Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

በአርሲ አንድ አድማ በታኝ ፖሊስ አዛዥ በጩቤ ተወግቶ ተገደለ

 ESAT
 

 

ሐምሌ ፲፱(አስራ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የሻለቃ ማእረግ ያለው ፖሊስ አዛዥ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎቹ ላይ በጩቤ ተወግቶ መገደሉን የደረሰን ዜና ያመለክታል። ግድያውን ተከትሎ ፖሊስ በትናንትናው እለት እና ዛሬ ከፍተኛ ፍተሻ ሲያካሂድ ውሎአል።

የገዳዮቹ ማንነት እስካሁን አልታወቀም። በዛሬው እለት በሻሸመኔ ከወትሮው በተለየ ቁጥር በየቦታው ፍተሻ ሲያኪዱ የታዩት የፌደራል ፖሊሶች፣ ምናልባትም ግድያውን ከሙስሊሞች ጥያቄ ጋር ሊያያይዙት እንደሚችሉ ፍንጮች መታየት መጀመራቸውን ጉዳዩን የሚከታተሉ ወገኖች ለኢሳት  ገልጸዋል።

ከ 27 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ይጠይቃል የተባለ የቴሌኮሙኒኬሽን ማስፋፊያ ሥራ ለቻይና ኩባንያ ተሰጠ።

ሐምሌ ፲፱(አስራ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከስልክ ኔትወርክ ጥራት ጋር በተያያዘ በየጊዜው የሚነሳውን ቅሬታ ይፈታል የተባለ እና 1ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ወይም ከ 27 ቢሊዮን ብር በላይ  ወጪ የጠየቀ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ሥራ ”ሁዋዌ”ለተሰኘው  የቻይና ኩባንያ ትናንት ተሰጠ።

የፕሮጀክቱን ውል ስምምነት ትናንት ማምሻውን ኢትዮ ቴሌኮም  እና የቻይናው ሁዋዌ ኩባንያ ጋር ተፈራርመዋል።

ፊርማውን የኢትዮ ቴሌኮም ተቀዳሚ ስራ አስፈፃሚ አቶ አንዱዓለም አድማሴ ፤ በሁዋዌ በኩል ደግሞ የኩባንያው ስራ አስፈፃሚ ሚስተር ጆኒዱኦን ያስቀመጡ ሲሆን ፥ በአጠቃላይ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ላይም ከሁዋዌ በተጨማሪ የዜድ ቲ ኢ የቴሌኮም ኩባንያም የቴሌን ደህንነት በማስጠበቅ በኩል ተሳታፊ ይሆናል ተብሏል።

የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ  በዋናነት ለጥራት ትኩረት በመስጠቱ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ሲጠናቀቅ አሁን የሚስተዋለውን የኔት ወርክ ጥራት ችግር ይፈታል ተብሎ ተስፋ እንደተጣለበትም   ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል  ተናግረዋል።

የሁዋዌ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሚስተር ጆንዱንግ በበኩላቸው ፥ ፕሮጀክቱን በፍጥነት በማጠናቀቅ የተሻለ የቴሌኮም አገልግሎት በቅርቡ ለማሰረከብ ቃል ገብተዋል።

ይሁንና የቻይናው ህዋዌ ኩባንያ ይህን ያህል ትልቅ ፕሮጀክት-ከ ኢትዮ ቴሌኮም የተረከበው በግልጽ ጨረታ ይሁን አለያም እንደተለመደው እንዲሁ ተሰጥቶት፤አቶ ደብረጽዮን ያሉት ነገር የለም።

ቻይና ለ ኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር እየሰጠች ያለች አገር ነች።

ሁዋዌ የተባለው የቻይና ኩባንያ የአሜሪካን መንግስት ይሰልላል በሚል ክስ ቀርቦበት እንደነበር ይታወቃል። ኩባንያው ለኢትዮጵያ መንግስት የስለላ ሶፍትዌሮችን ሊሰጥ መስማማቱን በቅርቡ መዘገባችን ይታወሳል።

 
 

ፒያሳ የሙስሊም ኢትዮጵያውያንን የተቃውሞ ድምጾች አስተናግዳ ዋለች

ሐምሌ ፲፱(አስራ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ፒያሳ ከሚገኘው ኑር መስጊድ አንስቶ ዙሪያውን ባሉ መንገዶች ላይ ቆሞ የረመዳንን ጁመዓ ስግደት ሲሰግድ  የዋለው ሙስሊሙ ኢትዮጵያዊ ፣ ከአንድ አመት በላይ ሲያሰማው ነበረውን ድምጻችን ይሰማ የሚለውን ተቃውሞ በከፍተኛ ድምጽ በማሰማት የፒያሳን አየር ተቆጣጥሮት ውሎአል።

ድምጻችን ይሰማ፣ የተነጠቅነውን መስጂዶቻችን ለህዝቡ ይመለሱ፣ የተባረሩ ኢማሞች ይመለሱ፣ አሸባሪ አይደለንም፣ ኢማሞቻችን ይፈቱ፣ ጥያቄው ይመለስ፣ ህገ መንግስቱ ይከበር፣ መጅሊሱ አይወክለንም የሚሉትና ሌሎችም ጥያቄዎች ቀርበዋል።

የዛሬው ተቃውሞ ከአንዋር መስጊድ መውጣቱ ብቻ ሳይሆን በተቃውሞው ላይ የታየው የህዝብ ብዛትና የተሰማው ድምጽ ህዝብን ትኩረት ስቦአል።

ተቃውሞው ከአዲስ አበባ ውጭ በተለይም በሻሻመኔ የፌደራል ፖሊሶች  በብዛት በተገኙበት ሁኔታ ተካሂዷል።

መንግስት የሙስሊሙን  ጥያቄ የጥቂቶች ጥያቄ ነው ቢልም በተለያዩ አካባቢዎች በገሀድ የሚታየው እውነታ ይህን የሚያረጋግጥ አልሆነም።

የኢትዮጵያ መንግስት ሙስሊሙ ለሚያቀርበው ጥያቄ እስካሁን ድረስ ተገቢውን መልስ አልሰጠም።

በስፔን የደረሰውን አሰቃቂ የባቡር አደጋ ተከትሎ የባቡሩ ሾፌር በቁጥጥር ስር መዋሉን ቢቢሲ ዘገበ።

ሐምሌ ፲፱(አስራ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአገሪቱ ሰሜናዊ ምዕራብ ከተማ በሆነችው በሳንቲያጎ ደ-ኮምፖስቴላ  ረቡዕ እለት በደረሰው የባቡር አደጋ 78 ሰዎች ሲሞቱ 130 ሰዎች ተጎድተዋል።

ከ130ዎቹ ቁስለኞች መካከል 35 ቀላል እርዳታ ተደርጎላቸው ከሆስፒታል የወጡ ሲሆን ከበድ ያለ ጉዳት የደረሰባቸው 95 ሰዎች በሆስፒታል ህክምና እየተከታተሉ ይገኛሉ።

የባቡሩን ሾፌር ለአደጋው ተጠያቂ ያደረገው የስፔን ፖሊስ ፤አደጋው በሚደርስበት ጊዜ ባቡሩ ከተፈቀደው ፍጥነት ከእጥፍ በላይ እየከነፈ እንደነበር ጠቁሟል።

የመቁሰል አደጋ የደረሰበትና ላደጋው ተጠያቂ የሆነው ሾፌር በአሁኑ ጊዜ በ አጃቢዎች እየተጠበቀ ህክምናውን እየተከታተለ ነው።

ከተጎዱት መካከል 32ቱ ክፉኛ መቁሰላቸውን ያመለከተው ቢቢሲ፤ ከነዚህም ውስጥ ከተለያዩ የ ዓለማችን ክፍሎች የመጡ ዜጎችና ህፃናት ጭምር እንደሚገኙበት ዘግቧል።

አደጋውን ተከትሎ በስፔን መጪዎቹ ሦስት ቀናት ብሔራዊ የሀዘን ጊዜ እንዲሆኑ ታውጇል።

በግብጽ የፕሬዚዳንት ሙርሲ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች የተቃውሞ እና የድጋፍ ሰልፎችን አደረጉ

ሐምሌ ፲፱(አስራ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የፕሬዚዳንት ሙሀመድ ሙርሲ ደጋፊዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት ፕሬዚዳንቱ ወደ ስልጣን እንዲመለሱ ሲጠይቁ ፣ የእርሳቸው ተቃዋሚዎች ደግሞ ፕሬዚዳንቱን ከስልጣን ላወረደው የመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ለመስጠት በታህሪር አደባባይ ተገኝተዋል።

ለፕሬዚዳንቱ ከስልጣን መወገድ ግንባር ቀደም ሚና የተጫወቱት ጄኔራል አብደል ፋታህ ኤል ሲሲ ሰሞኑን ህዝቡ ለወሰዱት እርምጃ ድጋፋቸውን እንዲሰጣቸው ተማጽነው ነበር።

በሌላ በኩል ደግሞ ፕሬዚዳንት ሙሀመድ ሙርሲ ከፍልስጤሙ ተዋጊ ድርጅት ሀማስ ጋር በመተባበር በግብጽ እስር ቤቶች ላይ ጥቃት ለመፈጸም አሲረው ነበር የሚል ክስ እንደሚቀርብባቸው ታውቋል።

አንዳንድ ተቺዎች ግን ክሱ ፕሬዚዳንቱ እንዲፈቱ ከተለያዩ ወገኖች ለሚሰነዘረው ተቃውሞ ሰበብ ነው በማለት አስተያየት ይሰጣሉ።

ግብጽ በፖለቲካው ምክንያት መከፋፈሉዋን ተከትሎ የእርስ በርስ ግጭት ሊፈጠር ይችላል የሚለው ስጋት እያየለ መጥቷል።

ESAT

posted by Tseday Getachew

Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: