Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

የአባይ ወንዝ ህዳሴ ግድብ ትርፎች፤ ቦንድ፣ ዕዳ፣ አፈር መዛቅ፣ የጦር ዛቻ

በዘውገ ፋንታ

መግቢያ

“የለም፣ አባይማ ይገደብ” በሚል አርዕስት ስለ አባይ ወንዝ ግድብ መቶ አለቃ አያልሰው ደሴ የሰጡትን አስተያየት አንብቤዋለሁ። ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነው በዚያ የተሰጠው አስተያየት ነው። መቶ አለቃ አያልሰው ደሴ በክብር የሚጠሩ ኢትዮጵያ ካለቻቸው አንዱ ጀግና ሰው ናቸው። አገራቸውን ያገለገሉና ጀብድነታቸው ጎልቶ የሚነገር መሆኑን፣ ሻለቃ ጌታቸው የሮም “ስም ከመቃብር በላይ” የተባለውን መጽሐፍ ለሳቸውና ሌሎች መታሰቢያ ማድረጋቸው አንዱ ታላቅ ምስክር ነው። ስለዚህ ከዚህ በታች ያለው አጭር አስተያየት ይኽን ክብራቸውን በመጠበቅ ነው።

አርዕስቱ ሁላችንንም የሚያነጋግር ስለሆነ፣ ያለኝን ጠንካራ የአስተያየት ልዩነት በድፍረት ሳይሆን አሁንም በአክብሮት ለመግለጽ እፈልጋለሁ። በዚች አጭር ጽሑፍ በቅድሚያ ለመግለጽ የምሻው፣ የአባይ-በለስ ወንዝ ግድብን ሁለቱም መንግሥቶች ከወደቁበት አዘቅት ውስጥ ለመነሳት ጊዜ መግዣ የፖለቲካ-ግድብ መሆኑን ነው። ሕዝቦቻቸው የጠየቋቸውን ዲሞክራሳዊ አስተዳደር ስለነፈጉ፣ ከገጠማቸው የፖለቲካ ችግር ለመሸሻ የፈጠሩት ውዥግብ እንጂ የወያኔው መንግሥት እንደሚቀላብደው ድህነትን ለማጥፋት አለመሆኑን አያሌ ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ። በቴክኒክ ወይም በገንዘብ እጥረት ካልቆመ በስተቀር፣ ስራው ቀጥሎ ግድቡ ከተሰራ፣ ዋናውና ሙሉ ተጠቃሚዎቹ ሱዳንና ግብጽ እንጂ ኢትዮጵያ እንደማትሆን የግድቡ አላማና ዕቅድ ያመለክታል። ስለዚህ፣ የሚነፍሰው የጦርነት ዛቻና ሴራ ሆነ ተብሎ ሕዝብን ከተነሳበት አላማ ለማዘናጋት እንደሆነ መታወቅ አለበት። ግብጽ የምትነዛው የጦርነት ዛቻ የወያኔ ውድቀትና ስንብት የማያዘገይ ስለሆነ፣ ኢትዮጵያኖች በተስፋ የሚጠብቁትን አስፈላጊ ለውጥ የሚረዳ እንጂ የሚያጨናግፍ አይሆንም። ግን ግብጽ ጦርነት ለመጀመር ምክንያትና አቅም ፈጽሞ የላትም። ግድቡን ለማፍረስ ከሆነ የሚጥለቀለቀውና የሚወድመው የሱዳን ሮሳሪየስ ግድብና በመቶ ሺህ የሚቆጠረው ሰፋሪው ሕዝብ፣ እንዲሁም የተዘረጋው ሰፊ ልማትና የኤሌትሪክ ኃይል እንጂ በኢትዮጵያ አንድም ቤት፣ አንድም ሰው፣ አንድ ማሳ አይጎዳም። በዝግ ቢሮ አድማ ለማድረግ ሲወያዩ የነበሩት የግብጽ ባለስልጣኖች በገጻቸው ላይ ብዙ መንገላታትና ባይተዋርነት ይታይባቸው ነበር። ምስጢር የተባለው ውይይት በማግስቱ በገባያ ተነዝቷል። እነዚህ ባለስልጣኖች በውይይታቸው ላይ ያሳዩት የዕውቀት ጥልቀት የሰው ልጅ ጥበብ መለኪያ ቢሆን፣ የወያኔው ፖሊት ቢሮ ተመጣጣኛቸው ነው። ግብጽ በግድቡ እንደ ሱዳን አትራፊ ናት። ግብጽ የኢትዮጵያ ወንዞች ውሃ፣ የእርሻ ምርጥ ለም መሬት፣ አሁን ደግሞ ለልማቷ የምትሻውን ኤሌትሪክ ኃይል ወያኔ ሰርቶ ሊያቀብል ነው። ስለዚህ፣ ይኼን የለገሳትን የወያኔ መንግሥት በስልጣን ለማቆየት ተጎጂ መስላ ለመታየት ትፎክራለች። የወያኔውም መንግሥት ግብጽ ጦርነት እያቀደች ነው እያለ ተላላዎቹን ወይም ተገኖቹን ዳንኪራ እያስመታ ነው። ኢትዮጵያ የአባይ-በለስን ወንዝ ውሃ አላቆመችም። ከግድቡ ባህር የሚከማቸውን ደለል በየጊዜው በመዛቅ የሱዳኑን ሮሳሪየስ ግድብ ከደለል ጉዳት ነጻ ልታደርግ ነው። አፈራችንን አስቀረን እያለ የሚፎክረው ባይተዋል፣ ኢትዮጵያ አንድ ቁና አፈር ለጥቅሟ አይውልም።

የፖለቲካው-ግድብ

መቶ አለቃ አያልሰው ደሴ “የለም፣ አባይማ ይገደብ” በሆነ አርዕስት ያቀረቡትን ሀሳም ተመልክቸ ስለ እሳቸው ባላውቅ ኖሮ የወያኔ ካድሬ ልሳን አርጌ በመቁጠር አልፈው ነበር። በዕርግጥ አርዕስቱ የሚከብድ መልዕክት አስተላልፏል። “ባርኬዋለሁ ይሁን!” የሚል ስልጣን የተጫነበት መልዕክት መስሏል። ስለ ግድቡ ችግር የተነገረውን አሳሳቢ ሁኔታ ሁሉ ቁምነገር የሚያሳጣ አባባል ነው። የፖለቲካ-ግድብ ችግር ቢባል መሳይነት አለው። የወያኔውን መንግሥት ተጻራሪ የሆኑትን የፖለቲካ ጎራዎች አወሳሳቢ አቋም ገጠማቸው ማለት ይቻላል። የተቀዋሚው ኃይል ባልሆነ አቋም ተከፋፍሎ እያለ ይኽ ደግሞ በይበልጥ የሚሰበጣጥረው ይሆናል። ስለዚህ በትክክለኛ ጥናት ምርምር ጉዳቱንና ጥቅሙን ለይተው ያቀረቡትን መርምሮ የተቀዋሚው ፖለቲካ ጎራዎች የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚጠቅመውን አቋም መያዝ ይገባቸዋል። የኢትዮጵያን ደህንነትና ሙሉ ጥቅም የሚጠብቁት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችና ድርጅቶች ሁሉ አገር አጥፊ የሆነውን የወያኔው መንግሥት በልማት ስም የሚያደርገውን ጥፋት መቋቋም ይገባቸዋል። በተናጠል ለወያኔ መደለቂያ የሚወረወረው የግል ውዳሴ የአንድ ሰው ዕንከን ብቻ ሳይሆን የሰፊው ተቃዋሚ ሕዝብ ልሳን መስሎ ሊታይ ይችላል። ክቡር መቶ አለቃ አያልሰው በጽሑፋቸው ውስጥ የብዙዎቹን በግድቡ ዕቅድ የተቃወሙትንና የሚደግፉትን ጽሑፎች ጠቅሰዋል። በግድቡ ላይ እኔ ተንትኘ የጻፍኩትን ጽሑፍ እንዳላዩት ተረድቻለሁ። ያም አስደስቶኛል። ምክንያቱም ጽሑፌን ቢጠቅሱት ኖሮ ከሌሎቹ ጋር አጣምረው እንደጣሉት በመረዳት ይህን ጽሑፍ አልጽፍም ነበር። የጻፍኩትን አንብቡ ብዬ ለመጠየቅ ብጨነቅም፣ ለሳቸው አስተያየት መልስ ይሆናል ብዬ ስለማምን እዚህ ልዘረዝር ስለማልችል ወደዚያው ጽሑፍ ባመለክታቸው ተገቢ ይመስለኛል። ፈጽሞ ሊሆን የማይችለውን የግብጽ ጦርነት ምክንያቱን በዚያ ጽሑፍ ውስጥ ተገልጿል።

የግድቡ ስራ ብዙ ስነጥበቦችን ያካተተ ስለሆነ፣ በዚሁ አንጻር፣ እጅግ በተወሳሰበ ቴክኒካል ጉዳይ ላይ መሪ ሀሳብ ለማቅረብና ለመስጠት አያሌ ምርምሮችንና ጥናቶችን እንደሚጠይቅ ግልጽ ነው። ዳሩ ግን “የአባይ ወንዝ ውሀችንን እንጠቀም። አባይ የሚዎስደውን አፈር እናስቀር!” በሚል በጎ ስሜት፣ ግን በባዶ ድንፋት ተነሳስቶ ወያኔን መደገፍ ጥፋት ላይ ያደርሳል። ወያኔ በአሁኑ ጊዜ ከዚህ ውጥንቅጥ ሁኔታ ቢላቀቅ የገንዘቡ ምንጭ ባይሆን ኖሮ የበለጠ ደስታው የነሱ ይሆን ነበር። ወያኔ ተስፋውን የጣለው “ቢበላሽም፣ ቢያምርም በናንተ ወያኔ መንግሥታችን! ለናንተ ዳግም ባድሚ እንሄዳለን” ከሚለው አካል ሕዝብ ላይ ነው። ከዚያ ውጭ አውቆ ተላላ የሆነውና የለየለት የወያኔ ኮቴቴና ካድሬ በእንደዚህ ጉዳይ ላይ መቆጠር አይገባቸውም። እውነተኛ ግድብ የረጅም ጊዜ ሰፊ ጥናትና ምርምር የሚጠይቅ ነው። ሟቹ መለስ ዜናዊ የአረቦች ችግር ሲጀመር ግድቡን ምናልባት በጥቆማ ወይም እንዲጸነስስ ተገዶ ስራውን በጣሊያኖች አጣድፎ አስጀመረ። ግድብ በዚህ መልክ ተወጥኖ አይሰራም። እንኳንስ በቢሊዮን የሚቆጠር ወጭ ቀርቶ በትንሽ ሚሊዮን ዋጋ የሚሰራ ግድብ በዚህ መልክ ተሰርቶ አያውቅም። ግድብ ሲጨናጎል የሚያመጣው ጉዳት በቀላሉ ሊተመን ስለማይችል፣ አስተማማኝ ውጤት እንዲኖረው ሰፊ ጥናትና ምርምርን ይጠይቃል። ግድብ የሚያመጣው ብዙ ጉዳት ስላለ ያም በብዙ ጥናት መታወቅ አለበት። የግድብ ጥቅሞች ዕቅዱ እንዳይቀጥል ወይም እንዲሰረዝ ወሳኝ ናቸው። ዕቅዱ ለብዙ ጥያቄዎች መልስ አልተገኘለትም። የዓለምን የፖለቲካ ሁኔታ ማወቅና መረዳት ያስፈልጋል። መቶ አለቃ አያልሰው ደሴ በዚህ ላይ ሰፊ ልምድና ዕውቀት እንዳላቸው በየጊዜው የሚያቀርቡት ጽሑፎች ይመሰክራሉ። ሆኖም ግን፣ በህዳሴው ግድብ ላይ የሰጡት ድጋፍ ሊሎች ለአለው የቴክኒካል ጉዳዮች ጥያቄ ተገቢ ቦታ አልሰጡትም። ሰፊው ወገን የሚጠቅመውንና የማይጠቅመውን እቅድ ለይቶ አውቆ አቋሙን እንዲይዝ ለማድረግ ሰፊ ውይይትና የሀሳብ ልውውጥ እንዲኖር ያለንበት ውዥንብር ሁኔታ ያስገድዳል። ስለዚህ ድርጅቶች፣ የሬድዮና የፓልቶክ አዘጋጆችና አቃቢዎች እንዲያስቡበት ይች ማሳሰቢ እንድትሆን ተስፋ አደርጋለሁ።

“የአባይ ወንዝ ህዳሴ ግድብ፥ ለማንና ለምን ጥቅም”(ዘውገ ፋንታ)

http://ecadforum.com

posted by Tseday Getachew

 
 
Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: