Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

የግፍ ጽዋ ትሞላለች ! ያኔ………! – 21 አመት ሙሉ ተሸከምናችሁ

Getaneh Balcha

መጋቢት 8/2ዐዐ5 ” ለፋሽስቱ የጦር ወንጀለኛ ለማርሻል ግራዚያኒ ክብር መስጠት የአባቶቻችንን መስዋእትነት ማራከስ ነው!” በሚል አላማ የጣሊያን መንግሥት አፊሌ በሚባል ግዛት ለግራዚያኒ የሰሩለትን ሙዚየምና የመናፈሻ ስፍራ በመቃወም በተጠራው የተቃውሞ ሰልፍ ጋር በተያያዘ የገጠመኝን እስራትና ዱላ ለፌስ ቡክ ዘመዶቼ ላካፍላችሁ፡፡ በጽሁፌ እሁድ መጋቢት 8/ 2005 የነበረውን ምርመራ ሂደት ብቻ እገልጻላሁ፡፡ እኔና 2 ልጆች ቅዳሜ መጋቢት 7/2005 በአራዳ ፖሊስ መምሪያ ውስጥ ታስረን ያደርን በመሆኑ ለምርመራ የመጀመሪያ ተጠሪዎች ሆንን ፡፡ ከሦስታችን አንድ ሰው ይምጣ ሲባል ብርሀኑ ተ/ያሬድ የሚባል የባለራዕይ ወጣቶች ማህበር አመራር ቀድሞ ሄደ፡፡ በምርመራ ክፍሉ ውስጥ በጣም ብዙ ቆየ ፤ በመሀልም በክፍሉ ውስጥ መንጓጓት ይሰማን ነበር፤ ውጭ ያለነው እየደበደበው ይሆን ብለን አሰብን! ሌላ ምን ማለት ይቻላል! አብራኝ የነበረችው ሌላ የባለራዕይ ወጣቶች አመራር ዮዲት ይገዙ ወደሌላ የምርመራ ክፍል ተጠርታ ሄደች፡፡ ብቻዬን ቀረሁ።ብርሀኑ ከረዥም የምርመራ ቆይታ በኋላ ወጣ! ዓይኑ ቀልቷል፣ ፊቱ አባብጧል፣ ሲራመድ እያነከሰ ነው። በብርሀኑ ፊትና አካል ላይ የሚታየው ሲገባ ከነበረው ገጽታ ፍጹም የተለየ ነበር።እንደደበደቡት ተረዳሁ!

ምርመራ የሚደረግበት ክፍል ተጠርቼ ስሄድ ዱላ ለእኔም እንደማይቀርልኝ ገምቼ ነበር። ግምቴም ትክክል ሁኖ ልክ ወደ ምርመራ ክፈሉ ስገባ መርማሪው እናትህን እንዲህ ላርጋት የሚል የብልግና ስድብና በመማታት ጀመረኝ! እንዳይሰድበኝ እንዲሁም እንዲመታኝ እንደማልፈቅድለት በቃላትም በአካልም እንቅስቃሴ ስገልፅለትና ለመቀመጥ ወደወንበር ስሄድ መሬት ተቀመጥ ብሎ አመናጨቀኝ፤ ፈቃደኛ አልሆንኩም ይሄኔ ብቻውን የፈለገውን የመንፈስ ስብራትና የበላይነት እንደማያገኝ ተረዳ። ከምርመራ ክፍሉም በመውጣት እርዱኝ በማለት ፖሊሶችና የእጅ ማሰሪያ ካቴና እንዲመጣለት ጠየቀ። የርዳታ ጥሪውን ተከትሎ ሁለት ፖሊሶችና (ወደፊት የመርማሪውንና የፖሊሶች ማንነት በስፋት እመለስበታለሁ) ካቴና ይዘው መጡ።ሊመቱኝ ሲመጡም ተቃውሞዬን በማሳየትና ሌሎች ታሳሪዎች ስደበደብ ምስክር እንዲሆኑ ከምርመራው ክፍል በመውጣት ባቅራቢያ የሚገኙትን ሰዎች ስም መጣራት ጀመርኩ።እየጎተቱ ወደምርመራ ክፍሉ ለሶስት አስገቡኝ፤ ወዲ ተረዋ፣ 20 አመት ሙሉ ተሸከምናችሁ፣ አንተን ብሎ መንግስት ገልባጭ፣ ተላላኪ ሌላም ክብር የሚነካ ቃል እየተናገሩ አናቴንና ፊቴን መቱኝ፤ በጫማ ጥፊና በቡጢ አፌንና አፍንጫዬንም ደገሙኝ፤ በሀይለኛውም ከአፌና ከአፍንጫዬ ደም ይፈሰኝ ጀመር፤ ብዙ ለጆሮ ይሚሰቀጥጡ የዘረኝነትና የብልግና ስድቦችን እየሰደቡ እጄን በካቴና አሰሩኝ።ፖሊሶቹም ለመርማሪው ትተውኝ ሄዱ።

ብዙ ድበደባ ከደረሰብኝና በካቴና እጄን ከተሰርኩ በኋላ መርማሪው የጠየቀኝ ጥያቄ ስሜን፣ የእናቴን ስም፣ የፌስ-ቡክና ኢሜይል አድራሻና የመክፈቻ ቁልፉን፣ የቅርብ ጓደኞቼን ስም፣ የቤተሰቦቼን ስም፣ በፖለቲካ ተቋም ውስጥ ያለኝን ኃላፊነት፣ ብሔር፣ መቼ የተቃውሞ ፖለቲካ ድርጅት አባል (ደጋፊ) እንደሆንኩ፣ የምሰራበትን ቦታ፣ የት/ደረጃዬን፣ የቤተሰብ ሁኔታ እና አድራሻ ነበር፡፡ እኔን ሣይጠይቅ የደህንነት ተቋም ነኝ የሚል አካል በቀላሉ ሊያገኛቸው የሚችላቸውን መልሶች ደብድቦ፣ በካቴና አስሮ ምናልባትም ከተያዝኩበት ሁኔታና መንፈስ ጋር ፍፁም ያልተያያዘ ጥያቄ የሚጠይቀኝ ለምን ይሆን? ለማስፈራራት! አንፈራም ! አሁንም አንፈራም ! ግራዚያኒ 30ሺህ ኢትዮጵያውያንን በሶስት ቀናት ውስጥ የጨፈጨፈ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ አርበኞች በዱር በገደል ያደረጉትን ትግል መስበርና ማስቆም አልቻለም። በአያቶቻችንና በአባቶቻችን ደምና አጥንት የተገነባውን ሀገር ለማስከበር በማስፈራራት ማስቆም አይቻልም!! እኛም የነዚህ አርበኞች ልጅና የልጅ ልጆች መሆናችን ሊታወቅ ይገባል።በወቅቱ በእስር ላይ የነበሩት ልጆች ሲያዜሙት በነበረው የመሀሙድ አህመድ ዜማ የዛሬውን ጹሁፍ ላብቃ። (ይቀጥላል)

ተከብረሽ የኖርሽው በአባቶቻችን ደም!

በአባቶቻችን ደም!

እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም!

ያስደፈረሽ ይውደም!

posted by Tseday Getachew

 

Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: