Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

ኢሳት ዜና – መጋቢት ፲፪ ቀን ፳፻፭፪ ዓ/ም

በአፋር ህጻነት በርሀብ እየረገፉ ነው
መጋቢት ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በክልሉ ካለፉት አራት ወራት ጀምሮ የተከሰተው ከፍተኛ ረሀብና የውሀ እጥረት የበርካታ ህጻናትን ህይወት መቅጠፉን ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።
ምንም እንኳ 60 በመቶ በሚሆነው የአፋር አካባቢ ከፍተኛ የሆነ የምግብና የውሀ እጥረት ቢከሰተም ፣ ችግሩ ከሁሉም ወረዳዎች አስከፊ ሆኖ በቀጠለበት የእዳ ወረዳ 6 ህጻናት በአንድ ወር ውስጥ ሞተዋል። ይህ አሀዝ በአንድ ሰፈር ብቻ የተጠናከረ እንጅ በአጠቃላይ በወረዳው በተከሰተው ረሀብና የውሀ እጥረት የሟቾች ቁጥር በብዙ መቶዎች ሊደርስ እንደሚችል የአካባቢው ተወላጆች ገልጸዋል።
አንድ ጀሪካን ውሀ በ60 ብር ለመግዛት መገደዳቸውን የገለጹት አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የእዳ ወረዳ ነዋሪ፣ የአካባቢው ነዋሪ ፍየሎቹና ግመሎቹ አልቀውበት ወደ አሳይታ ስደት መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡ አሳይታ በሰላም የደረሱት በህይወት ሲትረፉ ሌሎች ደግሞ በመንገድ ላይ አልቀዋል ።
የመንግስት እርዳታ እንዳልመጣላቸው የተነጋሩት ነዋሪዎቹ ፣ አስቸኳይ እርዳታ ካልደረሰ አስከፊ እልቂት ይፈጠራል ብለዋል።
በአካባቢው የትጥቅ ትግል በማድረግ ላይ የሚገኘው የአፋር ጋድሌ ሊ/መንበር ኮሎኔል ሙሀመድ አህመድ ለኢሳት እንደገለጡት ከፍተኛ ረሀብ በአካባቢው መግባቱን ድርጅታቸው እንደሚያውቅ ገልጸዋል።
በዚህ አመት ከአፋር ሌላ በሶማሊና በተለያዩ የአማራ፣ የደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች ድርቅ መግባቱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በአዲስ አበባ ህጻናት በምግብ እጦት ትምህርታቸውን መከታተል እንዳልቻሉ ሸገር ኤፍ ኤምን በመጥቀስ ኢሳት ትናንት መዘገቡ ይታወሳል።
በግብርናው መስክ ከፍተኛ እመርታ እንዳገኘ ከመናገር ተቆጠቦ የማያውቀው የኢህአዴግ አገዛዝ ፣ ላለፉት 21 አመታት ኢትዮጵያን በምግብ ራሱዋን እንደሚያስችል ቢናገርም እስካሁን ድረስ የታየ ለውጥ የለም። በቅርቡ ይፋ ሆነ አንድ ጥናት እንዳለመከተው ከ7 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በምግብ ለስራ ታቅፈው ከአለም ባንክና ከአውሮፓ ህብረት በሚለገስ ስንዴ እየተደጎሙ ነው። በዚህ አመት የአስቸኳይ ምግብ እርዳታ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከፍ ሊል እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በመላው አገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የውሀ እና የምግብ እጥረት ቢከሰተም ገዢው ሀይል በቅርቡ 200 ሚሊዮን ብር በማውጣት የብሄር ብሄረሰቦችን በአል አክብሮአል። ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት ደግሞ የመከላከያ ቀንን አክብሮአል።

የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በአብዛኛው ነባር አመራሮቻቸው በስራ አስፈጻሚነት ቀጠሉ
መጋቢት ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ሰሞኑን በተከታታይ ባካሄዱዋቸውና በመተካካት ረገድ እምብዛም ለውጥ ያልታየባቸው
ጉባዔዎች በአብዛኛው ነባር አመራሩን ይዘው ሲያስቀጥሉ መጠነኛ የሆነ እርምጃም ወስደዋል፡፡
በዚሁ መሰረት ኦህዴድ አቶ አባዱላ ገመዳን፣ ግርማ ብሩን እና ኩማ ደመቅሳን ከስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት ሲያሰናብት፤ ብአዴን በበኩሉ የፍትህ ሚኒስትር የሆኑትን አቶ ብርሃን ኃይሉን፣ደኢህዴን ደግሞ አቶ ተሾመ ቶጋን አሰናብቷል፡፡
ብአዴን በጤና ችግር መደበኛ ስራቸውን ማከናወን የተሳናቸውና ነባር ታጋይ የሆኑትን አቶ ህላዊ
ዮሴፍን፣ኦህዴድ ወ/ሮ አስቴር ማሞን በኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚነት እንዲመረጡ አድርጓል፡፡በተጨማሪም ኦህዴድ
የፌዴራል ፖሊስ ኮምሽነሩን አቶ ወርቅነህ ገበየሁን የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ አባል እንዲሆኑ መርጧቸዋል፡፡
በሟቹ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዕቅድ መሰረት በመተካካት ሒደቱ እስከ 2007 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ ቦታ ይለቃሉ
ተብለው ይገመቱ የነበሩት ነባር ታጋዮች ለቀጣይ ሁለት ዓመት ተኩል ጊዜያት እንዲቀጥሉ መደረጉ በተለይ ከፍተኛ
አመራሩ የመለስን ራዕይ ለማሳካት በተደጋጋሚ የገባውን ቃል ማጠፉን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ተናግረዋል፡፡
በ2003 ዓ.ም በመተካካት ስም የመንግስት ከፍተኛ ኃላፊነታቸው የለቀቁት አቶ አዲሱ ለገሰን ጨምሮ አቶ በረከት
ስምኦን፣አቶ ህላዊ ዮሴፍ፣አቶ አባይ ወልዱ እና የመሳሰሉት ስልጣናቸውን ወደማጠናከር ፊታቸውን
ማዞራቸው የመተካካት ዕቅዱ ውሃ እንደበላው ማሳያ ሆኗል፡፡ አቶ አዲሱ ከድርጅቱ በአቶ መለስ አማካኝነት ከተሰናበቱ በሁዋላ ተመልሰው መምጣታቸው አስገራሚ ሆኗል። አቶ አዲሱ ከስልጣን እንዲነሱ የተደረገው እርሳቸው ባልጠበቁበት መንገድ እንደነበር መግለጻቸው ይታወሳል።
በመተካካት ስም በ2003 የመንግስት እና ከፓርቲ ኃላፊነታቸው የለቀቁትን እነ አቶ ስዩም መስፍን ጨምሮ ሌሎች 9
የህወሃት አባላት በራሳቸው ፈቃድ በአብዛኛው ከጤና ጋር በተያያዘ ድርጅቱን ለመልቀቅ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት የተሰናበቱ ሲሆን የእነዚህ ሰዎች መልቀቅ እንደመተካካት ለማየት እየተደረገ ያለው የማደናገሪያ ፕሮፖጋንዳ አሳዛኝ መሆኑን ምንጮቻችን ተናግረዋል፡፡በራሳቸው ፈቃድ ከለቀቁት መካከል አቶ ስዩም መስፍን ፣ አቶ ብርሃነ ገብረክርስቶስ ፣ አቶ አርከበ
ዕቁባይና አቶ ዘርዓይ አስገዶም ይገኙበታል፡፡
የዘጠኝ የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በአንድ ጊዜ መልቀቂያ ማቅረባቸው አጋጣሚ ሳይሆን ከአቶ መለስ ህልፈት
በሓላ በህወሃት ውስጥ ከተፈጠረው ልዩነት ጋር በተያያዘ ሳይሆን እንደማይቀር ምንጫችን ቢጠቅስም ይህን በተመለከተ
ለማረጋገጥ ያደረግነው ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም፡፡ ብዙዎች እንደሚገምቱት ከአቶ አርከበ እቁባይ ጋር ጤነኛ ግንኙነት ያልነበራቸው ወ/ሮ አዜብ መስፍን በዚህ ጉባኤ በድል አድራጊነት ወጥተዋል። ህወሀት የአቶ አባይ ወልዱን ባለቤት ወ/ሮ ትረፉ ኪዳነማርያምንም በስራ አስፈጻሚነት መርጧቸዋል።
ድርጅቶቹ ባካሄዱት ምርጫ መሰረት ከህወሃት፡- አቶ አባይ ወልዱ፣ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል፣ወ/ሮ አዜብ
መስፍን፣አቶ አባይ ጸሐዬ፣ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሔር፣አቶ በየነ ምክሩ፣አቶ ኪሮስ
ቢተው፣አቶ አስመላሽ ወ/ስላሴ፤ከብአዴን፡-አቶ አዲሱ ለገሰ፣አቶ በረከት ስምኦን፣አቶ አያሌው ጎበዜ፣አቶ ገዱ
አንዳርጋቸው፣አቶ ደመቀ መኮንን፣አቶ አለምነው መኮንን፣አቶ ካሳ ተ/ብርሃን፣አቶ ህላዊ ዮሴፍ፣አቶ ተፈራ
ደርበው፤ከኦህዴድ፡-አቶ አለማየሁ አቶምሳ፣አቶ ሙክታር ከድር፣ወ/ሮ አስቴር ማሞ፣አቶ ወርቅነህ ገበየሁ፣አቶ
ሶፊያን አህመድ፣አቶ ድሪባ ኩማ፣አቶ አድልቃድር ሁሴን፣አቶ ኡመር ሁሴን፣አቶ አበራ ኃይሉ፤ ከደኢህዴን፡-አቶ
ኃይለማርያም ደሳለኝ፣አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣አቶ ሬድዋን ሁሴን፣አቶ መኩሪያ ኃይሌ፣አቶ ሲራጅ ፈጌሳ፣ዶ/ር ሽፈራው
ተ/ማርያም፣አቶ አለማየሁ አሰፋ አቶ ደሴ ዳልቼ፣አቶ ተስፋዬ ቢነግዴ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ሆነው እንዲሰሩ
በየድርጅቶቻቸው ተመርጠዋል፡፡
ከፊታችን ቅዳሜ መጋቢት 14 ቀን እስከ 17 ቀን 2005 ዓ.ም በባህርዳር ከተማ የሚካሄደው የኢህአዴግ ጉባዔ
አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን በሊቀመንበርነት፣አቶ ደመቀ መኮንን በምክትል ሊቀመንበርነት በድጋሚ ይመርጣል ተብሎ
እንደሚጠበቅ ምንጮቻን ጠቁመዋል፡፡
የኢህአዴግ ድርጅቶች ያደረጉትን ሹም ሽር በተመለከተ ጥያቄ ያቀረብንላቸው አንድ የቀድሞ የሀወሀት ነባር ታጋይ ፡ ምርጫውን “ውሀ ቢወቅጡት ነው” ብለውታል። “ከእነዚህ ሰዎች ምንም የሚጠበቅ ነገር የለም፣ ምን አዲስ ነገር እንደማይፈጥሩም ይታወቃል። የአፈና ስርአቱ እንደሚቀጥል ጥሩ ማሳያ ነው” ብለዋል ታጋዩ።

ኢትዮጵያውያን በጄኔቭ የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ
መጋቢት ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ኢትዮጵያውያኑ ትናንት ባደረጉት የተቃውሞ ሰልፍ ገዢው ፓርቲ በሙስሊም ኢትዮጵያውያን ጥያቄ ዙሪያ የየዘውን አቋም ከማውገዝ ባለፈ፣ በአገረቱ ውስጥ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እየተባባሰ መምጣቱን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች የተለያዩ ክፍሎች አስታውቀዋል።
የሰላማዊ ሰልፉ አስተባባሪ ፣ የቢላል ኮሚቴ መስራችና ዋና ጸሀፊ የሆኑት አቶ ኤልያስ ረሺድ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አንደገለጡት ሰላማዊ ሰልፉ ሙስሊም ኢትዮጵያን የሚያደርጉትን ትግል ለአለማቀፉ ማህበረሰብ የማሳወቅ አላማ ነበረው
አቶ ኤልያስ ጉዳያቸውን ለተለያዩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ክፍሎች ማሳወቃቸውንም ገልጸው፣ ድርጅቶቹ ጉዳዩን በሂደት እንደሚመረምሩ እንደነገሩዋቸውም አብራርተዋል

በአባይ ግድብ ከሳሊኒ በመቀጠል ከፍተኛው ተጠቃሚ የወ/ሮ አዜብ መስፍን ቤተሰብ ድርጅት ነው ተባለ
መጋቢት ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ከሁለት ዓመት በፊት ኢሳት በወ/ሮ አዜብ መስፍን የእህት ልጅ በወ/ሮ አቲኮ ስዩም አምባየ የተመሰረተው ኦርቺድ ቢዝነስ ግሩፕ በጣሊያኑ ሳሊኒ ኮንስትራክሽን አማካኝነት በሚገነቡት ግልገል ጊቤ አንድ እና ግልገል ጊቢ ሁለት የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ፕሮጀክቶች ስሚንቶ እና የግንባታ እቃዎችን እንዲሁም ከፍተኛ ማሺነሪዎችን በማቅረብ ከፍተኛ የሆነ ትርፍ ማጋበሱን ዘግቦ ነበር።
በአባይ ወንዝ ላይ የሚሰራውን የህዳሴውን ግድብ ፕሮጀክት በቅርብ የሚያውቁ ሰዎች ለኢሳት እንደተናገሩት ይህ ኩባንያ ከሳሊኒ ጋር ግልጽነት የጎደለው የቢዝነስ ስምምነት በማድረግ በአሁኑ ጊዜ ለግንባታው የሚያስፈልገውን ስሚንቶ እንዲሁም ከባድ ማሺኖችን በማቅርብ ላይ ይገኛል።
የውስጥ ምንጮች እንደሚሉት ግድቡን ከሚገነባው ሳሊኒ በመቀጠል ከፍተኛ የሆነ ትርፍ የሚያገኘው ኦርቺድ ፣ ከየትኛውም ድርጅት ጋር ሳይወዳደር በእነ ወ/ሮ አዜብ መስፍን አማካኝነት የስሜንቶና ማሸንሪዎች አቅራቢ ሆኖ ቀርቧል።
ከድርጅቱ ድረገጽ ላይ ለመረዳት እንደተቻለው ድርጅቱ በግልገል ጊቤ የሀይል ማመንጫ የመንገድ ስራ፣ በአዲስ አበባ ጅማ የመንገድ ጥገና፣ በግልገል ጊቤ ሶስት ኤር ስትሪፕ ግንባታ፣ በኮሌ ሃላላ የመንገድ ጥገና፣ በአዲስ አበባ አዳማ የመንገድ ፕሮጀክት፣ በአርባ ምንጭ አየር ማረፊያ የመንግድ ጥገና እና በሌሎችም የመንገድና የህንጻ ስራዎች ላይ ተሳትፎአል።
ኩባንያው ቦዲ ዋይዝ ጂም፣ ካፌ ፓኒኒ፣ ኦርቺድ ጄኔራል ኮንትራክተር፣ ኦርቺድ ትራንስፖርት፣ ኦርጂድ ትራንዚት፣ ኦርቺድ ማሽነሪ ሬንታል፣ ኤስ ኤንድ ኤስ እርሻ፣ ሂላላ ቱር ኤን ትራቭል፣ ሜትሮሉክስ ፍላወር፣ ናይል ስፕሪንግ ውሀ፣ ሬንቦው ጊፍት ሾፕ፣ ሪል ሳሎን፣ ወንደር ዊል ቢዝነስና ሌሎችም በአዲስ አበባና በመላው አገሪቱ ታዋቂ የሆኑ የንግድ ድርጅቶችን በስሩ አቅፎ የያዘ ነው።
ወ/ሮ አቲኮ ኢህአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ይህ ነዉ የሚባል ኃብት እንዳልነበራቸው ታሪካቸውን ያጠኑ የኢሳት ዘጋቢዎች ያረጋገጡ ሲሆን ባለፉት 20 አመታት ግን በልዩ ትዕዛዝ “ኦርቺድ” ቢዝነስ ግሩፕ የሚባል ድርጅት ተከፍቶላቸው ሆን ተብሎ አያሌ የግንባታ ጨረታዎችን እንዲያሸንፉና በአጭር ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ቱጃሮች ተርታ ለመመደብ እንደቻሉ መግለጻችን ይታወሳል።
የሀወሀት ኢህአዴግ ባለስልጣናት በዘመዶቻቸው ስም የሚገነቡዋቸው የቢዝነስ ተቋማት እየተበራከቱ መምጣቱን በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል። የባለስልጣናትን የሀብት ምዝገባ ጨርሶ በአጭር ጊዜ ይፋ አድረጋለሁ በማለት ሲፎክር የነበረው ጸረ ሙስና ኮሚሽንም ቃሉን ለመጠበቅ እንደተሳነው መዘገባችን ይታወሳል። ኮሚሽኑ ባለስልጣናቱ በዘመዶቻቸው ስም ዬያዙትን ሀብትና ንብረት ለመመዝገብ ስልጣን እንዳልተሰጠው መግለጹ ይታወሳል።
የህዳሴውን ግድብ ለመጨረሽ ከ90 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ይታወቃል። በቀን እስከ 30 ሰራተኞች በክፍያ ምክንያት ስራቸውን እየለቀቁ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል።

ESAT

posted by Tseday Getachew

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: