Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

ኢሳት ዜና – መጋቢት ፲፩ ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

በአባይ ግድብ ከሳሊኒ በመቀጠል ከፍተኛው ተጠቃሚ የወ/ሮ አዜብ መስፍን ቤተሰብ ድርጅት ነው ተባለ
መጋቢት ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ከሁለት ዓመት በፊት ኢሳት በወ/ሮ አዜብ መስፍን የእህት ልጅ በወ/ሮ አቲኮ ስዩም አምባየ የተመሰረተው ኦርቺድ ቢዝነስ ግሩፕ በጣሊያኑ ሳሊኒ ኮንስትራክሽን አማካኝነት በሚገነቡት ግልገል ጊቤ አንድ እና ግልገል ጊቢ ሁለት የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ፕሮጀክቶች ስሚንቶ እና የግንባታ እቃዎችን እንዲሁም ከፍተኛ ማሺነሪዎችን በማቅረብ ከፍተኛ የሆነ ትርፍ ማጋበሱን ዘግቦ ነበር።
በአባይ ወንዝ ላይ የሚሰራውን የህዳሴውን ግድብ ፕሮጀክት በቅርብ የሚያውቁ ሰዎች ለኢሳት እንደተናገሩት ይህ ኩባንያ ከሳሊኒ ጋር ግልጽነት የጎደለው የቢዝነስ ስምምነት በማድረግ በአሁኑ ጊዜ ለግንባታው የሚያስፈልገውን ስሚንቶ እንዲሁም ከባድ ማሺኖችን በማቅርብ ላይ ይገኛል።
የውስጥ ምንጮች እንደሚሉት ግድቡን ከሚገነባው ሳሊኒ በመቀጠል ከፍተኛ የሆነ ትርፍ የሚያገኘው ኦርቺድ ፣ ከየትኛውም ድርጅት ጋር ሳይወዳደር በእነ ወ/ሮ አዜብ መስፍን አማካኝነት የስሜንቶና ማሸንሪዎች አቅራቢ ሆኖ ቀርቧል።
ከድርጅቱ ድረገጽ ላይ ለመረዳት እንደተቻለው ድርጅቱ በግልገል ጊቤ የሀይል ማመንጫ የመንገድ ስራ፣ በአዲስ አበባ ጅማ የመንገድ ጥገና፣ በግልገል ጊቤ ሶስት ኤር ስትሪፕ ግንባታ፣ በኮሌ ሃላላ የመንገድ ጥገና፣ በአዲስ አበባ አዳማ የመንገድ ፕሮጀክት፣ በአርባ ምንጭ አየር ማረፊያ የመንግድ ጥገና እና በሌሎችም የመንገድና የህንጻ ስራዎች ላይ ተሳትፎአል።
ኩባንያው ቦዲ ዋይዝ ጂም፣ ካፌ ፓኒኒ፣ ኦርቺድ ጄኔራል ኮንትራክተር፣ ኦርቺድ ትራንስፖርት፣ ኦርጂድ ትራንዚት፣ ኦርቺድ ማሽነሪ ሬንታል፣ ኤስ ኤንድ ኤስ እርሻ፣ ሂላላ ቱር ኤን ትራቭል፣ ሜትሮሉክስ ፍላወር፣ ናይል ስፕሪንግ ውሀ፣ ሬንቦው ጊፍት ሾፕ፣ ሪል ሳሎን፣ ወንደር ዊል ቢዝነስና ሌሎችም በአዲስ አበባና በመላው አገሪቱ ታዋቂ የሆኑ የንግድ ድርጅቶችን በስሩ አቅፎ የያዘ ነው።
ወ/ሮ አቲኮኢህአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ይህ ነዉ የሚባል ኃብት እንዳልነበራቸው ታሪካቸውን ያጠኑ የኢሳት ዘጋቢዎች ያረጋገጡ ሲሆን ባለፉት 20 አመታት ግን በልዩ ትዕዛዝ “ኦርቺድ” ቢዝነስ ግሩፕ የሚባል ድርጅት ተከፍቶላቸው ሆን ተብሎ አያሌ የግንባታ ጨረታዎችን እንዲያሸንፉና በአጭር ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ቱጃሮች ተርታ ለመመደብ እንደቻሉ መግለጻችን ይታወሳል።
የሀወሀትኢህአዴግ ባለስልጣናት በዘመዶቻቸው ስም የሚገነቡዋቸው የቢዝነስ ተቋማት እየተበራከቱ መምጣቱን በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል። የባለስልጣናትን የሀብት ምዝገባ ጨርሶ በአጭር ጊዜ ይፋ አድረጋለሁ በማለት ሲፎክር የነበረው ጸረ ሙስና ኮሚሽንም ቃሉን ለመጠበቅ እንደተሳነው መዘገባችን ይታወሳል። ኮሚሽኑ ባለስልጣናቱ በዘመዶቻቸው ስም ዬያዙትን ሀብትና ንብረት ለመመዝገብ ስልጣን እንዳልተሰጠው መግለጹ ይታወሳል።
የህዳሴውን ግድብ ለመጨረሽ ከ90 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ይታወቃል። በቀን እስከ 30 ሰራተኞች በክፍያ ምክንያት ስራቸውን እየለቀቁ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል።

የኢህአዴግ የመተካካት ዕቅድ በተግባር እየከሸፈ ነው ተባለ
መጋቢት ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ኢህአዴግ ያወጣው የአመራር መተካካት ከመፈክር ባለፈ እየተተገበረ አለመሆኑን ለግንባሩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የግንባሩ ከፍተኛ አመራሮች ከ17 ዓመታት በላይ በጫካ ትግል ላይ ዕድሜያቸውን ያሳለፉ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ
በአሁኑ ወቅት በተለይ ከዕድሜና ሕመም ጋር ተያይዞ ብዙዎቹ የያዙትን ከፍተኛ ኃላፊነት መወጣት የማይችሉበት ደረጃ ላይ
እየደረሱ በመሆናቸው በሌላ አመራር የመተካታቸው ጉዳይ ታምኖበት የአፈጻጸም ፕሮግራም ወጥቶለት እንደነበር
ይታወሳል፡፡
በዚሁ ፕሮግራም መሰረት እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ ነባሩ አመራር በአዲስ ኃይል እንዲተካ በሟቹ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ የተነደፈ ዕቅድ ቢኖርም በአሁን ወቅት አፈጻጸሙ ከመፈክር በዘለለ እየተተገበረ አለመሆኑ ታውቋል፡፡ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ከፍተኛ አመራሩ ስልጣን ለማስረከብ ፈቃደኛ ካለመሆኑ ጋር የተያያዘ ነው፡፡
ከመስከረም 5 እሰከ 7/2003 ዓ.ም በአዳማ በአባገዳ አዳራሽ የተካሄደውን የግንባሩን 8ኛ ጉባዔ ተከትሎ በዚሁ
የመተካካት መርህ መሰረት ከህወሃት አቶ ስዩም መስፍን፣አቶ አባይ ጸሐዩ፣አቶ አርከበ ዕቁባይ፣ከብአዴን አቶ
አዲሱ ለገሰ ፣አቶ ተፈራ ዋልዋ፣አቶ ታደሰ ካሳ ከፓርቲ የአመራር ቦታቸው እንዲገለሉ ተደርገዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በስራ ላይ ያሉት እነአቶ አባይ ወልዱ፣ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል፣አቶ ጸጋዩ በርሄ፣አቶ በረከት
ስምኦን፣የመሳሰሉ ነባር አባላት ስልጣናቸውን ለተተኪዎች ከማስተላለፍ ይልቅ ማጠናከር ላይ ተደምጠው መታየታቸው
ዕቅዱ መክሸፉን ማሳይ ጥሩ ምልክት ነው ብለዋል ምንጮች።
የአቶ መለስን ራዕይ አስፈጽማለሁ በሚል ጠዋት ማታ የሚምሉት በስልጣን ላይ ያሉ ወገኖች ፣ የመተካካቱን ጉዳይ
ከወሬና ከወረቀት በዘለለ መተግበር አለመቻላቸው ብዙዎችን የድርጅቱን አባላት ጭምር እያነጋገረ ነው።
ከሁለት ዓመት በፊት በአዳማ የተካሄደው 8ኛ የኢህአዴግ ጉባዔ መተካካትን በተመለከተ ሲገልጽ፡ “በጉባኤያችን ማግስት በድርጅታችን የአመራር መተካካት ስርአትን ለመቅረፅና በተግባር ላይ ለማዋል ሰፋ ያለ
እንቅስቃሴ ተካሂዷል፡፡ ድርጅታችን አላማውን ከዳር ለማድረስ ትግሉ ከሚያልፍባቸው መድረኮች ጋር ራሱን እያጣጣመና
የመምራት ብቃቱን እያዳበረ መጓዝ እንዳለበት በማመን ቀጣይ የአመራር ትውልድ የመፍጠር ስራው በስርአት እንዲመራ
ጥረት ተደርጓል፡፡ በዚህ መሰረት ነባሩ የአመራር ሃይል በስራ ብዛትና በእድሜ መግፋት መስራት የማይችልበት ደረጃ
ላይ ከመድረሱ በፊት ደረጃ በደረጃ በአዳዲስ የአመራር ሃይሎች እየተተካ እንዲሄድ ማድረግ የሚያስችል አቅጣጫ
ሊቀየስ ችሏል፡፡ በዚህ አቅጣጫ መሰረት ነባሩ አመራር ከፊት መስመር ለቆ በአዲሱ እንዲተካና በድርጅት አመራርነት
ግን አስተዋፅኦውን እያበረከተ የሚቀጥልበት ሁኔታ እንዲፈጠር ተወስኖ ተግባራዊ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በዚህ
አቅጣጫ መሰረት ነባሩ አመራር በሶስት ምዕራፎች ተከፋፍሎ በሚቀጥሉት አምስት አመታት ከፊት መስመር የሚለቅና
ሚናውን እየተጫወተ የሚቀጥልበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡ ” ብሎአል።
ይህ መግለጫ አያይዞም “በተመሳሳይ መልኩ የአብዮታዊ ዴሞከራሲያዊ አላማዎቻችንን ቀጣይ ተፈፃሚነት ለማረጋገጥ የአመራር መተካካት ስርአታችን መካከለኛ አመራሩንም የሚያካትት እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችል አቅጣጫ አስቀምጠን
ተንቀሳቅሰናል፡፡ከዚህ አኳያ ቀደም ሲል የተጀመረውን ሰፊ የመካከለኛ አመራር ሃይል የመፍጠርና በየስራው መድቦ
በማጠናከር ሰፊ የመካከለኛ አመራር ሃይል እንዲኖረን ተደርጓል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በሁሉም እርከኖች
የመተካካት ስራው አፈፃፀም በየደረጃው ያሉ የአመራር አባላት ከአንድ እርከን ወደ ቀጣዩ እርከን ወይም ወደ ትምህርት
እድል የሚሸጋገሩበት አሰራር በዝርዝር ተጠንቶ እንዲፀድቅና ይህም መተካካቱ የሚፈፀምበት ተጨማሪ አቅጣጫ እንዲሆን
ተወስኗል፡፡ በአጠቃላይ ከመተካካት አኳያ የተከተልነው አቅጣጫ በአንድ በኩል የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ሃይላችንና
የስርአቱን ተጠናክሮ መቀጠል የሚያረጋግጥ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ህዝቡ ከመተካካት አኳያ ያነሳቸው ለነበሩ ጥያቄዎች
ትክክለኛ ምላሽ የሰጠ እንደሆነ በተግባር ከተገኘው ግብረ መልስ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ” ብሎአል።
በአሁኑ ወቅት አንዳንድ ነባር፣ ከፍተኛና መካከለኛ አመራር ላይ የሚገኙ ሰዎች ከትግል በሁዋላ ተምረን ብቃታችንን አሳድገን ሕዝባችንን ለማገልገል በተዘጋጀንበት ሰዓት መተካካት በሚል መገፍተራችን ተገቢ አይደለም በሚል በግልጽ
ተቃውሞአቸውን እየገለጹ ነው። አመራሮቹ በሙስና ያፈሩትን ሀብትና ንብረት ስልጣን ከለቀቅን እናጣዋለን ብለው ይሰጋሉ።
የፊታችን ቅዳሜ በባህርዳር ከተማ በሚጀምረው የግንባሩ 9ኛ ጉባዔ ላይ ከመተካካት አኳያ ብዙም የሚጠበቅ አዲስ
ነገር እንደማይኖር ይታመናል፡፡
ደኢህዴን ዛሬ ባካሄደው ጉባኤ እንደተጠበቀው አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝን የድርጅቱ ሊቀመንበር፣ አቶ ሽፈራው ሽጉጤን ደግሞ ም/ል ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል። በሌሎችም ድርጅቶችም ተመሳሳይ ምርጫዎች ሲካሄዱ ውሎአል።

የአፍሪካ መዲና-አዲስ አበባ የውሀ እና የመብራት ያለህ እያለች ነው
መጋቢት ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የውኃና የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ ይሻሻላል በሚል በትዕግስት ቢጠባበቁም፣ እየባሰበት እንደመጣና መፍትሔ በማጣታቸው ግራ መጋባታቸውን በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መግለፃቸውን ሪፖርተር ዘገበ።
እንደ ጋዜጣው ዘገባ ውኃና ኤሌክትሪክ ከዓመት እስከ ዓመት ተቋርጦባቸው እንደማያውቅ ሲነገርላቸው የነበሩ በተለይ በቤተ መንግሥት አቅራቢያ ያሉ ነዋሪዎች ሳይቀሩ አሁን ውኃ እያገኑ ያሉት በሳምንት ለሦስትና አራት ቀናት ብቻ ነው።
ኤሌክትሪክም በሳምንት ውስጥ በቀን ሁለትና ሦስት ጊዜ እየጠፋባቸው ንብረቶቻቸው ጭምር እየተቃጠሉባቸው መሆናቸውን የገለፁት ነዋሪዎቹ፤ አንዳንዴም በፍርኃት መብራት ሳያበሩ እንደሚያመሹ ገልጸዋል፡፡
በሞባይል ስልክ እየተነጋገሩ ሳለ መቃረጡን በተመለከተ ግን የተለመደ ችግር ስለሆነ ከመማረር ውጪ ምንም ሊያደርጉ አለመቻላቸውን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
የውኃና የኤሌክትሪክ ችግርን ግን በመማረር ሊያሳልፉትን ሊቋቋሙት እንዳልቻሉ ነው የሚናገሩት።
በተለይ የውኃ ችግርን መቋቋም እንደተሳናቸው የሚናገሩት ወ/ሮ በለጡ የተባሉ የ አካባቢው ነዋሪ፤ ቀደም ባሉት ጊዜያት አንዱ መንደር ውሀ ቢጠፋ በሌላ መንደር ካለ ቦኖ ውኃ ይገዙና የዕለት ችግራቸውን ይወጡ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን አሁን ግን በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኙ አካባቢዎች ሁሉ ውሀ ስለሚጠፋ የሚያደርጉት ግራ እንደገባቸው ተናግረዋል፡፡
የሕፃናትን ጥም ለማስታገስ የታሸገ ውኃ ለመግዛት ሲሞክሩ ለወትሮው አምስት ብር ይሸጥ የነበረው ግማሽ ሊትር እሽግ ውኃ ስምንት ብር ገብቷል እንደተባሉ የተናገሩት ወ/ሮ በለጡ፣ ነጋዴው ከሰው ያልተፈጠረ ይመስል አጋጣሚን ተጠቅሞ ለመክበር የሚያደርገው መሯሯጥ እንዳሳዘናቸው ይናገራሉ፡፡
ኤሌክትሪክ ቢቋረጥ በእንጨትና ከሰል ማብሰል እንደሚቻልና በኩራዝ ማምሸት ጊዜያዊ መፍትሔ እንደሚሰጥ የገለጹት ወይዘሮ በለጡ ‹‹የውኃን ችግር ግን ምን ያስታግሰው?›› በማለትም ይጠይቃሉ፡፡
ስለጉዳዩ በጋዜጠኞች የተጠየቁት የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋለም ባዩ ፤እርሳቸው ወደ ስብሰባ እንደሚገቡ በመጥቀስ አቶ ፈቃዱ የተባሉ የመሥርያ ቤቱ ባልደረባ ምላሽ እንደሚሰጡ ቢናገሩም፤አቶ ፈቃዱን ማግኘት ሳይቻል ቀርቷል።
አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የባለሥልጣኑ ባልደረባ ግን ውኃ የሚቋረጠው እጥረት ኖሮ ሳይሆን፣ ኤሌክትሪክ ሲቋረጥ ነው ብለዋል።
“የውኃ ፓምፖች የሚንቀሳቀሱት በኤሌክትሪክ ኃይል በመሆኑ፣ ኤሌክትሪክ ሲቋረጥ ውኃም ይቋረጣል፡፡” ያሉት የመስሪያ ቤቱ ባልደረባ፤” ችግሩ የባለሥልጣኑ ሳይሆን ከኮርፖሬሽኑ ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የውኃ እጥረት ችግር የሚፈጠረው ከኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ ጋር በተያያዘ እንደሆነ እና ከዚህም በላይ ኤሌክትሪክ በተደጋጋሚ እየተቋረጠ የነዋሪዎችን ንብረት እያቃጠለ ስለሚገኝበት ሁኔታ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁት የኮርፖሬሽኑን የዲስትሪቢዩሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ብርሃነ
‹‹ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ካልገጠመ በስተቀር በተለይ ከሐምሌ ወር 2004 ዓ.ም. እስከ የካቲት ወር 2005 ዓ.ም. ድረስ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል፤›› ብለዋል።
ኃይል የሚቋረጠው በፕሮግራም ለተለያዩ ጥገና ሥራዎች፣ ለመንገድ ግንባታና ለመሳሰሉት ጉዳዮች በመገናኛ ብዙኅን እየተነገረ ነው ያሉት አቶ መስፍና፤
ሌላው ኃይል የሚቋረጠው በተፈጥሮ አደጋና ትላልቅ ግንባታዎች በሚካሄዱባቸው አካባቢዎች የተለያዩ መሣሪያዎች ወድቀው መስመር ላይ ችግር ሲከሰት ብቻ ነው ብለዋል። አልፎ አልፎ ከዋናው ማሰራጫም ቴክኒካዊ ችግሮች ሲያጋጥሙ የኃይል ማቋረጥ እንደሚገጥም አቶ መስፍን አልሸሸጉም፡፡
አቶ መስፍን ችግሩ ከበፊቱ ቀንሷል ቢሉም በተጨባጭ መሬት ላይ የሚታየው ሀቅ ችግሩ እየከፋ መምጣቱን የሚያመላክት ነው።
እንደ ጋዜጣው ዘገባ ለወትሮው የችግሩ ተጠቂ ያልነበሩት መንደሮች ናቸው አሁን በውሀ እና በመብራት ችግር እየተማረሩ ያሉት።
እንደ ወ/ሮ በለጡ ሁሉ በአብዛኛዎቹ ክፍላተ ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎች የውኃና የኤሌክትሪክ በየጊዜው መጥፋት ችግር እየፈጠረባቸው መሆኑን ገልጸው፣ የሚመለከተውን የውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ቅርንጫፍና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ዲስትሪክት ጽሕፈት ቤቶችን ሲያነጋግሩ፣ እንኳን መፍትሔ ሊሰጧቸው ቀርቶ ሊያነጋግሯቸው ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ከ ኢትዮጵያ አልፋ የ አፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ የቧንቧ ውሀ፣የ ኤሌክትሪክ እና የስልክ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆነችው በአፄ ምኒልክ ጊዜ ቢሆንም እስካሁን ድረስ የተጠቀሱትን አገልግሎቶች ማሟላት አለመቻሏ ብዙዎችን ያስገረመ ሆኗል።
ለኢሳት የሚደርሱት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በሰቆጣ፣ መቀሌ፣ እና በተለያዩ የደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ከፍተኛ የሆነ የውሀ እጥረት ተከስቷል።

ፕሬዚዳንት ኦባማ እስራኤልን እየጎበኙ ነው
መጋቢት ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-አሜሪካዊው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ እስራኤል ሲገቡ ፣ አገራቸው ለእስራኤል ጠንካራ ወዳጅ አገር መሆኑዋን ገልጸዋል። እስራኤል እንደ አሜሪካ ጠንካራ ወዳጅ የላትም ብለዋል ፕሬዚዳንቱ። ለቅድስቲቱ አገር ሰላም መምጣት እንዳለበትም ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ ሀሙስ ወደ ዌስት ባንኩዋ ራማላህ ከተማ ተጉዘው ከፍልስጤም ባለስልጣናት ጋር ይነጋገራሉ። የፕሬዚዳንት ኦባማ ዋና የጉብኝት አላማ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የቆየ ወዳጅነት ማደስ ነው ተብሎአል።
ፕሬዚዳንቱ ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ በእስራኤል እና በአሜሪካ መካከል ያለው ግንኙነት ጥሩ አለመሆኑን ዘገባዎች ያመለክታሉ።
በኢራን የኒውክሊየር ጉዳይ ላይ በስልጣን ላይ ያለው የናታኒያሁ አስተዳደርና የኦባማ አስተዳደር የተለያዩ አቋሞች እንዳሉዋቸው ተንታኞች ይገልጻሉ።

ESAT

posted by Tseday Getachew

Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: