Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

የሰማያዊው ፓርቲ ሰልፍ ሰሞኑን አነጋጋሪ ሆኖዋል፤ ገናም አነጋጋሪነቱም ይቀጥላል )ሰላማዊ ሰልፍን አስመልክቶ ዶ/ር መራራ ጉዲና ቆይ ለእኛ እንቢ የተባለው ሰልፍ እንዴት ለእነርሱተፈቀደ?

 

merera_gudina

የሰማያዊው ፓርቲ ሰልፍ ሰሞኑን አነጋጋሪ ሆኖዋል፤ ገናም አነጋጋሪነቱም ይቀጥላል። መድረክን በተለይም ደግሞ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ እና ዶ/ር መራራ ጉዲና የሰጡትን አስተያየት በተመለከተ የምጽፈውን ነገር አሰበኩኝ እና ብዕሬ ልተፋብኝ የምትችውን የቃላት ውርጅብኝ በመፍራት ላልፋቸው ወደድኩኝ…. ቢያንስ እነዚህ ሰዎች ስለእኔ እና ስለራሳቸው ሲሉ ደክመዋል እና እግዚአብሔር ድካማችሁን ይቁጠርላችሁ፣ በቁማችሁ ኢትዮጵያ ነጻ ወጥታ ለማየት ያድላችሁ በማለት ለመመረቅ እወዳለሁኝ። ደግሞ በተለያዮ ጊዜአት የሚያነሱዋቸውን አተያየት በተመለከተ ሰምቶ እንዳልሰማ ቅር ተሰኝቶ ቅር እንዳልተሰኘ በመሆን ዝም ብሎ ማለፉንም አልወደድኩትምና የማደርገውን አሰብኩኝ ለጥቂት ጊዜም….ምን ላድርግ ይሆን? በማለት እያሰብኩ…እያወረድኩኝ… እያጠነጠንኩኝ ሳለ በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ ዮኒቨርስቲ ተማሪ እያለሁኝ ዶ/ር መራራ ጉዲና ስለ ግል ሕይወታቸው ፣ ስለ ቤተሰባቸው እና ስለ አጠቃላይ ስለ መላው እምነታቸው ከተወሰንን የዮኒቨርስቲው ተማሪዎች ጋር በመሆን አዘውትረው መኪናቸውን ከሚያቆሙበት ስፍራ ሄደን የተለያዮ ጥያቄዎችን ጠይቀናቸው…. ዶ/ር መራራ ግልጽ እና ተግባቢ ሰውን አቅራቢ የሆኑ ሰው ናቸው እናም በወቅቱ ለጥያቄዎቻችን ሁሉ ያገኘነውን ምላሽ አልረሳውም….. አንዳንዱ ምላሻቸው በተለይ ቤተሰብን፣ ትዳር እና ልጆችን በተመለከተ የዶ/ር መራራ መስዋዕትነት ትልቅ መሆኑን አስገንዝቦኝ ነበረና ነው። ምንም እንኳን አሁን ሰማያዊዎቹን በተመለከተ የሰጣችሁት አተያየት ባልስማማም እናንትን ከልቤ ማክበሬን በመግለጽ ወደ ፍሬ ነገሬ ወይ ወደ ፍሬ ከርስኪዮ ልግባ ( በቅንፍ ለእኔ ፍሬ ነገር የሆነው ለሌላው ፍሬ ከርስኪ ቢሆንስ ብዮ ነው)።

ሰላማዊ ሰልፍን አስመልክቶ መራራ ቆይ ለእኛ እንቢ የተባለው ሰልፍ እንዴት ለእነርሱ ለሰማያዊዎቹ መሆኑ ነው ተፈቀደ? ብለዋል እናም ጣቶቻቸውን ወደ ወያኔም ወደ ሰማያዊዎቹም ቀስረዋል…..በአገራችን የልማድ አባባል አመልካች ጣትን ወደ ሌላው ሲቀስሩ የተቀሩት ጣቶች የሚያመላክቱት ወደ ራስ ነውና ሰልፉ የተከለከለበትን ምክንያት በተመለከተ ራስንስ መፈተሽ መልካም አይለምን? እናም ወዳጆቼ ነገሩ ያለው ሰልፉን ከሚፈቅደው ወይንም ስለ ሰልፉ ከሚጠየቀው ከወያኔ ብቻ ባይሆንስ? ነገሩ ያለው ከጠያቂውስ ቢሆን? ለምሳሌ ወያኔ ፈቃድ አልሰጥም ሲል ይሕውላችሁ ይህ ጨቋኝ መንግስት ፈቃድ አልሰጥም አለኝ አይገርማችሁም? በማለት ከፍተኛ ጩኸት በመፍጠር ሃላፊነትን ከራስ ላይ እያወረዱስ ቢሆን? እኔ ባለኝ መረጃ መሰረት እነይልቃል ሰልፉ የተፈቀደላቸው በግድ ነው፤ እንዴት? ሰማያዊዎቹ የሰልፍ ለፍቃድ ለማግኘት የሚያስፈልገው ማሳወቅ ብቻ ነው ….. ሕጉ የሚለው አሳውቁ እንጂ እስኪፈቀድላችሁ ዝም ብላችሁ ጠብቁ አይልም በማለት ለማሳውቅ ሄዱ….። እናስ? ለማሳወቅ ሲሄዱ ብልጡ ወያኔ ስለ ሰልፉ አላውቅም ለማለት ደብዳቤውን አልቀበልም ማለት.. ይህችን “ አኳኩሉ” ጨዋታ ድሮ እናቃታለን አሉላቹሃ እነ ይልቃል። ስለሆነም ምስክሮችን በማደራጀት ስብሰባ አስተባባሪው የመንግስት ክፍል በመሄድ እና በተገኘው የመገናኛ ብዙሃን ሁላ ነገሩን ለፈፉታ….እና ወያኔ እንዴት አልሰማሁም ይበል? በቃ ወያኔ ጨዋታው እንደተነቃበት ሲያውቅ ከተደበቀበት ብቅ ብሎ ……ማንም “ የአኳኩሉው” ጨዋታ ነጋ ሳይለው ነጋ አለላችሁ እና እፍርቱን ቀጠለ…የሚሰማው ሲያጣ በቃ ቀኑ ይቀየር አለ፤ ቦታውም ተቀየረ … የኮባው አደባባይም ከ250 ሺህ ሰዎች በሚልቁ ሰልፈኞች ደመቀ። ይህ ቁጥር ቀላል መስሎዋችሁ ከሆነ ተሳስታችሃል የድፍን የሓዋሳን ህዝብ እጥፍ ማለት ነው። ( እዚህ ጋር ለሰልፉ አስተናባሪዎች ዘፈን ልጋብዛቸው….አንበሳው አገሳን ልጋብዝ ወይንስ የቴዴን ታሪክ ተሰራን!!!.)…..( ሌላ ቅንፍ ከርዕስ ውጪ የራስ ትዝታ ይህችን የኮባ አደባባይ የተዋወቅሃት በልጅነቴ ከኳስ ሜዳ አካባቢ ለአስረኛው አብዮት ክብረ ባህል መጥቼ ነበር፤ ካልተሳሳትኩኝ በ1977 ዓ.ም ነበር… ሰማያዊዎቹ ከስንት ዓመታት በሃላ እዚሁ ኩባ አደባባይ ይዘውኝ ተሰየሙ….አምላክ ይባርካቸው!!!!)

አሁን መድረክን ….ከክብር እና ከታላቅ አክብሮት ጋር የምጠይቀው ጥያቄ አለኝ…. የሰላማዊ ሰልፍን የሚያክል አስደንጋጭ ጥያቄ ወያኔን ስትጠይቁ የወያኔን ባህሪይ እና የሰላማዊ ሰልፉን ሕግ ሳታውቁት ነውን? ብዮ ልጠይቅ አሰብኩኝ እና ይህንን ጥያቄ በመጠየቅ መምህሮቼ እና አባቶቼ የሆናችሁትን እንደመሳደብ ሆኖ ስለተሰማኝ ጥያቄይቱን ተውኳት…. ምን ላድርግ የዕድሜያችሁን ሩብ እና እኩሌታውን ያህል ወያኔን ለመሞገት ያባከናችሁትን ጊዜ እንደ ቀልድ እና ቀለል ነገር ልቆጥረው አልወደድኩም እና ነው። ወደ ጥያቄ ልግባ …ከዚህ በፊት የብርቱኳን ሚደቅሳን እስር በተመለከተ ሰላማዊ ሰልፍ ስታቀነባብሩ ወያኔ ሰላማዊ ሰልፉ ላይ መገኘት ያለበት የሰው ብዛት 200 ሰው ብቻ ነው ሲላችሁ እሺ ብላችሁ መስማማታችሁ በራሱ ሳስበው ዲሞክራቶች ስለመሆናችሁ ተጠራጠርኳችሁ…ቆይ ብርቱኳን ትፈታ የሚለውን ጥያቄ በመደገፍ የኢትዮጵያን 80 እና 90 ሚሊየኑን ሕዝብ ትታችሁ የፈረንሳይ ለጋሲዮን ለዚያውም የቀበሌ 12 እና የኢየሱስ ሰፈር ልጆች ቢወጡ እንኳን ቁጥራቸው ከ20000 በላይ ቢሆን እንጂ ከዚያ አያንስም ….እና ብርቱኳን የፈፀመች ወንጀል የለም ወንጀል ተፈፀመባት እንጂ ብለው የተቃውሞ ድምጻቸውን ለማሰማት ከእናንተ ጋር ሰልፎን ለመቀላቀል ቢወጡ አይ እኛ የተፈቀደልን ለ200 ሰዎች ብቻ ነው ብላችሁ ልትከለክሉ ነበርን? ወያኔ የሰልፉን ተሰላፊ ቁጥር የመተመን መብትክ አይደለም፣ ይህ ዲሞክራቲክ አካሄድ አይደለም ልትሉት ሲገባ አሜን ብላችሁ መስማማታችሁ እና ሰልፉን ማካሄዳችሁ ምን አልባት ከእነይልቃል ይልቅ እናንተ ለወያኔ ያደረ እና የተንበረከከ ስለመሆናችሁ አያሳይም ትላላችሁ? ነገሩ፣. ነገሩን ለማስረዳት ልትምሉ ልትገዘቱ ትወዱ ይሆናል፤ እውነቱ ግን ተግባራችሁ ራሱ በራሱ ቆሞ ስለእናንተ እውነቱን ይነግረናል፣ አሁን እነርሱ እነይልቃል የወያኔን ብልጣ ብልጥነት እምቢ በማለታቸው ….እምቢተኝነታቸው ይኸው አደመቃቸው… ነገ ዘብጥያም ሊያወርዳቸው እንዲችል እነይልቃል ይረዱታል…. ለዛም የጨከኑ ይመስላል።

ወዳጆቼ፦ ተንብርካኪ ማንነት ይዞ ፖለቲካ ውስጥ ራስን መዶል ተገቢ አይደለም እንደ ጥፋት የምቆጥረው በዚህ ማንነት ፖለቲካ ውስጥ መነከሩ ላይ ነው፣ ትውልዱን ተንበርካኪ እንዲሆን እና በትውልዱ ላይ ፍርሃት እንዲነግስ ቀን እና ማታ በማወቅም ባለማውቅ ከመስራት መጠንቀቅ ያሻናል።

ስለ መድረክ ባላባቶች እንዴ….ታሪክን ወደሃሊት እንምዘዘዋ……ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል እንዲሉ አሁን ይኸው በሰማያዊዎቹ ሰላማዊ ሰልፍ ግለት እስቲ ወደ 1997ዓ.ም እንጓዝ…. የ1997 ዓ.ምቱን ምርጫ ግለት ከፍ እንዲል እና እንዲሟሟቅ ያደረገው ማን ነው? ቅንጅት ወይንስ ህብረት/መድረክ? እንደሚታወቀው አብዛኛዎቹ ከዚህ በፊት ምርጫ ተሳትፈዋል። ምንም ግለት አልነበረም፤ ምናልባት በ1997 ምርጫ ልዮ ክስተት የባለ “ ቪ”ው ምልክት ቅንጅት መከሰት ነው። አሁን የህብረትን ምልክት አስታውስ ብትሉኝ ትዝም አይለኝም…..የ1997 ምርጫ ማዕበል እንዲቀጣጠል ያደረገው ነገሩን የተቀሰቀሰው በቅንጅቱ ነው። ይህንን እኔ ብቻ ሳልሆን ታሪክም ይናገረዋል፣ ህብረቱ እኔም አለሁበት ቢል የአይጢቲን ታሪክ ማስታወሱ በቂ ይመስለኛል። አንዲት አይጥ ከዝሆኑ ጀርባ ላይ ቂብ ብላ አብራ በድልድይ ላይ ስትሻገር … ድልድዮ ሲያረገርግ …አይጢቱ ወደ ዝሆኑ ዘንበል በማለት ድልድዮን አነቃነቅነው ያለቺው አይነት ካልሆነ በስተቀር …. ድልድዮ ያረገረገው በቅንጅት እና በሕዝቡ ነበር። ከቅንጅት ደግሞ የልደቱ/ክደቱ ኢ.ዴ.ፓ እና የሃይሉ ሻውል መ.ኢ.አ.ድ ከዚህ በፊት የነበሩትን ምርጫዎች የተሳተፉ ብዙም ለውጥ ያላመጡ ህብረ ብሔራዊ ፓርቲዎች ናቸው…በ.ቅንጅት ውስጥ የቅንጅቱ እምብርት የነበሩት የብርሃኑ ነጋ ቀስተዳማዎች እና የዓለማየሁ ረዳ ኢ.ድ.ሊዎች ነበሩ።

ከሁሉም በላይ በወቅቱ ለነበረው እንቅስቃሴ እምብርት የነበረው ብርሃኑ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም፤ ብርሃኑ የመደራደር እና የማግባባት ልማዱን ከዘሩ በደም የቀዳው ይመስል ወያኔን እያቄለ እና እያረጋጋ የሚዲያውን በር ውልል ብሎ እንዲከፈት ያሰደረገ ተቃዋሚዎች ያላቸውን ድርጅታዊ አሰላለፍ፣ ፕሮግራም ለመላው ህዝብ እንዲያስተዋውቁ ዕድል እንዲፈጠር ያደረገ ጀግናም ነው፤ በዚያን ወቅት ህብረቶች እኛ ስንት ዓመት ስንደክም ነገሩ ሳይከፈት እንዴት አሁን ይህ ሁሉ በር ይከፈታል በማለት ብርሃኑ ነጋን ከወያኔ ጋር አብሮ ያበረ የተባበረ ሰይጣን አድርገው ሲያወሩ፣ የወያኔ ጆሮ ጠቢ ነውም ሲሉን ነበር፤ እውነቱ ግን እንዲህ አልነበረም፤ ብርሃኑ ነጋ ከእነበረከት ስምኦን ጋር እንደሚተዋወቅ ራሱ በግልጽ አብሮም ጫካ በመውረድ ሲታገልም እንደነበር በመገናኛ ብዙሃን በሚደረጉ ክርክሮች ላይ አስታውቆ ነበር፤ ብርሃኑ ነጋ የሚደበቅበት ምክንያት ስላልነበረው ሁሉንም በግልጽ ያወራም ነበር። ለእውነት ትንሽ ጊዜ ብቻ ከሰጠናት እና ካስተዋልን እውነት ፍንትው ብላ ትወጣለች… እናማ እውነቱ ፍንትው ሲል 200 ሰዎች ሞተው ወደ ፓርላማ አንገባም ብለው ለመረጣቸውን ሕዝብ እነብርሃኑ ነጋ እና እነ ሃይሉ ሻውል ክብር ሲሰጡ…. የ200 ሰዎች ንጹሃንን ሞት ከቁብ ሳይቆጥሩ በደማቸው ላይ ተረማምደው ፓርላማ ተንደርድረው የገቡት እነ ህብረት እና ከቅንጅት ደግሞ እነ ልደቱ/ክደቱ ናቸው….እዚህ ጋር ፍሬን መያዝ ያስፈልጋል። ጥያቄ፦ ያኔ ለወያኔ ያደረው ማን ነው? ለወያኔ የተንበረከከውስ ማን ነው? እነርሱ ያለምንም ሕፍረት ወደ ፓርላማ ተንደርድረው ሲገቡ እነ ብርሃኑ ነጋ ግን ወደ እስር ቤት ተግዘዋል ፤ በወቅቱ የልደቱ/ክህደቱ ሸርታታነት ስለበረታ ህብረቶችን እናንተም ሸርታታ ናችሁ ያላቸው የለም…. በልደቱ/ክህደቱ እኩይ ተግባር የህብረቶች ሸርታታነት ተሸፈነ እንጂ ህብረቶች ከድሮውም ጀምሮ ሸርታታ መሆናችሁን አሳምረን እናውቃለን.. አቋም የሚባል እንዳልፈጠረባችሁ አስተውለናቸዋል።

ሕብረቶች በእነብርሃኑ ላይ ብዙ ዘመቱ…..የተሳካላቸውም መሰለ…..ቀስተዳመናን ይዞ የተከሰተው ብርሃኑ ከእስር ቤት የነጻነት ጎሕ ሲቀድ የተሰኘውን መጽሐፍ አስነበበን…… ይህ ሰው የቅንጅቱ እምብርት መሆኑን በድጋሜ በደንብ አስመሰከረ፤ አብዛኛዎቹ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ታስረው ጠዋት እና ማታ ካርታ እና ዳማ ሲጫወቱ (እውነታቸውን ነው ቃሊቲን እስር ቤት ካርታ ከመጫወት ሌላ አማራጭ ላይኖር ይችላል) አጅሬው ግን ተደብቆ ይጽፍ ነበር። ስሙ ብርሃኑ የመጽሓፉም ስም ሆነ የፖለቲካ ድርጅቱ ስም ከብርሃን ጋር የተያያዘ ነበር ቀስተዳመና፣.የነጻነት ጎህ ሲቀድ ይለናል። ሰውየው ግጥጥሞሹ ድንገተኛ አጋጣሚ ነው ወይንስ ነገሩ እንዲገጥም ታስቦበት ነው? በሉልኝ። (እዚህ ጋር ለብርሃኑ ነጋ ከፍ ያለ ምስጋናዮን ላቀርብ እወዳለሁኝ…….ደግሞ ይህቺን ውዳሴ አንብባችሁ ግንቦት ሰባት ብላችሁ ክሰሱኝ አሉዋችሁ፤ ስለ ክስ ሳነሳ…እነ ብርሃኑ ስንት እና ስንተ ክስ ሲመሰረትባቸው እነ በየነ ጴጥሮስ ከዶ/ር እና ከረዳት ፕሮፌሰርነት ወደ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ተሸጋግረዋል አይደል? እንግዲህ አስቀድሜ ተናግሪአለሁ የሰማያዊው ሰልፍ ብቀል አናቴ ላይ ወጥቶዋልም ብያለሁ። አንዱ ሲሾም አንዱ ዘብጥያ ሲወርድ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተመልክተናል፤ .ዘብጥያ የወረደውን የወያኔ አድር ባይ ሰላይም ነው ሲሉት ሹመት እና ሽልማት ከወያኔ የተለገሳቸው ደግሞ ታጋይ እና ጀግና ተደርጎም ሲቀቡት አይተናል.. በዚሁ አገር በእኛው ምድር፤ ወዳጆቼ የዚህ ነገር ሒሳብ ድምር ፣ ብዜት፣ ምኑም አልገባኝም።

ግን ግን……መድረኮች ለምንድን ነው ዝም ማለት ያቃታችሁ? እናንተ መስራት ያልቻላችሁትን እኮ ልጆቻችሁ መስራት መቻል አለባቸው ይህንን በራሱ እኮ ትልቅ ድል ነው። በተለይ እናንተ ሳትሞቱ በቁም እያላችሁ መፍጠር ያቃታችሁን ጉዳይ አዲሱ ትውልድ ፈጥሮት ሕዝቡም በመሃል አደባባይ ነጻነት…ነጻነት እያለ ሲጮህ ለተመለከተ እና የዕድሜውን ሩብ ለትግል እና ለነጻነት የሰዋ ሰው ሊደሰት እና ሊቦርቅ ሲገባው የሰጣችሁት አተያየት ስሰማ መገረምን ሞልቶኛል…..ምናለ ቢያንስ ዝም ብትሉ ….መጽሐፉ በምሳሌ 17፡28 ሰነፍ ዝም ቢል ጠቢብ ሆኖ ይቆጠራል ይለናል እና ዝም ብትሉ ኖሮ ጠቢባን መስላችሁ በተቆጠረችሁ…. እዚህ ጋር መስፍን ወልደማሪያምን ለማክበር ዕድል ስጡኝ….ትውልዱን ለመቀስቀስ ለመደገፍ የማይቦዝን ትልቅ ጋሼ…..ትልቅ አባት ነው…. አቦ ዕድሜክን እንደማቱሳላ ያርዝምልክ ከማለት ውጪ ምን ልለው እችላለሁኝ። ስለ አገሪቷ የተመኘከውን እና በልብህ የፀለይከውን በሕይወት ሳለህ ለማየት ያብቃክ… ምኞትህ መክሸፍ አይግጠመው። ከእኛም ስትለይ የጀግንነትህን ክብር ምድሪቷ አትንፈግህ…ለዚህ እኛንም አንተንም አምላክ ይርዳን አንተ ጠቢብ እና አስተዋይ ሰው ነህና። እንደመስፍን ያሉ አርቆ አስተዋይ በተፈጠሩበት አገር መድረኮችን በተለይ ደግሞ አንጋፋዎቹ የተመለከተ እንዲሁም የምትሰጡት አተያየት ያደመጠ ነገሩ ያረጀ ያፈጀ የማይረባ ከንቱ ይሆንበታል …. መድረኮች ከቻላችሁ በማስተዋል ተረጋጉ፣ መረጋጋት ካልቻላችሁ ደግሞ ዝም በሉ። ዝም አንልም ካላችሁ ግን ያው ይህ ድንጋይ ነገር ነው ብለን ወደመረገጥ መወርወራችን አይቀሬ ነው።

ወደ ሰማያዊዎቹ እና ወደ ሰልፉ ስመለስ በሰማያዊ ፓርቲ ስር የተሰባሰቡት ልጆች አንድም የወያኔን መሰሪ ባህሪይ በቅጡ የተረዱ ይመስለኛል፤ ይህንን ለማለት ካነሳሳኝ ምክንያቶቼ መካከል የሰላማዊ ሰልፉዋ ቀን አንዷ ናት። ለሰላማዊ ሰልፉ የመረጡዋት ጊዜ በራሱዋ ቅድስት ቀን ነበረች፣ ለአፍሪካዊያን በተለይም ለኢትዮጵያ የተቀደሰች ቀን፤ ይህችን ቀን ቀድመው ቅድስነቱዋን ስለተረዱ ሰማያዊዎቹ ቀኒቷ ላይ ቅዱስ እና ሰላማዊ አሳብ ይዘው ከተፍ አሉ። እነ አባቶቼ መራራ እና በየነ ግን ስንት እና ስንት ቅድስት ቀናት በአይናቸው ስር ሲያሳልፉ ሳይጠቀሙባቸው ከርመው፣ ስንቱን የአፍሪካ ስብሰባ ሲያልፍ ችላ ብለው ተመልክተው፣ ዛሬ እንዴት ለእኛ ተከልክሎ ለእነርሱ ይፈቀዳል? በማለት ጠየቁ
እንደ እኔ እምነት ይህ ጥያቄ ተገቢ ጥያቄ ነው። እንዴት እነዚያ ተከለከሉ? እንዴት እነዚህ ተፈቀደላቸው? የተከለከሉት ሰዎች በፖለቲካው የከረሙ ፖለቲካም የሚያስተምሩ ሁሉ ናቸው፤ የተፈቀደላቸው ደግሞ ወደ ፖለቲካ ከገቡ ጥቂት በጣት ለዚያውም በአንድ ጣት ብቻ የሚቆጠር ዕድሜ ያላቸው እምቦቅላ ነገሮች ናቸው። የመድረክ ጥያቄ ተገቢነቱን በተመለከተ እኔ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ እስማማለሁ፤ የፖለቲካ ሰዎች የትላንቱን ድካም እና ብርታት አመዛዝነው ለተተኪው ትውልድ ጥንካሬአቸውን በማስተላለፍ በወቅቱ የሚገኘውን ዕድል ለመጠቀምም ሆነ ከፊታቸው የተደቀነውን ጋሬጣ ለመቀነስም ይረዳል የሚል እምነት አለኝ እና ነው። ነገር ግን መድረኮች ይህንን ጥያቄ ያነሱት ሌላውን ጥፋተኛ ለማድረግ እንጂ ለድካማቸው ለመማር አይደለም…. መድረኮች በተለይም ባለአባቶቹ እኛ ዳንኪራ ያልረገጥንበት መድረክ የተቀደሰ አይደለም የሚሉ ባተሌዎች ናቸው።ይህንን ባህሪያቸውን በ1997 ምርጫ ወቅት በቅንጅቱ ላይ በከፈቱት ክፉ ወሬም ታዝቤአቸው ነበር፤ አሁንም ይኸው ደግሜ በሰማያዊዎቹ ታዘብኩዋቸው።

ምንም እንኳን ለምን ለእኛ ሳይፈቀድ ለእነርሱ ተፈቀደ የምትለውን የመድረኮችን ጥያቄ ብወዳትም ድምዳሜውን ግን ከቶውኑ ልስማማበት አልችልም። ድምዳሜያቸው ፖለቲካ እና ፖለቲከኛም አይሸትም….ወያኔ ጠቅላዮ ከሞቱ በሃላ አናት የሌለው አውሬ ሆኖ ሳለ የሕዝብን ሙቀት ለመጨመርም ሆን ብሎ ሰልፍ የሚፈቅድበት ምክንያት ወይንም ከአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ ጋር ሰልፉን የሚያያይዝ ሞኝ ስብስብ እንደሆነ እኔ አላውቅም…ወያኔ መሰሪ እንደመሆኑ መጠን ፈሪም ነው በተለይ የሕዝብ ድምፅ እና ተቃውሞ ይፈራል፡፡ ይህ አይነቱን ድንጉጥ ማንነት ያላቸውን ግለሰቦች ያሰባሰበ የወያኔ ቡድን ሕዝብ እንዲቃወመው በተለይ ደግሞ የአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ ባለበት ወቅት ፈልጎ ነው የሚል መላ ምት ሊዋጥልኝ አይችልም። ነገር ግን ወያኔ በታሪኩ እንዲህ ያለውን የእሳት ጨዋታ የሚጫወትበት ተነሳሽነትም ፣ ሞራልም፣ ዝግጅትም የሌለው የመንደር ዋልጌ እና ዱርዮ ሰዎች የተሰበሰቡበት ስብስብ ከመሆኑም ከላይ ድንገት ድንገት ሕዝባዊ ተቃውሞ ሲገኝመው ምን አይነት እርምጃ ለመውሰድ እንደሚነሳ ይታወቃል። ይህንን ለመገንዘብ ሚያዚያ 10 ቀን 1992፣ የ1997 ምርጫን፣ በ1986 የአዲስ አበባ ዮኒቨርስቲውን የተማሪዎች ተቃውሞ ማስታወሱ ብቻ ይበቃል። ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ማዕበል በውስጡዋ ተሸክማ የምትጓዝ አገር ሆናለች፤ ለምሳሌ የሙስሊሞች እንቅስቃሴ ጠንካራ ደረጃ በደረሰበት በዚህ ጊዜ፣ የማህበረሰቡ ኑሮ የሚያማርር በሆነበት በአሁኑ ወቅት፣ የተማረ ሰው ዝቅ ብሎ ድንጋይ በሚፈልጥበት ሁኔታ፣ የሰው መብት፣ አፈናው፣ ስደቱ፣ እንግልቱ፣ በዘር ሐረግ ምክንያት መፈናቀሉ፣ በታሪካችን በከፍተኛ የውርደት ልክ ላይ በደረስንበት ዘመን ላይ ወያኔ ሰላማዊ ሰልፉን ለመፍቀድ አስቦ ነው ብሎ የሚያስብ መላምት በራሱ ስንኩል ትምስለኛለች፣ ከስንኩልነቷም ይልቅ ወያኔን ሁሉ በሁሉ የሆነ ገዢ ነው ብሎ የሚያምንን የፖለቲከኛ ማንንትም ታሳያለች።

የመድረክ ታላላቅ አዛውንቶች ለሰማያዊዎቹ ክብረ ከመስጠት ይልቅ ይህች አሳብ የወያኔ ናት በማለት ላለፉት 20 ዓመታት የነበራቸውን የትግል መስመር በግልጽ ለእኛም ያመላከተች ነች። እኔ እንደገባኝ ከሆነ እነርሱ በነበራቸው ሃያ ዓመታት እና ከዚያም በላይ ባፈጀው የትግል እንቅስቃሴ የሚሰሩትን ሁሉ የሰሩት ከወያኔ አንጻር ብቻ እንጂ እነርሱ ከቆሙለት የትግል መስመር እና ዓላማ አንጻር አለመሆኑን ያስገነዝበናል። የሰማያዊዎቹን ሰላማዊ ሰልፍ ለመረዳት አምልኮተ-ወያኔን እና ፍርሃትን ከልብ መሻር ያሻል። ይህ ሰልፍ የወያኔ አሳብ ናት ካሉ…ቀድሞውኑ ብርሃኑን ነጋን በእንዲህ ከጠረጠሩ እኛስ እነርሱን የማንጠረጥርበት ምክንያት ካለ ይህንን ጽሑፊን የሚያነብ ሰው ይንገረኝ። ይህንን እና ያንን ያደረገው ወያኔ ነው እያሉ ሲያወሩ ስመለከት እንደውም እኔ ከይቅርታ ጋር እነርሱን ጠረጠርኳው፣ ተመኮሮአቸውን እያወሩንስ ቢሆን? አልኩኛ፤ ደግሞስ የገብርኤል መገበሪያን የበላ ምን ያደረርገዋል እንዲሉስ ቢሆን?። ስለ ጥርጣሬዮ እዚህ ጋር ፍሬን ልያዝ.. ስለመድረክን መኳንንቶች ልጻፍ።

እኔ እንደታዘብኳቸው የመድረኮች መኳንንቶች ለሚያደርጉት የትግል እንቅስቃሴ ሁላ የወያኔን ይውንታ የሚጠባበቁ፣ ወያኔ የከፈተውን የፖለቲካ አውድ ብቻ ለመከተል ከራሳቸው ጋር ተማምለው የቆረጡ ሰዎች የተሰባሰቡበት ስብስብ ይመስለኛል። ወያኔ የከፈተላቸውን ቦይ ብቻ ተከትለው የሚፈሱ፣ የሰላማዊውን የትግል መስመር እምነት የሚያራምዱ ስብስቦች ናቸው። ሰማያዊውም ፓርቲ ሰላማዊ ትግልን የሚያቀነቅን ፓርቲ ነው። ልዮነታቸው የሚጀምረው መድረኮች መርሃ ግብር የሌላቸው ታጋዮች ሲመስሉ ሰማያዊዎቹ ግን እንቅስቀሴአቸውን በመርሃ ግብር ሸንሽነው እና ቀምረው የሚንቀሳቀሱ …መርሃ ግብራቸውን ለመፈፀመም ምቹ ነገሮችን እና አስገዳጅ ሁኔታዎችን የሚጠቀሙ የወያኔን መሰሪነት የተረዱ ይመስላሉ። በእርግጥ መድረኮችም ይህንኑ የወያኔ ባህሪይ የተረዱ ስለመሆናቸው በየመግለጫቸው ይሰማል፣ ልዮነቱ መድረክ ወያኔን ሁልጊዜ የሚያሸንፍ ጉልበተኛ በማደረግ ትግላቸውን ሲጀምሩ ሰማያዊዎቹ ግን ወያኔን ለማሸነፍ የወያኔን ደካማ ማንነት በመረዳት የጀመሩም ይመስላል። ሌላው እና ትልቁ ልዮነት መድረኮች ሕዝብ ተኮር ያልሆነ እና ሕዝብን ያላሳተፈ የባላባት መደቦች ሲሆኑ ሰማያዊዎቹ ግን ገና ከመነሻቸው ሕዝብ ተኮር አደረጃጀትን የተከተሉ፣ የሕዝብ ተሳትፎ ሃያልነት የተረዱ… ለዚህም አደረጃጀት የራሳቸውን አሰላለፍ ምቹ ያደረጉ ናቸው…መድረኮች ኑ እና አባል ሁኑን በማለት ጥሪ ሲያቀርቡ ሰማያዊዎቹ ግን ወደ ሕዝቡ በመውረድ እና በመስረጽ የሕዝቡን የልብ ትርታ በመረዳት የሚንቀሳቀሱ ናቸው።

ጽሑፌንም ሳጠቃልል…..ሰማያዊዎቹን በማወደስ ብቻ አልጠቀለልውም፤ ወያኔ የሚቃወመውን ሁሉ ወደ እስር ቤት ማጋዝ ልማዱ ነው። ስለዚህ ለወያኔ ምሱን እንስጠው ወያኔን መቃወም የሚፈልግ ሁላ ለመታሰርም ዝግጁ ይሁን። ዛሬ እነይልቃልን ድንገት ከየቤታቸው ለቅሞ ቢያስራቸው…. ነገ ብዙ ይልቃሎች…. ብዙ አቡበከሮች…… ብዙ እስክንድሮች …አንደ አሸን እና እንደ እንጉዳይ ወደ ትግሉ መድረክ ብቅ ልንል ይገባል።. ምናልባት ወደ እንደዚህ አለው ትግል ለመግባት ፍርሃታችን ይዞን ይሆናል….ላለመታሰር ብለንም ፈርተን ይሆናል….. አልገባን ይሆን ይሆናል ወይንም እውነታውን እየካድን ሊሆን ይችል ይሆናል እንጂ አሁንም የወያኔ እስረኞች ነን። ምናልባት ከእነ አቡበክር እና ከእነ እስክንድር ከእነ ርዕዮት ዓለሙ የሚለየን እኛ መዝገብ የማያውቀን እስረኞች እና ቤታችን የምናድር ግዞተኛ መሆናችን ብቻ ነው። እኛ ሁላችን ከፍርሃት በታች ተዘግተን ፣ ለፍርሃት ባሮች ሆንን ድፍን 21 ዓመታት አናታችን ላይ ዳንኪራቸውን እረገጡብን፣ በብዙ አዋረዱን ላላፉት 21 ዓመታት የፍርሃት ፣ የወያኔ የማስፈራሪያ ሰለባዎች ሆንን። አሁን ግን ሁላችን ከተሸሸግንበት ፣ የሞት ሽታ ከሸተተን መንደር ወጥተናል እና ወያኔ…በተራው ሊፈራ እና ሊደነግጥ ጀምሮዋል።

ወዳጆቼ በአዲስ አበባ ላይ የምንኖር ብቻ ቁጥራችን ከ2 ሚሊዮን በላይ የምንዘል በወጣት የዕድሜ ክልል የምንገኘ ሁሉ መዝገብ የሚያውቀው እስረኛ ለመሆን ብንፈቅድ እንኳን ወያኔ እኛን ሁላችንን ለማሰር አቅም አይኖረውም። በ1997 ዓ.ም በነበረው ታላቅ ትግል እንኳን ማሰር የቻሉት 50 ሺህ ሰው እንኳን አይሞላም፤ በፍርሃት በየቤታችን ተቀፍድደን ከምንታሰር በዘመናችን ትውልድ የሚዘከረው ታላቁ የኢትዮጵያዊያንን ትግል እንቀላቀል። ይህ ታላቅ ዘመቻ በእርግጥ ታላቁን የኢትዮጵያን ሕዳሴ ለመጀመር ፈር ቀዳጅ ይሆናል። አሁን ከፍርሃታችን ወጥተን ትልቅን እርምጃ ተራምደናል፤ ከዚህ በሃላ ተልሰን ወደፍርሃት ቀንበር መግባት አይገባንም። ወያኔ ምንም ሊያደርገን አይችልም፤ ምናልባት ሊያደርጉን ከቻሉ የሚችሉት እኛን ማሰር ብቻ ነው፤ ይህ ደግሞ በራሱ ትልቅ ድል ነው። 2 ሚሊዮን መዝገብ የነካውን እስረኛ መመገብ፣ ማስተዳደር፣ መጠበቅ በራሱ ወያኔን ያናጋዋል፣ ያፈርሰዋል። ስለዚህ ሰልፍ መውጣጣችንም ሆነ መታሰራችን ወያኔን ከተቀመጠበት የስልጣን ኮርቻ ሊያወርደው የሚችል ትልቅ ውሳኔ ነውና ወደፊት እንበል ይለይለት።

ድል ለመላው ሕዝብ

source/Beniam Solomon

posted by Tseday  Getachew

Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: