Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

ዋይታ በደቡብ ነግሷል የብሄር ጥያቄ ተመልሷል በተባለ ማግስት ጥያቄው አገረሸ

በደቡብ ክልላዊ መንግስት ጋሞጎፋ ዞን የምትገኘው ቁጫ ወረዳ ሰላም በር ከተማና አካባቢዋ ላለፉት ሁለት ቀናት በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ስትታመስ መቆየቷን የፍኖተ ነጻነት ምንጮች ከስፋራው አጋልጠዋል፡፡

እንደ ምንጮቻችን ዘገባ በቁጫ ወረዳ የሚገኙ ከ200.000የሚልቁ ነዋሪዎች ያለ ፍላጎታቸው በጋሞጎፋ እንዲጠቃለሉ መደረጋቸውን ሲቃወሙ ቆይተዋል፡፡‹‹እኛ ጋሞ ወይም ወላይታ አይደለንም››በማለት የማንነት ጥያቄ ያነሱት ቁጫዎች የራሳችን ቋንቋና ከጋሞም ሆነ ከወላይታ የሚለየን ባህል ያለን በመሆኑ ልጆቻችን በራሳችን ቋንቋ እንዲማሩ ይደረግ በማለት የማንነት ጥያቄ ሲያነሱ አመታት ተቆጥረዋል፡፡

የደቡብ ተወላጅ የሆኑት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን መንበር ከተረከቡ በኋላ በመለስ አስተዳደር ምላሽ ያላገኘው ጥያቄያቸው መልስ ሊያገኝ እንደሚችል ተስፋ በማድረግ ሽማግሌዎችን በመምረጥ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰድደዋል፡፡አዲስ አበባ የመጡት መልእክተኞች ጥያቄያቸው በፌዴሬሽን ምክር ቤት አማካኝነት ምላሽ እንደሚያገኝ ተስፋ ተገብቶላቸው ወደ መጡበት እንዲመለሱ ቢደረጉም መኖሪያ ቀዬአቸው ከደረሱ በኋላ ለእስር መዳረጋቸው የአካባቢውን ማህበረሰብ አስቆጥቷል፡፡

ፖሊስ ሽማግሌዎቹን በማሰር ሳይቆጠብ ቅዳሜ ምሽት ሌሎች ሰዎችን ከየቤታቸው በመለቃቀም ለእስር ዳርጓል፡፡ለፍኖተ ነጻነት በደረሰ መረጃ መሰረት ለእስር የተዳረጉ ሰዎች 15 የሚደርሱ ሲሆን ሙሉ ስማቸው የታወቀው ግን የአስሩ ብቻ ነው፡፡

1ኛ. አቶ ደፋሩ ዶሬ (የፋይናንስ ቢሮ ኦፊሰር)

2ኛ. አቶ ሻምበል ሻዋ (የፋይናንስ ቢሮ የሰው ኃይል ሥራ ሂደት ባለቤት)

3ኛ. አቶ አማኑኤል ጎቶሮ (የፋይናንስ ቢሮ ኦፊሰር)

4ኛ. አቶ ባንትይርጉ ሄባና (የፋይናንስ ቢሮ የገቢ አወሳሰን ኦፊሰር)

5ኛ. መሸሻ ዜማ (መምህር)

6ኛ. ባሻ ፋንታሁን ታደሰ (የማይክሮ ፋይናንስ ሠራተኛ)

7ኛ. ዶለቦ ቦንጃ (የመሰናዶ ትም/ቤት መምህር)

8ኛ. አቶ ቲንኮ አሻንጎ (የኅብረት ሥራ ማህበራት ኦፊሰር)

9ኛ. አቶ አበራ ገ/መስቀል (የትም/ት ኤክስፐርት)

10ኛ. አቶ ጴጥሮስ ሀላላ (ነጋዴ) ናቸው፡፡

እሁድ ማለዳ የተወካዮቹንና የወረዳውን ታዋቂ ሰዎች መታሰር የሰማው ህዝብ ከያለበት በመሰባሰብ ታሳሪዎቹ ወደ ሚገኙበት ፖሊስ ጣብያ በማምራት ፖሊስ በህገ ወጥ መንገድ ያሰራቸውን እንዲፈታ ጠይቀዋል፡፡ፖሊስ እስረኞቹን ለመፍታት ፈቃደኛ ባለመሆኑም ከ5000 የማያንስ ህዝብ ፖሊስ ጣብያውን በመክበብ ‹‹እነርሱን በመወከል የማንነት ጥያቄያችንን እንዲያቀርቡ የወከልናቸው እኛ ነን ከፈለጋችሁ እኛን ልታስሩ ይገባል››በማለት የወኪሎቻቸውን መታሰር ተቃውመዋል፡፡

ፖሊስ ወኪሎቼን ፍታ በማለት የጠየቀውን የቁጫ ነዋሪ ከጣብያ ገለል ለማሰኘት በወሰደው የሃይል እርምጃ ብዙዎች መጎዳታቸውን የፍኖተ ነጻነት ምንጭ አጋልጧል፡፡ምሽት ላይ በወታደር ካሚዮን የተጫኑ የፌደራል ፖሊሶች ወደ ወረዳው በመግባት ተቃውሞውን ለመቆጣጠር መሞከራቸውንና ሺዎችን ለእስር መዳረጋቸውን ምንጫችን ጨምሮ ገልጻል፡፡

ስለ ሁኔታው ማብራሪያ የተጠየቁት የወረዳው ፓሊስ ጣብያ አዛዥ ‹‹ምንም አይነት የሃይል እርምጃ ፖሊስ አለመውሰዱን ከመናገር ውጪ ተጨማሪ ጥያቄ ለመመለስ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ስልካቸውን ዘግተዋል፡፡

ኢህአዴግ የብሄር ጥያቄን እንደመለሰ በመግለጽ የብሄር ብሄረሰቦችን ቀን ማክበር የጀመረ ቢሆንም ጥያቄው ተገቢውን ምላሽ አለማግኘቱ በቁጫ ወረዳ የተነሳው የማንነት ጥያቄ ማሳያ እንደሚሆን ፍኖተ ነጻነት ያነጋገረቻቸው ባለሞያዎች ገልጸዋል፡፡

– See more at: http://www.fnotenetsanet.com/?p=4789#sthash.BjDJq0F0.dpuf

posted by Tseday Getachew

 

Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: