Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

ኦባንግ ለኃይለማርያም ግልጽ ደብዳቤ ላኩ – ለማሰር መጣድፍ እንደማያዋጣ አስጠነቀቁ

 

obang metho1

ባለፈው እሁድ በሰማያዊ ፓርቲ የተጠራውንና በሰላም የተጠናቀቀውን ሰላማዊ ሰልፍ በማስመልከት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ ለጠ/ሚ/ር ኃይለማርያም ደሳለኝ ግልጽ ደብዳቤ ላኩ፡፡ በደብዳቤው ላይ ኢህአዴግ ሰልፈኞቹንም ሆነ የፓርቲውን አመራሮች ለማሠር የሚያደርገውን ሃሳብ ከመፈጸም እንዲቆጠብ ማስጠንቀቂያ ልከዋል፡፡

አቶ ኦባንግ በደብዳቤያቸው ላይ በርካታ ጉዳዮችን የዳሰሱ ሲሆን በቅድሚያ ግን ጠ/ሚ/ር ኃይለማርያም ሠልፉን በመፍቀዳቸው ሊመሰገኑ እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡ ይህንንም በማድረግ ከቀድሞው መሪ መለስ እንደሚለዩና ምናልባትም ህዝብን ለማዳመጥ ፍላጎት እንዳላቸው ጠቋሚ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ምክንያቱንም ሲያስረዱ መለስ በእንደዚህ ዓይነቱ ሠልፈኞች ላይ የህወሓት አልሞ ተኳሾች ተኩስ በመክፈት እንዲገደሉ ማድረገቸውና የፓርቲ አመራሮችን ማሳሰራቸውን እንደ ማስረጃ ጠቅሰዋል፡፡

የሕዝብ ጥያቄ በአግባቡ ምላሽ እስካላገኘ ድረስ እንዲህ ዓይነቱ የታቃውሞ ሠልፍ እየቀጠለ እንደሚሄድ የተናገሩት ኦባንግ የሕዝብን ጥያቄ ማዳመጥና ተገቢውን ምላሽ አማራጭ መፍትሔ የሌለው ጉዳይ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ከዚህ ሌላ በአንዳንድ የኢህአዴግ አመራሮች ሠልፉ የጥቂቶች እንደሆነ ለማስመሰል የተወሰደው አካሄድ ፈጽሞ እንደማይሠራ ጠቁመዋል፡፡ በሠልፉ ላይ የታዩት ኢትዮጵያውያን ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ እንደሆኑና እነዚህም ክርስቲያን፣ ሙስሊም፣ የማያምኑ፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አረጋውያን፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ሥራ የሌላቸው፣ አካለ ስንኩላን፣ የኢህአዴግ አባላት፣ ተማሪዎች፣ ወዘተ መሆናቸውን በማስረጃ አስረድተዋል፡፡

ይህንን ዓይነት ሕዝባዊ ትዕይንት ላዘጋጁት የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች እንዲሁም ሰልፉን በሰላም ጀምሮ በሰላም በመጨረስ ጨዋነቱን ላሳየው ኅብረተሰብ በድርጅታቸውና በራሳቸው ስም ታላቅ አክብሮትና ምስጋና ያቀረቡት አቶ ኦባንግ ሜቶ እንዲህ ዓይነቱ ሠልፍ በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎችና ከተሞች ቢካሄድ ኖሮ ቁጥሩ እጅግ ከፍተኛና ውጤቱም ከዚህ የማይለይ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ በቅርቡም ይህንን ለማየት የሚቻል መሆኑን የጠቆመው ደብዳቤያቸው አቶ ኃይለማርያም እንደመሪ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉና በሕዝብና በመንግሥት መካከል የተፈጠረውን ልዩነት በምን ዓይነት ድልድይ እንደሚያገናኙት ጥያቄ በማቅረብ ይህንን የመወጣት ከፍተኛ ኃላፊነት እንደተደቀነባቸው ተናግረዋል፡፡

ትዕይንተሕዝቡን የጥቂቶች በተለይም የሙስሊሞች መጠቀሚያ እንደሆነ ለመናገር የሞከሩትን የኢህአዴግ አመራሮች ሊሄዱ ያሰቡት አካሄድ የተሳሳተ መሆኑን የጠቀሱት ኦባንግ በተለይ ሕዝቡን በሃይማኖት በመከፋፈል ሙስሊም ኢትዮጵያውያንን ለማግለል የተወሰደው አካሄድ የሚወገዝ መሆኑን በደብዳቤያቸው ላይ ጠቅሰዋል፡፡ ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር መሬትን ብቻ ሳይሆን በደምም አገራችንን እንደሚጋራ ያስረዱት የአኢጋን ዳይሬክተር ከዚህ ውጪ ግን ሙስሊሙን በማግለል በአሸባሪነት ላይ ጦርነት እያደረጉ ለማስመሰል በኢህአዴግ በኩል የተደረገው ሙከራ የምዕራባውያንን ልብ እንደማያማልል ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ባለፈው አንድ ዓመት ሙስሊሙ ኅብረተሰብ በሰላም ያደረገው የተቃውሞ ሠልፍ በራሱ ማስረጃ እንደሚሆን ጠቅሰዋል፡፡

ሠልፉ ከተጠናቀቀና መንግሥት ራሱ በሰላም መጠናቀቁን ካመነ በኋላ በሌላ ሁኔታ ሠልፈኞችንም ሆነ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችን ለማሰር የማስፈራሪያና የዛቻ ንግግር ከኢህአዴግ አመራሮች መሠጠቱ ፈጽሞ አግባብነት የሌለው መሆን የተናገሩት አቶ ኦባንግ ለጠ/ሚ/ር ኃይለማርያም የሚከተለውን ብለዋል፡፡ “የእርስዎ አስተዳደር እንዲህ ዓይነቱን እርምጃ የሚወስድ ከሆነ የበለጠ የህዝብን ቁጣ የሚያነሣሣ መሆኑን ላስጠነቅቅዎ እወዳለሁ” ካሉ በኋላ ይልቁንም እስካሁን የታሠሩት እንዲፈቱ፤ አፋኝ ሕጎች እንዲሠረዙ ግልጽና ፈጣን እርምጃ ባስቸኳይ እንዲወስዱ አማራጭ የሌለው ቁርጥ መፍትሔ አቅርበዋል፡፡

በአቶ መለስ ትዕዛዝ በመቶዎች የሚቆጠሩ ከተገደሉና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ከታሠሩና ከታፈኑ በኋላ ኢህአዴግ ሁሉም ሰላም ነው በሚልበት ጊዜ እንዲህ ዓይነቱ ሰልፍ ሕዝብን በማሰርና በመግደል የሕዝብን ድምጽ ማፈን በጭራሽ እንደማይቻል ያረጋገጠ መሆኑን የጠቆሙት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ ጠ/ሚ/ር ኃይለማርያም ሰማያዊ ፓርቲና ሕዝቡ የሚጠይቀውን በመመለስ ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ የማሸጋገር ከፍተኛ ሃላፊነት እንደወደቀባቸውና ይህንንም ሕዝብ እየጠበቀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ዶናልድ ቡት፤ በውጭ ጉዳይ ሚ/ር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ጸሐፊ ዶናልድ ያማሞቶ፤ ለአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ም/ቤት የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ሊቀመንበር ሴናተር ሮበርት ሜኔንዴዝ፤ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ከፍተኛ አባል ሴናተር ቦብ ኮርከር፤ በሕግ መወሰኛ ም/ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ሊቀመንበር ሴናተር ክሪስቶፈር ኩን፤ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ሊቀመንበር ክሪስቶፈር ስሚዝ፤ ለእንግሊዝ ውዕ ጉዳይ ሚ/ር፤ በአውሮጳ ኅብረት የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ሰብሳቢ እንዲሁም ለቢቢሲ፣ ጋርዲያን፣ ኒው ዮርክ ታይምስ፣ ዋሽንግተን ፖስት፣ ወዘተ የዜና አውታሮች በግልባጭ የተላከው የደብዳቤው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ነው፡፡

http://www.goolgule.com/

posted by Tseday Getachew

Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: