር ብእረኛ ነው። በአሉም የሰከነ ብዕር የነበረው ደራሲ ነው። ጀብደኛ ሊያሰኘው የሚችለው ስራው የቱ ነው? ምናልባት “ኦሮማይ”ን በማሰብ ከሆነ፣ በአሉ ግርማ በዚህ መፅሃፍ ምክንያት ሊገደል እንደሚችል ቢገምት ኖሮ ከዚያ የተሻለ ስራ ይሰራ ነበር። ወደ ጥያቄው ስመለስ የበአሉና የአሰፋ ጫቦ ተፅእኖ የለብኝም ለማለት አልችልም። ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት ግን የወርቃማው ዘመን የሩስያ ደራስያን ብእረኞች ይበልጥ ቀልቤን ይስቡታል። እንደምገምተው ማስታወሻዎቼ ይበልጥ የቱርጌኔቭ የህይወት ታሪክ ማስታወሻዎች ተፅእኖ ሳይኖርባቸው አይቀርም። ወደ ትረካው ጥበብ ስንመጣ ስብሃት ገብረእግዚአብሄርና ጎርኪይ ምንግዜም አብረውኝ አሉ። ዞረም ቀረ አንድ የብዕር ሰው በጊዜ ሂደት በተለያዩ ፀሃፊዎች የአፃፃፍ ስልት ሊገነባ ይችላል።

• በአሁን ጊዜ ለአማርኛ ስነ ጽሑፍ ምን ያህል ቅርብ ነህ? ከታተሙት መፃህፍት መካከል የምታደንቀው አለ? ‘አብሬው በሰራሁ’ ስለምትለው ወይም በልዩ ሁኔታ ስለምታስታውሳቸው ደራስያን የምትገልፀው ካለም እድሉን ልስጥህ?

 ለአማርኛ ስነፅሁፍ ቅርብ ነኝ ለማለት አልችልም። የሚታተሙ መፃህፍትን እንደልቤ ለማግኘት ስለምቸገር ስለታተሙ መፃህፍት በልበ ሙሉነት አስተያየት ለመስጠት እቸገራለሁ። በጥቅሉ ግን የአማርኛ ስነፅሁፍ አደጋ ላይ የወደቀ ሆኖ ይሰማኛል። አማርኛ በአዲሳባና በአማራ ክልል ቋንቋነት ብቻ ተወስኖ እንዲቀር ብዙ ተሰርቶበታል። ይህ ሁኔታ የአማርኛ ስነፅሁፍን ክፉኛ ጎድቶታል። አማርኛ ቋንቋ ጠላት ስለበዛበት ስነፅሁፉም ባለቤት አጥቶአል። ይህ አሳዛኝ እውነት ነው።

ስለ ደራስያን ወይም ስለ ብዕር ሰዎች የጠየቅኸኝ ጥያቄ ስሜታዊ የሚያደርግ ነው። በልጅነቴ ሳመልካቸው የኖርኩት አንዳንዶቹ የብዕር አማልክት ዛሬ በህይወት የሉም። ከጥቂቶቹ ጋር ከመተዋወቅ በላይ አብሬያቸው ለመስራት በቅቻለሁ። የቅርብ ጓደኞቼ የሆኑም አሉ። ከስብሃት ገብረእግዚአብሄር ጋር አብሬ በመስራቴ በምንም ነገር የማይለካ ልምድ አጊንቼያለሁ። የአርትኦትን ጥበብ ከአረፈአይኔ ሃጎስ ተምሬያለሁ። እሸቱ ተፈራ ቤተመፃህፍት ማለት ነበር። ማሞ ውድነህ ወዳጄ ነበሩ። “እነዚህ አለቆችህ” እያሉ ወያኔን ያሙልኝ ነበር። አበራ ለማ ወጣቶችን በማገዝ ሱስ የተለከፈ ደራሲ ነበር። የሺጥላ ኮከብ ምርጥ ደራሲ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ነካ ያደርገዋል። የእፎይታ መፅሄትን አንደኛ አመት ስናከብር መጣና እንዲህ አለኝ፣
“አንድ የማይረባ መፅሄት አንድ አመት ስለሞላው ምንድነው ይህ ሁሉ ቸበርቻቻ?”
የሺጥላ ይህን ሲናገር ነጋሶ ጊዳዳ እና አለምሰገድ ገብረአምላክ በአካባቢው ነበሩ።
“ሞቅ ስላለህ ወደ ቤትህ ሂድ” አልኩት።
መአዛ ብሩና አበበ ባልቻ የልብ ወዳጆቼ ነበሩ። ሃይስኩል እያለሁ ከመአዛ ብሩ ድምፅና ሳቅ ጋር ፍቅር ይዞኝ ነበር። አሁንም አልተወኝም። የመአዛን ሳቅ ለመስማት ስል የሸገር ሬድዮ ቁራኛ ነኝ። ተፈሪ አለሙና ማንያዘዋል እንደሻውን አልረሳቸውም። የማንያዘዋል ወንድም ይሁን እንደሻው ራሱ አሪፍ ፀሃፊ ነው። ከሳህለስላሴ ብርሃነ ማርያም እና ከአያልነህ ሙላቱ ጋር ባለመስራቴ በጣም ይቆጨኛል። ከተሰደድኩ በሁዋላ ግን ለአያልነህ ደወልኩለት። የማክሲም ጎርኪይን የትውልድ ቦታ ኒዥኒይ ኖቭጎሮድን ለመጎብኘት ፈልጌ ስለነበር አስጎብኚ እንዲያዘጋጅልኝ ለመጠየቅ ነበር የደወልኩለት። ሃይለመለኮት መዋእል ከኔ ጀግኖች አንዱ ነው።
በፍቃዱ ሞረዳን አልወደውም። ምክንያቱም ከመሬት ተነስቶ ነገር እየፈለገ ያበሳጨኛል። ተወኝ ብለው ሊተወኝ አልቻለም። 2009 ላይ ጦርነት ገጥመን ነበር። በቅርቡ ግን አሪፍ ግጥም ፅፎ ሳነብ ያናደደኝ ሁሉ ብን ብሎ ስለጠፋ አድናቆቴን በፅሁፍ ገለጥኩለት።
ምነው አብሬያቸው በሰራሁ የምላቸው በርካታ ወጣት የብእር ጀግኖች አሉ። በእውቀቱ ስዩም፣ ኑረዲን ኢሳ፣ ሲሳይ አጌና፣ ኤፍሬም ስዩም፣ አዳም ረታ፣ ይስማእከ ወርቁ፣ ማረፊያ በቀለ…እንዲህ እያልኩ ትዝታዬን ከቀጠልኩ መቶ ገፅ አይበቃኝም። ጥያቄህን መልሼልህ ይሆን?

• ለአንድ ጀማሪ ደራሲ በአንተ አስተውሎት መጠንና ጉልበት እንዲጽፍ ምን ትመክረዋለህ?

 በርግጥ በአስተውሎትና በብርታት እየፃፍኩ መሆኔን ካመንክ አመሰግናለሁ። ተሰጥኦ ያለው ጀማሪ ደራሲ ጥሩ የሚባሉ መፃህፍትን በጥንቃቄ መርጦ በዝግታ ያነብ ዘንድ እመክረዋለሁ። ብዙ ማንበብ ብቻውን ጥሩ ደራሲ አያደርግም። መምረጥና በጥልቀት ማንበብ ይገባል። በጥልቀትና በዝግታ ማንበብ ሲባል ታሪኩን ብቻ አይደለም። ቃላት አመራረጥ፣ አረፍተነገር አሰካክ፣ የአገላለፅ ዘዴዎችን በጥንቃቄ መመርመር ማለት ነው። ሌላው ጉዳይ ጀማሪ ደራስያን ያልኖሩበትን ህይወት ለመፃፍ እንዳይሞክሩ እመክራለሁ። ልጅ ያልወለደ ሰው ስለ ልጅ ፍቅር ሊያውቅና ሊፅፍ አይችልም። ቢፅፍም የተሳካለት አይሆንም። ስለ ገበሬ መፃፍ ከፈለጉ ጥቂት ቀናትን ከገበሬዎች ጎጆ ማሳለፍ መቻል አለባቸው። ይህን ጉዳይ ቼኾቭ አጥብቆ መክሮ ነበር። ስሞክረው ልክ እንደሆነ አወቅሁ። “በብርታት መፃፍ” የሚለው መቸም አከራካሪ ነው። እኔ በብርታት እየሰራሁ ያለሁት (በርግጥ ከሆነ) ሙሉ ጊዜዬን በፅሁፍ ስራ ላይ ስላዋልኩ ሊሆን ይችላል። ተሰጥኦ ያላቸው ሰዎች ሌላ ምንም ስራ ሳይሰሩ ፅሁፍ ላይ ብቻ የሚያተኩሩበት እድል ካገኙ በብርታት ብዙ ሊሰሩ ይችሉ ይሆናል። ኑሮውን ለመደጎም ሲል የማይወደው ስራ ላይ የሚባክን የብዕር ሰው የተሳካለት ስራ ለመስራት ይቸገር ይሆናል።

• ፖለቲካ ውስጥ ባይገባ ኖሮ “ስመጥር” ከሚባሉት ደራስያን መካከል አንዱ ይሆን ነበር ለሚሉት ምን ምላሽ አለህ?

 በአንድ ወቅት የኢህአዴግ አባል የሆንኩት ከፍላጎቴና ከእውቅናዬ ውጭ መሆኑን ተናግሬያለሁ። ከወያኔ ጋር በቆየሁበት ጊዜም ቢሆን ጋዜጠኛ ሆኜ ነው የሰራሁት። ከዚያ በሁዋላ ነፃ ሰው ነኝ። የማንም የፖለቲካ ፓርቲ አባል አይደለሁም። “ፖለቲካ ውስጥ ባይገባ” የሚለው አባባል የተጋነነ ነው። የኛ ዘመን ሰው እንዴት ከፖለቲካ መራቅ ይችላል? እንራቅህ ቢሉትስ መች ይሆናል? እንደ ጭስ ቀዳዳ ፈልጎ መኝታ ቤታችን ድረስ ይገባል። በአጋጣሚ ፖለቲካ ውስጥ ስለገባሁ እንደ ጋዜጠኛ እና እንደ ደራሲ የፖለቲካ ገጠመኞቼን ፅፌያለሁ። ይህን በማድረጌ ስህተቱ ምን ላይ እንደሆነ ሊገባኝ አይችልም። እርግጥ ነው፣ አምርረው የሚጠሉኝ ወገኖች አሉ። ከፖለቲካ አመለካከታቸው ተነስተው ሊሆን ይችላል። የምሰራው ስራ ዋጋ ካለው ክብር ያገኛል ብዬ አስባለሁ። እኔ ማድረግ ያለብኝ ልቤን መከተል ብቻ ነው።

• “የስደተኛው ማስታወሻ” መጽሐፍህ ሃገር ውስጥ እንዲነበብ ምን ጥረት ታደርጋለህ?

 ለአዲሱ ጠቅላይ ምኒስትር መልእክት ልኬ ነበር። ምላሽ አላገኘሁም። አንድ የኮክቴል ግብዣ ላይ በወሬ መካከል ስብሃት ነጋ፣ ለበረከት “ለምን አትተወውም? ያሳትም” ብሎት እንደነበር ሰምቻለሁ። በርግጥ ከዚህ አባባል ተነስቼ ችግሩ ያለው በረከት ስምኦን ጋር ብቻ ነው ለማለት አልችልም። በዚያም ሆነ በዚህ ግን ከመነበብ ሊያግዱት አይችሉም። ኮፒው በህገወጥ መንገድ ታትሞ መሰራጨቱ አይቀርም። የስርአት ለውጥ ሲደረግ ግን የታገዱትን መፃህፍት በድጋሚ አሳትማቸዋለሁ።

• ኢሕአፓዎች ይሔንንም መጽሐፍህ እንደማያባዙት ምን ዋስትና አለህ?

 መሞከራቸው አይቀርም። የሚያሰራጩባቸው ድረገፆችና የፊስቡክ ክፍሎች ስለሚታወቁ ህገወጡን ድርጊት ከፈፀሙ በህግ እንዲጠየቁ ጠበቆችን አዘጋጅተናል። በ’ርግጥ ኮፒ የማድረጉን ስራ የሚሰሩት የኢህአፓ ሰዎች ብቻ ናቸው ማለት አይቻልም። የምቀኝነት ህመም ያለባቸው አንዳንድ የአእምሮ በሽተኞችም ድርጊቱን ሊፈፅሙት ይችላሉ። በርግጠኛነት የምነግርህ ወያኔዎች ይህን ድርጊት እንደማይፈፅሙት ነው። የማይፈልጉትን መልእክት በማፈን እንጂ በማሰራጨት አይታወቁም። የኢህአፓ አመራር የኮሎኔል መንግስቱን መፅሃፍ ስካን አድርጎ ሲያሰራጭ መንግስቱ ሃይለማርያምን ገንዘብ ማሳጣት ነበር አላማቸው። የሚያስቅ ጅልነት ነው። መንግስቱ ገንዘብ አይፈልግም። ቀዳሚ አላማው መፅሃፉ እንዲነበብ ነው። ስለዚህ ኢህአፓ ማድረግ የነበረበት መፅሃፉን ገዝቶ ማቃጠል ነበር።

• ወደ ኢትዮጵያ የመመለስ ዕድሉ ያለ ይመስልሃል?

 የሕወሓት ስርአት ከወደቀ እመለሳለሁ።

• አዲስ አበባ ውስጥ የሚናፍቅህ የትኛው ቦታ ነው? ቁጭ ብለህ ቡና ወይም ቢራ ለመጠጣት የምትመርጠው ቦታስ?

 አዲስአበባ ብዙም አይናፍቀኝ። ይልቁን ደብረዘይት እና የስምጥ ሸለቆ ከተሞች ይናፍቁኛል።ጋራቦሩ ኮረብታ ላይ ቆሜ የረር ተራራን በሩቅ ማየት በጣም ይናፍቀኛል። ቢሾፍቱ ሃይቅ ዳርቻ ከሚገኙ መሸታ ቤቶች ተቀምጬ ማምሸት እፈልጋለሁ። የባቦጋያና የሆራ አርሰዲ ዳርቻዎች በህልሜ እንኳ ይታዩኛል። ድፍን አድአ፣ እስከ ጨፌ ዶንሳ፣ እስከ ሎሜ፣ ያደግሁበት አገር ነው። በቢሾፍቱ ገደሎች ደረት ላይ እንደ ወፍ በረናል። ጋራቦሩን ጋልበንበታል። በህይወት ዘመኔ አንድ ጊዜ ወደነዚህ የአድአ ገጠሮች መሄድ እፈልጋለሁ። ርግጥ ነው፣ የወያኔ ስርአት ሲወድቅ በሚቀጥለው አይሮፕላን ቦሌ ከሚያርፉት መንገደኞች አንዱ እኔ ነኝ። እና ሽው ወደ ቢሾፍቱ!

• በቡርቃ ዝምታ እና በቢሾፍቱ ቆሪጦች መጽሃፍትህ የተጸጸትክበት አጋጣሚ አለ? አሁንም ያለህ አቋም የመጽሐፍቱ ነጸብራቅ ነው?

 በመፃህፍቱ የምፀፀትበት ምክንያት የለም። ይህ ማለት ድክመት የለባቸውም ማለት አይደለም። በ20ዎቹ መጨረሻ እድሜ ላይ ሆኜ የፃፍኳቸው መፃህፍት እንደመሆናቸው ድክመት ሊኖርባቸው ይችላል። የህይወት ልምድ ማጣት፣ ሊንፀባረቅባቸው ይችላል። የቢሾፍቱ ቆሪጦች ከስነፅሁፍ አንፃር ሊተች የሚችል ነው። ድክመት አለበት። እንዲህ ያለ ነገር ሊያጋጥም ይችላል። በአሉ ግርማ “የቀይ ኮከብ ጥሪ” ተበላሽቶበታል። ጥሩ አልነበረም። ብርሃኑ ዘርይሁን በወጣትነቱ የፃፋቸውን፣ “ጨረቃ ስትወጣ” አይነቶቹን ተመልሰህ ብታነብ ብርሃኑ ነው የፃፋቸው ለማለት ትቸገራለህ። ስነፅሁፋዊ ክህሎት እያደገ ስለሚሄድ በገፀባህርያት ቀረፃ ላይ ድክመት ሊታይ ይችላል። የሃያስያን መኖር አስፈላጊ የሚሆነው ለዚህ ነው። የቡርቃ ዝምታ መልእክቱ ላይ ችግር የለበትም። አሁንም የማምንበት ነው። የቡርቃ ዝምታን በመፃፌ እንደማልፀፀት ደጋግሜ ተናግሬያለሁ። የኦሮሞ ህዝብ ሰብእና ላይ የተፈፀመውን ግፍ የሚያሳዩ የጥበብ ስራዎች ወደፊትም መፃፍ አለባቸው። መሸፋፈን መፍትሄ አይሆንም። አብሮ ለመኖር ባለፈው ታሪክ ላይ መተማመን ይገባል። የቡርቃ ዝምታ የጭቆናውን ክብደት ለማሳየት የሞከረ መፅሃፍ ነው። የጭቆናውን ክብደት ማወቅ ተከባብሮ ለመኖር ያግዛል እንጅ የዘር ጦርነትን አይቀሰቅስም።

• ተስፋዬ ገብረአብ ጠቡ ከኢህአዴግ ጋር ሳይሆን ከኢትዮጵያ ነው የሚሉህ ሰዎች ለዚህ እንደ ማሳያ የሚያቀርቡት መጽሐፍህ በአማራ በትግሬ እና በኦሮሞ ህዝብ ቁርሾዎች ላይ ብቻ ያተኮሩ በመሆናቸው ነው ይላሉ? ምን ትላለህ?

 ስለ ዘር መነጋገር ወቅቱ ያመጣው አጀንዳ ነው። በየትኛውም የፖለቲካ ውይይቶች ላይ ቁርሾዎች የመወያያ አጀንዳ ሆነዋል። እኔ የጀመርኩት አይደለም። ክልላዊነትን ያስቀደመ የፖለቲካ ስርአት ነው ያለው። የማንነት ጥያቄ ቀዳሚ አጀንዳ ሆኖአል። አንድ የጥበብ ሰው የዘመኑን ተጨባጭ ሁኔታ መሰረት አድርጎ መፃፍ ግዴታው ነው። “በአማራና በኦሮሞ መካከል ፀብ ለመፍጠር” የሚል አባባል እሰማለሁ። ይህ አባባል ከቡርቃ ዝምታ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው። የቡርቃ ዝምታ ታሪክ የኦሮሞ ህዝብ ስለ ራሱ ከሚያውቀው አንድ አራተኛውን እንኳ አልያዘም። ታሪኩን፣ አባባሎችን ቃላትን ያገኘሁት ከኦሮሞ ገበሬዎች እንጂ ከራሴ ፈጥሬው አይደለም። ያልተለመደ አቀራረብ ስለሆነ ሰዎች ሊሰጉ ይችላሉ። አዲሱ ወጣት ትውልድ መራራ ቢሆንም እንኳ እውነትን የመስማት ችሎታ አዳብሮአል። የሚደርሱኝ ደብዳቤዎች ይህን ጠቁመውኛል። በግልፅ በመነጋገር ችግሩ ይታወቃል። ችግሩ ከታወቀ ነው መፍትሄው የሚገኘው። በማድበስበስና በመሸፋፈን ግጭቶችን ማስቀረት አልተቻለም። ደርግም ሃይለስላሴም ሞክረውት አልተሳካም። ይልቁን ማፈን መፍትሄ እንዳልሆነ ማረጋገጫ ሰጡ። የታመቀ ስሜት ቢፈነዳ ይመረጣል።ቢነገር ይሻላል። ሲተነፍስ መፍትሄውም አብሮ ይመጣል።

• ከዚህ በፊት በአንተ ብሎግ ላይ ያሰፈርካቸው “የልዑሉ እናት”፣ “የመነን 4ተኛ ባል” እና “የንጉሱ ሴት ልጅ” መጣጥፎች ያነበቡ ሰዎች የኢትዮጵያን ታሪክ ጥላሸት ለመቀባት ሆን ብለህ ያደረግከው ነው ለሚሉት ምን ትላለህ?

 በ’ርግጥ የመሪዎች ደካማ ጎኖች ላይ የመፃፍ ፍላጎት አለኝ። ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ በጎ እና ጠንካራ ጎናቸው ብቻ ነው ተደጋግሞ የሚፃፈው። መፃህፍት መሪዎችን በማሞገስ የተሞሉ ናቸው። ደካማ ጎናቸው በግልፅ ቢፃፍ አንባቢ ብዙ ትምህርት ያገኛል ብዬ አምናለሁ። በተለይ ደ’ሞ መሪዎች እንደ ማንኛውም ሰው ተራ ሰዎች መሆናቸውን ማሳየት እፈልጋለሁ። በአካባቢያችን መሪዎችን የማምለክ ዝንባሌ አለ። ከወረዳ አስተዳዳሪ ጀምሮ ለተቀመጡ መሪዎች መስገድ ባህል ሆኖአል። መነሻዬ ይህ እንጂ ሌላ አይደለም። እንደ ደራሲ ታሪኩ እውነት እስከሆነ ድረስ በማንኛውም ርስሰ ጉዳይ ላይ እንደፈለግሁ አገላብጬ የመፃፍ መብት አለኝ። ታሪክ ቀመስ ልቦለድ ልሰራባቸውም እችላለሁ። ያም ሆኖ ተፈሪ መኮንን ለመነን 4ኛ ባሏ የመሆኑ መረጃ ስለ ፖለቲካዊ ጋብቻ ግንዛቤ ይሰጣል እንጂ ንጉሱን አያዋርድም። ደጃዝማች ተፈሪ 4 ልጆች ያላት ወይዘሮ በማግባቱ አደንቀዋለሁ። “ልጃገረድ ካልሆነች አናገባም” ለሚሉ አክራሪዎች ጥሩ አርአያነት ነው። መንግስቱ ሃይለማርያም ውባንቺ ቢሻው የተባለች ሚስቱን ያገባው አስገድዶ በጠለፋ ነው። ከዚህ ምንም ትምህርት አይገኝም። አዜብ መስፍን ለመለስ ዜናዊ ሻይ እንድታፈላ በድርጅቱ የተመደበችለት ታጋይ ነበረች። በዚያው ጠቀለላት። ይሄ ጥሩ ነው። እንዲህ ያሉ ታሪኮችን የመፃፍ ፍላጎት አለኝ። እንዳልኩት በመሪዎች ትከሻ ላይ የተቆለለውን የመኮፈስ ካባ ገፍፌ መጣል እፈልጋለሁ። “የልዑሉ እናት” የሚለውን ታሪክ የፃፍኩት የጳውሎስ ኞኞን መፅሃፍ መሰረት አድርጌ ነው። “የመነን 4ኛ ባል” ዘውዴ ረታ ከፃፉት የተወሰደ ነው። እኔ ስፅፈው የተለየ የሚሆንበት ምክንያት ምንድነው? እንዲህ የሚያስቡ ሰዎች ልባቸው ውስጥ የሸሸጉትን የዘረኛነት በሽታ ያክሙት ዘንድ እመክራቸዋለሁ። ሰዎች ስለኔ የሚያስቡትን ግምት ውስጥ እያስገባሁ ልፅፍ አልችልም። በማንኛውም ርእሰ ጉዳይ ላይ በራሴው እይታ እንዳሻኝ እፅፋለሁ። አንባቢዎቼን ለማስደሰት ወይም ለማናደድ ብዬ አይደለም የምፅፈው። ቢታተምም ባይታተምም የኔ ችግር አይደለም። ኳስ መጫወት የሚወዱ ሰዎች ኳስ ይጫወታሉ። እኔም መፃፍ ስለምወድ እፅፋለሁ። ሽማግሌው ቱርጌኔቭ እንደሚለው በጎ ከሰራን፣ ስራችንም ዋጋ ካለው፣ ያን ዋጋ ህዝብ ማስተዋል ከቻለ ለስራችን ክብር ይሰጠናል።

• በብዙ ጽሁፎችህ ለኦሮሞ መብት ጥብቅና የመቆም ዝንባሌ ታሳያለህ፡፡ ነጋሶ እንዳሉት ከኦሮሞ በላይ ኦሮሞ ነኝ ማለትን ታበዛለህ ለሚባለው ምላሽህ ምንድን ነው?

 የነጋሶን አባባል ሰምቼዋለሁ። More catholic than the Pope የሚለውን አባባል ገልብጠው ሊጠቀሙበት ነው የሞከሩት። ነጋሶ ጭንቅላታቸውን ተናግረው አያውቁም። ሌሎችን ለማስደሰት በማሰብ የመናገር ልማድ አዳብረዋል። ነጋሶ አሁን የአንድነት ሊቀመንበር ናቸው። አራተኛ ድርጅታቸው መሆኑ ነው። ከኦነግ ወደ ወያኔ፣ ከወያኔ ወደ አንድነት ሲዘሉ ምንም አልተደናቀፉም። መርህ ያለው ሰው እንዲህ በቀላሉ ከአንድ ጫፍ ወደ ሌላ ጫፍ መዝለል አይቻለውም። ጨለንቆ ላይ ጉድጓድ አስቆፍረው አፅም እየሰበሰቡ “ነፍጠኛውን” ያወግዙ እንዳልነበር፣ አኖሌ ላይ ስለ “ጡት መቆረጥ” ታሪክ ሲያስተምሩ እንዳልነበር አሁን 180 ዲግሪ ተገልብጠው የራስ ጎበና ዳጪ ተከታይ ሆነዋል። እድሜ ከሰጣቸው የነገውን አናውቅም። በተቀረ ለኦሮሞ ህዝብ ጥብቅና መቆም ሃጢአት አይደለም። ሃጢአት ሊሆን የሚችለው ከተገፋና ካመፀ ህዝብ ጎን አለመቆም ነው። ለኦሮሞ ህዝብ መቆም ሲባል ሌላውን ህዝብ ማጥቃት ማለት አይደለም። ጥያቄው የክብርና የእውቅና ማግኘት ጥያቄ ነው። የኦሮሞን የሞጋሳ ባህል የሚያውቅ በነጋሶ አባባል በጣም ይገረማል። ያም ሆኖ እኔ በኦሮሞ ህዝብ መካከል ተወልጄ ያደግሁ፤ ራሴን ኦሮሞ ብዬ ለመጥራት የሞራል ብቃት ያለኝ ሰው ነኝ። ልጅ እያለን የኢብሳ ኦሮሞ የጠበል ጠላ ስንቀምስ፣ Ijollee warra Bishoftu ነበር ፉከራችን! በእነዚያ የልጅነት ዘመናት ጋራቦሩ ላይ እርጎ ጠጥተን ስናበቃ ከአህያ እስከ ፈረስ እየጋለብን ነው ያደግነው። ይህ ፖለቲካ አይደለም። ህይወት ነው። ማንነት የተገነባበት ንጥረነገር ነው።

• በጹህፎቸህ ውስጥ የበቀል ስሜት የለህም ወይ? ጹህፎችህ የኢትዮጵያን ህዝብ አንድ የሚያደርግ ገንቢ ሃሳብ ምንም ቦታ ላይ የለም ትባላለህ። ለምን?

 በግልባጩ የኔ ፅሁፎች ለአንድነት የቆሙ ናቸው። ችግሮችን በግልፅ አውጥቶ መፃፍ ለመፍትሄ ፈላጊዎች ግማሹን ስራ እንደሰራሁላቸው ነው የሚቆጠረው። በቀል የሚለው ቃል እኔን አይገልፀኝም። በግል የበደለኝ ሰው ወይም ህዝብ የለም። ለበቀል የሚያበቃ የማስታውሰው ጉዳት አልደረሰብኝም። በቀል ቀርቶ በጥላቻ የማስታውሰው ሰው እንኳ የለም። በቀል የሚኖረው ቂምና ጥላቻ ሲኖር ነው። በኔ ልብ ውስጥ ለቂምና ለጥላቻ ቦታ የለም…

• ከኢትዮጵያና ኤርትራ ስሜትህ ለየትኛው ቅርብ ነው?

 ኢትዮጵያ የትውልድ አገሬ ናት። በደም ኤርትራዊ ነኝ። ማንነት የብዙ ግብአቶች ውጤት እንደመሆኑ ለሁለቱም አገራት ስሜት አለኝ። ቋንቋ፣ ባህል፣ አስተዳደግ፣ ወላጆች እነዚህ ሁሉ ማንነትን የሚገነቡ ግብአቶች ናቸው። ጥያቄው ስለ ዜግነት ከሆነ ሆላንድ የዜግነት አገሬ ሆናለች። በቀሪው የህይወት ዘመን በዚሁ የዜግነት ሰነድ መንቀሳቀስ እችላለሁ።

• ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደፊት የመዋሃድ ዕድል ይኖራቸው ይሆን?

 ተመልሰው የሚዋሃዱ ቢሆኑ ኖሮ 30 አመት ትግል አይደረግም ነበር። በሰላሳ አመታቱ ጦርነት ከሁለቱም ወገን በአስር ሺዎች ተሰውተዋል። እንደገና በድንበር ጦርነት በተመሳሳይ የብዙ ሺዎች ህይወት ተቀጥፎአል። ከዚህ ሁሉ በሁዋላ ስለ አንድነትና ውህደት መነጋገር የሚቻል አይመስለኝም። ከመነሻውም የኤርትራ ጥያቄ የነፃነት ጥያቄ ነበር። ስለዚህ ሁለቱ አገራት ተከባብረው እንደ ጎረቤት በሰላም መኖር ከቻሉ እንኳ ትልቅ ድል ነው። እንደ አውሮፓውያን ድንበራቸውን አፍርሰው፣ የንግድ ህግ ደንግገው በሰላም መኖር ከቻሉ ትልቅ ስኬት ይሆናል። ሁለቱ አገራት የየራሳቸው ፀጋ አላቸው። ከመዋሃድ ባላነሰ ተግባራዊ ሊሆን በሚችል መልኩ በትብብር መስራት ይችላሉ። ኤርትራና ኢትዮጵያን በተመለከተ የኔ ምኞትና ፍላጎት በአዲሱ መፅሃፌ ላይ በግልፅ ተቀምጦአል። በአፍሪቃ ቀንድ ደረጃ በጋራ ለመስራት ከወዲሁ ጥርጊያ መንገዱን ቢያነጥፉ የአካባቢው 140 ሚሊዮን ህዝብ ተጠቃሚ ይሆናል። የአፍሪቃ ቀንድ ህዝቦች ከጦርነት የሚገኘውን ኪሳራ ከማንም በላይ ይገነዘቡታል። ስለዚህ ሰላማዊ አካባቢ ለመፍጠር በቁርጠኛነት መተባበር ብቻ ነው የሚያዋጣቸው።

• “ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ” የተባለው መጽሐፍህ ግነት እንደነበረበት ተናግረህ ነበር። በአሁኖቹ መጽሃፍት በሆነ ወቅት ‘ግነት ነበራቸው’ ላለማለትህ ምን ዋስትና አለ? ለሚሉ አስተያቶች ምላሽህ ምንድነው?

 “ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ” በነፃነት የተሰራ ስራ አልነበረም። መፅሃፉ የኔው ፕሮጀክት ቢሆንም በመካከሉ ድርጅታዊ ጣልቃ ገብነት መጣ። ሁዋላ ከፕሮጀክቱ ራሴን ያገለልኩት በትእዛዝ መፃፍ ስላልፈለግሁ ነው። በግሌ በሰራሁዋቸው ስራዎች ላይ ስለ ግነትም ሆነ ስለ መፀፀት ተናግሬ አላውቅም።

• እስከ ዛሬ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ከመፃፍህ አንጻር ስለ ኤርትራ ምንም አለመጻፍህ ለብዙዎች እንቆቅልሽ ነው። ለምን?

 ገና ፅፌ መቼ አበቃሁ? የመሞቻዬ ጊዜም ገና አልደረሰም። የ45 አመት ሰው ነኝ። የመፃፊያ ጊዜዬ ገና መጀመሩ ነው። እነዚህ ማስታወሻዎች ወደ ስነፅሁፍ ስራ ለመግባት እንደመንደርደሪያ የተጠቀምኩባቸው ብቻ ናቸው። ከእንግዲህ ቢያንስ በየአመቱ አንድ መፅሃፍ ለማሳተም እቅድ አለኝ። በፕሮግራሜ መሰረት መቼ፣ ስለማን፣ ምን መፃፍ እንዳለብኝ መወሰን ያለብኝ እኔ ነኝ። ከዚህ ቀደም፣ “ስለ እዚህ ጉዳይ ለምን አልፃፍክም?” ተብሎ የተጠየቀ ደራሲ ያለ አይመስለኝም። ስለፃፍኩት እንጂ ስላልፃፍኩት ጉዳይ ልንነጋገር አይገባም። የሚገርመው “ለምን አልፃፍክም?” ተብዬ የምወቀሰው ስለማላውቀው ጉዳይ ነው። የምሰራው መፅሃፍ እንጂ ዜና አይደለም። በርግጥ ይህን ክስ የሚያራግቡት ወያኔዎች መሆናቸውን አውቃለሁ። ያቀረብኩትን መረጃ ማስተባበል ስላልቻሉ በዚህ ፕሮፓጋንዳ ከአንባቢ ሊነጥሉኝ ይሞክራሉ። ያም ሆኖ ባለፉት አመታት ወደ ኤርትራ የተጓዝኩ እንደመሆኑ የኤርትራ ጉዞዬን በአዲሱ መፅሃፌ ተርኬዋለሁ። ጀምሬያለሁ። እቀጥላለሁ…

• መለስ ራዕይ ነበራቸው በሚባለው ጉዳይ ብዙዎች ጥርጣሬ አላቸው። አንተስ? በቅርቡ በታተመ መጣጥፍህ፣ “መለስ ተመልሰው ቢመጡ አባይ ፀሐዬን እስር ቤት ያስገባው ነበር” ያልክበት ምክንያት ምንድነው?

 የመለስ ራእይ የሚባለውን የፕሮፓጋንዳ መፈክር መለስ ሲሞት በተደናበረ ሁኔታ የፈጠሩት ነው። መለስ ሲሞት እንደ ኢህአዴግ ማእከል ሆኖ ሊያሰባስባቸው የሚችል አይዲዮሎጂ አልነበራቸውም። አብዮታዊ ዴሞክራሲ ምን እንደሆነ ማንም ሳያውቀው አርጅቶ ሞቶ ነበርና አደጋ ላይ ወደቁ። “ምንድነው የመለስ ራእይ?” ብለህ ብትጠይቅ አንዳንዱ የዋህ ካድሬ፣ “የአባይ ግድብ”፣ “የባቡር ፕሮጀክት” ምናምን ይልሃል። የአባይ ግድብ ጥናት በጃንሆይ ዘመን የተጠና ነው። አቅም እና ምቹ ጊዜ እየተጠበቀ ነበር። ግብፅ ስትዳከም ምቹ ጊዜ ሆኖ ተገኘ። የባቡሩ ፕሮጅክት የሃይሉ ሻውል እቅድ ነው። ቅንጅት በ2005 ምርጫ ስልጣኑን ቢይዝ ሊፈፅመው ያቀደው ነው። ወያኔ ከአፍ እየቀለበ የመንጠቅ ልዩ ችሎታ አለው። “የመለስ ራእይ” የሚባል ነገር የለም። አሁን እንኳ ሽኩቻ ውስጥ ስለገቡ የራእዩ ከበሮ ረገብ ብሎአል። በመለስ ራእይ ስም መለስ የዘረጋውን መዋቅር በመበጣጠስ ላይ የሚገኘው አባይ ፀሃዬ ነው። አንዱ ጠንክሮ እስኪወጣ ድረስ ሽኩቻቸው ይቀጥላል።

• በመለስ ራእይ ስም መለስ የዘረጋውን መዋቅር በመጣጠስ ላይ የሚገኘው ዓባይ ፀሃዬ ነው ያልክበት ምክንያት ምንድነው?

 የሽኩቻው ድራማ ዋና አክተር አባይ ፀሃዬ ነው። በአፋቸው “የመለስ ራእይ” ይላሉ። በተጨባጭ ግን የመለስ ታማኞችን እየመነጠሩ ነው። መለስ ይዞት የነበረውን ብቸኛ አምባገነናዊ ሃይል ለመቆጣጠር እየሰራ ነው። ርግጥ ነው፣ አባይ ፀሃዬ በሚፈፅመው ድርጊት ተቃውሞ የለኝም። ለአገር ደህንነት ሲል አለመሆኑ ግን መታወቅ አለበት። አጤ ምኒልክ ሲሞቱ በደጃዝማች ተፈሪ እና በልጅ ኢያሱ መካከል የተፈጠረውን የስልጣን ሽኩቻ የሚያስታውስ ሁኔታ ላይ ነን። አባይ ወልዱ እንደ ወራሽ ልጅ እያሱ – አባይ ፀሃዬ እንደ ደጃዝማች ተፈሪ! በትክክል ተመሳሳይ የታሪክ ጊዜ ላይ ነን።

• እንደምታውቀው ኢሕአዴጎች “እዚህ ያለነው የመለስን ራዕይ ከግብ ለማድረስ ነው” ብለው ውሳኔ ላይ ደርሰው መንቀሳቀስ ከጀመሩ ዓመት አልፏቸዋል:: አንተ ደግሞ “የመለስ ራእይ” የሚባል ነገር የለም ብለሃልና ብታብራራው?

 መለስ ለመሞት አንድ ሳምንት ሲቀረው ነው ባለራእይ የሆነው? ምንድነው የሚያወሩት እነኚ ሰዎች? 20 አመታት ከመለስ አመራር የተገኘው ምንነበር? በዘር ከፋፍለው ህዝቡ እንዳይተማመን አደረጉት። ያልነበረበትን የሃይማኖት ግጭት ስር እንዲተክል ጥረት አደረጉ። በሰላም አስከባሪ ስም የዜጎችን ህይወት ቸበቸቡ። የምርጫ ኮሮጆ በመገልበጥ ህዝቡ በዴሞክራሲ ላይ ያለውን እምነት አሳጡት። ምንድነው የመለስ ራእይ የሚባለው ቀልድ? ጄኔራሎችን ከህወሃት ብቻ መሾም ራእይ ነው? ቡና ሲወቀጥ ግድግዳቸው የሚሰነጠቅ የኮንደሚንየም ቤቶችን መገንባት ራእይ ነው? ገበሬዎችን አፈናቅለህ ስታበቃ አንድ ሄክታር መሬት በአንድ ፓኮ ስጋራ ዋጋ መቸብቸብ ራእይ ነው? አንድ ፍሬ እህቶቻችንን ለአረብ ግርድና አሳልፎ መስጠት ነው ራእይ? በቀለ ገርባ፣ እስክንድር ነጋ፣ ርእዮት አለሙ፣ ኦልባና ሌሊሳ ለምን ታሰሩ? በመከላከያ ስም ሸቀጥ ያለቀረጥ በማስገባት የአገር ውስጥ ነጋዴዎችን መግደል ራእይ ነው? ምንድነው የመለስ ራእይ? ውሸትን በመደጋገም እውነት የማስመሰልን ጥበብ ተክነውበታል።

• በዚህ ወቅት ሕወኃት ለሁለት ተከፍሏል በሚባለው ትስማማለህ? ከሆነስ እነማን በአሸናፊነት የሚወጡ ይመስልሃል?

 በሁለቱ አባዮች (አባይ ፀሃዬ እና አባይ ወልዱ) መካከል ጦርነት መኖሩን እየሰማን ነው። መረጃው ግን የተረጋገጠ ነው ለማለት አልደፍርም። የምንሰማው እውነት ከሆነ ከመቀሌው አባይ በስተጀርባ ቴዎድሮስ ሃጎስ አለ። ከአዲሳባው አባይ ስር እነ ጌታቸው አሰፋ፣ እነ ደብረፅዮን መሰለፋቸው ይሰማል። ሳሞራ የአዲሳባውን አባይ ተቀላቅሎአል። አዜብ ‘አርፈሽ ቁጭ በይ! የመለስን ፋውንዴሽን ተከታተይ’ ተብላለች። እብድ ስለሆነች ያልተጠበቀ ነገር እንዳትፈፅም በመስጋት ሰንሰለቷን ሁሉ በጣጥሰውባታል። የዘረፋ ቀዳዳዎቿን እየዘጉባት ነው። ያም ሆኖ አዜብ አርፋ ትቀመጣለች ተብሎ አይታመንም። መሞከሯ አይቀርም። የግል አስተያየቴን ለመስጠት ያህል፣ የመቀሌ – አዲሳባ ሽኩቻ ይፋ ሳይወጣ ውስጥ ውስጡን ሊጠናቀቅ ይችላል። ሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች ሽጉጥ ከተኮሱ ቤተመንግስቷን ለዘልአለሙ እንደሚያጧት ያውቃሉና ሽጉጥ ወደ መምዘዝ የሚገቡ አይመስለኝም። ከሁለቱ ቡድኖች አንደኛው እስኪያሸንፍ ሃይለማርያም ወንበሩን በታማኝነት ይጠብቅላቸዋል። ማን በአሸናፊነት ሊወጣ እንደሚችል አብረን እናየዋለን። የአዲሳባው ቡድን የሚበረታ ይመስለኛል። ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ከሁለቱም ቡድኖች ገለልተኛ ሆኖ የአስታራቂነት ሚና ለመጫወት እሞከረ ነው። ምናልባት እሱን በማንገስ ልዩነታቸውን ይፈቱ ይሆናል።

• ሕወኃት በምርጫ ስልጣን የሚለቅ ይመስልሃል?

 በግልፅ ተናግረዋል። “ጀርባችንን በእሳት ሰንሰለት እያስገረፍን ያገኘነውን ወንበር በምርጫ ካርድ ስም ሳምሶናይት ይዘው ለመጡ ሰዎች አናስረክብም” ብለዋል። በርግጥ የምኒልክን ወንበር በምርጫ አላገኙትም። ስለዚህ በምርጫ መልቀቅ አይፈልጉም። በምርጫ እንደማይለቁትም በ2005 ምርጫ አስመስክረዋል። በተመሳሳይ በ2010 ማንኛውንም አይነት የማጭበርበር ዘዴ በሙሉ ሃይላቸው ስለተጠቀሙበት 99.6 በመቶ በማሸነፍ ወንበሮቹን ሁሉ ያዙ። በምርጫ በኩል ይገኛል የተባለውን የዴሞክራሲ ጭላንጭልም ደፈኑት። ከዚህ በሁዋላ ምንድነው የሚጠበቀው?

• የሕወኃት በኃይል ስልጣን ላይ የመቆየት አባዜ የሚያዛልቅ ይመስልሃል?

 አዛልቆአቸው 22 አመት ሆኖአቸዋል። ሌላ 22 አመታት እንደማይገዙ ምንም ዋስትና የለም። ወያኔና ሻእቢያ በጠመንጃ ባይመጡበት ደርግ እስከዛሬ ስልጣን ላይ ሊቆይ ይችል ነበር። ሙጋቤ አሁንም አለ። ጋዳፊ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ነበረ። ስዩም መስፍን ቻይና የሚማሩትን የህወሃት የአመራር አባላት ልጆች እያሰለጠነ ነው። በቻይና መንግስት ድጋፍ ተተኪ የአገሪቱ መሪዎች ሊያደርጓቸው ይፈልጋሉ። ይህ ተረት አይደለም። እስከቻሉት ድረስ ይሞክራሉ። ከአንዳንዶቹ ጋር እንዲህ በስልክ ስናወራ “ከዚህ በሁዋላ 40 አመታት መቆየት እንችላለን” ብለው በቀልድ መልክ ጣል ያደርጋሉ። እየቀለዱ ግን አይደለም። “የ65ሺህ ጓዶቻችንን ህይወት የከፈልነው ዋጋው ውድ ነው” ይላሉ። በጨዋታ መሃል ከምኒልክ እስከ ሃይለስላሴ የነበረውን ዘመን ያሰሉታል። የንጉስ ሳህለስላሴ የልጅ ልጆች የቤተሰብ ጥል እየተጣሉም ቢሆን ስልጣን ከቤተሰባቸው ሳይወጣ እየተተካኩ ቆይተዋል። ህወሃት በተመሳሳይ መንገድ ልዩነት የፈጠሩትን እያስወገደ ሁለት ወይም ሶስት ትውልድ ከዚያም በላይ ለመግዛት ይችላል አይነት ወጎች አሏቸው። በአደባባይ ደግሞ፣ “እኛ በስልጣን መቀጠል ካልቻልን ኢትዮጵያ ትበታተናለች” ብለው መዛታቸውን ቀጥለዋል። ኢትዮጵያ እንዳትበታተን በመስጋት ህዝቡ ፀጥ ለጥ ብሎ እንዲገዛላቸው ይመኛሉ።

• ሕወኃትን ለ22 ዓመታት በስልጣን እንዲቆይ ያስቻለው ምንድነው ትላለህ?

 ምስጢሩ ህዝቡን ከፋፍሎ መግዛት በመቻሉ ነው። የፌደራል አገዛዝ ስርአቱን ለስልጣን ማራዘሚያ ተጠቅሞበታል። ክርስትያኑን በሙስሊሙ ያስፈራራዋል። የአማራው ሃይል ሲበረታ በኦሮሞው እየመታ ዘልቆአል። ሌላ ምስጢር የለውም። ከፋፍሎ በመግዛት፣ የኢትዮጵያዊነት ብሄራዊ ስሜትን በማዳከም፣ ከተቻለ ጨርሶ በማጥፋት ዝንተ አለም መግዛት እንደሚችሉ አስልተው ጨርሰዋል። በርግጥ 95 በመቶ የመከላከያን አመራር ተቆጣጥረውታል። ደህንነቱ ሙሉ በሙሉ በእጃቸው ነው። ህዝቡ በዘር ተከፋፍሎአል። ለሃያላኑ አገራት ራሳቸውን በአገልጋይነት ስላቀረቡ በጫና ፈንታ እርዳታ እያገኙ ነው። የዚህ ሁሉ ድምር በስልጣን እንዲቆዩ አግዞአቸዋል።

• አሁን ያሉት ብዙዎቹ የሕወኃት ባለስልጣናት በአባት ወይም በእናት ኤርትራውያን ናቸው ይባላል:: የተባለው ትክክል ከሆነ ውሳኔዎቻቸው የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጎዳ ሊሆን አይችልም? ከዚሁ ጋር ተያይዞ የእነኚሁ ባለስልጣናት አያቶች ወይም ቅድመ አያቶች የጣሊያን ባለሟሎች የነበሩ ናቸው ስለሚባለው ምን መረጃ አለህ? የባንዳ ልጆች መሆናቸው የስነ ልቦና ቀውስ ውስጥ አይከታቸውም ?

 በአባት ወይም በእናት ኤርትራዊ መሆን የዘመናችን ዋና አጀንዳ መሆኑ ያሳዝነኛል። በረከት ስምኦን በእናቱም ሆነ በአባቱ ኤርትራዊ ነው። ለኤርትራ የፈፀመላት በጎ ነገር አለመኖሩን ግን አረጋግጥልሃለሁ። በረከት በኤርትራውያን ዘንድ እንደ ፖለቲከኛ እንኳ አይታይም። በኢትዮጵያውያንም አይታመንም። እድለኛ አይደለም። ይህ ሊሆን የቻለው በረከት የሚሰራው ለግሉ፣ ለዝናው፣ ለስልጣን ስለሆነ ነው። ግማሽ የኤርትራ ደም ያላቸው የህወሃት አመራር አባላት ለኤርትራ ያደላሉ ብዬ አስቤ አላውቅም። የተወለዱት እና ያደጉት ትግራይ ነው። ለትግራይ ነው የሚሰሩት። አንድን ሰው “ግማሽ ኤርትራዊ ነው” ብለን ከማሰባችን በፊት “ግማሽ ኢትዮጵያዊ ነው” የሚለውን ማስቀደም ለምን አልተቻለም? በአሉ ግርማ እኮ በአባቱ ህንዳዊ ነው። ገብሩ አስራት ግማሽ ጎጃሜ ነው። ጆሴፍ ስታሊን ሩስያዊ አልነበረም። ኦባማ በአባቱ ኬንያዊ ነው። ጥላሁን ግዛው የፊውዳል ቤተሰብ ነበር።ለኢትዮጵያዊነት ህይወታቸውን የከፈሉ ኤርትራውያንን ስም እንጥራ ብንል ሰአታት አይበቃንም። መለስ በአባቱ ኢትዮጵያዊ ነው። ለምንድነው ወደ እናቱ ጎሳ ያዘነብላል ተብሎ የሚታሰበው? ተወልዶ ያደገው ትግራይ ነው። መለስ ኢትዮጵያን ለመምራት ግማሽ ኢትዮጵያዊነቱ ከበቂ በላይ ነበር። እንደሚመስለኝ ችግሩ ግማሽ ኤርትራውያን መሆናቸው ሳይሆን መርህ አልባ፣ ወይም ስልጣናቸውን ብቻ የሚያስቀድሙ በመሆናቸው ሊሆን ይችላል። መለስ ዜናዊ የባንዳ ልጅ ስለመሆኑ ሲነገር የሰማሁት ከገብረመድህን አርአያ ነው። ገብረመድህን ስለሚያጋንን አይመቸኝም። የሆነው ሆኖ መለስ የባንዳ ልጅ ሊሆን ይችላል። የባንዳ ልጅ መሆኑ ግን እሱንም ባንዳ አያደርገውም። የመለስን ወላጆች እና ልጆች እንተዋቸው። መለስን ለመውቀስ የሚያበቃ በአገር ላይ የፈፀመው በርካታ ወንጀል አለ።

• መለስ ዜናዊ “የኤርትራ ህዝብ ከየት ወዴት“ የሚለውን መጽሐፍ መጻፋቸው፣ ኤርትራ ራስዋን ችላ ነፃ ሐገር ሆና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እውቅና እንድታገኝ ለዋና ጸሐፊው ቡትሮስ ጋሊ ደብዳቤ መጻፋቸው፣ ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብ ይገባኛል እንዳትል እንቅፋት መፍጠራቸውና ለኤርትራ ይገባል ማለታቸው ግማሽ ኤርትራዊ ባይሆኑ ኖሮ የሚሞክሩት ተግባር ነበር?

 ኤርትራን በተመለከተ በተወሰኑ ውሳኔዎች የኤርትራ ደም የሌለባቸውም ተሳትፈው አብረው ወስነዋል። የፖለቲካ አቋማቸውን ነው ያስፈፀሙት። ትግራይ ከኢትዮጵያ ጋር ስለመቀጠሏ እንኳ ሁለት ልብ ስለነበሩ የኤርትራን ነፃነት የማይቀበሉበት ሁኔታ ላይ አልነበሩም። ከዚያም ባሻገር አቋማቸውን ለመለወጥ ቢያስቡ ኖሮ እንኳ በወቅቱ ምንም ማድረግ አይችሉም ነበር። ተዋጊ የገበሬ ሰራዊትና ፖለቲካ የሚያንበለብሉ ሸምዳጅ ካድሬዎች እንጂ ሌላ አቅም አልነበራቸውም። አዲሳባን እንዴት እንደሚያስተዳድሩ አሳቡ እንኳ አልነበራቸውም። በርግጥ መለስ ዜናዊ ኤርትራን በተመለከተ ስሜቱ ስስ መሆኑ ብዙ የተባለበት ነው። ስለ መለስ የልብ ሚዛን የሚያውቀው ራሱ መለስ ብቻ ነበር። ሳይፅፈው ተሰናብቶአል።

• መለስና ጓደኞቻቸው ሽንጣቸውን ገትረው ለኤርትራ ነፃነት ሲዋጉ የነበሩት ለምን ይመስልሃል?

 እኔ እስከማውቀው ለኤርትራ ነፃነት የተዋጉት ኤርትራውያን ናቸው። መለስና ጓደኞቹ የራሳቸው አጀንዳና አላማ ነበራቸው። በቀይ ኮከብ ዘመቻ ወቅት ለስልጠና ኤርትራ ሄደው መስዋእትነት እንደገጠማቸው ሰምቻለሁ። የሻእቢያ ተዋጊዎችም በተመሳሳይ ህወሃትን በማገዝ ሂደት ውጊያ ላይ መስዋእትነትን ከፍለዋል። ይህ የጋራ ጠላትን ለመመከት ከተደረገ ታክቲካዊ ትብብር ያለፈ ስም ሊሰጠው አይችልም። የህወሃት እገዛ አንዳንድ ፀሃፊዎች አጋንነው እንደሚያቀርቡት አይመስለኝም።

• በኢትዮጵያ ባለጠመንጃ አስተዳዳሪ መሆኑ የሚቀርበት ጊዜ የሚመጣ ይመስልሃል?

 ተስፋ አደርጋለሁ።

• የሕወኃትን በኃይል ከስልጣኑ እናባርረዋለን የሚሉት ተቃዋሚዎች ሚሳካላቸው ይመስልሃል?

 ህዝቡ የወያኔን ስርአት ተንኮል ጠንቅቆ ተረድቶ አማፅያኑን በሙሉ አይኑ ማየትና ማመን ከጀመረ የሚሳካላቸው ይመስለኛል። በርግጥ እኔ በግሌ ጠመንጃ እንዲተኮስ አልፈልግም። ወጣቶች በጦርነት እንዲሞቱ አልመኝም። እኔ ራሴ የጦርነት ትራፊ በመሆኔ ህመሙ ይሰማኛል። ጠመንጃ ከማንሳት ባሻገር አማራጭ መጥፋቱ ግን ያሳዝነኛል።

የሚሊዮኖች ድምጽ ለነፃነት ሰላማዊ ሰልፍ በአዲስ አበባ በሰላም ተጠናቀቀ (የሰልፉ የሰዓት ለሰዓት ዘገባ)

1:05  PM   (ኢትዮጵያ ሰዓት)

» ፖሊሶች ከአቅማቸው በላይ ነዉ። ሕገ መንግስትና በሕግ ሳይሆን በመመሪያ ነዉ የሚተዳደሩት። ሕዝቡ ሰላማዊ ሆኖም ከመርካቶ፣ ከሳሪስ፣ ከሜክሲሶ ሕዝቡ እንዳያልፍ ማድረጋቸው የፍርሃታቸው ጥግ የት እንደደረሰ የሚያሳይ ነዉ። የሰዉን ሁኔታ የተረዱ ይመስለኛል» አቶ ግርማ ሰይፉ

«ለአይንህ መጨረሻዉን የማታየው ሕዝብን ማየት ያሰደስታል። ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ በራሱ  ግብ አይደለም። ላለፉት 3 ወራት በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት በሚል ስናደርግ የነበረው የመጀመሪያ ፌዝ አጠናቀናል። የመጀመሪያዉን ፌዝ አጠናቀቅን ስንል ፣ የትግሉ ሂደት ተጠናቀቀ ማለት አይደለም። ከመጣነዉ ይልቅ የሚቀረን እንደሚረዝም ነዉ የምናስበዉ» አቶ ሃብታሙ አያሌው። አቶ ሃብታሙ በቅርቡ በጸረ-ሽብር ሕጉ ዙሪያ በኢቲቪ በተደረገው ክርክር አንድነት ወክለዉ ቀርቦ የነበረ ወጣት የአንድነት አመራር አባል ነዉ።

AFP, Bloomberg News, AL JAzria ….የመሳሰሉ በርካታ የዉጭ ጋዜጠኞች ተገኝተዉ ነበር። ፖሊሶች መንገዱን መዝጋታቸውን ታዝበዋል።  «ሰልፉ አልተፈቀደም እንዴ ? ከተፈቀደ ለምንድን ነው መንገድ የሚዘጉትም ?  ህዝቡ እንዳይቀላቀል ለምን ያደርጋሉ ? » የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተዋል።

12:50  PM   (ኢትዮጵያ ሰዓት)

የሰላማዊ ሰልፉ መርሃ ግብር ተጠናቋል። ምንም እንኳን አገዛዙ አይን ባወጣ መልኩ የሕዝብን መብት ቢረግጥ የአዲስ አበባ ሕዝብ ምን ያህል የሰለጠነ እንደሆነም አሳይቷል። አንድ ሰው ሳይጎዳ፣ አንዲት ጠጠር ሳይወረወር ሰልፍ በሚያስደንቅ ሁኔታ ተጠናቋል።

ከመርካቶ፣ ከሳሪስ ልደታ የሚመጡ መንገድ ተዘግቶ መምጣት አልቻሉም። በመቶ ሺህ የሚቆጠረዉ በቀበና አደባባይ የተሰበሰበው ሕዝብ በአጭሩ ከአንድ አካባቢ የተሰበሰበዉ ህዝብ ነዉ። ፖሊሶች መንገድ ባይዘጉና፣  ከሁሉም የአዲስ አበባ ክፍሎች ሕዝቡ እንዲያልፍ ቢደረግ ኖሮ ሚሊዮኖች ሊገኙ የሚችሉበት ሁኔታ ነበር።

ሰልፉን ለመዝጋት ዶር ነጋሶ ንግግር አድርገዋል። ከሁለት ሳምንታት በፊት 70 አመታቸውን እንዳከበሩ የገለጹት  ዶር ነጋሶ የተሰማቸዉን ከፍተኛ ደስታ ገልሰዋል።

«እዚህ ያላችሁ አብዛኞቻችሁ የልጄቼ ልጆች ልትሆኑ ትችላላችሁ። ተስፋ የማድረግባችሁ ናችሁ» ብለዋል ዶር ነጋሶ

በመጨረሻ የሰልፉ አዘጋጆች መንገዱን ለዘጉባቸው ፖሊስ ሰራዊቶች ምስጋናቸዉን አቅርበዋል።

12:30  PM   (ኢትዮጵያ ሰዓት)

«ፖሊሶች በሚኒሊክ ሆስፒታል አድርጎ ወደ ጃን ሜዳ የሚሄደዉን መንገድ ብቻ ነበር የከፈቱት። ነገር ግን  ሕዝቡ እየገፋ ወደ ቀበና አደባባይ ደርሷል። በቀበና አደባባይ፣  ከመቶ ሺህ በላይ ሕዝብ ይገኛል። በዚያ የአንድነት አመራር አባላት ንግግር እያደረጉ ነዉ። ወደ ሚኒሊክ ሆስፒታል ከሚወስደው መንገድ ዉጭ ያሉ ሌሎች መንገዶች በሙሉ በታጠቁ ኃይላትና አመጽ በታኞች በመዘጋቱ፣ ሰልፉ በዚያዉ በቀበና አደባባይ ሳይጠናቀቅ አይቀርም።

አቶ ትእግስቱ አወሎ የአንድነት ፓርቲ ብሄራዊ ምክር ቤት ጸሃፊ ንግግር አድርገዋል። በህዝቡ ያላቸውን ኩራት ገልጸዋል። «ነጻነት እስኪሰፍን ትግሉ ይቀጥላል» ብለዋል።

የአንዷለም አራጌ መልእክት ተነቧል።

«ብዙ ፈተናዎችንና አፈናዎችን አልፋችሁ በምታደርጉት በዚህ ታላቅ ሰላምዊ ሰልፍ በካል ባለገኝም በመንፈስ ከጎናችሁ ነኝ። በዚህም ታላቅ ደስታ ይሰመኛል። ፍርሃትን  ያላሸነፈ በአዋጅ ነጻ ሊሆን አይቻልም። ፍርሃት ያላሸነፈ ለልጆቹ ነጻ አገር ሊያወርስ አይችልም። ፍርሃትን አሸንፋችሁ ድምጻችሁን ማሰማታችሁ ትልቅ ድል ነዉ። እኔ እዚህ ያቆመኝ (እሥር) የነጻነት ናፍቆት ነዉ»  አንዱዋለም አራጌ

ኢንጅነር ኃይሉ ሻዉል የክብር እንግዳ ተደርገዉ ተጋብዘው ነበር። ግን በሕመም ምክንያት በአካል አልተገኙም። ነገር ግን በሰልፉ የሰማቸዉን ደሳት ገልጸዋል።

ከነበቀለ ገርባም የተላለፈ መልእክት ተነቧል።

11:55  AM  (ኢትዮጵያ ሰዓት)

«አስተዳደሩ አዞናል። እባካችሁ ችግር ዉስጥ አትክተቱን»በሚል ፖሊሶች ልመና አድርገዋል።  የአገዛዙ ፓርቲዎች ተደብቀዉ ህዝቡን እና ፖሊሲን ለማጋጨት እየሞከሩ ነዉ። ግን የአንድነት አመራሮች በአገዛዙ ወጥመድ ዉስጥ ላለመግባት በማስተዋልና በእርጋታ ሕዝቡን እየመሩት ነዉ።

«ሃሩር የሆነ  ጸሃይ ነዉ። ሕዝቡ ሂድ ስንለው ይሄዳል። ተቀመጥ ስንለው ይቀመጣል። በጣም ጨዋና ሰላማዊ ህዝብ ነዉ።» አቶ ሃብታሙ አያሌዉ

https://www.youtube.com/watch?feature=player_embedded&v=QouaB6UpsSM

መፈክሮች !

ሕዝብ አሸማቆ መግዛት አሸባሪነት ነዉ !
ኢሕአዴግነት ከኢትዮጵያዊነት አይበልጥም!
አንድ ናት አገራችን !
ሙስና የስርዓቱ መገለጫ ነዉ !
መብታችንን ከኢሕአዴግ አንጠብቀም !
ይሄ ስርዓት እስኪለወጥ ትግላችን ይቀጥላል።

11:50  AM   (ኢትዮጵያ ሰዓት)

ዶር ነጋሶ «ከቀበና ወደ ሚኒሊክ ሆስፒታል አድርገን ወደ ጃን ሜዳ እንድንቀሳቀስ ነዉ የሚፈልጉት። ይሄ ደግሞ አይሆንም።አደባባዩን ለመዞር እየሞከርን ነዉ። ከዚያ ወደ አራት ኪሎ እንዞራለን።  ከፖሊስ ጋር ለመደባደብ አንፈልግም። እኛ ሰላማዊ ነን። »  ዶር ነጋሶ የአንድነት ሊቀመንበር

«ይሄን ሰልፍ ፖሊሶች እየዘጉት ያለዉ በአስተዳደሩ ቀጥተኛ ትእዛዝ ነዉ። ተጠያቂዉ አስተዳደሩ ነዉ» አቶ ዳንኤል ተፈራ።

ቋጠሮ ፣ አቡጊዳ፣ ዘሃበሻ ፣ ኢትዮጵያን ሪቪው ድህረ ገጾች በአሁኑ ጊዜ አገር ቤት የሚደረገዉን ሰልፍ በስፋት እየዘገቡት ነዉ። የቃሌ፣ ሲቪሊቲ፣ ከረንት አፌር የፓልቶክ ክፍሎችም በቀጥታ ከአዲስ አበባ ስልክ እየደወሉ ሰልፉን እያስተላለፉ ነዉ።

11:30  AM   (ኢትዮጵያ ሰዓት)

የሰው ግድግዳ ላይ ያለ አግባብ ፖስተር ለጥፈሃል በሚል የታሰረው የአንድነት የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዳንኤል የሚከተለዉን አስተያየት ሰጠዋል፡

«ትላንት የነበረኝ ስጋት መታሰሩ ሳይሆን፣ ለብዙ ጊዜ የሰራንበት ሰልፍ ላይ ላልገኝ ይሆን የሚል ነበር ስጋቴ። ከምሽቱ ሁለት ሰዓት በዋስ ፈተዉኛል። በዚህ ታላቅ ሰልፍ  መገኘቴ በጣም አስደስቶናል። በኢትዮጵያ ሕዝብ በጣም ኮርቻለሁ። ከመቶ ሺሆች በላይ ሕዝብ ነዉ አሁን የሚገኘው። በመስቀል አደባባይ ቢኬድ ደግሞ አስቡት ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል። አገዛዙ ለህዝብ የማይገዛ መሆኑን፣ ህግን የማያከበር መሆናቸውን  አሳይተዋል። ወደ ዘጠኝ አደባባዮች አማራጭ ብንሰጣቸውም አንዱን እንኳ መፍቃደ የመቻል አቅም የሌላቸው ናቸው። »

 

11:20  AM   (ኢትዮጵያ ሰዓት)

ብዙ ሕዝብ በሰልፉ ተገኝቷል። በየቦታዉ መንገዶች በፖሊሲ በመዘጋታቸው እጅግ በጣም ብዙ ሕዝብ ገና ሰልፉን አልተቀላቀለም። በመስቀል አደባባይ አካባቢም ብዙ ህዝብ ይገኛል። ሰልፈኞቹ ወደ ቀበና አደባባይ አካባቢ ናቸው። አገዛዙ መንገዶችን ከለቀቀና ዜጎችን ሰልፉን እንዲቀላቀሉ ካደረገ ሰልፈኛው ከቁጥጥር ዉጭ ይሆንብናል የሚል ፍራቻ ያላቸው ይመስላል። ሰላማዊ የሆነ የራሱን ሕዝብ እንደዚህ የሚያፍን መንግስት፣ በዚህ ዘመን መኖሩ ያሳዝናል።

http://www.ethiopianreview.com/video/watch.php
ተጨማሪ ቪዲዮ እዚህ ይመልከቱ !

11:05   AM   (ኢትዮጵያ ሰዓት)

ሕግን ማስከበር፣ ሕዝብን ማገልገል የሚገባቸው ፌዴራሎች የሕዝብን ድምጽ ለማፈን ፣ ሕዝቡ እንዳያልፍ ለማድረግ፣  እጅ ለእጅ ተያይዘው መንገድ ሲዘጉ !!ሕዝቡ ግን እንደ እነርሱ እንዳልሆነ ለማሳየት «ፖሊስ የኛ» እያለ ነዉ። ፖሊሶች ይሄን እያዩ ከሕሊናቸው ጋር እንደሚነጋገሩ ነዉ።

«መንግስት በአስቸኳይ ብሄራዊ እርቅ ይጠራ !  ነጻነታችንን ከኢሕአዴግ አንጠበቅም !!!!» ከተሰሙት መፈክሮች መካከል !!!  ሰልፈኞቹ ቀናባ መንገዱ ላይ ተቀምጠዋል። ሰልፉ ደምቋል። ህዝቡ በብዛት እየተቀላቀለ ነዉ።

11:00   AM   (ኢትዮጵያ ሰዓት)

የርዮት አለሙ እህት «የርዮት መታሰር ቢያሳዝነኝም። በሺሆች የሚቆጠሩ ርዮቶችን እንዳፈራች ነዉ የሚያሳየዉ። የሕዝቡ ስሜት በጣም የሚያስደስት ነዉ። መስቀል አደባባይ ለሰልፍ አይመችም ነበር ያሉት። ግን ደመራ ሲብስራበት አይተናል። ይሄ የሕዝብን ድምጽ ማፈን ነዉ»

ዶ/ር ነጋሶን ጨምሮ ሁሉም የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የ33ቱ ፓርቲዎች አመራሮች ሰልፉን ለማደናቀፍ ከተኮሎኮሉት የፖሊስና የደህንነት ሀይሎች ጋር ፊትለፊት ተጋፍጠዋል፡፡ ዶ/ር ነጋሶ ሰልፉን ሲቀላቀሉ ህዝቡ “ነጋሶ ማንዴላ!! ነጋሶ ማንዴላ!!” በማለት ተቀብሏቸዋል፡፡

ወጣት ሳሙኤል “ ነጻነትን ስለተጠማሁ ነዉ እዚህ የመጣሁት”

10:55   AM   (ኢትዮጵያ ሰዓት)

ታላቅ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ነዉ። ሰልፉ በጣም ደምቋል። ፖሊሲ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደዉን መንገድ ዘግቷል። ሕዝቡ እየተንቀላቀለ ነዉ። ወደ መስቀል አደባባይ እንዳይኬድ ፖሊስ ስለዘጋ የፓርቲዉ አመራሮች ለጊዜዉ ወደ ቀበና አደባባይ ቀስ በቀስ ለመሄድ እየገፋ ነዉ። ከዚያም ወደ አራት ኪሎ ለመሄድ ሙከራ ይደረጋል።

ወደ ጃንሜዳ የሚወስደው መንገድ ክፍት ነዉ። አገዛዙ ጃንሜዳ ሄዳችሁ ሰልፍ አደርጉ እያለ ነዉ። ፓርቲዉ ግን ሰልፍ በጃንሜዳ ማድረግ ሕግን መጣስ እንደሆነ በመጥቀስ  ፣ «ሕግ እንዲከበር እናደርጋለን እንጂ ለሕግ ጥሰት አንተባበርም» በሚል የጃን ሜዳዉን ዉድቅ አድርገዉታል። የወታደራዊ ካምፕና ትምህርት ቤቶች በቅርበት ባሉበት ቦታ ሰልፍ መደረግ እንደማይቻል የሚጠቅሰዉን ሕግ በማጣቃስና በጃንሜዳ ትምህርት ቤቶችና ወታደራዊ ካምፖች በመኖራቸው ፣ በዚያ ስልፍ ማድረግ እንደማይታሰብ አሳዉቀዋል።

10:30   AM   (ኢትዮጵያ ሰዓት)

“ፖሊስ የሕዝብ ነዉ” እያሉ ሰልፈኞች እየጮሁ ናቸው። በጣም ብዙ ሕዝብ እየመጣ ነዉ። ወደ መስቀል አደባባይ ብዙ ሕዝብ እየሄደ ነዉ።

ይሄን ቪዲዮ ይመልከቱ !

ፖሊሶችን ለማግባባትን ለማሳመን ሙከራ ቢደረግም ፌዴራሎች በጭራሽ ፍንክች አንልም ብለዋል። በሺሆዎች የሚቆጠሩ ወደ ሰልፉ እየመጡ ነዉ። ፖሊስ ወደ አደባባዩ እንዳይመጣ እያገደ ነዉ። አገዛዙ ረብሻ እንዲፈጠር የሚፈልግ ይመስላል። የአንድነት አመራሮችና ህዝቡ ግን በተቻለ መጠን ከፖሊስ ጋር ግጭት ላለማድረግ እየሞከረ ነዉ።ፖሊሶች  በየቦታዉ ወደ ሰልፉ የሚመጡትን እየበተኑ ነዉ።

አቶ ትእግስቱ አወሉ፣ የብሄራዊ ምክር ቤት ዋና ጸሃፊ፣ የፓርቲዉ አመራር አባላት ስብሰባ አድርገዉ የፖለቲካ ዉሳኔ እንደሚወስዱ ገልጸዋል።

10:04   AM   (ኢትዮጵያ ሰዓት)

“የኢትዮጵያ ሕዝብ በኃይል አይንበረከክም ! ሙስና የስርዓቱ መገለጫ ነዉ ! የታሰሩ የሕሊና እስረኞች ይፈቱ ! የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላማዊ ነዉ !  ”እያለ ሰልፈኞች ሰላማዊነታቸዉን  እና ጨዋነታቸውን እያሰሙ ነዉ።

ፖሊስ ሰልፉን ለማደናቀፍ ዘብ ቆሟል:: ፖሊስ ሰልፉን ለማደናቀፍ ዘብ ቆሟል ትራፊክ ፖሊሶችም ትራንስፖርት እንዳይኖር መኪኖችን እያስቆሙ ነው፡፡ይህንን ሁሉ መሰናክል አልፈው ጀግኖቻችን በቦታው እየደረሱ ነው፡፡

ሰልፈኛዉ እንዲቀመጥ ጥሪ ቀርቧል። ፖሊሶች ወደ መስቀል አደባባይ አላሳልፍ ብለዋል። የሚያስገርም ነዉ።

9:50   AM   (ኢትዮጵያ ሰዓት)

ከኢትዮጵያ ጋር መስመር ማግኘት በጣም እያስቸገረ ነዉ። እስከአሁን ግን በደረሰዉ ዘገባ ፣ ሕዝቡ ወደ ቀበና እየመጣ ነዉ። ከፓርቲዉ ጽ/ቤት አልፎ አስፋልት ላይ ደርሷል። ነገር ግን ወደ ቀበና የሚያመጣ ትራንስፖርት ሁሉ አገዛዙ አቋርጧል።  ሕዝቡ በእግር ነዉ የሚመጣዉ።  ፖሊስ አላሳልፍም እያለ ነዉ ያለዉ።  ወደ መስቀል አደባባይ አትሄዱም እያሉ ነዉ ፖሊሶቹ !!!! የአመራር አባላት ለማነጋገር እየሞከሩ ነዉ።

አንዲትም ጠጠር አትወረወርም ! በሰላም ነዉ ሁሉንም የምናደርገዉ እያሉ ነዉ። ፖሊሶች እጅ ለእጅ ተያይዘው መንግዱን ዘግተዋል። ከአራት ኪሎ የመጡ ወደ ሰልፉ ለመቀላቀል የሚሞክሩትን፣  ፖሊሶች መንገዱን ዘግተዉ አላሳልፍ እያሉ ነዉ።

9:40   AM   (ኢትዮጵያ ሰዓት)

ለጊዜዉ ከአዲስ አበባ አንድነቶች የሚያስተላለፉት ዘገባ ተቋርጧል። ስልክ ሲደወል፣ በመሃከሉ ቴሌ በኢቲቪ የሚሰማን  ክላሲካል በመልቀቅ ስርጭቱን ጃም አርገዉታል። እንደገና ከኢትዮጵያ ጋር ለመገናኘት ሙከራ እየተደረገ ነዉ።

መስቀል አደባባይ በፖሊሶች ተከቧል። በዚያ አካባቢ በርካታ ሕዝቡ አለ። ሰልፈኞቹ የሚያመሩት ወደ መስቀል አደባባይ እንደሆነ የአመራር አባል የሆኑት አቶ ተክሌ በቀለ ገልጸዋል።

በአንድ በኩል የሚያስቅ በሌላ በኩል የሚያሳዝን ሥራ ነው ቴሌ እየሰራ ያለው። በሕግ የተፈቀደን ሰልፍን ኢትዮጵያዉያን እንዳይከታተሉ ማድረግ ምን ያህል አገዛዙ የፖለቲካ ኪሳራ ዉስጥ እንዳለ የሚያሳይ ነዉ። «99% ሕዝብ መርጥኛል፣ 4.5 ሚሊዮን አባላት አሉኝ፣ ኮንዶሚኔየሞች አስርቻለሁ፣ ልማትን አምጥቻለሁ …» የሚል ድርጅት ምን አስፈርቶት ነዉ ይሄን ያህን እራስን የሚያስገመት ተግባራት ላይ የሚሰማራዉ ?

9:30   AM   (ኢትዮጵያ ሰዓት)

ተከበረሽ የኖርሽዉ ባባቶቻችን ደም !
እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይወደም !

እያሉ ሰልፈኞች በማዜም በደማቅ ሁኔታ የኢትዮጵያዊነትን ስሜት እያንጸባረቁ ነዉ።

የሚከተለው በፓርቲዉ ጽ/ቤት የነበረዉ እንቅስቃሴ የሚያሳይ ነዉ።

9:20   AM   (ኢትዮጵያ ሰዓት)

የሰልፈኛው ቁጥር እየጨመረ ነዉ። የፖሊስ ቁጥርም ብዙ ነዉ። መንገድ እስከ አሁን አልተዘጋም። ሰለፈኞች መፈክሮች እያሰሙ ነዉ። ከመፍክሮች የሚከተሉት ይገኛሉ

– አሸባሪ አይደለንም፣ ዲሞክራሲ  እንፈልጋለን፣ እኩልነት እንፈክጋለን ፣ የጸረ ሽብር ሕጉ ጸረ-ሕገመንግስታዊ ነዉ ! አንዱዋለም አራጌ፣ እስክንደር ነጋ ፣ ርዮት አለሙ፣ በቀለ ገርባ፣ ናትናዔል መኮንን ..አሸባሪ አይደሉም፤ ድል የሕዝብ ነዉ

በእንግሊዘኛም መፈክሮች አሰምተዋል።

WE NEED FREEDOM ! FREEDOM ! FREEDOM!

WE NEED JUSTICE ! JUSTICE ! JUSTICE !

WE NEED EQUALITY ! EQUALITY ! EQUALITY !

9:00  AM   (ኢትዮጵያ ሰዓት )

በአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት በርካታ ሕዝብ ተሰብስቧል። መፈክሮች በከፍተኛ ድምጽ እየተሰሙ ነዉ።  ሕዝቡ በብዛት እየመጣ ነዉ። ሰልፉ ተጀምሯል። ይሀ ታሪካዎ ቀን ነዉ። አበል ተሰጧቸው ወይንም ፈርተዉ፣ ወይንም ተገደው ሳይሆን፣ ከልባቸው በራሳቸው ፍላጎት ዜጎች እንደዚህ በድፍረት ለመብታቸውና ለነጻነታቸው ሲወጡ ማየት በጣም ያስደስታል። ይህ ለአገር ወዳዶች፣ ነጻነት ናፋቂዎች ድል ነዉ።

የአንድነት ፓርቲ የዛሬዉን ሰልፍ ከማድረጉ በፊት በደሴ፣ ጎንደር፣ ባሀር ዳር፣ ጂንካ፣ አርባ ምንጭ፣ ፍቼ ሰላማዊ ሰልፍቾ ሕዝቡን ማንቀሳቀሱ ይታወቃል። በዚያ የታየዉ ዛሬ ደግሞ በመዲናችን ፊንፊኔ አዲስ አበባ እየተደገመ ነዉ።

 አንድነት በቀበና አካባቢ መነሻው ነው ያለው ሰልፍ ሊጀመር ነው…. ሰው ሁሉ ወደ ቀበና እየተጓዘ ነው….. ዝግጅቱ በፎቶ ይህን ይመስላል

 

7፡ 20  AM (ኢትዮጵያ ሰዓት)

የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት ሌሊቱን ሙሉ ሲሰሩ ነዉ ያደሩት። በርካታ መፈክሮች ተዘጋጅተዋል።  አስተባባሪዎች ቦታ ቦታዎችን እየያዙ ነዉ። በአንድነት ጽ/ቤት በርካታ ሰዎች ይገኛሉ። ከቀበና የሚነሱት ሰልፈኞች ወዴት እንደሚሄዱ ገና አይታወቅም። ነገር ግን ገዢዉ ፓርቲ እንደፈለገዉ ግን፣ ጃንሜዳ አይሆንም። ሰልፉ ሲጀመር የሰልፉ ማብቂያ የት እንደሚሆን ይታወቃል።

7፡00  AM   (ኢትዮጵያ ሰዓት )

አዲስ አበባ ነግቷል። የሚደረገዉን እንቅስቃሴ ከአዲስ አበባ በቃሌና ሲቪሊቲ ፓልቶክ ክልፎች በቀጣት ይተላለፋል። በተጨማሪም በቴሌኮንፈራንስ ኦዲዮ በመስማት መከታተልም ይችላሉ።

Teleconference: Sunday, September 29, 2013 at 1:00 AM  EST and 7:00 AM CET: Central European Time

Live Broadcasting – You can listen to our live stream by dialing  1-862-902-0100 and use Conference Code:838802

5፡30  AM   (ኢትዮጵያ ሰዓት )

አሁን ኢትዮጵያ እሁድ መስክረም 19 ቀን ነዉ።  ሊነጋ ትንሽ ሰዓታት ይቀራል። ከጠዋቱ  5፡30 AM ( በኢትዮጵያ አቆጣጠር አሥራ አንድ ሰዓት ተኩል)። የአንድነት ፓርቲ ከሌሎች ሰላሳ ሶስት ድርጅቶች ጋር በመሆን ሰላማዊ ሰልፍ የሚደርግበት ቀን ነዉ። የሰልፉ መነሻ  ቀበና በሚገኘዉ የአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት ሲሆን መድረሻዉ የት እንደሆነ በሂደት የምናየዉ ይሆናል።

ገዢዉ ፓርቲ በመስቀል አደባባይ አይደረግም ብሏል። ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ። በአጥር የታጠራበት፣ ረጃጅም ሳር የበቀለበት፣ ለጥምቀት በዓል እንጂ ለሰላማዊ ሰልፍ ፍጹም በማይመች ቦታ ማድረግ ትችላላቹህ እያለ ነዉ።ነገር ግን ጃን ሜዳ ሰልፍ እንደማይደረግ የአንድነት ፓርቲ አሳውቋል።

ገዢዉ ፓርቲ ፍጹም አሳፋሪ አደርባይነት የሞላበት እንቅስቃሴ እያደረገም፣ ይኸው  በሚያስደንቅ ሁኔታ ፣ ለዚህ ቀን ደርሰናል።

http://www.zehabesha.com/

posted by Tseday Getachew

 

ሰበር ዜና፣ የግንቦት ሰባት ህዝባዊ ኃይል የገቢ ማሰባሰቢያ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ!

ዛሬ ሴፕቴምበር 28 በኦስሎ ኖርዌይ ለግንቦት ሰባት ህዝባዊ ኃይል የታሳካ የገቢ ማሰባሰቢያ ተደረገ። በገቢ ማሰባሰቢያው ላይ በስጦታ እና ጨረታ ብቻ 408 ,633.85 የኖርዌጅያን ክሮነር የተገኘ ሲሆን ። ይህ ገቢ ከምግብ ሺያጭ ፣ ከመግቢያ ትኬት፣ ከቲሸርት ሺያጭ እንዲሁም ከተለያዩ ባህላዊ ቁሳቁሶች ሺያጭ ሳይጭምር መሆኑ ወዳጆችን ሲያስፈነድቅ ጠላቶችንን አንገት አስደፍቷል ። በፕሮግራሙ ላይ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እና ኮማንደር አሰፋ ማሩ በመገኘት ከሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያኖች ጋር ምክክር አድርገዋል። ሙሉ ዘገባውን በቅርብ ይዘን እንቀርባለን ።

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር !
ከኖርዌይ

Norway G7 fundrise

 

http://ecadforum.com/Amharic/

posted by Tseday Getachew

የከሰረ የሲዖል ፈላስፋው ኢሳይያስ አፈወርቂ “Vs.” ሲ. አይ ኤ፡

Isaias Afewerki Vs. CIA

ይህ የሚመለከቱት መታወቂያ አሥመራ ከተማ ቃኘው ተብሎ በሚታወቀው የአሜሪካ መንግሥት የስለላና የመረጃ ማዕከል ተጋዳላይ ኢሳይያስ አፈወርቂ በሚገፈለጉበት ሰዓት አንደ አባታቸው ቤት ገብተው የሚወጡበት ወጥተውም የሚገቡበት ልዩ የይለፍ መታወቂያ ነው።

የጽሑፉ ዓላማ፥

የኤርትራና የኤርትራውያን የትግል ታሪክ መዛግብት፤ በወቅቱ በጉዳዩ ቀዳሚ እጅና አስተዋጽዖ የነበራቸው ትውልደ ኤርትራውያን የዓይን ምስክሮች እንደሚተርኩትና እንደሚያወሱት የአቶ ኢሳይያስ አፈወርቂና የምዕራባውያን ሀገራት የጠበቀ ግኑኝነት የማይገልጸው ወዳጅነት ምን ይመስል እንደ ነበረና ይህን ግኑኝነት የሻከረበት ምክንያትም በጣም በጥቂቱ የሚያስቃኝ፤ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውን ለማድማት የተሰለፉ የጥፋት መልዕክተኛ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጨምሮ የመረጃ እጥረት ላላቸው ዜጎች ሁሉ መረጃ ለማድረስ ተጻፈ።

የጽሑፉ ውሱንነት፡

ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ እንደ አንድ ግለሰብ ጠንካራና ደካማ ጎን ያላቸው የሀገር መሪ ናቸው። ፕሬዝዳንቱ ምንም እንኳ ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በኋላ በኤርትራ የቴሌቪዥን ጣቢያና ድምጺ ሓፋሽ ኤርትራ እየቀረቡ በሚሰጥዋቸው ቃለ ምልልሶች ተራ ዜጋ ሳይቀር የሚያስደምሙ፣ ግር የሚያሰኙና በውል ነገሮች መቀላቀል የጀመሩበት አዲስ ምዕራፍ ቢሆንም የዚህ ጽሑፍ ይዘትና ውስንነት ግን በግለሰቡ ግለ ጸባይና  የእብደት ልምምዶች የሚያተኩር ሳይሆን ተስፋሚካኤል ጆርጆ የተባሉ ኤርትራዊ ጸሐፊ ጥር 1974 ዓ/ም አምስት ጸሐፊያን በጥምር “የምጽዋ ሲምፖዝዩም” በሚል ርዕስ ባዘጋጁት መጽሐፍ ውስጥ ከገጽ 44- 62  “የተገጣዮችና የሲ.አይ.ኤ ግኑኝነት” በሚል ንዑስ ርዕስ ሥር በጻፉት ታሪካዊ ሰነድ ብቻ ላይ መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ ጽሑፍ ነው።

ሐተታ፥ 

እርግጥ ነው ስለ ኤርትራ ሆነ ስለ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ የሚጽያፍ አንዳች ጉዳይ የለኝም። በመርህ ደረጃ ለኤርትራና ለኤርትራውያን የሚበጀውንና የሚረባውን የሚያውቅ ኤርትራዊ “ብቻ” ነውና። ሆነም ግን የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ስብስብ የሆነችው የአገራችን የኢትዮጵያ አገር በቀል ጠላቶች ስንዋጋ ሳይጠሩና ሳይፈለጉ ከነ ተረቱም “አይጥ ለሞትዋ የድመት አፍንጫ ታሸታለች” እንደሚባለው በቀደመ ዱላ ትምህርት ያልወሰዱ ቀቢጸ ተስፋ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ሳይጠሩ አቤት ማለታቸው ስላልተው ብቻ ነው። እንግዲህ፦

  • አቶ ኢሳይያስ ማለት አሥመራ ከተማ ቁጭ ብለው መላ ዓለም በምላሳቸው የሚያስሱ፣ የሚያዳርሱና የመጨረሻ የየቅዠት “ብጽእና” ደረጃ የደረሱ አገራቸው እንደ አገር ማስቀጠል የተሳናቸው ገዢ መሆናቸው እየታወቀ፤ 
  • አቶ ኢሳይያስ በምላሳቸው ብቻ የሚታይና የማይታይ ዓለም አንቀጥቅጠው የሚገዙና የሚያስተዳድሩ የከሰረ የሲዖል ፈላስፋ መሆናቸው እየታወቀ፤ 
  • አቶ ኢሳይያስ ማለት በገዛ አገራቸውና ሕዝባቸው እያደረሱት ያለው መጠነ ሰፊ ትውልድ የመጨረስ፣ የመቅጨትና የማጥፋት ዘመቻ ተደብቆ የማይደበቅ አሰቃቂ የምድሪቱ ግፍና በደልም ዋና መሃንዲስ ሆኖ ሳለ፤ 
  • ፕሬዳዝዳንት ኢሳይያስ ይህ ሁሉ ግፍና በደል እየፈጸሙ እስከ ዛሬ ድረስ በህይወት የመሰንበታቸው ምስጢር የሚረከባቸው ኃይል በመጥፋቱ ብቻ በበሰበሰ ዙፋን ላይ የተቀመጡ የሌለች አገር ለይስሙላ የሀገር መሪ ተብለው የሚታወቁ  የትልቅዋ እስር ቤት ሀገረ ኤርትራ መንዳቢ መሆናቸው እየታወቀ፤ 
  • አቶ ኢሳይያስ በምላሳቸው ከጸሐይ በታችም ሆነ ከጸሐይ በላይ እሳቸው የማያውቁት ከእሳቸው የተሰውረ አንዳች እውቀት ባይኖርም መሬት ያለው የሚመርዋት አገር ተጨባጭ ሁኔታ ግን ከአቅርቦት እጦት የተነሳ ወታደሮቹ በ90ዎቹ መጨረሻ የሰበሰቡት አስርት ዓመታት ያስቆጠረ የጠነበሰና የከራረመ ደረቅ እንጀራ በወንዝ ውሃ የሚመግብ መንግሥት ሆኖ ሳለ የሰው አገር ለማድማትና የሕዝቦች ስላም ለማደፍረስ ግን እንቅልፍ አጥተው የምላስ አርበኞችና ባንዳዎች አሰልፈውብናል።

ለምሳሌ ያክል የተመለከትን እንደሆነ ባሳለፍነው ሳምንት አቶ አንዳርጋቸው የተባሉ አንድ ኢትዮጵያዊ ኮሌነል በዛብህ ጴጥሮስ ማስለቀቅ የተሳናቸው ግለሰብ ዳሩ ግን ሰማኒያ ሚልዮን “ነጻ አወጣለሁ!” ባይ የነጻነት ትርጉም ያጠፉብን ቀልደኛ በበላይነት የሚመሩት የግንቦት 7 ልሳን በሆነው በኢሳት ቀርበው ከላይ ከፍ ሲል የተመለከትናቸው ድፍን ዓለም በአንድ ጉዳይ አንጥሮና አበጥሮ የሚያውቃቸው ፕሬዳዝዳንት ኢሳይያስና  ሻዕቢያ በተመለከተ እንዲህ ይላሉ።

የሀገርና የሕዝብ ክብር የሚባል ነገር አለ ሻዕቢያ ጋር። የምልህ ያለኸው ድሃ ነን ነገር ግን ከድህነት በምጽዋት ለመውጣት አንዋረድም የሚል አመለካከት አላቸው። ከሦስት አስከ አራት ቢልዮን እርዳታ ኢትዮጵያ ታገኛለች ያለው አምስት ሳንቲም ግን እርዳታ ኤርትራ አታገኝም ያለው። ያንን ገንዘብ አግኝቶ ሥራ ላይ ለማዋል አለመፈለግ አይደለም ገንዘቡን ስጡን ሥራ ላይ እናውላለን እንደማነርቀው እንደማናጭበረብር መከታተል ትችላላችሁ ነገር ግን እናንተ በፈለጋችሁትና በውስጥ ፖሊሲያችንን ተጽእኖ ማሳደር በሚችል መንገድ እኛ ይጠቅማል በማንለው ቦታ ላይ ለእናንተ ልጆችና ዘመዶች ደመወዝ መክፊያ በሚሆንበት መልኩ እርዳታ ሰጥተናል እያላችሁ እንድታሾፉ ግን አንፈቅድም ነው እያሉ ያሉት።” አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ

አዳፍኔ ምስክርነት በመስጠት የተካኑ እንደ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የሐሰት ምስክርነት መሰረት “አቶ ኢሳይያስ ለምራባውያን መንግሥታት የማይንበረከኩ፤ የማይበገሩና ሕዝባቸው ጥይት የማይበሳው ዳቦ ጋግረው የሚያጎርሱ፤ ምንም በተጽእኖ ውስጥ ቢሆኑም ያሰቡትን ከማድረግ የማይመለሱ ጀግና መሪ ናቸው” በማለት በውዳሴ እያሽሞነሞኑ ሲያስተዋውቁንና በተራ ቃላት ሲያደክሙን አቶ አንዳርጋቸው ኢሳይያስ አፈወርቂን ጥጦ እያጠባ ያሳደገ፣ በሞራልና በማተርያል ያደራጀ ከዚህም አልፎ ሁለት እጃቸውን ይዞ ወደ አሥመራ ቤተ መንግሥት/ወደ ሥልጣን ያመጣ፣ እስከ ኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ማግሥት ድረስ የአስመራ መንግሥት የጀርባ አጥንት ስለ ነበረ ኃይል/መንግሥት ግን አልነገሩንም። ለመሆኑ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ኤርትራም ሆነች አቶ ኢሳይያስ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ለማስተዋወቅ የደፈሩበት ምክንያት ምንድ ነው? ማንስ ሆዳቸው ቢረግጣቸው ነው እንደ ክፉ ደብተራ ያልተጻፈ የሚያነቡልን?

አቶ ኢሳይያስ አፋቸው በከፈቱ ቁጥርና ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሲ.አይ.ኤ ሆነ የአሜሪካ መንግሥት ሳይወነጅሉ፣ ሳያብጠለጥሉ፣ ሳይዘልፉና ሳይወነጅሉ ያለፉበት ዕለት የለም ቢባል ማጋነን አይደለም። በሌላ አነጋገር አቶ ኢሳይያስ በመንግሥትነት የሚመርዋት ትልቅዋ እስር ቤት ሀገረ ኤርትራ አሁን ለምትገኝበት ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ፤ አገራቸው ጥለው የሚኮበልሉ ወጣቶች ቁጥር መበራከት፤ የሕዝቦችዋ ከዕለት ወደ ዕለት እየከፋና እየከረፋ የመጣው የዘቀጠ የኑሮ ደረጃ፤ በአጠቃላይ ኤርትራ አሁን ለምትገኝበት ድቅድቅ ጨለማ በቃላት ተገልጾም የማያልቅ ምስቅልቅል ያለ የዜጎችዋ ህይወት በዋናነት የአሜሪካ የስለላ ድርጅት ሲ.አይ.ኤን ተጠያቂ ሲያደርጉ ነው የምንሰማቸው። (ሲ.አይ.ኤ ምግባረ ሰናይ ድርጀት ነው እያልኩ እንዳልሆነ አንባቢ እንዲገነዘብልኝ እወዳለሁ።)

አቶ ኢሳይያስ ሲ.አይ.ኤ ሆነ የአሜሪካ መንግሥት በነጋ በጠባ ቁጥር የእርግማን መዓት የሚያወርዱበት ምክንያት ምን ቢያገናኛቸው ነው? አቶ ኢሳይያስ ለመንግሥትነት ያበቃ ኃይል ማን ሆኖ ነውና ዛሬ አቶ ኢሳይያስ በምዕራባውያን ያላቸው አቋም ትኩረት ተሰጥጦት አቶ ኢሳይያስ የሚወደሱና የሚሞገሱ? ለመሆኑ የትናንቱ ሽምቅ ተዋጋ የዛሬው የሀገረ ኤርትራ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂና የምዕራባውያን መንግሥታት ግኑኝነት ምን ይመስል ነበር? ጸቡስ እንዴትና መቼ ተጀመረ? ለመሆኑ ኤርትራ ማን ናት ምንድ ናት? ብሎ በመጠየቅም ብልህነት ነው።

ሁላችን እንደምናውቀው ኤርትራ እስከ 1890 እ.አ.አ እንደ አገር ምንም ዓይነት ህልውና ያልነበራትና የትግራይ ክፍለ ግዛት የነበረች ለጣልያን ተላልፋ ከተሰጠች በኋላ ግን ጣሊያን ኤርትራ ሲል የሰየማት አገር መሆንዋን ይታወቃል። ወደ ርዕሳችን የተመለስን እንደሆነ ወደኋላ መለስ ብለን የኤርትራና የኤርትራውያን በተለይ በአቶ ኢሳይያስ ይመራ የነበረውን የትግል መስመር አደረጃጀት፣ እድገትና ግብ ታሪክን በጥንቃቄና በጥልቀት የመረመርን እንደሆነ አቶ አንዳጋቸው ሳያፍሩ እንደቀደዱልን ሳይሆን እውነቱ የአቶ ኢሳይያስ ከአሜሪካ መንግስትም ሆነ ከሲ.አይ.ኤ ጋር መላተም የአቶ ኢሳይያስ አገር ወዳድነትና አርበኝነት ሳይሆን ምስጢሩ የታጋይ ኢሳይያስ ከጀብሃ መገንጠል ማግስት ጀምሮ አቶ ኢሳይያስ ወታደራዊ አቅማቸው ለመገንባትና ተቃናቃዮቻቸው የውኃ ሽታ ለማድረግ አጋጣሚዎች ሁሉ ለመጠቀም በወሰዱት እርምጃ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የስለላ ድርጅቶችም እርዳታ ሊያገኙ በሚችሉበት መንገድ የተለያዩ ታሪኮች በመፍጠር ግኑኝነት መጀመራቸውን ተያይዞ በወቅቱ ከአሜሪካ መንግሥት ለሚሰጣቸው ተልዕኮ በአግባቡ እስከተወጡ ድረስ ማንኛውም ዓይነት ዕርዳታ ለማግኘት እንደሚችሉ ከሲ.አይ.ኤ በተሰጣቸው አፈጣኝ ምላሽ አቶ ኢሳይያስ ዓይናቸውን ሳያሹ ጊዜያዊ ጥቅማ ጥቅሞች ለማግኘት ሲሉ ብቻ የአገራቸውና የህዝባቸውን ጥቅም አሳልፈው በመስጠት የተፈራረሙት ውሎችና የፈጸሙት የሀገር ክህደት ወንጀል ከተጠያቂነት ለማምለጥ እንዲሁም የኤርትራ ሕዝብ ድጋሜ ለመደለል እንደውም አቶ ኢሳይያስ ሲ.አይ.ኤ ተብሎ ከሚታወቅ ስጋ ለበስ ማህበረ አጋንንት የስለላ ድርጅት ምንም ዓይነት ግኑኝነትም ሆነ እውቀት እንዳልነበራቸው ለመሸምጠጥ ሆነ ተብሎ አስበውበት እያደረጉት ያለ የክህደት ሥራ ነው። የሚያሳዝነው ይህን ታሪክ ጠንቅቀው የሚያውቁ በዓላ በርሃ አከባቢ ከነበሩ ታጋዮች መካከል ዛሬ አንዳቸውም በህይወት የሉም።

ይህን በተመለከተ ማለትም አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ በሕዝባቸውና በሀገራቸው የፈጸሙት ክህደት፣ አድርባይነት፣ ነፈሰ ገዳይነትና በተለይ ፕሬዝዳንቱ ከአሜሪካ መንግስት የስለላ ድርጅት ጋር የነበራቸው ወዳጅነትና ስምምነቶች በስፋትና በጥልቀት የሚዳስስ ከመታሰቤ በፊት ለህትመት የበቃ ለጸሐፊው ህይወት መቀጨትም ምክንያት የሆነ ሰነድ ሊንኩን በመጫን ማንበብ ይችላሉ http://www.ehrea.org/TesfaMikegiorgioAmarina.pdf

ሰነዱ “የምጽዋ ሲምፖዝዩም” በሚል ርዕስ ተዘጋጅቶ ለህትመት የበቃ ጥር 1974 ዓ/ም [ምጽዋ] ሲሆን ጸሐፊው ተስፋሚካኤል ጆርጆ ይባለሉ። ተስፋሚካኤል ጆርጆ በኃይለ ሥላሴ ዘውዳዊ ሥርዓት የደቀ ምሐረ ወረዳ ገዥ የነበሩ፤ በወቅቱ ሻዕቢያ ለማግባባት ከተሰየመው ጉባኤ አባላት መካከል አንዱ ሲሆኑ ኢሳያያስ ከዓላ በርሃ እጁን ይዘው አስመራ ድረስ በመምጣት በኤርትራ ክፍለ ሀገር በችግኝ ተከላ ሽፋኝ ይንቀሳቀስ ከነበረ በቀንድ አፍሪካ የሲ.አይ.ኤ ከፍተኛ ባለ ሥልጣን ሪቻርድ ፓውላንድ ያገናኙ ሰው ናቸው። የጀብሃ በወያኔና ህግሓኤ ትብብር መመታት ተያይዞ በሱዳን በኩል ወደ ውጭ ለመውጣት ያደረጉት ሙከራ ቀደም ብለው በአቶ ኢሳይያስና በሲ.አይ.ኤ መካከል የነበረ ግኑኝነት ይፋ በማድረጋቸው ከአሜሪካ መንግሥት ጥግተኝነት ሳያገኙ የቀሩና ከዚያ በኋላም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ይኖሩ እንደ ነበርና ሚያዝያ 13/1982 ዓ/ም በአቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮች መኸል አዲስ አበባ በድምጽ አልባ መሳሪያ ተደብድበው የተገደሉ ሰው ናቸው።

በነገራችን ላይ አቶ ኢሳይያስ በአሜሪካ መንግሥት ሆነ በሲ.አይ.ኤ ላይ አፋቸው ማላቀቅና ጸረ ምዕራባውያን ሀገራት አቋም ማንጸባረቅ የጀመሩት አቶ ኢሳይያስ በአንድ ወቅት በጀርመን አገር የሚገኙ ኤርትራውያን ሰብሰበው፦

“በባድመ ጦርነት ስለሆነ ነገር ራስህን ማባበል የምትችለው ነገር አይደለም። በእውነት ለመናገር ከሆነ ቆሽጥን የሚያሳርር ነው። ከምገልጸው በላይ የከፋ ነገር ነው የተፈጸመው። ሌላ መግለጫ የለውም። በውግያው የተሳተፉ ያውቁታል። ስትናገረው መልሶ መላልሶ የሚያናድድና የሚያበግን ነው። ይህ የምናገረው ለመጀመሪያ ጊዜ አሁን ነው።” 

ሲሉ የገለጹት ለአንዴና ለመጨረሻ በባድመ ተጀምሮ በባድመ የተገባደደውን የአቶ ኢሳይያስ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የመሆን ህልም የከሰመበትና አቶ ኢሳይያስ ባሰቡት ቁጥር የሲዖል ያህል የሚከብዳቸው የሞት ያህልም የሚመራቸው ጉም የዘገኑበትና የሲዖል ፈላስፋ ሆነው አርፈው የተቀመጡበት ከባድመ ጦርነት በኋላ እንደነበር ታሪክ ልብ ይለዋል። አቶ ኢሳይያስ በምዕራባውያን ላይ ምላሳቸውን ማስረዘም የጀመሩ እንግዲህ ከባድመ ጦርነት ሽንፈት ወዲህ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያትም አቶ ኢሳይያስ ኢትዮጵያን ስወጋ አሜሪካ ለምን አልደገፈችኝም?! ለምን ከጎኔ አልቆመችም?! ከሚል አጉል ልጅነትና እልህ ነበር። ሕዝባቸው እንደ እህል እየፈጩትና በማጭድ እየላጩት የሚገኙም ከአሜሪካ ጋር እልህ መጋባት ከጀመሩ ወዲህ ነው (በሰፊው)። ከዚያ በፊት የሁለትዮሽ የወዳጅነት ግኑኝነት ምን ይመስል ነበር? በማለት ጥያቄ ያነሳን እንደሆነ ግን አሜሪካውያን አቶ ኢሳይያስን “መተኪያ የሌለው!” በማለት ሲያወዳድሱት አቶ ኢሳይያስም በተመሳሳይ ጌቶቹን በቁልምጫ ይቀዳና ይጠራ እንደነበር ነው የሚታወቀው።

 ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

E-mail: yetdgnayalehe@gmail.com

posted by Tseday Getachew

በአዲስ አበባ በርካታ ቤቶች ሊፈርሱ ነው

 ኢሳት ዜና :-በከንቲባ ድሪባ ኩማ የሚመራው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የያዘውን የአምስት ዓመት ዕቅድ ሰሞኑን ባካሄደው ስብሰባ ወደሁለት ዓመት ካጠፈ በኋላ በሚቀጥሉት ሁለት አመታት የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ያረጋግጣል ያለውን መልሶ ማልማት ሥራ በሰፊው እንደሚያከናውን አስታውቆአል፡፡

በዚህ የመልሶ ማልማት ሥራ በመሃል ከተማ የሚገኙ በርካታ ቁልፍ ቦታዎች የሚፈርሱ ሲሆን ነዋሪዎችም የመፈናቀል አደጋ ተደቅኖባቸዋል፡፡

በ2006 እና  በ2007 በጀት ዓመትም የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር  በጥቅሉ 2 ሺህ 140 ሄክታር ቦታ ለመልሶ ማልማትና ለማስፋፊያ ስራዎች ለማዋል አቅዷል። ቦታዎቹ ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ ለንግድ ቦታዎች፣ ለኢንዱስትሪና ለመሳሰሉት በጨረታና በምደባ ስራ ላይ የሚውሉ ናቸው፡፡

የመልሶ ማልማት ከሚከናወንባቸው አካባቢዎች መካከል ፥ አራዳ ክፍለ ከተማ ደጃች ውቤ ሰፈር 11 ነጥብ 6 ሄክታር ፣ አራዳ ክፍለ ከተማ  የሚገኘው  የአሜሪካ ጊቢ   6 ሄክታር መሬት ያህል  የሚለማ ይሆናል፡፡ አፍሪካ ህብረት ቁጥር 2 ፣ ቡልጋሪያ ኤምባሲ አካባቢ 12 ሄክታር እና ለገሃር ዙሪያም 40 ሄክታር እንዲሁ የሚዘጋጅ  ይሆናል፡፡

በተመሳሳይ በልደታ ክፍለ ከተማ ዲአፍሪክ አካባቢ ለመልሶ ማልማት 10 ነጥብ 43
ሄክታር ተዘጋጅቷል ፤ ቀደም በመልሶ ማልማት የኮንደሚኒየም ቤቶች ግንባታ ከተከናወነበት አጠገብ የሚገኘው የጌጃ ሰፈርም  16 ነጥብ 7 ሄክታር መሬት በመልሶ ማልማት ስራው ተካቶአል።

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማም የአሜሪካ ጊቢ ጨምሮ 36 ሄክታር ቦታም ይለማል ተብሎ ይጠበቃል።

የቀበሌ ቤቶችን ተከራይተው የሚኖሩ የአ/አ ነዋሪዎች በመልሶ ማልማት ምትክ የኮንዶሚኒየም ቤቶች የተሰጣቸው ሲሆን በደባልነትና በአነስተኛ ክፍያ ተከራይተው የሚኖሩ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ምትክ ቤት ባለመሰጠቱ እንደ አራት ኪሎ ባሉ አምና የተነሱ አካባቢዎች ዜጎች ለጎዳና ኑሮ ተዳርገው መታየታቸው የሚታወቅ ነው፡፡

ከመንግስት የእድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጋር እንዲጣጣም በማሰብ የአምስት ዓመቱ ዕቅድ ወደሁለት ዓመት የታጠፈ ሲሆን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ 70ሺ የጋራ የመኖሪያ ቤቶች ለመገንባት ተይዞ የነበረው ዕቅድ ከወዲሁ ከፍተኛ ትችት ስለገጠመው ወደ130ሺ እንዲያድግ ተደርጎአል፡፡

ይህም ሆኖ በተለይ የጋራ መኖሪያ ቤት ልማት፣  ቤት ለማግኘት ከተመዘገበው ጋር ሲነጻጸር እንዲሁም አስተዳደሩ ካለው አቅምና የአፈጻጸም ታሪክ ጋር ሲነጻጸር የዕቅዱን ስኬት ጥያቄ ላይ ጥሎታል።

ለኮንዶምኒየም ቤት ብቻ ከ800 ሺ በላይ ነባርና አዲስ ቤት ፈላጊዎች መመዝገባቸው የሚታወቅ ሲሆን በየዓመቱ 65 ሺ ቤቶችን እየገነቡ ይሳካል ቢባል እንኩዋን ተመዝጋቢውን ለማዳረስ በትንሹ ከ12 ዓመታት በላይ እንደሚፈልግ ታውቆአል፡፡

ይህ አፈጻጸም ደግሞ የቤት እጥረት በፍጥነት ለመፍታት ቃል ለገባው አስተዳደር ራሰምታት ነው ተብሎአል፡፡

ESAT

posted by Tseday Getachew

በእስር ላይ የነበሩት የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ተፈቱ

udj-andinet-party-leaders-issuing-statement-on-renaissance-dam

በእስር ላይ የነበሩት የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች

ዛሬ መስከረም 17 ቀን 2006 ዓ.ም. የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት እና የአሁኑ የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እንዲሁም በፓርላማ ብቸኛው የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካይና የአንድነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ግርማ ሰይፉን ጨምሮ በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የታሰሩት 26 የአንድነት አባላት ከሰዓታት ቆይታ በኋላ ተፈተዋል፡፡ በፖሊስ ተይዘው ወደጣቢያ የተወሰዱት የፓርቲው ዋና ፀሐፊ አቶ አስራት ጣሴ፣ የፓርቲው ሊቀመንበር ለመሆን በእጩነት የቀረቡትና የፋይናንስ ኃላፊ አቶ ተክሌ በቀለ፣ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ስዩም መንገሻ፣ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራና ሌሎች አመራሮችም ነበሩበት፡፡

አመራሮቹ የፊታችን እሁድ መስከረም 19 ቀን 2006 ዓ.ም. ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት ጀምሮ ቀበና መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፊትለፊት ከሚገኘው የፓርቲው ዋና ጽህፈት ቤት አንድነት ፓርቲ ከ33 ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በመሆን ለጠሩት የተቃውሞ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ በተለይ በአራዳ ክፍለ ከተማ በቅስቀሳ ላይ እያሉ መታሰራቸው ይታወቃል፡፡ ነገር ግን የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ለእሁዱ ሰላማዊ ሰልፍ እውቅና ቢሰጥም የከተማው ፖሊስ ለቅስቀሳ የሚሰማሩ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎችን በተደጋጋሚ ያለምንም በቂ ምክንያትና ክስ እያሰረ መፍታቱ አዲስ አይደለም፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ የአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አመራሮቹንና አባላቱን ለምን እና በምን የህግ አግባብ ለሰዓታት እንዳሰረ ብንጠይቅም ታዘንነው ከማለት ውጭ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡

https://www.facebook.com/MillionsOfVoicesForFreedomUdj?ref=hl

 

posted by Tseday Getachew

ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ለብሔራዊ ምክር ቤት አባላት ለቅስቀሳ ከመሰማራታቸው በፊት ያስተላለፉት መልዕክት

https://i1.wp.com/www.zehabesha.com/amharic/wp-content/uploads/2013/09/7788.jpg

የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በቅስቀሳ ላይ

UDJ

posted by Tseday Getachew

ፕሬዝዳንት ነጋሶ መሪ ሆኑ – ከአበበ ገላው (ጋዜጠኛ)

“ካሁን በኋላ አባሎቻችን ሳይሆኑ መታሰር ያለብን እኛ ነን…” ዶ/ር ነጋሶ ለዘ-ሐበሻ የሰጡት ትኩስ ቃለ ምልልስ

ጋዜጠኛና አክቲቪስት አበበ ገላው ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ትናንት ለዘ-ሐበሻ ከሰጡት አጭር ቃለ ምልልስ በኋላ በፌስ ቡክ ገጹ ያሰፈራት አጭር ግን ብዙ የምትናገር መልዕክት፦
መሪ ማለት ሌሎችን አጋፍጦ ዘወር የሚል ሳይሆን ከፊት ቀድሞ የመጣውን ሁሉ የሚጋፈጥ ማለት ነው። በትናትናው እለት የአንድነት አባላት በሰላማዊ መንገድ ስራቸውን በመስራታቸው ሲታሰሩ አብሬ እታሰራለሁ በማለት መደ ቤት ሳይሆን ወደ እስር ቤት ገብተዋል። በዚህም የታሰሩትን አስፈትተው መሪ መሆናቸውን አስመስክረዋል። ከዚህ በሁዋላ መታሰር የሚገባን እኛ እንጂ አባላቶቻችን አይደሉም ማለታቸው ቁርጠኝነታቸውን ያሳያል። ነጋሶ ወያኔን በቃኝ ብለው ህዝቡን በመቀላቀል ክብራቸውን አስመልሰዋል።
በሌላ በኩል አንድነቶችና ሰማያዊዎች ከምርጫ ፱፯ በሁዋላ የነጻነት ጥሪ እንዲያስተጋባ ማድረጋቸው ታላቅ እመርታ ነው። ፍርሃት ሲሸነፍ የአንባገነኖች የምጽአት ቀን ይቃረባል። ሁለቱ ፓርቲዎች እየተደጋገፉ መታገል ይጠበቅባቸዋል። የአንድነቶች ቅስቀሳ ምርጥ ነው።

 

posted by Tseday Getachew

ይይት ከግንቦት 7 የፍትህ የነፃነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ

አብርሃም ያየህ

ማ ስ ታ ወ ቂ ያ

የግንቦት 7 ዋና ፀሐፊና የድርጅቱ ያመራር አባል የሆኑት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ፣ ከቅርብ ቀናት በፊት ከኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) ጋር ባደረጉት ሰፊ ቃለመጠይቅ አማካኝነት በሰነዘሯቸው የተለያዩ አብይ ሃሳቦችና፣ ከቃለ-መጠይቁ ውጭ ነገር ግን ተያያዥ የሆኑ ሌሎች ጉዳዮች፣ መሰረት በማድረግ ለመወያየት ወስኛለሁ።

 

በውይይቱ ለመሳተፍ የፈለግኩበት ምክንያት፤

ያቶ አንዳርጋቸው ወቅታዊና አነጋጋሪ ቃለመጠይቅ የበርካታ ኢትዮጵያዊያኖችና ትውልደ ኢትዮጵያዊያኖች ሰሞነኛ ትኩስ የመወያያ ርዕስ ሆኗል። በተለይ ትኩረት የተሰጠው የውይይት ርዕስ ደግሞ፣ አቶ አንዳርጋቸው አፅንኦት ሰጥተው ሰፊ ማብራሪያ የሰጡበት፣ ማለትም – ከኤርትራ መንግሥት ጋር ግንኙነት ማድረግ አስፈላጊነቱና ጠቃሚነቱ የሚመለከተው ክፍል ነው። ብዙ ሰው እንደሚያወቀው፣ እኔም የወያኔና የሻዕቢያ ግጭት በተከሰተ ማግስት (ከአሥራ ሁለት ዓመታት በፊት መሆኑ ነው) ወደ ኤርትራ በመሄድ ከኤርትራ መንግሥትና ህዝብ ጋር መገናኘቴና መመካከሬ ይታወሳል። ከኤርትራ ጉዞየ መልስ፣ ከኤርትራ መንግሥትና ህዝብ ጋር የሚደረገው ግንኙነት ያለው ዘላቂ ፋይዳ ምን እንደሆነ በማስመልከትም “የኤርትራ ፋይል ሲከፈት” በሚል ርዕስ በተዘጋጀ ሰፊ መጣጥፌ አማካኝነት ለህዝብ ይፋ አድርጌያለሁ።

ሰፊውና በተከታታይ እትሞች የተስተናገደው መጣጥፌ፣ ውጭ ሀገር ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያኖችና ትውልደ ኢትዮጵያዊኖች ለማድረስ በማቀድ፣ ካናዳ በሚታተመው “ሐዋርያ” በተባለ ጋዜጣ አማካኝነት አስተናግጃለሁ። ሀገር ቤት ለሚኖረው ህዝባችን ለማድረስ ደግሞ፣ አሁን የኢሳት ባልደረባ የሆነው (መልካም አጋጣሚ ሆኖ የቅርብ ጊዜውን የአቶ አንዳርጋቸው ቃለ መጠይቅም ያስተናገደው) ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ይመራውና ያኔ ሀገር ቤት ይታተም በነበረው “ኢትኦጵ” በተባለ እውቅ መጽሔት አማካኝነት አስተናግጃለሁ።

ይሁን እንጂ፣ ያገራችን መሰረታዊ ችግር ሁሌም የሊሂቆቻችንና የፖለቲከኞቻችን (በተለይ የአማራ ብሔር ኤሊቶቻችን) የማዳመጥና የመደማመጥ ባህል እጥረት ነው። በመሆኑም፣ አሁን አቶ አንዳርጋቸውን እያደነቁና እየካቡ ያሉት በርካታ ሰዎች (በተለይ የአማራ ብሔር ተወላጆች) ያኔ እኔን ለማዳመጥ ግን አልተጉም። ተምረናል፣ ተመራምረናል ከሚለው ከኔ ትውልድ ይልቅ፣ ከፈሪሃ እግዚአብሔር እምነታቸው በመነጨ ምክንያት ይበልጥ ጥበበኞችና ብልሆች የነበሩ ጥንታዊያን ወላጆቻችን እንዳሉት – “ቀድማ ያሸተች ማሽላ፣ አንድም ለወፍ አሊያም ለወንጭፍ ትዳረጋለች” ሆነና፣ በትክክለኛ ጊዜ ያስተላለፍኩት ትክክለኛ መልዕክት በፅሞና ለማዳመጥ አልተፈለገም። አላዳመጡም ብቻ ሳይሆን፣ ይባስ ብሎ ከወያኔ ካድሬዎችና ጋሻጃግሬዎች ባልተናነሰ መንገድ ሊሸነቁጡኝ የቃጡ ተቃዋሚ ነን ባይ ጋጠወጦችም በወቅቱ አልታጡም ነበር።

እውነቱን ለመናገር ያህል፣ በደርግ ውድቀት ዋዜማ ከካርቱም ተነስቸ አዲስ አበባ የደረስኩት በግል ገንዘቤ ያውሮፕላን ትኬት ገዝቼ ነው። እንደዚሁም፣ ወያኔዎችን ለማጋለጥ ብቻ ወዳገሬ ከተመለስኩበት ጊዜ ጅምሮ ወያኔ አዲስ አበባን እስከተቆጣጠረ ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ በቆየሁባቸው 15 ወራቶች (ራሴ አልፈልግም ስላልኩ) ለአንዲት ወር ቢሆን እንኳ ስሜ በመንግሥት ደመወዝ መቀበያ ሊስት (payroll) ሰፍሮ አይገኝም። ይህ አሁንም በህይወት ያሉ የቀድሞ ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም የሚመሰክሩት ሐቅ ነው። በብዙ ድካምና ጥረት ወዳገሬ ተመልሸ ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያምን በግል ለአምስት ሰዓታት በማነጋር የመጣሁበትን ልዩ ምክንያት አስረድቼ፤ እሳቸውም ዓላማየን በሚገባ ተረድተው ሁሉም ያገሪቱ ሚድያዎች ክፍት ተደርገውልኝ በሰፊው የሰጠሁት ማስጠንቀቂያ አድማጭ አጥቶ ውሃ በልቶት መቅረቱ የሚያስቆጭ ቢሆንም፤ ብዙ አላሳዘንኝም። ምክንያቱም፣ ምንም እንኳ ጥፋቱና ብልሽቱ የወታደሮቹ ብቻ ሳይሆን፣ ከየፈረንጁ ሀገር የጎረፉት የኢትዮጵያ ሊሂቃን፣ የኤርትራን ጉዳይ ጨምሮ የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ሳያገናዝቡ ሥልጣን ከወታደሮቹ ጉያ እናስጥላለን በሚል ቁማር በፈጠሩት ውዥንብር ምክንያት ጭምር፤ በደርግ ያሥራ ሰባት ዓመታት አስተዳደር አብዛኛው ህዝብ ያኮረፈና የተበሳጨ በመሆኑ፣ የኔን የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ለምን በውል አላዳመጠም የሚል ቅያሜ የለኝም።

እኔን በግል የሚያስቀይመኝና የሚያስቆጣኝ ነገር ቢኖር፣ በወያኔና ሻዕቢያ ግጭት ማግስት በጽሁፍ በተለያዩ የሚዲያ ውጤቶች (በግጭቱ ማግስት የዘረጋሁት ባለ 18 ገፅ “አስቸኳይ መግለጫ” ያስታውሷል)፣ እንደዚሁም በተለያዩ ያውሮጳና ያሜሪካ ስብሰባዎች በአካል በመገኘት በቃል ያስተላለፍኩት ማስጠንቀቂያ መልዕክቱ ያለመደመጡ ነው። ምክንያቱም፣ በደርግ ጊዜ ባስተላለፍኩት ማስጠንቀቂያ መሰረት የተናገርኩት ሁሉ በተግባር የተመሰከረ ስለሆነና፣ በሻዕቢያና በወያኔ ግጭት ማግስት ግን እንደ ደርጉ ጊዜ ከሰማይ የወረድኹ ያልታወቀች ወፍ ስላልነበርኩ ነው።

የቁጣየ መሰረት ደግሞ፣ ያለምንም የህዝብ ውክልና፣ ለኤርትራ ከኤርትራዊያን በላይ የሚጣበቅና ኤርትራን በጠራራ ፀኃይ ከሕግ ውጭ በሆነ መንገድ ያስረከበን ሥርዓት ባዲስ አበባ ቤተመንግሥት አስቀምጠው፣ ባገር ድንበርና ሉዓላዊነት ሽፋን ከወያኔ ሥርዓት ጎን በመሰለፍ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የድሃ ልጆች በጦርነት ተማግደው እንዲያልቁ ያደረጉት ወያኔዎች ብቻ ሳይሆኑ ተቃዋሚ ነን የሚሉት የኢትዮጵያ ሊሂቃን ጭምር በመሆናቸው ነው። እነዚህ ነገር የማይገባቸው ሊሂቃን ከወያኔ ሥርዓት ወግነው ያስጨረሱብን ልጆቻችንን ብቻ ሳይሆን፣ ያንን ተደፈረ ያሉት መሬትና በመሬቱ ላይ ያለው ህዝባችንም (በተለይ ታላቁ የኢሮብ ህዝባችን) በማስወሰድ ጭምር ነው። ይኽ የማያስቆጨው የለም። እጅግ አሳሳቢውና ገና ያልተዘጋው የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝብ የውዝግብ ፋይል በእንጥልጥል ላይ እያለ፣ የወያኔ ሥርዓት ከሰማይ መና ያወርድልኛል ብሎ የሚያምን ሰው ካለ በቁሙ የሞተና የበከተ ወይም ለግል ጥቅሙ ሲል ከዲያብሎስ ጋር ቢሆንም በሽርክና ለመነገድ የተዘጋጀ አሳፋሪ ፍጡር ብቻ መሆን አለበት።

ከዚህ ጭብጥ በመነሳትና፣ ወደፊት በተከታታይ በሚቀርቡ መጣጥፎቼ በሚገለፁ ሌሎች ምክንያቶች፣ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በቅርቡ ያደረጉት ወቅታዊ ቃለመጠይቅ ከማንም ይበልጥ እኔን ለውውይት የሚጋብዝ ነው። ስለሆነም፣ እኔም በዚህ ውይይት በመሳተፍ በቅንነትና በግልፅነት ውይይቱን ለማስፋት ወስኘ ተዘጋጅቻለሁ።

ይህ ዛሬ የምወያይበት አብይ ጉዳይ በተመለከተ፣ ወዳጆቼ፣ ዘመዶቼ፣ ደጋፊዎቼና ሌሎች በርካታ ዜጎች በተለያዩ ጊዜያቶች፣ ወደ ኤርትራ ለምን ሄድክ? በዚያ በኩልስ ፋይዳ ያለው ሥራ ማከናወን ይቻላል ወይ? ያኔ ወደ ኤርትራ ያስኬደኽ ጉዳይስ አሁን በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? ወዘተ … የሚሉ ጥያቄዎች እያቀረቡልኝ በሚገባ ሳስረዳቸውና ሳሳምናቸው ቆይቻለሁ። ይህንን ጉዳይ በተመለከተ መወያየትም ሆነ መግባባት የማይቻለው ከወያኔ ደጋፊዎችና ጋሻጃግሬዎች ጋር ብቻ ነው። ምክንያቱም ግልፅ ነው፤ በዋናው መጣጥፎቼ ላይ እመለስበታለሁ።

ከኤርትራ መንግሥትና ህዝብ ጋር ተቀራርቦ መነጋገር ያለውን ፋይዳ ያስረዳኋቸውና ሃሳቡን ያመኑበት ብዙ ሰዎች (በተለይ የትግራይ ተወላጆች) በተደጋጋሚ የሚሰጡኝ ግብረ-መልስና የሚለግሱኝ ምክር፣ ሚዲያውን ተጠቅመህ ይህንን ጉዳይ ባጠቃላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ፣ በተለይ ደግሞ ለትግራይ ህዝብ፣ ይፋ ማድረግ አለብህ የሚል ነው። እኔም ሃሳባቸውና ምክራቸው በአክብሮት የምቀበለውና የማምንበት ቢሆንም፣ ሁሌም የምከተለው የአሠራር ስልት ወቅትንና ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ያስገባ በመሆኑ፣ ይህንኑ እያስረዳሁ ትዕግስታቸውን እንዲለግሱኝ ስማጠን ቆይቻለሁ። አሁን ያ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ስጠብቀውና ስመውኘውም የነበረ ወቅት ደርሷል። ምስጋናየ፣ ባጠቃላይ ለግንቦት 7 መሪዎች በተለይ ደግሞ ምንም ሳይፈራና ሳይደባብቅ ሃሳቡን በይፋ ግልፅ በማድረግ ይህንን ጠቃሚ ውይይት እንዲጀመር አጋጣሚውን ለፈጠሩልኝ ላቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ይሁንልኝ።

የውይይት መጣጥፎቼ ይዘትና ትኩረት

ይህንን ወቅታዊና ልዩ ውይይት ለመጀመር፣ ምንም እንኳ አጋጣሚውን የፈጠረልኝ ያቶ አንዳርጋቸው ቃለ-መጠይቅ ቢሆንም፣ የውይይቱ ይዘት ዋና ትኩረት ግን ባቶ አንዳርጋቸው ቃለ-መጠይቅ ዙሪያ ብቻ የሚያጠነጥን አይደለም። ያቶ አንዳርጋቸው ቃለመጠይቅ የራሴን የውይይት መድረክ እንድከፍት ሰበብ ከመሆኑ በቀር፣ የመጣጥፎቼ ይዘት ብቸኛ ወይም ዋነኛ አካል አይደለም። የኔ በዚህ ውውይት መሳተፍ፣ ምናልባትም ያቶ አንዳርጋቸውን ቃለ- መጠይቅ በማብራራትና በማዳበር አመኬላውንና ሸውራራ አመለካከቶችን አፅድቶ የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች ከሰመጡበት ማጥ በማስወጣት አዎንታዊ አስተዋፅዖ ይኖረዋል የሚል ተስፋ አለኝ።

በተለያዩ ርዕሰ-ነገሮች ተከፋፍለው የሚቀርቡት የመጣጥፎቼ ፍሬ-ሃሳቦች በዋነኛነት የሚያወያዩትና የሚያጠነጥኑት፤ ብዙ ውዝግብ፣ ክፍፍል፣ የኃይል አሰላለፍ ለውጥ፣ የትግል ስልቶች ለውጥና፣ ፀረ-ትግራይና የትግራይ ህዝብ (እኔን ጨምሮ) የተከሰተበት ማለትም ከኢትዮ-ኤርትራ ግጭት ጀምሮ እስከ አወዛጋቢው ምርጫ-97 ደረስ ባለው የጊዜ እርከን በተከናወኑ ጉዳዮች ላይ በማነጣጠር ነው። ከዚህ በተጨማሪ፣ መጣጥፎቼ፣ በምከተለው ወቅትን ግምት ያስገባ ስልታዊ አሠራር ምክንያት፣ ካሁን በፊት ለህዝብ ይፋ ያላደረግኳቸው ከበድ ያሉ ምስጢራዊ ጉዳዮች ጭምር ያካተቱ ናቸው። በዚሁ መሰረት፣ አጠቃላዩ የመጣጥፎቼ ይዘት ከዚኽ በታች በተመለከቱ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ የተመሰረቱ ይሆናሉ፤

1. መግቢያ፣

2. ከኤርትራ መንግሥትና ህዝብ ጋር የሚደረግ ግንኙነትና ትብብር ለምን?

3. የኔና የነአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ (የግንቦት ሰባቶች) ወደ ኤርትራ ሄዶ ከኤርትራ መንግሥት ጋር መነጋገር ሲነፃፀር፣

4. በወያኔና-ሻዕቢያ ግጭት ማግስት፣ ከሻዕቢያ ጋር በተደረገ ግንኙነትና ምክክር መሰረት፣ የኢትዮጵያ የሽማግሌዎች ምክር ቤት ለመመስረት ስለማስፈለጉ፤ ይህንኑ ለማሳካት የተደረገው አድካሚ ጥረትና ያልተሳካበት ምክንያት። የኢትዮጵያ ሽማግሌዎች ምክር ቤት መመስረት ለምን አስፈለገ?

5. እኔ የመሥራቹ አመራር አባል የሆንኩለት “የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ” (ትህዴን) መቼና ለምን ተመሰረተ? እድገቱና አሁን የሚገኝበት ሁኔታ ምን ይመስላል። ትህዴን በትግራይ ህዝብ ዘንድ እንዴት ይታያል?

6. በምርጫ-97 ዋዜማ “የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ህብረት – “Union of Ethiopian Democratic Forces” (ኢዴኃህ/UEDF) አዋላጅ የነበረው “የሁሉም ፓርቲዎች ኮንፈረንስ” – “All Parties Conference” (ሁፓኮ/APC) ሂደትና በኢዴኃህ/UPDF ምስረታ ትህዴንና የትግራይ ህዝብ ለማግለል የተፈፀመው አሳፋሪ ደባ፤ በዚህ አፍራሽ ደባ ምክንያት በ”ህብረቱ” (በኢዴኃህ) ላይ የደረሰው አጠቃላይ ኪሳራ። የ”ኢዴኃህ” አክሳሪ ደባ ለቅንጅት የሰጠው ጥቅም።

7. ምርጫ-97 እና በምርጫ-97 ዙሪያ የመአህድ/መኢአድ (የውጭ ክንፍ) የምርጫ “እቅድ-ሀ” (Plan-A)። የምርጫ-97 አንፀባራቂ ውጤትና የቅንጅት ስኬት ኢዴኃህን፣ ሻዕቢያን፣ ኦነግንና፣ ኦብነግን ስለማስደንገጡ፤ በተለይ ኦነግና ኦብነግ ስለወሰዱት ፈጣን እርምጃና፣ በዚህ እርምጃ የኔ ተሳትፎ።

8. የቅንጅት አመራሮች ተጠራርገው ወደ ቃሊቲ እንደወረዱ፣ በምርጫው ውጤት እጅግ ተደናግጠው ከነበሩት ኃይሎች መካከል፤ ሻዕቢያ፣ ኦነግና፣ ኦብነግ የወሰዱት ፈጣን እርምጃ። ከዚህ የሦስትዮሽ እርምጃ ጋር ተያይዞ የመአህድ/መኢአድ “እቅድ-ለ” (Plan-B) ስለመተግበሩ።

9. አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ከኢሳት ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ ውስጥ በመርሆ ደረጃ የምስማማባቸውና፣ በአፈፃፀምና በወቅታዊነት ምክንያት የምለይባቸው አንዳንድ ነጥቦች።

10. የአማራ ሊሂቃን (ኤሊቶች) የዕይታና የአደረጃጀት ችግር፤ ስልት የጎደለውና የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ያላገናዘበ ፖለቲካዊ አመለካከታቸው፤ ከእውነታው እጅግ የራቁና የተሳሳቱ ቅስቀሳዎቻቸው አደገኛነት፤ በሊሂቃን/በኤሊቶች ልጆቹ ያልታደለው የመላው አማራ ህዝብ ዕጣ ፈንታ ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ሲገመገም።

11. ምን መደረግ አለበት? የኔ የመፍትሔ ሃሳብ።

ስለዚህ፣ እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ጉዳዮች በቅደም ተከተልና፣ በተለያዩ የቀናት ልዩነት ስለማስተናግድ የሚመለከታቸው ሁሉ በጥሞና እንዲከታተሉኝ እጋብዛለሁ። የነገ ሰው ይበለን!

የአቶ አንዳርጋቸው ቃለ-መጠይቅ ያልተከታተሉ ሰዎች ይህንን የኢሳት ድረ-ገፅ (ሊንክ) በመጎብኘት ሊያዳምጡ ይችላሉ።
http://ethsat.com/video/esat-yesamintu-engida-ato-andargachew-tsege-sep-2013-ethiopia/ 


አብርሃም ያየህ
መስከረም 15 ቀን 2006 ዓ.ም. (September 25, 2013)

https://i2.wp.com/www.zehabesha.com/amharic/wp-content/uploads/2013/09/andadergachew.jpg

posted by Tseday Getachew

ስበር ዜና – አንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮችና አባላት ታሰሩ

የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ዛሬም ታግተው ወደ አራዳ ፓሊስ ጣቢያ ተወስደዋል፡፡ አብረዋቸው የታሰዩት አመራሮችና አባላት እንደሚከተለው እንዘረዝራለን !Millions of voices for freedom – UDJ

በፖለስ የታሰሩ አመራሮችና አባላት በከፊል

ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ – የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር
የተከበሩ ግርማ ሰይፉ – የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር
አቶ ስዩም መንገሻ – የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ
አቶ ዳንኤል ተፈራ – የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ
አቶ አስራት ጣሴ – ዋና ጸሃፊ
አቶ ተክሌ በቀለ – የፋይናንስ ጉዳይ ኃላፊ
አቶ ሽመልስ ሃብቴ – የማህበራዊ ጉዳይ ኃላፊ

አቶ ሃብታሙ አያሌው – የህዝብ ግንኙነት ም/ኃላፊ

አቶ ብሩ በርመጂ – የብሔራዊ ምክር ቤት አባል
አቶ አበበ አካሉ – የብሔራዊ ምክር ቤት አባል
አቶ እንግዳ ወ/ፃዲቅ – የብሔራዊ ምክር ቤት አባል

አቶ አለባቸው ነጋሽ – አባል
አቶ መካንንት ብርሃኑ – አባል
አቶ እንዳልካቸው ባዩ – አባል
አቶ ብስራት ተሰማ – አባል
አቶ ወንደሰን ክንፉ – አባል
አቶ ኃይሉ ግዛው – አባል
አቶ ደረጀ ጣሰው – አባል
አቶ ገዛህኝ – አባል
አቶ ባዩ ተስፋዬ – አባል
አቶ ወርቁ – አባል

EMF

posted by Tseday Getachew

 

“አጐቶቼ ሙስሊሞች ናቸው” – ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም

“ኢትዮጵያዊ አሸባሪ አለ ብዬ አላምንም”
“የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የምሆነው ፓርቲዎች ከተዋሐዱ ብቻ ነው”
“አጐቶቼ ሙስሊሞች ናቸው”

ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም

ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም ለሁለት ወራት በአሜሪካ ቆይታ አድርገው ተመልሰዋል፡፡ ስለቆይታቸው እንዲሁም በሌሎች ፖለቲካዊ ጉዳዮች “በተለይ” ከሎሚ መጽሔት ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡ የዘ-ሐበሻ አንባቢዎች በሃገር ቤት የሚታተመውን የሎሚ መጽሄት ለማንበብ እድሉ ካልገጠማቸው በሚል የዶ/ር ያ ዕቆብን ቃለ ምልልስ እንደወረደ አስተናግደነዋል።

ሎሚ፡- እንኳን በሰላም ተመለሱ!
ዶ/ር ያዕቆብ፡- እንኳን ደህና ቆያችሁኝ፡፡
ሎሚ፡- የአሜሪካ ቆይታዎ ምን ይመስል ነበር;
ዶ/ር ያዕቆብ፡- አሜሪካ የሄድኩት ከፊል ቤተሰቤ እዛ ስለሚገኝ ነው፡፡ እነሱን ለመጠየቅና እነሱን ለማየት ነው የሔድኩት፡፡ በአሜሪካ በርካታ ኢትዮጵያውያኖች እንደመኖራቸው መጠን ከእነሱ ጋር መገናኘቴ አልቀረም፡፡ ውይይቶችም የማድረግ አጋጣሚ ነበረኝ፡፡ በ”ቴሌ ኮንፍረንስ፣ ፓልቶፕ” አማካይነት በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርጊያለሁ፡፡ እንደሚታወቀው እኔ በአሁኑ ወቅት የማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ አባል አይደለሁም፡፡ እንደ ኢትዮጵያዊነቴ እራሴን ወክዬ ነው ከነዚህ ወገኖች ጋር ውይይት ያደረኩት፡፡ በሀገር ውስጥ ለዴሞክራሲና፣ ለፍትህ የሚደርጉትን እንቅስቃሴዎች ማወቅ ከሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት አድርገናል፡፡ በቆየሁበት ጊዜያት በዛ ያሉ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ ዙሪያ እንቅልፍ እንደሌላቸው ተመልክቻለሁ፡፡ የተለያዩ ድርጅቶች አሉ፡፡ የብዙዎቹ ምልከታ በሀገር ውስጥ ለዴሞክራሲ ለሚደረገው እንቅስቃሴ ድጋፍ መስጠት ነው፡፡ ለምሣሌ ማንሣት ካለብኝ “ኢትዮጵያዊነት” የሚባል አንድ ድርጅት አለ፡፡ ይህ ድርጅት ሲቪል ድርጅት ነው፡፡ የፖለቲካ ድርጅት አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ባህልና ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሀገር ውስጥ አንዳንድ ነገሮችን መስራት ይፈልጋሉ፡፡ ሌሎች የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ ደጋፊዎች አሉ፡፡ ከእነሱም ጋር በሀገራችን የሚደረገውን የዴሞክራሲና የፍትህ እንቅስቃሴ አስመልክቶ በውይይት መልክ ተነጋግረናል፡፡ እናም በአብዛኛው ቆይታዬ ያተኮረው በነዚህ ጉዳዮች ላይ ነበር፡፡
ሎሚ፡- በአሜሪካ ቆይታዎ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን ዓይነት መንፈስ እናዳላቸው ተገነዘቡ;
ዶ/ር ያዕቆብ፡- ለሰላማዊ ትግል የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ ተገንዝቢያለሁ፡፡ ከኔ ጋር መገናኘት የቻሉ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች በእውነቱ በሀገራችን ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ፍትህ እንዲሰፍን ፍላጐት አለን ሲሉ ገልፀውልኛል፡፡ የሚቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኛ ናቸው፡፡ በጉልበታቸውና በገንዘባቸው ድጋፍ ለማድረግ ይፈልጋሉ፡፡ ፈቃደኛም ናቸው፡፡ በአብዛኛው እንግዲህ ሰላማዊ ለውጥ እንዲመጣ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ በሌላ መስመር የሚሄዱ ይኖራሉ፡፡ እኔ ከእነሱ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት አልነበረኝም፡፡ ግን አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ጭንቀቱ በሀገራችን ሰላም ይኖራል ወይ; የሚል ነው፡፡ ጥያቄም ብቻም አይደለም፤ “ጭንቀትም ጭምር ነው” በዚህ በኩል ይህንን የማያስብ ኢትዮጵያዊ የለም፡፡ ብዙ አይነት ድርጅቶች አሉ፤ ብዙ ሲቪክ ድርጅቶች አሉ፡፡ አሁን አንዱን ጠቀስኩ እንጂ ሌሎችም አሉ፡፡ በነገራችን ላይ በአሜሪካ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ቁጥር ወደ አንድ ሚሊዮን ደርሷል፡፡ ያ ሁሉ ታዲያ በሀገሩ ጉዳይ ያገባኛል ይላል፡፡ እኔ በተለያዩ ሀገራት ኖሪያለሁ፤ እንደ ኢትዮጵያዊ የሀገሩ ጉዳይ የሚቆረቁረው ሕዝብ አይቼ ግን አላውቅም፡፡ ምናልባት የአቅም አለመኖር ተዳምሮ ብዙ አስተዋጽኦ ላያደርግ ይችላል፡፡ ግን በሀሣብ ደረጃ እንደ ኢትዮጵያዊነት ሁሌም የሚቆረቆር ሕዝብ ነው፡፡
ሎሚ፡- በውጭ የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ይሁንና ግን የአቋም ልዩነት አለ፡፡ በቅርቡ ኦነግ ለሁለት ተከፍሏል፡፡ ኢህአፓም ቢሆን አመራሮቹን በማሰናበት መግለጫ አውጥቷል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የራሣቸውን ችግር ሳይፈቱ፣ ለሀገር ችግር የሚኖራቸው ፋይዳ ምን ዓይነት ይሆናል ብለው ያስባሉ?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- ርግጥ ነው፤ ክፍፍሉ ለማንም እንደማይጠቅም ግልፅ ነው፡፡ ሁላቸውም ይረዱታል፡፡ በአገኘሁት አጋጣሚ ያነሣሁት ዋናው ነጥብ መተባበር አለብን፣ አንድ ላይ መስራት አለብን የሚል ነው፡፡ ከተቻለ መዋሐድ አለብን፡፡ በሀገር ደረጃና በአደራ መልክ ጭምር ሁሉም ለምን ፓርቲዎቹ አይተባበሩም; አብረው አይሰሩም; አይዋሃዱም; የሚል ጥያቄ ያነሳል፡፡ ዓላማችን ለሀገራችን ዴሞክራሲና ብልፅግና ማስፈን እስከሆነ ድረስ ምን ያለያየናል? የሚለው ጥያቄ ነው ወሳኙ፡፡ ከባህላችንም ይሁን ከፀባያችን ከየት እንደተገኘ ባላውቅም በሀገራችን አብሮ መስራት በጣም አስቸጋሪ ነገር ሆኗል፡፡ በፖለቲካዊ ብቻ ሣይሆን በማህበራዊ ሕይወት ጭምር፡፡ ይህ ነገር ደግሞ እዛም አለ፡፡ ይህ ተቀርፎ አንድ ላይ መሰባሰብ አለብን፤ ተቃዋሚዎች ተሰባስበን፣ ውጭም፣ ውስጥ ያለነው በአንድ ልብና ቃል ከቆምን ኢህአዴግን በምርጫ ማሸነፍ እንደሚቻል እንገነዘበዋለን ይላሉ፡፡ ቅንጅት ያሸነፈው እኮ በፓርቲዎቹ ውህደት ምክንያት ነው፡፡ እነሱ ፓርቲዎች ተዋህደው እስከሰሩ ድረስ በገንዘባችን፣በጉልበታችን ምንም ሣንቆጥብ እንረዳለን ነው እያሉ የሚናገሩት፡፡ እንደሚታወቀው ብዙ ድርጅቶች አሉ ግን በየፊናቸው መካሰስ፣ መወቃቀስ፣ መነቋቆር አለ፡፡ ለቆሙለት አላማ ገፍተው ከመሄድ ይልቅ በመጨቃጨቅ ጊዜያቸውን ያሣልፋሉ፡፡ አሁን እንደተባለው ኢህአፓ ለሁለት ተከፍሏል፤ እንዲሁም ኦነግ ለሁለት ተከፍሏል፡፡ ሌሎችም ፓርቲዎች ከነዚህ ውጭ ያሉ ተከፋፈሉ ሲባል ነው የምንሰማው፡፡ ቀደም ብዬ እንዳልኩት ይሄ ነገር የባህልም ይሁን የታሪክም የምን ውጤት እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ይሄ እንደውም ሶሲዮሎጂስቶች በሰፊው ሊያጤኑት የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያት ከተባለ “ለምንድ ነው ኢትዮጵያውያኖች አብረን በጋራ መስራት የማንችለው;” ለዚህ ጥሩ ምሣሌ ላንሣ፤ በውጪ አንድ የጥብቅና ቢሮ 1800 ጠበቆች አሉት፡፡ እኛ ጋር አንድ ቢሮ ውስጥ ሁለት ጠበቆች አብረው መስራት አይችሉም፡፡ ርግጥ ነው በሀገራችን ሽርክናን ሕጉ አይፈቅድም፡፡ በጣም አስገራሚ ነው! ለምን እንደማይፈቅድ አይገባኝም፡፡ ይህም ሆኖ ሁለት ጠበቃ አብሮ የሚሰራ የለም፡፡ የሕግ ስራ ደግሞ አብሮ ውይይት ተደርጐ ተመክሮበት የሚሰራ ስራ ነው፡፡ ሆኖም ግን እኔ የማውቃቸውና አብረው የሚሰሩ ሁለት ሦስት የሚሆኑ ጠበቃዎች የሉም፡፡ የሀገራችን አንድ ትልቁ ድክመት መከፋፈሉ ነው፡፡ መከፋፈል ባይኖር ይህንን ሁሉ ተቃዋሚ አንድ ላይ ማሣለፍ ቢቻል ኢህአዴግን በምርጫ በቀላሉ ማሸነፍ ይቻላል፡፡ ሕዝቡ የተከፋፈሉ ፓርቲዎችን አይፈልግም፡፡ በ1997 ዓ.ም. ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ ነበር የሚለው፡፡ ውጭ ያሉትም ቢሆን ትልቁ ችግራቸው የትኛውን ፓርቲ እንደግፍ? ሰማያዊ? አንድነት? መኢአድ… የትኛውን እንደግፍ ነው የሚሉት፡፡ በተከፋፈለ ኃይል ግን የትም ቦታ ላይ ሊደረስ አይቻልም፡፡
ሎሚ፡- በቆይታዎ ከሰብዓዊ መብት ተቋማትና ከአሜሪካ መንግስት አንዳንድ ኃላፊዎች ጋር የመገናኘት አጋጣሚ ነበርዎት;
ዶ/ር ያዕቆብ፡- አልነበረኝም፡፡ ሊያገናኘኝም የሚችል ሁኔታም አልነበረም፡፡ እንዳልኩህ እኔ የፖለቲካ ፓርቲን ወክዬ አይደለም የሄድኩት፡፡ ስለዚህ ምንም ሊያገናኘኝ የሚችል ነገር የለም፡፡
ሎሚ፡- ወደ አሜሪካ ከመሄድዎ በፊት ለጠ/ሚ ኃ/ማርያም አንድ ደብዳቤ አስገብተው ነበር፡፡ ጉዳዩም በቤንሻንጉል (ጉራፈርዳ) በተባለ አካባቢ የተፈናቀሉ ዜጐችን የሚመለከት ነበር፡፡ እናም ከአሜሪካ ሲመለሱ ክስ እንደሚመሰርቱ ገልፀው ነበር፡፡ የክሱን ይዘት ምንድን ነው? ተከሣሾቹስ እነማን ናቸው;
ዶ/ር ያዕቆብ፡- መጀመሪያ ክስ ከመመስረቱ በፊት፣ ለተከሣሹ ማስጠንቀቂያ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ልትከሰስ ነው፣ ይሄንን ነገር አስተካል የሚል ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፡፡ ይሄንን አስመልክቶ ለጠ/ሚ ኃ/ማርያም ደሣለኝ በጉራፈርዳና በቤንሻንጉል ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ በተባረሩት ኢትዮጵያውያን ምክንያት የእነሱን መብት ለማስከበር ክስ እንደምንመሰርት ማስጠንቀቂያ ሰጥቻቸዋለሁ፡፡ ደብዳቤ ፅፌላቸዋለሁ፡፡ ለዛ ደብዳቤ መልስ አላገኘንም፡፡ የዛን ደብዳቤ መልስ ለማግኘት ትንሽ ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ ጊዜም ሰጥተናቸው ነበር፡፡ በቀጣይ ደግሞ ክሱን ወደመመስረት ነው የምንሔደው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የነዚህ ሰዎች መፈናቀል ከፍተኛ ወንጀል ነው፡፡ በሰው ዘር ላይ የሚፈፀም ወንጀል “Crime against humanity” ነው፡፡ ይህ ደግሞ ብዙ ነገሮችን ይይዛል፡፡ ማፈናቀልን፣ ሰዎችን መደብደብን፣ የመሳሰሉትን ይይዛል፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ወንጀል ነው፡፡ በተለይ በዘር ላይ ተመስርቶ ከተደረገ በአለም አቀፍ ደረጃ ሊያስጠይቅ የሚችል ወንጀል ነው፡፡ በአለም አቀፍ ፍ/ቤት ክስ ከመመስረት በፊት በሀገር ውስጥ ያለውን የፍትህ ሁኔታ ማስጨረስ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ነው በኢትዮጵያ ውስጥ ክስ ለመመስረት የምንዘጋጀው፡፡ የክሱም ይዘት፣ ሰዎች ከቀያቸው ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ መፈናቀላቸውን ተከትሎ፣ ይህ ጉዳይ በሚመለከታቸው ባለስልጣናት ላይ ክስ መመስረት ነው፡፡ክሱ ሲመሰረት ማመልከቻ እናስገባለን፤ ማመልከቻው ፖሊስ ምርመራውን አጠናቆ፣ አቃቤ ሕግ ካመነበት ወደ ፍርድ ቤት ሊሄድ ይችላል፡፡ ሌላው በተፈናቀሉ ጊዜ ብዙ ንብረቶቻቸው ተዘርፈዋል፤ ወድመዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ንብረቶቻቸውን ጥለው ነው የሄዱት፡፡ ዘር ሊያመርቱ አልቻሉም፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ በፈለገበት አካባቢ የመዞርና፣ ኑሮ የመመስረት መብት አለው፡፡ በኢትዮጵያ ሕግ ብቻ ሣይሆን በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች አዋጅ የተከበረ ሕግ ነው፡፡ አንድ ዜጋ በሀገር ውስጥ በፈለገበት ቦታ ሄዶ የመኖርና፣ ንብረት የማፍራት መብት አለው፡፡ ይሄ ህግ ነው የተጣሰው፡፡ እነዚህ ሰዎች ወደቀዬአቸው እንዲመለሱ፣ የተዘረፈው ንብረታቸው እንዲመለስላቸው፣ ለደረሰባቸው ጉዳት ካሣ እንዲከፈላቸው እነኚህን ጥያቄዎች እናቀርባለን፡፡ ፍ/ቤቱ ይህን ተቀብሎ ሊያስተናግደን ከቻለ ጥሩ፤ ካልሆነ ግን ወደ አለም አቀፉ መድረክ መሄዳችን የማይቀር ነገር ነው፡፡ አሁን ክሱን በማዘጋጀት ላይ እንገኛለን፡፡ ክስ መመስረት የማንኛውም ኢትዮጵያዊ መብት ነው፡፡ የተፈፀመባቸው ነገር ግን እጅግ አሣፋሪ ነገር ነው፡፡ ኢትዮጵያን የሚያሣፍር ነው፡፡ ትናንት የተመሠረተች ሀገር አይደለችም፡፡ የብዙ ሺህ አመት ታሪክ ያላት ሀገር ናት፡፡ አንዱ ዜጋ በፈለገው አካባቢ መኖር አይችልም ብሎ ማፈናቀል…በእውነት በኢትዮጵያ ላይ ከዚህ የበለጠ ውርደት ያደረሰ ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡
ሎሚ፡- ክሱ እነማንን ያጠቃልላል;
ዶ/ር ያዕቆብ፡- በመጀመሪያ ደረጃ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ኃላፊዎች ይህንን ጉዳይ ሣያውቁ፣ እነዚህ ሰዎች ከቀያቸው ተባረሩ ማለት በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ባያውቁ እንኳን ማወቅ ነበረባቸው ተብሎ መክሰስ ይቻላል፡፡ ኃላፊነታቸው የነዚህን ሰዎች መብት ማስከበር ነው፡፡ ይሄ የክልሉ ብቻ ኃላፊነት አይደለም፡፡ የፌዴራል መንግስትም ኃላፊነት ነው፡፡ ስለዚህ በአንደኛ ደረጃ ተከሳሾች የፌዴራል መንግስት ባለስልጣናት ይሆናሉ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የክልሉን አስተዳደሮች…ከፕሬዚዳንቱ አንስቶ ሌሎችንም ሊያጠቃልል ይችላል፡፡
ሎሚ፡- እርስዎ በአሜሪካ በነበሩበት ወቅት በፀረ ሽብር ሕጉ ዙሪያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት አድርገው ነበር፡፡ እርስዎ የፀረ ሽብር ሕጉን እንዴት ይመለከቱታል;
ዶ/ር ያዕቆብ፡- አስፈላጊ አይደለም፡፡ ለኔ ኢትዮጵያዊ አሸባሪ የለም፡፡ ምናልባት ከውጭ የሚመጣ አሸባሪ ሊኖር ይችላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ድንበርን አጠናክሮ መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ እኔ በበኩሌ ኢትዮጵያዊ አሸባሪ አለ ብዬ አላምንም፡፡ እስከዛሬም ድረስ አልታየም፡፡ እንደኔ አስተሳሰብ አሸባሪነት እኮ የራሱ ትርጉም አለው፡፡ የፖለቲካ ዓላማ አድርጐ ተነስቶ ሕዝብን ለመበጥበጥ፣ ለማስረበሽ፣ የሕዝብን ሰላም ለማናጋት የሚደረግ ድርጊት ነው፡፡ የፖለቲካ ለውጥ እንዲመጣ ጫና ማድረግ፣ ጥያቄ ማቅረብ አሸባሪነት አይደለም፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ሕጉ ራሱ አሣፋሪ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የዚህ ዓይነት ሕግ አይሰራም፡፡ አንድ ሰው ፃፈ፣ተናገረ ተብሎ ወህኒ ቤት አይገባም፡፡ ብዙዎቹ በሽብርተኝነት የተከሰሱ ሰዎች ቦንብ አልወረወሩ፣ የመንግስት መዋቅር አላበላሹ፣ የመንግስት መዋቅር አላወደሙ፤ ለምን ተናገራችሁ፣ ፃፋችሁ በሚል ነው የታሰሩት፡፡ የፀረ ሽብር አዋጁ በሕገ መንግስቱ የተቀመጠውን ነፃነትን ይገድባል፡፡ የፖለቲካ እንቅስቃሴን ይገድባል፡፡ ይሄ ሕግ አንድ ሰው አሰበ ብሎ እንኳን የሚቀጣበት ሁኔታ አለ፡፡ አንድ ነገር ማሰቡን በምን ማረጋገጥ ይቻላል? ማረጋገጫ መንገድ የለም፡፡ ማንም የፈለገውን ነገር ማሰብ ይችላል፡፡ አንተ ከፈለክ እኔን ለመግደል ልታስብ ትችላለህ፡፡ ወንጀል ሰራህ ማለት ግን አይደለም፡፡ እኔን ለመግደል አስበህ እንደሆነ እንዴት አድርጌ ነው የማውቀው፡፡ እና በእውነት የፀረ ሽብር አዋጁ የሀገሪቱን የሕግ አካሄድ፣ የፍትህ አካሄድ የበለጠ ይጐዳል እንጂ የሚጠቅም አይደለም፡፡ የወንጀል ሕጉ ወንጀለኛን ለመቅጣት በቂ አንቀፆች አሉት፡፡ ይሄን አዋጅ በርካታ የሰብዓዊ መብት ተቋማት በአብዛኛው ያወገዙት ነው፡፡ ይህ በእውነት ለኢትዮጵያ ጥሩ ስም አይደለም፡፡ የዚህ አይነት ህግ የውጭ ባለሀብቶች እዚህ ሀገር መጥተው እንዳይንቀሣቀሱ ይከለክላቸዋል፡፡ ይሄ ሕግ በጣም ፅንፈኛና አላስፈላጊ ሕግ ነው፡፡ አሸባሪነትን መከላከል ካስፈለገ በሀገሪቱ ውስጥ ዴሞክራሲያዊና የሕዝቡ መብት መከበር አለበት፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ ዴሞክራሲ ካለ፣ ሕዝቡ የኔ መንግስት ነው ብሎ ካመነ ራሱ ሽብርተኝነትን ይከላከላል፡፡ ከሕዝቡ በላይ ማንም የለም፡፡
ሎሚ፡- ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ማመልከት ነው የሚያስፈልገው፤ እንጂ መንግስት የመከልከልም ሆነ የመፍቀድ መብት የለውም ይላል-ሕጉ፡፡ ይሁን እንጂ ሰማያዊ ፓርቲ ለሁለተኛ ዙር የጠራው ሰልፍ ታግዷል፤ ይሄን እንዴት ይመለከቱታል?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- ሰላማዊ ሰልፍ መከልከል ተገቢ አይደለም፡፡ ሰማያዊ ፓርቲም ቢሆን በወቅቱ ለሚመለከተው ክፍል አስታውቋል፡፡ በሀገሪቱ ሕግ ወይም በሕገ መንግስቱም ይሁን በሌላው አለም አቀፍ ሕግ ማስታወቅ እንጂ ማስፈቀድ አያስፈልግም፡፡ ይሄ ሰብአዊ መብት ነው፡፡ መብቴ ይከበር ብለህ አታስፈቅድም፤ ትጠቀምበታለህ እንጂ፡፡ መብት እንደተገሰሰ ታስታውቃለህ እንጂ መብቴ ይጠበቅልኝ ማለት አስፈላጊ አይደለም፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ በጊዜው አስታውቆ ነበር፡፡ መልስም የተሰጠው አልመሰለኝም፡፡ “ጉዳዩን በርግጥ በዝርዝር አላውቅም፡፡ አልነበርኩም፡፡” መልስ ተሰጠውም አልተሰጠውም በ48 ሰዓት ውስጥ ምላሽ ካላገኘ ሰላማዊ ሰልፍ ሊያደርግ ይችላል ይላል ሕጉ፡፡ ከዛ ባለፈ ግን ቢሯቸው ድረስ ሄዶ መደብደብ፣ ማንገላታት፣ ሰላማዊ ሰልፍን መከልከል ቀጥታ ሕገ መንግስቱን ቃል በቃል የሚፃረር ድርጊት ነው፡፡ መንግስት ያላከበረውን ሕገ መንግስት ማን ሊያከብረው ይችላል? መጀመሪያ መንግስት አርዓያ መሆን አለበት፤ መንግስት ካመፀ በምን ልትከላካል ነው? ይሄ የመንግስት አመፅ ነው፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የተዘጋጁ ሰዎችን መደብደብ ቢሯቸውን መበርበር አመፅ ነው፡፡ ይሄ በእውነት አሣፋሪ ድርጊት ነው፡፡ ከዚህ አይነት ድርጊት መውጣት አለብን፡፡ ዛሬ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፣ የመፃፍ፣ የመናገር መብት የትም ሀገር ያለ ነው፡፡ ቱርክ፣ ፈረንሣይ፣ እንግሊዝ ይደረጋል፡፡ ለምንድነው እኛ ሃገር ሰላማዊ ሰልፍ በዱላና በግድያ የሚስተናገደው? ከእንደዚህ አይነት ነገር መውጣት አለብን፡፡ እንደሌሎች ሕዝቦች ሁሉ መብቶቻችን እንዲከበሩልን እንፈልጋለን፡፡ ሰዎች ነን፤ እንደሌሎች ሕዝቦች ሁሉ ዴሞክራሲ እንፈልጋለን፡፡ ፍትህ እንፈልጋለን፣ ቅር ሲለን የመንግስት ፖሊሲ ሣይስማማን ሲቀር ወጥተን በሰላማዊ መንገድ መቃወም እንፈልጋለን፡፡ ይሄን መከልከል አያስፈልግም፡፡
ሎሚ፡- መንግሰት “አክሪራነት” የሚለውን ቃል ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ጥያቄ ጋር የማያያዝ አዝማሚያ ታይቶበታል፡፡ ይሄ ለጉዳዩ መፍትሄ ሊሆን ይችላል ወይ;
ዶ/ር ያዕቆብ፡- የማንኛውም ሕዝብ ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ካልሆነ በስተቀር በጉልበት ሊፈታ አይችልም፡፡ በመንግስት በኩልም ኃይል ተጠቅሞ የሕዝብን ጥያቄ ማዳከም አይቻልም፡፡ የሚሻለው ምንጊዜም ቢሆን ወደ ዘላቂ መፍትሄ የሚያመራውን ውይይት መምረጥ ነው፡፡ እነኚህ ሰዎች መንግስት በኃይማኖታችን ውስጥ ጣልቃ አይገባ ማለታቸው ትክክል ነው፡፡ ጣልቃ የሚገባ ከሆነ ይሄንን ነገር ማቆም አለበት፡፡ ዋናው ነገር ግን ኢትዮጵያ በኃይማኖት ተቻችሎ በመኖር በጣም ዝናን ያተረፈች ሀገር ነች፡፡ ይሄ አሁንም ሊቀጥል ይችላል፡፡ ግብፅ ሰላማዊ ሰልፍ የሚያደርጉት ሙስሊሞች ብቻ ናቸው፡፡ ክርስቲያኖች አስር ፐርሰንት ናቸው፡፡ ሶሪያ ሙስሊም ብቻ ነው ያለው፤ ሊቢያም እንደዛው፡፡ ኢትዮጵያ እኮ ከዚህ የተለየች ነች፡፡ እኔ አጐቶቼ ሙስሊሞች ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ዘመድ የሌለው የለም፡፡ ስለዚህ ዘመዶቼ ናቸው፡፡ ታዲያ በኔ ላይ ነው የሽብር ተግባር የሚፈፅሙት; አያደርጉትም፡፡ አስታውሳለሁ፤ ከሆኑ የቅርብ ጓደኞቼ ጋር ስንጨዋወት ሙስሊም ዘመድ የሌለው ኢትዮጵያዊ የለም በሚለው ተማመንን፡፡ በሀገራችን የሙስሊም አሸባሪነት የሚያስፈራ ነገር አይደለም፡፡ መብታቸው እስከተከበረ ድረስ ምንም የሚያስፈራ ነገር የለም፡፡ ዋናው ነገር ተግባብቶ ከሙስሊሞቹ ጋር መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ መብታችን ይከበር ብለው ጥያቄ ያቀረቡትን የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ሰዎችን ቃሊት ሄጄ አነጋግሪያቸዋለሁ፡፡ “እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሀገራቸውን የሚወዱ፣ ለሀገራቸው በጐ ነገር የሚመኙ፣ ሰላምና ዴሞክራሲን የሚመኙ ሰዎች ሆነው ነው ያገኘኋቸው፡፡ ከማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሚለዩበትን ሁኔታ አላየሁም፡፡
ሎሚ፡- ኢህአዴግ ላለፉት አንድ አመታት “የመለስ ራዕይ” በሚለው መርሁ ቀጥሏል፡፡ አንድ ፓርቲ በአንድ ሰው ወይም በሕይወት በሌለ የቀድሞ መሪው ሀገር መምራት ይችላል?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- በእውነት በጣም የሚገርም ነው፡፡ ሰው ከሞተ በኋላ በሬሳው ይግዛን ብሎ ይሄን ያህል ማጋነን፣ ማቅ ለብሶ ማዘን ተገቢ አይደለም፡፡ በጣም ኋላቀርነት ነው፡፡ እኔ እንደማየው “ሰው ስራው ታሪኩ ነው” ታሪክ ደግሞ ለማንም አያዳላም፡፡ የአቶ መለስ ስራ ታሪኩ ነገ ከነገ ወዲህ ይወጣል፤ እንጂ ዛሬ የተሰሩ ነገሮች (ጥሩ ተሰርተውም ይሁን መጥፎ) ሊደመሰሱ አይችሉም፡፡ ብዙ የማይደመሰሱ ነገሮች አሉ፡፡ በ1997 ዓ.ም. በመንግስት አባባል እንኳን 200 ሰዎች ሞተዋል /ተገድለዋል/፡፡ በዚህ ዙሪያ ማነው ተጠያቂው? ተብሎ የተፈረደበት አመራር የለም፡፡ ኢትዮጵያ ሀገራችን በታሪኳ ወደብ አልባ እንድትሆን ተደርጓል፡፡ ይሄን ሁሉ ታሪክ የሚፈርደው ነገር ነው፡፡ ዛሬ “ራዕይ፣ራዕይ” ስለተባለ እነኚህ ድርጊቶች ይሰረዛሉ ማለት አይደለም፡፡ በጐውም፣ መጥፎውም፣ ስህተቱም ተደብቆ አይቀርም፤ ይወጣል፡፡
ሎሚ፡- ሀገሪቱ ወዴት አቅጣጫ እየሄደች ይመስልዎታል?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- የዚህች ሀገር የወደፊት መፃኢ ዕድል ሁሉንም የሚያሳስብ ነው፡፡ የብዙዎች ጭንቀትም ይሄ ነው፡፡ ሀገሪቱ በብሔረሰብ ተከፋፍላ በአንዳንድ አካባቢ ከፍተኛ ጥላቻ እየተፈጠረ ነው፡፡ ልንሸሸው የማንችለው ነገር ነው፡፡ ተረባርቦ ሀገሪቱን ማዳን ሕዝቡን ማዳን ያስፈልጋል፡፡ ጥላቻ ሲፈጠር እያየን ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ወደ መጥፎ አቅጣጫ ሊያመራ ይችላል፡፡ ጥላቻው የለም ማለት፣ አውሎ ነፋስ ሲመጣ ሰጐን አንገቷን ቀበረች የሚሉት ተረት ዓይነት ቢጤ ነው የሚሆነው፡፡ ጥላቻ ስለመኖሩ ከጉራፋርዳና ከቤንሻንጉል የበለጠ ምን ማስረጃ ያስፈልጋል? ይሄ በፍጥነት እልባት ማግኘት አለበት፡፡ ምንም ጥርጥር የሌለውም፤ ሀገሪቱ በብሔር ተከፋፍላለች፡፡ ስም ባልጠቅስም፤ አሜሪካ በነበርኩበት ወቅት የአንድ ብሔር ቀን ብለው ሲያከብሩ ተመልክቻለሁ፡፡ ይህንን ስናይ ወዴት ነው የምንሄደው? የዚህች ሀገር መፃኢ ዕድልስ ምን ይሆን? በዚህ ዓይነት አካሔድ ሀገር እንደ ሀገር ሊቀጥል ይችላል ወይ? የሚል ስጋት አዘል ጥያቄ ማንሳታችን አይቀርም፡፡ ርግጥ ነው፤ የአንዱ ጐሣ መብት አይከበር አይባልም፡፡ ቋንቋው መከበር አለበት፤ በቋንቋው መናገር መቻል አለበት፤ ግን በጎሳው ኢትዮጵያዊነቱን ሊሰርዝ አይችልም፡፡ አሜሪካ ውስጥ “ኢትዮጵያዊነት በግድ ተጫነብኝ፤ እኔ የዚህ ጐሣ ተወላጅ ነኝ” ሲሉ የሚናገሩ አሉ፡፡ ይሄ ምንን ያመለክታል? የወደፊቷን ኢትዮጵያ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ የሚጥል ነው፡፡
ሎሚ፡- በጥብቅና ሞያ በመስራት ላይ ይገኛሉ፤ አሁን ያለውን የፍ/ቤቶች አሰራር እንዴት ያጤኑታል? ቢሮክራሲያዊ አሠራሮችስ ምን ያህል ተንሰራፍተዋል?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- ቢሮክራሲያዊ አሠራሩ በፍርድ ቤት ብቻ ሣይሆን በአጠቃላይ የመንግስት ተቋማት ውስጥ ያለ እንከን ነው፡፡ በርግጥ ዳኞችም በጣም ስራ ይበዛባቸዋል፡፡ ብዙ ክርክሮችና ብዙ ጭቅጭቆች አሉ፡፡ ግን መንግስትን በሚመለከት ጉዳይ (ኢትዮጵያ) ውስጥ ፍትህ አገኛለሁ ማለት ዘበት ነው፡፡ ምናልባት ሁለት ግለሰቦች ተካስሰው ፍትህ ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ የመንግስት እጅ ያለበት ጉዳይ ከሆነ ግን ፍትህ አገኛለሁ ማለት ዘበት ነው፡፡ ሙስና መንሰራፋቱን መንግስት ራሱ ተቀብሎታል፡፡ ከፍተኛ ሙስና ተንሰራፍቷል፡፡ በፍ/ቤት ብቻ ሣይሆን ሀገሪቱንም የወረር ክስተት ነው፡፡ ሙስና እንደ ነቀዝ ኢትዮጵያን እያጠቃ ነው፡፡ ዛሬ ያለገንዘብ ጉዳይህን የሚያይልህ የለም፡፡
ሎሚ፡- ዶ/ር ያዕቆብ እስከመቼ ነው ከየትኛውም የፖለቲካ ፖርቲ ጋር የማይሰሩት? የፖለቲካ አቋማቸውስ ምንድነው;
ዶ/ር ያዕቆብ፡- አንድ ፅኑ እምነት አለኝ፡፡ በፖለቲካ አመራሩ ወጣቶች መተካት አለባቸው፡፡ እኔ ያለሁበት ወይም የነበርኩበት ሁኔታ አክትሟል፤ ማለትም ጊዜው አልፏል፡፡ ሌሎች መረከብ አለባቸው፡፡ አሁን ያለው ትውልድ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት፡፡ እኛ እኮ የተቀረፅነው በማርኪስዝም ሌኒንዝም ነበር፡፡ ዛሬ ማርክሲዝም ሌኒንዝም የትም አይሰራም፡፡ ዛሬ ለዴሞክራሲ የተማሩ፣ ለፍትህ ግንዛቤ ያላቸው ወጣቶት በአመራር ደረጃ መተካት አለባቸው፡፡ ይሄ ደግሞ አማራጭ የሌለው እውነታ ነው፡፡ ብቻችንን ከ40 አመት በላይ ነው በፖለቲካ ውስጥ የቆየነው፡፡ አስታውሳለሁ፤ መሬት ላራሹ ብለን ሰልፍ የወጣነው የዛሬ 43 አመት ነው፡፡ በዛ ጊዜ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ፕሬዚዳንት ነበርኩ፡፡ እስካሁን ድረስ አልተውኩትም፡፡ በአመራር ደረጃ ፖለቲካ በቂዬ ነው፡፡ ኃላፊነት ግን አለብኝ፤ እንደ ኢትዮጵያዊነቴ ይህቺ ሀገር ብዙ ብዙ ዕድል ሰጥታኛለች፡፡ መካስ አለብኝ፡፡ እንደ ኢትዮጵያዊነቴ ለዴሞክራሲና ለፍትህ በሚደረገው እንቅስቃሴ የምችለውን አደርጋለሁ፡፡ ከአንድነት ፓርቲ ጋር ጥሩ ቅርበት አለን፤ ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር ቅርበት አለኝ፡፡ ከመኢአድም ጋር ቅርበት አለኝ፡፡ አንዳንዴም ሲጋብዙኝ ካለኝ ተሞክሮ በመነሣት ንግግር አደርጋለሁ፡፡ ትምህርት ለመስጠት እሞክራለሁ፡፡ አመራሩ ግን በወጣቶች መተካት አለበት፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የምሆነው ፓርቲዎቹ ከተዋሃዱ ብቻ ነው፡፡ ይህን ካደረጉ የአባልነት ቅፅ ለመሙላት ዝግጁ ነኝ፡፡ በዚህ በተከፋፈለ ሁኔታ ግን መቀላቀል አልፈልግም፡፡ በኔ እምነት የተከፈለ ፓርቲ የትም ይደርሳል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ስለዚህ አባል የመሆን ፍላጐት የለኝም፡፡

http://www.zehabesha.com/

posted by Tseday Getachew

 

አዲስ አበባ ሆይ ድምጽሽን አሰሚ ! በአማኑኤል ዘሰላም

 

በደሴ፣ ጎንደር፣ ባህር ዳር፣ ፍቼ፣ አዳማ/ናዝሬት፣ ሮቢ/ባሌ፣ መቀሌ፣ ወላይታ ሶዳ፣ ጂንካ፣ አርባ ምንጭ …ሰላማዊ ሰልፎችና ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል። በአዋሳ፣ ድሬደዋ፣ ወሊሶ፣ አሶሳና ጋምቤላ፣ እቅዱ ዉስጥ የነበሩም ቢሆንም በገንዘብ አቅም ምክንያት ለጊዜዉ ሰልፎች ሊካሄዱ  አልቻሉም።

መስከረም 19 ቀን 2006 ዓ.ም ትኩረቱ አዲስ አበባ ፊንፊኔ ይሆናል። የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት የጀመረዉ የመጀመሪያዉ  ዙር የሶስት ወራት እንቅስቃሴ የሚደመደምበት !

ከአዲስ አበባው ሰልፍ ጋር በተገናኘ፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት  እና የአሁኑ የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶር ነጋሶ ጊዳዳ  በፖሊሶች መታሰራቸዉን የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት በፌስቡኩ  ዘግቧል።

«ፖሊስ የቀድሞውን የኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት አሰረ። የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ፕሬዘዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የታሰሩ የፓርቲውን የቅስቀሳ ቡድን አባላት ለማስፈታት ወደ ጉለሌ ክፍለ ከተማ የሽሮ ሜዳ ፖሊስ ማዘዣ ጣብያ በማምራት ለፖሊሶቹ «ልጆቹ የፈጸሙት ህገ ወጥ ድርጊት የለም፣ ሲቀሰቅሱ የነበሩትም እውቅና የተሰጠውን ሰላማዊ ሰልፍ ነው፡፡ ቅስቀሳው ህገ ወጥ ነው የምትሉም ከሆነ እነርሱን የላኳቸው እኔ በመሆኔ እኔን ልታስሩኝ ትችላላችሁ » ብለዋል፡፡
ፖሊስ የቀድሞውን የኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳን በማሰር ወጣቶቹን ለቅቋቸዋል»

የኢሕአዴግ ፓርቲ በአንድ በኩል እየፈቀደ፣ በሌላ በኩል የፈቀደዉን የሚሽር ተግባራት መፈጸሙ ብዙዎቻችንን  እያስገረመ ነዉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ  የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ፍላጎት እንዳላቸው የሚናገሩ ጥቂቶች አይደሉም። የዉጭ ጉዳይ ሚኒስተሩም ዶር ቴዎድሮስ አዳኖም፣  ድርጅታቸው ኢሕአዴግ ለዴሞክራሲ ግንባታ ቁርጠኝነት እንዳለው ገልጸውም ነበር። ለዚህም ሳይሆን አይቀርም፣ ሰላማዊ ሰልፎች የማድረግ፣ እስረኞችን ያለገደብ የመጠየቅ ፣ የፖለቲካ ክርክሮችን በኢቲቪ የማድረግ የመሳሰሉትን፣  በመለስ ዜናዊ ዘመን ከነበረዉ ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር፣ የተሻሉ ሁኔታዎችን ማየት የጀመርነዉ።

ነገር ግን፣  በጎን፣  የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያምን ዉሳኔ ለማክሸፍ፣ ጠቅላይ ሚኒስተሩ  በሕዝብ እንዲጠሉ፣ ተቀባይነት እንዳይኖራቸው ለማድረግ የሚሰሩ፣ ከበስተጀርባ እየወጓቸው ያሉ፣ ከአቶ ኃይለማሪያም ሳይሆን ከሌላ ቦታ መመሪያ የሚቀበሉ ቡድኖች ያሉ ይመስለኛል። ከበስተጀርባ ሆኖ የሚሰራ ሌላ ሁለተኛ መንግስት ማለት ነዉ …

ጠቅላይ ሚኒስትሩ «ሰልፎች መደረግ አለባቸው። ሕገ መንግስቱ የሚፈቅደዉን ማገድ አንችልም»   የሚል መመሪያ ይሰጣሉ። ነገር ግን በጎን የኦህድድ አክራሪዎች ፣ በባሌ/ሮቢ « ሰልፍ ካደረጋችሁ ደም ይፈሳል» የሚለው አይነት  ዛቻ በመስጠት ሰልፉን አስተጓግለዋል። በመቀሌ ሕወሃቶች « መቀሌን እንኳን አንድነት ቅንጅትም አልደፈራትም» በማለት የመቀሌ ሕዝብ ድምጹን እንዳያሰማ አድርገዋል። በአዲስ አበባ እንዲሁም ሌሎች ቦታዎች፣  የተከበሩ ዶር ነጋሶን ጨምሮ በርካታ የአንድነት አባላትን እና ደጋፊዎች ታስረዋል። በዉስጣዊና ሚስጥራዊ አሰራር፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩን  ዉሳኔ የመቀልበስ እንቅስቃሴ ሲደረግ ነዉ እያየን ያለነው።

እንደዚያም ሆኖ፣ የአንድነት ፓርቲም ሆነ ሰላሳ ሶስቶቹ የመብት ጥያቄን ከማንሳት ወደ ኋላ አላሉም። በከባድ ሁኔታም ትልቅ መስዋእትነት እየከፈሉ ሕዝቡን እያደራጁትና እያንቀሳቀሱት ነዉ። መስክረም 19 የአዲስ አበባና አክባቢዋ ሕዝብ ድምጹን እንዲያሰማ ቅስቀሳ እየተደረገ ነዉ።

እንግዲህ ለአዲስ አበባ ሕዝብ  መልእክት አለኝ። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ፣ የፖለቲካዉን ምህዳር ለመክፈት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በመደገፍ፣ የአንድነት ፓርቲ፣ ሰላም፣ ፍቅር፣  ብሄራዊ እርቅ፣ መቻቻል፣ ነጻነትና እኩልነት እንዲሰፍን፣  የዜጎች ሰብአዊ መብት እንዲከበር  የሚያደርገዉን እንቅስቃሰሴ በመቀላቀል፣ ኢሕአዴግ ዉስጥ ያሉ በሙስናና በጥላቻ የተዘፈቁ፣ ለሕዝብ ንቀት ያላቸው፣ ያላቸዉን ስልጣን ተጠቅመዉ ዜጎችን እያሸበሩ ያሉትን በመቃወም፣ መስከረም 19 ቀን ሰልፍ በመዉጣት ድምጽህን አሰማ።

ለኢሕአዴግ አባላትና ደጋፊዎችም መልእክት አለኝ። ጥያቄዉ የስልጣን ጥያቄ አይደለም። የፍትህ እንጂ። ጉዳዩ ኢሕአዴግን የመጥላት አይደለም። ኢሕአዴግንም ያካተተ ብሄራዊ እርቅ የማምጣትና የፍቅር እንጂ።

የአንድነት ፓርቲ ሰልፍ የጠራው ኢሕአዴግን በመቃወም አይደለም። ሰልፉ ጸረ-ኢሕአዴግ ሰልፍ አይደለም። ሰልፉ የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ፣ ብሄራዊ እርቅ እንዲመጣ፣ የታሰሩ የሕሊና እስረኖች እንዲፈቱ፣ በሽብርተኖች ላይ ሳይሆን በሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠረው የጸረ-ሽብር ሕጉ እንዲሰረዝ አሊያም እንዲሻሻል ፣ የኢኮኖሚ እድገት ጥቂቶችን ብቻ ሳይሆን አብዛኛዉን ሕዝብ ባቀፈ መልኩ እንዲቀጥል..የሚጠይቅ ሰልፍ ነዉ። እነዚህንም ጥያቄዎች አገራችዉን የሚወዱና ልቦና ያላቸው፣ የኢሕአዴግ ደጋፊዎች ይጋሩታል ብዬ አምናለሁ። በመሆኑም የመስክረም 19ኙን ሰልፍ እንዲቀላቀሉ አበረታታለሁ። ይሄ የፖለቲካ ጉዳይ ሳይሆን የአገር ጉዳይ ነዉ። ይሄ ለፓርቲ ታማኝነት የማሳየት ወይንም ያለማሳየት ጉዳይ ሳይሆን አገርን የማዳንና ወደፊት የማስኬድ ጉዳይ ነዉ። ከኢሕአዴግ በፊት ኢትዮጵያ !!!! ከአንድነት ፓርቲ በፊት ኢትዮጵያ !!! ከመኢአድ በፊት ኢትዮጵያ !!!!!

በዉጭ  አገር ላለነዉ ይሄን እላለሁ። ሰሞኑን እንደምንሰማዉ ፣ አንዳንዶች፣ በመላዉ ኢትዮጵያ ሕዝቡ እየተንቀሳቀሰ እያዩ፣ በአዲስ አበባ ሰልፎች እየተደረጉ ባሉበት ወቅት፣ ከየት መጡ ሳይባሉ፣  ትኩረት በማጣታቸው ቀንተዉ ነዉ መሰለኝ፣  «መዳን በኢሳያስ አፈወርቂ ነዉ» እያሉን ነዉ። ከጋንዲ፣ ከማርቲን ሉተር ጊንግ፣ ከነአንሳ ሱንኪ፣ከነጂን ሻርፕ በልጠዉ፣ «ስለሰላማዊ ትግል እኛን አትጠይቁ። ከኛ የበለጠ ስለሰላም ትግል የሚያውቅ የለም። ኢትዮጵያ ዉስጥ ሰላማዊ ትግል አይሰራም » በማለት ሲለፍፉ  እየሰማናቸው ነዉ። መንገዱን ጨርቅ ያርግላቸው እላለሁ።

ነገር ግን ይህ አይነቱ የፖለቲካ መርዝ ፣ ብዙዎችን እየበከለ እንዳለም ታዝቢያለሁ። ይሄን አይነት የጥላቻና የጦረኝነት ፖለቲካን በጭፍን ተቀብልን እያስተጋባን ያለን ጥቂቶች አይደለንም። በዚህ ጉዳይ ላይ ወደፊት ብዙ የምንወያይበት ይሆናል። ለጊዜው ግን በዉጭ አገር ያለኸው ወገኔ፣ ሁሉንም በሚዛን ላይ እንድታስቀምጥ እምክርሃለሁ።

በእዉኑ ተስፋህን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ መጣል ይሻላል ወይንስ፣ የሚገዛዉን ሕዝብ እያሰቃየና እያረዳ ባለ በአንድ የአበደ መሪ ላይ ?  በእዉኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያን ያህል የማይረባ ሆኖ ነዉን ነጻነትና ዲሞርካሲን ከሻእቢያ መጠበቅ የሚገባዉ ? በእዉኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር አመራር አባላት አድራሻቸው ጠፍቶ (ታስረዉና ተገድለዉ) ፣ በኢትዮጵያዊ ፖለቲካ አመለካከታቸው ከበሬታን ያገኙ እንደ ጄነራል ከማል ገልሺና ጀነራል ሃይሉን ጎንፋን የመሳሰሉ ወገኖች ከአገር እንዳይወጡ ታግተዉና ታስረዉ፣ ያለምንም ችግር በቲራቮሎ አስመራር እየተመላለሱ፣ የኢሳያስ አፈወርቂን ታላቅነት የሚሰብኩንን ሰምተን፣ ፊታችንን ሕዝቡ በአሁኑ ወቅት እያደረገ ካለዉ ወሳኝ ትግል ማዞር ይኖርብናልን ? እነዚህ ወገኖች በረጩትስ መርዝ ተስፋ ቆርጠን የአገር ቤቱን ወሳኝ ትግል ከመርዳት መቆጠብ ይግባናልን ? እንግዲህ አገሩን የሚወድ በዉጭ አገር ያለ ኢትዮጵያ ሁሉ እራሱን ይመርምር እላለሁ።

ከሕዝቡ ጎን ቆመናል የምንል ሁሉ የድርሻችህንን እንወጣ። አዲስ አበባ እየደወልን ሕዝቡ ለሰፍ እንዲወጣ እናበረታታ። የሚሊየንም ድምጽ ለነጻነት የተሰኘዉን ንቅናቄ በገንዘባችን እንርዳ። ከዳር ሆነን፣ ወሬ የምንለቃቅም ተመልካቾች አንሁን። የትግሉ አካል፣ ከሚሊዮኖች አንዱ እንሁን !!!!!!!  እኛ ካልተነሳን ማን ? ዛሬ ካልተነሳን መቼ !!!!

አዲስ አበባ ሆይ ድምጽሽን አሰሚ !
አማኑኤል ዘሰላም
amanuelzeselam@gmail.com

መስከረም 15 ቀን 2006 ዓ.ም

http://www.zehabesha.com/

posted by Tseday Getachew

 

 

 

 

Post Navigation

%d bloggers like this: