Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

የሙስሊሙ ትግል ህወሓትን ያስደነገጠበትና ያስቸገረበት ምክንያት ህብረብሔራዊ ትግል መሆኑ ነው!!

“ሀዜብ የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆና የምትመጣ ከሆነ ለከተማዋ አደገኛ ውድቀት ያስከትላል” ሁለተኛ ክፍል

የዛሬው የፍኖተ ነፃነት እንግዳ ወጣቱ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና ተንታኝ አቶ ጃዋር መሀመድ ነው፡፡ ከጃዋር መሀመድ ጋር ያደረግነውን ቆይታ ሁለተኛ ክፍል እንደሚከተለው አዘጋጅተነዋል መልካም ንባብ

jawar

ፍኖተ ነፃነት፡- የማፈናቀል ዘመቻው የኢህአዴግ መንግስትን በመቃወም በሙስሊም ኢትዮጵያውያን የሚደረገውን ትግል ለማክሰም የተወሰደ እርምጃ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ

ጃዋር፡- የሙስሊሙ ትግል ህወሓትን ያስደነገጠበትና ያስቸገረበት ምክንያት ህብረብሔራዊ ትግል መሆኑ ነው፡፡ ሃይማኖቱ ሁሉንም ብሔር የሚነካ ከመሆኑ የተነሳ ሁሉንም ብሔር፣ ከባህርዳር እስከጅጅጋ ያንቀሳቀሰ ነው፡፡ ከፋፍሎ አማራው ሃይማኖቱን ጥሎ ብሔሩን ወደ መከላከል እንዲገባና ትግሉ እንዲዳከም የትኩረት አቅጣጫን የማሳት አላማ አለው፡፡ ስርአቱ በአንድ ቦታ እሳት ሲቀጣጠልበት በሌላ መንገድ ማጥፋት ሂደት አለው፤ በእኔ ግምት ይህ ይሳካለታል ብዬ አላምንም፡፡ ከእንግዲህ ሁሉንም መብቶች ለማስከበር በአንድ ጊዜ ውደ መጠየቅ መግባት ያለብን ይመስለኛል፡፡ አማራው ሲጠቃ የአማራውን መብት ለማስከበር በምናደርገው ስራ ሌሎቹ የመብት ማስከበር ትግሎች መቆም የለባቸውም፡፡ የሙስሊሙን መብት ለማስከበር ትኩረት ሰጥተን በምናደርገው ትግል ምክንያት የጋዜጠኞች ነፃነት ጥያቄ የእነእስክንድር ጥያቄ መቆም የለበትም፡፡ የጋዜጠኞች የመብት ጥያቄ ላይ ትኩረት ስናደርግ የኦሮሞ የፖለቲካ እስረኞች የመብት ጥያቄ ወደኋላ መቅረት የለበትም፡፡

መብት ተሸራርፎ የሚሰጥ ነገር አይደለም፡፡ የሃይማኖት መብት ከተነፈገ የጋዜጠኛው መብት ይነፈጋል፡፡ የብሔር መብት ከተነፈገ የሃይማኖት መብት ይነፈጋል፡፡ ስለዚህ መብት ተሸራርፎ ሳይሆን በጅምላ የሚሰጥ ነው፡፡ ሁሉም መብቶቻችን እንዲከበሩ ከተፈለገ ሁሉም የመብት ጥያቄዎች በአንድ ጊዜ መነሳት አለባቸው፤ ይህ ሲባል ግን በጣም በከፋ ሁኔታ እየተደመሰሱ ባሉ መብቶች ላይ አነጣጥሮ መስራቱ ትክክል አይደለም እያልኩ አደለም፡፡ ሆኖም ግን ሌሎቹንም ወደኋላ መርሳት የለብንም፤ እንደውም ሁሉንም አንድ ላይ ይዘን የምንሄድ ከሆነ በተለያየ ፊና የሚደረጉት ትግሎች እርስበርሳቸው እየተደጋገፉና እየተጠነካከሩ በቂ ጫና በስርአቱ ላይ እንዲያመጡ ያደርገዋል፡፡ በርግጥም እኛ በአንድ መብት ዙሪያ አተኩረን ስንንቀሳቀስ ስርአቱ ሌሎች መብቶችን እንደፈለገው ለመናድ ያስችለዋልና በሁሉም አቅጣጫ ሁሉም ማህበረሰብ የሚሳተፍበት ትግል ማድረጉ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- የአቶ አዲሱ ለገሰ መመለስና የአባሮቹ የብአዴን ሰዎች አለመተካት ብአዴንን በኢህአዴግ ውስጥ እያጎላው ነው ማለች ይቻላል?

ጃዋር፡- አቶ አዲሱ ከኢህአዴግ ጋር ሃያ አመት ስልጣን ላይ ነበሩ ምክትል ጠ/ሚር በነበሩበትም ወቅት ያላደረጉትን ነገር ዛሬ ምንም ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ ህወሓት ነው እንደዚህ ያደረገው፡፡ እነአዲሱ እንዲመለሱ እነ አባዱላ እንዲወርዱ የሚያደርገው ህወሓት ነው፤ ይህን የሚያደርግበት ምክንያት ለምሳሌ ኦህዴድ ውስጥ የእነአባዱላ እየጎሉ መምጣት፣ ፓርቲውን የሚያስማሙ(unifying figure) እየሆኑ መምጣታቸው፣ በተለይ መለስ ከሞተ ወዲህ ፓርቲው ኢህ አዴግ የፈለገውንና የመለመለውን ሰው ለመሾም የተሞከሩ ሙከራዎችን በከፍተኛ ደረጃ ወቃወሙ ኦህዴድ ውስጥ ጠንካራ የሚባሉ ግለሰቦች መመታት አለባቸው በሚል የተነሳ ጁነይዲ፣አባዱላ፣ ግርማ ብሩ፣ ለማ መገርሳና ሌሎችም ሰዎች ከፓርቲው ውስጥ ተመንጥረው የወጡበትን ሁኔታ ነው የምታየው፡፡

ወደ ብአዴን ስትመጣ ደግሞ ከዚህ በፊት የወጡት ለምን ተመለሱ ስትል፣ የህወሓት ችግር ምንድነው አብረዋቸው ከጫካ የመጡ ሰዎች በቁመታቸው መትረው ያስቀመጧቸው ነበሩ፡፡ ችግሩ ግን አሁን በብአዴን ውስጥም ሆነ በኦህዴድ ውስጥ ወጣቱ በኛ ዕድሜ ያሉ ስርአቱ ስልጣን ከያዘ በኋላ ለስራም ይሁን ለተለያየ ነገር ውስጥ ውስጡ የገቡ በስርአቱ ተአማኒ ያልሆኑ ግን ለህዝባቸው በተወሰነ ደረጃ የሚቆረቆሩ ልጆች በብአዴን ውስጥ እየወጡ ያለበት ወደ ስልጣን እየተጠጉ ያለበት ሁኔታ ስላለ፣ ህወሓቶች እነዚህን ሰዎች አያምኗቸውም፡፡

ለምሳሌ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩን ብትወስደው አያምኑትም፤ ስለዚህ ብአዴንን በታማኝ ሰዎች ቁጥጥር ስር ለማቆየት ወሳኝ ነበር ለህወሓት፡፡ ለዚህ ነው በረከት ስምኦን ይወርዳል ተብሎ እሱም እወርዳለሁ ብሎ ከደመደመ በኋላ ተመልሶ ስልጣን የያዘበት፣ አቶ አዲሱ ድል ባለ ድግስ ጡረታ ከወጣ በኋላ ተመልሶ የመጣበትና ብአዴን ከሞላ ጎደል አሁን ከላጥ ያሉትን ስታይ ፈላጭ ቆራጮቹ ከዚህ በፊትም የነበሩ ናቸው፡፡ እና ብአዴን በለውጥ እየቀጠለ ከሄደና በአዳዲስ ትውልድ እየተተካ ከሄደ ይዋል ይደር እንጂ አፈንግጦ የራሱን ክልልና የራሱን ህዝብ ማንነትና ጥቅም ሊያስከብር የሚችልበትና ከሌላው ተቃዋሚ ጋር ሆነው ህወሓት ላይ ሊዞር ይችላል ሚል ከፍተኛ ፍራቻ አላቸው፡፡

በነገራችን ላይ ለዚህ ደግሞ የራሳቸው ምክንያት አላቸው፤ ትዝ የሚልህ ከሆነ ከ97 በኋላ የብአዴን የነበሩ ወታደራዊ መኮንኖች በህወሓት ላይ አምፀው ስርአቱ እንደሚለው መፈንቅለ መንግስት የሰቡበት ሁኔታ ነበር፡፡ ህወሓቶች አንድ በግልፅ የሚያውቁት ነገር በተለይ የብአዴንና የኦህዴድ ሰዎች ቀን ይጠብቃሉ እንጂ ተነስተው እነሱ ላይ እንደሚነሱባቸው ያውቃሉ፡፡ ስለዚህ ይሄ የመነሳት እድሉን ለማቆርቆዝና እነዚህ ፓርቲዎች ሁሌም በታማኝ በሆኑ ሰዎች ቁጥጥር ስር ለማድረግ እንጂ የመለሱት የብአዴን በኢህአዴግ ውስጥ ለው ድርሻ ከድሮው የተዳከመ ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን ብአዴን በቀጥታ በህውሓትና በትግራይ ልሂቃን ስር ነው፡፡ ሌሎቹም እንደዚሁ ማለት ነው፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- ህወሓት ኢትዮጵያ ላይ ይከተለው የነበረውን አቋሙን እየቀየረ የመጣ አይመስልህም

ጃዋር፡- ከ97 በኋላ ህወሓት ፖለቲካዊ ተረኩን (political narrative) እየቀየረ መጥቷል፡፡ በፊት ሲታወቅበት የነበረውን የትግራይ ብሄረተኝነት በማለዘብ፤ በፕሮፓጋንዳ ደረጃ የኢትዮጵያ ጠባቂነኝ ለማለት እየሞከረነው፡፡ ይህ ሁለት አይነት ሂደት ነው ያለው፤ አንዱ የህወሓትን ታሪክ የኢትዮጵያ ታሪክ በማድረግ በፊት የትግራይ ጀግኖች የሚላቸውን አሁን የኢትዮጵያ ጀግና በማለት፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የኢትዮጵያን ታሪክ የትግራይ የማድረግ ነው፡፡ ለዚህ መለስ በኢትዮጵያ ሚሊኒየም አከባበር የተናገረውን ማስታወስ በቂነው መለስ በወቅቱ “የመጀመሪያው ሚሊኒየም በእድገት የገሰገስንበት፣ ሁለተኛው ወደኃላ የቀረንበትነበር ሶስተኛው ደግሞ ህዳሴያችን ነው” ብሎ ነበር፡፡ ይህን ስታየው ኢትዮጵያ በትግራይ አገዛዝ ጊዜ ትልቅ ነበረች አማራ ሲገሳት ነው የወደቀችው ለማለት ነው፤ ከዚህ ጋር ስብሀት ነጋ የሚናገራቸውን ንግግሮች ስትሰማ አስተሳሰባቸው ይገባሀል፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ ሰምተህ ከሆነ ኢትዮጵያን ዘመናዊ ሰራዊት የተገነባው ከ1983 በኋላ ነው የሚል አይን ያወጣ ውሸት ሲነገር ነበር፡፡ እውነቱን ለመናገር የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሰራዊት የተገነባው በአፄ ኃይለስላሴ የስልጣን ዘመን ነው፤ህወሓት አዲስ ያቋቋመው አንድም ተቋም የለም፣ እንደውም ህወሓት ሲመጣ ባህር ኃይሉን አጥተናል፡፡ ይህን ክደው እነሱ እንደገነቡት ለማስመሰል ይሞክራሉ፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- በቅርቡ አዜብ መስፍን “መለስ በአራት ሺ ብር ደመወዝ የኖረ ነው” ማለታቸው መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፤ በተቃራኒው ደግሞ መለስም ሆኑ ስርአታቸው በሙስና ይታማሉ፡፡ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለህ?

ጃዋር፡- በአራት ሺ ብር… እንኳን የናጠጠ ቤተመንግስት ውስጥ የሚኖር ግለሰብ ይቅርና አዳማ የምትኖረው እናቴ እንኳን በዛ አትኖርም፡፡ ይሄ ሹፈት ነው፡፡ የሆነ ጊዜ ሰማሁት ቀልድ አለ፡፡ በስልሳዎቹ የነበሩት ወጣቶች የጻፉት ቀልድ ነው፤ አንድ ጊዜ የንጉሱ ልጅ አሜሪካን መጥታ “የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት ስንት ነው ሲሏት፤ ሀምሳ አራት ነው አለች” የሚል፡፡ እሷ የቆጠረችው የቤተመንግስቱን ሰው ብቻ ነው፡፡ አሁንም ሴትየዋ የተናገሩት ነገር ቀልድ ነው፡፡ ሌላም ሰምቻለሁ “መለስ አይዲ ካርድ እንኳን አልነበረውም” ብላለች፡፡ እንዴት ነው ነገሩ ሰውየው በምን ነበር ውጪ ሀገር ይሄድ የነበረው? ነው ወይስ ሴትየዋ ፓስፖርት አይ ዲ ካርድ እንደሆነ አታውቅም? ደሞ በፔሮል ነው ይኖር የነበረው ብላለች እንዴት ነው አይ ዲ ካርድ የሌለው ሰው በፔሮል የሚከፈለው አይ ዲ ካርድ የሌለው ሰውኮ በመንግስት አይታወቅም መኖሩም አለመኖሩም አይታወቅም ማለት ነው፡፡ ይሄን ስታየው ምን አይነት ሰዎች ሀገር እያስተዳደሩ እንደሆነ ግራ ይገባሀል፡፡

የሴትየዋ ንግግር ግን ሌላም መልዕክት አለው፤ አየህ እንደሚታወቀው ህወሓቶች ትላልቅ ሙክቶች ሆነዋል፣ ብዙ ገንዘብ አካብተዋል፡፡ መለስ ገንዘቡን የት እንደሚያስቀምጠው አይታወቅም፣ የሌሎቹ ግን በፓርቲ ውስጥ ሆነህ ስታየው ይታወቃል፤ ፎቅ አላቸው ሌላ ሌላም፡፡ ከዚህ ስትነሳ ንግግሯ እነዛን ሰዎች ለመሳደብና ለማሳነስ የምታደርገው ይመስለኛል “እናንተ ለገንዘብ ስትሯሯጡ ነበር የእኔ ባል ግን ገንዘብ ሳያስብ ለፓርቲውና ለሀገሩ ነዶ ያለቀ ሰው ነው” በማለት በውስጥ ያሉ ሀብት ያካበቱ ሰዎችን ለመንካት የተናገረችው ይነስለኛል፡፡ ከዚህ በፊትም ተመሳሳይ ነገር አሜሪካ መጥታ ተናግራለች፡፡ ለነገሩ ብዙም ቦታ የሚሰጠው አይመስለኝም እንኳን ሌላው ማህበረሰብ ይቅርና በፓርቲው ሰዎችም ንግግሯ እንደሹፈት እንጂ በቁምነገር የሚወስዱት አይመስለኝም፡፡

ከሁሉ በላይ የሚያሳስበኝ ሀዜብ የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆና የምትመጣ ከሆነ ለከተማዋ አደገኛ ውድቀት ያስከትላል የሚለው እንጂ እሷ ይሄን ተናገረች አልተናገለች ሰው ምን ያህል ገንዘብ እንደዘረፉ ያውቃል፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- የፌደራሉ መንግስት ሹመኞች ወደአዲስ አበባ ምክርቤት መምጣታቸው ምና ያሳያል?

ጃዋር፡- እንደሚታወቀው አዲስ አበባ የሀገሪቱ እምብርት ነች ስለሆነም ከተማዋን መምራት ሀገር እንደመምራት ይቆጠየራል ለዚህነው፡፡ በተለይ የሀዜብ ወደ አዲስ አበባ መምጣት የስልጣን ፍላጎች ይመስለኛል፡፡ እንደሚታወቀው የፓርላማ ወንበር የምትፈልገውን ለመስራት አይመቻትም፣ በፌደራል ደረጃ ያለው ትልቁ ስልጣን ተያዟል ስለዚህ የሆነ ቦታ ከፍተኛ ስራ አስፈፃሚ(executive) መሆን ስላለባት አዲስ አበባ ላይ ከንቲባ ለመሆን እንደፈለገት ነው የሚገባኝ፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- ውድ ጊዜህን ሰውተህ ለጥያቄዎቻችን ምላሽ ስለሰጠኸን እናመሰግናለን

ጃዋር፡- እኔም ከልብ አመሰግናለሁ እዛሀገር ውስጥ የአፈናና ስንት አይነት ጫና እየደረሰባችሁና ጋዜጣችሁ ተዘግቶባችሁ በቁርጠኝነት እጃችንን አጣጥፈን አንቀመጥም ብላችሁ ለምታደርጉት ስራ ያለኝ አድናቆት በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ እኛ የሚያስፈልገን እንዲ አይነት ስራ ነው፤ ወደ ፊትም በትፈልጉትና በምችለው አቅሜ ሁሉ ከጎናችሁ ለመቆም ቃል እገባላችኋለው፡፡

http://www.fnotenetsanet.com/?p=4026

posted by Tseday Getachew

Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: