Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

ግልፅ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ (ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማሪያም)

Amhara Ethnic group members Ethiopia
የቤኒሻንጉል ተፈናቃዮች አሁንም በችግር ላይ ናቸው” (መኢአድና ሠማያዊ ፓርቲ) ከቤኒሻንጉል ክልል ተፈናቅለው ከነበሩት የአማራ ክልል ተወላጆች ጋር በተያያዘ የክልሉን የስራ ሃላፊዎችና መንግስትን ለመክሰስ….. ሰማያዊ ፓርቲና መላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ጥብቅና ያቆሟቸው አለም አቀፍ የህግ ባለሙያው ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማሪያም፤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ግልፅ ደብዳቤ መፃፋቸው ተገለፀ፡፡ ሁለቱ ፓርቲዎች ከትናንት በስቲያ ከሠዓት በኋላ በሠማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት በጋራ በሠጡት መግለጫ፤ ተፈናቃዮቹ አሁንም ችግር ላይ መሆናቸውን፣ ልጆቻቸው ትምህርት ማቋረጣቸውን፤ በሚዲያ እንደሚነገረው ወደ ቀድሞ ኑሯቸው አለመመለሳቸውንና በአጠቃላይ ችግር ላይ መሆናቸውን በማስረጃ በማስደገፍ፣ የጉራፈርዳንና የቤኒሻንጉል ተፈናቃዮችን በማነጋገርና በበርካታ መረጃዎች የተደገፉ ዶክሜንቶችን በማያያዝ ዶ/ር ያዕቆብ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የላኩትን ደብዳቤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ፈርሞ
መቀበሉንም ፓርቲዎቹ ገልፀዋል፡፡
የሠማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት እንደተናገሩት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግሩን በፓርላማ ቀርበው ማመናቸውን፣ ድርጊቱን ፈፅመዋል የተባሉት የክልልና የወረዳ ስራ አስፈፃሚዎች ከስራ መሰናበታቸውን፣ ተፈናቃዮቹ ወደነበሩበት ተመልሠው በሠላም እየኖሩ እንደሆነ የገለፁ ቢሆንም እውነታው ግን ከዚህ በተቃራኒው መሆኑን ዶ/ር ያዕቆብ ከተፈናቃዮች ጋር በመነጋገር ማረጋገጣቸውን ጠቁመው፣ ጉዳዩ ወደ ፍ/ቤት ከመሄዱ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሠጡ ዶ/ር ያዕቆብ ለጠ/ሚኒስትሩ በላኩት ደብዳቤ አስታውቀዋል፡፡ ዶ/ር ያዕቆብ፤ አፋጣኝ ምላሽ ያሻቸዋል ያሏቸውን አራት ዋና ዋና ነጥቦች በደብዳቤያቸው ላይ ያሰፈሩ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ተፈናቃዮቹ
ወደ ቀድሞ ቦታቸው በመንግስት ወጪ ተመልሠው መሬታቸው፣ የንግድ ተቋሞቻቸውና ቤት ንብረታቸው በአስቸኳይ እንዲመለስላቸው፣ ተፈናቃዮቹ ለደረሰባቸው ቁሳዊ ጉዳት፣ አካላዊና ሞራላዊ እንግልት መንግስት ተመጣጣኝ ካሳ እንዲከፍላቸው የሚመለከታቸውን አካላት እንዲያዝዙ፣ በቤኒሻንጉል የሚኖሩ የማንኛውም ብሄር ተወላጆች ተመሳሳይ ወንጀል እንዳይፈፀምባቸው ጥበቃ እንዲደረግላቸው እና ተዋዶና ተፋቅሮ የሚኖረውን ህዝብ በመከፋፈል የማፈናቀል ድርጊት የፈፀሙ የመንግስት ባለስልጣናት ህግ ፊት ቀርበው ቅጣት እንዲያገኙ ውሳኔ እንዲያሳልፉ የሚሉት ነጥቦች ተቀምጠዋል፡፡

መንግስት ወንጀለኞች ያላቸውን የወረዳ ስራ አስፈፃሚዎች ከስራ ማሠናበቱንና ጉዳያቸው በፍ/ቤት እየታዩ ያለ ባለስልጣናት እንዳሉ፣ ተፈናቃዮቹም ወደ ቀድሞ ህይወታቸው ተመልሠዋል እየተባለ ነው የተፈናቃዮቹን ጉዳይ ለምን በተደጋጋሚ ማንሳት ፈለጋችሁ በሚል ከጋዜጠኞች ለተነሳው ጥያቄ “ኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲከኛ ለመሆን በርካታ ምክንያቶች አሉ” ያሉት ኢ/ር ይልቃል፤ ነገር ግን ተፈናቃዮች አሁንም በችግር ላይ ናቸው ቤት ንብረታቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት ተቀራምተውት በክረምት ሜዳ ላይ የወደቁ አሉ፣ በፋሲካ በዓል ቤታቸው የተቃጠለባቸው ተፈናቃዮች አሉ፣ ወደ ቀድሞ ቦታቸው ያልተመለሱትም በርካቶች ናቸው ካሉ በኋላ “ጠበቃችን ዶ/ር ያዕቆብ ይህንን ጉዳይ ከተፈናቃዮቹ በተጨባጭ አረጋግጠዋል” ሲሉም አክለዋል፡፡ የመኢአድ ዋና ፀሀፊ አቶ ተስፋዬ ታሪኩ በበኩላቸው፤ የጉራፈርዳ ተፈናቃዮች በችግር ላይ ለመሆናቸው ጋዜጣዊ መግለጫውን እስከሠጡበት ሰዓት እንኳን መረጃዎች እየደረሷቸው እንደሆነ ገልፀው፣ በጠበቃው ዶ/ር ያዕቆብ በኩል ደብዳቤ መፃፋችን ጉዳዩ በፍ/ቤት እልባት እስኪያገኝ አስቸኳይ መፍትሄ  እንዲሠጣቸው ነው ብለዋል፡፡

ችግሩ መቆም ያልቻለው ከመረጃ እጥረት ይሆናል በሚል ምን ያህል ሰዎች በችግር ላይ እንዳሉ፣ ቤት ንብረታቸውን ቆጥረው የተመዘገቡበት መረጃ ከየምርጫ ጣቢያው የወሠዱትን ካርድ መልሠውና ንብረታቸውን አስመዝግበው እንዲወጡ በሀላፊዎች ፊርማና በመንግስት ማህተም የታዘዙበት ደብዳቤና በርካታ ዶክሜንቶችን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከደብዳቤው ጋር አያይዘው መላካቸውም ተገልጿል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገሪቱ መሪ እንደመሆናቸው ችግሩንም በፓርላማ ቀርበው ማመናቸው እንደ ማስረጃ ተቆጥሮ የአገሪቱ የስራ አስፈፃሚ ከፍተኛ አካል በመሆናቸው ስለሚከሰሱ “መረጃው የለኝም አላየሁም” እንዳይሉ ታስቦ፣ ዶክሜንቱ እንደተላከላቸውም በፓርቲዎቹ ተገልጿል፡፡ ወደ ክስ ከሄዳችሁ ደብዳቤው ለምን አስፈለገ? ጠ/ሚኒስትሩ ምላሽ ከሠጡስ ክሱ ይቆማል ተብሎ ከጋዜጠኞች ለተነሳው ጥያቄ “ችግሮች መፍትሄ ካገኙ ክሱ ቀድሞውኑ ለምን ያስፈልጋል” ያሉት ኢ/ር ይልቃል፤ “መንግስት ይህን ወንጀል የፈፀሙትን አስሬያለሁ ከስራ አሠናብቻለሁ” የሚለው ጉዳዩ አለም አቀፍ ስለሆነበት ውጥረቱን ለማርገብ ነው ብለዋል፡፡ ምላሽ ካላገኛችሁ በትክክል ክስ መቼ ትጀምራላችሁ ለሚለውም፤

ወንጀሉ የይርጋ ጊዜ ስለሌለው ዶ/ር ያዕቆብ ለህክምና ከሄዱበት አሜሪካ ሲመለሱ ይጀመራል፣ በአገር ውስጥ ፍ/ቤት ካልተሳካ ጉዳዩ ወደ አለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች ያመራል ብለዋል – የመኢአድ ዋና ፀሀፊ አቶ ተስፋዬ ታሪኩ፡፡ እስካሁንም በጉራፈርዳ ከሚኖሩ 78ሺህ የአማራ ተወላጆች መካከል 21ሺህ ያህሉ መፈናቀላቸውንና በቤኒሻንጉልም ከአምስት ሺህ በላይ ተፈናቃዮች አፋጣኝ መፍትሔ እንደሚሹ የፓርቲው አመራሮች ተናግረዋል፡፡

http://www.maledatimes.com/

posted by Tseday Getachew

Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: