Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

አቶ ብርሃነ መዋ ኢትዮጵያውያን በአንድነት እንጂ በተናጠል ትግል ውጤት ለማምጣት እንደሚቸገሩ ገለጹ

በሰሜን አሜሪካ የአንድነት ድጋፍ ማህበር፣ ጁላይ 5 ቀን ሕዝባዊ ስብሰባ በዋሺንገትን ዲሲ አካባቢ ባደረገው ሕዝባዊ ስብሰባ ከሕዝብ ጋር ተወያየ። በስብሰባዉ በአካል ተገኝነተዉ፣ አንጋፋዉ የቀድሞ የሰሜን አሜሪካ ቅንጅት ድጋፍ ማህበር አመራር አባል የነበሩት አቶ ብርሃን መዋ፣ እንዲሁም የአንድነት ፓርቲ የዉጭ ግንኙነት ክፍል ሃላፊው አቶ ተመስገን ዘዉዴ፣ ለሕዝቡ ንግግር አድርገዋል።

አቶ ተመስገን የአንድነት ፓርቲ ስለጀመረዉ የሶስት ወራት የሚሊዮኖች ድምጽ እንቅስቃሴ ገለጻ የሰጡ ሲሆን ኢትዮጵያዉያን የተዘጋጁ ፔትችኖችን በመፈረም የእንቅስቃሴው አካል እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል። በአገር ቤት የሰማያዊ ፓርቲ በጠራዉ ስብሰባ የአንድነት አባላትና ደጋፊዎች እንደተባበሩ፣ የአመራር አባላቱን በሰልፉ እንደተገኙ የገለጹት አቶ ተመስገን፣ አንድነት ትግሉን እስከረዳ ድረስ፣ ማንም ጠራ ማንም፣ በማናቸዉም ሰላማዊ እንቅስቃሴዎች ጎን እንደሚቆም አስረድተዋል። ብዙዎች እየታሰሩ፣ እንግልትና መከራ እየደረሰባቸው እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ተመስገን፣ ትግሉ ከመቼዉም በበለጠ ወሳኝ ደረጃ ላይ እንዳለም ገልጸዋል።

አቶ ብርሃነ መዋ በበኩላቸው፣ የአንድነት ፓርቲ፣ በተለይም ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር ያለዉን ግንኙነት በጣም እንዲያጠክር፣ የመከሩ ሲሆን ኢትዮጵያዉያን በአንድነት እንጂ በተናጥል ከሰሩ ብዙ ዉጤት ማምጣት እንደሚያስቸግራቸው አስረድተዋል። በተለይም በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የተቃዋሚ ፓርቲዎች መብዛትና እርስ በእርስ መጠላለፍ ትግሉን እንደጎዳው የተናገሩት አቶ ብርሃነ መዋ ከተቃዋሚው ወገን ያለውን ያለመተባበር ችግር አስረግጠው ከነመፍትሄው አስረድተዋል። ሁሉም የራሱን ሕልውና ማ ዕከል የመሠረተ ድርጅት ስለሚመሰርት ትግሉ ውጤት እንዳላመጣ በንግግራቸው ላይ የጠቀሱት አቶ ብርሃነ መዋ “ተቃዋሚው አቶ መለስ ዜናዊ ስልጣን ላይ 18 ዓመት ተቀመጡ ብሎ ይተቻል። ራሳቸው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ስልጣኑ ላይ ለተመሳሳይ አመታት ቁጭ ብለውበታል። ስልጣን መቀያየርን ሁሉም መልመድ ይኖርበታል።” በማለት ተናግረዋል።

ትግሉን ወጣቶች እንዲመሩት መደረግ እንዳለበት አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ብርሃነ የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ ለመመስረት ሁሉም ተቃዋሚ ኃይል በአንድነት ቆሞ እንዲታገል ጥሪ አቅርበዋል።

በሌላም በኩል ይህን የዚህ ስብሰባ ሌላ ገጽታ ከኢትዮጵያ በቀጥታ ለተሰብሳቢዉ ንግግር ያደረጉ ወጣት የአንድነት አመራር አባላት መኖራቸው ነበር። አቶ በላይ ፍቃዱ የአንድነት የብሄራዊ ምክር ቤት አባል እና የፍኖት ኤዲቶሪያል ሰብሳቢ እንዲሆም የአንድነት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊዉ፣ አቶ ዳንኤል ተፈራ፣ በስካይፕ በአገር ቤት እየተደረገ ስላለዉ አገረ ሰፊ የሚሊዮኖች ድምጽ እንቅስቃሴ በስፋት አብራርተዋል። ይሄም ፓርቲዉ በጣም የበሰሉ፣ የሰከኑና መስዋእትነት ለመክፈል የተዘጋጁ በርካታ ወጣት አመራሮች እንዳሉት ለብዙዎች ያሳየበት ሁኔታ ነዉ የነበረው።

ከስብሰባው ተሳታፊዎቹ ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆኑቱ ወጣቶች መሆናቸው፣ የድጋፍ ድርጅት አመራር አባላትን በእጅጉ እንዳስገረመም አንዳንድ የውስጥ አዋቂዎች ጠቁመዋል። «የአንድነትን እንቅስቃሴ በፌስቡክና በሌሎች የማህበረሰብ ሚዲያዎች ብዙዎች እንደሚከታተሉትና በርካታ ለቴክኖሎጆ ቅርብ የሆኑት ወጣቶችን አንድነትን ለመደገፍና የትግሉም አካልን ለመሆኑ ከመቼዉም በላይ ፍላጎት እያደረባቸው መሆኑን የሚያሳይ ነዉ» ሲሉ አንዱ የቆዩ የአንድነት ድጋፍ ማህበር አባል ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአንድነት ፓርቲ ሐምሌ 7 ቀን በጎንደር ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ሲሆን በመቀጠልም በመቀሌ፣ በደሴ ተከታታይ ህሕዝባዊ ስብሰባዎች እንደሚያደርግ ካወጣው መርሃ ግብር ለመረዳት ተችሏል። ፓርቲዉ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎችንም እያደረገ ከሁለት ወራት በኋላ ለሚያደርገዉም የጠቅላላ ጉባዔ እየተዘጋጀ መሆኑ ሲታወቅ ጠቅላላ ጉባዔዉ ሲደረግ በርካታ ወጣቶች ወደ አመራሩ ይመጣሉም ተብሎ እንደሚታወቅ የውስጥ አዋቂ ምንጮች መረጃውን ሰጥተውናል።

በሌላ ዜና፦
በአዲስ አበባ የአንድነት አባላትን ማሰር ተጀምሯል-

ከዳግማዊ ቴዎድሮስ

የአንድነት ፓርቲ በስፋት የሚሊዮኖች ድምጽ በሚል ህዝባዊ እንቅስቃሴ አዉጁ በሁሉም ክልሎች በተለያዩ ማኤዠናት ትልቅ ሥራ የተስራ ነዉ። በዚህም እንቅስቃሴ ከፍተኛ ዋጋም እየተከፈለ ነዉ። በአዲስ አበባ የፀረ ሽብር ህጉ እንዲሰረዝ የሚጠይቅ በራሪ ወረቀት የበተነ የአንድነት አባል በአደራ ታሰሯል።

አንድነት ፓርቲ ‹‹የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት›› በሚል መሪ ቃል የጀመረውን ህዝባዊ ንቅናቄ አጠናክሮ መቀጠሉን ተከትሎ መንግስት የማደናቀፍ ተግባሩን በአዲስ አበባም ጀምሯል፡፡ የአንድነት ፓርቲ አመራሮች ለፍኖተ ነፃነት እንደገለፁት ሙሉጌታ ተፈሪ የተባለውን የአንድነት ፓርቲ የወረዳ 15 አባል ካዛንችስ አካባቢ በህገወጥ መንገድ በፖሊስ ታስሯል፡፡ ሙሉጌታ ካዛንችስ አካባቢ የፀረ ሽብር ህጉ እንዲሰረዝ የሚጠይቅ በራሪ ወረቀት ሲያሰራጭ መታሰሩን ፖሊስ ተናግሯል፡፡

የአባሉን መታሰር የሰሙት የአንድነት ከፍተኛ አመራሮች አቶ ግርማ ሰይፉና አቶ በላይ ፍቃዱ ካዛንችስ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ተገኝተው ሙሉጌታ በህገወጥ መንገድ መታሰሩን በማስረዳት ተከራክረዋል፡፡ የጣቢያው ፖሊሶች ግን “ሙሉጌታን ያሰረው ፖሊስ ስለሌለ እሱ ሳይመጣ አይፈታም” በማለት “የአደራ እስር” ከጎንደር በተጨማሪ በአዲስ አበባም መኖሩን አረጋግጠዋል፡፡ አመራሮቹም “እኛም ወረቀቱን እየበተንን በመሆኑ እሰሩን” በማለት ተሟግተዋል፡፡

ዘግይቶ በደረሰን ዜና የአንድነት አመራሮች የታሳሪውን ጉዳይ መከታተላቸውን ተከትሎ ሙሉጌታ ተፈሪ ክቤ በተባለች ፖሊስ “ተመርምሮ” ወደ 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ ሊወሰድ መሆኑን የፍኖተ ነፃነት የፖሊስ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡

የአንድነት ፓርቲ አዲስ አበባ ዞን አባላት ዛሬ ጠዋት በፓርቲው ዋና ጽ/ቤት በመገኘት ከፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ህዝባዊ ንቅናቄውን በአዲስ አበባ ተደራሽ የማድረግ ተልዕኮ ተቀብለው ከቀኑ 7 ሰዓት ጀምሮ በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከ100ሺ በላይ የሆነ በራሪ ወረቀትም በማሰራጨት ላይ ይገኛሉ፡፡

Short URL: http://www.zehabesha.com/amharic/?p=5047

posted by Tseday Getachew

Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: