Fitih le Ethiopia

I wish democracy and unity for Ethiopia

Archive for the month “November, 2012”

የአቡነ ጴጥሮስ ሃውልትን አንስቶ በሙዚየም ለማቆየት ኮሚቴ መቋቋሙ ተነገረ

ህዳር ፳፩ (ሃያ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የህወሀት ኢህአዴግ ልሳን የሆነው ሬዲዮ ፋና እንደዘገበው የአቡነ ጴጥሮስ ሃውልት በግንባታው ስለሚነካ በጊዜያዊነት ይነሳና በጥንቃቄ በሙዚየም ይቀመጣል፣ ግንባታው ሲጠናቀቅም ወደ ስፍራው ይመለሳል።

የዳግማዊ ምኒልክ ሃውልት ግን ከፕሮጀክቱ ጉድጓድ 15 ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ በመሆኑ አይነሳም ብሎአል።

ይፈርሳል በሚል የሚናፈሰው ወሬም ከእውነት የራቀ ነው በማለት የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ፣ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን፣ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣንና ሌሎችም ባለድርሻ አካላትን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

ሀውልቱ ሲነሳም ሆነ መልሶ በሚተከልበት ወቅት ምንም አይነት ጉዳይ እንዳይደርስበትም ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚደረግና ምንም አይነት የቦታ ለውጥ እንደማይደረግበትም ራዲዮው ዘግቧል።

ራዲዮው ይህን መግለጫ የሰጡትን ሰዎች ማንነት ይፋ አላደረገም። ሀውልቱን የሚያነሳውና መልሶ የሚተክለው ድርጅት ማን እንደሆነም አልተጠቀሰም። በየትኛው ሙዚየም ለምን ያክል ጊዜ እንደሚቆይ፣ ሀውልቱ ቢፈርስ ወይም ጉዳት ቢደርስበት አፍራሽ ግብረሀይሉ የመልሶ ማሰሪያ ገንዘብ ማስያዝ እና አለማስያዙ ወይም ኢንሹራንስ መግባቱና አለመግባቱ በዜናው ላይ አልተገለጸም። ሀውልቱ ተመልሶ እንደሚተከል ምን አይነት ዋስትና እንደተሰጠም አልታወቀም።

የአቡነ ጴጥሮስ ሀውልት መነሳት ጉዳይ ከፍተኛ የህዝብ መነጋገሪያ መሆኑ ይታወቃል። እስካሁን ድረስ በአገር ውስጥ የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ምሁራን ወይም ባለሙያዎች አስተያየቶቻቸውን በመግለጫ መልክ ወይም በማንኛውም መንገድ አልሰጡም በማለት የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ዘገባውን አጠቃሎአል።

posted by Tseday Getachew

Advertisements

ብአዴን ሕወሓትን በባርነት እያገለገለ ያለበትን 32 ዓመት በዓሉን እያከበረ ነው

(ዘ-ሐበሻ) በአማራ ሕዝብ ስም እየነገደ ነው በሚል እየተተቸ የኖረው የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓትን) በታማኝ ባርነት እያገለገለ ያለበትን 32ኛ ዓመት በዓሉን እያከበረ ነው።
“የመለስ ራዕይን አስፈጽማለሁ” የሚለው አነጋገር በኢትዮጵያ ፋሽን በሆነበት በዚህ ወቅት በሕወሓት ባርነት ውስጥ ያለው ብአዴን “የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ያወጧቸውንና ኢህአዴግም ያፀደቃቸውን የልማትና የዕድገት ንድፎች በመተግበር ዓላማቸውን ከግብ በማድረስ ራዕያቸውን ማሳካት እንደሚያስፈልግ” ለአባላቶቹ በመስበክ ላይ ይገኛል።
በተለይም አቶ መለስ ዜናዊ በሕይወት በነበሩበት ወቅት የተቃጣባቸውን የመፈንቅለ መንግስት በማክሸፍ ታማኝ ባርነታቸውን ያሳዩት የብአዴን ሥራ አስፈፃሚ አባልና ኢህአዴግ የሥልጠና ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ አዲሱ ለገሰ በሥልጠና ላይ የሚገኙት የብአዴን ኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር አባላትን በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ሰብስበው “የሰማዕቱን መለስ ዓላማ ለማሳካትና የአገሪቱን ብልፅግና ለማረጋገጥ ጠንክሮ መታገል ያስፈልጋል” በማለት ተናግረዋል። በኢሕአዴግ ውስጥ አቶ መለስን ከዕምነት ሰማ ዕታት እኩል ማየት አዲስ ነገር ባይሆንም ብአዴን ከ32 ዓመታት በኋላም በሕወሓት ባርነት ቀንበር ውስጥ ላለመቆየት አንዳችም ለውጥ አለማሳየቱ የፖለቲካ ታዛቢዎችን እያስተዛዘበ ነው።
አቶ አዲሱ ለገሰ የብአዴን ኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር አባላንት በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በማሰልጠን ላይ መሆናቸውን የጠቁሙት የዘ-ሐበሻ የአዲስ አበባ ዘጋቢዎች ሥልጠናው ከተጀመረ 10 ቀናት ቢያልፉትም እስከ 50 ቀናት ድረስ እንደሚቆይ አስታውቀዋል። የአዲሱ ለገሰ ስልጠና ብአዴንን በሕወሃት ሳንባ እንደተነፈሰ ለቀጣዩ 30 ዓመታት እንዲቆይ የሚያደርግ እንጂ ከባርነት የሚወጣ ድርጅት እንደማያደርገው ታዛቢዎች ይናገራሉ።
ብአዴን በትግሉ ውስጥ የሕወሓት አሽከር ከመሆን ባለፈ በስሙ ለሚነግድለት የአማራ ሕዝብ ያደረገው ነገር እንደሌለ ሲተች ቆይቷል።

Short URL: http://www.zehabesha.com/?p=13280

posted by Tseday Getachew

ወያኔዎች የደበቁት የፕሮቴስታንት ታሪክ በትግራይ

ይህ ታሪክ በአገር ውስጥ ደራሲ ሲታተም የመጀመሪያ መጽሐፍ ነው። ያልተጻፉ ብዙዎቹ ታሪኮቻችንን አፈላልገን አሁን ላለው ሕዝብ እና ለተተኪው ትውልድ በሃሰት ሳይሆን ታሪኩን በእውነት ዘግቦ ታሪኩን እንዲገነዘብ ማድረግ አገራቸውን በሚያፈቅሩ ዜጎች መከናወን ያለበት ከባድ የሕሊና ግዴታ እና ሸክም ነው።
ታሪክ ማለት በአመዛኝ መልኩ በሁለት ጎራዎች በተከፈሉ ተቃራኒ እይታዎች የተከናወኑ የማሕበረሰቡ ህይወት የሚያትት ዘገባ ነው።ደቂቀ ተወልደመድኅን ብየ የሰየምኩት ይህ መጽሐፍ የሚያትተው፤በጥንቱ ዘመን ትግራይ ውስጥ በዓድዋው ተወላጅ በአለቃ ተወልደመድኅን ገብሩ እና በአክሱም ተወላጅ በአለቃ ጐበዜ ጐሹ የተመራው የኢቫንጀሊካል(ፕሮተስታንት/ከኒሻ)ሃይማኖት እንቅስቃሴ ከአካባቢው የኦርቶዶክስ ሃይማኖት መሪዎች፤ አማኞችና የአካባቢው ተወላጅ በነበሩት አስተዳዳሪዎች መሃል የታየው የእምነት “ፍጭት” በጥልቅ የሚያትት ነው። በፍጭቱ ሂደት የተወሰዱ
የጭካኔ እርምጃዎች ዘግናኝ የሆኑ የከፉ እርምጃዎች (ኤክስትሪም ሜዠር) ተወስደዋል።
የተጠቀሱት ሁለቱ መሪዎች ወደ ፕሮተስታንት እምነት ከመከነሻቸው በፊት ወላጆቻችውም ሆኑ እራሳቸው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት አማኞች እና በተዋህዶ ትምህርት የመጠቁ የተከበሩ ሊቃውንት ነበሩ። በአዲሱ እምነታቸው ምክንያት የገጠማቸው ተቃውሞ ላለመሸነፍ እስከመጨረሻ ተጋትረው በጽናት በመቆም በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ እየተከራከሩ በርካታ ተከታዮች በማፍራታቸው አስተዳዳሪዎች፤ የሃይማኖት መሪዎችና መነኰሳት ከየገዳማቱ የተሰባሰበ ብርቱ ተቃውሞ ደርሶባቸው ለእስራት፤ለእርዛት፤ ለግርፋት፤ ለቤት እጦት፤ከማሕበረሰብ መገለል እና በመጨረሻም ለስደት ተዳርገዋል።
ይህ መጽሐፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ ምክንያት ህወሓት/ወያኔዎች ለአማራ እና ለአማርኛ ቋንቋ መረን የለቀቀ የጎሳ ጥላቻቸው በጐሰኝነት ጥማት የታመመው ልቦናቸውን ለማርካት ሲሉ፤በ14ኛው ክፍለዘመን የነገሠው የቤተክህነት ሊቅ በነበረው በገናናው ንጉሥ ዘርአ ያዕቆብ ላይ የጥላቻ መርዛቸውን በንጉሡ ታሪክ ላይ በመርጨት፤ የውሸት መጽሐፍ በመጻፍ፤ በእዛው ዘመን በነበሩት በታወቁት የትግራይ መነኩሴው በአባ እስጢፋኖስ እና ተከታዮቻቸው (ደቂቀ እስቲፋኖስ በመባል ይታወቃሉ)የተመራው ለየት ባለ ባልተለመደ መልኩ የተከሰተው የሃይማኖት ክርክር (እንቅስቃሴ) ምክንያት፤የትግራይ አበምኔቶች ተቃውሞአቸውን በጋለ ቁጣ በማሳየት ክርክሩ እየጦፈ ከቁጥጥር በላይ እየሆነ በመሄዱ በደቂቀ እስጢፋኖስ ላይ ሕግን ያልተከተለ የሃይል እርምጃ መውሰድ እንደጀመሩ ታሪኩን ከክቡር ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ የተጻፈውን “ደቂቀ እስጢፋኖስ” መጽሐፍ ያነበባችሁ ዜጎች የምታስታውሱት ታሪክ ነው። በዚህ መልኩ ነገሩ እየጋለ ሲሄድ የትግራይ አበምኔቶቹ ለክርክሩ እልባት ለማስገኘት ይመቻቸው ዘንድ ጉዳዩን ወደ ቤተክህነቱ ሊቅ ወደ ንጉሥ ዘርአ ያዕቆብ ሥልጣን በላይ ንጉሡ ወደሚኖርበት ወደ ድብረብርሃን (ሸዋ) ድረስ በመውሰድ ክርከሩን አስቀጠሉት።
በክርክሩ ወቅት በንጉሡ እና በአባ እስጢፋኖስ መሃል መግባባት የነበረ ቢሆንም፤ ተቃዋሚዎቻቸው ንጉሡን ለማሳመን ብዙ ክሶች ደርድረው ለማሳበቅ በመጣር ባንዳንድ ጎዳዮች ላይ ያለመግባባት ተከስቶ፤ንጉሡ ከረር ያለ ቅጣት በመኖኩሴው በአባ እስጢፋኖስ ላይ በይኖ ቅጣቱ ተግባራዊ እንደሆነም የሚታወስ ነው። ያ ብይን በማስታወስ ነው ዛሬ ወያኔዎች በ14ኛው ክፍለዘመን የተፈጸመው ሃይማኖታዊ የአስተዳዳር ውሳኔ በጎሳ ፖለቲካ ተርጉሞው “አማራ” እያሉ የሚጠሩት ንጉሥ ዘርአ ያዕቆብ የትግሬ ጥላቻ ስለነበረው እንደ እነ አባ እስጢፋኖስ እና ተከታዮቻቸው የመሳሰሉ የትግራይ የሃይማኖት ፈላስፎች አብበው እንዳይወጡ በማሰብ በእንጭጩ እንዲቀጩ አድርጓል፡ በማለት ንጉሥ ዘርዓ ያዕቆብን በጸረ ትግሬነት ከስሰውታል።
በጣም የሚገርመው “የሸዋ አማራዎች” የትግሬ ጥላቻቸውን የጀመሩት በዛው በ14ኘው ክ/ዘመን ጀምሮ ነው በማለት አማራው እና ትግሬው በጠላትነት እንዲተያይ መርዛቸውን በመርጨት የጻፉትን የሃሰት መጽሐፋቸውን ከሸፈቱበት “ከደደቢት” ያመነጩት የፈጠራ “አተላ ታሪክ” መሆኑን የማሳይበት በመረጃ የምከራከርበት ሌላው መጽሐፌ ነው። እኔ በዚህ መጽሀፍ ያቀረብኩት የታሪክ ሰነድ ”ትግራይ ውስጥ” በ19ኛው ክ/ዘ መግቢያ ከላይ በተጠቀሱት ሁለት ሰዎች የተመራው ተመሳሳይ የሃይማኖት እንቅስቃሴ ተነስቶ በነበረበት ወቅት በወቅቱ የነበሩ የአካባቢው ተወላጅ የመንግሥት ባለሥልጣኖች አዲሱን የሃይማኖት ክርክር ባስነሱትና በመሩት በዓድዋው ተወላጅ በአለቃ ተወልደመድኅን ገብሩ፤በአክሱማዊው በአለቃ ጐበዜ ጐሹ እና ተከታዮቻቸው ላይ የተፈጸመው የ19 ክ/ዘመን ኢፍትሃዊ እና የግፍ ድርጊት በትግሬ ተወላጆች አስተዳዳሪዎችና ውሳኔ አስፈጻሚዎች የተከናወነ የእርስ በርስ ድርጊት ስለነበር፤“የትግሬዎች የውስጥ ገመና” ላለማጋለጠጥ
ሲሉ፤ወያኔዎች ይህንን ታሪክ አውቀው በመደበቅ ‘እንደ ጥዋት ውሃ የነጡ ወርቆቹ የትግሬ ነገሥታት እና አስተዳዳሪዎች በሙሉ’ “የፍትሕ ሰዎች፤መብት አስከባሪዎች፤አገር ወዳዶች” የደቂቀ ምኒሊክ እና ደቂቀ ዛርአ ያዕቆብ አማራዎች ግን“አገር ሻጮች፤ከዳተኞች፤የዜጎች መብት ተጋፊዎች፤ ፍትሕ አልባዎች፤የትግራይ የጀግንነት እና ፍትሕ ታሪክ ዘራፊዎች…” እያሉ አጉል ስለሚመጻደቁ ያንን ውስጥ ገበናቸውን ላለማስወጣት ሲሉ እፊታቸው ላይ ተገትሮ እያዩት ያለውን በየቤታቸው የተደበቀው የቅርብ ጓዳቸውን ትተው በ14ኛው ክ/ዘመን ተፈጸመው በሺሕ ኪሎሜትር ርቀት ወደ እሚገኘው ደብረብርሃን / ወደ ሸዋ ክ/ሃገር/ አሻግረው በመመልከት የራሳቸውን የቅርብ ዘመን ጉድፍ እንዳላዩት ሆነው ሆን ብለው “ዓይናቸወን በጥቁር ጨርቅ ሸፍነው” የ19ኘውን ክ/ዘ ትልቁን የትግራይ የግፍ ተራራ አይተውት እንዳላዩት አጎንብሰው በጐሰኝነት ስሜት፤ዘልለውት በማለፍ ወደ 14ኛው ክፍለዘመን ጉብ ብለው በወቅቱ የተፈጸመው ሃይማኖታዊ እና አስተዳዳራዊ ብይን ወደ ጐሳ ፖለቲካ የተረጐሙትን የወያኔዎችን ማለቂያ የሌለው የታሪክ ብረዛ እውነቱን ለሕሊና ፍርድ እንዲቀርብና የገዛ መልካቸውን በዚህ መጽሐፍ እንዲያዩበት ይረዳቸው ዘንድ የጻፍኩት የመጽሐፍ መስተዋታቸው ነው።
ለእናንተ የኢትዮጵያ እውነተኛ አገር ወዳዶች የሆናችሁ ሁሉ የማስተላልፈው መልእክት ቢኖር ‘መጽሐፉን በመግዛት’ ወያኔዎች የትግራይን አዲስ ትውልድ ለመመረዝ በብዛት እያሳታሙ የሚያሰራጯቸው በውሸት የታጀቡ ጎሰኛ መጽሕቶቻቸውን መቋቋም የሚቻለው ከወገንተኛነት የጸዱ ሚዛናዊ መጽሐፍቶችን እየገዛችሁ መጪው ትውልድ እንዳይሞኝ መከላከያ ሰነዶች እንዲኖረው ማድረግ ነው። ይህ ጐጠኛ ባሕሪያቸው ለመመርምር ይህ መጽሐፍ ስጽፍ የታዘብኩት ነገር ካለ፤ “በ 14ኛው ክ/ዘመን የተፈጸመውን ግፍ፤ በ19ኛው ክ/ዘመን የኖሩ አስተዳዳሪዎች እና ማሕበረሰቦች ሲደግሙት፤በ20ኛው ክ/ዘመን እየኖሩ ያሉት ወያኔዎች በ14ኛው እና በ19ኛው ክ/ዘመን የተፈጸመውን ግፍ ሳይማሩበት ያንኑን ድርጊት እነሱም እንደገና ሲደግሙት ስመለከት፤ ከ14ኛው ክ/ዘመን ሕሊና መውጣት ያቃታቸው እነዚህ ትውልዶች በ14ኛው ክ/ዘመን የተፈጸመው ግፍና ስሕተት አንስተው የ14ኛው እና የ19ኛው ክ/ዘመን የነበሩትን መሪዎች ሊከስሱ እና ሊወቅሱ የሚችሉበት ሞራል ከየት እንዳገኙት ሳስበው“ድፍረታቸው” በጣም ይገርመኛል።”
ስለ መጽሐፍ ማንሳት ላልቀረ አንድ ነገር ልበል። ካሁን በፊት ያሳተምኳቸው መጽሐፍቶች ከወያኔ በላይ መጽሓፍቶቼ እንዳይሰራጩና ለሕዝብ እንዳይዳረሱ ብዙ ሴራዎች የጐነጐኑ ቀናተኛ ግለሰቦች እና በተቃዋሚነት የቆሙ የፖለቲካ መጻጉእ የድርጅት አባሎችና ድረገጾቻቸው እንደነበሩ ካሁን በፊት አስታውሼአችሁ እንደነበር የሚታወስ ነው። ሆኖም በጠንካራ አርቆ አሳቢ አገር ወዳድ ግለሰቦች ብርታት እና ትብብር መጽሐፍቶቼ ከሞላ ጎደል ተሰራጭተው ለትውልድ እንዲተላለፉ ያደረጉ ወጣቶች፤ ግለሰቦች እና ደምበኞች እጅግ የከበረ ኢትዮጵያዊ አክብሮት እና ምሳጋናዬን ለማስተላለፍ እወዳለሁ። ዛሬም በቁጥር እጅግ በጣም ጥቂት የሆኑ ቅጆች ያሰተምኩት ይህ መጽሐፍ ለትውልድ እንድታስተላልፉለት እንደገና በድጋሜ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
“አንዲት ኢትዮጵያ” እንደቀድሞዋ ህያው ሆና የተነጠቁባትን ዳር ድንበሯን፤ሰንደቃላማዋን እና ክብሯን ከዋየኔ በፊት ለዘመናት ታፍራ እንደነበረቺው ለማስመለስ የወያኔ የውሸት ሰነዶች ከታሪክ መድረክ አሳፍረን የምናስወግደው በእውነት የተመረኰዘ ሰነድን በማቅረብ ትውልድን ማስተማር ስንችል ብቻ ነው። ከዚህ ወዲያ ለትውልድ የምናወርሰው የተከበረ ገድል ሊኖር አይችልም።
እኔ ጐሳዬ ትግሬ ነኝ። ለብዙ ጊዜ የነሱን ውሸት ለመጋራት ብዙ የማታለያ የምቾት መማለጃ ምልጃዎች አቅርበውልኛል።ጠንካራ ኢትዮጵያዊነቴ መበገር ስላልቻሉ፤ ተስፋ ብቆርጥ ብለው በዚህ ይደናገጥና ይተወን ይሆናል በማለት ትግሬነቴን ለመንጠቅ አጉል የሆኑ ብዙ የውሸትና ጐሰኛ ሙከራዎች እና ስድቦች ለብዙ አመታት በወያኔ ጀሌዎች ተሰንዝረውብኛል።የግብዝነታቸው ክምር መጠኑ ሲበዛ አንዳንዴ በጣም እያሳቀኝ መዝናኛ አደርጋቸዋለሁ።ውሸት እና የዘረኛ ዓላመውን ስላልተከተልክ ማንነትክን ለመንጠቅ ከሚሞክር ግለሰብ ወይንም ድርጅት የከፋ አራዊት በምድር ውስጥ ሊኖር አይችልም።በአራዊት ባሕሪያቸው ማንነቴን ለመጋፋት በተጋፉኝ ቁጥር እየቀያየሩ የሚለብሷቸው የናዚዎችና የፋሺስት ካባቸው እራሳቸው በጫሩት እሳት ሳቃጥልላቸው እጅግ እረካለሁ።መዝናኛም አደርጋቸዋለሁ።ደስታየ ግላዊ ሳይሆን ሕዝባዊ ደስታ ነው። በነዚህ የታሪክ አተላዎች ምክንያት፤ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ቆሽቱ ያረረውን ያሀል አዲስ መጽሐፍ አሳትሜ ፋሺስታዊ ካባቸው ባቃጠልኩላቸው ቁጥር ዜጎች በጣም ሲደሰቱ ስመለከታቸው “ድካሜ እንደ ጉም ይበንናል”ደስታየ ወሰን የለውም። ወያኔን በታሪክ መድረክ መጋፈጥ ጠንካራ መንፈስ እና ቆራጥነት የሚጠይቅ ቢሆንም ‘የሕሊና እርካታ እና እፎይታ/ፕለዠር/ነው’ የምለውም ለዚህ ነው።
እነኚህ አውሬዎች የሰው ሥጋ የለበሱ የአዳም እና የሄዋን ቋንቋ የሚናገሩ “ያልተገሩ አራዊቶች” ትግሬነቴን ለመንጠቅ በሚያደርጉት የአራዊት ባሕሪያቸው ምክንያት ጓዳቸው እያስፈተሹ መሆናቸውን መገንዘብ አቅቷቸዋል። ዛሬ ወያኔም ሆነ ማንኛውንም ጎሰኛ በፈጣሪ ሥልጣን ውስጥ ገብቶ የዘር የደምና የአጥንት ጥራትና ቆጠራ ውስጥ የሚፈተፍት መስፍናዊ አውሬ ካለ የትግሬን ጎሳ አመሰራረት ታሪክ ወይንም የኢትዮጵያን ህብረተሰብ የደም ትስስር አያውቅም ማለት ነው።ሌላ ቀርቶ ከአውሬነት ሕሊና መውጣት አቅቶት አገርን ያክል ለባዕዳኖች ሲያስረክብ ከነበረው ‘ከመለስ ዜናዊ’ አስገራሚ የህይወት ቅስፈትና የፈጣሪ ቁጣ እንኳ ማመር አቅቷቸው የባንዳ እና የፋሺስት ታሪክ ትቶላቸው የሄደውን መመሪያውን እንቀጥልበታለን ብለው ሲግማሙ ሳስተውላቸው “አራዊቶቹ” ዛሬም ከዛው ተብትቦ አስሮ ከወጠራቸው አራዊት ሕሊናቸው ሰብረው መቸ መውጣት እንደሚችሉ ሳስበው ለነሱ እሳቀቃለሁ። እራሳቸውን ነፃ ማውጥ ካልቻሉ ከአውሬ ሕሊና መውጣት ያቃታቸው እነኚህ የሰው አውሬዎች የሚያሰራጯቸውን የውሸት መጽሐፍቶቻቸው መጪው ትውልድ እንዲታገላቸው ያመቸው ዘንድ የበኩሌን ድርሻ ለመወጣት መጽሕፈቶች ጽፌአለሁ። ከናንተ የሚጠበቀው ግዴታ ደግሞ ይህ ታሪካዊ አዲስ መጽሐፍ በማሰራጨትና “የእውነት ብርሃን” ላለማየት ዓይናቸው ጨፍነው፤ የውሸት እንቅልፍ ተኝተው፤ እያንኰራፉ ያሉትን አብዛኛዎቹ የትግሬ ምሁራን ከተኙበት ቀስቅሳችሁ እንዲያነቡት ይህ የብርሃን መጽሐፍ ዓይናቸው ላይ እንዲበራ ማድረግ ይጠበቅባችሗል።
በጣም አመሰግናለሁ
ጌታቸው ረዳ
P.O.Box 2219

posted by Tseday Getachew

የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጣ ከተናጥል ወደ ማህበረሰባዊ ሊቀየር ይገባል ተባለ

ህዳር ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ ህዝብ በሚደርስበት የኢኮኖሚና የፖለቲካ በደል የሚያሰማውን የተናጥል ቁጣ በጋራ ማሳየት ይገባዋል ሲሉ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ገልጡ።

የኢሀዲግ መንግስት ለፓርቲው እንጂ ለህዝብ ደንታ የለውምም ብለዋል።

የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ባደረጉት ውይይት እንደገለጹት የኢትዮጵያ ህዝብ ብሶቱን ቋጥሮ በማጉረምረም ላይ የሚገኝ ነው ፤ ቁጣውም ቢኋን በተናጠል የሚገለጽ ነው፤ ይህ የተናጥል ቁጣና ማጉረምረም ግን እንደሌሎች ሀገሮች በጋራና በአንድነት ሊገለጽ ይችላል ብለዋል።

እስከ አሁን እንደታየው ማህበራዊ፣ ኢኮኖምሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮቹን ይዞ ሰቆቃና ብሶቱን በተናጥል ወይም በጥቂት ቡድን ደረጃ የማርራል እንጂ በጋራ ሆኖ ድምጹን አላሰማም ያሉት ዶ/ር ነጋሶ ይህ ንዴቱና ብሶቱ ወደ ህብረተሰባዊ ንዴትና ቁጣ አልተለወጠም ብለዋል።

በሌሎች ሀገሮች የዳቦና የነዳጅ ዋጋ ላይ ትንሽ ጭማሪ ከታየ የህብረተሰብ ንዴቶች ይገነፍላሉ በኛ ሀገር ግን ከተናጥል ቁጣና ንዴት አልፎ ወደተደራጀና ህዝባዊ የእንቢተኝነት እንቅስቃሴ አልተለወጠም ያሉት የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ አንባገነንነትና ለህዝብ ብሶት ግድ የሌለውን መንግስት ለመፈተን የተደራጀና ህብረተሰባዊ ቁጣ ያስፈልጋል ብለዋል።

ህዝባዊ ጥያቄንና ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ለማፈን ሲል ገዥው ፓርቲ ህገመንግስት ይጥሳል ፤ ህግ በማውጣት ህግ አስከብራለሁ ብሎ ሰባዊ መብቶችን ይጥሳል ብለዋል።

posted by Tseday Getachew

ህወሃት አረጋግቶ አገገመ

ብቸኛው ተቃዋሚ የንግድ ሚኒስትሩን ሹመት ኮነኑ

ኢህአዴግ “አረጋግቶ አገገመ” ከተባለው አዲሱ “ምደባ” መካከል የንግድ ሚኒስትር ተብለው በተሰየሙት ላይ ብቸኛው የፓርላማ ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ ጠንካራ መከራከሪያ በማቅረብ ተቃወሙ። አቶ ግርማ የሚሾሙ ብቻ ሳይሆን የሚነሱ ባለስልጣናት ከሃላፊነታቸው የተነሱበት ምክንያትም ለህዝብ መቅረብ እንዳለበት አሳሰቡ። አቶ ሃይለማርያም ተቃውሞውን “መክረንና ገምግመን ያደረግነው ነው” ሲሉ ተከላከሉ። አቶ ግርማ ብሩ (አሁን አምባሳደር) ሲመሩት የነበረውን ሚኒስቴር መ/ቤት “ስያሜና ምልክት መለየት የማይችል” በማለት አንቋሸሹት።

ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ አገሪቱን በመሩበት ሶስት ወራት ካቢኒያቸውን በደንብ መገምገማቸውን በግምት በመግለጽ ተቃውሞ ያቀረቡት አቶ ግርማ ሰይፉ በምደባው በተወሰነ ደረጃ እንደሚስማሙ ተናግረዋል። የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔን ምደባ የተቃወሙት በማስረጃ ነው። የዓለም ባንክ ለንግድ ምዝገባ የማያመቹ አገሮችን ዝርዝር ጥናት ይፋ ሲያደርግ ኢትዮጵያ ከ185 አገሮች የ165ኛ ደረጃ ማግኘቷን፣ ለዚህም የዳረጉት ቀደም ሲል በተጠባባቂ ሚኒስትርነት ለረዥም ጊዜ ያገለገሉት አቶ ከበደ ጫኔ በመሆናቸው አዲሱ ሹመት እንደማይገባቸው አቶ ግርማ በተቃውሞ ተናግረዋል። በተጨማሪም ህዝብ የማወቅ መብት ስላለው ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከሃላፊነታቸው ሲነሱ ምክንያቱ ይፋ ሊሆን እንደሚገባው ማሳሰቢያ አቅርበዋል።

አቶ ግርማ ብቻ የተቃውሞ አስተያየት ያቀረቡበት ምደባ በስፋት ሃሳብ ሲሰጥበት ለነበረው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ወንበር መልስ በመስጠት ተጠናቋል። ምደባውን ህወሃት ሲያሸንፍ የተመደቡት ሚኒስትር አቶ መለስ በህይወት እያሉ ይተኳቸዋል የተባሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ናቸው። የግራ ዘመሙን የፖለቲካ ጎዳና እምብዛም የማያውቁት ዶ/ር ቴዎድሮስ “ልምድ ያላቸው ታጋይ አይደሉም” በሚል ህወሃትን በከፍተኛ አመራርነት ስለመወከላቸው ጥያቄ የሚያቀርቡባቸው ነበሩ።

ለሼኽ መሐመድ ሁሴን አላሙዲን እጅግ ቅርብ የሆኑት አዲሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ድር /ኔትዎርክ/ አካል ናቸው። በምደባው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ማዕረግ የፋይናንስና የኢኮኖሚ ዘርፍ አስተባባሪ ሆነው የተመደቡት ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልም በተመሳሳይ የአቶ መለስ ቅርብ ሰው ናቸው። ጎልጉል ዶ/ር ደብረጽዮን ወደ ከፍተኛው ስልጣን ርካብ እንደሚሻገሩ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆኑ ዘግቦ ነበር።

ክፍት በነበሩና በአዲሶቹ ሶስት አደረጃጀቶች መሰረት የተካሄደውን የባለሥልጣናት ምደባ አስመልክቶ አቶ ሃይለማርያም “ጠ/ሚኒስትሩ በቀጥታ ከሚከታተላቸውና ከሚመራቸው የመከላከያ፣ የደህንነት፣ የዲፕሎማሲ፣ የማክሮና ሜጋ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ ያሉትን የማህበራዊ፣ የመልካም አስተዳደር፣ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ዘርፎችን የመከታተል ስራ እንዲሰሩ ክላስተሮች ተቋቁመዋል” ብለዋል። አይይዘውም አደረጃጀቱ ስራዎችን በየደረጃው ለመምራት የሚያስችል እንደሆነ አመልክተዋል።

የኢህአዴግ ፓርላማ በዛሬው ዕለት የቀረቡለትን ምደባዎች ሲያጸድቅ ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ያቀረቡት የከፍተኛ ባለሥልጣናት ምደባ ከአቶ ደመቀ መኮንን በተጨማሪ ሁለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮችን አካትቷል። ምደባው ከትግራይ ሁለት፣ አንድ ከኦሮሚያ፣ አንድ ከጉራጌ ብሄረሰብ የተካተቱበት መሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለተመዳቢዎቹ ሲያስታውቁ ገልጸዋል።

ምደባው በደፈናው ሁሉም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የተካተቱበት ቢመስልም ጎልጉልን ጨምሮ በተለያዩ ሚዲያዎች አስቀድሞ እንደተነገረው ከአቶ መለስ ዜናዊ ህልፈት በኋላ ተግባራዊ ተደርጓል ለተባለው የቡድን አመራር ማረጋገጫ ተደርጎ ተወስዷል። በጸደቀው ምደባ መሰረት ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ አቶ ሙክታር ከድር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር፣ አቶ ከበደ ጫኔ የንግድ ሚኒስትር እንዲሆኑ ተደርጓል።

በዚሁ ምደባ መሰረት ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የፋይናንስና የኢኮኖሚ ዘርፍ አስተባባሪ ሆነው ቢመደቡም ከደህንነት ጋር የተቆራኘውን የመገናኛና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትርነታቸውን አልተነጠቁም። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሃላፊነታቸውን ስለመቀጠላቸው በይፋ ያልተገለጸው አቶ ሙክታር ከድር በምክትል ጠ/ሚኒስትርነት ማዕረግ የመልካም አስተዳደር ማሻሻያ ዘርፍ አስተባባሪና የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር ሆነዋል። አቶ ሙክታር ከኦሮሚያ ምክትል ፕሬዚዳንትነታቸው ተነስተው ለሁለት ዓመት ኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ያለ ስራ እንዲቀመጡ ተደርጎ የነበረው በመልካም አስተዳደር ችግርና አቅም ማነስ እንደነበር በማስታወስ አስተያየት የሰጡ “ምደባው ኦህዴድ የምክትል ጠ/ሚኒስትርነት ቦታ አገኘ በሚል የፖለቲካ ጨዋታ ለመጫወትና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትርነቱን ቦታ በመጠየቁ ለማስተዛዘኛ ነው” ብለዋል። በሌላ በኩልም አቶ ሙክታር ለባለሃብቱ አላሙዲ ቅርበት ያላቸውና በዚሁ ቅርበታቸው ሳቢያ ኦሮሚያ ክልል ባለሃብቱ ግብር እንዲከፍሉና የወሰዱትን ቦታ እንዲያለሙ ለማስገደድ ሲንቀሳቀስ አቶ ሙክታር በመቃወማቸው በኦህዴድ ስራ አስፈጻሚ በጉድለት መገምገማቸውን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ይናገራሉ።

ደመቀ መኮንን እና ሃይለማርያም ደሳለኝ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የትምህርት ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጨምሮ ሶስት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች የሚደገፉት አቶ ሃይለማርያም፣ አቶ መለስን ተክተው መስራት በጀመሩ ማግስት “የምንሰራውና የምንመራው በቡድን ነው” ባሉት መሰረት በሶስት ም/ጠቅላይ ሚኒስትሮች መታጀባቸው ይፋ ሆኗል። ጎልጉል ብዙም ትኩረት ያልተሰጣቸውን ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ጠ/ሚኒስትር ለማድረግ ታስቦ በአሜሪካን ተጽዕኖና በቅድመ ማግባባቱ ላይ የኦህዴድን ድጋፍ ሊያገኙ ባለመቻላቸው አቶ ሃይለማርያም በነበሩበት እንዲቀጥሉ መደረጉ መዘገቡ ይታወሳል።

በአዲሱ ምደባ የዶ/ር ቴዎድሮስን ቦታ በመረከብ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር የሆኑት ምክትላቸው ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱ ናቸው። የአምስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ምደባ ይፋ በሆነበትና በዛሬው ዕለት አቶ ሃይለማርያም እንደ ወትሮው ሁሉ ንግግራቸውን የጀመሩት የአቶ መለስን ስም በማስቀደም ነበር። በዚሁ ንግግራቸው “ቀደም ሲል የተያዘው የአመራር መተካካት ከታቀደው በፊት ተግባራዊ ይደረጋል” ሲሉ ተደምጠዋል።

አቶ ግርማ ሰይፉ ላቀረቡት ተቃውሞ መልስ የሰጡት አቶ ሃይለማርያም ቀደም ሲል አቶ ግርማ ብሩ ይመሩት የነበረውን የንግድ ሚኒስቴር “የንግድ ምልክትና የንግድ ስያሜ እንኳን መለየት የማይችል እጅግ ኋላ ቀር” ሲሉ ነው ያንኳሰሱት። የዓለም ባንክ ሪፖርት ይፋ ባይደረግም አቶ ከበደ ጫኔ ችግር እንዳለ በማወቅ አዲስ አዋጅ በማዘጋጀትና ዘመናዊ አሰራር በመዘርጋት ተቋሙን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመለወጥ እየሰሩ ያሉ ሚኒስትር መሆናቸውን በመግለጽ አቶ ሃይለማርያም ተከራክረውላቸዋል። አዳዲሶቹ የፌደራል ስራ አስፈጻሚዎች ቃለመሃላ ፈጽመዋል። ኦህዴድ ያገኘዋል የተባለውን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትርነት መቀመጫ ማጣቱን ተከትሎ አስተያየት ለማሰባሰብ ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም። ምደባው እንደተለመደው በአንድ ድምጸ ታቅቦ ነው የጸደቀው። በዕለቱ ምክንያቱ ባይታወቅም አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ አልተገኙም።

http://www.goolgule.com

posted by Tseday Getachew

አሁንም የተሃድሶ ያለህ!!!

“አንድነትን ስንመሰርት በቅንጅት ወቅት ስለሰራነው ጥፋትና የፖለቲካ ስህተት የገመገምነው ነገር የለም” ዶ/ር ያዕቆብ ሃ/ማርያም አንድነት ፓርቲን ከቅንጅት ጋር በማነጻጸር ከተናገሩት፡፡

በኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፓርቲና ድርጅቶች መዋቅራዊ ጥንካሬና ደጋፊዎቻቸውን አስተባብረው ውጤት ማስመዝገብ ያለመቻላቸው ጉዳይ አነጋጋሪ ነው። ተቃውሞ በኢትዮጵያ በፓርቲ መሪዎችና በገዢው ኢህአዴግ መካከል የሚደረግ እሰጥ አገባ ካልሆነ በስተቀር በደጋፊዎች ተሳትፎ ገዢውን ፓርቲ የማስገደድና እጁን የመጠምዘዝ ደረጃ ላይ ደርሶ ሊታይ አልቻለም። ከቅንጅት መፈራረስና ልዕልናው መክሰም ጋር የህዝብ ስሜትም አብሮ ተዳፍኗል የሚለው አስተያየት ሚዛን የደፋ የሚሆንባቸው የበዙት ለዚሁ ነው። በድርጅት ደረጃ ችግሩን ተመልክተው ስለመታደስ የሚያስቡ ስለመኖራቸው ግን ለረዥም ጊዜ አልሰማንም።

በኢትዮጵያ ህዝብን ለትግልና ለእምቢተኝነት የሚያነሳሱ ጉዳዮች ሞልተው የፈሰሱ ቢሆንም ህዝብ በስርዓቱ ከመበሳጨት የዘለለ እንቅስቃሴ አለማድረጉ ስርዓቱ ከዘረጋው የአፈና መዋቅር ጋር የሚያገናኙት ቢኖሩም በዋናነት የተቃዋሚዎች ድክመት ጎልቶ እንደሚታይ አሁን አሁን ይፋ እየሆነ ነው። በተለይም ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ሰሞኑን “የግል አስተያየቴ ነው” በማለት ያቀረቡት ጽሁፍ የችግሩ ቁልፍ ነውና ሁሉም ወገኖች አሰራራቸውን ሊፈትሹ እንደሚገባ ይሰማናል – አሁን!!

“ከኔ አመለካከት ጋር የማይስማሙ እንዳሉም እገነዘባለሁ፡፡ በበኩሌ ከኔ ጋር የማይስማሙትን አከብራለሁ፡፡ ሃሳባቸውንና አመለካከታቸውን ባልጋራና ባልስማማባቸውም እነሱንም ሆነ ሃሳባቸውን፣ አመለካከታቸውንና አቋማቸውን አዳምጣለሁ። አከብራለሁ፡፡ የመረጃ ስህተት ካለ ስህተቴን ለመቀበልና ለማረም ዝግጁ ነኝ፡፡ የኔን ሃሳብ፣ አመለካከትና አቋም የማይጋሩት ግን እንዲያዳምጡኝና እንዲያከብሩልኝ አደራ እላለሁ” ሲሉ የወቅቱን የአገራችንን ሁኔታና የወደፊቱን የትግል አቅጣጫ በተመለከተ ለመወያየት በተጠራ ስብሰባ ላይ የአንድነት ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ባቀረቡት ንግግር የተናገሩት ነው። ሌላስ ምን አሉ?

“ኅብረሰባችንን ስናይ ብሶተኛና የማጉረመርም ደረጃ ላይ እንጂ ተናድዶ ንዴቱን በእንቅስቃሴ ለማሳየት ዝግጁ የሆነበት ደረጃ ላይ የደረሰ አይመስልም፡፡ ብዙ የማህበራዊና የኢኮኖሚ ችግሮች አሉበት፡፡ ይህንን ሰቆቃውንና ብሶቱን ያማርራል፡፡ በይፋና በአደባባይ አይገልጽም፡፡ ብሶቱ በማጉረምረም ደረጃ የሚገልጽ ነው እንጂ በአጠቃላይ ወደ ኅብረተሰባዊ ንዴት አልተለወጠም፡፡ የተናጠል ንዴቶች አልፎ አልፎ ቢገለፁም ሠፊና የአጠቃላይ የኅብረተሰቡ አልሆኑም፡፡ እነዚህ የተናጠልና ትናንሽ ንዴቶች ወደ ተደራጀና የተቀናጀ ሕዝባዊ እምቢተኝነት እና የእምቢተኝነት እንቅስቃሴዎች አልተለወጡም፡፡ በሌሎች አገሮች በዳቦ ወይም በነዳጅ ዋጋ ላይ ትንሽ ጭማሪ ከታየ የኅብረተሰቡ ንዴት ይገነፍላል፡፡ በኛ ህዝብ ዘንድ ግን ይህ አይታይም፡፡ ምልክት ከታየም ጥቂት፣ የተናጠል፣ ያልተደራጁና ያልተቀናጁ ናቸው” ነበር ያሉት።

አዎ!! ያለመደራጀት ችግር፣ የግንዛቤ ችግር፣ ደጋፊን አሳምኖ የመምራት ችግር፣ ከስህተትና ከውድቀት ያለመማር ችግር፣ የተሃድሶ ችግር፣ የእውቀት ተሃድሶ ችግር፣ የራዕይ ችግር፣ በስድብና ተቃውሞ ላይ ያተኮረ ትግል፣ ፍረጃና ማግለል ላይ የተንጠለጠለ የትግል ጉዞ፣ ካለፈው ያለመማርና ይሉኝታን ያዘለ ትግል፣ በግልጽ ራስንና ተሞክሮን ያለመገምገም ችግር፣ የተድበሰበሰ አቅጣጫ የመከተል ችግር፣ እንደኔ አስብ የሚል አባዜ፣ ድርጅትህን አፍርሰህ እኔ ጋር ተጠቃለል የሚል ሌላውን ያለማክበር ችግር፣ እኛ ያልባረክነው የተቃውሞ መንገድ ውግዝ ነው የሚል የትምክህት ስሜት፣ በተመሳሳይ አጀንዳ እየተመሩ መቧደን፣ ማነስ፣ ትንንሽ መሆን፣ ከትግልና ከትግሉ መስመር ይልቅ ወንበርና ስልጣን መናፈቅ፣ ልዩነትን በሰለጠነ መንገድ በውይይት ከማስወገድ ይልቅ በሃሜትና በማሳጣት መስመር መረባረብ … የሚጠቀሱት በሽታዎች ናቸው። በተግባር እንደታየውና ሁሉም እንደሚመሰክሩት እነዚህ ችግሮች የተቃዋሚውን ጎራ ጨረቃ ላይ ጥለውታል። ባለበት እንዲረግጥ አድርገውታል። በዚህም ሳቢያ አብዛኞች ከየትኛው ወገን እንደሚሆኑ መወሰን አቅቷቸዋል። በኛ እምነት ይህኛው የኅብረተሰብ ክፍል ታላቅና ሃይል ያለው ስለሆነ በእውቀት ተሃድሶ ወደ ትግሉ የሚገባበት መንገድ መቀየስ አለበት። የተከፈለው ዋጋ ተከፍሎ!!

“እውቀት የሌለው፣ መረጃ የማያገኝ ህዝብ፣ የተደራጀና የተቀናጀ አደረጃጀቶች የሌለው ሕዝብ ለውጥ ሊያመጣ አይችልም፡፡ ከፖለቲካ ድርጅቶች የሚጠየቀውና የሚጠበቀው የተናደደ ኅብረተሰብን መፍጠር ሳይሆን መረጃ የሚያገኝ፣ እውቀት ያለው፣ የተደራጀና ድርጅቶቹ የተቀናጁ ኅብረተሰብ መፍጠር ነው” ሲሉ አሰተያየታቸውን ያሰፈሩት ዶ/ር ነጋሶ ደግ ብለዋልና ጆሮ ላላቸው ታላቅ መልዕክት ነው።

ስለሆነም የወደፊት የትግል አቅጣጫችንን የማሳወቅ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ የማደራጀትና፣ ድርጅቶችን የማቀናጀት ሥራን ማዕከል ያደረገ መሆን እንዳለበት ልምዳቸውንና በግልጽ የተመለከቱትን አስታከው ያቀረቡት የመፍትሄ ሃሳብ በስፋት መድረክ ሊሰጠው የሚገባ ነው ብለን እናምናለን። በእውቀት ላይ የተመሰረተ ትግል እንደገለባ መንሽ በተመለከተ ቁጥር አይቦንም፤ እውቀቱም ቀላል ነው። በየወቅቱ የሰለቸንን የመቡነን አደጋና ከድርጅት ወደ ድርጅት የመገላበጥ እንዲሁም ስም እየቀየሩ ብቻ ለቁጥር የሚያዳግት ድርጅት መመስረት የሚቆመው ይኸው የእውቀት ተሃድሶ ተግባራዊ ሲሆን ነው። እውቀቱ በኮሌጅ ወይም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚሰጥ አይደለም። በእውነተኛነትና በቅንነት ላይ የተመሠረት እውቀት ነው፡፡ ከራስ በራስ የሚቸር ቀናነትን መሰረት ያደረገ ለራስ የመታመን ጥያቄ ነው። ሰው ምን ይለኛልን አውሎቆ የጣለ እውቀት ነው፡፡ በጥቅምና በወዳጅነት የሚደለል ሳይሆን በሐቀኝነት ዓለት ላይ በመተማመን ጸንቶ የቆመ እውቀት ማለት ነው፡፡ ለራሱ የሚታመን የትግል መስመርና ታጋይ ራዕይ አለው። ለለውጥ ንቅናቄ መሪውን አይጠብቅም፡፡ ያነገበው ራዕይ እያንደረደረ የድሉ በር ላይ ያደርሰዋል። ከሁሉም በላይ የነቃና በመረጃ የታጠቀ ህዝብ ድርሻውን ያውቃል። መብቱን ለማስከበር የትኛውንም ወገን የማስገደድ አቅም ያዳብራል። እንዲህ ያለ ህዝብ በተፈጠረ ቁጥር የአምባገነኖች ጡንቻ እየሰለለ ይሄዳል። ልባቸውም ይርዳል። እንዲህ ያለው የእውቀት ተሐድሶ ከድርጅት ወይም ከፓርቲ አይመጣም፡፡ በስብሰባ ብዛትና በጥናትና ምርምር ምጥቀት አይከሰትም፡፡ ግንኙነት ማድረግ በሚቻልበት አጋጣሚ ሁሉ ወሬ በመውቀጥ በተዓምር ብቅ አይልም፡፡ እንዲያውም ይህንን ዓይነቱ አካሄድ በሙሉ የራስ ማንነትን በማጥፋት በአጀብ፣ በቡድን ተግበስብሶ ለመመራት ያጋልጣል፡፡ ስለዚህ ተሃድሶው ከራስና በራስ መጀመር አለበት፡፡ እያንዳንዱ ሰው የሚፈልገውን በደመነፍስ ሳይሆን በእርግጠኝነት ማወቅ አለበት፡፡ ስለዚህ ከመምራትም ሆነ ከመመራት፤ ከመደራጀትም ሆነ ከማደራጀት በፊት እውቀት ይቀድማል! ለዚህ ደግሞ ተሃድሶ ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም አሁንም ደግመን የምንለው ቅድሚያ ከራስ የሚጀመር ተሃድሶ ባስቸኳይ!!

http://www.goolgule.com

posted by Tseday Getachew

የሁለት ምክትል ጠ/ሚኒስትሮች ሹመት ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌን የጣሰ ነው ተባለ

ኢሳት ዜና:-በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ ፓርላማ የሰጠው ተጨማሪ የሁለት ምክትል ጠ/ሚኒስትሮች ሹመት ሕገመንግስታዊ ድንጋጌን
የጣሰ መሆኑን የሕግ ባለሙያዎች አስታወቁ፡፡
በሕገመንግስቱ አንቀጽ 75 ለአንድ ጠ/ሚኒስትር ብቻ ዕውቅና እንደሚሰጥ ያስታወሱት ባለሙያዎቹ በዚሁ አንቀጽ
75(1)ለ ላይ የተመለከተው ጠ/ሚኒስትሩ በማይኖርበት ጊዜ ምክትል ጠ/ሚኒስትሩ ተክቶት ይሰራል የሚለው ንኡስ አንቀጽ አንድ ምክትል ጠ/ሚኒስትር ብቻ እንደሚኖር የሚያሳይ ነው ይላሉ፡፡በአሁኑ ወቅት ቀደም ሲል የተሾሙትን ጨምሮ ሶስት ምክትል ጠ/ሚኒስትሮች መሾማቸውን ባለሙያዎቹ አስታውሰው ይህ ሕገመንግስታዊ ድንጋጌን የጣሰ አካሄድ ነው ብለውታል፡፡
ጠ/ሚኒስትር ሀይለማርያም እንዲህ ዓይነት ሹመት ለመስጠት ከሕገመንግስቱ በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት በስራ ላይ ያለው
የአስፈጻሚ አካላትን እንደገና ለማደራጀት የወጣው አዋጅ ቁጥር 691/2003 ያግዳቸዋል ብለዋል፡፡በዚህ አዋጅ
ክፍል ሁለት አንቀጽ 6 ላይ የሚኒስትሮች ም/ቤት አባላት በሚል የዘረዘራቸው ጠ/ሚኒስትሩን፣ምክትል /ጠ/ሚኒስትሩን፣የሚኒስትር መ/ቤቶችን የሚመሩ ሚኒስትሮች እና በጠ/ሚኒስትሩ የሚሰየሙ ሌሎች ባለስልጣኖች መሆናቸውን ደንግጓል፡፡
ይህው አስፈጻሚ አካላትን እንደገና ለማዋቀር የወጣው አዋጅ አንቀጽ 4 የምክትል ጠ/ሚኒስትሩ ሥልጣንና ተግባር
በሕገመንግስቱ በአንቀጽ 75 የተመለከተው እንደሚሆን በግልጽ አስቀምጧል፡፡
ባለሙያዎቹ ሹመቱ በተለይ ሕገመንግስቱን የጣሰ መሆን እንዳልነበረበት አስታውሰው በዚህ ሹመት መሰረት ጠ/ሚኒስትሩ
በማይኖሩ ጊዜ ማን ይተካቸዋል የሚለው ግልጽ የሆነ ምላሽ የለውም ሲሉ ተችተውታል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ የዚህን ዓይነት ሹመት መስጠት አይችሉም ያሉት ባለሙያዎቹ መስጠት ቢፈለግ እንኳን በቅድሚያ
ሕገመንግስታዊ ማሻሻያ መቅደም ነበረበት በማለት አካሄዱን ነቅፈዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሹመቱ በዛሬው እለት እንዲሰጥ የተፈለገው በነገው እለት በኦሮሚያ ምክር ቤት ውስጥ ይነሳል ተብሎ የሚጠበቀውን ውዝግብ ከአሁኑ ለማብረድ መሆኑን ምንጮች ጠቁመዋል።

የኦህዴዱን አቶ ሙክታር ከድርን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በማድረግ በኦሮሚያ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ነገ ይነሳል ተብሎ የሚጠበቀውን ውዝግብ ለማብረድ ታቅዶ በዛሬው እለት አዲሱ ሹመት ይፋ እንዲሆን መደረጉን የኢህአዴግ ኦህዴድ ምንጮች ገልጸዋል።

ዛሬ በሚጀመረው የኦሮሚያ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ፣ የምክር ቤት አባላቱ በአቶ ሀይለማርያም ሹመትና ኦህዴድ ከጨዋታ ውጭ ሆኗል በሚለው ዙሪያ ከፍተኛ ውዝግብ ይነሳል ተብሎ ይጠበቃል። አዲሱ ሹመት በኦህዴድ ውስጥ ተፈጥሮ የነበረውን ውዝግብ ያርግበው አያርግበው የታወቀ ነገር የለም። ይሁን እንጅ አቶ ደመቀ ምክትል ጠቅላይ ሚኒሰትር ተብለው ከተሾሙ በሁዋላ ሌሎች ተጨማሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒሰትሮች እንዲሾሙ መደረጉ በአራቱ ድርጅቶች ውስጥ ያለውን ፍትጊያ የሚያመላክት መሆኑን ተንታኞች ይናገራሉ።

posted by Tseday Getachew

በአየር መንገድ ውስጥ በጉልበት ስራ ላይ ይሰሩ የነበሩ ከ500 በላይ ሰራተኞች በኢህዴግ ፎረም አባላት ከነገ ጀምሮ ሊተኩ ነው

ኢሳት ዜና:-ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ የአየር መንገድ ሰራተኞች ለኢሳት እንደገለጡት ከነገ ጀምሮ ከ500 እስከ 700 መቶ የሚጠጉ የጉልበት ሰራተኞች ስራቸውን ይለቃሉ። በተለያዩ ቀታሪ ኤጀንሲዎች ውስጥ ከ4 አመታት ላለነሰ ጊዜ በጉልበት ስራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ሰራተኞች የሚባረሩት የኢህአዴግ ፎረም አባላት አይደላችሁም ተብለው ነው። ሰራተኞች እንደገለጡት በፎረም ተጠናክረው ሲመጡ ተመልሰው ሊቀጠሩ እንደሚችሉ ቃል ተገብቶላቸዋል። በሚባረሩት ወጣቶች ቦታ በስልጠና ላይ አሉ በሺ የሚቆጠሩ የወጣት ፎረም አባላት ከነገ ጀምሮ ስራ ይጀምራሉ።

ኢህአዴግ በወሰደው እርምጃ ያዘኑ ሰራተኞች እንደገለጡት፣ የኢህአዴግ ፎረም አባላት አይደላችሁም በሚል ከስራ መባረራቸው ህገመንግስቱን የሚጥስ ብቻ ሳይሆን ሳንወድ በግድ ለእንጀራ ብለን ኢህአዴግን እንድንደግፍ የሚያደርግ ነው።

ኢህአዴግ በቀጣዩ የወረዳና የከተማ ምርጫ አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት ያስችለው ዘንድ የወጣት ፎረም አባላትን በጊዜያዊ ስራ እየሸነገለ ነው በማለት ተቃዋሚዎች በተደጋጋሚ ወቀሳ ያቀርባሉ።

በተያያዘ ዜናም ኢህአዴግ አንዳንድ አባላቱን ከድርጅት አባልነት ያስወጣ በማስመሰል በወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች አስመራጮች አድርጎ ሊያሾም መሆኑን ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ አመልክቷል።

በይፋ የማይታወቁ የድርጅቱ አባላት በገለልተኛ ስም በምርጫ አስፈጻሚነት ለማወዳደርና ለማሰራት መታቀዱን ነው ለማወቅ የተቻለው።

posted by Tseday Getachew

ኃይለማርያምን ፍለጋ

ከሰለሞን ስዩም
(ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ በሃገር ቤት እንዳይታተም ተዘዋዋሪ ጫና ስለተረገበት በዘ-ሐበሻ ድረ ገጽ እንዲነበብ የላከው)
በተለያዩ ጊዜያት ስለጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ ፅፌያለሁ፡፡ ይህን ያደረግሁት ስለ ሰውዬው መከታተል ከጀመርኩ ከረዥም አመታት በኋላ ነው፡፡ ጠ/ሚ/ሩ ወደ ስልጣን ከመጡ ከረዥም አመታት በኋላም፡፡ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊትማ እንኳን እርሳቸውን ራሴንም አላውቅም ነበር፡፡ ስለ ጠ/ሚ/ር ኃይለ ማሪያም ደሳለኝ ለመሞገት ግን እድል በእጄ ላይ ጥላቸዋለች፡፡ ሰውዬውን ከደቡብ ብሔረ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ፕሬዚዴንትነታቸው ጀምሮ ስለማውቃቸው፡፡ በነገራችን ላይ ስለ ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊና ኢህአዴግ ሙሉ ሀተታ የያዘ ወጥ መፅሐፍ (አሁን እንደተለመደው ጋዜጣ ላይ ከወጡ ፅሁፎቼ የተወደ አይደለም) በቅርብ ቀን እንደማስነብባችሁ ቃል እየገባሁ ለዛሬ በተወሰነ መልኩ ብቻ ከኃ/ማሪያም ጋር እያወዳደርኩ ካልሆነ ትኩረት አላረጋቸውም፡፡
አቶ መለስ ሀሳባቸውን በመግለፅ አይታሙም፡፡ ሀሳባቸው ግን ከራሷ ግዛት ውጭ የሆኑትን ነገሮች በግድ ለመጠቅለል የምትጥር ነበረች፡፡ የመለስ ሀሳብ አብዛኛውን ጊዜ መሬት ካለው ነገር የበዛ ነበር፡፡ ይህ ማለት ጀርመናዊው ፈላስፋ ሄግል ‹‹በሀሳቤና ሀሳቤ በቆመለት ነገር መካከል ያለውን ልዩነት›› በማለት ለማስታረቅ ካደረገውን ጥረት በተቃራኒ ማለት ነው፡፡ አቶ መለስ ሀሳባቸው መሬት ካለው ነገር አልፎ የሚሄደው በሁለቱ መካከል (በሀሳቡና እውነታው) መካከል ያለው ልዩነት ባብዛኛው ወደሀሳቡ ስለሚያደላ ነበር፡፡ ሆኖም ግን፣ ሰውዬው ይህንንም ለማድረግ ብዙ ማሰባቸው ስለማይቀር የዘመናዊ ፍልስፍና አባት የሚባለው ዴካርተስ “I think hence I’m” ያለውን የሚያሟላ ይመስላል፡፡ ዴካርተስ “ስለማስብ እንዳለሁ አረጋገጥሁ” ያለው ቁምነገር በአቶ መለስ እና ተከታዮቹ ዘንድ ግን ወደ ዝቅተኛ ደረጃ ወርዷል፡፡
ኢህአዴግ በፖሊሲዎቹ ሁሉ ቁሳዊ ልማት የማረጋገጥ ጥረት ላይ ያጠነጥናል፡፡ የኢህአዴግ ፖሊሲ በተቻለ መጠን ሰዎች በልተው ስለማደራቸው ብቻ እንዲያስቡ የሚያትት ነው፡፡ ሆኖም ግን፣ በልቶ ስለማደር መወትወት መልካም ነው እንኳ ብንል መንገዱ የተበላሸ ይመስለኛል፡፡ ሊረጋገጥበት የሚችለው ጥራት ያለው ትምህርት ሲኖር ነውና፡፡ ኢህአዴግ ግን ‹‹እንብላ›› የሚለው የትምህርትን እናት ቀብሮ ነው፡፡ “የሰው ልጅ የሚያጠነጥነው በሆዱ ዙሪያ ነው” የሚለው ካርል ማርክስ የኢህአዴግን ፖሊሲ ተንብዮ መሆን አለበት፡፡ አሊያም መለስ/ኢህአዴጎቹ በሰውዬው ሀሳብ ከመጠን በላይ ተመስጠዋል ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት አቶ መለስ ከላይ ያሰፈርነውን የዴካርተስ “I think hence I’m” ሲያነብ “I eat thus I’m” (በልቼ ስለማድር መኖሬን አረጋገጥኩ) ብሎ ነው ማለት ነው፡፡ እኔ ግን መብላት የመኖር ትርጉም ነው አልልም፡፡ ከዚህ ሁሉ ግን፣ ብሉይ ቢሆንም “I’m certain that I’m, because I think” ብል ይቀለኛል፡፡ ጠ/ሚ/ር ኃ/ማርያም ደሳለኝ እንደ መለስ ዜናዊ በቃላት አይጫወትም፡፡ በቃላት መጫወት የምለው ልክ እንደ ሶፊስቶች አሊያም ዲያሌክቲስቶች የቃላት ሰርከስ በመስራት ለእውነት ግን ግድ ማጣትን ነው፡፡
አቶ መለስ አንድ ከተሰጣቸው ዓረፍተ ነገር አሊያም ራሳቸው ከሰሩት ዓረፍተ ነገር (premise) ሌሎችን እያራቡ በመጨረሻ የመጀመሪያውን ዓረፍተ ነገር የሚቃረን ሀሳብ ጋር ሊወስዱን የሚችሉ መሪ ነበሩ፡፡ በከፍተኛ ምክንያታዊነት የደረሰበት የሚመስለው የመጨረሻው ዓረፍተ ነገር ግን የእውነቱ ተቃራኒ ነው፡፡ ይህ የ ‹‹Dialectics›› ጥበብ ነው፡፡
ሶፊስቶች ደግሞ አሉ፡፡ ሶፊስቶች እንጀራቸውን የሚያበስሉት ምክንያታዊነትን ያለ አግባብ በመጠቀም ነው፡፡ አግባብ ያልሆነ አመክኒዮ በመጠቀም እውነትን በማድማት ኑሯቸውን የሚመሩ ናቸው፡፡ አሊያም ደግሞ የተሰጣቸው ደረጃ፣ ደረጃውን ለሰጧቸው ቡድኖች እውነትን ባደሙላቸው መጠን ነው፡፡ ነገር ግን ይህን ሲያደርጉ እውነተኛ ለመምሰል በቃላት ጨዋታ የተካኑ መሆን አለባቸው፡፡ የግላቸው ዋና አላማ ደግሞ በየትም ብለው የተመኙትን ቦታ መያዝ ነው፡፡ እነዚህን ለመዋጋት ፍልስፍና እንደጀመረ የሚነገርለት ታላቁ ፕላቶ የሶፊስቶችን መንገድ “unreal wisdom” /እውነተኛ ያልሆነ ጥበብ/ ይለዋል፡፡
የመለስ ዜናዊ እንጀራ ስልጣን ላይ ረዥም ጊዜ ለመቆየት ከሆነ ሶፊስትም ነበሩ ልንል ነው፡፡ ኃ/ማሪያም ግን ሶፊስትም ዲያሌቲክስትም ሳይሆኑ እንደምን የመለስ አልጋ ወራሽ ሆኑ? ይህ ማለት ኃ/ማሪያም ለእውነት የቆሙ ናቸው ብዬ አይደለም፡፡ ይልቅ እንደ መለስ የቃላት ጫካ መሃከል ሳይደበቁ በግልጽ እውነትን ስለሚያጠቁ ብዬ ነው፡፡ መለስ ዜናዊ ንግግር አዋቂ ናቸው እንላለን፡፡ ‹‹እውነት›› አዋቂ ግን አልነበሩም፡፡ ንግግርም እውነትም የማያውቁት አቶ ኃይለማሪያም ታዲያ እንዴት ለመለስ ተተኪ ሆኑ ነው ጥያቄዬ፡፡
የዛሬ አላማዬ መጠየቅ በመሆኑ ያለ መልስ እቀጥላለሁ፡፡ አቶ ኃ/ማሪያም የኢህአዴግ ፕሮግራም ከመፅሐፍ ቅዱስ ጋር ይመሳሰላል ሲሉ ክርስትና ሊሰብኩን የሞከሩ እለት “እውነት እኚህ ሰው ኢህአዴግን ያውቃሉ?” ብያለሁ፡፡ አንድ አብነት እንኳ ባነሳ የኢህአዴግ /ህወሓት ህገ መንግስት ሰዎችን በብሔራቸው፣ በብሔረሰባቸው አሊያም በህዝባቸው በኩል ካልሆነ እንደማይቀበል ሳያውቁ በእንደምን ጠ/ሚ/ር ሆኑ እላለሁ፡፡ መፅሐፍ ቅዱስ በክርስትና መስፋፋት ላይ ስኬት ያገኘው ሰዎችን ከቡድናቸው ውጭ እኩል በማየቱ ነው፡፡ ኃ/ማሪያም ግን የመንግስታቸው ህገ መንግስት መግቢያ የሚለውን ሳያነቡ (ቢያነቡ ያንን አይሉም ነበር) ጠ/ሚ/ር መሆናቸው እንቆቅልሽ ይሆንብኛል፡፡ መግቢያው “እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች . . .” ከማለት የዘለለ “በምርጫዬ ኢትዮጵያዊ ነኝ” የሚለውን ክላውድ ሳምነር፣ ህይወቱን ሙሉ ኢትዮጵያን ያገለገለውን ሪቻርድ ፓንክረስት . . . አያጠቃልልም፡፡ “ዘሬ ክርስቶስ ነው” የሚለኝ ፕሮቲስታንት ጓደኛዬን ‹‹ከመፅሐፍ ቅዱስ ጋር ይመሳሰልብኛል›› የሚሉት የኢህአዴግ ፕሮግራም የት ያውቀዋል? ኃይሌ የኢህአዴግን ፕሮግራም እንደማያውቁ ግን መልስ አግኝቻለሁ፡፡ መልሴንም መጠየቅ (quesstion) ብትችሉም ቅሉ፡፡ “አንድን ነገር” ማወቅ ምንነቱን መተንተን፣ መዘርዘርና መናገር ነው፡፡ ነገር ግን በተመሳሳይ ሰዓት “አንድ ነገር” ምን እንዳልሆነ መተንተን፣ መዘርዘር እና መናገር ይጠይቃል፡፡ በዚህ መስፈርት መሰረት ኃ/ማሪያም ኢህአዴግ ምን እንደሆ እንጂ ምን እንዳልሆነ አያውቁም፡፡ ይህ ሌላኛው ገጽ ዋነኛው የኢህአዴግ ገጽ ነበር፡፡ ዴሞክራሲያዊ ያለመሆኑ፣ ክፍት ያለመሆኑ፣ ሆደ ሰፊ ያለመሆኑ፡፡ ማወቅ ግልጽና ልዩ (clear & distinct) የሆነ ፀባይ መተንተንን ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ አቶ ኃይለማሪያም ኢህአዴግን አያውቁም፡፡
ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ ለሀ/ማሪያም ስለ ኢህአዴግ ብዙ ነገር ይነግሯቸው ነበር ብዬ እገምታለሁ፡፡ ጠ/ሚ/ር ኃ/ማሪያምም ያለ መጠራጠር እንዳሉ ይውጧቸዋል፡፡ ይህን ለምን ያነሳሁ መሰላችሁ፡፡ ዴካርቴስ ‹‹ከማሰቡ›› በተጨማሪ ሁለተኛው የመኖሩ ማረጋገጫ ያደረገው ‹‹መጠራጠሩን›› ስለነበር ነው፡፡ ዝም ብሎ መስማትማ እንስሳትም ይሰማሉ፡፡ አይመርጡትም፣ አይጠረጥሩትም፡፡ ይህ አርስቶትል “Animals are true machines” ብሎ ከዘረዘረው ከግዑዝነት ትንሽ ብቻ ከፍ ማለት መስፈርት ጋር ይጣጣማል፡፡ እንስሳት የሚመጣውን መረጃ /ሁነት ከማስተናገድ ውጭ የገባውን አያመዛዝኑም፣ አይሰልቁም፡፡ የገባውን ሁነት ካላመነዠኩት እንደሚያስቡ እንዴት እናረጋግጣለን?
ለሰው ግን እንዲህ መሆን ባልተገባው፡፡ የኃ/ማሪያም ሁሉን መዋጥ ግን መጠራጠሩንና ማሰቡን እንድጠራጠር አድርጎኛል፡፡ ታላላቆቹ የሀሳብ ሰዎች “A mind can’t cease to think unless cease to be”/አዕምሮ መኖር(መሆን) ካላቆመ ማሰብ አያቆምም / ከሚለው ሀሳብ ጋር እየተጣረሰብኝ ነው፡፡ ለዚህም ነው “እውን ሰውየው አሉ?” ስል ፍለጋ የጀመርኩት፡፡ እውን ሰውየው አሉ?

Source: http://www.zehabesha.com/?p=13207

posted by Tseday Getachew

ኢትዮጵያ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ምርት እድገት አሳየች!

አቶ ሃይለማም ሲፈሩ ሲተቡ ቆይተው ዛሬ የካቢኔ ሹመት ለማደረግ ፓርላማ ብቅ ብለው ነበር አሉ። ይዘዋቸው ከመጡዋቸው ካቢኔዎቻቸው መካከል ሌላ ሁለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮችን ይገኙበታል።

አቶ ሃይለማሪያም ሲያስቡት ሲያስቡት ለአቶ ደመቀ ብቻ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን መስጠት አይችሉትም ብለው ሰጉ መሰለኝ…(መሰለኝ ነው ያልኩት) ዛሬ አቶ ሙክታር ከድር እና አቶ ደብረ ፅዮን ገብረሚካኤልን ደጋፊ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አድርገው አሹመዋል። በጥቅሉ በአሁኑ ሰዓት ሀገራችን ሶስት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች አሏተው።

እኛ ሹመቱን ከላይ ከላይ የምናየው የመንግስታችን አድናቂዎች “እሰይ ሀገራችን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እድገት እመርታ አሳየች” ብለን ካገኘን ፅዋ ካጣን ደግሞ ግንባራችንን እያጋጨን ደስታችንን እንገልፃናል።

የምር ግን አቶ ሃይለማሪያም ያኔ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ይሰሩ የነበረ ጊዜ እንደው ሰውየው መለስ ሆነውባቸው “ተሸከሙ” ያሏቸውን ሁሉ “እሺ ጌታዬ” ይሏቸው ነበር እንጂ፤ የጫኑባቸው ሸክም በእጅጉ ከብዷቸው ነበር ማለት ነው!? አዎና ይኸው አቶ ደመቀ ሸክሙን አይችሉትም ብለው የጠረጠሯቸው ከራሳቸው ልምድ ተነስተው አይመስልዎትም!?

ሌላው ጥርጣሬ የኢህአዴግ “ፈላጭ ቆራጮች” (ይሄ “ፈላጭ ቆራጭ” የሚለው ቃል ኢህአዴግ ይፈልጣል ይቆርጣል ብሎ ለማሽሟጠጥ ታስቦ የገባ ቃል አለመሆኑን በቅንፍ አሰውቀን እንቀጥል) እና የኢህአዴግ ፈላጭ ቆራጮች አቶ ሃይለማሪያምን ለአንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ብቻ አምነው መተው ምቾት አልተሰማቸውም ይሆናል!

ለማንኛውም ዶክተር ቴውድሮስ አድሃኖምን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትርነት ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል። ዶክተሩ ከጤና ጥበቃ የተነሱት ጤና ስለነሱ ይሁን ወይስ የውጭ ጉዳዩ ስራ ህክምና ስለሚያስፈልገው አልታወቀም። ሲታወቅ እናወጋዋለን!

http://www.abetokichaw.com

posted by Tseday Getachew

የእስላም ኢትዮጵያውያን የትግል ስልት

ኘ/ር መስፍን ወልደማርያም

በአለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ እስላም ኢትዮጵያውያን ማካሄድ የጀመሩት ትግል በዓይነቱም፣ በስፋቱም፣ በአስተሳሰቡም፣ በስሜቱም እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ ከአገዛዙ ጋር ከተደረጉ ትግሎች በጣም የተለየ ነው፤ በመጀመሪያ ደረጃ ትግሉ ለሃይማኖት ነጻነት ነው፤ ስለዚህም በአገዛዙ በኩል የፖሊቲካ ዓላማና የፖሊቲካ መልክ እየተሰጠው ሲሆን በእስልምና ምእመኖቹ በኩል ግን ትግሉን ከፖሊቲካ የጸዳ ለማድረግ ግሩም የሆነና የተሳካ ጥረት እያደረጉ ነው፤ ሁለተኛ የትግሉ ስልት ፍጹም ሰላማዊ በመሆኑ የአገዛዙን የጉልበት ስልት እያከሸፈ ያጋለጠው ይመስላል፤ አንዱና ዋነኛው የትግሉ ሰላማዊነት መግለጫ በቤተ መስጊድ መወሰኑ ነው፤ ይህ ስልት አዲስ አይደለም፤ በብዙ የአረብ አገሮች የሚጠቀሙበት ነው።
ተፋላሚዎቹ ያልተገነዘቡዋቸው አንዳንድ ጉዳዮች ይታዩኛል፤ አንደኛ እስልምና በጎሣ የታጠረ ባለመሆኑ ከወያኔ/ኢሕአዴግ የአመራር መሠረት ጋር የመቃወም ዝንባሌ ያሳያል፤ እስልምና አብዛኛዎቹን፣ በተለይም ትልልቅ የሚባሉትን ጎሣዎች ሁሉ በተለያየ ደረጃ የሚያቅፍ ነው፤ ስለዚህም አንዳንዶች የእስልምና መሪዎች ሌሎች (ማለት – ክርስቲያኑ) አልተቀላቀሉንም እያሉ የሚያላዝኑበትን ቆም ብለው መመርመር ያሻቸዋል፤ ክርስቲያኑ በተለይ የኢትዮጵያ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች ያሉበትን ሁኔታ በትክክል መረዳት ያስፈልጋል፤ እስላሞች ገና ቀደም ብለው ከብዙ ዓመታት በፊት በተደረገ ትልቅ ሰላማዊ ሰልፍ ‹‹እስላሞች በጎሣ አይከፋፈሉም›› በማለት የገለጹትን ቁም-ነገር አገዛዙ የረሳው ወይም እስላሞቹ ረስተውታል ብሎ ያሰበ ይመስላል፤ አለዚያ እንዲህ ያለ የከረረ እልህ ውስጥ የገባበትን ምክንያት ለመረዳት ያዳግታል፤ ይቺ ባቄላ ያደገች እንደሆን የሚያሰኝ ነገር ለብዙዎች ሰዎች ምንም አልታየም፤ በጉልበት የማይጨፈለቅ ምንም ነገር የለም ከሚል እምነት ተነሥተው ከሆነ ስሕተቱ እየታየ ነው።

በዚህ ጉዳይ ላይ የእስላሙ ኅብረተሰብ ገና በጠዋቱ በጎሣ የመከፋፈሉን አመራር እንደማይቀበለው በማያጠራጥር መንገድ የገለጠ ይመስለኛል፤ ነገር ግን ብዙ ቤተ ክርስቲያኖች የጎሣ ትግላቸውን ወደቤተ እግዚአብሔር አምጥተው የተከፋፈሉና የተዘጉም ቤተ ክርስቲያኖች ነበሩ፤ ይህ የሚያሳፍር ነው፤ ቤተ መስጊዶች እዚህ ደረጃ አልወረዱም፤ እስልምና በጎሣ አይቀደድም፤ እስላሞች ሁሉ የአላህ ልጆች ናቸው፤ በቤተ መስጊድ የሚሰበሰበው ሁሉ በአላህ ልጅነቱ ነው፤ ስለዚህም በመሀከላቸው ልዩነት የለም፤ ይህ የእስላሞች አቅዋም ሃያ ዓመት ተፈተነ፤ የማይበገር ሆነ፤ ስለዚህም ከጎሣ አስተሳሰብ ወጥቶ ሌላ ቀዳዳ መፈለግ ግዴታ ሆነ፤ አል-ሀበሽ አስፈላጊ የሆነው ለዚህ ነው።

እስቲ ጉዳዩ ለሁላችንም ግልጽ እንዲሆንልን ወደክርስትና ዞረን እንየው፤ የኢትዮጵያ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ከነገ ጀምሮ የሉተራን ቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት ተከተሉ ቢባል አንደኛ የኢትዮጵያ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን (ካለች) ምን ትላለች? ሁለተኛ የኢትዮጵያ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ምን ይላሉ? ሦስተኛ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 11 ‹‹መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፤›› የሚለው በጤና አለ ወይ? ብሎ መጠየቅ የማይቀር ይሆናል፤ መልሶቹስ ምን ይሆናሉ?

ከጥቂት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን ስዒረ ሊቀ ጳጳስ እንደተደረገ አሁን ታወቀ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱም፣ ምእመናኑም፣ ማንም ምንም ያለ የለም፤ የተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያንን ሊቀ ጳጳስ የሻረው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ ዛሬ እግዚአብሔር ተገለጠልኝ በማለት ሊቀ ጳጳስዋን የሻረባትን ቤተ ክርስቲያን ትቶ ወደሌላ ተገልብጦአል፤ የተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን አባል በነበረበት ጊዜ የሠራውን ኃጢአት ዛሬ የሌላ ቤተ ክርስቲያን አባል ሆኖ እውነቱን ገልጦልናል፤ ታምራት ላይኔ የኢትዮጵያ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያንን ከለቀቀ በኋላ የክርስቶስን ጸሐየ ጽድቅነት መረዳቱ ለቤተ ክርስቲያኒቱ የሚያሳፍር ነው፤ ከዚያም በላይ የኢትዮጵያ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን አሁንም እውነቱን አላወጣችም፤ አንድም ለሹመት ያኮበኮበ ጳጳስ የክርስቶስን ጸሐየ ጽድቅነት አምኖና ተቀብሎ እውነቱን ለመናገር የደፈረ አልተሰማም፤ ጴጥሮሳዊነት ከጴጥሮስ ጋር ተቀብሮአል አንበል? ይበልጥ ያሳፍራል፡፡

የኢትዮጵያ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያንን ለንጽጽር አመጣሁ እንጂ ዋናው ነገሬ በእስልምና ሃይማኖት ላይ ነው፤ ድርቅና ቁልጭ ያለው እውነት እስልምና አስፈላጊውን መስዋእት ከፍሎ በሰላማዊ መንገድ ጎሠኛነትን ተቃወመ፤ ተቋቋመ፤ አሁን ደግሞ አንደኛ በእስልምና ምእመናን ላይ እንዲጫን የታቀደውን አዲስ የእስልምና ዓይነት አንቀበልም በማለትና ሁለተኛም የእስልምና ካህናትን የምንመርጠው ራሳችን ምእመናኑ ነን፤ ሦስተኛም የእስልምና ካህናቱ ምርጫ የሚካሄደው በመንፈሳዊ ቦታ በቤተ መስጊድ ነው እንጂ በፖሊቲካ ቦታ በቀበሌ አይደረግም አሉ፤ በጎሣ አንከፋፈልም ብለው ጥንካሬያቸውን ያሳዩትን እስላሞች በሃይማኖት ለመከፋፈልና ካህናቶቻቸውን ራሳቸው በየመስጊዳቸው እንዳይመርጡ መከልከል በግልጽ ሕገ መንግሥቱን መዳፈር ነው።

ሁለተኛው ቁም-ነገር አገዛዙ በየቀበሌው ያካሄደው ከሕዝብ ፈቃድ ውጭ ለሆነ ምርጫ እስላሙ ኅብረተሰብ የሰጠው ሰላማዊ መልስ የማያዳግምና የሚያስደንቅ ነው፤ በአገዛዙ ስልት በተመረጡት ሰዎች በሚተዳደሩ ቤተ መስጊዶች ውስጥ አንሰግድም በማለት መስጊዶቹን ባዶ ማድረጋቸው አገዛዙን ራቁቱን አቁሞ ስሐተቱን ያጋለጠው እውነተኛ ሰላማዊ ትግል ነው፤ በቅርቡ ሦስት የአፍሪካ፣ አንድ የእስያ፣ ሁለት ዓለም-አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለአቶ ኃይለ ማርያም ኢትዮጵያ ለዓለም-አቀፍ ሕጎች የገባችውን ቃል ኪዳኖች ሁሉ እንድትጠብቅ ከመቼውም የበለጠ ጥረት ማድረግ እንዳለባት የሚገልጽ ረጅም ደብዳቤ ተልኮላቸዋል፤ ለመብቶቻቸው የቆሙ ሁሉ፣ ጋዜጠኞችም ይሁኑ የሃይማኖት ሰዎች በሽብርተኛነት እየተከሰሱና እየተፈረደባቸው ወህኒ ቤት በመግባታቸው ፍርድ ቤቱንም ወህኒ ቤቱንም ጎብኝተው የሄዱት የስዊድን ጋዜጠኞች በሚያሳፍር ሁኔታ ለዓለም አጋልጠውታል።

የቤቴ መቃጠል ለትኋኑ በጀኝ ያለው ቂል ሰው ነው፤ ከኑግ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ ያለው ሰው ሰነፍ ነው፤ ቂልነትም፣ ስንፍናም ለመሪዎች አይበጅምና እግዚአብሔር በጎ መንፈሱን ያሳድርባቸው፤ ያሳድርብን።

http://www.ecadforum.com/Amharic/archives/4915

posted by Tseday Getachew

How the TPLF ruling junta gave away Ethiopia’s genetic rights to teff

Negash

How Ethiopia Lost Control of Its Teff Genetic Resources
By Regine Andrsen and Tone Wenge | Fridtjof Nansen Institute (FNI)

In 2005, Ethiopia concluded an agreement with the Dutch company HPFI, sharing its teff genetic resources in return for a part of the benefits that would be achieved from developing teff products for the European market.
In the end, Ethiopia received practically no benefits. Instead, due to a broad patent and a questionable bankruptcy, it lost its right to utilize and reap benefits from its own teff genetic resources in the countries where the patent is valid.
The amazing story of the Teff Agreement has been uncovered and meticulously documented in a recent FNI report by FNI researchers Regine Andersen and Tone Winge.
Teff is a food grain endemic to the Ethiopian highlands, where it has been cultivated for several thousand years. Rich in nutritional value, it is an important staple crop for Ethiopians. Since it is gluten-free, it is also interesting for markets in other parts of the world.
A 2005 agreement between Ethiopia and the Dutch company HPFI gave HPFI access to 12 Ethiopian teff varieties, which it was to use for developing new teff-based products for the European market. In return, the company was to share substantial benefits with Ethiopia.
The Teff Agreement was hailed as one of the most advanced of its time. It was seen as a pilot case for the implementation of the Convention on Biological Diversity (CBD) in terms of access to and benefit-sharing from the use of genetic resources (ABS).
But the high expectations were never met: The only benefits Ethiopia ever received were 4000 Euro and a small, early interrupted research project.
And then, in 2009, the company went bankrupt. In the years prior to bankruptcy, however, HPFI managed to obtain a broad patent on the processing of teff flour in Europe, covering ripe grain, as well as fine flour, dough, batter and non-traditional teff products. This patent, along with other values of the company, had then been transferred to new companies set up by the same owners.
These companies now possess the exclusive rights to a large range of teff-based products. But as it was the now bankrupt HPFI that was Ethiopia’s contract partner, these new companies are not bound by the contractual obligations of HPFI towards Ethiopia.
Ethiopia thus ended up receiving practically none of the benefits promised under the agreement, and its future opportunities to profit from teff in international markets were smaller than before.

posted by Tseday Getachew

በናዝሬት በአንድ አመት ውስጥ ብቻ 4 ከንቲባዎች ተቀያየሩ

ኢሳት ዜና:-በቅርቡ በተደረገ ግምገማ ላለፉት አራት ወራት በስልጣን ላይ ቆይተው የነበሩት የናዝሬት ወይም የአዳማ ዋና ከንቲባ እና ከእኝሁ ባለስልጣን ጋር ግንኙነት አላቻው የተባሉት የከተማዋ የኦህዴድ የድርጅት ጉዳይ ሀላፊ ከቦታቸው እንዲነሱ ተደርጓል።

ገምጋሚዎቹ የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት የነበሩ ሲሆን ግምገማውም በመልካም አስተዳዳር፣ በከተሞች እድገት፣ በኪራይ ሰብሳቢነትና በልማት ሰራዊት አደረጃጃት ላይ ያተኮረ ነበር።የከተማው ከንቲባ የነበሩት አቶ ጉታና የከተማው የልማት ሀላፊ የነበሩት አቶ ከፍያለው የከተማዋን መሬት በመቸብቸባቸው ፣ ህዝብ ያሰማውን ሮሮ ተከትሎ እንዲወርዱ ተደርጓል።

ከእርሳቸው በፊት የነበሩት 3ቱ ከንቲባዎችም እንዲሁ መሬት በመቸብቸብና በሙስና ከሀላፊነት መነሳታቸው ይታወቃል። ከንቲባው አቶ ጉታ የፓርላማ አባል ሲሆኑ፣ በከተማዋ ውስጥ የሚታየውን የአስተዳዳር ብልሹነትና ስር የሰደደውን ሙስና እና መሬት ዝርፊያ ያስቆማሉ ተብሎ እምነት ተጥሎባቸው ነበር። ይሁን እንጅ ባለስልጣኑ ከሌሎች ግብረአበሮቻቸው ጋር በመሆን ከፍተኛ ሙስና ውስጥ መግባታቸው ለማወቅ ተችሎአል።

የድርጅት ቢሮ ሀላፊው አቶ ሳዳት በበኩላቸው በአዳማ ውስጥ ባሉ የሀላፊነት ቦታዎች ላይ የሚገኙ ሰዎችን እንዲመደቡ ያደረጉዋቸው ከአርሲ አካባቢ የተወለዱትን ብቻ ነው በሚል በዘርኝነት ተገምግመው ወርደዋል።
አንድ የኦህዴድ የማእከላዊ ኮሚቴ አባል ለኢሳት እንደገለጹት የድርጅቱ መሪዎች ከላይ እስከታች በሙስና የተዘፈቁ በመሆናቸው ፣ በየአካባቢው እየተገመገሙ የሚወርዱ የከተማ ከንቲባዎችና የድርጅት አመራሮች ወደ ሌሎች ቦታዎች ተመልሰው ይመደባሉ። በዚህም የተነሳ ሙስና ውስጥ የተዘፈቀ ባለስልጣን ምንም ችግር ሳይገጥመው ወደ ሌላ አካባቢ ሄዶ ይመደባል ብለዋል። በናዝሬት ውስጥ የሚታየው አይን ያወጣ የመሬት ዝርፊያ ፣ ነዋሪውን በእጅጉ እያሳሰበ ይገኛል።

posted by Tseday Getachew

በጉዲፈቻ ወደ ዴንማርክ የመጣች ህጻን ለከፍተኛ የስነ አዕምሮ ችግር መዳረጎን ከዴንማርክ የደረሰን ዘገባ አመለከተ

ኢሳት ዜና:-የዛሬአራት አመት ከወላጅ እናቷና አባቷ ተረክበው ህጻኗን ከወንድሟ ጋር የወሰዳት የዴንማር ሰዎች ህጻኗ ለቤተሰቦቿ ያላትን ናፍቆት በየአጋጣሚው በመግለጽ እናቷ ጋር እየዲወስዷት በመጠየቅና ያልተለመደ በሀሪእያሳየች ደስታ በማጣቷ ለህጻናት ማሳደጊያ እንደሰጧት የኢሳት ምንጮች ከዴንማርክ ገልጣለች::

ከዴንማርክ የደረሰን ይሀው መረጃ እንደሚያመለክተው የህጻኗ ማእሾ ታሪክ በዴንማርክ ከፍተኛ መነጋገሪያ የሆነ ሲሆን ቤተሰቦቿን ያነጋገረና የህጻኗን ወደ ሀገር ቤት በመመለስ ጽኑ ፍላጎት ያሳየ ዶክመንተሪ ፊልም ተሰርቶ በቴሌቭዥን መሰራጨቱን ለምንጮቻችን ገልጻለች::

በህጻኗና በወላጆቿ ፍላጎት ወደ ሃገር ቤት መመለስ በሚለውና የለም መመለስ የለባትም በሚለው ላይ የዴንማርክ ህዝብ ድምጽ እንዲሰጥ ተደርጎ 67 ከመቶው ህጻኗ ወደ ሀገሯ ትመለስ በማለት ድምጽ መስጠቱን ምንጮች አረጋጠዋል::
17 ከመቶየአፍ መፍቺያ ቋንቋዋን ረስታለችና መመለስ የለባትም ሲሉ 20 ከመቶዎቹ ድምጽ ከመስጠት መቋጠባቸውንም ለማወቅተችሏል::

በህጻኗህይወት ታሪክ ዙሪያ ተሰርቷ በተሰራጨው ዶክመንተሪ ፊልም የህጻኗ ወላጆች ልጃቸው እንድትመልስ እያለቀሱ ሲለምኑ የሚታይ ሲሆን የህጻኗ ጤናን ያሳባ የስነ አእምሮ ችግርም ህጻኗ እንዳጋጠማትም ፊልሙን የተመለከተው ምንጫችን ከዴንማር በስልክ ገልጻለች::የደን ማርጥ ዜጋ አንድ ህፃን ወደ ሃገሩ ሲያመጣ ከ450 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ እንደሚከፍል የምንጮቻችን ዘገባ ያመለክታል::

posted by Tseday Getachew

ባለፉት 10 አመታት በአዲስ አበባ የተገነባው ከአጼ ሚኒሊክ ጀምሮ ከተገነባው ይበልጣል ሲሉ አቶ ኩማ ደመቅሳ ተናገሩ

ኢሳት ዜና:-ከንቲባው ይህን የተናገሩት በቅርቡ የአዲስ አበባ 125ኛ አመት ክብረ በአል ሲጠናቀቅ ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር ነው።

አቶ ኩማ ከተማዋን የቆረቆሩትን እና በከተማዋ ላይ አሻራቸውን ያሳረፉትን በሙሉ በማውገዝ የኢህአዴግን ስራ ለማሞካሸት ሞክረዋል።

በነገሥታቱ ዘመን የከተማዋ የመሬት ይዞታ ለመኳንንት፣ ለመሳፍንትና ለጦር አበጋዞች ተከፋፍሎ አብዛኛው የከተማዋ ነዋሪዎች ሲሰቃዩ እንደኖሩ፣ የከተማዋ ዕድገት ማስተር ፕላንን ያልተከተለ በመሆኑና በመኳንንቱና በመሳፍንቱ ግላዊ ፍላጐት ተወስኖ ቆይቷል ሲሉ ነው ከንቲባው የገለጹት።

ባለፉት አሥር ዓመታት በከተማዋ በሁሉም መስኮች የተገኘው ውጤትና እየታየ ያለው ለውጥ፣ ከመቶ ዓመታት በላይ በከተማዋ ተሠርተው ከነበሩት ልማቶች በብዙ እጥፍ ይበልጣል በማለት ነው አቶ ኩማ የተናገሩት።

አዲሱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒሰትርና የትምህርት ሚኒሰትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ፣ ‹‹ነዋሪዎቿ በቀጥታ ተሳትፈው የዕድገት ምህዋር ውስጥ ገብታ የዓለም አቀፍና የአፍሪካ መዲና ሆና የወጣችው ካለፉት ሁለት አሥርተ ዓመታት ወዲህ ነው፤›› በማለት የአቶ ኩማን ንግግር አጠናክረዋል፡፡

ከተማዋን የቆረቆሩት አጼ ሚኒሊክም ሆኑ እቴጌ ጠሐይቱ እንዲሁም አጼ ሀይለስላሴ በጊዜው በፈቀደላቸው ቴክኖሎጂና በነበራቸው የገንዘብ አቅም እና እውቀት ለአዲስ አበባ ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን የታሪክ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

አጼ ሀይለስላሴ አፍሪካ አንድነት ድርጅትንና የአለም የኢኮኖሚ ኮሚሽን ጽህፈት ቤት አዲስ አበባ እንዲሆን የታገሉና አዲስ አበባ ዛሬ ላገኘችው አለማቀፍ ክብር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ድርሳናት ያወሳሉ።

የአቶ መለስ መንግስት በአዲስ አበባ ላይ ከፍተኛ መዋለ ንዋይ በማፍሰስ ከተማዋ እንድትለማ ያደረገው ከምርጫ 97 በሁዋላ በአዲስ አበባ የደረሰበትን ሽንፈት ተከትሎ መሆኑን ታዛቢዎች ይናገራሉ።

ያም ሆኖ በከተማዋ የሚኖሩ ነዋሪዎች አሁንም በመሰረተ ልማት አቅርቦት በተለይም በውሀና በመብራት እጦት በእጅጉ እየተማረሩ ነው። ቤታቸው እየፈረሰባቸው ያለ በቂ ካሳ መንገድ ላይ እንዲያድሩ የተደረጉትም ቁጥራቸው ቀላል አለመሆኑን ኢሳት በተደጋጋሚ ሲዘግብ ቆይቷል።

አቶ ኩማ በከተማዋ የሚታየውን የመሬት ዝርፊያ ለማስቆም ሳይችሉ ኢህአዴግን ከነጋስታቱ ዘመን ጋር ለማወዳደር መቻላቸው ለትችት ዳርጎአቸዋል። አዲስ አበባ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ስትነጻጸር አሁንም ሁላ የቀረች ከተማ ነች።

posted by Tseday Getachew

Post Navigation

%d bloggers like this: