Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

በጦርነቱ ሰበብ በተዘረፈ ሐብት የሕወሃት ጄነራሎች ሚሊየነር ሆነዋል፡፡

 
“ማን ያውራ የነበረ…….ማን ያርዳ የቀበረ……”
“….የጦር መኮንን ሆነህ እንደባለሙያ ስታየው ውጊያው በጥቅሉ የሙያ ብቃት ያልታየበት አሳፋሪ ጦርነት ነበር ማለት ይቻላል፡፡በጃንሆይ እና በደርግ ዘመን ኤርትራ ላይ ውጊያ ተደርጎ የተሰዋው ዜጋችን ቁጥር ከ250 ሺ እስከ 300 ሺ ይደርሳል፡ከዚህ አንፃር ወያኔ በአንድ ዓመት ውስጥ ኤርትራ ላይ ያስፈጀው የወታደር ቁጥር በጣም አሳፋሪ ነው፡፡ከመከላከያ የሰው ኃይል አስተዳደርና ልማት መምሪያ ሰነዶች ያገኘሁት መረጃ እንደሚያሳየው በጠቅላላ በኢትዮ ኤርትራ ውጊያ 98,700 ወታደር ሲሞትብን 194¸300 ቁስለኛ ተረክበናል፡፡ ከኦርዲናንስ እዝ ያገኘሁት መረጃ ደግሞ መጀመሪያ ለውጊያ ከተዘጋጀው ከባድ መሳሪያ 2ሐ3ኛው መውደሙን ነግረውኛል፡፡ ይህንን ትርጉም አልባጦርነት የመሩት መሪዎች ሰዓረ መኮንን፣ ሳሞራ የኑስ፣ዮሀንስ ገብረመስቀል፣ታደሰ ወረደ፣ኳርተር /አብርሃ ወልደማርያም/፣ ብርሃነ ነጋሽ የተባሉት ጄነራሎች ናቸው፡፡
የጦርነቱ ማዕከላዊ እዝ አባላት ደግሞ መለስ ዜናዊ፣ ስዬ አብርሃ፣ ተወልደ ወልደማርያም፣ አለምሰገድ ገብረአምላክ፣ ተፈራ ዋልዋ፣ ፃድቃን ገብረትንሳኤ እና ክንፈ ገብረመድሕን ነበሩ፡፡ ያ ሁሉ ዜጋ ያለቀበትና ያ ሁሉ የሀገር ሀብት የወደመበት ጦርነት ከጦርነት አመራር ችግር መሆኑ በግልፅ እየታወቀ አንድም የጦርነቱ መሪ ተጠያቂ ሳይሆን እንዲሁ መቅረቱ በጣም ያሳዝናል፡፡…….”
ኮሎኔል አለበል አማረ
የአጋዚ ኮማንዶ አመራር አባል የነበሩ እና በግንቦት 7 መፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተጠርጥረው ዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት የተፈረደባቸው
ሌላኛው ኮሎኔል ደግሞ እንዲህ ይሉናል፡
“……የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ለጦርነቱ መሪዎች የሐብት ምንጭ ሆኖ ማገልገሉን ማየት ችያለሁ፡፡ በጦርነቱ ሰበብ በተዘረፈ ሐብት የሕወሃት ጄነራሎች ሚሊየነር ሆነዋል፡፡ ፃድቃን፣ ጀቤ፣ ብርሃነ ነጋሽ፣ ገዛኢ አበራ፣ አባዱላ ገመዳ፣ አበባው ታደሰ፣ ባጫ ደበሌ፣ ታደሰ ወረደ፣ ሰዓረ መኮንን፣ እና ሌሎችም ጄነራሎች በአዲስ አበባ በባህርዳርና በመቀሌ ያስገነቡት ቪላና ፎቅ ውበቱ አይንን ያፈዛል፡፡ የቤት እቃዎቻቸው፣ ምንጣፎቹ፣ መብራቶቻቸውና ኮርኒሶቻቸው በውድ ዋጋ ከአውሮፓ እየተጫኑ የመጡ ናቸው፡፡ የመጨረሻውን ቴክኖሎጂ እየተጠቀሙ ለቪላዎቻቸው ማሞቂያና ማቀዝቀዣ ተክለውላቸዋል፡፡ ከዚያ ሁሉ እልቂት በኋላ ጄነራሎቹ በቀጥታ ወደ ሃብት ፉክክር ነው የገቡት፡፡ የሚፈሰው ገንዘብ በጦርነቱ ወቅት የተዘረፈ ነው፡፡ …..”
ኮሎኔል አበበ ገረሱ
ጎበዝ የአበበችን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም ይባላል፡፡ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ለሀገራቸው ዳር ድንበር መከበር ሲሉ በኢትዮጵያዊነት የሀገር ፍቅር ስሜት ግን ደግሞ የወያኔን መሰሪ ባህርይ ባለመረዳት ውድ ሕይወታቸውን መስዋዕት ያደረጉት የነ በረከት፣ አባዱላ፣ ስዩም፣ አዲሱ እና ከላይ ያየናቸው ጄነራሎች እና የወያኔ ባለስልጣናት ልጆች አልነበሩም፡፡ የምስኪኑ ደሃ ኢትዮጵያዊ ልጆች እንጂ፡፡ ለዚያውም እኮ ያ ሁሉ ጀግና ወታደር ያለቀበት መሬት በጀርባ በተደረገ ስምምነት የኢዮጵያን ሕዝብ አጭበርብሮ ለወራሪው ሃገር እንዲመለስ አድርጓል፡፡ እነዚህ መስዋዕት የሆኑ ልጆቻችን ግን ለቤተሰባቸው መርዶ ማድረስ ቀርቶ ለአንድ ደቂቃ እንኳን የሕሊና ፀሎት እንዲደረግላቸው ያስታወሰ አንድም የወያኔ ባለስልጣን የለም፡፡ ባጭሩ ወያኔ ድሃውን ኢትዮጵያዊ የሚያየው ልክ እንደ ኮንደም ነው፡፡ በአፀያፊ ሁኔታ ይጠቀምባቸውና እንደ ቆሻሻ ይጥላቸዋል፡፡
ይኸው አሁን ደግሞ ግብፅ፤ ልትወረን ነው በማለት የጦርነት ነጋሪት እንደለመደው እያስጎሰመ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በታሪኳ ከግብፅ ጋር ባደረገችው ጦርነት አንድም ጊዜ ተሸንፋ አታውቅም፡፡ ይኸውም የአባቶቻችን ወኔ እንዳለ ሆኖ በዋናነት የጦር መሪዎቹ አመራር ወሳኝ ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን የዚህ ዓይነት ጄነራሎችን ይዘን ወደ ጦርነት ብንገባ ዳግም ድሃውን ኢትዮጵያዊ ማስጨረስና ለወያኔ ጄኔራሎች የሐብት ዝርፊያ መመቻቸት መስሎ ይታየኛል፡፡ በዋናነትም የወያኔ የሰሞኑ ልፍለፋ እንደለመደው የሀገር ውስጥ ችግርን ለማስቀየስ የሸረበው አዲስ ተንኮል እንጂ ከልቡ ለአባይና ሀገር ተቆርቋሪ ሆኖ በማሰብ ነው ብዬ በግሌ አምናለሁ፡፡ ከዚህ በኋ በወያኔ ቆስቋሽት በሚነሳ ጦርነት የአንድም ኢትዮጵያዊ ደም መሬት ላይ ይፈስ ዘንድ ፈፅሞ አልሻም፡፡ አባይ ቢገደብ በጣም ደስ ይለኛል ከሁሉም በላይ ደግሞ ወደ ውጭ ሀገር በመሰደድ ላይ ያለው የሀገሬ የተማረ ሰው ፍልሰት ቢገደብ እንዲሁም ከአባይ የበለጠ ሀገርን ሊያሳድግ የሚችል ፈጠራና ግኝቶችን ማውጣት የሚችለው የሰው ልጅ ሕይወትና ሕሊና በአባይ ሰበብ መስዋዕት ይሆን ዘንድ ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፡፡
ደብተራው ፀጋዬ
 
posted by Tseday Getachew
Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: