Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

አንዳንድ የፓርላማ አባላት አዲሱን የአማራ ህዝብ ቁጥር እንደማይቀበሉት አስታወቁ

ESAT Amharic News

ኢሳት ዜና :- በማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የሕዝብ ቆጠራ ኮምሽን በ1999/2000 ዓ.ም የሶስተኛው የሕዝብና ቤት ቆጠራ ውጤት ይፋ በተደረገበት ወቅት በተለይ የአማራ ክልል ሕዝብ ብዛት ከሌሎች ክልሎች በተለየ ሁኔታ ከትንበያው ዝቅ ብሎ ተገኝቷል በሚል በቀድሞ የፓርላማ አባላት በቀረበው ቅሬታ ላይ ኮምሽኑ ፍተሻዎችን ቢያደርግም፣ አዲስ የቀረበውንም ሪፖርት አንዳንድ የፓርላማ  አባላት ሳይቀበሉት ቀርተዋል።

የብአዴን ሊቀመንበር እና የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን በአሁኑ ጊዜ የአማራ ህዝብ ቁጥር 19 ሚሊዮን መድረሱን፣ ከዚህ ቀደም የአማራ ህዝብ ቁጥር በ 1 ነጥብ 73 በመቶ ብቻ እያደገ መሆኑ የተገለጸው በስህተት መሆኑን እንዲሁም  ጥናቱ በጥንቃቄ ተካሂዶ በአዲሱ ጥናት መሰረት የአማራ ህዝብ ቁጥር 2 ነጥብ 4 በመቶ ማደጉን ለፓርላማ አባላቱ ተናግረዋል።

በክልሉ ውስጥ የሚታየው የህዝብ መፈናቀል ከዚህ ቀደም በጥናቱ ውስጥ አለመካተቱን የገለጡት አቶ ደመቀ፣ በአዲሱ ቆጠራ የተፈናቀሉ ሰዎች መካተታቸውን አስረድተዋል። ጥናቱን እንደገና ለማካሄድ ከመንግስት በተሰጠው ትእዛዝ መሰረት ተግባራዊ መደረጉን፣ አሁኑ ጥናት በጥንቃቄና ግልጽነት በተሞላበት መንገድ መሰራቱን አክለዋል።

የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ሳሚያ ዘካሪያ እና አቶ ደመቀ ቀድሞውንም ችግሩ የተፈጠረው ትንበያ ላይ እንደነበረ በሰፊው አስረድተዋል።

የአቅራቢዎችን ገልጻ ተከትሎ አቶ ሙጬ የተባሉ የፓርላማ አባላት የጥናቱን ውጤት እንደማይቀበሉት ገልጽ አደረጉ። ጥናቱ አሉ አቶ ሙጬ  ” የህዝብና ቤት ቆጠራ ኪሚሽን ከዚህ ቀደም የአማራ ህዝብ ቁጥር የቀነሰው ህዝቡ በበሽታ ስላለቀ ነው በማለት ለዚህ ፓርላማ ተናግሯል። ሰዎቹ በምን ሞቱ ስንላችሁ ደግሞ በኤድስ ብላችሁ መለሳችሁልን። ይህ ስህተት ነበር። የሞቱ ምክንያት ወረርሽኝ፣ ጦርነት ወይም ሌላ ሊሆን ይችላል፤ በዚህ ጊዜ ስለዚያ ጉዳይ አንስቶ መነጋገሩ ፋይዳ ለውም። የህዝቡ ቁጥር የቀነሰው በ ሞት ነው ብላችሁ በቀላሉ መደምደም ችላችሁዋል፣ እንዲህ በማለታችሁ  ስህተት ሰርታችሁዋል ህዝቡን ይቅርታ ልትጠይቁ ይገባል።” ብለዋል።

ተወካዩ አክለውም ” የአማራ ህዝብ ከሌላው ክልል ህዝብ ለብቻው ተነጥሎ የኤድስ ቫይረስ አልተወጋም። እንደዚህ ብላችሁ መናገር አልነበረባችሁም። የአማራ ህዝብ በ1 ነጥብ 7 በመቶ እያደገ ነው ብላችሁ ትናገራላችሁ፣ ይሄ የህዝብ ቁጥር እድገት ቀንሶባቸዋል በሚባሉት በስካንደቪኒያ አገራትም አልታየም። ” ካሉ በሁዋላ ” የአማራ ህዝብ ባለፈው ጊዜ በ1 ነጥብ 7 አደገ ማለታችን ስህተት ነበር ካላችሁና  ትክክለኛ እድገቱ  2 ነጥብ 4 ነው ካላችሁ እናንተው በሰጣችሁን መሰረት 969 ሺ የአማራ ህዝብ ላለፉት 6 አመታት ያለበጀት እንዲኖር ተፈርዶበት ነበር ማለት ነው። እነዚህ ሰዎች ላለፉት 6 አመታት ዳቦ አልበሉም ወይም ካገሪቱ ዳቦ እንዲበሉ አልተደረገም ነበር ማለት ነው። ይቅርታ ልትጠይቁ ይገባል ብለዋል።

ሌላው ተናጋሪ ደግሞ እናንተ በአቀረባችሁት አዲሱ የእድገት አሀዝ ቢሰላ የአማራ ህዝብ ቁጥር 22 ሚሊዮን ይሆናል እንጅ 19 ሚሊዮን ሊሆን አይችልም፣  ስለዚህ አሁንም ያቀረባችሁት ሪፖርት ትክክል አይደለም አልቀበለውም ብለዋል።

ብቸኛው የአንድነት ፓርቲ ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ በአዲስ አበባ ህዝብ ቁጥር ላይ የቀረበውን አዲስ አሀዝም ሳይቀበሉት ቀርተዋል።

ማእከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የኢንተር ሴንስዋል ሰርቬይ የስነሕዝብ ጥናት በአማራ ክልል በ4 ሺ 322፣በአዲስአበባ በ7 ሺ 576 ፣በሶማሌ ክልል በ7 ሺ 826 የቆጠራ ቦታዎች በሚገኙ ለናሙና በተመረጡ ቤተሰቦች ላይ አምና ጥናት አካሂዶ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር  በ2004 ዓ.ም ወደ 82 ነጥብ 6 ከፍ ማለቱን፣ የአማራ ሕዝብ ቁጥር ከ17 ሚለዮን 100ሺ ወደ 19 ሚሊዮን 2 መቶ ሺ ማደጉን የአዲስአበባ ሕዝብ ከ2 ሚሊዮን 6 መቶ ሺ ወደ 2 ሚሊዮን 9 መቶ ሺ ማደጉን መግለጹ ይታወቃል።

በመብራት ችግር ምክንያት ከባድ እንዱስትሪዎች ስራ እያቆሙ ነው

ኢሳት ዜና :- በሃገሪቱ የሚገኙ ዋና ዋና የሲምንቶ ፋብሪቻዎች በመብራት ሃይል እጥረት ምክንያት ስራ ለማቆም ወይም ምርታቸውን ለመቀነስ መገደዳቸው ታውቋል።

አቢሲኒያ ፣ ናሽናል፣ ሙገር እና ደርባን ሲምንቶ ፋብሪካዎች በመብራት ችግር ሳቢያ የምርት ሰአታቸውን ከመቀነስ ጀምሮ ለተወሰኑ ቀናት ስራ ማቆም ጀምረዋል። ሌሎች ፋብሪካዎች ደግሞ መብራት ቆጥበው እንዲጠቀሙ የሚያሳስብ ደብዳቤ ከመብራት ሀይል ደርሶአቸዋል። አንዳንድ ፋብሪካዎች ጄኔረተሮችን ለመጠቀም መገደዳቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

መብራት ሀይል የኤልክትሪክ ሀይል ለጅቡቲ መሸጥ መጀመሩ ይፋ መደረጉ ይታወቃል። ሱዳን፣ ኬንያና የመንም እንዲሁ የኤልክትሪክ ሀይል ለመግዛት መስማማታቸው በመንግስት የመገኛ ብዙሀን ይፋ ቢደረግም በአገሪቱ ያውም በክረምት ወራት በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል የመብራት መጥፋት በተደጋጋሚ መከሰቱ የመንግስትን ፖለሲ ጥያቄ ውስጥ ከትቶታል ሲል ዘጋቢያችን ከአዲስ አበባ ገልጿል።

መቀሌ የትግራይ ሰማአታትን አክብራ ዋለች

ኢሳት ዜና :- በደርግ ዘመን በአየር ድብደባ የሞቱ የሀውዜን ነዋሪዎች እና ታጋዮች ለ5ኛ ጊዜ በመቀሌ ከተማ ታስበው ውለዋል።

የመንግስት የመገናኛ ብዙሀን እንደዘገቡት በሀውዜን በደረሰው ጭፍጨፋ ከ2500 በላይ ሰዎች ተገድለዋል፤ በትጥቅ ትግሉም ወቅት 40 ሺ በላይ የህወሀት  ታጋዮች ተገድለዋል።

የክልሉ ፕሬዚዳንት አባይ ወልዱ ወጣቱ ትውልድ የሰማእታቱን አላማ ከግብ ለማድረስ እንዲረባረብ አሳሰበዋል።

በሀውዜን ለደረሰው ጭፍጨፋ የደርግ ባለስልጣናት ብቻ ሳይሆኑ ጭፍጫውን ያቀነባበሩት የህወሀት ሰዎችም ተጠያቂ መሆን አለባቸው በማለት የቀድሞው የህወሀት ታጋይ አቶ ገብረመድህን አርአያ መናገራቸው ይታወሳል።

ESAT 

posted by Tseday Getachew

Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: