Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

ጥንታዊው ባንኮ ዲሮማ ሕንፃ የመደርመስ አደጋ ተጋርጦበታል

 

በሰንደቅ ጋዜጣ ሪፖርተር

ከረጅም ዓመታትበፊት በልዩ ዲዛይን በአፄ ሀ/ስላሴና በምስካየ ህዙናን መድሃኒአለም የጋራ ገንዘብ የተሰራውና ንብረትነቱ የኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የሆነው ባንኮ ዲሮማ ሕንፃ ያለበቂ ጥናትና ጥንቃቄ በተያዘ የሌላ ሕንፃ ግንባታ እቅድ ለመደርመስ አደጋ መጋለጡን የአካባቢው ነዋሪዎች አስታወቁ።

በሀገሪቱ በስነሕንፃው ዘርፍ ቅርስ የሆነው ፒያሳ አካባቢ የሚገኘው ባንኮ ዲሮማ ሕንፃ የመደርመስ አደጋው የተጋረጠበት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን በሕንፃው ቅጥር ግቢ በስተሰሜን በኩል በሚገኘውና ከህንፃው መሠረት ጋር ይገናኛል ተብሎ በሚገመተው ባዶ ቦታ ላይ ለመስራት በተያዘው የሌላ ህንፃ ግንባታ የመሰረት ቁፋሮ ጋር በተያያዘ ነው። ከሕንፃው 10 ሜትር እንኳን በማይርቅ ክፍት ቦታ /የህንፃው ፓርኪንግ/ ላይ ቁፋሮ ለመጀመር ማሽነሪዎች የገቡ ሲሆን ቁፋሮው ወደ መሬት 10 ሜትር ጥልቀት እንዳለው ከባለሙያዎች ለመረዳት መቻላቸውን ተናግረዋል።

በተለይ ከተወሰኑ ሜትሮች ጥልቀት በኋላ አለት /ድንጋይ/ ይገኛል የሚል ግምት መኖሩን፣ በቁፋሮ ወቅት የአለቱ መገኘት እውን ከሆነ የነባሩን ባንኮ ዲሮማ ሕንፃ መሰረት ሊያናጋውና ለመደርመስ አደጋ ሊያጋልጠው እንደሚችል በሕንፃ ግንባታ ሙያተኞች ጭምር እንደተገለፀላቸውና በዚህም ምክንያት ከፍተኛ ሥጋት ላይ መውደቃቸውን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። የግንባታ ሥራውን የወሰደው ተቋራጭ ድርጅትም ባለው ከፍተኛ ሥጋት የተነሳ ለባንኮ ዲሮማ ሕንፃ ቀድሞ ኢንሹራንስ የገባለት መሆኑ ተሰምቷል። ኢንሹራንስ ቀድሞ መግባቱ ደግሞ ሕንጻው ለአደጋ የመጋለጥ ሥጋቱ ምንያህል ከባድ እንደሆነ የሚያረጋግጥ ነው።

በመዲናችን በስነ ሕንፃው ዘርፍ ቀደምት ከሆኑት ሁለት ሕንፃዎች አንዱ የሆነው ባንኮ ዲሮማ ህንፃ ሊደርስበት ለሚችለው ጉዳት ኢንሹራንስ መገባቱ ከቅርስ ጥበቃ አኳያ ሲታይ መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

ምክንያቱም ሕንጻው ከተደረመሰ በኋላ በተገባለት ኢንሹራንስ መሠረት ሊገነባ ቢችልም እንኳን ታሪካዊነቱንና ቅርስነቱ ሙሉ ለሙሉ የሚያጣ በመሆኑ ነው።

ስለዚህ እንዲህ አይነት የሀገርና የሕዝብ ሀብት የሆኑ ቅርሶችን የመጠበቅ፣ ታሪካቸውን አፈላልጎና አደራጅቶ የመመዝገብ ኃላፊነት ያለበት የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ተቋም ይህንን በህዝብ ልብ ውስጥ በቅርስነት ተመዝግቦ እንደ አይን ብሌን የሚታይ ሕንፃ ከውድመት ለማዳን ፈጥኖ እንዲንቀሳቀስ ጥሪ አቅርበዋል።

“ሕንጻው በቅርስነት ተመዝግቧል? ወይ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ “ዋናው ቁምነገር በቅርስነት የተመዘገበ ያልተመዘገበ የሚለው ሳይሆን የሀገር ቅርስ መሆኑ በሕዝቡ መታመኑ ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ከመዲናችን አዲስ አበባ ቀደምት ከሆነውና ባንድ ወቅት ትልቅ ፎቅ ነው ተብሎ ጉዳት ደርሶበት ከነበረው ገብረ ወልድ ሕንፃ ተመጣጣኝ እድሜ ያለው ባንኮ ዲሮማ ሕንፃ ያለበቂ ጥናት በሚደረግ የሌላ ሕንፃ ግንባታ ምክንያት እንዳይደረመስና ቅርስነቱ እንዳይጠፋ የሚመለከተው አካል ሁሉ በተለይም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ተቋም ፈጥነው ሊደርሱለትና ከግንባታ በፊት ለነበሩ ህንፃ ደህንነት ሲባል በቂ ጥናት ሊደረግበት ይገባል። ከጥቂት ዓመታት በፊት ተፈጥሮአዊ ቀለሙን ሊያሳጣ የሚችል ቀለም የመቀባት እድሳት ሊደረግ ሁሉ ነገር ካለቀ በኋላ ታሪካዊነቱን ወይም ቅርስነቱን ያጣል በሚል የነበረውን የቀለም ይዘት ይዞ እንዲቀጥል መደረጉን አስታውሰዋል።

ሌላው ስጋት ከሕንፃው መሰረት ስር መነሻው ያልታወቀ ከፍተኛ የውሃ ክምችት መኖሩ አሁን ከታቀደው ሥራ ጋር ተያይዞ ሕንጻውን ለውድመት ይዳርገዋል የሚል ነው።

በባንኮዲሮማ ፓርኪንግ ውስጥ ሊሰራ ስለታቀደው አዲስ ሕንፃ እና ነዋሪዎች ያቀረቡትን ስጋት በተመለከተ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።

ምንጭ፡ ሰንደቅ ጋዜጣ

posted by Tseday Getachew

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: