Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

ከእሁድ እስከ እሁድ /(የሳምንቱ አጫጭር ዜናዎች)

 

tplf

“ፀላእትና ክንከራታትሞም ኢና”
“ህወሓትን እናስቀድም … ‘ጠላቶቻችንን እናውድም’!”

ሦስት ቀናት የፈጀው የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ስብሰባ ትናንት ተጠናቋል። ለጉባኤው የሚሆን ኣጀንዳ ለመለየትና ልዩነታቸው ለማጥበብ ህወሓቶች ሲነታረኩ ቆይተው ቀጣዩ 11ኛ የህወሓት ድርጅታዊ ጉባኤ በሰላም ለማጠናቀቅ የተስማሙ ይመስላሉ ሲል ኢትዮ ሚዲያ መድረክ የመቀሌ ዘጋቢውን አብርሃም ደስታን ጠቅሶ ዘገበ።

የስብሰባው ተሳታፊዎች በሁለት ተከፍለው ዘለፋና የጠብ መንፈስ የተሞላበት ጭቅጭቅ ከተካሄደ በኋላ ሌላ ሦስተኛ ቡድን ተፈጥሮ “ህወሓትን እናስቀደም፣ ልዩነታችን ወደ ጎን ትተን የጋራ ጠላቶቻችንን እንታገል፣ ሁለታቹ (ቡድኖቹ) የህዝብ ድጋፍ የላችሁም፤ ስለዚህ በሁለት ከተከፈልን ህወሓት ህልውናው ያበቃል።” በሚል ተማጽኖ ማሰማታቸውን ድረገጹ አመልክቷል። በዶ/ር ቴድሮስ ኣድሓኖም የተመራ የሽምግልና ጥረት ታድያ ሁለቱም ቡድኖች ልዩነታቸው አጥብበው አብረው በጉባኤው እንዲሳተፉና በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩላቸው እንዲተባበሩ ስምምነት ላይ መደረሱንም አመልክቷል።

ልዩነታቸው የከረረ ጠብ እንደወለደና እስካሁን ‘የእግዚሄር ሰላምታ’ እንኳ እንደማይለዋወጡ የገለጸው ዘገባ ከልዩነታቸው መግዘፍ የተነሳ አንዳቸው ሌላኛው ቡድን ቢያሸንፍ እንኳ ለብቻው ህወሓትን ለማስቀጠል የሚያስችል የህዝብና ካድሬ ድጋፍ ሊኖራቸው እንደማይችል ገልጿል። የሚቀጥለው የህወሓት 11ኛ ድርጅታዊ (ዉድባዊ) ጉባኤ “ጉባኤ መለስ” (የመለስ ጉባኤ) ተብሎ ተሰይሟል። መለስ የሁለቱም (የሁሉም) ቡድኖች የጋራ ነጥብ መሆናቸውም ተጠቁሟል። ከጉባኤው በኋላ “ጠላቶች” ያሉዋቸውን አካላት እንደሚመቱ (እንደሚጨፈልቁ) ዝተዋል። ‘ፀላእትና ክንከራታትሞም ኢና!’ የሚል መግለጫ አውጥተዋል፡፡

ህጻናት በርሃብ ትምህርት መማር እየተሳናቸው ነው

ህጻናት እየራባቸው ትምህርት መማር እንዳቃታቸው ሸገር አዲስ ኤፍ ኤም ያነጋገራቸው መምህራንና ተማሪዎች ተናገሩ። ሸገር ያነጋገራቸው ተማሪዎች በየተራ እንደተናገሩት በምግብ ችግር ትምህርታቸውን መከታተልና ክፍል ውስጥ ትኩረት ማድረግ ተስኗቸዋል።

“ሌሎች ምሳ ያላቸው ምሳ ሲበሉ እኔ የቤት ስራ እሰራለሁ። ወይም ቤተክርስቲያን እሄዳለሁ” በማለት አንድ ተማሪ ሲናገር፣ ሌላኛው ምሳ የሚባል ነገር እንደማያውቅ ገልጿል። በርሃብ ምክንያት ትምህርታቸውን በወጉ መከታተል ያልቻሉ ተማሪዎች ጉዳይ እንዳሳሰባቸው መምህራኑ ሲናገሩ ሸገር አስደምጧል። በሰሙት ዜና ረፍት ያጡ በርካታ ወገኖች ስልክ በመደወል ተማሪዎቹ በትምህርት ቤታቸው ውስጥ የምሳ አገልግሎት እንዲያገኙ የበኩላቸውን ለማድረግ ሲነጋገሩና ቃል ሲገቡ ለመስማት ተችሏል።

አዲስ አበባ በኑሮ ውድነት ሳቢያ የሚበሉ ያጡ፣ በክፍል ውስጥ ረሃብ እያዞረ ክፍል ውስጥ የሚጥላቸው፣ በየጥጋ ጥጉ አጥርና ጥላ ስር ቀን የሚገፉ፣ የባሰባቸው ቤተሰቦቻቸውን ለማትረፍ ያለ እድሜያቸው ስጋቸውን ለመሸጥ እንደሚገደዱና ቤተሰብ፣ በተለይም እናቶች ልጆቻቸውን ለገበያ ወሲብ ማበረታታት እየተለመደ መምጣቱን የጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ አመልክቷል።

“ዋ” ብሎ

ሰው የሚማረው
አንድም በፊደል
አንድም በመከራ ነው፤
አንድ ቃል ከፊደል መዝገብ
አንድ ቃል ከመከራ መዝገብ
አንድም በሳር ‘ሀ’ ብሎ
አንድም በአሳር ‘ዋ’ ብሎ::
ጸጋዬ ገብረመድኅን

ከበአሉ ግርማ መድረክ ደንበኞች የተቀዳ

“ስለማጥመጃ ሶፍትዌሩ የምናውቀው ነገር የለም ብለዋል”

በኢንተርኔት አማካኝነት የተቃዋሚዎችን መረጃ ለመሰለልና እንቅስቃሴያቸውን ለመከታተል የሚያገለግል ማጥመጃ ሶፍትዌር (Trojan horse) የሚጠቀሙ 25 አገራት እንዳሉ የገለፀ አንድ የካናዳ የጥናት ተቋም፤ ኢትዮጵያን በማካተት የበርካታ አገራትን በስም ጠቅሷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ጉዳዩን አስተባብሏል፡፡ ማጥመጃው ሶፍትዌር በተለያዩ መንገዶች የቫይረስ መከላከያ ዘዴዎችን አልፎ እየሾለከ ወደ ኮምፒዩተር መግባት የሚችል ሲሆን፤ መረጃዎችን ለመምጠጥ፣ የማለፊያቃላትን (passwords) ለመስረቅ፣ የስልክና የስካይፕ ግንኙነቶችን ለመቅረጽ፣ በተለይም የኢሜይል መልእክቶችን ለመሰለል ያገለግላል ተብሏል፡፡

በቶሮንቶ ዩኒቨርስቲ ሥር “ሲቲዘን ላብ” የተሰኘው የጥናት ተቋም ረቡዕ እለት ይፋ ባደረገው ማስጠንቀቂያ፤ ሰዎች በኮምፒዩተርና በሞባይል ስልክ ውስጥ የሚያስቀምጡት መረጃ እንዲሁም የሚለዋወጡት መልእክት ለስለላ የተጋለጠ ነው ብሏል፡፡ እንዲያውም በኮምፒዩተራችሁ ላይ የተገጠሙ ማይክሮፎኖችና ካሜራዎችን በመጠቀም ቤት ውስጥ የምታደርጉት እንቅስቃሴና የምትናገሩት ነገር ሁሉ፣ የስለላ አይንና ጆሮ ውስጥ ሊገባ ይችላል ብሏል፡፡

ለስለላ ያገለግላል የተባለውና “ፊንፊሸር” የተሰኘው ማጥመጃ ሶፍትዌር በተገኘባቸው አገራት ሁሉ፣ መንግስታት በተቃዋሚዎችና በዜጐች ላይ ስለላ ያካሂዳሉ ማለት ባይቻልም፤ እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ አምባገነናዊ (authoritarian) መንግስታት እጅ ውስጥ መግባቱ ግን አሳሳቢ ነው ብሏል ተቋሙ፡፡ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በበኩላቸው፤ ስለማጥመጃ ሶፍትዌሩ የምናውቀው ነገር የለም ብለዋል፡፡

ምንጭ- ጥናቱን ጠቅሶ የዘገበው አዲስ አድማስ ነው

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ “አዲሱ ቴሌ እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ)፡ የህወሃት/ኢህአዴግ የስለላ መረብ” በሚል ከአንድ ዓመት በፊት ባቀረበው 47ገጽ ጥናታዊ ጽሁፍ ተመሳሳይ የዜጎችን መረጃ የመሰብሰብና የመሰለል ተግባራት እንደሚደረጉ ማስረጃዎችን ጠቅሶ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ ጥናታዊ ዘገባው የደረሳቸው ምዕራባዊ መንግሥታትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የህወሃት/ኢህአዴግን የስለላ መረብ በጥልቀት እየመረመሩት እንደሆነ “የህወሃት/ኢህአዴግ የስለላ መረብ እየተበረበረ ነው” በሚል ርዕስ ባወጣነው ዜና መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ኢህአዴግ በዘር ማጥፋት ወንጀል ተነክሯል

ኢህአዴግ በዘር ማጥፋት ወንጀል መነከሩ በተግባር በተደጋጋሚ እየታየ ነው። በተለይም አማርኛ በሚናገሩ ዜጎች ላይ የሚፈጸመው ወንጀልና ወንጀሉን የሚፈጽሙትን ክፍሎች የሚገስጽ መጥፋቱ ጉዳዩን እያወሳሰበው ነው። ኢሳት መኢአድ ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ እንደዘገበው “በቋንቋ ማንነት ህዝብን መግደል፣ ማፋናቀል እና ማሰር የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው” በሚል ርዕስ ሰሞኑን በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአማራ ተናገሪ ማህበረሰብ ላይ የተከፈተው ማፈናቀል፣ በጅጅጋ እና በአፋርም የቀጠለ ሲሆን በመላው አገሪቱ የአማርኛ ተናጋሪ ህዝብ ቤት እንዳይኖረው፣ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ እንዳይሳተፍ በተለያየ ስልት ድሃ ሆኖ በጎዳና እንዲበተን የህወሃት/ኢህአዴግ ካድሬዎች አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም ትእዛዝ የሰጡ ሲሆን በአዲስ አበባ ከፈረሱ እና እያፈረሱ ካሉ ቤቶች አብዛኞቹ የአማራ ተናጋሪዎች መኖሪያ መሆናቸውን መታዘቡን ገልጿል። የባንክ ብድርን መከልከልን ጨምሮ መሬት እንዳያገኙ ከመደረጉም በላይ ከፍተኛ ግብር እየተጫነባቸው ከንግድ ስርአቱ እንዲወጡ መደረጉን መኢአድ አመልክቷል። በአሁኑ ጊዜ ከ200 በላይ ከቤንሻንጉል ጉምዝ የተፈናቀሉ የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች በባህርዳር ያለመጠለያ በጎዳና እየኖሩ መሆኑን መኢአድ በመግለጫው አመልክቷል። በባህርዳር ለጎዳናና ተዳዳሪነት ከተዳረጉት መካከል ብዙ ነፍሰጡሮችና ህጻናት እንደሚገኙበትም ገልጿል።

አማርኛ ተናጋሪውን ህዝብ በብሄራዊ ጨቋኝነት በመፈረጁ በአርባ ጉጉ ፣ በበበደኖ፣ በአርሲ፣ በባሌ፣ በጋምቤላ እንዲጨፈጨፍ ሲያደርጉ አገዛዙ ምን ያክል የአማርኛ ተናጋሪውን ህዝብ ለማጥፋት እንደተፈለገ አመላካች መሆኑን የጠቀሰው መኢአድ፣ ከአንድ አመት በፊት በቤንች ማጂ ዞን በጉራፈርዳ ወረዳ በከፍተኛ ጭካኔ በአማርኛ ተናጋሪ አርሶአደር ፣ ሴቶች፣ ነፍሰ ጡር፣ ህጻናት እና ሽማግሌዎች ላይ የተጀመረው ጭካኔ የተሞላበት ስደት ተባብሶ ቀጥሎ በየጎዳናው የሚጣለው የኔቢጤ ከመሆን አልፎ ለአውሬና ለአሰቃቂ ኑሮ የተጋለጠው የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ህብረተሰብ ቁጥር እየጨመረ በቤንሻንጉል ፣ በጅጅጋ፣ በአፋር እና በአንዳንድ የአሮሚያ ክልል እየቀጠለ ነው ብሏል፡፡

መኢአድ “ማንኛውም ሰው በቋንቋው ፣ በጎሳው፣ በእምነቱ፣ በቀለሙ እና በማንኛውም ልዩነት ምግብ ሲያጣ ፣መጠለያ ሲነፈገው ፣ጨቅላ ህጻናት በየጎዳናው ሲሞቱ፣ ነፍሰጡሮች በየበረንዳው ሲወድቁ፣ ህሊናን የሚያደማ መሆኑን ገልጾ” ይህንን ጨቋኝ ስርአት በአለም ህዝብ ፊት በዘር ማጥፋት ወንጀል ልንከሰው ይገባል” ማለቱን የኢሳት ዜና ያስረዳል።

ግራዚያኒ ቢወገዝ ኢህአዴግን ምነው ከፋው?

ለፋሽስቱ ግራዚያኒ መታሰቢያ ሃውልት እንዲቆም የሚደረገውን እንቅስቃሴ በይፋ ለመቃወም አደባባይ የወጡ ወገኖች ታስረዋል። ታዋቂ ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ በርካቶች ወህኒ መግባታቸውን ተከትሎ ለዝግጅት ክፍላችን አስተያየቶች ተልከዋል። ከአስተያየቶቹ መካከል “ግራዚያኒ ቢወገዝ ኢህአዴግን ምነው ከፋው?” በሚል የደረሰን ይገኝበታል።

“ከደምና ከጅምላ ጭፍጨፋ ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያለው ህወሃት የሚመራው ኢህአዴግ ፋሽስት በባንዳና በባንዳ ጌቶች ከተጨፈጨፉት ወገኖች ይልቅ ፋሽስትና የፋሽስት አለቆች በልጠውበት አትቃወሙ ማለቱ ከህዝብ ጋር የመለያየቱ መገለጫ ነው” የሚል ሃረግ አለበት። በሌላም በኩል ለአቶ መለስ ሃውልትና የጥናት ማዕከል የሚገነባው ህወሃት ህዝብ ግራዚያኒን ሲቃወም ዝም ካለ ነገ መለስንም ባደባባይ ፋሽስት ነው በሚል ለሚቃወሙ በር ላለመክፈት የሚደረግ ቅድመ ዝግጅት እንደሆነ የሚገልጽ ሃተታም አለበት።

ማጅራት ገትር “ወረርሺኝ ደረጃ አልደረሰም”

በኦሮሚያና በደቡብ ክልል በወረርሺኝ ደረጃ ጉዳት እያደረሰ ያለው የማጅራት ገትር በሽታ አዲስ አበባ በወረርሽኝ ደረጃ አልተከሰተም ሲል የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ማስታወቁን አዲስ ዘመን ዘግቧል። አዲስ ዘመን በቢሮው የተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ቅኝትና አሰሳ ኦፊሰር አቶ መሳፍንት አለባቸውን ጠቅሶ እንደዘገበው ከተለያዩ ክልሎች ወደ አዲስ አበባ ከሚመጡ ተጠርጣሪዎች በስተቀር አዲስ አበባ በወረርሺኝ ደረጃ የተመዘገበ ሪፖርት የለም ብለዋል።

አቶ መሳፍንት አለባቸው (ፎቶ: አዲስ ዘመን)

“ማጅራት ገትር ተላላፊና በወቅቱ ካልታከመ ደግሞ ገዳይ በሽታ ነው” ያሉት ባለሙያው፤ ከታካሚ ጋር ግንኙነት ያላቸው የህክምና ባለሙያዎች ሁሉ ሥልጠና እንዲያገኙ እና የበሽታውን መከሰት ነቅተው እንዲጠብቁ ዝግጅት መደረጉን አስረድተዋል።

ማንኛውም ሰው ከፍተኛ የራስ ምታትና ትኩሳት ካለውና ማጅራትን የመገተር ስሜት ከተሰማው ፈጥኖ ወደ ጤና ተቋማት መሄድ እንዳለበት አስገንዘብው፤ በየደረጃው በሚገኙት የጤና ተቋማትም የሪፈራል የቅብብሎሽ ስርዓት በተጠናከረ መልኩ የተዘረጋ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ አቶ መሳፍንት ገለፃ፤ የማጅራት ገትር በሽታ በባክቴሪያ የሚተላለፍ እና የተለየ የዓይነት ሲሆን፤ በሽታውን አስቀድሞ ለመከላከል ኀብረተሰቡ እጁን በሳሙናና ውሃ መታጠብ በማሳልና በማስነጠስ ወቅት አፍና አፍንጫውን መሸፈን ይኖርበታል። በባክቴሪያው ቀድሞ የሚጠቃው አፍና አፍንጫ አካባቢ ሲሆን፤ በአፍ አካባቢ የመድረቅ ስሜት እንዳይኖር ማድረግ ይገባል። ህዝቡ ተጠጋግቶ በሚኖርበት አካባቢ፣ ትምህርት ቤት በትራንስፖርት እና በሌሎችም ቦታዎች በቂ አየር እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል።

http://www.goolgule.com/briefs-21/

posted by Tseday Getachew

Advertisements

Single Post Navigation

Comments are closed.

%d bloggers like this: