Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

ሦስት ዓይነት ኢትዮጵያዊያን

በፋሽስት ጣልያን ወረራ ጊዜና እና በዘመነ ወያኔ

 በታደሰ ብሩ 

1.    መግቢያ

በፋሽስት ጣልያን አምስት ዓመታት የወረራ ዘመን በአገራችን የተፈፀሙ አሳዛኝ ክስተቶች አሁን በወያኔ አገዛዝ እየተደገሙ ነው።  ያኔ ሦስት ዓይነት ኢትዮጵያዊያን ነበሩ፤ ዛሬም ሦስት ዓይነት ኢትዮጵያዊያን አሉ። እነዚህ ሦስት ዓይነት ኢትዮጵያዊያን ከመጠሪያቸው በስተቀር ባህሪያቸው ተመሳሳይ ነው።

በፋሽስት የወረራ ዘመን ተስማምቶ፣ ተመሳሰሎ፣ ተለሳልሶ፣ ተሞዳምዶ መኖር ተበረታታ። በወያኔ የአገዛዝ ዘመን ደግሞ ይህ የአኗኗር ስልት “ልማታዊ” እየተባለ ይሞካሽ ጀመር፤ ሕዝቡ ግን “ወይን ለመኖር” ብሎ  ጠራው። ወይን ለመኖር በከፍተኛ ፍጥነት በመስፋፋቱ ጭቆናንና ጥቃትን እየታገሰ የሚኖር ከፍተኛ መጠን ያለው የኅብረተሰብ ክፍል እየተፈጠረ ነው። ይህ አጅግ አሳሳቢ ጉዳይ ነው።

ምን ነካን? ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ምን ብናድርግ ይበጀናል?  ይህ ጽሁፍ እነዚህ ጥያቄዎች የፈጠሩብኝ ስጋት  ይገልጽልኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። በቂ ባይሆንም ችግሩን መቀነሻ አንድ መንገድ ለማመላከት እሞክራለሁ።

2.   ኢትዮጵያዊያን በጣልያን ወረራ ዘመን

በኢትዮጵያ ምድር የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ተረግጦ የፋሺስት ጣልያን ባንዲራ ከፍ ብሎ የተውለበለቡባቸው  አምስት የመከራና የተጋድሎ ዓመታትን (1928 – 1933) እናስታውስ። በዚያ ጊዜ ሦስት ዓይነት ኢትዮጵያውያን ነበሩ።

2.1.      አርበኞች        እነዚህ ጠላት በድርጅት፣ በትጥቅና ስንቅ እንደሚበልጣቸው እያወቁም ቢሆን በአልበገር ባይነት ሲፋለሙ የቆሙ ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ናቸው። የእነዚህን ወገኖቻችን ተግባር በክብርና በወኔ እናስታውሳለን። “አባቶቻችንና እናቶቻችን” ወይም “ቀደምቶቻችን” ብለን ስንናገር በአብዛኛው በአዕምሮዓችን የሚመጡት እነዚህ ኢትዮጵያዊያን ናቸው። ያኔ ቁጥራቸው ጥቂት የነበረ ቢሆንም እንኳን ፋሽስት ጣልያን ተረጋግቶ “መንግሥት” እንዳይሆን አድርገውታል። ከድል በኋላ ብዙዎቹ በግል የተረሱ ቢሆንም ያኔ እነሱ የነበሩ በመሆናቸው ነው የዛሬው ትውልድ ስለ ቀድሞው የአርነት ተጋድሎ ታሪክ ደረቱን ነፍቶ ለመናገር የሚደፍረው። እነሱ በመኖራቸው ነው እኔም “የቅኝ ግዛት ዘመን” ሳይሆን “የወረራ ዘመን” ብዬ ስለዚያን ጊዜ የምጽፈው።

2.2.     ተሸናፊዎች      እነዚህ መሸነፋቸውን ተቀብለው እየተቆጩና እያጉረመረሙ አንገታቸውን ደፍተው የተቀመጡ ኢትዮጵያዊያን ናቸው። እነዚህ ኢትዮጵያዊያን የሚወዷት ኢትዮጵያ መደፈሯ ይቆጫቸዋል፤ በባዕድ መገዛታቸው ያንገበግባቸዋል። ግና “ቀን አስኪያልፍ ያባትህ ባርያ ይግዛህ” በማለት ራሳቸው እየሸነገሉ “ጊዜ ያመጣውን ጊዜ እስኪመልሰው”  በፍርሀትና በተስፋ ሲጠባበቁ ቆይተዋል። በዚህ መደብ ውስጥ የነበሩ ኢትዮጵያዊንን ያልነበሩ ያህል ልንረሳቸው እንሞክራለን። በወቅቱ ግን ከፍተኛው ቁጥር የያዘው ኢትዮጵያዊ በዚህ መደብ ውስጥ እንደነበር መገመት ይቻላል።

2.3.     ባንዳዎች        እነዚህ “የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ” እያሉ ለጊዜዓዊ ጥቅሞች ከበዳዬች ጋር ሆነው በወገኖቻቸው ላይ በደልን የፈፀሙና ያስፈፀሙ ኢትዮጵያዊያን ናቸው። እነዚህ ከጠላት ባላነሰ (አንዳንዴም በከፋ) ጭካኔ አርበኞችን ወግተዋል። የእነዚህ ታሪክ የምናፍርበት ሲሆን መጠሪያቸውንም –  “ባንዳ” –  መሰዳደቢያ አድርገነዋል።

በጠላት ዘመን በሁለተኛውና በሶሰተኛው ቡድን የተሰለፉት ኢትዮጵያዊያን ቁጥር አሳንሶ “ጥቂት” ተብሎ የሚታለፍ እንዳልነበር የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ። ተራው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የንጉሠ ነገሥቱ ሥልጣን ቀጥታ ተጠቃሚ የነበሩ በርካታ ሹማምንትም መሸነፋቸውን ተቀብለው አንገታቸውን ደፍተው ለጣሊያን ተገዝተዋል።  በፕሮፌሰር አልቤርቶ ስባኪ (1985) ተጽፎ በእምሻው ዓለማየሁ (2002) የተተረጎመው “ኢትዮጵያ በኢጣልያ ፋሽስቶች የወረራ ዓመታት (1928 -1933)” በተሰኘው መጽሐፍ ከፍተኛ ዝና የነበራቸው ኢትዮጵያዊያን መኳንንትና ሹማምንት ለዝምታቸው ብቻ በጣልያን መንግሥት የጉርሻ ደመወዝ ይቆረጥላቸው እንደነበር ያጋልጣል። ስሞቻቸውና በየወሩ ይከፈላቸው የነበረው የገንዘብ መጠንም ተገልጿል። ከእነዚህ ውስጥ በልባቸው የኢትዮጵያን ነፃነት ይናፍቁ የነበሩት በርካታ እንደነበሩ መገመት ቀላል ነው። ሆኖም ግን ተደብቆ በመፀለይና ድምጽ አጥፍቶ በማጉረምረም ካልሆነ በስተቀር ይኸ በቁጥር ብዙ የሆነው ኢትዮጵያዊ ለአርነት ትግሉ ይህ ነው የሚባል አስተዋጽዖ አድርጓል ማለት ያዳግታል[1]

በቅስቀሳው ዘርፍ የተሰለፉ ባንዳዎች የጣልያን መንግሥት በመንገድ ሥራ፣ በትምህርትና በጤና አገልግሎት ኢትዮጵያን ለማሳደግ የመጣ  “ልማታዊ መንግሥት”  እንደሆነ ሰብከዋል። አንዳንድ ባንዶች እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ስለሚወድ የጣልያን ፋሺስት መንግሥትን ላከላት እያሉ ቀስቅሰዋል።  ባንዳዎች የጣልያን መንግሥትን ገናናነትና አይበገሬነት እያጋነኑ በማቅረብ በሕዝብ ልብ ውስጥ ፍርሀትና ሽብር ነዝተዋል። ከጠላት ጦር ጋር ተሰልፈው አርበኞችን ወግተዋል።ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ “የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983” (2001)  በተሰኘው መጽሐፋቸው አያሌ ኢትዮጵያውያን በግል ጥቅም ተታለው ወይም “ራስክን አድን” በሚለው መርህ የኢጣልያን ባንዳ ሆነው እንደነበር ጽፈዋል። ከዚህም በተጨማሪ ባንዳዎቹ ውስጠ “ዐዋቂ በመሆናቸውም በአርነት ትግሉ ላይ የኢጣልያ ሠራዊት ካደረሰው የበለጠ ጉዳት አድርሰዋል” ብለዋል።

በፕሮፌሰር አልቤርቶ ስባኪ መጽሐፍ ላይ እንደተብራራው የአገርና የክብር ጉዳይ እየተረሳ “እኔ ከእከሌ ያነስ እንዴት ይከፈለኛል?” በሚል በኢትዮጵያዊያው ተሸናፊ ሹማምንት መካከል የነበረው ከፍተኛ ሽኩቻ ራሱን የቻለ ፓለቲካ ሆኖ ነበር።  በዚህ ሁሉ ምክንያት አርበኞች እየተዳከሙ፤ ድል እየራቀ መጣ። ዓለም ዓቀፍ ሁኔታዎች ባይቀየሩ እና የእንግሊዝ ድጋፍ ባይገኝ ኖሮ ወረራው ወደ ተረጋጋ ቅኝ ግዛት ተቀይሮ የኢትዮጵያ የውርደት ዘመን የተራዘመ ይሆን ነበር።

3.   ኢትዮጵያዊያን በወያኔ አገዛዝ

በዛሬዋ ኢትዮጵያ የወያኔ አገዛዝና እና በፋሽስት ጣልያን የወራሪ አገዛዝ መካከል አስደንጋጭ ተመሳሳይነት አለ። እርግጥ ነው ወራሪው ፋሺስት ጣልያን ባህር አቋርጦ የመጣ ሲሆን ወያኔ ግን አገር በቀል ነው። የጣልያን ወራሪዎች የቆዳቸው ቀለም፣ የሚናገሩት ቋንቋ፣ የሚበሉትና የሚለብሱት ለአገሬው ባዕድ ነበር፤ ወያኔ ግን በቆዳ ቀለምም፣ በቋንቋም፣ በባህል እጅግም የሚለይበት የለም። ይሁን እንጂ በአገዛዝ ባህርይ አንፃር ከታየ ወያኔ ከፋሺስት ጣልያን ይብስ እንደሆን እንጂ አያንስም።

ወያኔን እፋሽስት ጣልያን ቦታ ላይ ስናስቀምጠው ሶስቱ ዓይነቶቹ ኢትዮጵያዊያን ዛሬም ጎልተው ይታያሉ።

  1. በተቻላቸው አቅም ሁሉ ወያኔን እየታገሉ ያሉ የነፃነት ታጋዮች፣
  2. በወያኔ እየተማረሩም ቢሆን “ቀን ያልፋል” እያሉ ኑሮዓቸውን የሚገፉ “ዝምተኞች[2]”፣ እና
  3. ከወያኔ በላይ ወያኔ ሆነው ዘርፈው የሚያዘርፉ፤ ገርፈው የሚያስገርፉ፤ አዳዲስ ወያኔዎች

3.1. የነፃነት ታጋዮች

ጥቂቶች ቢሆኑም ለወያኔ አንበረከክም ያሉ፤ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል የቆረጡ የነፃነት ታጋዮች አሉ። እርግጥ ነው ከወያኔ ጋር ሲነፃፀር በድርጅት፣ በትጥቅና ስንቅ ረገድ ደካሞች ናቸው። ሆኖም ግን ወያኔን በጽናት እየታገሉት ነው። የወያኔ እስር ቤቶች በነፃነት ታጋዮች ተሞልተው ፋሽስት ጣልያን ከፈፀመው የባሰ ሰቆቃ እየተፈፀመባቸው ነው። ከፊሎች የነፃነት ታጋዮች በከተሞች ጥቂቶቹ በበረሀና በተራራዎች አናት ላይ ይገኛሉ። ገሚሱ የዚህ ቡድን አባላት ከአገር ተሰደው በመላ ዓለም ተበትነዋል።

በዚሁ ቡድን አባላት መካከል ስምምነት የለም። በዚህም ምክንያት ዝምተኞቹ አምርረው ይተቿቸዋል፤ ነባሮችም አዳዲሶቹም ወያኔዎች ደግሞ ይሳለቁባቸዋል።

በነፃነት ታጋዮች መካከል ስምምነት አለመኖሩ አዲስ ነገር ይምሰለን እንጂ በፋሺስት ወረራ ጊዜም እንደዚሁ ነበር። ባህሩ ዘውዴ እንዲህ ይላሉ

ለነፃነት ለመታገል በቆረጡት መሀልም ቢሆን ብዙውን ጊዜ ከኅብረት ይልቅ ልዩነት ነበር የሚታየው፡፡ በአያሌ የሽምቅ ተዋጊ ቡድኖች መካከል የሰፈነው ስሜት የጎጠኝነትና የእርስ በርስ መፎካከር ነበር፡፡  የአንድ ጓድ አባላት አፈንግጠው ከሌላው መቀላቀል፣ ይህም የሚያስከትለው የአንዱ ማበጥና የሌላው መኰስመን ግንኙነቶችን ለማቃቃር ረድቶ ነበር፡፡ ስለሆነም አርበኞቹ ብዙ ጊዜ ጠላትን አብረው ከመውጋት ይልቅ እርስ በርስ መፋጀቱን ነበር የተያያዙት፡፡ ለዚህም ሁኔታ በምሳሌነት መጥቀስ የሚቻለው በጎጃም በደጃች መንገሻ ጀምበሬና በደጃች ነጋሽ በዛብህ መካከል፣ እንዲሁም በልጅ ኃይሉ በለውና በልጅ በላይ ዘለቀ መካከል የነበረውን ችግር ነው፡፡ በአርበኞቹ መካከል ኅብረት ለመፍጠር ያዳገተው የሚጋሩት ርዕዮትና የፖለቲካ ድርጅት ቀርቶ ሁሉም መሪያችን ብሎ የሚመለከተው አንድ ሰው ባለመኖሩ ነው፡፡

ይህ ከዛሬው ሀቅ ጋር ያለው መመሳሰል አይገርምም?

አዎ ዛሬም እንደ ድሮው ሁሉ የነፃነት ታጋዮች በብዙ በኩል እየተወጉ ነው። በግንባር ወያኔ፤ “ዝምተኛው” ደግሞ ከጀርባው ይወጋቸዋል። እርስ በርሳቸውም ይጎነታተላሉ።

3.2.        ዝምተኞች

ዝምተኞች ራሳቸውን ጭምቶች አድርገው ይቆጥራሉ። “ጊዜ ያመጣውን” ጊዜ እንደሚመልሰው እርግጠኛ በመሆን የዕለት ለዕለት ሥራቸውን እየሠሩ የድል ብሥራትን  ይጠባበቃሉ።

ዝምተኞች እንደ ስማቸው ነገሮችን በዝምታ የሚያሳልፉ አይደሉም። ለተግባሮቻቸው አሳማኝ ምክንያቶች ፍለጋ አሰልቺ ክርክር ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። ለምሳሌ ወያኔን “ጠጋ ብሎ መቦጨቅ” መበረታታት ያለበት ብልጠት እንደሆነ አድርገው በወኔ ሲከራከሩ ልታገኟቸው ትችላላችሁ። የነፃነት ትግሉን መቀላቀል ያልቻሉት “የረባ ሰው ባለመኖሩ” እንደሆነ “በቁጭት” ሲከራከሩ ማግኘት ቀላል ነው።

ዝምተኞች ከፍተኛው የማኅበረሰብ ክፍል ይይዛሉ።  የነፃነት ታጋዮችም ወያኔዎችም ዝመተኞቹን ወደ ራሳቸው ለመሳብ ጥረት የሚያደርጉ በመሆኑ ዝምተኞቹ ራሳቸው የትግል ሜዳ ናቸው።

“ዝምተኝነት” ሲበዛ የኑሮ ዘይቤ ይሆናል፤ ይህም የከፋ የማኅበረሰብ ችግር ይፈጥራል። የዛሬይቷ ኢትዮጵያ ዝምተኞች እየገነቡት ያለው የኑሮ ዘይቤ “ወይን ለመኖር” የሚል ስላቃዊ መጠሪያ ተሰጥቶታል።

3.3.        አዳዲስ ወያኔዎች

ነባሮቹ ወያኔዎች ትግራይን ነፃ ለማውጣት በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ሕዝብ ትግራይ (ሕወሓት) የተደራጁ፤ ከመጀመሪያው የትግራይ  እንጂ የኢትዮጵያ አጀንዳ ያልነበራቸው ሰዎች ናቸው። ትግራይን ነፃ ለማውጣት ተነሱ፣ ታገሉ፤ ተሳካላቸው። ትግራይን ለብቻው የማስተዳደር ፈተና ለአጭር ጊዜም ቢሆን ቀምሰውታል። የቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት ነባሮቹ ወያኔዎች ሲነሱ ከተመኙት በላይ በላይ ግዛት ለማግኘት የሚያስችል ሁኔታ ፈጠረላቸው። እናም ኢትዮጵያን ተቆጣጠሩ።  ለእነሱ ኢትዮጵያ ተዋግተው ያስገበሯት ግዛት ነች። ስለዚህም ባህሪያቸው የቅኝ ገዢ ዓይነት ቢሆን ሊገርመን አይገባም።

ጣልያን ኢትዮጵያን በምስለኔዎች አማካይነት ቢገዛም፤ ባንዳንዎችን በአንዳንድ የሥልጣን ቦታ ላይ ቢሾምም ከኢትዮጵያዊያን መካከል ጣልያንን አልፈጠረም። ለዚህ የሚያበቃ ጊዜ አልነበረውም፤ የባህልና የቆዳ ቀለም ልዩነቱም ትልቅ መሰናክል ሆኖበታል። በአንፃሩ ግን ወያኔ ከራሱ የባሱ ወያኔዎችን ከሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች መፍጠር ችሏል። እነዚህን ነው “አዳዲስ ወያኔዎች” የሚል መጠሪያ የሰጠኋቸው።

በነባሮቹ ወያኔዎች እና በአዲሶቹ ወያኔዎች መካከል ጉልህ ልዩነቶች አሉ። አንኳር አንኳር ልዩነቶችን ከቀላል ወደ ከባድ እንዘርዝራቸው:

  • ነባሮቹ ወያኔዎች “ወያኔ” ተብሎ መጠራት ያስደስታቸዋል እንጂ አያበሳጫቸውም፤ ራሳቸውንም ወያኔ እያሉ ነው የሚጠሩት።  አዲሶቹ ወያኔዎች ግን “ወያኔ” መባል ያሳብዳቸዋል።
  • ነባር ወያኔዎች ትግራይ የምትባል አገር ያላቸው መሆኑ የሚሰጣቸው የልብ ልብ አለ። ችግር ቢያጋጥም ማፈግፈጊያ ያላቸው መስሎ ይሰማቸዋል። አዲሶቹ ወያኔዎች ግን ማፈግፈጊያም ቀርቶ መንጠላጠያ የሌላቸው በመሆኑ ተስፋቸው ያለው በነባሮቹ ወያኔዎች ነው።
  • ነባር ወያኔዎች ቢያንስ በመጠቡት አካባቢ ሕዝብ በቀና የሚታዩ መስሎ ይሰማቸዋል። አዲሶቹ ወያኔዎች ግን እንኳን በመጡበት ማኅበረሰብ በወጡበት ቤተሰብም የተናቁና የተወገዙ መስሎ ስለሚሰማቸው ክፍተኛ የስነሥልቦና ስብራት ውስጥ ያሉ ናቸው።
  • አዲሶቹን ወያኔዎች ከቀድሞዎቹ የባሱ ተናዳፊዎች፣ ተሳዳቢዎች፣ ዋሾዎችና ሙሰኞች ናቸው።

4.     “ወይን ለመኖር” እንደ ኑሮ ዘይቤ

“ወይን ለመኖር” ጥቂት ጥቅሞችን ለማግኘት ወይም ጉዳቶችን ለመቀነስ ሲባል የወያኔ ወዳጅ ሆኖ የመቅረብ የአኗኗር ዘይቤ ነው። ከልብ ሳይታመንበት ወይም ግልጽ የሆነ ጫናም ሳይኖር ጥቃቅን ጥቅሞችን ለማግኘት ወይም ጉዳትን ለመቀነስ ሲባል ወዶና ፈቅዶ  የወያኔ ድርጅቶች አባል መሆን የወይን ለኑሮ ዓይነተኛ መግለጫ  ነው።

ዝምተኛ በተባለው ምድብ ውስጥ ካሉት ኢትዮጵያዊያን ውስጥ በርከት ያሉት “ወይን ለመኖርን” እንደ “ኑሮ በዘዴ” ስልት ይጠቀሙበታል። በዚህም ምክንያት በነፃነት ትግሉና በአገራችን የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ ከፍተኛ አደጋ እያንዣበበ  ነው።

ገበሬዎች የእርሻ መሬታቸው እንዳይነጠቅባቸው ለመከላከል፤ የግብርና ባለሙያዎች የምክር እገዛ ለማግኘት፤ የማዳበሪያና ዘር መግዣ ብድር ወይም እርዳታ ለማግኘት የአባልነት ፎርም ይሞላሉ። በከተሞች ውስጥም ሥራ ለመቀጠር፣ ለደረጃ እድገት፣ የከፍተኛ ትምህርት እድል ለማግኘት ከወያኔ ድርጅቶች የአንዱ አባል መሆን አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ ነው:: በንግዱም ዘርፍ የሥራ ቦታ ለማግኘት፣ የመንግሥት ጨረታዎችን ለማሸነፍ፣ የባንክ ብድር ለማግኝት፣ ከጉምሩክ እቃ ለማስለቀቅ፣ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት በአባልነት መታቀፍ ወሳኝ ነው። በዚህም ምክንያት የወያኑ ድርጅቶች ከሁሉም የሥራ መስክ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ኢትዮጵያዊ በአባልነት ሰብስበዋል። እነዚህ ኢትዮጵያዊያን በልባቸው የወያኔ እድሜ ማጠርን እየተመኙ በተግባር ግን የወያኔን እድሜ ያራዝማሉ።

በውጭ አገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ውስጥም ቁራጭ መሬት ለማግኘት፤ ያለሰቀቀን ኢትዮጵያ ደርሶ ለመመለስ፤ ኮንዶሚኒየም ቤት ለመግዛት፤ “ልማታዊ ባለሀብት” ተብሎ  ለመኮፈስ …  ወዘተ.  ወያኔን ይወዳጃሉ።

“ወይን ለመኖር” ለወያኔ የልብ ወዳጅ አያበዛለትም፤ ሆኖም ግን በጣም ይጠቅመዋል። ልክ ጣልያን ሹማምንቱን ደመወዝ እየከፈለ ዝም እንዳሰኛቸው ወያኔም በአባልነትና በጥቅማ ጥቅም እየደለለ ተቃዉሞ ያለዝባል።  “ወይን ለመኖር” ለወያኔ ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች ውስጥ የሚከተሉት ዋነኛዎቹ ናቸው።

4.1.       ሁሉን ጠቅላይ አገዛዝን ማስፈን

በርካታ ሕዝብን በድርጅት አባልነት ወይም ደጋፊነት ስም በመዋቅር ማስገባት ለቁጥጥር ያመቻል። በወያኔ መዋቀር ውስጥ የገባ ሰው ነፃነቱን አጥቷል። የወያኔ የድርጅት መዋቅር በመሠረቱ የስለላ መዋቀር ነው፤ ዋነኛው ተልዕኮው  የማኅበረሰብን ስነልቦና መስበር ነው። “በወይን ለኑሮ” የታቀፉ ዜጎች የወያኔንን ኃይል በመጠን በላይ አግዝፈው፤ የራሳቸውን ደግሞ አንኳሰው ይመለከታሉ።  “መንግሥት እያንዳንዱን ነገር አብጠርጥሮ ያውቃል” በሚል የፍራቻ ቆፈን ተይዘው እንኳንስ በተግባር መቃወም ስለወያኔ ክፉ ማሰብን እንኳን እንዲፈሩ ያደርጋቸዋል።

“በወይን ለኑሮ” አማካይነት ብዙ ሰው በወያኔ መዋቅር መያዙ ሕዝብ ልብ ውስጥ የዘራው ፍርሃት ወያኔ የሌለው ጉልበት ያለው መስሎ  እንዲታይ አድርጓል።

4.2.     “እንድዘርፍ አግዘኝ፤ አለበዚያ ግን አጠፋሃለሁ”

ወያኔ ኢትዮጵያን በመጥላት ያደጉ ግለሰቦች ቡድን ነው። እነዚህ ግለሰቦች ሲዘርፉም ሆነ ሲዋሹ ለከት የላቸውም። ወያኔ የሚያካሂደው መጠነ ሰፊ ዝርፊያ ያለ ብዙ ኢትዮጵያዊያን ትብብር በጥቂት የወያኔ ግንባር ቀደም አባላት ብቻ ሊከናወን ፈጽሞ ባልቻለም ነበር። እናም ለኑሮ ብሎ ወያኔን የተቀላቀለ ከሚከተሉት ቢያንስ በአንዱ መንገድ መተባበሩ አይቀርም።

4.2.1.  በዝርፊያ መተባበር

ኢትዮጵያዊያን ለትናንሽ ጥቅሞች ብለው የወያኔ አባል ወይም ደጋፊ በሆኑ መጠን ወያኔ የዝርፊያውን አድማስ ያሰፋል።  በትንሹ እንኳን የጥቅም ተካፋይ የሆነ ሰው ትልቁን ዘረፋ የመቃወም ድፍረት ያጣል። በዚህ የተበረታታው የወያኔ ዘረፋ እየሰፋ መጥቶ እነሆ የእርሻ መሬቶችን ለባእዳን እስከ መሸጥ ደርሷል።

አንድ ኢትዮጵያዊ በወያኔ አባልነቱ የሚያገኘው ጥቅም ራሱን ለባርነት የሸጠበት ዋጋ አድርጎ ቢያየው ይመረጣል።

4.2.2.     በዝምታ መተባበር 

ፍርሃት በፈጠረው የአቅመ ቢስነት ስሜት ወይም ከዚህ በፊት የተደረጉት ጥረቶች ባለመሳካታቸው ሳቢያ የተፈጠረው ደንታ ቢስነት ለወይን ለኑሮ መስፋፋት ተጨማሪ ምክንያቶች ሆነዋል። “ፓለቲካ አያገባኝም” ማለት ወያኔን ከመደገፍ ያልተናነሰ ተግባር ነው።

4.2.3.     ፊውዳላዊ  መኮፈስ

ግብር ማብላት የኢትዮጵያ ፊውዳል ባህል ነው። ሀዲስ ዓለማየሁ “በፍቅር እስከ መቃብር” በበዛብህ አንደበት እንደተናገሩት የመኳንንት ግብር ግብዣ ሳይሆን ሰው ለቁራጭ እንጀራ ራሱን አዋርዶ፣ ተገፍትሮ፣ ተደብድቦ፣ የማይበላ በልቶ ተገዢነቱን በተግባር የሚገለጽበት፤ መኳንንቱም ይህንን እያዩ የሚደሰቱበት ሥርዓት ነው።

ወያኔ ይህንን የቆየ የፊውዳል ባህል አዲስ ቀለም ሰጥቶታል። የወያኔ አባል ወይም ደጋፊ በመሆን ለሚገኝ ትንሽ ጥቅም ብዙዎች ክብራቸውን አሳልፈው ሲሰጡ፤ በየግምገማው ስድብን እንደ ምርቃት ሲቀበሉ የወያኔ መኳንንት ሃሴትን ያደርጋሉ፤ “ተራሮችን ስላንቀጠቀጠው” ትግላቸው በየጊዜው አዳዲስ ነገር እየጨማመሩበት ይደሰኩራሉ።

5.     ከዚህ ትንተና ምን ቁም-ነገር እናገኛለን?

አንባቢ “በማንኛውም ሥርዓት ውስጥ ጥቂት ደጋፊዎች፣ ጥቂት ተቃዋሚዎች እና በርካታ ‘መሀል ሰፋሪዎች’ መኖራቸው የተለመደ  በመሆኑ ምን አዲስ ነገር ተገኘ?” ሊል እንደሚችል እገምታለሁ።

ልዩነት አለው። በዚህ ጽሁፍ ትኩረት የተሰጠው ክፍል ዝም ብሎ መሀል ሰፋሪ አይደለም። መሀል ሰፋሪ አቋሙ ዋዣቂ ነው። እዚህ የምንነጋገረው ግን ጠንካራ አቋም ይዞ በተግባር ግን ተቃራኒውን ስለሚፈጽመው ሰዉ ነው። በጣልያን ወረራ ጊዜ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ትራሳቸው ውስጥ አድረገው ሲተኙና ሲነሱ እየተሳለሙ በአደባባይ ግን ለጣልያን ባንዲራ ሰላምታ ይሰጡ ስለነበሩ ሰዎች ነው። ለእነዚህ ሰዎች ስለ አገር ፍቅር ማስተማር እጅግም ዋጋ የለውም። በአገር ፍቅር ዘወትር እየነደዱ ነበር፤ ሆኖም ግን ራሳቸውን ሆነው እየኖሩ አልነበረም።

አሁንም ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። በወያኔ ፋሽስታዊ አገዛዝ ውስጣቸው እያረረ በተግባር ግን እያገለገሉት ያሉ ሰዎች አሉ። እንዲህ ዓይነት ሰዎች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። ይህ የነፃነት ትግሉን እየጎዳው መሆኑ ገሀድ ነው። ሆኖም ጉዳቱ ከዚህም ይሰፋል። እንዲህ ዓይነት ሰዎች በእርግጥ ሰዎች ናቸውን? “ሰው” የሚያሰኛቸውን ህሊናቸውን ለጥቅም አሳለፈው ከሰጡ በኋላ ምንድነው የተረፋቸው? በእንዲህ ዓይነት ሰዎች የምትገነባ አገር ምን ትመስላለች?

6.  ምን ይደረግ?

ከሁሉ አስቀድሞ እኛ የምናልማት ኢትዮጵያ ጥቅማቸውን ለማብዛት፤ ወይም ጉዳትን ለመቀነስ (ማለትም በፍርሃት ምክንያት) ሲሉ ነፃነታቸውን አሳልፈው በሚሰጡ ሰዎች መገንባት እንደማትችል መተማመን ይኖርብናል። ዝምተኞች ከአዳዲሶቹ ወያኔዎች ባላነሰ የነፃነት ትግሉን እየጎዱት መሆኑም ግልጽ ሊሆን ይገባል። ነገር ግን በውስጣቸው ባለው እምነት ምክንያት ከወያኔዎች ይለያሉ። እነዚህ ሰዎች የነፃነት ትግሉን በከፍተኛ እየጎዱት ቢሆንም እንኳን በተለየ ስልት ማቅረብ ይገባል።

በፋሽስት ወረራ ወቅት ስመ ጥር ከነበሩት አርበኞች አንዱ ደጃዝማች ታከለ ወልደሐዋሪያት ናቸው። የሌሎች የአርበኛ መሪዎች ሠራዊት እየተመናመነ  በሄደበት ጊዜ እንኳን የደጃዝማች ታከለ ጦር እየደረጀ ነበር ይባላል። ብዙዎች የአርበኛ መሪዎች ፈሪዎችን አይታገሱም ነበር። ደጃዝማች ታከለ ግን “እኔም እኮ እፈራለሁ፤ ግን ተፈርቶ የት ይገባል” ይሉ ነበር ይባላል። በዚህም ምክንያት “የፈሪ ባላ” በመባልም ይታወቁ ነበር። ልባቸው ያልጠነከረ አርበኞች ፊታውራሪ ታከለን መከተል ይመርጡ ነበር፤ ከሌሎች አዝማቾችም እየፈለሱ ገቡላቸው። ደጃዝማች ታከለ ከፈሪዎች ጀግኖችን ያወጡ ጀግና ናቸው።

የደጃዝማች ታከለን አርዓያነት መከተል አንዱ መፍትሔ ሊሆን ይችላል። በወይን ለመኖር የሄድብንን አሊያም ሊሄድብን ያኮበኮበበን ሠራዊት መመለስ የሥራችን አንድ አካል ማድረግ ይገባናል።

ይህ በተግባር ምን ማለት ነው?

ለምሳሌ ወዳጃችን ለኮንዶሚኒየም ቤት በመመዝገቡ የስድብ መዓት ከማውረድ “አገራችን ውስጥ ቤት ቢኖረው ማን ይጠላል፤ ዋስትናው የለም እንጂ፤  የተገደሉ ዜጎች፤ የተፈናቀሉ ድሆች ዋይታ እረፍት ይነሳል እንጂ”;;  “በገዛ አገር ኢንቬስት ማድረግ ማን ይጠላል፤ አገር የለምን እንጂ”፤ “መሬት ቢገኝ ማን ይጠላል፤ ዋስትናው የለን እንጂ”፤ “ምቾችን ማን ይጠላል፤ ወቃሽ ህሊና አለ እንጂ” እንበላቸው።የዛሬው ዝምታ ከጣልያን ጊዜው ተሸናፊነት ጋር መሳ መሆኑን እናስታውሳቸው።

ደጃዝማች ታከለ ወልደሐዋሪያት ከፈሪዎች ጀግኖች ማውጣትን እንደቻሉ እኛም ከዝምተኞች ትንታግ የነፃነት አርበኖች ማውጣትን እንልመድ::

አስተያየት መስጠት ከፈለጉ: tkersmo@gmail.com

http://ecadforum.com

posted by Tseday Getachew

 

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: