Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

ይድረስ ለፕ/ር አስራት ወልደየስ “መስዋዕትነትዎ ዋጋ አለው” ከጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ

 

ይህ ፅሁፍ ከ17 ዓመት በፊት (በ1988 ዓ.ም) አገራችን ውስጥ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ትታተም በነበረችው “ሃበሻ” ጋዜጣ ላይ ታትሞ የወጣ ነው። ፅሁፉ በወቅቱ የነበረውን መንፈስ፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ያኔም የነበረውን ብቃትና ጥንካሬ፣ እንዲሁም በዕውቁ ኢትዮጵያዊ የቀዶ ጥገና ሊቅ በፕ/ር አስራት ወ/የስ ም ሆነ በርሱ ላይ ሲፈፀም የነበረውን ግፍ መለስ ብሎ ለማስታወስ ይረዳል በሚል የቆዩ ድርሳኖቼን በማገላበጥ ዛሬ በዚህ መልኩ ይዤላችሁ ቀርቤአለሁ።
መልካም ንባብ!
እስክንድር ነጋን ጨምሮ ሌሎቹም ያለአግባብ የታሰሩት የህሊና እስረኞች ይፈቱ!
ድል ለኢትዪጵያ ሕዝብ!
ቅዱስ ሃብት በላቸው
 
“ከቀናት በፊት ይሄን ደብዳቤ ለርሶ መፃፍ ምን ያደርጋል? የሚል እምነት ነበረኝ። ሆኖም ውሎ እያደር አስፈላጊነቱን እያመንኩበት ስለመጣሁ ይኸው በዚህ መልኩ አሰናድቼዋለሁ።
የተከበሩ ፕሮፌሰር፣ አሁን ከታሰሩ ስንት ጊዜ ሆነዎት? ግዜው በጣም የራቀ ቢመስልም ቅርብ ነው። ስለርሶ የሰማሁባት ቀን የምትረሳ አይደለችም። ወደ ረፋዱ ላይ ቢሮዬ ደጃፍ ላይ እንደቆምኩ ነው፤ አንድ እግር ጥሎት ብቅ ያለ ጓደኛዬ እንባ እየተናነቀው የሁለት ዓመት እስራት እንደፈረዱቦት ነገረኝ። ጉድ ነው እኮ? … የነቀነቀኝ ዜና ቢኖር ይህ ነው።
“እዚህ ደረጃ ደርሰናል ለካ?!” አልኩት ለራሴ፤ “ወያኔ ቆርጣለችና ተቃዋሚዎቿን ኑ! ይዋጣልን እያለች ነው” ብዬ እራሴን አሳመንኩት። ስሜት ዋጠኝ ….ምናልባት ይህ ድፍረታቸው የሚቀጣጠሉ ነገሮችን ቀስቅሶ ለወያኔ ውድቀት መንገድ ይጠርጋል የሚል ተስፋ በውስጤ ጫረብኝ።
ከጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ
ተስፋ አደረግኩ፤ …. ተስፋ ደግሞ የሕይወት ጨው ናት። ወያኔ ከሰሜን ተራራዎች ተንደርድራ አዲስ አበባን ከረገጠች ወዲህ እንደ እግር እሳት ላንገበገበቻቸው ሁሉ ተስፋ ትልቅ ነገር ነው።
ወደ ቢሮዬ አልተመለስኩም። ከተማውን ለማየት ወጣሁ። ግን ምንም አልሆነምና ደነቀኝ። በኋላ ላይ የመአሕድ ባለስልጣናት ሕዝብ ለተቃውሞ እንዳይወጣ እንደከለከሉ ደረስኩበት። እንግዲህ ክቡር ፕሮፌሰር፦ አንድ ጓደኛዬ ይህ ተቃዋሚዎች ሓሞት እንደሌላቸው ማስረጃ ነው ይላል።
ከወር በፊት ጠዋት ላይ ስልክ ተደወለልን። ጥሪው ከፖሊስ ነበር፦ … ከማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ፖሊስ፤ ኑ! ነው ነገሩ። በስራ ተጠምደን ነበርና ብዙም ቦታ አልሰጠነውም። አንድ ነገር ልብ ይበሉ ፕሮፌሰር። እኛ የነፃው ፕሬስ አባላት የማንም ጀግኖች አይደለንም። ምናልባት ለምናምንበት ነገር ደረቆች ነን። ፈጽሞ ንቅንቅ አናውቅም። ከዚህ በተረፈ ከማንኛውም ሰው አንለይም። ስለዚህም የመረበሽ ስሜት ሳያድርብን የሚሉትን ሰምተን ስራችንን መስራት ቀጠልን።
ነገሩን ሳስታውሰው እንባዬ ቅርር ይላል። አዎ! የኩራት እንባ! …የደስታ እንባ! …የነፃው ፕሬስ ባልደረባ በመሆኔ ኩራት፤ .. ይህን ሁሉ የምናደርገው አማራጭ ላልተገኘለት ለክቡር አላማ ስለሆነ ደስታ፤ …
የልቤን ልንገሮት ፕሮፌሰር፦ በማንኛውም ደቂቃ ከኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ መለየት አልፈልግም። ከድሉ ጋር አብሬ እልልታዬን፤ ከሞቱም ጋር ሞትን መሞት እሻለሁ። ማዕከላዊ ወር ታስሬ ወጣሁ። ስፈታም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ተጠናክሬ ወጣሁ። እስሩ ያሳደረብኝ ስሜት አሳሪዎቼ እኔን በማሰቃየት ሊፈጥሩብኝ ከፈለጉት ስሜት በተቃራኒ ነበር። ሆኖም ያጋጥመኛል ብዬ ያላሰብኩት ነገር ያጋጠመኝ።
ከእስር ከተፈታሁ ከቀናት በኋላ አንድ የቅርብ ጓደኛዬን አገኘሁት፤ አብሮት አንድ ሰውዬ ነበር። ጓደኛዬ ከዚሁ ሰው ጋር ገና እንዳስተዋወቀኝ በጥያቄ ያጣድፈኝ ገባ። ሰውዬው “የነፃው ፕሬስ አባላት ሕግን ለመጣስ ለምንድነው የምትፈልጉት? ይህንን ለማወቅ እፈልጋለሁ፤” ሲል አፈጠጠብኝ።
እንግዲህ እዚህ ላይ ልመልስለት የምችልበት ብዙ መንገዶች ነበሩ። “ፍትሃዊና ፍትሃዊ ያልሆነ ሕግ አለ፤ ፍትሃዊ ካልሆኑት ሕጎች ደግሞ የፕሬስ ሕጉ ነው።” ልለው እችል ነበር። በነፃው ፕሬስና በመንግስት መካከል ያለው አለመግባባት የሕግ ጥያቄ ሳይሆን ፖለቲካዊ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ግጭት እንደሆነና ሁለቱ ተቀናቃኞች የሚጣሉት በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጥያቄ ዙሪያ ነው ልለው እችል ነበር። ከዚያም በላይ ነገሮች ምን ዓይነት አስቀያሚ ጎሳዊ መልክ እየያዙ እንደሆነ ልናገረው እችል ነበር። ግን ከውስጤ አንድ ነገር ያዘኝ። ዝም አልኩት! … በዚሁ ተለያየን!
በሚቀጥለው ቀን ይኸው ጓደኛዬ ደውሎልኝ ሊያገኘን እንደሚፈልግ ስለገለፀልኝ ቀጠሮ ያዝን፤ የተቀጣጠርነው ምሽት ላይ ስለነበር ጥሩ ጊዜ እናሳልፋለን የሚል ግምት ነበረኝ። ነገር ግን በተገናኘንበት ወቅት ሌላ ሌላውን ነገር ተጨዋውተን የምንለያየበት ምሽት እንዳልሆነ ገባኝ። በዚያ ምሽት የነገረኝ ነገር ነው ለዚህ ደብዳቤዬ መንደርደሪያ የሆነኝ።
“እየው!” አለኝ ጓደኛዬ … “በአንተ ምክኒያት ብዙ ተጣልቻለሁ፤”
ደነገጥኩ፤ …. እንዴት? ከማን? በምን? ….ማሰብ የቻልኩት እነዚህን ነገሮች ብቻ ነበር።
“አየህ …. ሰዎች መታሰር ሲያንሰው ነው፣ ሲሉህ ነበር፤ ብዙ ጮኋል፣ በጣም ገፋ፣ ታክቲክ አያውቅም፣ ስሜታዊ ነው፣ ስሜቱን ነው ማማረር ያለበት ይሉሃል፤” አለኝ። በዚሁ አልተወኝም፤ … “የኢትዮጵያ ሕዝብን በዚህ ማዳን አይቻልም ነው የሚሉት። ሕዝቡ አልነሳም ብሏል። በራሱ ጉዳዮች ላይ ፊቱን አዙሮ ለመኖር ብቻ ቆርጧል ብለዋል” አለኝ።
እዚህ ላይ እንግዲህ የርሶን ስም ይጠቃቅሳሉ፤ “ከፕሮፌሰር አስራት አይማርም እንዴ?” ይሉ እንደነበር ይኸው ጓደኛዬ አልሸሸገኝም። “ሕዝቡ ውጭ ሆነው ሆይ! ሆይ! ብሎ በኋላ ለወያኔ ጥሏቸው ጠፋ” አለኝ። “ግዜው ክፉ እንደሆነ ከዚህ በላይ ምን ማስረጃ አለ? … ሕዝቡ ወላዋይ እንደሆነ ከዚህ በላይ ምን ማስረጃ አለ? … ታዲያ እስክንድር ይህንን እያየ ምን ልሁን ነው የሚለው? … ነገር አይገባውም፤” ብለውሃል አለኝ።
ጓደኛዬ ይህንን ሁሉ ሲሉህ ተከላክዬልሃለሁ አለኝ። አምኜዋለሁ ፕሮፌሰር። ጥሩ ሰው ነው፤ በሌለሁበት የሚያነሱኝን ዝም ብሎ የሚያልፍ ሰው አይደለም። ከዚህ በኋላ ነገሩን ልዘጋው ብፈልግም ጓደኛዬ እንዳልጨረሰ ነገረኝ። ምን ሊኖር ይችላል? … አሁንም ለመስማት ጓጓሁ።
“የተከላከልኩልህ ያነሱህ በሌለሕበት ስለሆነ ነው እንጂ፣ እኔም በነርሱ ሃሳብ እስማማለሁ” ሲል ነገረኝ። “ምንድነው የምትሰራው? … ሕዝቡ እንደሞተ ማየት አትችልም? አዎን! ከፕሮፌሰር አስራት መማር አለብህ! ብቻህን ነህ! የጀመርከው ጉዞ ለውድቀት ነው የሚዳርግህ ።” ሲልም አስጠነቀቀኝ። “አንተን የሚያንቋሽሹት ደግሞ አብዛኞቹ አማሮች መሆናቸውን አትርሳ!” አለኝ። ከዚህ በኋላ ከርሱ ጋር ለመጨቃጨቅ አልፈለግኩም። ተለያየን። በታክሲ ከምሄድ ብዬ ቀስ እያልኩ ወደ ቤቴ አዘገምኩ።
በሚቀጥለው ቀን ሌላ የስልክ ጥሪ ደረሰኝ፤ ይሄኛው ደግሞ ከዋሽንግተን ዲሲ በቅርቡ ከመጣ ጓደኛዬ ነበር። ስለዲሲ ብዙ መስማት የምፈልገው ነገር ነበርና የዚያኑ ዕለት ማታ ልንገናኝ ተቀጣጠርን።
እንደተገናኘንም በሌሎች ጉዳዮች ላይ ጊዜ ሳናጠፋ በቀጥታ ወደ ፖለቲካው ገባን። በዋሽንግተን ወያኔ የቆመችለትን ሁሉ በመጥላት ስለተቃጠሉት ኢትዮጵያውያን ለመስማት ቸኩዬ ነበር፤ ዲሲ የዋዛ ከተማ ስላልሆነችና የወያኔም ጥላቻ ስር የሰደደ ስለሆነ ነፃ መሬት (ከወያኔ) በመባል ትታወቃለች። ምን እየሆነ ነው? ….ምን አዲስ ነገር አለ? ስል ጠየቅኩት። ምላሹ አጭር ነበር፤ “ምንም!” የሚል።
እንዴት? …. እነዚያ በሺዎች የሚቆጠሩ ፀረ-ወያኔዊች የት ሄዱ? ምን ዋጣቸው? አሜሪካኖቹ ወደ አዲስ አበባ አባረሯቸው፣ ግን እኮ አላያቸውም፤ አልኩት።
ጭንቅላቱን እየነቀነቀ፤ “በፍጹም!” አለኝ። “ስማ ወያኔ ሥልጣን ከያዘች አራት ዓመታት እንዳለፉ ረሳህ እንዴ? …. ይህ ረጅም ጊዜ ነው፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ ብዙ ነፃ-አውጭዎች መጥተው ሄደዋል። ሰዎች ዛሬ ተጠራጣሪ ሆነዋል፤ ስለዚህ ብዙው ሰው አንገቱን መድፋት መርጧል።” ሲል ሊያብራራልኝ ሞከረ።
ያውሎት እንግዲህ ፕሮፌሰር፤ ብዙም ደስ የሚል ነገር አይደለም እዚህ ውጭ ያለው። እንዲያውም ሕሊና ያለው ሰው ከርሶ ጋር እዚያው መደባለቁን ሳይመርጥ አይቀርም። ግን ሁሉም ነገር አላለቀም። ሽንፈት በጭንቅላት ውስጥ ነው። ሽንፈት ፀባይ ነው። ተስፋ የቆረጠ ብቻ ነው የተሸነፈ። ምንም የማይቻል ነገር የለም። ማድረግ ከፈለጉ የማይቻለውንም ነገር ማድረግ ይቻላል።
የተከበሩ ፕሮፌሰር፦ የዚህ ደብዳቤ ዋነኛ ነጥብ ላይ ደርሻለሁ። ብዙ ሰዎች ተስፋ ቆርጠዋል። ሆኖም የቆሙለት ዓላማ ትክክል ስለመሆኑ አሁንም አይጠራጠሩም። ጥፋተኞች ናቸው? …. አይመስለኝም። እርስ በርስ መወነጃጀላችንን ማቆም አለብን። ለዚህም ጊዜው አሁን ነው። የተወሰኑ ጥቂቶች ለሌላው አርዓያ በመሆን መንገዱን ሊጠርጉ ይችላሉ የሚል ጠንካራ ዕምነት አለኝ። ተስፋ የቆረጡት እንደሚሉት መስዋዕትነትዎ ዋጋ የሌለው አይደለም። ተስፋ አሁንም አለን። ምንጊዜም አለን! ከ እጃችን የማታመልጠዋ ድልም እንዲሁ።
ከአክብሮት ጋር
እስክንድር ነጋ
 

 
posted by Tseday Getachew

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: