Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

የአባይ ኢትዮ-ግብጽ ጦርነት ወይንስ የነፃነት ትግላችን!

ግርማ ሞገስ

nile_basin_countries

አምባገነኖች ስልጣናቸውን ለማጠባበቅ አጋጣሚውን ሁሉ ይጠቀማሉ። ሰሞኑን የአባይን ግድብ አስታከው አምባገነኖቹ ህውሃት/ኢህአዴግ እና የግብጽ መንግስት መምታት የጀመሩት የጦርነት ከበሮም ከዚህ የተለየ አይደለም። የህዝባቸውን ብሄራዊ ክብር ስሜት ተቆጣጥረው የዲሞክራሲ ኃይሎችን ለማዳከም እና ስልጣናቸውን ለመጠጋገን የሚያደርጉት ድራማ ነው። ኢትዮ-ግብጽ ጦርነት አይቀሬ አይደለም። የግብጽ ዴሞክራሲ ኃይሎች ወደ ጦርነት አይሄዱም። የኢትዮጵያ ሰላማዊ ትግል ወታደር አይኑን ከነፃነት ትግሉ መንቀል የለበትም።

የአባይ ወንዝ የሚጓዝበትን ሽምጥ ሸለቋማ ክፍል የአዲሱ ግድብ አካል ቢደረግ ግድቡ ሰፊ ቦታ እንዳይዝ፣ ውሃው ለጸሐይ ብዙ ተጋልጦ እንዳይተን እና መጠኑ እንዳይቀንስ ይረዳል። የግድብ ግንባታ ወጪም ይቀንሳል። ይኽን ተፈጻሚ ለማድረግ ደግሞ የአባይን ወንዝ ለጊዜው አቅጣጫውን ማስቀየር ያስፈልጋል። ይኽ የግድብ ግንባታ ምህንድስና ሀ ሁ ነው። በዚህ እርምጃም የመጀመሪያዋ ተጠቃሚ ግብጽ እንጂ ኢትዮጵያ አይደለችም። ይኼን ሃቅ የግብጽ መሃንዲሶች ያውቁታል። አክራሪው የሞርሲ መንግስት ሳይቀር በልቦናው ያውቀዋል። ግብጽ የምትጠቀመው ከኢትዮጵያ ጋር ከመወዳጀት እንጂ ጸበኛ በመሆን እንዳልሆነ አለም ያውቀዋል። በቅርብ አልባራዳይ በአደባባይ ወጥቶ የግብጽ መንግስት ኢትዮጵያን ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል ያለውም ለዚኽ ነው። ኢትዮ-ግብጽ ጦርነት የለም። የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሰራዊት ከነፃነት ትግሉ መዘናጋት የለበትም።

የውሃው መጠንም አይቀንስም። ላብራራ። ከውሃ ኃይል (Energy) የኤሊክትሪክ ኃይል (Energy) ማመንጨት ቴክኖሎጂ ጥንታዊ በመሆኑ በሰፊው የሚታወቅ ጉዳይ ነው። ከአባይ ወንዝ ውሃ ኃይል (Energy) 5ሺ አራት መቶ ሜጋዋት ኤሊክትሪክ ኃይል (Energy) ማመንጨትም ውስብስብነት የለውም። ግብጽም ከአስዋን ግድብ የምታመነጨው 2 ሺ አንድ መቶ ሜጋዋትም የሚጠቀመው ዘዴ ተመሳሳይ ነው። በግድብ ሲሰበሰብ በውስጡ የታመቀ የውሃ ኃይል (Energy) ይገነባል። ውሃው ከግድቡ ሲለቀቅ ደግሞ አምቆት በነበረው ኃይል መዘውሮችን እየመታ የኤሌክትሪክ ኃይል ይሰጣል። መዘውሮችን የመታው ውሃ የት ሄደ? ወደ ሱዳን ከዚያ ወደ ግብጽ። የውሃው መጠን አይቀንስም። ይኼን ቴክኖሎጂ የግብጽ መሃንዲሶች እና ሳይንስትስቶች ያውቁታል። ይኽን ሃቅ የሙባረክን መንግስት በሰላማዊ ትግል ከስልጣን ካስወገዱ በኋላ በገፍ ኢትዮጵያን የጎበኙት የግብጽ ዴሞክራሲ ኃይሎችም ያውቁታል። ይኼን ቴክኖሎጂ የተባበሩት መንግስታት ያውቀዋል። የአፍሪካ ህብረት ያውቀዋል። የሞርሲ መንግስት እና የግብጽ አክራሪዎች ሁካታ መፍትሄው ዲፕሎማሲ ነው። ኢትዮ-ግብጽ ጦርነት የለም። የኢትዮጵያ ሰላማዊ ትግል ሰራዊት በህውሃት ጦርነት ድራማ መዘናጋት የለበትም። ለነፃነት የሚያደርገውን ትግል በጽናት አጠናክሮ መቀጠል አለበት።

ስለየትኛው ‘ውል’ ነው የምታወራው? ትምህርት የቀመሰው የኢትዮጵያ የዛሬ እና የነገ ትውልድ እንደማይቀበለው የግብጽ ፕሬዚዳንት ሳይቀር ልቦናው ያውቀዋል። የ‘ውሉ’ ሰነድ ይተጻፈው በኢንግሊዝ ሲሆን ግቡ የግብጽን እና የሱዳን ህዝብ እንዳይጠማ ማድረግ ሳይሆን በዚያን ዘመን በኢንግሊዝ አገር ተስፋፍቶ የነበረው የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ በጥጥ እጥረት እንዳይጠማ ማድረግ ነበር። እንግሊዝ በቅኝ ገዢነት በምታስተዳድራቸው ግብጽ እና ሱዳን ሰፊ የጥጥ እርሻ ነበራት። ቅኝ አገዛዝ ለዘላለም የሚኖር መስሏት የጥጥ እርሻዋ እንዳይጠማ የጻፈችው ሰነድ ነበር። የዛሬው አለም መሪ ነኝ ባይዋ  አሜሪካም ብትሆን የውሉን መናኛነት ታውቀዋለች። ሁለቱ በአፍሪካ ቁልፍ ሸሪኮቿ በአባይ ወንዝ የተነሳ ጦርነት እንዲሄዱ እና በአፍሪካ ቀንድ ሽብርተኛነት እንዲያገረሽ አትሻም አሜሪካ። ኢትዮ-ግብጽ ጦርነት የለም። የኢትዮጵያ ነፃነት ሰራዊት በህውሃት የጦርነት ከበሮ መታለል የለበትም።

የህውሃት/ኢህአዴግ መንግስት የህዝብ ድጋፍ እና ክብር ማግኘት ከፈለገ የጦርነት ከበሮ ከመምታት ፈንታ እሁድ ግንቦት 25 ቀን 2005 ዓመተ ምህረት ሰማያዊ ፓርቲ በጠራው ሰላማዊ ሰልፍ የተገኘው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ኃይል ለጠየቃቸው ጥያቄዎች አዎንታዊ መልስ መስጠት አለበት። ዐርብ ዐርብ ሳያሰልሱ ከአንድ አመት በላይ መብታቸው እንዲከበር ለሚጠይቁት ሙስሊም ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን አዎንታዊ መልስ መስጠት አለበት። በማን አልብኝነት የዘጋቸውን ፍኖተ ነፃነት፣ ፍትህ እና ሌሎች ጋዜጦች እንዲታተሙማድረግ አለበት። ከሬድዋን እና ሽመልስ ከማል ከመሳሰሉ ተራ አድርባዮች እራሱን ማጽዳት አለበት። ነፃ ምክር ነው!

የኢትዮ-ግብጽ ጦርነት አይቀሬ ነው ቢባል እንኳን የመለስ ዜናዊ ራዕይ ጠባቂው ህወሃት/ኢህአዴግ እምነት ተጥሎበት ጦርነቱን ብቻውን እንዲመራ መፈቀድ የለብንም። አድነት ፓርቲ፣ ሰማያዊ ፓርቲ፣ መኢአድ፣ የቀሩት የመድረክ አባል ድርጅቶች እና የቀድሞ ታዋቂ አገር ወዳድ የጦር መኮንኖች ከመንግስት ጋር በእኩልነት በጣምራ የሚመሩት የኢትዮ-ግብጽ ጦርነት ኮምሽን ማቋቋም የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ህወሃት ተዓማኒ አይደለም።

(girmamoges1@gmail.com)

http://www.goolgule.com

posted by Tseday Getachew

Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: