Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

በከፍተኛ ሙስና የተዘፈቀው መከላከያ ሂሳቡ እንዳይመረመር ታዘዘ

እንዳይመረመር ታዘዘ

 

-የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በሚያዚያ ወር 2005 ዓ.ም ባቀረበው ሪፖርት የመከላከያና የደህንነት ተቋማት
የፋይናንስ አያያዝ ከፍተኛ ችግር እንዳለበት ማመልከቱን ተከትሎ በየመ/ቤቶቹ የተነሳውን ቅሬታ ለመፍታት በቀጥታ
እነዚህን ተቋማት በተለየ ሁኔታ ኦዲት ለማድረግ የሚያስችል አዋጅ እየተረቀቀ መሆኑ ተጠቆመ፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ ሚያዚያ 22 ቀን 2005 ዓ.ም ለፓርላማው ባቀረቡት የ2004 ዓ.ም
የፌዴራል የመንግስት መ/ቤቶች የሂሳብ አያያዝ ሪፖርት በተለይ በዘጠኝ መ/ቤቶች 3 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር
ባልተሟላ ሰነድ ወጪ ሆኖ መገኘቱን፤ ከዚህ ውስጥ 3 ነጥብ 2 ቢሊየን ብሩ የመከላከያ ሚኒስቴር መሆኑን
መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
እነዚህ ተቋማት ላወጡት ገንዘብ ትክክለኛ ማስረጃ እንዲያቀርቡ ተጠይቀውም ማቅረብ አለመቻላቸውን ለፓርላማው
ሪፖርት ካደረጉ በኋላ በተለይ የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈረጌሳን ጨምሮ የተለያዩ ሹማምንት ሪፖርቱን
በአደባባይ እስከማብጠልጠል የደረሰ ትችት ሲያቀርቡ ተደምጠዋል፡፡ ዋናው መከራከሪያቸውም የመከላከያ ወጪ ሚስጢር
ነው የሚል ነበር፡፡

ይህንን ተከትሎ የፓርላማ አፈጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ በቴሌቪዥን ቀርበው “ባልተሟላ ሰነድ
ወጪ ተደረገ ማለት ብሩ ተበላ ማለት አይደለም” በማለት ማብራሪያ ለመስጠትና ተቋሙን ከተጠያቂነት ነጻ ለማድረግ
ሞክረዋል፡፡

አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከተሾሙ በኋላ የመጀመሪያቸው የሆነውን መግለጫ ትላንት ጠዋት
በጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች በሰጡበት ወቅት በተመሳሳይ መንገድ መከላከያን ኦዲት ማድረግ
ሚስጢር ማባከን መሆኑን በመግለጽ በቀጣይ ሁኔታውን ለማስተካከል አዲስ ሕግ እንደሚወጣ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
ዋና ኦዲተር በአዋጅ ቁጥር 669/2002 መሰረት የፌዴራል የመንግስት ተቋማትን ኦዲት የማድረግና የማስደረግ ሙሉ ሥልጣን

እንደተሰጠው ጠቅላይ ሚኒሰትሩ አስታውሰው በዚህ ሕግ መሰረት ባለፉት ዓመታትም መከላከያን ጨምሮ ሁሉንም ተቋማት ኦዲት ሲያደርግ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡

አቶ መለስ ዜናዊ በሕይወት በነበሩበት ጊዜ በሚያዚያ ወር 2004 ዓ.ም የ2003 የሂሳብ ሪፖርት ለፓርላማው ቀርቦ እንደነበር በዚህም ሪፖርት መሰረት

ከተወቀሱት ተቋማት መካከል መከላከያ አንዱ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ በ2003 በጀት ዓመት በመከላከያ 133 ነጥብ
8 ሚሊየን ብር ውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብ መኖሩን፣ የተሟላ ማስረጃ ሳይቀርብ 19 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በወጪ
ተመዝግቦ መገኘቱን ሪፖርት አድርጓል፡፡  በተጨማሪም የወጪውን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ካልተቻለው ገንዘብ መካከል 1
ነጥብ 9 ቢሊየን ብር የመከላከያ ሲሆን ፣ 54 ነጥብ 3 ሚሊየን ደግሞ ብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ 33
ነጥብ 34 ሚሊየን ብር የአገር ውስጥ ደህንነት ጥበቃ ዋና መምሪያ መሆኑ መጠቀሱ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ መ/ቤቱ
እንደዘንድሮ ከፍተኛ ቅሬታ ያላቀረበ ሲሆን የዘንድሮ ቅሬታ ምናልባትም በአዲሱ ጠ/ሚኒስትር ላይ ተጽዕኖ በማሳደር
ነገሩን ለመሸፋፈን የታሰበ ሳይሆን እንደማይቀር ተገምቷል፡፡

ምንጮቻችን እንደገለጹት በአገሪቱ ከፍተኛ ሙስና ከሚፈጸምባቸው ተቋማት መካከል ግንባር ቀደሙ መከላከያ መሆኑን
አስታውሰው አንድ ወርሃዊ ደመወዙ 4 ሺ ብር የማይሞላ ከፍተኛ የመከላከያ ሹም በአዲስአበባ ቁልፍ ቦታዎች ጭምር
በሚሊየን ብር የሚገመቱ ቪላዎችንና ሕንጻዎችን የሚገነባበት እንዲሁም ትልልቅ ንግዶችን የሚያንቀሳቅስበት ሁኔታ
የአደባባይ ሚስጢር ነው በማለት የእነአቶ ኃይለማርያም ሙግት ጥቅሙ ለሙሰኞቹ ነው ብለዋል፡፡
አዲሱ ሕግ በቀጣይ ዓመት ለፓርላማው ቀርቦ ይጸድቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ዋና ኦዲተር ሕጉ እስኪጸድቅ
መከላከያና የደህንነት ተቋማትን ኦዲት እንዳያደርግ መታዘዙንም ምንጮቻችን አረጋግጠዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ 60 ከፍተኛ ጀኔራሎች መካከል 58ቱ በትጥቅ ትግሉ ወቅት የህወሀት አባል ሆነው የመጡ ናቸው።

መከላከያን ከላይ ሆነው የሚዘወሩት 7ቱ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች በሙሉ የህወሀት ታጋዮች ናቸው። ባለፉት 22 አመታት በዚህ ከፍተኛ

አመራር ውስጥ የሌላ ብሄር ተወላጅ ተካቶ አያውቅም።

በሌላ በኩል ደግሞ አቶ ሀይለማርያም በአባይ ግድብ ዙሪያ ከተቃዋሚዎች ጋር እንደማይነጋገሩ አስታውቀዋል።

ኢሳት ዜና

Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: