Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

‹‹እኛ ንፁሆች ነን እየተወነጀልን ያለነው በተቀነባበረ ድራማ ነው›› አቶ ገብረዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ

 

-አቶ መላኩ ፈንታ ሆስፒታል ተኝተው እየታከሙ ነው

-ሁለት ተጠርጣሪዎች በዋስ ሲለቀቁ አንድ ተጠርጣሪ ተይዟል

በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ በሚገኙት የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ኃላፊዎችና ነጋዴዎች ላይ 230 የሰው ምስክሮች መቆጠራቸው ታወቀ፡፡

የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ቡድን ሰኔ 17 እና 18 ቀን 2005 ዓ.ም. በእነ አቶ ገብረዋህድ ወልደ ጊዮርጊስና በእነ አቶ መላኩ ፈንታ የምርመራ መዝገብ ላይ ላለፉት 14 ቀናት የሠራቸውን የምርመራ ውጤቶች፣ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት አቅርቦ አስረድቷል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በእያንዳንዱ ተጠርጣሪ ላይ የሠራውንና የቀረውን የምርመራ ሒደት በዝርዝር ባያስረዳም፣ አልፎ አልፎ በአንዳንዳቹ ላይ የሰበሰበውን የሰነድ ማስረጃ ግልጽ ለማድረግ ከመሞከሩ ጐን ለጐን የምስክሮችን ቃል መቀበል በሚመለከት፣ የ96 ምስክሮችን ቃል መቀበሉን አስታውቋል፡፡ ቃላቸውን ያልተቀበላቸው 74 ምስክሮችና  60 የሙያ ምስክሮች እንደሚቀሩትም ተናግሯል፡፡

አቶ ገብረዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ፣ አቶ በላቸው በየነ፣ አቶ ጥሩነህ በርታ፣ አቶ ተስፋዬ አበበ፣ አቶ ነጋ ገብረ እግዚአብሔር፣ አቶ ምሕረተአብ አብርሃ፣ አቶ ሙሌ ጋሻው፣ አቶ አሞኘ አወቀ፣ ኮሎኔል ሃይማኖት ተስፋይና አቶ ተወልደ ብርሃን ገብረ መድኅን በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል ለ14 ቀናተ ያከናወናቸውን የምርመራ ተግባራት መርማሪ ቡድኑ ለችሎቱ አስረድቷል፡፡ ከቀረጥ ነፃ የገቡ የሆቴልና የግንባታ ዕቃዎች ለታለመላቸው ዓላማ አለመዋላቸውን የሚያስረዳ ሰነድ መሰብሰቡን፣ የተመሠረተን ክስ ከማቋረጥ ጋር በተያያዘ የሰነድ ማስረጃ መሰብሰቡንና የተወሰኑ የምስክሮች ቃል መቀበሉን ገልጿል፡፡ ሕገወጥ በሆነ የፍራንኮ ቫሉታ ፈቃድ የገባ ሲሚንቶን አስመልክቶ ባለሥልጣኑ ክስ ቢመሠርትም ተጠርጣሪዎች በክሱ እንዳይካተቱ ማድረግን በሚመለከት፣ በአቶ ገብረዋህድ፣ በአቶ ነጋ፣ በአቶ አሞኘ አወቀና በአቶ ተወልደ ብርሃን ላይ ማስረጃ መሰብሰቡንና ቀሪ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች እንዳሉትም አስረድቷል፡፡

የተመሠረቱ ክሶች በሕገወጥ መንገድ እንዲቋረጡ ከተደረጉ 60 የክስ መዝገቦች ውስጥ ቀደም ሲል ከሰበሰበው ማስረጃ በተጨማሪ ባለፉት 14 ቀናት 21 መዝገቦችን መሰብሰቡንና መመርመሩን፣ የምስክሮች ቃል መቀበሉን፣ በዚህ የወንጀል ተግባር የተጠረጠሩትም አቶ ገብረዋህድ፣ አቶ በላቸው፣ አቶ ተስፋዬና አቶ ሙሌ መሆናቸውን ለችሎቱ አስረድቷል፡፡

በመመሳጠርና በማስመሰል በሕገወጥ መንገድ የተወሰደ የጥቆማ አበልን በሚመለከት ሰነድ መሰብሰቡንና በዚህም የወንጀል ተግባር የተጠረጠሩት አቶ ገብረዋህድ፣ አቶ በላቸውና አቶ ጥሩነህ በርታ መሆናቸውን የገለጸው የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን፣ ከናዝሬት ወደ አዲስ አበባ የሚገባ ዕቃ ሳይፈተሽ እንዲያልፍ በማድረግ፣ ቃሊቲ ጉምሩክ ሲፈተሽ ሕገወጥ የታክስ ማጭበርበር ሥራ መሆኑ ተደርሶበት የተመሠረተን ክስ ያቋረጡና በድርጊቱ የተሳተፉት አቶ ገብረዋህድ፣ አቶ ነጋ፣ አቶ ምሕረተአብ፣ አቶ አሞኘና አቶ ተወልደ ብርሃን መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡

በሕገወጥ መንገድ የኦዲት ሪፖርትን በመከለስና ገቢን በማሳነስ በናዝሬት፣ በሚሌና በድሬዳዋ ኮንትሮባንድ ዕቃዎች ሳይፈተሹ በማሳለፍ በመንግሥትና በሕዝብ ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ወንጀል የተጠረጠሩት ደግሞ፣ ከአቶ ጥሩነህ በርታና ከኮሎኔል ሃይማኖት ተስፋይ በስተቀር ሁሉም መሆናቸውን የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን ገልጿል፡፡ አቶ ገብረዋህድና አቶ ጥሩነህ በርታ የተጠረጠሩበት ሌላው ድርጊት ደግሞ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል የሚገቡ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ክስ ተመሥርቶባቸው ፍርድ ቤት ከደረሱ በኋላ፣ ክሳቸው እንዲቋረጥ መደረጉንና የኩባንያዎች የታክስ ኦዲት እንዲከለስ ማድረጋቸውን መርማሪ ቡድኑ አስረድተቷል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ለችሎቱ ማስረዳቱን ቀጥሎ እያለ፣ ፍርድ ቤቱ በመሀል ገብቶ ‹‹ተጠርጣሪ ኩባንያዎች ስንት ናቸው? ያጣራችሁትስ ምንድነው? ይኼንን ግልጽ አድርጋችሁ አስረዱ፤›› በማለት ጠይቋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ በርካታ ኩባንያዎች እንዳሉ በቃል ለመግለጽ ቢሞክርም፣ ለችሎቱ መግለጽ የቻለው የታዋቂው ነጋዴ አቶ ነጋ ገብረ እግዚአብሔር ንብረት የሆኑትን ነፃ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ፣ ባሰፋ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ፣ ሞኒት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ፣ አቶ ምሕረተአብ አብርሃ በባለቤትነት ይመሩታል የተባለው መፍአም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና አቶ አሞኘ አወቀ በባለቤትነት የሚመሩት እንግዳዬ አሰፋ ኮንስትራክሽን ማሽነሪ አከራይ ድርጅቶች መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡

ጊዜ ቀጠሮ ባልተጠየቀባቸውና ለፍርድ ቤቱ ይፋ ባልደተረገበት ሁኔታ በኩባንያዎቹ ላይ የሚደረገው ምርመራ አግባብነትን በሚመለከት ፍርድ ቤቱ ለመርማሪ ቡድኑ ያነሳውን ጥያቄ፣ ሕገ መንግሥቱ በሚያዘው መሠረት በኩባንያዎቹ ባለቤቶች ላይ ምርመራ ሲደረግ በመካከላቸው ትስስር አለ ተብሎ ስለሚገመት መሆኑን መርማሪ ቡድኑ በመናገር ብዙም ግልጽ ሳይደረግ ታልፏል፡፡

ባለፉት ሦስት የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜያት በተደረጉት ምርመራዎች ሥልጣንን አላግባብ በመጠቀም ክሳቸው እንዲቋረጥ ከተደረጉ 60 የክስ መዝገቦች ውስጥ 45 መሰብሰቡንና ምርመራ ማድረጉን የገለጸው መርማሪ ቡድኑ፣ ቀሪ 15 የተቋረጡ የክስ መዝገቦች እንደሚቀሩ፣ ከላይ እንደጠቀሰው 96 የሰዎች ምስክሮች ቃል ቢቀበልም 74 ምስክሮችና 60 የሙያ ምስክሮች እንደሚቀሩት፣ በተጠርጣሪዎች ላይ የሰነድ ማስረጃ ቢሰበስብም የሚቀረው እንዳለ፣ በክልል የባለሥልጣኑ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች የሚሰበሰቡ ሰነዶች እንዳሉትና ከኦዲት ምርመራ ጋር በተያያዘ የባለሙያ ማብራሪያ እንደሚቀረው አስረድቷል፡፡

የአቶ ገብረዋህድ ባለቤት ኮሎኔል ሃይማኖት ተስፋይን በሚመለከት፣ በተጠርጣሪዋ የተሰወረ ሰነድ መኖሩን ፍንጭ በማግኘቱ ክትትል እያደረገ መሆኑን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ኮሎኔሏ የሞኒት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ተቀጣሪ ሆነው ሲሠሩ የባለቤታቸውን ሥልጣን ተጠቅመው በጥቅም በመተሳሰር ከግብር ስወራ ጋር መጠርጠራቸውንና ቀሪ ምርመራ እንደሚቀረው ለችሎቱ በማስረዳት፣ ለቀሪ የምርመራ ሥራዎቹ የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ እንዲፈቀድለት በወንጀል ሕግ ቁጥር 59(2) መሠረት ጠይቋል፡፡ የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን በተፈቀደለት ጊዜ የሠራቸውን የምርመራ ክንውኖች አስረድቶ እንደጨረሰ በጠየቀው ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ላይ ተጠርጣሪዎች የሚሉት ካለ ፍርድ ቤቱ ጠይቋቸው፣ የአቶ ገብረዋህድ ጠበቃ በቅድሚያ አጭር መከራከሪያ ነጥብ አንስተዋል፡፡ ኮሚሽኑ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋል በጀመረበት ጊዜ ማለትም ከ42 ቀናት በፊት በቂ ማስረጃ መሰብሰቡን መግለጹን ያስታወሱተ የአቶ ገብረዋህድ ጠበቃ፣ መርማሪ ቡድኑ ተጨማሪ ጊዜ እየጠየቀ ያለው በተሠራ ሥራ ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መጠየቁንም ተቃውመዋል፡፡

ተጨማሪ የሚያስረዱት ነገር እንዳላቸው የገለጹት አቶ ገብረዋህድ ሲፈቀድላቸው፣ ‹‹መርማሪ ቡድኑ ክስ መሥርቶ የጠረጠረበትን ወንጀል በማስረጃ አረጋግጦ ወንጀለኛነታችንን በፍርድ ቤት ሳያረጋግጥ፣ ጉቦ እየተቀበሉ በማለት ደምድሞ መናገሩ ሊታረም ይገባል፡፡ እኛ ንፁሆች ነን፡፡ ይኼ ከአለቆቻቸው ጋር ያቀነባበሩት ድራማ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በዳኞች ፈቃድ የ14 ቀናት ጊዜ እየተፈቀደ ሁለተኛ ወራቸው መሆኑን ያከሉት አቶ ገብረዋህድ ‹‹ለዚች አገር የሠራን ዜጐች ነን፤ አገልግለናል፡፡ የእነሱን ድራማ ብቻ እየሰማን መቀጠል የለብንም፤›› በማለት ስሜታዊነት የተቀላቀለበት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የወንጀል ሕግ ቁጥር 59(2) በጠባቡ ካልተተረጐመ ማቆሚያ እንደሌለው በመግለጽ፣ መርማሪ ቡድኑ ባለፉት ቀጠሮዎች ከሠራው ውጭ ምንም የሠራው ነገር እንደሌለ ለችሎቱ በማስረዳት፣ የደንበኛቸው የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው የጠየቁት የአቶ በላቸው ጠበቃ ናቸው፡፡ ‹‹ከአንድ ወንጀል ወደ ሌላ ወንጀል እየተዘለለ ነው፡፡ እኔን በእስር ላይ በማቆየት የወንጀል መመሥረቻ ሰነድ እየተፈለገ ነው፡፡ ይኼ የሚያመለክተው ደግሞ በእኔ ላይ ምንም ዓይነት ወንጀል አለመገኘቱን ነው፡፡ ኮሚሽኑ፣ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት እንዲሁም ፌዴራል ፖሊስ በጋራ በመሆን መላ አገርን የሚያዳርስ ኃይል ያላቸው ናቸው፡፡ በእኔ ላይ የቀረቡትን ሁለት ክሶች እንዴት ባለፉት 40 ቀናት አጣርተው ማቅረብ ያቅታቸዋል?›› በማለት የጠየቁት ደግሞ አቶ ጥሩነህ በርታ ሲሆኑ፣ በዋስ ቢወጡ ከላይ ከጠቀሱት ኃይሎች ሊሰወሩ የማይችሉ መሆኑን በመግለጽ፣ ባለቤታቸው ምንም ገቢ የሌላቸው መሆናቸውንና በሁለት ሕፃናት ልጆቻቸው ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ከግምት በማስገባት ዋስትና እንዲፈቀድላቸው በተደጋጋማ ጠይቀዋል፡፡

አቶ ተስፋዬ አበበም የተጠረጠሩበት ወንጀል ግራ እንዳጋባቸው ተናግረው፣ ቀደም ሲል ከአራጣ ጋር እንደተጠረጠሩ ሰምተው አሁን ደግሞ ከቀረጥ ነፃ ከገቡ የሆቴልና የግንባታ ዕቃዎች ጋር መጠርጠራቸው እንዳስገረማቸው ገልጸዋል፡፡ የልብና የኮሌስትሮል ሕመም እንዳለባቸው ደጋግመው በማስረዳት፣ ለአገራቸው ዲሞክራሲ ግንባታና ለልማት ያደረጉት አስተዋጽኦን ከግምት ውስጥ በማስገባት የዋስትና መብታቸውን እንዲከበር ጠይቀዋል፡፡

ተጠርጥረው ሲያዙ የተነገራቸው ባልተፈቀደ የፍራንኮ ቫሉታ ፈቃድ ሲሚንቶ በማስገባት መጠርጠራቸውን፣ ቀጥሎ ከናዝሬት ወደ አዲስ አበባ የሚገባ ዕቃ ሳይፈተሽ እንዲያልፍ በማድረግ መጠርጠራቸውንና እንዲሁም በኮንትሮባንድ ንግድ የተከሰሱን ተከሳሾች ክስ በማቋረጥ፣ ወዘተ በማለት ላለፉት 42 ቀናት በእስር ላይ መቆየታቸው አግባብ አለመሆኑን የገለጹት የአቶ ነጋ ገብረ እግዚአብሔር ጠበቃ ናቸው፡፡ ‹‹መርምሬ አልጨረስኩም ማለት ተጠርጣሪዎችን የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብታቸውን መንፈግ ነው፤›› ያሉት የአቶ ነጋ ጠበቃ፣ ላለፉት 42 ቀናት በደንበኛቸው ላይ በዝርዝር የተሠራ የምርመራ ውጤት አለመቅረቡን፣ ምን ያህል ምስክር በእሳቸው ላይ ተቆጥሮ ምን ያህሉ እንደተሰማና እንዳልተሰማ በማብራራት ከዚህ በላይ ደንበኛቸው በእስር መቆየት እንደሌለባቸው ተናግረዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ የጠየቀው የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ውድቅ ተደርጐ የዋስትና መብታቸው ተከብሮ ውጪ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ጠይቀዋል፡፡

አቶ ምሕረተአብ አብርሃን በሚመለከት መርማሪ ቡድኑ ከባለሥልጣናቱ ጋር በመመሳጠር ክስ በማቋረጥ ተጠርጥረው እንደታሰሩ ቢያስረዳም፣ ጠበቃቸው ክሱ እንዳልተቋረጠና አሁንም በጠቅላይ ፍርድ ቤት እየታየ መሆኑን ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡ ቃላቸውን ሰጥተው በማጠናቀቃቸውም የዋስትና መብታቸው ተከብሮላቸው ከእስር እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡ የኮሎኔል ሃይማኖት ተስፋይ ጠበቃ በደንበኛቸው ላይ የተጠየቀውን የ14 ቀናት ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ተቃውመዋል፡፡ ኮሎኔል ሃይማኖት ‹‹የአቶ ነጋን ሰነድ ሊያሸሹ ይችላሉ፣ የተሸሸገ ሰነድ እንዳለ ፍንጭ አግኝተናል ግን አልያዝንም፤›› የሚባለው ነገር የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብታቸውን የሚገፉ መሆኑን በመግለጽ ተቃውመዋል፡፡ ሌላው ኮሎኔል ሃይማኖት ያነሱት ነጥብ ጡረተኛ መሆናቸውን ሲሆን፣ ጡረታቸውን ሄደው ለመቀበል ባለመቻላቸው በአጃቢ ሆነው መቀበል እንዲችሉ እንዲታዘዝላቸው በጠበቃቸው አማካይነት ጠይቀዋል፡፡

ኮሎኔል ሃይማኖት ተጨማሪ ሊያስረዱት የሚፈልጉት ጉዳይ እንዳላቸው በማመልከት ሲፈቀድላቸው ‹‹እናት ነኝ፤ ልጆቼ ተበትነዋል፡፡ እስቲ እናትና አባት ሆናችሁ፣ በሕግ ጥላ ሥር ሆናችሁ ልጆቻችሁ ሲበተኑ ምን ይሰማችኋል?›› በማለት ጥያቄያቸውን ለችሎቱ ዳኞች አቅርበው፣ ልጆቻቸው አጉል ዕድሜ ላይ በመሆናቸው ወደ ጐዳና ይወጣሉ የሚል ሥጋት እንዳደረባቸው ተናግረዋል፡፡ የወለደ አንጀት የሚሰማውን ሁሉም እንደሚያውቀው በማከል፣ አንደኛው ልጃቸው ጀማሪ ተማሪ በመሆኑ ተረጋግቶ ለማጥናት አለመቻሉን፣ ጠዋትና ማታ እነሱን ለማየት ወደ እስር ቤት እንደሚመላለሱና ‹‹አስቤዛ አልቆብናል›› የሚል ሪፖርት እንደሚልኩባቸው አስታውቀዋል፡፡ ‹‹እኔ ሕግ የሚለኝን ሁሉ ለመሆን ዝግጁ ነኝ፤ በምጠየቅበት ነገር ልጠየቅ፤ እነዚህ ልጆች ግን ምን ይሁኑ?›› በማለት በድጋሚ ጠይቀው ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብታቸውን ጠብቆላቸው ልጆቻቸውን እንዲንከባከቡ ጠይቀዋል፡፡ ሌሎቹም በአቶ ገብረዋህድ የምርመራ መዝገብ ያሉ ተጠርጣሪዎች የመርማሪ ቡድኑን የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ በመቃወም የዋስትና መብትቸው እንዲጠበቅላቸው ጠይቀዋል፡፡

ሌላው ሰኔ 18 ቀን 2005 ዓ.ም. የታየው የምርመራ መዝገብ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎችን ያካተተው የእነ አቶ መላኩ መዝገብ ነበር፡፡ የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን በእነ አቶ ገብረዋህድ የምርመራ መዝገብ የሠራውን የምርመራ ክንውን በተመሳሳይ በእነ አቶ መላኩ ፈንታ መዝገብም ማከናወኑን ገልጿል፡፡ በእነ አቶ መላኩ ፈንታ መዝገብ ለየት ያለ መረጃ ለፍርድ ቤቱ ያቀረበው መርማሪ ቡድኑ፣ 1.3 ሚሊዮን ብር በቤታቸው ውስጥ ቀብረው እጅ ከፍንጅ የተያዙትን የተጠርጣሪ መርክነህ ዓለማየሁ ወንድምን አቶ ብርሃኑ ዓለማየሁንና የእነሱ ዘመድ መሆናቸውን የተናገሩትን አቶ ገተሮ ሐጢያን በዋስ መልቀቁን ማሳወቁ ነው፡፡

ለሆቴል ቤት ዕቃና ለግንባታ በሚል ከቀረጥ ነፃ ገብተው ለሌላ ዓላማ ስለዋሉ ዕቃዎች፣ ስለ ግብር ስወራ፣ ታክስ ማጭበርበር፣ ክስ ማቋረጥ፣ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ሳይፈተሹ ስለማሳለፍ፣ ምንጩ ያልታወቀና ተገቢ ያልሆነ ሀብት ማፍራትና ሌሎችንም በተጠርጣሪዎቹ ተፈጽመዋል ባላቸው የወንጀል ድርጊቶች ዙሪያም ምርመራ አድርጐ ሰነድ መሰብሰቡንና የምስክሮች ቃል መቀበሉን መርማሪ ቡድኑ አብራርቷል፡፡ የሚቀሩት ሥራዎች እንዳሉም በመግለጽ የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ጠይቋል፡፡

አንድ ተጠርጣሪ ለምርመራ ተጠርቶ ቃሉን ከሰጠ በኋላ በማረፊያ ቤት የሚቆይበት የሕግ አግባብ እንደሌለ በመግለጽ፣ ደንበኛቸው በማረፊያ ቤት ከ47 ቀናት በላይ መቆየታቸው ከሕግ አግባብ ውጭ በመሆኑ የመርማሪ ቡድኑ ጥያቄ ውድቅ ተደርጐ ደንበኛቸው እንዲሰናበቱ የጠየቁት የአቶ መላኩ ፈንታ ጠበቆች ናቸው፡፡ አቶ መላኩ ቃላቸውን ሰጥተው ስለጨረሱ በዋስ ሊለቀቁ ወይም የሕግ አማካሪዎቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ማግኘት የሚችሉበት ማረሚያ ቤት እንዲዛወሩ ጠይቀዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ በቀረበ ቁጥር ጊዜ ቀጠሮ እየጠየቀ ያለው ፍርድ ቤቱ ጠበቅ ያለ ትዕዛዝ ስለማይሰጥ መሆኑን የገለጹት ጠበቆቹ፣ አቶ መላኩ ከተያዙ ጀምሮ ጠበቆቻቸውንም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን በሕገ መንግሥታዊ መብታቸው መሠረት አግኝተው እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውም እየተጣሰ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ምርመራው ቢቀጥል ተቃውሞ እንደሌላቸው ጠበቆቹ ለችሎቱ አስረድተው፣ አቶ መላኩ ግን በዋስ እንዲለቀቁ ወይም ሰው ወደሚያገኙበት ማረሚያ ቤት እንዲዛወሩ በድጋሚ ጠይቀዋል፡፡

ዶ/ር ፍቅሩ ተፈራ የተጠረጠሩት፣ ‹‹ለእነ አቶ መላኩ ፈንታ ጉቦ ሰጥተሃል›› በሚል መሆኑን የገለጹት ጠበቃቸው፣ ሰኔ 14 ቀን 2005 ዓ.ም. መርማሪ ጠርቷቸው፣ ‹‹ከእነ አቶ መላኩ ጋር ያለህ ነገር ተዘግቷል አንፈልግህም፤›› እንዳሏቸውም አክለዋል፡፡ በመሆኑም ዶ/ር ፍቅሩ የሚያጠፉት ሰነድና የሚያባብሉት ምስክር ስለሌለ ምርመራቸው ያለቀው ከአንድ ወር በፊት በመሆኑ በዋስ እንዲለቀቁ አመልክተዋል፡፡ ሌሎቹም ተጠርጣሪዎች የመርማሪ ቡድኑን ተጨማሪ የ14 ቀናት ጊዜ ተቃውመው፣ እንዲሁም በየጊዜው ምርመራው እየሰፋ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ እልባት ሊሰጠው እንደሚገባ በማሳሰብ፣ ደንበኞቻቸው በዋስ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በሰጠው መልስ፣ አቶ ገብረዋህድ፣ ‹‹የኮሚሽኑ ሥራ ድራማ ነው›› ማለታቸው ትክክል ባለመሆኑ ፍርድ ቤቱ ተግሳጽ ጭምር እንዲሰጥላቸው፣ አቶ መላኩም ከጠበቃና ከቤተሰቦቻቸው እየተገናኙ በመሆኑ አቤቱታው ውድቅ እንዲደረግላቸው፣ አቶ መላኩ ፖሊስ ሆስፒታል በሪፈራል ተኝተው እየታከሙ መሆናቸውንና ፍርድ ቤትም የቀረቡት ከሆስፒታል መሆኑን፣ በሁሉም ተጠርጣሪዎች ዙሪያ የሚሰበሰብ ቀሪ ሰነድ እንዳለ፣ የምስክሮችንና የባለሙያዎችን ቃል መቀበል እንደሚቀረው አስረድቷል፡፡ የተጠርጣሪዎቹ ጥያቄ ውድቅ ተደርጐ ለቀሪ ምርመራው የጠየቀው የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ እንዲፈቀድለት በድጋሚ አመልክቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ በሁለቱም የምርመራ መዝገቦች በሰጠው ትዕዛዝ፣ ኮሎኔል ሃይማኖት ከአጃቢ ጋር ሆነው ጡረታቸውን እንዲቀበሉ አዟል፡፡ መርማሪ ቡድኑ በቀጣይ ቀጠሮ በእያንዳንዱ ተጠርጣሪ ላይ ስንት ምስክር እንደሰማ፣ ስንት እንደቀረውና ሌላም የሠራው ነገር ካለ በተናጠል እንዲያቀርብ አዟል፡፡ መርማሪ ቡድኑ የሠራውን የምርመራ ሥራ ተመልክቶ ብዙ የምርመራ ሥራ ማከናወኑን መገንዘቡን ገልጾ፣ የጠየቀውን የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ መፍቀዱንና የተጠርጣሪዎች የዋስትና መብትን አለመቀበሉን አስታውቋል፡፡ አቶ መላኩ ፈንታ ቤተሰብና የሕግ አማካሪ አይጠይቃቸውም ለተባለው ጥያቄም ሰብዓዊ መብት ይከበር ብሏል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ባሹ ዘርጋው የሚባል የባለሥልጣኑ የቃሊቲ ጉምሩክ ዋጋ ተማኝ ኦፊሰርን በቁጥጥር ሥር አውሎ የ14 ቀናት ጊዜ ጠይቆበታል፡፡

ethiopian reporter

posted by Tseday Getachew

Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: