Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

በመተማ ወረዳ አርሶ አደሮች ከመፈናቀላቸውም፡በላይ ድረንበር ጥሰዋል ተብለው ሦስት ሰዎች መገደላቸው ተዘገበ

 

ሚያዚያ ፳፩ (ሃያ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በሰሜን ጐንደር ዞን በመተማ ወረዳ ከዮሐንስ ከተማ በስተሰሜን <<ደለሎ>> ተብሎ በሚጠራው አካባቢ፣ ለረዥም ዓመታት መሬት  ወስደው በሕጋዊ መንገድ  ግብር ሲከፍሉ፡የቆዩ አርሶ አደሮች፣ አካባቢውን ጥለው እንዲሄዱ በወረዳው ውሳኔ መተላለፉን  የሪፖርተር ዘገበ፡፡

ጋዜጣው ምንጮቹን በመጥቀስ  እንደዘገበው፤ድንበር አልፈዋል በሚል ሦስት አርሶ አደሮችም በሱዳን ታጣቂዎች ተገድለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ሰሞኑን በፓርላማ ሪፖርት ሲያቀርቡ በቤንሻንጉል ክልል የተፈፀመው ማፈናቀል በመንግስት ተቀባይነት እንደሌለውና ከ፡እንግዲህ ምንም አይነት ማፈናቀል እንደማይኖር ቃል፡መግባታቸው ይታወሳል።

የክልሉ አካባቢ ጥበቃና መሬት አስተዳደር ባለሥልጣን -ከወረዳው አስተዳደር ጋር በመተባበር አርሶ አደሮቹ የእርሻ ቦታቸውን ጥለው እንዲወጡ ማድረጋቸው አግባብ አለመሆኑን የሚናገሩት ምንጮቹ፣ አርሶ አደሮቹ መሬታቸውን በማለስለስ ለዘር ዝግጁ አድርገው እየተጠባበቁ ባሉበት ሁኔታ ውሳኔው መተላለፉ ፤ተስፋ አስቆራጭ እንደሆነባቸው ገልጸዋል፡፡

የክልሉ አካባቢ ባለሥልጣን የመሬት አያያዝ ብሎክ ፤ አርሶ አደሮችና -ባለሀብቶች ድንበራቸውን የመለየት ሥራ በሚል ሰበብ፣ ቀደም ብሎ በጂፒኤስ ተለክቶ የተሰጠን መሬት፣ ከ15 ዓመታት በኋላ ኋላቀር በሆነና ለማዳላት በሚያመች መንገድ በገመድ እየለካ መሆኑንም ምንጮቹ ጠቁመዋል፡፡

ባለሥልጣኑ እየሠራ ባለው ኋላቀር አሠራር፤ ለአስተዳደሩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች የሚፈልጉት ተጨማሪ ቦታ እየተመቻቸላቸው መሆኑን የሚናገሩት ምንጮቹ፤ አቅም የሌላቸው፣ አነስተኛ አርሶ አደሮችና ለአስተዳደሩ አመራሮች ቅርበት የሌላቸው አልሚዎች ተጐጂ መሆናቸውንም  አክለዋል፡፡

የገመድ ልኬቱ፤ የድንበርን ወሰንን በትክክለኛው ሊያስቀምጥ ባለመቻሉ እና አልፎ አልፎ ወደ ሱዳን ድንበር እየገባ በመሆኑ፤ በሱዳን አርሶ አደሮች በኩል አላስፈላጊ እንቅስቃሴ እየፈጠረ እና አካባቢውን ወደ አለመረጋጋት እየወሰደው መሆኑን ምንጮቹ  ተናግረዋል፡፡

ስለጉዳዩ የተጠየቁት የአማራ ክልል የአካባቢ ጥበቃና መሬት አስተዳደር ባለሥልጣን ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ባይህ ጥሩነህ  የተፈናቀለ አርሶ አደር እንደሌለ በመጥቀስ፤ በ አካባቢው ዘመናዊና ሥርዓት የያዘ  የመሬት አስተዳደር እንዲኖር በሰሜን ጐንደር መተማ ወረዳ ደለሎ አካባቢ  የባለሀብቶችንና የአርሶ አደሮችን ድንበር የመለካት ሥራ እየተሠራ  መሆኑን ተናግረዋል።

<<ደለሎ>> ተብሎ በሚጠራው አካባቢ  ሁለት ዓይነት ይዞታ አለ የሚሉት ኃላፊው፣ በ አንድ በኩል  በሕገወጥ መንገድ መሬት በመያዝ ግብር ሳይከፍሉ የሚኖሩ ከሌላ ቦታ የመጡ  አርሶአደሮች ሲኖሩ በሌላ በኩል   ሕጋዊ የሆኑ አርሶ አደሮች አሉ ብለዋል።

‹‹ተፈናቀልን›› የሚሉትም ሕጋዊ ሰነድ እንዲያቀርቡና ሕጋዊ እንዲሆኑ ተጠይቀው፣ ማቅረብ ያልቻሉ ሊሆኑ እንደሚችሉ ሀላፊው ግምታቸውን ጠቅሰው፤ ወደ ቢሮውም ቢመጡ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡

ቀደም ሲል ከደቡብ ክልል ጉራ ፈርዳም ሆነ አሁን በቅርቡ ከቤንሻንጉል ለተፈናቀሉት አርሶአደሮች ለመፈናቀላቸው የሚቀርበው ምክንያት እንዳሁን<<ከሌላ ቦታ የመጡ ህገ-ወጦች ናቸው>.የሚል መሆኑ ይታወቃል።

አርሶ አደሮቹ  እንደሚሉትም፣ ዘር ለመዝራት ያዘጋጁት መሬት መወሰዱ ኢፍትሐዊ መሆኑን ለወረዳው አስተዳደርና ለዞኑ ቅሬታ ቢያቀርቡም፣ ማንም ሊያነጋግራቸው ፈቃደኛ አልሆነም።

በቀጥታ ለክልሉ መንግሥት ቅሬታ ሲያቀርቡም፤ ከወረዳ እስከ ዞን ባለው የቅሬታ አቀራረብ ሰንሰለት እንዳልመጡ በመግለጽ እንዳልተቀበላቸው ጠቁመዋል፡፡

ክልሉ ባለው መዋቅር መሠረት ሰንሰለቱን ጠብቀው ቅሬታቸውን ለማድረስ የሚወስደው ጊዜ ረጅም በመሆኑ፣ ለዓመታት ሲያለሙት የኖሩትን መሬት ለቀው ለመውጣት መገደዳቸውን ምንጮቹ አክለዋል፡፡

የአቶ መለስን ሌጋሲ በማስቀጠል ስም የሚነግዱና ለኢንቨስትመንት መዘጋጀት  የሚችልን መሬት ለግል ጥቅማቸው ለማዋል የሚፈልጉ የወረዳና የዞን አመራሮች እንዳሉ የሚገልጹት ምንጮቹ፣ መንግስት አንዳንድ ከእነሱ ጋር ግንኙነት የመሠረቱ ባለሀብቶችን ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርግ አሠራር መኖሩን  ተገንዝቦ ክትትል እንዲያደርግ እንዲሁም የ አርሶአደሮችን መፈናቀል እና  ከጐረቤት አገሮች ጋር ግጭት ውስጥ የሚጥል የልኬት ሥራን እንዲያስቆም ጠይቀዋል፡፡

በተመሣሳይ  ከድንበር ልኬት ጋር በተገናኘ ከመተማ ዮሐንስ ከተማ በስተደቡብ በኩል <<ቱመት-ቲያ>> ተብሎ በሚጠራው የኢንቨስትመንት አካባቢ ሦስት አርሶ አደሮች፣ ‹‹ድንበራችንን አልፋችሁ ገብታችኋል›› በሚል ሰበብ በሱዳን ታጣቂዎች መገደላቸውንም ሪፖርተር ምንጮቹን በመጥቀስ ጨምሮ ዘግቧል።

የመተማ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ተስፋ መኮንን አርሶ አደሮቹ በሱዳን ታጣቂዎች ተገድለዋል መባሉ እውነት መሆኑን ቢያረጋግጡም፣ ምክንያቱ ግን ከድንበር ልኬትና ከእርሻ ጋር የተገናኘ አይደለም ባይ ናቸው።

አንዳንድ ጊዜ የመተማ አርሶ አደሮች ድንበር ተሻግረው የመስፈር ሁኔታ መኖሩንና ከሱዳኖቹም በኩል ተመሳሳይ ባህሪ እንደሚታይ የገለጹት አቶ ተስፋ፣በዚህ ሳቢያ  ከሱዳኖች በኩል አንድ ታጣቂ ተገድሎ እንደነበርና ሱዳኖቹም በዚያ ድርጊት ቂም ይዘው ግድያውን ሳይፈጽሙ እንዳልቀሩ ግምታቸውን ገልጸዋል፡፡

የዜናው ምንጮች ግን ለ አርሶአደሮቹ ሞት ምክንያት የሆነው የመሬት ልኬቱ ድንበር እያለፈ ግጭት በመፍጠሩ እንደሆነ በመጥቀስ የ አካባቢውን አስተዳደር ተጠያቂ ያደርጋሉ።

ጠ/ሚ/ር ሀይለማርም ፦<<ዳግም መፈናቀል አይኖርም>>ብለው ቃል በገቡ ማግስት ይህን ዜና ያነበቡ ሰዎች፦<<ድርጊቱ አቶ መለስ ካለፉ በሁዋላ በ ኢህአዴግ ውስጥ መርህ፣ መደማመጥና መከባበር መጥፋቱን የሚያመለክት ነው”ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

posted by Tseday Getachew

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: